ሐምሌ 3/2009
ዓ.ም
“ሚሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊ” የተሰኘውን የቅብአት መጽሐፍ እያገላበጥን ነጥብ
በነጥብ እየተመለከትን ነው ያለነው፡፡ እዚህ ላይ ከውይይት እና በማስረጃ ተደግፎ ከመቃወም ባለፈ ለስድብ እና ለዛቻ አስተያየት
ሊሰጥ የሚመጣን ማንኛውንም አካል የማናስተናግድ መሆኑን ከወዲሁ እንገልጻለን፡፡ ከመጽሐፉ ስገለብጥ ማለትም “---” ምልክት መካከል
አድርጌ የምጽፈው የፊደል ግድፈቱንም እንዳለ ስለምወስደው የፊደል የቃል ስህተት ብታገኙ ሙሉ በሙሉ የመጽሐፉ እንደሆነ አሳውቃለሁ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ መጽሐፉ በእውነት እኔ እንዲህ አሉ እያልኩ የምላችሁን ነገር በትክክል ይዟል ወይስ አልያዘም እያላችሁ ጥርጣሬ ውስጥም
እንዳትወድቁ በማሰብ ራሱን መጽሐፉን ገጽ በገጽ ፎቶ እያነሣሁ ከዚህ ጋራ አያይዝላችኋለሁ፡፡ እናንተም እነዚህን በፎቶው ላይ ያሉትን
የመጽሐፉን ክፍሎች በማንበብ ሙሉውን የመጽሐፉን መንፈስ እንድትረዱት እያሳሰብሁ ስህተት ናቸው የምላቸውን ነጥቦች ግን በተቻለኝ
መጠን ከመጻሕፍት አንጻር ያለውን ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ መልስ እያስቀመጥሁ
እሄዳለሁ፡፡ ይህ ማለት ግን እኔ አዋቂ ነኝ ምሥጢር ጠንቃቂ ነኝ ማለቴ እንዳልሆነ ልብ በሉልኝ! ስለዚህ በዚህ መልኩ ወደዛሬው
ጽሑፌ ላምራ፡፡
፨፨፨፨******************************************************************************፨፨፨፨
ከዚህ ቀጥለን ደግሞ የከዊንን
ሦስትነት ወደማስረዳት እንመጣለን፡፡ “ሚሥጢረ ሃይማኖት” የተባለው መጽሐፍ በፎቶው ላይ እንደምትመለከቱት ሁሉን ነገር ለአብ ሰጥቶ
ወልድና መንፈስ ቅዱስ ከአብ ተቀባዮች አድርጎ ያሳያል፡፡ አንድነታቸው አብ ነው፤ መለኮታቸው አብ ነው፤ ባሕርያቸው አብ ነው፤ ሥር
መሠረታቸው አብ ነው ወዘተ ይላል፡፡ ከዚህ እንደምንረዳው አምላክነትን ጠቅሎ የያዘ አብ ብቻ ሲሆን ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ እንደ
ርስት እየከፈለ እንደሰጣቸው ነው የሚገልጸው፡፡ ይህ አገላለጽ በጣም የከፋ ክህደትን ያመጣልና ክርስቲያን ሆይ አስተውል! ባሉት
በዚያው አንቀጽ ራሳቸውን መልሰን አስተውሉ ልንላቸው ይገባናል፡፡
ምሥጢረ ሃይማኖት የተባለው የቅባት መጽሐፍ |
የከዊንን ሦስትነት እነርሱ
እንዴት እንደገለጹት በፎቶው ተመልከቱት ከዚህ ላይ ደግሞ የከዊንን ሦስትነት ከቀደሙ ሊቃውንት አባቶች ያገኘሁትን እነሆ እላለሁ፡፡
ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ ማለት ተከፍሎ በሌለባት በአንዲት ባሕርይ
ያለ የከዊን ስም ነው፡፡ የከዊን ስም “ልብ” አብ ለራሱ ለባዊ አዋቂው (አዋቂ) ሆኖ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ልቡና (ዕውቀት)
መሆኑን የሚያመለክት ስም ነው:: ቃልም የወልድ የከዊን ስም ነው:: ለራሱ ነባቢ (ተናጋሪ) ሆኖ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ንባብ
