Wednesday, July 12, 2017

የክህደት ቁንጮው ሚሥጢረ ሃይማኖት--- ክፍል ፭



ሐምሌ 5/2009 ዓ.ም



ሚሥጢረ ሃይማኖት የተሰኘው የቅባቶች ድርሰት
“ሚሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊ” የተሰኘውን የቅብአት መጽሐፍ እያገላበጥን ነጥብ በነጥብ እየተመለከትን ነው ያለነው፡፡ እዚህ ላይ ከውይይት እና በማስረጃ ተደግፎ ከመቃወም ባለፈ ለስድብ እና ለዛቻ አስተያየት ሊሰጥ የሚመጣን ማንኛውንም አካል የማናስተናግድ መሆኑን ከወዲሁ እንገልጻለን፡፡ ከመጽሐፉ ስገለብጥ ማለትም “---” ምልክት መካከል አድርጌ የምጽፈው የፊደል ግድፈቱንም እንዳለ ስለምወስደው የፊደል የቃል ስህተት ብታገኙ ሙሉ በሙሉ የመጽሐፉ እንደሆነ አሳውቃለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መጽሐፉ በእውነት እኔ እንዲህ አሉ እያልኩ የምላችሁን ነገር በትክክል ይዟል ወይስ አልያዘም እያላችሁ ጥርጣሬ ውስጥም እንዳትወድቁ በማሰብ ራሱን መጽሐፉን ገጽ በገጽ ፎቶ እያነሣሁ ከዚህ ጋራ አያይዝላችኋለሁ፡፡ እናንተም እነዚህን በፎቶው ላይ ያሉትን የመጽሐፉን ክፍሎች በማንበብ ሙሉውን የመጽሐፉን መንፈስ እንድትረዱት እያሳሰብሁ ስህተት ናቸው የምላቸውን ነጥቦች ግን በተቻለኝ መጠን ከመጻሕፍት አንጻር ያለውን ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ መልስ  እያስቀመጥሁ እሄዳለሁ፡፡ ይህ ማለት ግን እኔ አዋቂ ነኝ ምሥጢር ጠንቃቂ ነኝ ማለቴ እንዳልሆነ ልብ በሉልኝ! ስለዚህ በዚህ መልኩ ወደዛሬው ጽሑፌ ላምራ፡፡
፨፨፨፨******************************************************************************፨፨፨፨

ሚሥጢረ ሃይማኖት የተሰኘው የቅባቶች ድርሰት
ዛሬ ደግሞ በጣም የተዘበራረቀ ነገር ነው የማቀርብላችሁ፡፡ ምክንያቱም ቅባቶች ዝብርቅርቅ ብለው በዚህ መጽሐፍ ተመልክቻቸዋለሁና ነው፡፡ እኛ የምናምነው አብን ወላዲ ወልድን ተወላዲ መንፈስ ቅዱስን ሰራጺ ብለን ነው ቅባቶች ግን መንፈስ ቅዱስን ወላዲ እና አስራጺ ሲያደርጉት ገጽ 11 ላይ ይታያል፡፡ “መንፈስ ቅዱስም በአካሉ ቋሚ ሁኖ ሳለ ከልብ አብ በአካሉ ቋሚ ሁኖ ሳለ በወልድ አካል ልብ ሁኖ የወልድን ቃል ይወልደዋል፡፡ የመንፈስ ቅዱስን እስትንፋስ ያሰርፀዋል፡፡ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ አካል ልብ ሁኖ ወልድን ይወልደዋል መንፈስቅዱስን ያሰርጸዋል” በማለት ከየት እንደመጣ የማይታወቅ ተረት ተረት መዝገብ ውስጥ እንኳ ያልሰፈረ አዲስ የልብወለድ ደራስያን ሊያስባለቸው እንኳ የማይችል የተቆራረጠ ሃሳብ ጽፈዋል፡፡ ይህ በግልጽ እንደሚያስረዳን “መንፈስ ቅዱስ ወልድን ይወልደዋል ራሱን መንፈስ ቅዱስን ያሰርጸዋል” ማለታቸው ነው፡፡ በየትኛው ሊቅ በየትኛው መምህር ነው ይህንን የተማሩት? በእርግጥ “ክርስቲያን ሆይ ስማ ልብ አድርግ የቤተክርስቲያን መምህራን እና ሊቃውንት ያደረጉትን  አደርጋለሁ ያስተማሩትን አስተምራለሁ ባልክ ጊዜ የዝንጀሮ ጎዳና ተከተልክ ወደ ትልቅ ገድ(ደ)ልም ያደርስሃል” ብለው አስቀድመው ስለተናገሩ ለእነርሱ መምህራን ያስተማሩትን ትምህርት እና ሃይማኖት መጠየቅ እንደ ጅልነት የሚያስቆጥር ተግባር ስለሆነ እንድትታዘቡ ያህል ይህል ካልኩ ወደ ቀጣዩ ላምራ፡፡





