Friday, July 7, 2017

የክህደት ቁንጮው ሚሥጢረ ሃይማኖት--- ክፍል ፪




 © መልካሙ በየነ
ሰኔ 30/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

“ሚሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊ” የተሰኘውን የቅብአት መጽሐፍ እያገላበጥን ነጥብ በነጥብ እየተመለከትን ነው ያለነው፡፡ እዚህ ላይ ከውይይት እና በማስረጃ ተደግፎ ከመቃወም ባለፈ ለስድብ እና ለዛቻ አስተያየት ሊሰጥ የሚመጣን ማንኛውንም አካል የማናስተናግድ መሆኑን ከወዲሁ እንገልጻለን፡፡ ከመጽሐፉ ስገለብጥ ማለትም “---” ምልክት መካከል አድርጌ የምጽፈው የፊደል ግድፈቱንም እንዳለ ስለምወስደው የፊደል የቃል ስህተት ብታገኙ ሙሉ በሙሉ የመጽሐፉ እንደሆነ አሳውቃለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መጽሐፉ በእውነት እኔ እንዲህ አሉ እያልኩ የምላችሁን ነገር በትክክል ይዟል ወይስ አልያዘም እያላችሁ ጥርጣሬ ውስጥም እንዳትወድቁ በማሰብ ራሱን መጽሐፉን ገጽ በገጽ ፎቶ እያነሣሁ ከዚህ ጋራ አያዝላችኋለሁ፡፡ እናንተም እነዚህን በፎቶው ላይ ያሉትን የመጽሐፉን ክፍሎች በማንበብ ሙሉውን የመጽሐፉን መንፈስ እንድትረዱት እያሳሰብሁ ስህተት ናቸው የምላቸውን ነጥቦች ግን ከመጻሕፍት አንጻር ያለውን ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ መልስ  እያስቀመጥሁ እሄዳለሁ፡፡ ስለዚህ በዚህ መልኩ ወደዛሬው ጽሑፌ ላምራ፡፡
“አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ምሥጢረ ሃይማኖት የተባለችውን መጽሐፈ ርትዕ እነሆ እንጽፋለን እንገልጻለን” ስለሚለው ነጥብ ስንመለከት፡፡ ይህ መጽሐፍ በመጀመሪያ “መጽሐፈ ርትዕ” ሊባል አይችልም፡፡ ምክንያቱም በሊቃውንቱ ሥም የሚነግድ ልክስክስ ነጋዴ ነውና፡፡ አንድም ይህ መጽሐፍ ስለርትዕት ተዋሕዶ ሃይማኖታችን የሚመሠክር የሚናገር የሚያስተምር ሳይሆን የካቶሊክ ቅርንጫፍ ስለሆነው “ወልድ በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” የሚል ኑፋቄን የተሞላ የክህደት መጽሐፍ ነው፡፡ አንድም ይህ መጽሐፍ ስለቅድስት ቤተክርስቲያናችን የሚናገር የሚያትት የሚተረጉም ሳይሆን በስሟ የሚነግድ ባለሁለት ሚዛን ነጋዴ ነው፡፡ አንድም ይህ መጽሐፍ ምእመናንን በቀደመችው ርትዕት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት የሚያጸና ሳይሆን ኑፋቄን በልቡናቸው የሚዘራ ክፉ ዲያብሎሳዊ ገበሬ ነው፡፡ ስለዚህ “መጽሐፈ ርትዕ” ሊባል የሚገባው እንዳልሆነ በዚህ እንረዳለን ማለት ነው፡፡
ከዚህ በመቀጠልም የሥላሴን አንድነት እና ሦስትነት በገባቸው መጠን ለማመስጠር እና ለማራቀቅ ሞክረዋል፡፡ “የአካላት ባሕርይ በሦስትነት የመለኮት ባሕርይ በአንድነት” የሚል ገጸ ንባብ አለ፡፡ ሥላሴን በባሕርይ አንድ ናቸው በአካላት ግን ሦስት ናቸው እንላለን፡፡ ይህ ማለት ግን አካላቸው ሦስት ስለሆነ ባሕርያቸውም ሦስት ሆኖ ይከፈላል ማለት አይደለም፡፡ በርግጥ ይህንን በፎቶው ላይ የምትመለከቱት ስለሆነ አልጽፈውም እኔ ግን አባቶቻችን ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ይህንን የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት እንዴት እንደሚሉት መጻፍ እፈልጋለሁ፡፡ እዚህ ላይ በመለኮት አንድ ስለሚሆኑበት ነገር እንመልከት እስኪ ታላቁ ሊቅ አለቃ ጌታው ኅሩይ ፍኖተ አግዚአብሔር ብለው ከጻፏት መጽሐፋቸው ላይ ወስጀ ልጻፍላችሁ፡፡ ሥላሴ በመለኮት አንድ መባላቸው በብዕል አንዱ ከአንዱ ሳይበልጥ አንዱም