Tuesday, July 18, 2017

የክህደት ቁንጮው ሚሥጢረ ሃይማኖት--- ክፍል ፰



ሐምሌ 11/2009 ዓ.ም


“ሚሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊ” የተሰኘውን የቅብአት መጽሐፍ እያገላበጥን ነጥብ በነጥብ እየተመለከትን ነው ያለነው፡፡ እዚህ ላይ ከውይይት እና በማስረጃ ተደግፎ ከመቃወም ባለፈ ለስድብ እና ለዛቻ አስተያየት ሊሰጥ የሚመጣን ማንኛውንም አካል የማናስተናግድ መሆኑን ከወዲሁ እንገልጻለን፡፡ ከመጽሐፉ ስገለብጥ ማለትም “---” ምልክት መካከል አድርጌ የምጽፈው የፊደል ግድፈቱንም እንዳለ ስለምወስደው የፊደል የቃል ስህተት ብታገኙ ሙሉ በሙሉ የመጽሐፉ እንደሆነ አሳውቃለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መጽሐፉ በእውነት እኔ እንዲህ አሉ እያልኩ የምላችሁን ነገር በትክክል ይዟል ወይስ አልያዘም እያላችሁ ጥርጣሬ ውስጥም እንዳትወድቁ በማሰብ ራሱን መጽሐፉን ገጽ በገጽ ፎቶ እያነሣሁ ከዚህ ጋራ አያይዝላችኋለሁ፡፡ እናንተም እነዚህን በፎቶው ላይ ያሉትን የመጽሐፉን ክፍሎች በማንበብ ሙሉውን የመጽሐፉን መንፈስ እንድትረዱት እያሳሰብሁ ስህተት ናቸው የምላቸውን ነጥቦች ግን በተቻለኝ መጠን ከመጻሕፍት አንጻር ያለውን ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ መልስ  እያስቀመጥሁ እሄዳለሁ፡፡ ይህ ማለት ግን እኔ አዋቂ ነኝ ምሥጢር ጠንቃቂ ነኝ ማለቴ እንዳልሆነ ልብ በሉልኝ! ስለዚህ በዚህ መልኩ ወደዛሬው ጽሑፌ ላምራ፡፡

፨፨፨፨********************************************፨፨፨፨





ዛሬ የምንመለከተው ከገጽ 14 ምእራፍ 3 ጀምረን ይሆናል፡፡ የቅባቶች ዋናው የልብወለድ ድርሰት የተጀመረው ከዚህ ጀምሮ ነው፡፡ “እናንተ የኢትዮጵያ ሰዎች እንዲህ ትላላችሁ፡፡ አለ አብ ወላዲና ቀባዒ ወልድ ተወላዲና ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስም ሰራፂ ይኸውም ቅብዕ ነው ወልድ በመዋሐዱ አብም በመቅባቱ መንፈስ ቅዱስም ቅብዕ በመሆኑ ቃል ሥጋ በሆነ ጊዜ በእናቱ ማኅጸን በሰውነቱ መንፈስ ቅዱስን ተቀብቶ የባሕርይ ልጅ ሆነ ትላላችሁ፡፡ እኒህ የሮሜ ሰዎች ግን እንዲህ ይላሉ አብ ወላዲ ወልድ ተወላዲ መንፈስ ቅዱስ ሰራፂ፡፡ በማርያም ማኅፀን የወልድ መለኮት ባደረ ጊዜ እስከ ሰላሳ ዘመን መለኮት ስጋ አልሆነም ሥጋም መለኮት አልሆነም አንድ ባለመሆን ተቀመጠ በተጠመቀ ጊዜ ግን በርደተ መንፈስ ቅዱስ የፀጋ አምላክ ሆነ እንጅ፡፡ ከሰላሳ ዓመት አስቀድሞ የአምላክ ሥራ አልሰራም በሰውነት ሥራ ኖረ እንጅ” በማለት ተረት ተረት ሲተርቱ ይታያሉ፡፡ ይህ ታሪክን ማበላሸት በሊቃውንቱ በዝክሪ እና በጳውሊ ስም መነገድ ካልሆነ በቀር ሌላ ምን ተልእኮ ሊኖረው ይችላል? ዝክሪ እና ጳውሊ እኮ ለአገራችን ሊቃውንት አፈጉባዔ የተደረጉት በትምህርታቸው በእውቀታቸው በሊቅነታቸው መጻሕፍትን ሁሉ በማወቃቸው እንጅ በሌላ በምንም ዓይነት ምክንያት አይደለም፡፡ ታዲያ እነዚህ ሊቃውንት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የማታምነውን እንዲህ ታምናላችሁ ተብለው ሲጠየቁ ይህንን አናምንም በማለት ፋንታ ቅባቶች ሌላ ተረት ተረት አስገብተው ዝክሪ እና ጳውሊም በዲማ ይኖሩ የነበሩ የቅብአት እምነት ተከታዮች ነበሩ ማለታቸው በጣም የሚያሳዝን ድርጊት ነው፡፡ “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” ሆኑ በማለት ዝክሪ እና ጳውሊ አያምኑም፡፡ ታዲያ ይህንን የማያምኑትን እምነት ከገጽ 15 ጀምረው ዝክሪ እና ጳውሊ እንደተናገሩት በማስመሰል ጽፈውታል፡፡