ሚሥጢረ ሃይማኖት የተሰኘው የቅባቶች ድርሰት
ከብዙ ስሕተት የሚያደርስ የሥላሴ የስማቸውን ምሥጢር ለይቶ አለማወቅ ነው:: በባሕርይ የሚጠሩበት ስም አለ:: በአካል የሚጠሩበት ስም አለ፣ በግብር የሚጠሩበት ስም አለ:: በባሕርይ የሚጠሩበትን ስም ለአካልና ለግብር፣ በአካል የሚጠሩበትን ስም ለባሕርይና ለግብር፣ በግብር የሚጠሩበትን ስም ለባሕርይና ለአካል ሰጥተው ሲናገሩ የአንድነታቸው፣ የሦስትነታቸው ምሥጢር ፈራሽ ሆኖ ይገኛል:: ስለዚህ ጠንቅቆ አስተውሎ መመልከት ይገባል:: አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ መባል የአካል ስም ነው:: አብ ማለት ጥንት መሠረት መገኛ ማለት ነው:: ጥንት መሠረት መገኛ በመሆንም ወላዲ አሥራጺ ይባላል:: ጥንት መሠረት አስገኝ በመሆን ወላዲ አሥራጺ ተባለ እንጅ ወላዲ አሥራጺ በመሆኑ አብ የተባለ አይደለም:: ይህንም ለመረዳት ጎርጎርዮስ ፲፰ኛ የተናገረውን መመልከት ነው:: “አእምር ኲሎ ግብረ፣ እም፫ ግብራት፣ ዘውእቶሙ አስማት፣ ወውእቱ ፍጥረት ወስም ወዘመድ ዘይተበሀል ሰብእ ወገብር ወመጋቢ:: ሰብእሰ በእንተ ፍጥረተ ጠባይዒሁ ወገብርኒ በእንተ ግብርናቲሁ ወመጋቢኒ በእንተ ስም ዘተሠይመ:: ወናሁ ንቤ ካዕበ በእንተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ወአኮ እሉ አስማት ዘቦኡ ላዕሌሆሙ ድኀረ አላ እሙንቱ አካላት:: ወብሂለ ሰብእሂ አኮ ውእቱ ስም ዳዕሙ ውእቱ ፍጥረቱ:: እስመ ለኩሎሙ ሰብእ ቦሙ ፩ ስም በበይናቲሆሙ ለለ፩ እምኔሆሙ:: እሉ እሙንቱ አዳም አብርሃም ይስሐቅ ወያዕቆብ:: ወአቃኒመ እግዚአብሔርሰ እሙንቱ አስማት ወአስማትኒ እሙንቱ አቃኒም እስመ ትርጓሜሁ ለአቃኒም፣ አካላት ጽኑዓን ወቀዋምያን ፍጹማነ ገጽ ወመልክዕ ብሂል:: ወሥሉስ ቅዱስ ይሰመዩ አስማተ ጽኑዐነ ፤በ፫ አካላት ያለውን ግብር ሁሉ በሦስት ግብራት እወቅ እኒህም ፍጥረት፣ ስም፣ ዘመድ የሚባሉ ስሞች ናቸው:: ፍጥረት የተባለው ሰብእ (ሰው) መባል ነው:: ስም የተባለው ገብር (አገልጋይ) መባል ነው:: ዘመድ የተባለውም መጋቢ መባል ነው:: ሰብእ መባሉ ስለ ባሕርዩ መገኘት ነው:: ገብር መባሉም ተገዥ ስለሆነ ነው:: መጋቢ መባሉ ስለተሾመ ነው:: ሰው ስለ አካሉ መገኘት “ሰብእ” እንደተባለ ስለ አካላቸው ሕላዌ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ይባላሉ:: ስለ ተገዛ ገብር፣ ስለ ተሾመም “መጋቢ” እንዲባል ስለ ወለደ ወላዲ፣ ስለተወለደ ተወላዲ፣ ስለ ሠረጸ ሠራጺ እንላለን:: እኒህም ስሞች አካላት ሲኖሩ የኖሩ ናቸው እንጂ ኑረው ኑረው ኋላ የተጠሩባቸው አይደለም:: ሰብእ መባልም በተፈጥሮው የወጣ ስም ነው እንጂ ኋላ የወጣ ስም አይደለም:: ለሰዎች ሁሉ እያንዳንዳቸው የሚጠሩበት ኋላ የወጣላቸው ስም አለና:: ይኸውም አዳም፣ አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ እንዳለው ነው:: የእግዚአብሔር ዓቃኒም ግን አስማት ናቸው:: አስማትም ዓቃኒም ናቸው:: የዓቃኒም ትርጓሜ በመልክ፣ በገጽ፣ ፍጹማን ሆነው፣ ፀንተው የሚኖሩ አካላት ማለት ነውና:: ልዩ ሦስት የሚሆኑ አካላትም ፀንተው በሚኖሩ በነዚህ ስሞች ይጠራሉ” ብሏል  ጎርጎርዮስ ገባሬ ተአምራት ሃ.አበው ምዕ ፲፫ ክፍል ፩ ቁ. ፬-፮