ከአንዱ ሳያንስ የሚተካከሉ ባለጸጎች፣ ብዕላቸው በየቤታቸው ሳለ በመተካከላቸው አንድ እንዲባሉ መለኮታቸው በየአካላቸው ሳለ በክብር ስለተካከሉበት ነው ማለት ይገባናልን? ብለው ቢጠይቁ መልሳችን አይገባም የሚል ይሆናል:: ሥላሴ በመለኮት አንድ መባላቸውስ፣ መለኮት እንደ አካላት ተከፍሎ ሳይኖርበት፣ በአንድነቱ ፀንቶ፣ አካላትን በተከፍሎ ሳሉ በሕልውና እያገናዘበ፣ አንድ ልብ፣ አንድ ቃል፣ አንድ እስትንፋስ ስላደረጋቸው ነው እንጂ በክብር ስላስተካከላቸው አይደለም:: መለኮት ከአካል ጋር ከሦስት የሚከፈልስ ከሆነ አንድ ልብ፣ አንድ ቃል፣ አንድ እስትንፋስ መሆን የለም:: ይህም ከሌለ በአብ ለባውያን፣ በወልድ ነባብያን፣ በመንፈስ ቅዱስ ሕያዋን መባል አይገኝም:: እንዲህም ከሆነ በአንደኛው አንቀጽ የተጠቀሰው ሃይማኖተ አበው ዘአቡሊዲስ “ወልድኒ ቃሎሙ ለአብ ወለመንፈስ ቅዱስ፣ መንፈስ ቅዱስኒ መንፈሶሙ ለአብ ወለወልድ፤ ወልድም ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው፣ መንፈስ ቅዱስም ለአብና ለወልድ እስትንፋሳቸው (ሕይወታቸው) ነው” ያለው ሐሰት ሆኖ በየራሳቸው ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ አላቸው በማለት እንደ ዮሐንስ ተዐቃቢ ዘጠኝ መለኮት ያሰኛል:: ዮሐንስ ተዐቃቢ ከዚህ ሌላ አልተናገረምና:: ሕልውናም እንዲያገናዝባቸው ሃይማኖተ አበው ምዕ ፴፱ ÷፰-፱፡፡ ጌታችንም እንዲህ ብሏል “ለግብርየ እመኑ ከመ ታእምሩ ወትጠይቁ ከመ አነ በአብ ወአብ ብየ ፤ በሥራዬ እመኑ ታውቁ ትረዱም ዘንድ እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ” ብሏልና ዮሐ ፲፣፴፰፡፡  ዳግመኛ “ኢተአምንሁ ከመ አነ በአብ ወአብ ብየ፣ ወዝኒ ቃል ዘአነ ነገርኩክሙ አኮ ዘእምኀቤየ ዘነበብኩ አላ አብ ዘሀሎ ብየ ውእቱ ይገብሮ ለዝንቱ ግብር ፤ አታምንምን እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ:: ይህ ለእናንተ የምነግራችሁ ነገር ከኔ ከራሴ የተናገርኩት አይደለም:: በእኔ ያለ እርሱ አብ ይህን ሥራ ይሠራዋል እንጂ” ብሎ ለፊልጶስ ነግሮታል ዮሐ ፲፬÷፲፡፡ ዮሐንስ ዘአንጾኪያም  “አንኮ ዘንተአመን በ፫ እደው በ፫ አማልክት ወኢ በ፫ መለኮት አላ ንትአመን በ፫ አካላት ወበ፫ ገጻት እንተ ፩ ባሕርየ መለኮት ፤መገናዘብ እንደሌላቸው እንደ ፫ ሰዎች አድርገን በሦስት ሰዎች፣ በሦስት አማልክት፣ በሦስት መለኮት የምናምን አይደለንም:: ባሕርየ መለኮት አንድ በሚያደርጋቸው በሦስት አካላት በሦስት ገጻት እናምናለን እንጂ” ብሏል ሃይማኖተ አበው ክፍል ፩ ምዕ ፻፲፬ ÷ ፮-፯፡፡ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ዮሐንስም “ንሕነ ንትአመን ከመ አብ ሕልው በወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፣ ወልድኒ ሕልው በአብ ወመንፈስ ቅዱስ፣ ወመንፈስ ቅዱሰኒ ሕልው በአብ ወወልድ አብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ሕልው እንደሆነ፣ ወልድ በአብና በመንፈስ ቅዱስ ሕልው እንደሆነ፣ መንፈስ ቅዱስም በአብና በወልድ ሕልው እንደሆነ እኛ እናምናለን” ብሏል:: (ሃይማኖተ አበው ክፍል ፯ ምዕ ፺ ÷ ፲፩፡፡ ዲዮናስዮስም መለኮትን እንደ አካላት ብንለይ፣ ሰይጣናዊ እምነትን እናምናለን ማለቱ፣ መለኮትን ሦስት ብሎ፣ ሦስትነት ያለው አኃዝ በመለኮት ከተነገረ፣ መንገዱ የዮሐንስ ተዐቃቢ ነውና እምነቱ ሰይጣናዊ መሆኑን ሲያስረዳ ነው:: መጻሕፍት ሁሉ “ይትወሐዱ በመለኮት” እያሉ፣ ለአካላት ማስረጃ ያደርጉታል እንጂ መለኮትን ሦስት ብለው የሚከፍሉበት አንቀጽ አይገኝም::

ሌላው የመለኮት አንድነት አካላትን እንዳይጠቀልል፣ የአካላትም ሦስትነት መለኮትን እንዳይከፍል የሚያስረዳ ነገር የአንጾኪያው ሊቀ ዻዻሳት አትናቴዎስ ፵፱ኛ እንዲህ ሲል ተናገሯል “ወሶበሂ ንቤ አሐዱ እግዚአብሔር፣ ወ፩ዱ ሕላዌ፣ ወ ፩ዱ መለኮት፣ አኮ ዘያበጥል ላዕሌነ ዝንቱ ተስምዮተ ፫ አካላት:: እስመ ለለ፩ እም ፫ አካላት ሃላውያን በበአካላቲሆሙ:: ወመለኮትሂ ሕልው በሕላዌሁ፣ ወኢይትፈለጥ ለከዊነ ፫ መለኮት፣ እስመ ቅድስት ሥላሴ ፩ እሙንቱ በተዋሕዶ እንበለ ፍልጠትትርጓሜ ፤አንድ እግዚአብሔር አንድ ሕላዌ አንድ መለኮት ብንል፣ አንድ ማለታችን ፫ አካላት ማለትን የሚያፈርስብን አይደለም:: ሦስት አካላት ማለታችንም መለኮትን ከሦስት የሚከፍልብን አይደለም:: ከሦስቱም አካላት አንዱም አንዱ በየአካላቸው ፀንተው የሚኖሩ ናቸውና፣ መለኮትም በአንድነቱ ፀንቶ የሚኖር ነው እንጂ:: ሦስት መለኮት ለመሆን የሚከፈል አይደለም፣ ቅድስት ሥላሴ ያለመለያየት በተዋሕዶ አንድ ናቸውና” ሃይማኖተ አበው ምዕ ፻፮ ÷ ፰-፱ ብሏል::
=====================================
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት
#comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡

No comments:

Post a Comment