© መልካሙ በየነ
ሐምሌ
1/2009 ዓ.ም
ደብረ ኤልያስ፤ምሥራቅ ጎጃም፣ ኢትዮጵያ
ዛሬ ዕድሜን እንደፈለግነው ከምትለግሰን ከተማችን አዲስ አበባ 70 ዓመታትን በዕድሜያችን ላይ
ጨምራልናለች፡፡ አዲስ አበባ የማትመቸው ዕድሜያቸውን ለእርሷ ለሰጧት ሰዎች እንጅ ዕድሜዋን ለሰው መስጠት ታውቅበታለች፡፡ ከተማችን
አዲስ አበባ ለእርሷ የጣረላትን ለእርሷ የጋረላትን ሳይሆን ቅጥሯን ለሚያፈርስ ጠላት ማሽቃበጥ ታውቅበታለች፡፡ የሞተላትን የምትገድል
የገደላትን የምትሸልም ናላዋ የዞረ ከተማ ናት አዲስ አበባ፡፡ አሽቃባጭነቷ የጎላባት ከተማችን ውጮቹን በክብር ስትይዝ የራሷን ሰዎች
ግን አውጥታ የምትጥል ባንዳ ከተማ ናት፡፡ አዲስ አበባ ለሊቃውንቱ የሚሆን ቦታ የላትም፡፡ አዲስ አበባ ለቅዱሳኑ የሚሆን ቦታ የላትም፡፡
አዲስ አበባ ለሠራላት የሚሆን ቦታ የላትም፡፡ አዲስ አበባ ቀና ላደረጋት ሰው ቦታ የላትም፡፡ እርሷ የተገላቢጦሽ የሆነች የሰለጠነች
የመሰላት ግን ያልሰለጠነች ከተማ ናት፡፡ አዲስ አበባ በሕይወት ሳለህ እንደ ሸንኮራ አገዳ አላምጣ የምትተፋህ ሸንኮራ መጣች ከተማ
ናት፡፡ አዲስ አበባ ጣርልኝ ጋርልኝ ሥራልኝ ድከምልኝ ትልሃለች ነገር ግን አታስታውስህም በጭራስ ማስታወስ አትችልም አትፈልግምም፡፡
ዛሬ ግን አዲስ አበባን ቸር ለጋሽ ነሽ እላታለሁ፡፡ በእውነት የዕድሜ ባለጠጋን አድርጋናለችና፡፡
እኔ ቢያንስ 40 ዓመታትን በዛሬዋ ዕለት ለግሳኛለችና አመሰግናታለሁ፡፡ ይኼውላችሁ በ1979 ዓ.ም ተወልጄ በያዝነው 2009 ዓ.ም
70 ዓመቴን ደፈንኩላችሁ፡፡ ለምን እንዴት ስትቆጥር ተሳስተሃል ምናምን ምናምን ብትሉኝ በፍጹም አልሰማችሁም፡፡ ዕድሜ ለአዲስ አበባ
እንጅ ይኸው ሰባ ዓመት ሞላኝ፡፡ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ በ1939 ዓ.ም እንዳረፉ አዲስ አበባ ነግራኛለች፡፡
ካረፉ ይኼው ዛሬ 2009 ዓ.ም ድፍን 70 ዓመታችው ሆኗል፡፡ ታዲያ ይች ለሊቃውንት የሚሆን ቦታ የሌላት አዲስ አበባ ለ70 ዓመታት
ያህል ዐርፈው እፎይ ብለው በተኙበት መቃብራቸው ላይ ዐዋጅ አወጀች፡፡ በቃ እኔ የተማረ ለሀገር ሲደክም የኖረ በተለይ ሊቅ የሆነ
ሰውን ማየት አልሻም አለች፡፡ ተዪ ብሎ ብዙ ሰው መከራት ብዙ ሰውም ተቆጣት እርሷ ግን በፍጹም አልፈልግም ውሰዱልኝ ብላ ለፈፈች፡፡
ምን ይደረጋል ታዲያ! አንች ባትፈልጊ የሚፈልጋቸው ሞልቷል አንች እረፍት ብትነሻቸው እረፍትን የሚያጎናጽፋቸው አገር አላቸው ብለን
እኛም ለ70 ዓመታት ያህል እየጎራበጣቸው ከተቀበሩበት አዲስ አበባ ማርና እና ወተቱ ወደሚፈስበት ገነትን የሚያጠጣው የግዮን መነሻ
ወደ ሆነው ጎጃም በእልልታ አጅበን ወሰድናቸው፡፡ ድሮስ ቢሆን ሀገር እያለን ሀገር እንደሌለው በዚያ መቀበራችን ምን ሊፈይድልን
ምንስ ሊረባን ነበር፡፡
አዲስ አበባ ሆይ እኔ ግን አመሰገንሁሽ! ምክንያቱም ከማያልቀው ዕድሜሽ ቆርሰሽ የ70 ዓመት አዛውንት
አድርገሽኛልና፡፡ ከቀኝ ጌታ ዮፍታሔ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ከጃን ሆይ ጋራ እነሆ ተገኘሁ፡፡ ምን ታደርጊዋለሽ ዕድሜን ከሰጠን
ገና ብዙ ትለግሽናለሽ ብለን ተስፋ አድርገናል፡፡ ዕድሜን ዝቀሽ አፍሰሽ ሰጠሸኝ እኔም በአኮቴት ተቀብየ እነሆ ዛሬ ያለዕድሜየ አስረጀሽኝ
ያውም ወደኋላ መልሰሽ 70 ዓመታትን ለገስሽኝ፡፡ ለዚህ ብቻ ነው የማመሰግንሽ፡፡ ድሮ ያላገኘሁትን ዕድል አደልሽኝ ድሮ ያላገኘሁትን
ጸጋ አጎናጸፍሽኝ ድሮ ያላገኘሁትን ክብር አከበርሽኝ በቃ አመሰግንሻለሁ፡፡ አንች ምቀኛ ከተማ ባትሆኝ ኖሮ በዚህ ዕድሜየ በ1979
ዓ.ም ተወልጀ ከቀኝጌታ ዮፍታሔ ቀብር ሥነሥርዓት ላይ በ1939 ዓ.ም የመገኘቱን ዕድል ከወዴት አመጣው ነበር ከየትም፡፡
ቀኝጌታ ዮፍታሔ ለ 70 ዓመታት ያህል ተቀብረው ከነበሩበት አዲስ አበባ በዓለ ወልድ ቤተክርስቲያን
አጽማቸው በክብር ወደተወለዱበት ደብረ ኤልያስ ገብቷል፡፡ በዚህም በደብረ ኤልያስ በተሰቦቻቸው ወዳጆቻቸው እንዲሁም የሀገር ፍቅር
ያቃጠላቸው ሁሉ ከየቦታው ተሰባስበው በክብር እንዲያርፉ ተደርጓል፡፡ በዚህ ታሪካዊ ቀንም በታላቁ ቦታ በደብረ ኤልያስ በመገኘቴ
ፈጣሪየን አመሰግነዋለሁ፡፡ የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ አጽም አሁን በክብር አርፏል፡፡ የተወለዱበትም ቦታ ነውና ማንም እረፍታቸውን አይነሣቸውም
እረፍታቸውን ሊነሣ የሚመጣ ቢኖር እንኳ ይህ አዲስ አበባ አይደለም በወገኖቻቸው መካከል ናቸውና ምንም ስጋት የለባቸውም፡፡ እርሳቸውስ
በክብር አረፉ ሐውልት ቆመላቸው፡፡ አዲስ አበባ የነፈገቻቸውን ትንሽየ ቁራጭ መሬት እዚህ በገፍ አግኝተውታል፡፡ በ1939 ዓ.ም በበዓለ ወልድ ቤተክርስቲያን አብረዋቸው የተቀበሩት የአዲስ
አበባ ነዋሪዎች ግን በዕለተ ምጽአት ጊዜ ማዘናቸው አይቀሬ ነው፡፡ በዓለወልድ የተቀበሩት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በዕለተ ምጽአት
ጊዜ ከጎናቸው ቀኝጌታ ዮፍታሔን ሲፈልጉ ሲያጧቸው ምን ይሉ ይሆን? አፈ ጮሌው የበዓለ ወልድ አስተዳዳሪ ሲጠየቅ ደብረ ኤልያስ ናቸው
ሊል እኮ ነው፡፡ ከዚያማ አብረውን እዚህ ተቀብረው እንዴት ደብረ ኤልያስ ሄደው ይነሣሉ ትንሣኤም በክልል ሆነ እንዴ ማለታቸው አይቀርም፡፡
አስተዳዳሪው ነው መቼም መልስ ሊሰጥ የሚቀርብ ታዲያ ያኔ “ትንሣኤስ በክልል አይደለም ቀብሩ ነው እንጅ” ብሎ መመለሱ አይቀርም፡፡
አንዱ “እንዴ እዚህ አብረውን እኮ ነበር የተቀበሩት መቼ ጀምሮ ነው በክልል የሆነ” ብሎ ማፋጠጡ አይቀርም፡፡ ያኔ አስተዳዳሪው
“ተውትማ እርሳቸው እኮ እዚህ የተቀበሩት አስተሳሰባችን በክልል ባልታጠረበት ወቅት በ1939 ዓ.ም ነበር፡፡ አስተሳሰባችን በክልል ብቻ ሲወሰን በ2009 ዓ.ም ግን እርሳቸውም
ወደክልላቸው ሄደዋል” በማለት መልሶ ለትንሣኤ ዘጉባዔ የቆመውን ሰው ፈገግ ማስደረጉ አይቀሬ ነው፡፡ ብቻ ለዚያ ቀን ያገናኘን እንጅ
እኛንም ፈገግ ሳያስደርገን አይቀርም፡፡
ምርኳዝ ሳትሰጠን ዕድሜን ብቻ ለግሳ ያለዕድሜያችን ያስረጀችን 2009ን ወደ 1939 ዓ.ም ጎትታ
የመለሰች ብቸኛ ከተማ አዲስ አበባ፡፡ ዛሬ ራሴን ተጠራጠርሁት እንዴት በ1979 ዓ.ም ተወልጀ በ1939ኙ የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ
ቀብር ላይ እገኛለሁ? እንዴ! ነገሩ ምንድን ነው? ወላጆቼ ዋሽተውኛል ልበል ወይስ የዓመተ ምሕረቱ ካብ ተንዶ 1939 ዓ.ም ላይ
ቆመ እንጃ!
“ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ
አገርም እንደሰው ይናፍቃል ወይ” አልልሽም ምክንያቱም አትናፍቂኝምና ስለዚህም “ አገርም እንደ
ሰው ይበድላል ወይ” ብየ እገጥምልሻለሁ፡፡ ገጣሚውም ስለራሱ ትንቢቱን እንዲህ ሲል ጽፏል፡፡
“አገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” ይህ ትንቢት የተፈጸመው በራሱ ይህን ግጥም በጻፈው ቀኝጌታ ዮፍታሔ
መሆኑ ነቢይ ነበሩ እንዴ አስባለኝ!!!
ለዚህ ታሪካዊ ቀን ላደረስከኝ አምላክ አሁንም ለዘላለምም አመሰግንሃለሁ፡፡ ዕድሜየን አርዝመህ
በቀኝጌታ ዮፍታሔ ቀብር ላይ አደረስከኝ፡፡ ተወልደው ባደጉበት በተማሩበት ባስተማሩበት ቀኝ ጌታ ተብለው በተሾሙበት በታላቁ ደብረ
ኤልያስም የቤተመዘክር የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦላቸዋል፡፡
No comments:
Post a Comment