Thursday, July 20, 2017

የክህደት ቁንጮው ሚሥጢረ ሃይማኖት--- ክፍል ፱



© መልካሙ በየነ

ሐምሌ 12/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

“ሚሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊ” የተሰኘውን የቅብአት መጽሐፍ እያገላበጥን ነጥብ በነጥብ እየተመለከትን ነው ያለነው፡፡ እዚህ ላይ ከውይይት እና በማስረጃ ተደግፎ ከመቃወም ባለፈ ለስድብ እና ለዛቻ አስተያየት ሊሰጥ የሚመጣን ማንኛውንም አካል የማናስተናግድ መሆኑን ከወዲሁ እንገልጻለን፡፡ ከመጽሐፉ ስገለብጥ ማለትም “---” ምልክት መካከል አድርጌ የምጽፈው የፊደል ግድፈቱንም እንዳለ ስለምወስደው የፊደል የቃል ስህተት ብታገኙ ሙሉ በሙሉ የመጽሐፉ እንደሆነ አሳውቃለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መጽሐፉ በእውነት እኔ እንዲህ አሉ እያልኩ የምላችሁን ነገር በትክክል ይዟል ወይስ አልያዘም እያላችሁ ጥርጣሬ ውስጥም እንዳትወድቁ በማሰብ ራሱን መጽሐፉን ገጽ በገጽ ፎቶ እያነሣሁ ከዚህ ጋራ አያይዝላችኋለሁ፡፡ እናንተም እነዚህን በፎቶው ላይ ያሉትን የመጽሐፉን ክፍሎች በማንበብ ሙሉውን የመጽሐፉን መንፈስ እንድትረዱት እያሳሰብሁ ስህተት ናቸው የምላቸውን ነጥቦች ግን በተቻለኝ መጠን ከመጻሕፍት አንጻር ያለውን ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ መልስ  እያስቀመጥሁ እሄዳለሁ፡፡ ይህ ማለት ግን እኔ አዋቂ ነኝ ምሥጢር ጠንቃቂ ነኝ ማለቴ እንዳልሆነ ልብ በሉልኝ! ስለዚህ በዚህ መልኩ ወደዛሬው ጽሑፌ ላምራ፡፡