ዝክሪ እና ጳውሊ “ወልድ ዋሕድ በተዋሕዶ ከበረ” የሚሉ ሊቃውንት እንጅ “በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” ባይ መናፍቃን እንዳልሆኑ ሁላችን እናውቃቸዋለን፡፡ መጽሐፍ ስምዐት 124÷34 “ወካዕበ ይቤ እስመ ክርስቶስ ኢተቀብዐ በእንተ መፍቅድ ዘቦቱ አላ ለሊሁ ቀባዒ ውእቱ ወዐርገ ኀበ ሥልጣነ መለኮቱ እንዘ ሰብእ ውእቱ ወለሊሁ እግዚአብሔር አምላክ ተብህለ በእንቲአሁ ከመ ውእቱ ተለዐለ ፈድፋደ በእንተ ትህትና ወሕጸጽ እንተ ዘትስብእት ወንዴት ወለሊሁ ጸገዎ ስመ ዘላዕለ ኩሉ ዝንቱ ዘኮነ በህላዌ ከመ አምላክ ከመ ያልዕለነ ለነሂ ዓዲ ኀበ ሀሎ ዝኩ፤ ዳግመኛ ክርስቶስስ ክብር መሻት ኖሮበት አልከበረም እርሱ ራሱ አክባሪ ነው እንጅ ሰው ቢኾንም በባህርይ ክብሩ ከበረ እርሱ ራሱ እግዚአብሔር አምላክ ነው ሥጋ ትሁት ሕጹጽ ነዳይ ስለሆነ ተለዐለ ተብሎ ተነገረለት ከሁሉ በላይ የሆነ ስምንም እሱ ራሱ ሰጠው ተባለ ይህም የሆነ በባህርይ ተዋሕዶ ነው አምላክ እንደሆነ እኛንም እሱ ወደ አለበት ያቀርበን ዘንድ” እያለ ዝክሪ እና ጳውሊ ይህንን ዘንግተው “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” ይሉ ዘንድ አይችሉም አይደፍሩምም፡፡ ሌሎች በርካታ ማስረጃዎችን በመጥቀስ “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” ናቸው ማለት ክህደት እንደሆነ እናስገነዝባለን፡፡ “አብ ወላዲ ወልድ ተወላዲ መንፈስ ቅዱስ ሰራጺ” ከሚለው የግብር ሦስትነት ውጭ “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” የሚል የምን ስም እንደሆነ የማይታወቅ ስም መስጠት ክህደት ነው፡፡ የግብር ስማቸው ነው እንዳይባል ወላዲ ተወላዲ ሰራጺ ቢባሉ እንጅ ቀባዒ ተቀባዒ ቅብዕ የሚል መጽሐፍ አናገኝም፡፡ በትርጉሙም ብንሄድ እኮ ትክክል አይደለም መሰረተ እምነትን ትምህርተ መለኮትን ያፋልሳል፡፡ አብ ቀባዒ ማለት አብ አክባሪ ማለት ነው፡፡ ወልድ ተቀባዒ ማለትም ወልድ ከባሪ/ተከባሪ ነው ማለት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ማለትም መንፈስ ቅዱስ ክብር ነው ማለት ነው፡፡ ታዲያ በየትኛው መጽሐፍ ነው አብ በመንፈስ ቅዱስ ክብርነት ወልድን አከበረው የሚል? እንዲያውም በመንፈስ ቅዱስ ከበረ የሚለውን ትምህርት አባቶቻችን አውግዘውታል፡፡ “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በእርሱ አጋዥነት ድንቅ ተአምራትን ያደርግ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ ከበረ የሚለው፤ ርኩሳን አጋንንትን በማውጣት ጊዜም ኃይልን ተአምራትን ከመንፈስ ቅዱስ ይቀበላል፤ በሰውም የአምላክነትን ሥራ ይሠራል የሚለው፤ መንፈስ ቅዱስ የባሕርዩ ነው፤ የአምላክነትንም ሥራ እርሱ ራሱ ይሠራል የማይል ቢኖር ውጉዝ ይሁን” ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ 73÷49 ይላል፡፡ ታዲያ ይህንን የተወገዘ ትምህርት ዝክሪ እና ጳውሊ እንዴት እውነት ነው ብለው ይቀበሉታል? ዝክሪ እና ጳውሊ በሮማውያን የተጠየቁትን ጥያቄና የሰጡትን መልስ ከቅባቶች መጽሐፍ ጋር እያነጻጸራችሁ ትመለከቱት ዘንድ ከታሪክ ድርሳናት ያገኘነውን እነሆ፡፡
                                            
