© መልካሙ በየነ
ሰኔ 29/2009
ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
“ሚሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊ” የተሰኘውን የቅብአት መጽሐፍ እያገላበጥን ነጥብ
በነጥብ እንመልከተው እስኪ፡፡ እዚህ ላይ ከውይይት እና በማስረጃ ተደግፎ ከመቃወም ባለፈ ለስድብ እና ለዛቻ አስተያየት ሊሰጥ የሚመጣን
ማንኛውንም አካል የማናስተናግድ መሆኑን ከወዲሁ እንገልጻለን፡፡ ከዚህ ክፍል ጀምሮ በምጽፈው ማንኛውም ነገር ከመጽሐፉ ስገለብጥ
ማለትም “---” ምልክት መካከል አድርጌ የምጽፈው የፊደል ግድፈቱንም እንዳለ ስለምወስደው የፊደል የቃል ስህተት ብታገኙ ሙሉ በሙሉ
የመጽሐፉ እንደሆነ አሳውቃለሁ፡፡
የክህደት ቁንጮው ሚሥጢረ ሃይማኖት--- ክፍል ፩ |
ይህ መጽሐፍ በመግቢያ ገጹ ላይ እንዲህ ይላል “ይህ ሚሥጢረ ሃይማኖት የተባለ መጽሐፍ በዳሪ ዝክሪ
በማለት ነው የሚታወቅ ምክንያቱም ከግራኝ መሐመድ ወረራ በኃላ በአጼ ገላውዴዎስ ዘመነ መንግሥት ግራኝ መሐመድን ከገደሉ በኃላ አጼ
ገላውዴዎስን በሃይማኖት ምሰለን አሉ እርሳቸውም እስቲ ሊቃውንቱን ልጠይቅ አሉ ሊቃውንቱንም ሰብስበው ጉባዔ አደረጉ በጉባዔውም ዋና
መሪዎች በምሥራቅ ጎጃም የምትገኝ ስሟ ደብረ ጥሞና በተባለች ገዳም የሚኖሩ አባ ዝክሪና ጳውሊ ነበሩ እኒህም ሊቃውንት አውሮፓውያኑን
ረታቸው ከዚህ በኃላም ከሐገራችን ይውጡ አሉ ንጉሡ ግን ስለጥበባቸው ይቀመጡ አለ፡፡ በዚህ ጊዜ አባ ዝክሪ ትንቢት ተናገሩ እኒህ
ሰዎች በሀገራችን ከተቀመጡ ከወገናችን እየተዋለዱ የእኛ ሃይማኖት ቀዝቅዞ የእነርሱ ሃይማኖት ይገናል ደጉ ቴዎድሮስ እስኪወጣ ድረስ
ሃይማኖታችን ጤና አያገኝም አሉ፡፡ ስለዚህ ይህ ሃይማኖት በአጼ ሱስንዮስ ዘመነ መንግስት ጎልቶ ተነሳ በአጼ ፋሲል ጊዜ መልሶ ጠፉ
ነገር ግን ውስጥ ውስጡን መልኩን ቀይሮ መቀጠሉን አልተወም እስከ አድያም ስገድ ኢያሱ ዘመን መንግስት ድረስ ያለውን ጉባዔ እና
ክርክር ሊቃውንት በግዕዝ ቋንቋ በብራና ጽፈው ስሙንም ምስጢረ ሃይማኖት ብለው ሰየሙት ዛሬም በታላላቅ አድባራትና ገዳማት ይገኛል
አሁንም አዲሱ ትውልድ ሃይማቱን አንብቦና ተመልክቶ እንዲረዳ በማሰብ በግዕዝ ብቻ የነበረውን በአማርኛ ጭምር ተተርጉሞ እንዲታተም
አቅርበናል አሳታሚ የቅጋ ኪዳነ ምሕረት ገዳም መነኰሳት አንድነት
በኮምፒዩተርና በሕትመት የተራዱንን እግዚአብሔር ይርዳቸው በሥራውና በሁሉ ነገር ወጥተው ወርደው የተራዱንን ወልደ ተክለሃይማኖትን
ከባለቤታቸውና ከልጆቻቸው ጋር እግዚአብሄር ይጠብቅልን” በማለት ይጽፋሉ፡፡
ከዚህ የመግቢያ ገጽ ላይ እንደምንረዳው ታሪኩን ሲጀምሩ ጀምረው
ማበላሸታቸውን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ይህ ምንፍቅና ከዝክሪ እና ጳውሊም በፊት የነበረ የአባቶቻችን ሃይማኖት ነው ለማለት ጥንታዊ
