Friday, October 6, 2017

✍✝ ባለን ሳንጠቀም የሌለንን ልመና! ✝✍



፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ላይክ ላይክ ላይክ
facebook.com/beyenemelkamuA
facebook.com/melkamubeyeneB
ላይክ ላይክ ላይክ
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠

ብዙ ነገር በአንተ እጅ አለ ነገር ግን ያንተ ስለሆነ አታስተውለውም፡፡ ፈጣሪ ላንተ ብቻ የሰጠህ ልዩ ጸጋ ልዩ ስጦታ አለህ ነገር ግን አልተጠቀምህበትም፡፡ አንተ በፈጣሪ ዘንድ አንድ ተብለህ የተቆጠርህ ልዩ አድርጎ የፈጠረህ ነህ፡፡ እርሱ ፈጥሮሃልና አይረሳህም ከራስ ጸጉርህ እስከ እግር ጥፍርህ ሁለመናህን ያውቅሃል፡፡ ጸጉርህን ቆጥሮ ሰፍሮ ለክቶ አንተ የምትባልን ፍጡር ፈጥሮሃልና ፈጣሪ አይዘነጋህም፡፡ አንተ ግን በአንጻሩ ተፈጥረህ ስለመገኘትህ እንኳ አታስተውልም፡፡ ፈጣሪህ ማን እንደሆነ እንኳ ማስተዋል ተስኖሃል፡፡ ዛሬ ጉልበትህን ነገ ሃብትህን ዛሬ ውበትህን ነገ እውቀትህን ታመልካለህ፡፡ እርሱ ፈጣሪህ ግን የእጁ ሥራ ነህና አይረሳህም አንተ ግን ፈጽመህ ዘንግተኸዋል፡፡

ልታይበት ዓይን ሰጠህ ልትሰማበት ጆሮ ሰጠህ፡፡ ልትሄድበት እግር ሰጠህ ልትዳስስበት እጅ ሰጠህ፡፡ ልትናገርበት ልሳን ሰጠህ ልታሸትበት አፍንጫ ሰጠህ፡፡ እነዚህን ሲሰጥህ ደግሞ ነጠላ ነጠላ አድርጎ አይደለም እጥፍ እጥፍ አድርጎ ነው እንጅ፡፡ ፈጣሪ በጣም እንደሚያስብልህ ለመረዳት የእነዚህን ጥንድ መሆን አስተውል፡፡ አንድ ዓይን ብቻ ቢኖርህ ኖሮ በሆነ አጋጣሚ አንዷ ስትደክም ማየት በተቸገርህ ነበር ነገር ግን አንዱ አንዱን ይረዳ ያግዝ ዘንድ ይኼው ጥንድ ጥንድ አድርጎልሃል፡፡ እስኪ አንድ እግር አንድ እጅ አንድ ዓይን አንድ ጆሮ አንድ አፍንጫ ወዘተ… ብቻ እንዳለህ አድርገህ ራስህን ሳለው ምን ትመስላለህ? ፈጣሪ እኮ ሁሉን ሲፈጥር ውብ አድርጎ ነው አየህ፡፡ ምላስህን ግን አንድ ብቻ አደረገው ሁለት ምላስ ቢኖርህ ኖሮ ዓለም በምላስ ብዛት ያለዕድሜዋ ተቃጥላ በጠፋች ነበር፡፡ በአንድ ምላስስ ተቸግረን የለም እንዴ እንኳን በሁለት ምላስ፡፡ ፈጣሪ ሁሉን ነገር እርሱ ባወቀ አሳምሮ ፍጥረታትን ሁሉ ፈጥሯል፡፡