ዐምስተኛ ጥያቄ፡፡
ስሙን ልዮን የሚሉት አንድ ሮማዊ ተነሥቶ ወልደ አብ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ሥጋ ማርያምን በለበሰ ጊዜ ሰይፍ በሰገባው እንዲከተትና እንዲቀመጥ አደረበት እንጅ አልተዋሐደውም በሰላሳ ዘመኑ በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በራሱ ላይ ሲቀመጥ መለኮቱ ከትስብእቱ ተዋሐዶ የጸጋ አምላክ ኾነ መዋቲ ትስብእትም የማይሞት ኾነ ከሰላሳ ዘመን በፊት የጸጋ አምላክ ስላልኾነ አምላካዊ ሥራ አልሠራም ከተጠመቀ በኋላ ግን የጸጋ አምላክ ስለኾነ ውኃውን ወይን አደረገ ብዙ የአምላክነት ሥራ ሠራ አለ፡፡

እንደዚኸውም በንግድ ምልክት መጥቶ እስክንድርያዊ መስሎ በኢትዮጵያ የሚኖር አንድ ሰው ተነሥቶ እንዲህ ሲል ተናገረ እናንተ ኢትዮጵያውያን ቃል ሥጋ በለበሰ ጊዜ በማኅጸነ ማርያም መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ የባሕርይ አምላክ ኾነ ትላላችሁ በማኅጸን መንፈስ ቅዱስን ሲቀበል ያየው የለም፡፡ ሮማውያን ግን እስከ ሰላሳ ዘመን በሰብአዊ ግብር ኖሮ ሲጠመቅ መንፈስ ቅዱስ ሰው ሁሉ እያየው በራሱ ላይ ስለተቀመጠበት የጸጋ አምላክ ኾኖ የአምላክነት ሥራ ሠራ ይላሉና ከእስክንድርያ ሃይማኖት የሮማ ሃይማኖት ትሻላለች አለ፡፡

