ሐምሌ 10/2009
ዓ.ም

፨፨፨፨********************************************፨፨፨፨

ገጽ 11 ላይ “መለኮት ማለት አምላክ ማለት ነው” በማለት ቅባቶች
የተረጎሙትን ቃል እኛ በሊቃውንቱ አንደበት የተተረጎመውን የመለኮትን ትርጓሜ እንመልከት፡፡ መለኮት ንባቡ አንድ ሲሆን፣
ትርጓሜው ብዙ ነው፡፡
፩ኛ. ብርሃን ማለት ይሆናል::
አግናጥዮስ “እኁዛን እሙንቱ በፅምረተ ፩ መለኮት ዘውእቱ ብርሃን ዘይሰርቅ እምኔሁ ሥላሴ” እንዳለ:: ሃይማኖተ አበው ምዕ ፲፩
÷ ፰-፱ በዚህ አንቀጽ ብርሃን የተባለ መለኮት ከሦስት የሚከፈል ከሆነ፣ አንዱን ልብስ ሦስት ሰዎች ከሦስት እንዲለብሱ፣ ሦስቱ
አካላት አንዱን ብርሃን ከሦስት ተካፈሉት ሊባል ይገባልን? ቢሉ እኛስ በአብ አካል ያለች ብርሃን በወልድ አካልና በመንፈስ ቅዱስ
ያለች አንዲት ብርሃን ናትና “በአንድ መለኮት አንድ አድራጊነት፤ የተገናዘቡ ናቸው፤ ይህም መለኮት የአካል ሦስትነት የሚገኝለት
አንድ ብርሃን ነው” ብሎ አግናጥዮስ ስለነገረን፤ ከሦስት የማይከፈል አንድ ብርሃን በሦስቱ አካላት እንዳለ እናምናለን:: ዮሐንስ
ዘአንጾኪያ ፶፩ኛ “አብ ብርሃን ወልድ ብርሃን መንፈስ ቅዱስ ብርሃን
ዳዕሙ ውእቱ ፩ ብርሃን ዘኢይትከፈል ወኢይትዌለጥ በህላዌ መለኮት፤ አብ ብርሃን ነው ወልድ ብርሃን ነው መንፈስ ቅዱስ ብርሃን ነው፤
ነገር ግን በመለኮት ሕላዌ የማይለወጥ የማይከፈል አንድ ብርሃን ነው” ብሏል:: ሃይማኖተ አበው ምዕ ፻፲፬ ክፍል ፩ ቁጥር ፭፡፡
፪ኛ. ሕይወት ማለት ይሆናል፡፡ አግናጥዮስ ዘአንጾኪያ “ኢተአምርኑ ከመ ለእመ ትቤ መለኮት ሞተ፣ ትከውን
ቀታሊሆሙ ለሥሉስ ቅዱስ እስመ ባሕርየ ሥላሴ ፩ ውእቱ ዘውእቱ ፩ መለኮት፤ መለኮት ሞተ ብትል አንተ የሥሉስ ቅዱስ ገዳያቸው እንድትሆን
አታውቅምን? የሥላሴ ባሕርይ አንድ ነውና፤ ይኸውም አንድ /ሕይወት/ መለኮት ነው” ብሏል:: ሃይማኖተ አበው ምዕ ፲፩ ክፍል ፩
ከቁጥር ፲፫-፲፬ በዚህ አንቀጽ መለኮት የተባለ ባሕርይ ሦስቱን አንድ የሚያደርግ አንድ ሕይወት እንደሆነ ያስተውሏል:: ሕይወት
የተባለ መለኮት በአካል ከሦስት የሚከፈል ከሆነማ አንዱ ቢሞት ሦስቱ ሞቱ እንደምን ባላሰኛቸውም ነበር? አንድ ቢሆን አይደለምን?
በሕይወት ከሚመሳሰሉ ብዙ ሰዎች አንዱ ቢሞት ሁሉም ሞቱ ያሰኛልን::
፫ኛ. አገዛዝ ማለት ይሆናል::
ነቢዩ ዳዊት “ውስተ ኩሉ በሐውርት መለኮቱ፤ አገዛዙ በሀገሮች ሁሉ ነው” እንዳለ:: መዝሙር ፻፪÷፳፪
፬ኛ. ጌትነት ማለት ይሆናል::
ጳውሎስ “ወከመዝ ይትአመር ኃይሉ ወመለኮቱ ዘለዓለም፤ የዘለዓለም የሚሆን ኃይሉ ጌትነቱም እንዲህ ይታወቃል” እንዳለ:: (ሮሜ ፩÷፳)
ቅዱስ ጴጥርስም “ዘበኃይለ መለኮቱ ወኀበ ለነ ኩሎ ምግባረ ዘይወስድ ኀበ ሕይወት ወጽድቅ፤ በጌትነቱ ኃይል ወደ ሕይወትና ወደ ጽድቅ
የሚወስድ ምግባርን የሰጠን” ብሏል:: (፪ኛ ጴጥ ፩÷፫) ኄሬኔዎስም ፫ኛ
ቅዱስ ጳውሎስ “እስመ ዘሐመ ተሰቅለ በድካም፤ ሕያው ውእቱ በኃይለ እግዚአብሔር፤ ደክሞ የተሰቀለውና የሞተው በእግዚአብሔር
ኃይል ሕያው ነው” ያለውን (፪ኛ ቆሮ ፲፫ ÷፬-፭) ሲተረጉም “ወሐይወ በኃይለ እግዚአብሔር ዘውእቱ መለኮት፤ በእግዚአብሔር ኃይል
ተነሣ፣ ይኸውም መለኮቱ ነው” ብሏል:: ሃይማኖተ አበው ምዕ ፯ ክፍል ፩ ቁጥር ፴ በዚህ መለኮት የተባለ ጌትነት ወይም ሥልጣን
እንደሆነ ማስተዋል ነው::
፭ኛ. ክብር ማለት ይሆናል::
ሐዋርያው ጴጥሮስ “ከመ በእንተ ዝንቱ ትኩኑ ሱቱፋነ ለመለኮተ ዚአሁ፤ ስለዚህ ነገር የክብሩ ተካፋዮች ትሆኑ ዘንድ ለምግባር ለትሩፋት
ሁሉ” ፪ኛ ጴጥሮስ ፩÷፬ ባለው መረዳት ነው::
፯ኛ. አምላክነት ማለት ይሆናል::
ዮሐንስ ዘአንጾኪያ “ይገብር መንክራተ በመለኮቱ፤ ወይትዌከፍ ሕማማተ በትስብእቱ፤ በአምላክነቱ ተአምራትን ያደርጋል፣ በሰውነቱ መቀበል”
አንዳለ (ክፍል አንድ) እመልክተ ሲኖዲቆን፡፡
የመለኮት ትርጉሙ ከላይ የተመለከትነው
ነው፡፡ ምንም እንኳ ዝክሪ እና ጳውሊ ቅባቶች እንደሚሉት ያልተናገሩ ቢሆንም ለእነርሱ መልስ ይሆን ዘንድ ሁለተኛውን እና ሦስተኛውን
የሮማውያን ጥያቄ እና የዝክሪ እና የጳውሊን መልሶች ከታሪክ ድርሳናት ያገኘነውን እንጽፋለን፡፡ ይኸውም ታላቁ የሀገራችን ሊቅ መልአከ
ብርሃን አድማሱ በመድሎተ አሚን መጽሐፋቸው በመቅድን ገጻቸው ተጽፎ የተገኘ ነው፡፡ ይህንንም በተመለከተ ከየካቲት 20-22 ድረስ
“ዝክሪ እና ጳውሊ እነማን ናቸው?” በሚል ርእስ ለሦስት ተከታታይ ክፍሎች መጻፌ ይታወቃል፡፡ አሁን በያዝኩት ርእስም በክፍል አንድ
ሙሉውን የጻፍሁት መሆኑ ይታወቃል ሆኖም ግን ቅባቶች በመጽሐፋቸው
ለጻፉት የተሳሳተ መረጃ ሁሉ አልፌ አልፌ ማቅረቤን እቀጥላለሁ፡፡
ኹለተኛ
ጥያቄ፡

አባ ዝክሪ ሲመልስ ነፍስ ርቀቷን ሳትለቅ ሥጋ ግዙፍ
ውሱን መኾኑን ሳይለቅ ተዋሕደው አንድ ሰው እንዲኾኑ መለኮት ምልዐቱን ስፍሐቱን ርቀቱን ሳይለቅ ትስብእትም ግዙፍነቱን ውሱንነቱን
ሳይለቅ በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ኾኗል እንጅ እንደ ልብስና እንደ ገላ አይደለም አለ፡፡
ሮማዊ መለኮት ከደረሰበት ኹሉ ይህ መዋቲ ትስብእት
ደረሰ ትላለህን አለ፡፡