፨፨፨፨********************************************፨፨፨፨












ዛሬ “ሚሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊ” ከተሰኘው መጽሐፍ ምእራፍ 4 ገጽ 19 ጀምሬ ነው የምጽፍላችሁ፡፡ ዝክሪ እና ጳውሊ በአፈጉባዔነት በሚመሩት በዚህ ጉባዔ ላይ ሮማውያን (ካቶሊካውያን) መልስ በማጣት በዝምታ እየተዋጡ ናቸው፡፡ በዚህም ንጉሡ ሮማውያን እንደተሸነፉ ባወቀ ጊዜ ዘመናዊውን ትምህርት እንዲያስተምሩን በሀገራችን ቢቆዩ ብሎ ተናገረ፡፡ በዚህ ጊዜ የደብረ ጽሚናው ሊቅ አባ ዝክሪ ትንቢት ተናገረ፡፡ ቅባቶች ግን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ክፍተት እየፈለጉ ያልተባለውን ተባለ፣ የተባለውንም አልተባለም በማለት የራሳቸውን ፍልስፍና ጨምረው ጽፈውት እናገኛለን፡፡ ንጉሡ የተናገረው እና ዝክሪና ጳውሊም የተናገሩት ንግግር በታሪክ ድርሳናት የምናገኘው የሚከተለው ነው፡፡
በዚህ ጊዜ ንጉሡ ገላውዴዎስ አባ ዝክሪንና አባ ጳውሊን እኔ የክርስቶስ ባሪያ ሃይማኖቴ እንደ ሃይማኖታችሁ ኦርቶዶክስ እስክንድርያዊ ነው ይህነንም እናንተ ታውቁልኛላችሁ ነገር ግን እኛ የሕክምናና የተግባረ እድ ትምህርት የለንም ሮማውያን ብዙ ጥበብ ያውቃሉና ይህን ጥበባቸውን እስኪያስተምሩን ድረስ በሀገራችን እንዲቆዩ ፈቃዳችሁ ይኹን ሲል ለመናቸው፡፡
አባ ዝክሪ የተባለው መነኲሴ ተነሥቶ እናንተ የኢትዮጵያ ሰዎች እሊህ ሮማውያን በሀገራችን ይቀመጡ ካላችሁ ወደፊት በኢትዮጵያ ላይ የሚደርስባትን ነገር ልንገራችሁ እኒህ ሰዎች ከእህቶቻችን ከልጆቻችን ይወልዳሉ እኒያ ልጆች በድብቅ ያባቶቻቸውን የካቶሊካውያንን ትምህርት ይማራሉ እኛ ወገኖቻችን መስለውን ቅስና ዲቁና ስንሾማቸው የመምህርነት ማዕርግ ስንሰጣቸው ውስጥ ውስጡን የኹለት ባሕርይን ባህል እያስተማሩ ሃይማኖታችንን ይለውጧታል ይህም የተናገርኩት ነገር አይቀርም አምስት ነገሥታት ካለፉ በኋላ ስድስተኛ ንጉሥ ከወደ ዐረማውያን ሀገር መጥቶ ይነግሣል በርሱ ጊዜ ይፈጸማል ሲል ትንቢት ተናገረ፡፡ ከዚህ በኋላ ከዐፄ ገላውዴዎስ ዐፄ ፋሲል፤ ከዐፄ ፋሲል ዐፄ ሚናስ፤ ከዐፄ ሚናስ ዐፄ ሠርጸ ድንግል፤ ከዐፄ ሠርጸ ድንግል ዐፄ ያዕቆብ፤ ከዐፄ ያዕቆብ ዐፄ ሱስንዮስ  ዐፄ ሱስንዮስ ከዐረማውያን ሀገር መጥተው ነገሡ፡፡ በስድስተኛው ንጉሥ በዐፄ ሱስንዮስ ጊዜ የአባ ዝክሪ ትንቢት ተፈጸመ፡፡
ታሪኩ ይኼ ከላይ የተመለከትነው ሆኖ ሳለ ቅባቶች ግን ገጽ 21 ላይ የጨመሩት ተረት ተረት አለ፡፡ ንጉሡ ገላውዴዎስ እና ሊቃውንቱ በብዙ እንደተከራከሩ እና እኛ የምንልህን ብቻ አድርግ በማለት እንዳስጠነቀቁት አድርገው ጽፈዋል፡፡ በእውነት ንጉሡ ግን ይህን ያህል ተከራክሯቸዋልን ብለን ስንመለከት የምናገኘው ጉዳይ ከዚያ ተለየ ነው፡፡ “ንጉሡም እንዲህ ይላቸዋል እኔ በጎውንና ክፍውን ለይቸ አላውቅም፡፡ እናንተ መጻሕፍትን የተማራችሁ ሊቃውንት የሰጣችሁኝን ሃይማኖት እቀበላለሁ እኔ በአረሚ ሀገር የኖርኩ ምን አውቃለሁ” አላቸው በማለት የፈጠራ ድረሰት ጽፈው እንመለከታለን፡፡ ንጉሡ ከፉውንና በጎውን ሃይማኖት ማያውቅ ሆኖ ቢሆን ኖሮ ይህን ጉባዔ ማዘጋጀት ለምን አስፈለገው? እንዲያውም “በአረሚ ሀገር እየኖርኩ” ብሎ እንደተናገረ ጽፈዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንጉሥ በኢትዮጵያ እየኖረ ኢትዮጵያን እያስተዳደረ በአረሚ ሀገር እየኖርኩ ብሎ ይናገራል ብየ አላስብም አልገምትምም፡፡ ንጉሡ ሊቃውንቱን እየጠየቀ ያለው ሃይማኖታዊ ጉዳይን አይደለም ምክንያቱም ሮማውያን የሚመልሱ አጥተው አፍረው ተቀምጠዋልና እነርሱን ሊመስላቸው አይችልም፡፡ ‹‹በዚህ ጊዜ ንጉሡ ገላውዴዎስ አባ ዝክሪንና አባ ጳውሊን እኔ የክርስቶስ ባሪያ ሃይማኖቴ እንደ ሃይማኖታችሁ ኦርቶዶክስ እስክንድርያዊ ነው ይህነንም እናንተ ታውቁልኛላችሁ ነገር ግን እኛ የሕክምናና የተግባረ እድ ትምህርት የለንም ሮማውያን ብዙ ጥበብ ያውቃሉና ይህን ጥበባቸውን እስኪያስተምሩን ድረስ በሀገራችን እንዲቆዩ ፈቃዳችሁ ይኹን ሲል ለመናቸው፡፡›› ነው የሚለው እውነተኛው የቤተክርስቲያናችን ታሪክ፡፡ 
ሌላው የሚገርመው ነገር አባ ዝክሪ ተናግሮታል የሚሉት ትንቢት ነው፡፡ አባ ዝክሪ የተናገረው ትንቢት ይህ ነው፡፡ ‹‹አባ ዝክሪ የተባለው መነኲሴ ተነሥቶ እናንተ የኢትዮጵያ ሰዎች እሊህ ሮማውያን በሀገራችን ይቀመጡ ካላችሁ ወደፊት በኢትዮጵያ ላይ የሚደርስባትን ነገር ልንገራችሁ እኒህ ሰዎች ከእህቶቻችን ከልጆቻችን ይወልዳሉ እኒያ ልጆች በድብቅ ያባቶቻቸውን የካቶሊካውያንን ትምህርት ይማራሉ እኛ ወገኖቻችን መስለውን ቅስና ዲቁና ስንሾማቸው የመምህርነት ማዕርግ ስንሰጣቸው ውስጥ ውስጡን የኹለት ባሕርይን ባህል እያስተማሩ ሃይማኖታችንን ይለውጧታል ይህም የተናገርኩት ነገር አይቀርም አምስት ነገሥታት ካለፉ በኋላ ስድስተኛ ንጉሥ ከወደ ዐረማውያን ሀገር መጥቶ ይነግሣል በርሱ ጊዜ ይፈጸማል ሲል ትንቢት ተናገረ፡፡ ከዚህ በኋላ ከዐፄ ገላውዴዎስ ዐፄ ፋሲል፤ ከዐፄ ፋሲል ዐፄ ሚናስ፤ ከዐፄ ሚናስ ዐፄ ሠርጸ ድንግል፤ ከዐፄ ሠርጸ ድንግል ዐፄ ያዕቆብ፤ ከዐፄ ያዕቆብ ዐፄ ሱስንዮስ  ዐፄ ሱስንዮስ ከዐረማውያን ሀገር መጥተው ነገሡ፡፡ በስድስተኛው ንጉሥ በዐፄ ሱስንዮስ ጊዜ የአባ ዝክሪ ትንቢት ተፈጸመ፡፡››
በዚህ መጽሐፍ ግን “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” የሚለውን የቅባቶች ፍልስፍና አባ ዝክሪም በትንቢቱ እንደተናገረው አስመስለው ጽፈውት ይገኛል፡፡ ይህ ድፍረት ካልሆነ በቀር ሌላ ምን ሊባል ይችላል፡፡
=====================================
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት
#comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡

No comments:

Post a Comment