አባ ጳውሊ ሲመልስ ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ሲያበሥራት መንፈስ ቅዱስ ባንቺ ላይ ይመጣል የአብም ኃይሉ ይጋርድሻል ካንች የሚወለደውም ቅዱስ ነው የልዑል የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል ብሎ ሦስቱም አካላት በማኅጸነ ማርያም እንደ አደሩ ተናግሯል፡፡ ማደራቸውም አብ ለአጽንዖ መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ ወልድ ለለቢሰ ሥጋ ነው እንጅ ሦስቱ ኹሉ ለለቢሰ ሥጋ ያደሩ አይምሰልህ፡፡
በዚህ ጊዜ መለኮት ርቀቱን ለቆ ሳይገዝፍ ሳይለወጥ ትስብእትም ግዘፍነቱን ለቆ ሳይረቅ ሳይለወጥ እንደ ነፍስና እንደ ሥጋ በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ኾነ፡፡ ወልድ ለለቢሰ ሥጋ ማለት ይህ ነው አብ ለአጽንዖ ማለትም ሰማይና ምድር የማይወስኑትን ምሉዕ ስፉሕ ረቂቅ መለኮትን እመቤታችን በጠባብ ማኅጸን እንድትችለው አጸናት ማለት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ ማለትም ትስብእትን ከአዳም መርገም አንጽቶ ቀድሶ ለተዋሕዶተ መለኮት የበቃ አደረገው ማለት ነው፡፡ ይህን በማኅጸን በረቂቅ ምሥጢር የሠሩትን አምላካዊ ሥራ በዮርዳኖስ ወልድ ባጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ሲጠመቅ በመታየት አብ ዝንቱ ውእቱ ወልድየ የሚል ድምጽ በማሰማት መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ተቀምጦ አብ ልጀ ይህ ነው ብሎ የመሰከረለት ወልድ ይህ ነው ብሎ በጣት ጠቅሶ እንደ ማሳየት በመመስከሩ ገልጸውለታል እንጅ እስከዚያ ድረስ ሰላሳ ዘመን መንፈስ ቅዱስ ተለይቶት ኖሮ በዮርዳኖስ አደረበት ማለት አይደለም አለ፡፡ ያ ሮማዊ መልስ አጥቶ ዝም አለ፡፡
ቅባቶች ግን በፎቶው ላይ የምትመለከቱት መጽሐፋቸው ላይ ቅዱስ ገብርኤል ሳይቀር “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” ናቸው በማለት ድንግል ማርያምን እንዳበሰራት ይጽፋሉ፡፡ ይህንን ከየት እንዳገኙት አምላክ እርሱ ይወቀው፡፡ በእውነት እንዲህ ያለ ታሪክን የመበረዝ ተልእኮ ከሰይጣን ካልሆነ በቀር ከማን ሊቀበሉት ይችላሉ፡፡ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ያልተባለውን እንደተባለ እያደረጉ “ቅባት ቀደምቲቱ ሃይማኖት ናት” ለማለት ደፋ ቀና ሲሉ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ ቅባት ሃይማት ቀደምት ነው ከተባለ ከአስተምህሮው ጋራ የሚሄድ መጽሀፍ እስኪ ጥቀሱልን፡፡ በእርግጥ ወልደ አብ እና ሚሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊን እንደምትጠቅሱ እናውቃለን፡፡ እነዚህ መጻሕፍት ግን ከየትኛው የቤተክርስቲያናችን መጻሕፍት ጋራ የማይስማሙ በመሆናቸው እንደ ማስረጃ ሊጠቀሱ አይገባም፡፡

=====================================
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት
#comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡

No comments:

Post a Comment