መገለጫችን የሆኑትን የግዕዝ ቋንቋን እና የብራና መጻሕፍትን እንደ ማስረጃ ያቀርባል፡፡ አንድ መጽሐፍ የሚለካው በውስጡ በያዘው
ፍሬ ነገር እንጅ ብራና ስለሆነ አልያም ወረቀት ስለሆነ በአማርኛ ስለተጻፈ አልያም በግዕዝ ስለተጻፈ አይደለም፡፡ ሊቃውንቱ ምሥጢረ
ሃይማኖት ብለው በግዕዝ የጻፉት ይህንን እንዳልሆነ ልብ ያለው ሁሉ ልብ ያደርገዋል፡፡ ምክንያቱም ከመሠረተ እምነታችን የወጣ ማንኛውም
ዓይነት አስተምህሮ የቤተክርስቲያናችን ስላልሆነ ነው፡፡
እነዚህ ዝክሪ እና ጳውሊ የሚባሉት እነማን እንደሆኑ ስለእነዚህ ሊቃውንት መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ በ1954 ዓ.ም በጻፉት “መድሎተ
አሚን” ላይ በመቅድም ገጻቸው ይናገራሉ፡፡ ሊቁ በመቅድማቸው ኹለተኛ ክፍል ላይ “ይህ የካቶሊክ ባህል ወደ ኢትዮጵያ በምን ጊዜ
እንደመጣና የኢትዮጵያ ሊቃውንት በምን ዓይነት እንደተቃወሙት የሚገልጽ ታሪክ” በማለት ጽፈዋል ታሪኩን እንደሚከተለው በቀጥታ እገለብጠዋለሁ፡፡
እነርሱ ከጻፉት ታሪክ ጋር መመሳሰል አለመመሳሰሉን ለእናንተው እተወዋለሁ፡፡ ኢትዮጵያን ግራኝ መሀመድ በወረራት ጊዜ ዐፄ ልብነ
ድንግል ከፖርቹጊዝ መንግሥት እርዳታ ጠይቀው እርሳቸው ከሞቱ በኋላ በፖርቹጊዞች እርዳታ ግራኝ ድል ሆኖ ኢትዮጵያ ሙሉ ነጻነቷን
አግኝታ መንግሥቷን በትክክል ማቋቋሟ የታወቀ ነው፡፡
በዚህ ጊዜ ከኢትዮጵያ ተልኮ ፖርቹጊዞችን ለእርዳታ
ያመጣው ቤርሙዲዝ ከኢትዮጵያ ግዛት ገሚሱ ለፖርቹጊዝ መንግሥት ይሰጥ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንም ከእንግዲህ ወዲያ አቡን ከእስክንድርያ
መምጣቱ ቀርቶ ከሮም ይምጣ እኔም ለኢትዮጵያ አንደኛ መጀመሪያ ሮማዊ ጳጳስ ልሁን ብሎ ዐፄ ገላውዴዎስን ጠየቀ፡፡ ዐፄ ገላውዴዎስም
ሊቃውንቱን ሰብስበው ምን እናድርግ ብለው ጠየቁ፡፡ የኢትዮጵያ ሊቃውንትም ፍርድ በቃ ይስጡን እንከራከርና ሮማውያን ቢረቱን እንልቀቅላቸው
ብንረታቸው ይልቀቁልን አሏቸው፡፡ ንጉሡም ፈቅደው ጉባዔ ተደረገ ለኢትዮጵያ ሊቃውንት አፈ ጉባኤ ዝክሪና ጳውሊ ኾኑ፡፡
ዝክሪና ጳውሊም በጎጃም ጠቅላይ ግዛት በዲማ ቅዱስ
ጊዮርጊስ አጠገብ የሚገኝ የደብረ ጽሙና ገዳም ሊቃውንት ናቸው፡፡
ኢትዮጵያውያን ሮማውያንን ሀገራችሁ ወዴት ነው ሃይማኖታችሁ
ምንድን ነው ሲሉ ጠየቋቸው፡፡ ሮማውያን ሲመልሱ ሀገራችን ሮም ነው፤ ሃይማኖታችንም ኹለት ባሕርይ ኹለት ጠባይዕ አንዱ የመለኮቱ
አንዱ የትስብእቱ እንላለን፡፡ ኹለተኛም ወልድ ከአብ ያንሳል መንፈስ ቅዱስም ከወልድ ያንሳል እንላለን አሏቸው፡፡
ኢትዮጵያውያን ሲመልሱ ከቅዱሳት መጻሕፍት እንዲህ
የሚል ምን አለ እስኪ አስረዱን አሏቸው፡፡
ሮማውያን ሲመልሱ እርሱው ራሱ ወልድ ደቀመዛሙርቱ