ወደ ርእሰ ጉዳያችን እንግባ፡፡ እኛ ብዙ ነገር አለን ነገር ግን አልተጠቀምንበትም፡፡ ፈጣሪያችንንም ከማመስገን ይልቅ ማማረር ስለሚቀናን ባለን ነገር ሳናመሰግን በሌለን ነገር ላይ ስናማርር እንስተዋላለን፡፡ መጀመሪያ እስኪ ያለህን ነገር በአግባቡ ተጠቀምበት፡፡ ዓይን እያለን ሁሉን በምናይበት ወቅት ፈጣሪያችንን ያላመሰገንን ሰዎች ዓይናችን ሲጠፋ ለምን እናማርራለን? ጆሮ እያለን ሁሉን በምንሰማበት ጊዜ ፈጣሪያችንን ያላመሰገንን ጆሯችን መስማት ሲሳነው ለምን እናማርራለን? እግር እያለን ከፈለግነው ቦታ ሮጠን መድረስ በምንችልበት ጊዜ ፈጣሪን ያላመሰገንን ሰዎች እግራችን መራመድ ሲሳነው ለምን እናማርራለን? እጅ እያለን ሁሉን አጥብቀን መያዝ በምንችልበት ጊዜ ፈጣሪን ያላመሰገንን ሰዎች እጃችን ሲቆረጥ ለምን እናማርራለን? አያችሁ የእኛን ነገር እኛ እኮ ባለን ነገር ሳናመሰግን በሌለን ነገር የምናማርር ሰዎች ነን፡፡
አንተ ጥሩ ሰው መሆን ከፈለግህ በመጀመሪያ ባንተ ዘንድ ያለውን ነገር ለይተህ እወቅ ከዚያም ስለነዚያ ነገሮች ፈጣሪህን አመስግነው፡፡ ፈጣሪህን የምታመሰግነው ስላለህ ብቻ አይደለም ስለሌለህም ጭምር እንጅ፡፡ ስለሌለህ ነገር ለማመስገን ግን ባለህ ነገር ማመስገንን መለማመድ አለብህ፡፡ “በቅርብ ያለ ጸበል…” እንደሚባለው ባንተ ዘንድ ስላለው ነገር ማመስገን እንዳትችል ከፈጣሪህ ሊለይህ የሚፈልገውን ጠላት ታገለው፡፡ አንተ እኮ ሃብታም ነህ እጅ አለህ እግር አለህ ዓይን አለህ ጆሮ አለህ ግን አልተጠቀምህበትም፡፡ ይህ ሁሉ እያለህ ሠርተህ ማደግ እየቻልህ ከአልጋ ላይ ተኝተህ የማይፈታ ህልም ስትቃዥ ማደርህ ለምን ነው? ያለህን ሳትጠቀምበት የሌለህን ስትለምን መመልከት በራሱ አሳዛኝ ነው፡፡ ሁለት ዓይን ኖሮህ መጽሐፍ ያልተመለከትህ ሰው ስለእውቀት በፈጣሪህ ፊት ልመና ብታቀርብ ከንቱ ልመና እንዳይሆንብህ ማሰብ አለብህ ምክንያቱም ዓይንህን አልተጠቀምህበትማ፡፡ ቤት አልሠራሁም፣ ሀብት አላፈራሁም፣ ትዳር አልመሠረትሁም፣ ልጅ አልወለድሁም፣ ትምህርት አልተማርሁም ወዘተ እያልህ ትጨነቃለህ ነገር ግን አሁን ባለህበት ሁኔታ ላይ ፈጣሪህን ለማመስገን ምን እያደረግህ ነው?
ባለን ሳንጠቀም የሌለንን እንድንለምን የሚያደርገን ክፉ ጠላት ያለ ይመስለኛል፡፡ የሞቀው ሰው ብርድን ይለምናል፤ የበረደው ሰው ደግሞ ሙቀትን ይለምናል፡፡ አንዱ ራሱም ቢሆን በረደኝ ሙቀት አድለኝ ብሎ ከፈጣሪው ለምኖ ሙቀት ሲሰጠው ነገር ዓለሙን ይዘነጋውና ብርድ ይለምናል፡፡ ገንዘብ ባገኝ እኮ ቤተክርስቲያንን እረዳ ነበር የሚል ሰው ገንዘብ ሲያገኝ የቤተክርስቲያኗ የወንድ እና የሴት መግቢያ በሩን ይዘነጋዋል፡፡ አንድ ብር እያለህ ዐሥር ሳንቲም መስጠት ካልቻልህ ሚሊየነር ስትሆን በሺዎች የሚቆጠር ብር ትሰጣለህ ብሎ ማንም አይገምትህም፡፡ ስለዚህ በመጀመሪያ ባለህ ነገር አመስግን ባለህ ነገር ሥራ ከዚያም የሌለህን ነገር ፈጣሪ እንዲሰጥህ ለምን፡፡

፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝
© መልካሙ በየነ
መስከረም ፳፫ / ፳፻፲ ዓ.ም
መርጡለ ማርያም፣ ኢትዮጵያ
✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት #comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡
✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝

No comments:

Post a Comment