አባ ዝክሪ ሲመልስ እኔስ መለኮት እና ትስብእት በተዋህዶ
አንድ ስለሆኑ መለኮት በሥጋ ውሱን ግዙፍ ኾነ፤ ትስብእትም በመለኮት ምሉዕ ስፉሕ ረቂቅ ኾነ እላለሁ፡፡ ትስብእት ከመለኮት ተለይቶ
በሦስተኛው ሰማይ እንዳልቀረ በየማነ አብ በዘባነ ኪሩብ እንደተቀመጠም
ሲያስረዳ አሜሃ ትሬእይዎ ለወልደ እጓለ እመሕያው እንዘ ይነብር በየማነ እግዚአብሔር ብሏል፡፡ በክበበ ትስብእት በግርማ መለኮት
ዳግም እንዲመጣ ሲያስረዳም ወአመ ይመጽእ ወልደ እጓለ እመሕያው በስብሐተ አቡሁ ወኲሎሙ መላእክቲሁ ምስሌሁ ብሏል፡፡ ይህ ንባብ
በቅዱስ ወንጌል መጻፉን ታምናለህ ትክዳለህ? አለው፡፡ ሮማዊ መልስ አጥቶ ዝም አለ፡፡
ሦስተኛ
ጥያቄ፡፡
ሮማዊ እኔ ክርስቶስን ፍጡር እለዋለሁ አለ፡፡
ሮማዊ አምላክ ከኾነ ከሣምራዊት ውኃ እስኪለምን ድረስ
ለምን ተጠማ ከላይ ያለው ሐኖስ ከታች ያለው ውቅያኖስ በመኃል እጁ ሲሆን አምላክ ይጠማልን አለ፡፡
አባ ጳውሊ ሲመልስ ፍጡር ከኾነ የእግዚአብሔርንስ
ስጦታ አውቀሽ ቢኾን ይህ ውኃ አጠጭኝ ብሎ የሚለምንሽ ማን እንደሆነ ተገንዝበሽ አንች የሕይወት ውኃን አጠጣኝ ብለሽ በለመንሺው
ነበረ እርሱም በሰጠሸ ነበረ ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ኹሉ ዳግመኛ ይጠማል እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ግን ዳግመኛ ይህ እኔ የምሰጠው
ውኃ ለዘላለም ሕይወት ሊኾነው ከውስጡ ሲመነጭ ይኖራል እንጅ ዳግመኛ አይጠማም ለምን አላት አለው፡፡
ዐራተኛ
ጥያቄ፡፡
ሮማዊ አምላክ ከኾነ አልዓዛርን ወዴት ቀበራችሁት
ብሎ ለምን ጠየቀ የተቀበረበትን ባላወቀውም ነበረን፡፡ ኹለቱ ዕውራንስ የዳዊት ልጅ ይቅር በለን ባሉት ጊዜ ምን ትሻላችሁ ብሎ ለምን
ጠየቃቸው የሚሹትን ባላወቀውም ነበረን አለ፡፡
አባ ጳውሊ ሲመልስ እግዚአብሔር አዳምን አይቴ ሀሎከ ብሎ ጠየቀው ይላል ዘፍ ፫÷፱፡፡ ሙሴንም ምንት ውስተ እዴከ ብሎ ጠየቀው
ይላል፡፡ ዘፀ ፬÷፪፡፡ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ መጠየቁ አዳም ያለበትን ቦታ አጥቶት፤ ሙሴም በእጁ ምን እንደያዘ አላውቀው ብሎ
ይኾን አይደለም፡፡ ይህም ይህን የመሰለ ጥያቄ ነው፡፡ በዚያውስ ላይ ፍጡር ከኾነ አልዓዛር አልዓዛር ነዓ ፃዕ አፍአ እመቃብር ብሎ
ሊያስነሣው እንደምን ቻለ፡፡ በደረቅ ግንባርስ ላይ ዐይን ሊፈጥር እንደምን ቻለ አለው፡፡
ሮማዊ ይህን የመሳሰለስ ቅዱሳንም ልዩ ልዩ የኾኑ
ብዙ ተአምራት ያደርጋሉ አለ፡፡

ቅባቶች በመጽሐፋቸው ያቀረቡትንና በታሪክ ድርሳናት
ተጽፎ የምናገኘውን ጽሑፍ ልብ ብላችሁ በማስተዋል ተመልከቱት፡፡ የጥያቄውን ቅደም ተከተል የአገራችን ሊቃውንት መልስ እና ሮማውያንን
ጥያቄ በሁለቱም የተጻፈውን አስተውላችሁ ተመልከቱት፡፡ ከዚያም በኋል ንጽጽራችሁን አስተያየት መስጫው ላይ አስቀምጡ፡፡
No comments:
Post a Comment