ሕልፈተ ዓለም የሚሆነው መቼ ነው ብለው ቢጠይቁት መላእክትም ቢሆኑ ወልድም ቢሆን ከአብ በቀር ያችን ዕለት ያችን ሰዓት የሚያውቃት
የለም ብሏል፡፡ ስለዚህ አብ መለኮት ስለሆነ ያውቃል ወልድ መንፈስ ቅዱስ ግን መለኮት ስላልሆኑ አያውቁም እንላለን እናንተ ይህን
ነገር ምን ትሉታላችሁ አሉ፡፡
አባ ዝክሪ ሲመልስ ሦስቱን አካላት አብ ወልድ መንፈስ
ቅዱስን አንድ አምላክ የምንላቸው አብን ልብ ወልድን ቃል መንፈስ ቅዱስን እስትንፋስ ብለን በአብ ልብነት ያስባሉ ያውቃሉ፤ በወልድ
ቃልነት ይናገራሉ፤ በመንፈስ ቅዱስ እስትንስነት ሕያዋን ሆነው ይኖራሉ ለየራሳቸው ልብ ቃል እስትንፋስ የላቸውም በማለት ነው፡፡
ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ ያለው አንድ ሰው በልቡ አስቦት አውቆት ለመናገር ጊዜው ባለመድረሱ ሰዓት እየጠበቀለት ሰውሮ የያዘውን ነገር
ጊዜው ባለመድረሱ ምክንያት በቃሉ ሳይናገረው ቢቆይ ቢጠየቅም ዛሬ አልናገረውም ቢል አያውቅም እንደማይባል ወልድም ያችን ዕለት ያችን
ሰዓት የምትገለጽበት ጊዜው እስኪደርስ በልቤ በአብ ሰውሬ አቆያታለሁ እንጅ ዛሬ በቃልነቴ አውጥቼ አልናገራትም ማለቱ ነው እንጅ
የማያውቃት ሆኖ አይደለም፡፡ እንዲህስ ባይሆን የከዊን ስማቸውና ግብራቸው ተፋልሶ አብ ቃል፤ ወልድ ልብ በተባሉ ነበረ አለው፡፡
በዚህ ጊዜ ሮማውያን መልስ አጥተው ዝም አሉ፡፡
ኹለተኛ
ጥያቄ፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንድ ሮማዊ ተነሥቶ መለኮት ሥጋ
አልሆነም ሥጋም መለኮት አልሆነም ሥጋ ለመለኮት እንደ ብረት ልብስ እንደ ጥሩር ኾነው መለኮትና ሥጋ እንደ ኀዳሪና ማኅደር ኾነው
መለኮት የመለኮትን ሥራ ትስብእትም የትስብእትን ሥራ ሲሰሩ ኖረው በዕርገቱ ጊዜ የለበሰውን ሥጋ አውልቆ በሦስተኛው ሰማይ አኑሮት
በየማነ አብ በዘባነ ኪሩብ ተቀመጠ፡፡ የዚህም ምሳሌው አንድ ንጉሥ ለጦርነት ወደ ሰልፍ ሲገባ የጦርነት ልብስ ይለብሳል፡፡ ሲዋጋ
ውሎ ድል ካደረገ በኋላ የለበሰውን የጦር ልብስ አውልቆ ከግምጃ ቤት ሰቅሎ ልብሰ መንግሥቱን ለብሶ በዙፋኑ ላይ እንደሚቀመጠው ያለ
ነው እንጅ ትስብእቱን ከመለኮቱ ጋራ በአባቱ ቀኝ አያስቀምጠውም አለ፡፡
አባ ዝክሪ ሲመልስ ነፍስ ርቀቷን ሳትለቅ ሥጋ ግዙፍ
ውሱን መኾኑን ሳይለቅ ተዋሕደው አንድ ሰው እንዲኾኑ መለኮት ምልዐቱን ስፍሐቱን ርቀቱን ሳይለቅ ትስብእትም ግዙፍነቱን ውሱንነቱን
ሳይለቅ በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ኾኗል እንጅ እንደ ልብስና እንደ ገላ አይደለም አለ፡፡
ሮማዊ መለኮት ከደረሰበት ኹሉ ይህ መዋቲ ትስብእት
ደረሰ ትላለህን አለ፡፡
አባ ዝክሪ ሲመልስ እኔስ መለኮት እና ትስብእት በተዋህዶ