መሆኑ የሚገለጽበት የከዊን (ቃል የመሆን) ስሙ ነው:: እስትንፋስ የመንፈስ ቅዱስ የከዊን ስሙ ነው:: መንፈስ ቅዱስ ለራሱ ሕያው
ሆኖ ለአብና ለወልድ ሕይወት እንደሆነ የምናውቅበት የከዊን (ሕይወተ አብ ወወልድ) የመሆን ስሙ ነው:: ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ
ማለት ተከፍሎ በሌለባት በአንዲት ባሕርይ ያለ የከዊን ስም ነው፡፡ ይኸውም ልዩነት ሳለበት አንድነት አንድነትም ሳለበት ልዩነት
አለበት:: ልዩነቱ በከዊን ነው አንድነቱ ግን በሕልውና መገናዘብ ነው:: ወልድ ሰው ሆነ በተባለ ጊዜ አካል ተዋሐደ እንጂ ባሕርይ
አልተዋሐደም እንዳይባል ወንጌላዊ ቃል ሥጋ ኮነ አለ እንጂ ወልድ ሥጋ ኮነ አላለም:: ባሕርይም ከተዋሐደ የሥላሴ ባሕርይ አንድ
ነውና:: ፫ቱ ሰው ሆኑ እንዳያሰኝ ከልብና ከእስትንፋስ ለይቶ “ቃል ሥጋ ኮነ” አለ:: ቃልም ማለት በአካለ አብና በአካለ መንፈስ
ቅዱስ በከዊን የምትለይ በሕልውና የምትገናዘብ እንደሆነች “ነገር በምሳሌ መዝሙር በሃሌ እንደተባለው በነፋስና በፀሐይ በእሳትና
በቀላይ መስለን መረዳት ይገባናል:: መለኮት እንደ አካላት ከ፫ ይከፈላል የሚል ሰው ይህን ነገር ከራሱ አንቅቶ በልብ ወለድ ቃል
ተናግሮታል እንጂ መጻሕፍት ከተናገሩት ኃይለ ቃልና ከመሰሉት ምሳሌ ምስክር አምጥቶ ለማስረዳት አይችልም:: የሥላሴን ባሕርይና አካል
እንደ ሰው ባሕርይና አካል አድርጎ አካል የሌለው ባሕርይ፣ ባሕርይም የሌለው አካል የለምና ባሕርይ፣ አካልን ተከትሎ ከሦስት ይከፈላል
ይላል:: ይህ ሰው ባያስተውለው ነው እንጂ ይህ ነገር ከሰማይና ከምድር ይልቅ የተራራቀ ነው:: የሰው ባሕርይ በአካል ቢከፈል በየራሱ
ልብ፣ በየራሱ ቃል፣ በየራሱ እስትንፋስ ያለው ሆኖ በየራሱ ልዩ ልዩ ሥራውን ይሠራል:: አንዳንድ ቅዱሳንም በፀጋ ቢተዋወቁና አንዳንድ
ሥራ ቢሠሩ ያደረባቸው መንፈስ ቅዱስ በሀብት አገናኝቷቸው ነው እንጂ የባሕርይና የሕልውና አንድነት ኖሯቸው አይደለም::ሥላሴ ግን
አካላቸው የተለየ ሲሆን ባሕርያቸው ተከፍሎ የሌለበት አንድ ለመሆኑ ማስረጃው የሦስቱ ልብ አንድ አብ ሆኖ አንድ ዕውቀትን ያውቃሉ::
የሦስቱ ቃል አንድ ወልድ ሆኖ አንድ ነገርን ይናገራሉ:: የሦስቱ እስትንፋስ አንድ መንፈስ ቅዱስ ሆኖ አንድ የሕይወትን ሥራ ይሠራሉ::
ቅብአቶች ግን ይህንን ሁሉ ምሥጢር ስለማያውቁ አብ አንድነታቸው፣ መለኮታቸው፣ ሥር መሠረታቸው ነው ወዘተ በማለት ይጽፋሉ፡፡ ይህስ
ይሁን አብ አንድነታቸው፣ መለኮታቸው እና ሥር መሠረታቸው ነው ከተባለ የወልድ እና መንፈስ ቅዱስ አንድነታቸው፣ መለኮታቸው እና
ሥር መሠረታቸው የሆነ በማን ሕያው ሆኖ ነው በማንስ ቃልነት ተናግሮ ነው ቢባል መልስ የላቸውም፡፡ ይህንን የተናገሩት የዋሐንን
በምሥጢር የረቀቁ መስለው ለማደናገር ካልሆነ በቀር የቤተክርስቲያናችን ሊቃውንት እንዲህ ያሉበት አንቀጽ የለም አለ ካሉም ሊሳዩን
እና ሊጠቁሙን ይችላሉ “የብራናው መጽሐፍ ቆጋ ያለው እንዲህ ይላል” ካላሉን በቀር፡፡
ምሥጢረ ሃይማኖት የተባለው የቅባት መጽሐፍ |
