Monday, July 3, 2017

ብርሃን የወለደው የብርሃን አለቃ---አድማሱ ጀንበሬ


© መልካሙ በየነ

ሰኔ 27/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

  • ለመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ልጆች እና የልጅ ልጆች ስለመካነ መቃብራቸው መልእክት እናድርስ፡፡

  • ዲማ የሊቁን አጽም ለማፍለስ ቤተሰቦቻቸውን እየጠየቀ ነው፡፡ የቤተሰቦቻቸው መልስ ግን ገና አልታወቀም፡፡

  • የቅብአቶች ሁለተኛው መጽሐፍ “ሚሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊ” በእጄ ገብቷል፡፡ ወደፊት በዚህ መጽሐፍ ጉዳይ የምንባባለው ይኖራል፡፡
======================================================================




መልአከ ብርሃን ተብለው የተሾሙበት ብቸና ጊዮርጊስ
“እኔ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ የተወለድኩበትና ያደግሁበት የተማርኩበት ሀገሬ በጎጃም ጠቅላይ ግዛት ዲማ ጊዮርጊስ መልአከ ብርሃን ተብየ የተሾምኩበት ብቸና ጊዮርጊስ ነው” ይላሉ የመድሎተ አሚን እና የኮኲሐ ሃይማኖት ደራሲ ታላቁ ሊቅ አድማሱ ጀንበሬ፡፡ እነኝህ የቤተክርስቲያናችን ታላቅ ባለውለታ በአሁኑ ሰዓት ከመካነ መቃብራቸው ጋራ በተያያዘ ቤተክርስቲያናችን ተገቢውን ትኩረት እንዳልሰጠቻቸው እየተነገረ ነው፡፡ እስካሁን ድረስ በዳግም ኅትመት እነዚህን ጽፈውልን ያለፏቸውን መጻሕፍት በመሸጥ የምትጠቀምባቸው ቤተክርስቲያናችን ናት፡፡ ነገር ግን ከመካነ መቃብራቸው ጋራ በተያያዘ ለእርሳቸው በሚመጥን ቦታ ላይ እንዳልሆኑ ተነግሯል፡፡




የቅኔ ተማሪዎች መኖሪያ
መልአከ ብርሃን ተብለው የተሾሙበት ብቸና ጊዮርጊስ
ታላቁ ሊቅ አድማሱ ጀንበሬ መልአከ ብርሃን የሚለውን ሹመታቸውን የተቀበሉበት ቦታ ታላቁ ደብረ ብርሃን ብቸና ጊዮርጊስ ነው፡፡ ይህን ቦታ ማየት የታላቁን ሊቅ አጽም እንደመሳለም ስለቆጠርሁት እሁድ ሰኔ 25/2009 ዓ.ም በዚያው ቦታ መገኘትን መርጫለሁ፡፡ ቦታው ታላቅ ቦታ ነው፡፡ ጸጥታው እረፍትን የሚሰጥ በተመስጦ ጸሎትን ማድረስ የሚቻልበት ታላቅ ቦታ ነው፡፡ ይህ የብርሃን ተራራው (ደብረ ብርሃን) ታላቁን ሊቅ የብርሃን አለቃ (መልአከ ብርሃን) እንዲባሉበት የብርሃን አለቃን የወለደ የብርሃን ተራራ ነው፡፡ ምንም እንኳ እርሳቸውን የሚዘክር የተመለከትሁት ምንም ነገር ባይኖርም አድማሱ ጀንበሬ የወርቅ ዘውድ በራሳቸው ደፍተው መልአከ ብርሃን ተብለው የተሸሙበት ቦታ ብቸና ጊዮርጊስ ነው፡፡

ከታች በፎቶና በቪዲዮ የምትመለከቱት ብቸና ጊዮርጊስን ነው፡፡ የሊቁ አጽም አሁንም ተገቢውን ክብር እና ቦታ ያገኝ ዘንድ ሁላችንም ልንጠይቅ ይገባናል፡፡ ይህ ጉዳይ የሁላችንም ነውና! በተለይ ግን የዲማ ሊቃውንት ይህን ጉዳይ በዝምታ መመልከት ያለባቸው አይመስለኝም፡፡ ሥራቸው ለዓለም ሊገለጥ ይገባል፡፡ ከተቻለም ስንክሳር ውስጥ እንዲገቡ ገድል እንዲጻፍላቸው ቢደረግ በጣም ጥሩ ጉዳይ ነው፡፡ እኔ እስከገባኝ እና እስከተረዳሁት ድረስ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ጽላት ሊቀረጽላቸው የሚገባ ታላቅ ቅዱስ ናቸው፡፡ ቅድስናን ከሊቅነት ጋራ አጣምረው የያዙ ዘላለማዊ መምህር ናቸው፡፡ 







ብርሃናቸው የማያልቅ ለሁሉም የሚያበሩ ድንቅ ሻማ! ቀልጠው የማያልቁ ዘላለማዊ ብርሃንን የሚፈነጥቁ ሻማ! በመድሎተ አሚን ካቶሊክን በኮኲሐ ሃይማኖት ፕሮቴስታንትን የቀጠቀጡ ድንቅ የሃይማኖት በትር፡፡ መካነ መቃብራቸው ግን የቤተክርስቲያንን ውበት ለመጠበቅ ሲባል እንደ ተራ ምእመን የፈራረሰ፡፡
=====================================
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት #comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡

No comments:

Post a Comment