አንድ ስለሆኑ መለኮት በሥጋ ውሱን ግዙፍ ኾነ፤ ትስብእትም በመለኮት ምሉዕ ስፉሕ ረቂቅ ኾነ እላለሁ፡፡ ትስብእት ከመለኮት ተለይቶ
በሦስተኛው ሰማይ እንዳልቀረ በየማነ አብ በዘባነ ኪሩብ እንደተቀመጠም
ሲያስረዳ አሜሃ ትሬእይዎ ለወልደ እጓለ እመሕያው እንዘ ይነብር በየማነ እግዚአብሔር ብሏል፡፡ በክበበ ትስብእት በግርማ መለኮት
ዳግም እንዲመጣ ሲያስረዳም ወአመ ይመጽእ ወልደ እጓለ እመሕያው በስብሐተ አቡሁ ወኲሎሙ መላእክቲሁ ምስሌሁ ብሏል፡፡ ይህ ንባብ
በቅዱስ ወንጌል መጻፉን ታምናለህ ትክዳለህ? አለው፡፡ ሮማዊ መልስ አጥቶ ዝም አለ፡፡
ሦስተኛ
ጥያቄ፡፡
ሮማዊ እኔ ክርስቶስን ፍጡር እለዋለሁ አለ፡፡
አባ ጳውሊ ሲመልስ ክርስቶስን ፍጡር የሚል ንባብ
ከምን ታገኛለህ አለው፡፡
ሮማዊ አምላክ ከኾነ ከሣምራዊት ውኃ እስኪለምን ድረስ
ለምን ተጠማ ከላይ ያለው ሐኖስ ከታች ያለው ውቅያኖስ በመኃል እጁ ሲሆን አምላክ ይጠማልን አለ፡፡
አባ ጳውሊ ሲመልስ ፍጡር ከኾነ የእግዚአብሔርንስ
ስጦታ አውቀሽ ቢኾን ይህ ውኃ አጠጭኝ ብሎ የሚለምንሽ ማን እንደሆነ ተገንዝበሽ አንች የሕይወት ውኃን አጠጣኝ ብለሽ በለመንሺው
ነበረ እርሱም በሰጠሸ ነበረ ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ኹሉ ዳግመኛ ይጠማል እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ግን ዳግመኛ ይህ እኔ የምሰጠው
ውኃ ለዘላለም ሕይወት ሊኾነው ከውስጡ ሲመነጭ ይኖራል እንጅ ዳግመኛ አይጠማም ለምን አላት አለው፡፡
ዐራተኛ ጥያቄ፡፡
ሮማዊ አምላክ ከኾነ አልዓዛርን ወዴት ቀበራችሁት
ብሎ ለምን ጠየቀ የተቀበረበትን ባላወቀውም ነበረን፡፡ ኹለቱ ዕውራንስ የዳዊት ልጅ ይቅር በለን ባሉት ጊዜ ምን ትሻላችሁ ብሎ ለምን
ጠየቃቸው የሚሹትን ባላወቀውም ነበረን አለ፡፡
አባ ጳውሊ ሲመልስ እግዚአብሔር አዳምን አይቴ ሀሎከ ብሎ ጠየቀው ይላል ዘፍ ፫÷፱፡፡ ሙሴንም ምንት ውስተ እዴከ ብሎ ጠየቀው
ይላል፡፡ ዘፀ ፬÷፪፡፡ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ መጠየቁ አዳም ያለበትን ቦታ አጥቶት፤ ሙሴም በእጁ ምን እንደያዘ አላውቀው ብሎ
ይኾን አይደለም፡፡ ይህም ይህን የመሰለ ጥያቄ ነው፡፡ በዚያውስ ላይ ፍጡር ከኾነ አልዓዛር አልዓዛር ነዓ ፃዕ አፍአ እመቃብር ብሎ
ሊያስነሣው እንደምን ቻለ፡፡ በደረቅ ግንባርስ ላይ ዐይን ሊፈጥር እንደምን ቻለ አለው፡፡
ሮማዊ ይህን የመሳሰለስ ቅዱሳንም ልዩ ልዩ የኾኑ
ብዙ ተአምራት ያደርጋሉ አለ፡፡
አባ ጳውሊ ሲመልስ ቅዱሳን ልዩ ልዩ ተአምራት ቢያደርጉ
የርሱን ስም ጠርተው በስሙ ለኢየሱስ ናዝራዊ ተንሥእ ወሑር እያሉ ነው፡፡ ግብ ሐዋ ፫÷፮ ፤፱÷፴፬፤ ፲፮÷፲፰ እርሱ ግን እኤዝዘከ
ፃዕ እምኔሁ እያለ በገዛ ሥልጣኑ ነውና ቅዱሳን ከሚያደርጉት ተአምራት ጋራ ሊነጻጸር አይገባውም አለ፡፡ በዚህ ጊዜ ሮማዊ መልስ
አጥቶ ዝም አለ፡፡
ዐምስተኛ
ጥያቄ፡፡
ስሙን ልዮን የሚሉት አንድ ሮማዊ ተነሥቶ ወልደ አብ
ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ሥጋ ማርያምን በለበሰ ጊዜ ሰይፍ በሰገባው እንዲከተትና እንዲቀመጥ አደረበት እንጅ አልተዋሐደውም በሰላሳ
ዘመኑ በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በራሱ ላይ ሲቀመጥ መለኮቱ ከትስብእቱ ተዋሐዶ የጸጋ አምላክ ኾነ መዋቲ ትስብእትም
የማይሞት ኾነ ከሰላሳ ዘመን በፊት የጸጋ አምላክ ስላልኾነ አምላካዊ ሥራ አልሠራም ከተጠመቀ በኋላ ግን የጸጋ አምላክ ስለኾነ ውኃውን
ወይን አደረገ ብዙ የአምላክነት ሥራ ሠራ አለ፡፡
እንደዚኸውም በንግድ ምልክት መጥቶ እስክንድርያዊ
መስሎ በኢትዮጵያ የሚኖር አንድ ሰው ተነሥቶ እንዲህ ሲል ተናገረ እናንተ ኢትዮጵያውያን ቃል ሥጋ በለበሰ ጊዜ በማኅጸነ ማርያም
መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ የባሕርይ አምላክ ኾነ ትላላችሁ በማኅጸን መንፈስ ቅዱስን ሲቀበል ያየው የለም፡፡ ሮማውያን ግን እስከ ሰላሳ
ዘመን በሰብአዊ ግብር ኖሮ ሲጠመቅ መንፈስ ቅዱስ ሰው ሁሉ እያየው በራሱ ላይ ስለተቀመጠበት የጸጋ አምላክ ኾኖ የአምላክነት ሥራ
ሠራ ይላሉና ከእስክንድርያ ሃይማኖት የሮማ ሃይማኖት ትሻላለች አለ፡፡
አባ ጳውሊ ሲመልስ ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ሲያበሥራት መንፈስ ቅዱስ ባንቺ ላይ
ይመጣል የአብም ኃይሉ ይጋርድሻል ካንች የሚወለደውም ቅዱስ ነው የልዑል የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል ብሎ ሦስቱም አካላት በማኅጸነ
ማርያም እንደ አደሩ ተናግሯል፡፡ ማደራቸውም አብ ለአጽንዖ መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ ወልድ ለለቢሰ ሥጋ ነው እንጅ ሦስቱ ኹሉ ለለቢሰ
ሥጋ ያደሩ አይምሰልህ፡፡
በዚህ ጊዜ መለኮት ርቀቱን ለቆ ሳይገዝፍ ሳይለወጥ ትስብእትም ግዘፍነቱን ለቆ ሳይረቅ
ሳይለወጥ እንደ ነፍስና እንደ ሥጋ በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ኾነ፡፡ ወልድ ለለቢሰ ሥጋ ማለት ይህ ነው አብ ለአጽንዖ
ማለትም ሰማይና ምድር የማይወስኑትን ምሉዕ ስፉሕ ረቂቅ መለኮትን እመቤታችን በጠባብ ማኅጸን እንድትችለው አጸናት ማለት ነው፡፡
መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ ማለትም ትስብእትን ከአዳም መርገም አንጽቶ ቀድሶ ለተዋሕዶተ መለኮት የበቃ አደረገው ማለት ነው፡፡ ይህን
በማኅጸን በረቂቅ ምሥጢር የሠሩትን አምላካዊ ሥራ በዮርዳኖስ ወልድ ባጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ሲጠመቅ በመታየት አብ ዝንቱ
ውእቱ ወልድየ የሚል ድምጽ በማሰማት መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ተቀምጦ አብ ልጀ ይህ ነው ብሎ የመሰከረለት
ወልድ ይህ ነው ብሎ በጣት ጠቅሶ እንደ ማሳየት በመመስከሩ ገልጸውለታል እንጅ እስከዚያ ድረስ ሰላሳ ዘመን መንፈስ ቅዱስ ተለይቶት
ኖሮ በዮርዳኖስ አደረበት ማለት አይደለም አለ፡፡ ያ ሮማዊ መልስ አጥቶ ዝም አለ፡፡
በዚህ ጊዜ ንጉሡ ገላውዴዎስ አባ ዝክሪንና አባ ጳውሊን እኔ የክርስቶስ ባሪያ ሃይማኖቴ
እንደ ሃይማኖታችሁ ኦርቶዶክስ እስክንድርያዊ ነው ይህነንም እናንተ ታውቁልኛላችሁ ነገር ግን እኛ የሕክምናና የተግባረ እድ ትምህርት
የለንም ሮማውያን ብዙ ጥበብ ያውቃሉና ይህን ጥበባቸውን እስኪያስተምሩን ድረስ በሀገራችን እንዲቆዩ ፈቃዳችሁ ይኹን ሲል ለመናቸው፡፡
አባ
ዝክሪ የተባለው መነኲሴ ተነሥቶ እናንተ የኢትዮጵያ ሰዎች እሊህ ሮማውያን በሀገራችን ይቀመጡ ካላችሁ ወደፊት በኢትዮጵያ ላይ የሚደርስባትን
ነገር ልንገራችሁ እኒህ ሰዎች ከእህቶቻችን ከልጆቻችን ይወልዳሉ እኒያ ልጆች በድብቅ ያባቶቻቸውን የካቶሊካውያንን ትምህርት ይማራሉ
እኛ ወገኖቻችን መስለውን ቅስና ዲቁና ስንሾማቸው የመምህርነት ማዕርግ ስንሰጣቸው ውስጥ ውስጡን የኹለት ባሕርይን ባህል እያስተማሩ
ሃይማኖታችንን ይለውጧታል ይህም የተናገርኩት ነገር አይቀርም አምስት ነገሥታት ካለፉ በኋላ ስድስተኛ ንጉሥ ከወደ ዐረማውያን ሀገር
መጥቶ ይነግሣል በርሱ ጊዜ ይፈጸማል ሲል ትንቢት ተናገረ፡፡ ከዚህ በኋላ ከዐፄ ገላውዴዎስ ዐፄ ፋሲል፤ ከዐፄ ፋሲል ዐፄ ሚናስ፤
ከዐፄ ሚናስ ዐፄ ሠርጸ ድንግል፤ ከዐፄ ሠርጸ ድንግል ዐፄ ያዕቆብ፤ ከዐፄ ያዕቆብ ዐፄ ሱስንዮስ ዐፄ ሱስንዮስ ከዐረማውያን ሀገር መጥተው ነገሡ፡፡ በስድስተኛው ንጉሥ በዐፄ
ሱስንዮስ ጊዜ የአባ ዝክሪ ትንቢት ተፈጸመ፡፡
ታሪኩ ይህ ሆኖ ሳለ እነርሱ ግን ሌሎች ነገሮችን
በራሳቸው ፈቃድ እየጨመሩ ዝክሪ እና ጳውሊ “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” ብለዋል በማለት በሊቃውንቱ ላይ ሲያፌዙ
ተስተውሏል፡፡ የዚህ መጽሐፍ መግቢያ ገጽ ላይ እንደምትመለከቱት የፊደሉን ግድፈት ማንም “ኢዲት” እንዳላደረገው የሚያሳይ ነው፡፡
ይህን መጽሐፍ በማሳተም በኩል እርዳታ ያደረጉላቸውን ወልደ ተክለሃይማኖትን ከባለቤታቸውና ከልጆቻቸው ጋራ ማመስገናቸው የሚከፋ ባይሆንም ወልደ
ተክለሃይማኖትን ከባለቤታቸውና ከልጆቻቸው ጋራ ግን እየሄዱበት ካለው የስህተት ጎዳና እንዲመለሱ የሚመክራቸው ቢኖር መልካም እንደሆነ
አስባለሁ፡፡
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡
No comments:
Post a Comment