እንዲህም ከሆነ ሊቃውንት
“ይሤለሱ በአካላት ወይትወሐዱ በመለኮት” ያሉትን ተመልክቶ ይልቁንም “አጤን ይበልጡ ቃለ አጤ” እንዲሉ እርሱ ባለቤቱ “አነ ወአብ
፩ ንሕነ፤ እኔና አብ አንድ ነን” ዮሐ ፲÷፴:: “አነ በአብ ወአብ ብየ
፤እኔ በአብ ሕልው ነኝ አብም በእኔ ሕልው ነው” ዮሐ ፲፯÷፲ ያለውን ተረድቶ ባሕርየ መለኮት በአካል ከሦስት የማይከፈል
መሆኑን ማመን ይገባል:: ከእነዚህ ጥቅሶች የምንረዳው አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በመለኮት አንድ እንደሆኑ እንጅ መለኮታቸው አብ
እንደሆነ አይደለም፡፡ አብ በሚጠራበት ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ አይጠሩበትም፡፡ ወልድ በሚጠራበትም አብና መንፈስ ቅዱስ አይጠሩበትም፡፡
መንፈስ ቅዱስ በሚጠራበትም አብና ወልድ አይጠሩበትም፡፡ በመለኮት ግን አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ ናቸው፡፡ በሚለያየዩበት ስም
ጠርቶ አንድ የሚሆኑበትን ነገር ነገር ለአንዱ መስጠት ሦስት መለኮት ዘጠኝ አካላት ወደሚል የዮሀንስ ተዐቃቢ ክህደት ያስገባል፡፡
“ወመለኮትሰ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፤ መለኮትስ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ናቸው” ይላል ሊቁ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም
ምስጋናው፡፡ ቅባቶች እንደሚሉት የወልድ እና የመንፈስ ቅዱስ መለኮታቸው አብ ቢሆን ኖሮ አባ ሕርያቆስ “ወመለኮትሰ አብ ወወልድ
ወመንፈስ ቅዱስ” ባላለም ነበር፡፡
የኲነታት ሦስትነት እንደ
አካላት አይደለም፤ አካላት መጠቅለልና መቀላቀል ሳይኖርባቸው፣ በተከፍሎ በተፈልጦ፣ በፍጹም ገጽ፣ በፍጹም መልክ፣ በየራሳቸው የሚቆሙ
ናቸው፤ ኲነታት ግን ተፈልጦ ተከፍሎ /መለየት መከፈል/ ሳይኖርባቸው በተዋሕዶና በተጋብኦ በአንድነት አካላትን በሕልውና /በአኗኗር/
እያገናዘቡ፣ በአንድ መለኮት የነበሩ፣ ያሉ፣ የሚኖሩ ናቸው፤ እሊህም ከዊነ ልብ፣ ከዊነ ቃል፣ ከዊነ እስትንፋስ ናቸው። “ከዊነ
ልብ” በአብ መሠረትነት እራሱ ለባዊ ሆኖ፣ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ዕውቀት /ማወቂያ/ መሆን ነው። “ከዊነ ቃል” በወልድ መሠረትነት
ለራሱ ነባቢ ሆኖ፤ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ንባብ /ማናገሪያ/ መሆን ነው። “ከዊነ እስትንፋስ” በመንፈስ ቅዱስ መሠረትነት ለራሱ
ሕያው ሆኖ፣ ለአብና ለወልድ ሕይወት መሆን ነው። ሦስት ኩነታት ያልናቸው እሊህ ናቸው። የሊህም ኩነታት ምሥጢር፣ “ንግበር ሰብአ
በአርአያነ ወበአምሳሊነ፤ ሰውን በመልካችንና በምሳሌያችን እንፍጠር” ያለውን ንባብ /ዘፍ ፩÷፳፮/ መሠረት አድርጎ፣ የነፍስን የአካሏንና
የባሕርይዋን ከዊን ቢመረምሩ ይታወቃል ይረዳልም። ሲመረመርም የባሕርያቸው ከዊን በአካሏ ከዊን፤ የአካለቸውም ከዊን፣ በባሕርይዋ