ሚሥጢረ ሃይማኖት የተሰኘው የቅባቶች ድርሰት
ቅባቶች ስለወልድ በተናገሩት ላይ የእኛ ሊቃውንት ምን እንደሚያስተምሩ በአጭሩ ላስቀምጥላችሁ፡፡ ወልድ ማለት የተረክቦ ስሙ እንደሆነ ይናገራል (ተረክቦ ማለት መገኘት ማለት ነው) ወልድ ማለት አካሉ በቃልነቱ ከዊን ተድኀሮ  ሳይኖርበት (ወደ ኋላ ሳይቀር) አብን አህሎ መስሎ ከአብ አካል በመገኘቱ የሚጠራበት የተረክቦ ስሙ ነው:: ተረክቦውም ተፈልጦ ሳይኖርበት በሕልውና እያለ ነው:: የነፍስ ቃሏ ከልብነቷ ተገኝቶ ሳይለይ አካሏ ሕልው ሆኖ እንደሚኖር ማነጻጸር ነው:: ቄርሎስ በእስተጉቡእ “ወልድ ዋሕድ በሕላዌሁ ዘእምኀበ እግዚአብሔር አብ ይሰመይ ቃለ፣ እስመ ፩ ውእቱ ተወለደ እም ፩ አብ፤ ወልድ ዋሕድ ከእግዚአብሔር አብ ተወልዶ በአብ ሕልው ሆኖ በሚኖርበት ባሕርዩ ቃል ይባላል:: “አንዱ እርሱ ከአንድ አብ ተወልዷልና” ብሏል:: ተወላዲ ማለት ግን በተከፍሎ የሚጠራበት የግብር ስሙ ነው:: ወልድ ማለትና ተወላዲ ማለት በግሥ አንቀጽ መልክ ፊደሉ አንድ ሲመስል፣ የምሥጢር ልዩነት እንዳለው አሁን የተናገርነውን የተረክቦንና የተከፍሎን ምሥጢር ጠንቅቆ ማስተዋል ነው:: ተረክቦ ያልነውም የአካሉ ሕላዌ ከአብ አካል የተለየ ሆኖ በፍጹም ገጽና በፍጹም መልክ መታወቁ ነው እንጂ፤ እግዚአበሔር የተገኘበት ጊዜ አይደለም:: ሱኑትዩስ  “ወኢይትረከብ ሀልዎቱ እምኃበ ወኢምንትኒ ፤አኗኗሩ ከምንም ከምን አይገኝም” እንዳለ:: “ከምንም ተገኘ አይባልም” ሃይማኖተ አበው ምዕ ፻፲ ክፍል ፪ ቁ. ፬ ሠለስቱ ምዕትም በቅዳሴ “ኢይክል መኑሂ ይባዕ ማዕከለ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ከመ ያዕምር ዘከመ እፎ ህላዌሁ፣ ወለዶ አብ ለወልዱ ኢይትበሀል ዘጊዜ ወበዘከመዝ መዋዕል ወለዶ፤ ኢይትአመር ልደቱ እም አብ እስመ ዕፁብ ውእቱ፣ ወኢይትአወቅ ህላዌሁ እስመ ስውር ውእቱ፤ ማንም ማን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ መካከል ሊገባ አይችልም:: አኗኗሩ እንደምንም እንደሆነ ያውቅ ዘንድ፣ አብ ልጁን ወልዶታል:: ነገር ግን አብ ልጁን በዚህ ጊዜ እንዲህም ባለ ዘመን ወለደው አይባልም፤ ከአብ መወለዱ አይመረመርም፣ የሚያስጨንቅ ነውና፤ አኗኗሩ አይታወቅም የተሰወረ ነውና” እንዲሉ:: ተከፍሎም በመለየት እንደሆነ የሚያስረዳ ሊቃውንት በብዙ አንቀጽ ገልጸዋል “ተጋብኦ በተከፍሎ ወተከፍሎ በተጋብኦ ፤አንድነት በመለየት መለየትም በአንድነት አለ” ሃይማኖተ አበው ምዕ ፻፮÷ ፫

ሌላው ገጽ 12 ላይ የምትመለከቱት አስቂኝ ነገር ነው፡፡ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ሲያበሥራት ምን እንዳላት ሲገልጹ “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ሆነው እንደሚመጡ” አበሠራት በማለት ደፍረው ይናገራሉ፡፡ ይህን የመልአኩን ብሥራት የምናገኘው  በሉቃ 1÷26-38 ባለው መጽሐፍ ክፍል ነው፡፡ ይህንን ቃል ከምጽፈው እናንተው ተመልከቱት እነርሱም ከጻፉት ጋራ አገናዝቡት የት ላይ ልብወለድ ፈጠራ እንደጀመሩ ግልጽ ይሆንላችኋል፡፡ የቻላችሁ ደግሞ አንድምታ ወንጌሉን ተመልከቱት እስኪ “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ሆነው እንደሚመጡ ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ነገራት” የሚል ቃል ካገኛችሁ አንገቴን ቁረጡኝ፡፡ በሞቴ! ይህን ከላይ የሰጠኋችሁን የሉቃስ ወንጌል ግን ሳታነቡት እንዳታልፉ ያንን ሳታነቡ ካለፋችሁ በጣም አዝንባችኋለሁ፡፡ ወንጌል የሌለው ሰው ደግሞ ይዌድስዋ መላእክትን ያንብበው እስኪ፡፡

ገጽ 13 ላይ ከላይ የተመለከትነውን የመልአኩን ብሥራት ሲደመድሙ “ቃል በድንግል ማርያም ማደሩ መላኩ ገብርኤል አስቀድሞ እንደነገራት አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ሆነው ወደ ድንግል ማርያም መጡ” ይላሉ፡፡ እኛ ይህንን ተረት ተረት የምንሰማበት ጆሮ የለንም ቅባቶች፡፡ እኛ የምናውቀው “ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ ይደረግልኝ” ስትለው ያንጊዜ አካላዊ ቃል ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷም ነፍስን ነሥቶ ያንጊዜ በተዋሕዶ በድንግል ማርያም ማኅጸን አደረ (ተጸነሰ) ነው፡፡ ከዚያ ውጭ “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ሆነው መጡ” የሚል ትምህርት የለንም፡፡ ቀጥለውም “በመንፈስ ቅዱስ ቅብዕነት በአብ ቀባዒነት የቃል አካል ከነፍስ እና ከሥጋ አካል ጋር በመዋሐዱ እና በመቀባቱ የባሕርይ ልጅ ሆነ” ይላሉ፡፡ ልብ በሉ! ቀባዒ ማለት አክባሪ፣ ተቀባዒ ማለት ከባሪ/ተከባሪ፣ ቅብዕ ማለት ደግሞ ክብር ማለት ነው፡፡ ታዲያ አብ አክባሪ ወልድ ከባሪ/ተከባሪ መንፈስ ቅዱስ ክብር የሚሆነው በምን ዓይነት አስተሳሰብ ነው፡፡ በመለኮት አንድ ናቸው ብለን የምናምን ከሆነ የአብ መለኮት በመንፈስ ቅዱስ መለኮት ክብርነት የወልድን መለኮት  እንዴት ነው አከበረው ሊባል የሚችለው? በእርግጥ እነርሱ የወልድ እና የመንፈስ ቅዱስ መለኮታቸው አብ ነው ስለሚሉ ይህንን ቢሉ ላይፈረድባቸው ይችላል፡፡ በመለኮት አንድ ናቸው በማለት ፈንታ መለኮታቸው አብ ነው የሚለው ፍልስፍናቸው የወልድን መለኮት በመንፈስ ቅዱስ መለኮት ቅብአትነት የአብ መለኮት አከበረው እንዲሉ የምንፍቅና በሩን ከፍቶላቸዋል፡፡ እኔም ይህንን ደፍሬ በመናገሬ ይቅር ይበለኝ እናንተም ስላነበባችሁት ይቅር ይበላችሁ ቅባቶችን ግን ዓይነ ልቡናቸውን ይግለጥላቸው እና የተሠወረውን መለኮታዊ ጥበብ እንዲረዱ ይፍቀድላቸው እላለሁ፡፡ በምን መሥፈርት ነው እንደነገሥታት በመቀባባት የባሕርይ ልጅ መሆን የሚቻለው ያማ ቢሆን ተቀብተው የነገሡት እነ ሳዖል፣ እነ ዳዊት፣ እነ ሰሎሞን እነዚህ ሁሉ የባሕርይ ልጅነትን ባገኙም ነበር፡፡ ስለዚህ ይኼ ተራ ፍልስፍና ስለሆነ ወደ እምነት ጎዳና እንዲመጡ እንመክራቸዋለን፡፡ ቅዱስ ገብርኤል “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ሆነው ወደ ወደአንች ይመጣሉ” ብሎ ነግሯት ቢሆን ኖሮ ሊቁ ቄርሎስ  ስምዐት 124÷34 “ወካዕበ ይቤ እስመ ክርስቶስ ኢተቀብዐ በእንተ መፍቅድ ዘቦቱ አላ ለሊሁ ቀባዒ …ዳግመኛ ክርስቶስስ ክብር መሻት ኖሮበት አልከበረም እርሱ ራሱ አክባሪ ነው እንጅ ሰው ቢኾንም በባህርይ ክብሩ ከበረ..” ባላለም ነበር፡፡ ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ሲያበሥራት መንፈስ ቅዱስ ባንቺ ላይ ይመጣል የአብም ኃይሉ ይጋርድሻል ካንች የሚወለደውም ቅዱስ ነው የልዑል የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል ብሎ ሦስቱም አካላት በማኅጸነ ማርያም እንደ አደሩ ተናግሯል፡፡ ማደራቸውም አብ ለአጽንዖ መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ ወልድ ለለቢሰ ሥጋ ነው እንጅ ሦስቱ ኹሉ ለለቢሰ ሥጋ ያደሩ አይምሰልህ፡፡ ስለዚህ አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ሆነው ወዳንች ይመጣሉ ያለ ገብርኤል የለንም አናውቅምም፡፡ እስላሞች ለመሐመድ እስልምናን ያስተማረው ቅዱስ ገብርኤል ነው በማለት ራሳቸውን እንደሚያታልሉ ሁሉ ቅባቶችም በቅዱስ ገብርኤል ስም አዲስ ፍልስፍና መጀመራቸውን ልብ ይሏል፡፡


“የጌቶች ጌታ የካህናት አለቃ የነቢያት ርዕስ መሆን ይህ ሁሉ አንድ ጊዜ እንደ ዓይን ጥቅሻ  ሆነ” ይላሉ፡፡ የዓይን ጥቅሻ ማለት በጣም ትንሽ የሆነች የጊዜ ክፍል ናት፡፡ የዓይን ጥቅሻ ማለት ከቅጽበት ከፍ ያለች ከሰከንድ ደግሞ ያነሰች ጊዜ ናት፡፡ ስለዚህ የጌቶች ጌታ በመሆን እና የካህናት አለቃ በመሆን የነቢያት ርዕስም በመሆን መካከል የዓይን ጥቅሻ ያህል ጊዜ አለ፡፡ ይህ ማለት ሲዋሐድ ሲቀባ፣ ሰው አምላክ ሲሆን አምላክም ሰው ሲሆን፣ እንደዓይን ጥቅሻ አንድ ጊዜ ነው የሚሉ በመሆናቸው ከቅጽበት ከፍ ከሰከንድ ዝቅ ያለች ትንሽ ጊዜ ያህል አምላክነቱን አጥቷል በኋላ እንደዓይን ጥቅሻ በመንፈስ ቅዱስ ቅብዕነት አምላክ ሆነ ከበረ እንደ አብ እንደ መንፈስ ቅዱስ ገዛ አዘዘ የሚል ምንፍቅና ውስጥ የተቆለቆሉ ናቸው፡፡

ከዚህ በበለጠ ደግሞ መጽሐፉን ገጽ በገጽ እያነበባችሁ ከመምህራን እየተረዳችሁ የቅብአትን ምንፍቅና ለሁሉም እንድታጋልጡ በእግዚአብሔር አምላክ ስም እጠይቃለሁ፡፡
=====================================
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት
#comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡

No comments:

Post a Comment