ከዊን፣ ይመረምረዋል፣ ነፍስ በአካሏ፣ ከሦስት የማትከፈል ከዊን አላት። ይኸውም ከዊነ ልብ÷ ከዊነ ቃል÷ ከዊነ እስትንፋስ ነው::
በባሕርይዋ ሦስት ከዊን ያላት መሆንዋ፤ አካሏን ከሦስት አይከፍለውም:: እንዲህ ሳትከፈል፣ የልብነትዋ ከዊን /ልብ መሆንዋ/ ከቃሏና
ከእስትንፋሷ ከዊን ሳይለይ፣ በራስዋ ከዊን ከሥጋዊ ልብ ጋር ይዋሐዳል። በቃልነትዋም ከዊን /የቃሏም ከዊን/ ከልብነትዋ ከዊንና
ከእስትንፋስዋ ከዊን ሳይለይ፤ በራሱ ከዊን ከሥጋ አንደበት ጋራ ይዋሐዳል:: የእስትንፋሷም ከዊን ከልብነትዋ ከዊንና ከቃልዋም ከዊን
ሳይለይ፣ በራሱ ከዊን ከሥጋ እስትንፋስ ጋር ይዋሕዳል:: እንዲህ አድርጎ የሥላሴን ከዊን በነፍስ ከዊን ቢመረምሩ፣ ሦስቱ ሰው ሆኑ
ከማለት ይጠብቃል:: መለኮትን በአካል ሦስት ማለት ግን፤ ሊቃውንት ሁሉ በየአንቀጹ፣ “ይሤለሱ በአካላት ወይትወሐዱ በመለኮት፤ በአካል
ሦስት ሲሆኑ በመለኮት አንድ ናቸው” ያሉትን አፍርሶ፣ ሦስት አማልክት፣ ዘጠኝ አካላት ከማለት ያደርሳል፡፡
ምሥጢረ ሃይማኖት የተባለው የቅባት መጽሐፍ |
ቅባቶች ግን “አብ ብቻ”
የሚል አዲስ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ይዘው ብቅ ብለዋል፡፡ ፕሮቴስታንቱ ዓለም “ኢየሱስ ብቻ” በሚል ትምህርት ናላው እየዞረ ባለበት
በዚህ ዘመን ከወልድ እና ከመንፈስ ቅዱስ ለይቶ “አብ ብቻ” የሚለው የቅባቶች አዲሱ እምነት ወደገደል እንደሚያስገባ ልብ በሉ፡፡
“አብ ብቻ” ብለን ካላመንን ገደል እንደገባን አድርገው የሚቆጥሩት እነኝህ ለጉድ የፈጠራቸው የ21ኛው ክፍለ ዘመን መናፍቃን ገደሉን
የምታውቁት ከሆነ እናንተ የቆማችሁበት አፋፍ ነው የሚላቸው ሰው ያስፈልጋል፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በመለኮት፣ በባሕርይ፣ በሕልውና፣
በመፍጠር በማሳለፍ አንድ ናቸው ብለን እናምናለን እንጅ “አብ ብቻ” የሚል ትምህርት ቤተክርስቲያናችን አላስተማረችንም፡፡ በመለኮት
አንድ ናቸው የሚለውን ገልብጠው ከአብ ውጭ ሌላ መለኮት የላቸውም የሚሉ ከሆነ፤ በባሕርይ አንድ ናቸው የሚለውን ገልብጠው ከአብ
ውጭ ሌላ ባሕርይ የላቸውም የሚሉ ከሆነ፣ በሕልውና አንድ ናቸው የሚለውን ገልብጠው ከብ ውጭ ሌላ ሕልውና የላቸውም የሚሉ ከሆነ፤
በመፍጠር በማሳለፍ አንድ ናቸው የሚለውን ገልብጠው ምን ይሉት ይሆን? የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም ነው መቼም “በመፍጠር በማሳለፍ
አንድ ናቸው የሚለውንም ገልብጠው እኮ ከአብ ውጭ ሌላ ፈጣሪ እና አሳላፊ የላቸውም” ይሉን ይሆናል ይቅር ይበለንና!
ወገኖቼ ለአቅመ ምክር ወተግሳጽ
የደረስሁ ባልሆንም ገደሉ ቤት በኩል እንዳለ ግን አውቀዋለሁ፡፡ ስለዚህ ገደሉ ያለው በቅባቱ በኩል እንጅ በተዋሕዶው በኩል አይደለም፡፡
በተዋሕዶው በኩል የሚያንሸራትት ምንም ዓይነት መንገድ የለም ምክንያቱም ተዋሕዷልና፡፡ በቅባቱ በኩል ግን የሚያንሸራትት በቅባት
የለዘበ ነገር አለው እርሱም ወደ ገደል የሚጨምር የስህተት እና የክህደት መንገድ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment