© መልካሙ በየነ
ግንቦት
22/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ተጽሕፈ እም አሐዱ ሊቅ ኢትዮጵያዊ
ኅሩይ ወመፈክራዊ
ጌታው አለቃ ኅሩይ
ኃይልና ክሂል ሥልጣንም በአካል የማይከፈሉ አንድ እንደሆኑ ይናገራል፡፡
ጥያቄ:- የሥላሴ ኃይል፣
ክሂል፣ ሥልጣን፣ በአካል ከሦስት ይከፈላል ማለት ይገባልን? መልስ:- አይገባም፤ ኃይል፣ ክሂል፣ ሥልጣን፣ በአካል የሚከፈል ሦስት
ከሆነ፣ አእምሮ ንባብ ሕይወት የሌለው፤ ኃይል፣ ክሂል፣ ሥልጣን የለውምና፤ አእምሮም ንባብም ሕይወትም ከሦስት ይከፈላል ያሰኛልና፤
ኃይል፣ ክሂል፣ ሥልጣን የሚባል፤ አእምሮ ንባብ ሕይወት እንደሆነ፣ “ንግበር ሰብአ በአርአያነ ወበአምሳሊነ” ዘፍ ፩÷፳፮ በተባለው በሰው እንዲታወቅ፤ ከየመጻሕፍቱ እያመጣን በብዙ አንቀጽ እናስረዳለን::
ንባብ:- “እግዚአብሔር ገብሮ ለእጓለ እመሕያው ርቱዕ፤ ወገብረ ሕላዌሁ ከሀሌ” ትርጉም:- “እግዚአብሔር ሰውን የቀና አድርጎ፤
ባሕርዩንም አዋቂ አድርጎ ፈጠረው” ጥበበ ሰሎሞን ፪÷፳፫ ብሏል:: ይህንንም ንባብ ዮሐንስ ኤጲስ ቆጶስ ዘኢየሩሳሌም ሲተረጉም ፳፬ኛ
ንባብ:- “ይብል ዘንተ ከመ ቦቱ ሥልጣን በርእሱ ባሕቲቱ፤ ወይክል ያቅም ትሩፋተ” ትርጉም:- “ከሃሊ ማለትን በራሱ ብቻ ሥልጣን
እንዳለው፣ ትሩፋቱን መፈጸም እንዲቻለው ሲያስረዳ ይህን ተናገረ ብሏል::” (ክፍል ፩ ብቻ) ሃ.አበው ምዕ ፶፪÷፲፭ ማቴዎስም በወንጌል
ጌታችን ለሐዋርያት ምሳሌ መስሎ ሲያስተምራቸው ሰምተው ቤተ አይሁድ እንዳደነቁ ሲጽፍ:- ንባብ:- “እምአይቴ ሎቱ ዝንቱ ኩሉ ጥበብ
ወኃይል” ትርጉም:- “ለእርሱ ከወዴት ተሰጠው፤ ይህ ሁሉ ጥበብ ኃይልስ አሉ” አለ:: ማቴ ፲፫÷፶፬ ኃይል ያለውን ንባብ አእምሮም
እንደሆነ ያስተውሏል:: ቅዱስ ጳውሎስም ንባብ፦ “ወብነ ዝንቱ መዝገብ ውስተ ንዋየ ልሕኩት፤ ከመ ይኩን ዕበየ ኃይል ዘእምኀበ እግዚአብሔር፤
ወአኮ ዘእምኀቤነ” ትርጉም፦ “ይህም መዝገብ /ነፍስ/ በሸክላ ዕቃ አለን:: የኃይል ታላቅነት ከእኛ ያይደለ ከእግዚአብሔር ይሆን
ዘንድ” አለ:: (፪ኛቆሮ ፬÷፯-፰) የዚህም ምሥጢሩ ከእግዚአብሔር የተገኘ ብዙ እውቀት ይሰጠን ዘንድ፣ በሥጋችን ነፍስ አለች ማለት
ነው:: ኃይል ያለው ለነፍስ የተሰጠ እውቀት መሆኑን ያስተውሏል:: አሞንዮስና አውሳብዮስም፤ የአዳምን ተፈጥሮ ሲናገሩ፣ በመቅድመ
ወንጌል ንባብ፦ “ወተፈጸመ ፍጥረቱ ለአዳም በዝንቱ ዘቦ ውስቴቱ ፫ ኃይል፤ ኃይለ ዘርዕ፤ ኃይለ እንስሳ፤ ወኃይለ ንባብ፤ ወኃይል
እንስሳዊት ህውክት ይእቲ ዘበስምረት ወይእቲ ባ እምነ አእምሮ ወበዘባቲ ኃይል ዘይእቲ እንስሳዊት ወውስቴታ ይትረከብ ነጽሮ ወሰሚዕ”
ትርጉም፦ “የአዳም ተፈጥሮ ኃይለ ዘርእ፣ ኃይለ እንስሳ፣ ኃይለ ንባብ ባለው በዚህ በሦስቱ ኃይል ፍጹም ሆነ:: ኃይለ እንስሳ የተባለችው
እንስሳዊት እውቀት በፈቃድ የምትነሣሣ ናት:: ለዚህችውም ከእውቀት ወገን አላት፤ ባላትም እውቀት ይችውም እንስሳዊት ናት:: በእሷም
ማየት መስማትም ይገኛል” ብለው ሁሉን ቆጥረው ተናግረዋል:: (መቅድመ ወንጌል) “ኃይለ ንባብ” ያሉትንም:- ንባብ፦ “ዛ ይእቲ
ማኀተመ ሕይወት መንፈሳዊት፣ እንተ ባቲ አክበሮ እምኩሉ ፍጥረት ዘታሕተ ሰማይ፤ ወትትዐወቅ በኃይለ ንባብ:: ዛ ይእቲ አርአያ ገጹ
ለእግዚአብሔር ወአምሳሊሁ፤ ኩናኒተ ሥጋ ወኃይሉ፤ በእንተ ዘኮነት አሐተ ውስተ ኩሉ፤ ወባቲ ይትረከብ ጥበብ ዘየሐስብ ወየኀሪ ልብ፤
ወአእምሮ አዝማን፤ ወመካናት፤ ወኩሉ ምግባራት እንተ ትከውን በዘይእቲ ላዕሌሁ:: በሥልጣን ባሕታዊት ሥዕልት ዘእንበለ ገቢር::
ወገብረ ላቲ ሥልጣነ ውስቴታ ትግብር ዘከመ ኀርየት፤ እንዘ አልቦ ዘይኰንና ወዘይሄይላ፣ ከመ ትኩን ሠናያቲሃ ወእከያቲሃ በስምረተ
ኅሊናሃ፤ በአምሳለ መላዕክት” ትርጉም፦ “ይህችም መንፈሳዊት የምትሆን ከሰማይ በታች ካለው ፍጥረት ሁሉ ለይቶ እርሱን ያከበረባት
የሕይወት ፍጻሜ ናት:: ምሥጢርንም በመናገር ትታወቃለች፤ የእግዚአብሔር መታወቂያው፤ የምትመስለውም ናት:: ሥጋን የምትገዛው ዕውቀቱም
ናት:: በሥራው ሁሉ አንድ ስለሆነች ልብ የሚሻው የሚመረጠውም ጥበብ ዘመኖችንና ቦታቸውን ማወቅ በእርሷ ይገኛል:: የሚሠራውም ሥራ
ሁሉ ሥጋን በተዋሐደች በእርሷ ነው:: በዕውቀት ልዩ ናት፤ ግብር እምግብር ያልተፈጠረች ናት:: በጐነቷም ክፉነቷም በመላዕክት አምሳል
በራሷ ፈቃድ ይሆን ዘንድ፤ የሚገዛት የሚያዛትም ሳይኖር እንደወደደች ልትሠራ:: የምትሠራበትንም ስልጣን /ዕውቀት/ ለእርሷ ሰጧት
ብለዋል” (ዝኒ ከማሁ መቅድመ ወንጌል) ብሏል:: ፊልክዩስም ንባብ፦ “ወእንተሰ እምፍጥረታ ባቲ ሥምረት፣ ክሂል፣ ወፍትወት፣ ለገቢረ
ጽድቅ ወአእምሮ ዘበአማን” ትርጉም፦ “ከተፈጠረች ጀምሮ የተሰጣት ፈቃድ ዕውቀትም መሻትም ጽድቅን ለመሥራትና እውነተኛውን እውቀት
ለማወቅ ነው” ብሏል:: አሁን ከዚህ በላይ እንደተናገርነው፣ ኃይልም ክሂልም ሥልጣንም የተባለ፣ አእምሮና ንባብ ሕይወትም እንደሆነ፤
“ንግበር ሰብአ በአርአያነ ወበአምሳሊነ” በተባለ በሰው የታወቀ የተረዳ ሲሆን፣ ኃይል ስልጣን ክሂል እንደ አካል ከሦስት ይከፈላል
ማለት፤ በሦስቱ አካላት በየራሳቸው ሦስት ልብ፣ ሦስት ቃል፣ሦስት እስትንፋስ አሉ ማለት እንደሆነ ታወቀ ተረዳ፤ እንዲህም ከሆነ፣
የዚህ ሃይማኖት መንገድ የዮሐንስ ተዐቃቢ መንገድ መሆኑ የማይጠረጠር ነው::
ክፍል ፩
አንዳንድ ሰዎች እንደሚናገሩት
ኃይል፣ ክሂል፣ ሥልጣን፣ በአካል ከሦስት የሚከፈልና የሚለይ ከሆነ፤ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ በእመቤታችን በድንግል ማሕፀን
ሥጋን ፈጥሮ በተዋሐደ ጊዜ የተዋሐደውን ሥጋ በማን አካል ባለ ኃይል፣ ክሂል፣ ሥልጣን ፈጥሮ ተዋሐደ ይባላል፤ በራሱ ስልጣን ብቻ
ፈጥሮ ተዋሐደ እንዳይባል፤ አብም መንፈስ ቅዱስም፤ ፈጥረው እንዳልተዋሐዱት መጻሕፍት በብዙ አንቀጽ ይመሰክራሉ:: /ማስረጃ/ ሰሎሞን
ንባብ፦ “ትቤ ጥበብ ፈጠረኒ እግዚአብሔር መቅድመ ተግባሩ” ትርጉም፦ “ጥበብ ከፍጥረቱ ሁሉ አስቀድሞ እግዚአብሔር ፈጠረኝ አለች”
ብሏልና:: ምሳ ፰÷፳፪ ይህንም ሲተረጉም ባስልዮስ ዘቂሣሪያ ፲፪ኛ ንባብ፦ “ይብል ዘንተ በእንተ ልደቱ በሥጋ ከመ ውእቱ ፍጡር
ወግቡር” ትርጉም፦ “በሥጋ ስለተወለደው ልደት ሰው መሆኑን መናገር እንደሆነ ሲያስረዳ “ፈጠረኒ” አለ” ብሏል:: (ሃይ አበው ክፍል
፩) ሃ. አበው ምዕ ፴፪÷፲፫ ዳግመኛም ንባብ፦ “እስመ ብሂለ ወለደኒ
ይተረጉም በእንተ መለኮት፤ ወብሂለ ፈጠረኒ ይትረጉም በእንተ ትስብእቱ” “እመሰ ለሊሁ ወልደ እግዚአብሔር ይቤ እስመ እግዚአብሔር
ፈጠረኒ ለምንትኑ ይትመለክ እንከ እስመ ብሄለ ወለደኒ ይተረጎም በወልደ እግዚአብሔር ወብሂለ ፈጠረኒ በእንተ ትስብእቱ” ትርጉም፦
“እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር ፈጠረኝ ካለ እንኪያ ለምን አምላክ ይባላል? ቢሉ ወለደኝ ማለት የእግዚአብሔር ልጅ ስለመሆኑ
ፈጠረኝ ማለትም ሰው ስለመሆኑ ይተረጎማልና” ትርጉም፦ “ወለደኒ ያለው
ስለ መለኮቱ ይተረጉማል” ብሏላ:: (ሃይማኖተ አበው ክፍል ፪) (ዝኒ
ከማሁ ፴፪÷፲፰ ) ቴዎዶስዮስ ተአማኒ በጽድቅም ፴፩ኛ ንባብ፦ “ወበእንተዝ ይቤ፤ ዝኩ ሥጋ ቅዱስ ጸርሐ እንዘ ይብል፤ ሊተ ለጥበብ
ፈጠረኒ እግዚአብሔር እምቅድመ ተግባሩ፤ እስመ ዝኩ ሥጋ ቅዱስ ጥበብ ውእቱ ዘተነግረ በብዙኅ መክፈልት” ትርጉም፦ “ያ ክቡር ሥጋ፣
ጥበብ እንደሆነ፣ በብዙ አንቀጽ ተነግርዋልና፣ ስለዚህ ያ ቅዱስ ሥጋ፤ እግዚአብሔር ከፍጥረቱ አስቀድሞ፤ ጥበብ እኔን ፈጠረኝ ሲል
አሰምቶ እንደ ተናገረ ሰሎሞን ተናገረ” ብሏል:: (ሃይማኖተ አበው መልዕክት ፪ኛ) ሃ. አበው ምዕ ፹፫ ÷ ፬-፮ ኢሳያስም ንባብ፦
“ፈጠረኒ በውስተ ከርሥ ከመ እኩን ገብሮ” ትርጉም፦ “አገልጋዩ እሆን ዘንድ በማሕፀን ፈጠረኝ አለ” ብሏል:: ኢሳ ፵፱÷፭ ቅዱስ
ጳውሎስም ንባብ፦ “ምእመን ለዘፈነዎ” ትርጉም፦ “ለላከው /ለሾመው/ የታመነ ነው” ያለውን ዕብ ፫÷፪:: ኤጲፋንዮስም ፳፮ኛ ንባብ፦
”ምእመን በኀበ ዘገብሮ” ትርጉም፦ “በፈጠረው ዘንድ የታመነ ነው” ብሎታል:: (መልዕክት ፫) ሃ. አ በው ምዕ ፶፬÷፶፱ ቴዎዶስዮስም
በ፫ኛው መልዕክት ፴፩ኛ ንባብ፦ “በኀበ ዘፈጠሮ” ትርጉም፦ “በፈጠረው ዘንድ” ብሎታል:: በማቴዎስ ወንጌልም ንባብ፦ “እስመ ዘይትወለድ
እምኔሃ እመንፈስ ቅዱስ ውእቱ” ትርጉም፦ “ከእርሷ የሚወለደው በመንፈስ ቅዱስ ነው” ያለውን ማቴ ፩÷፳:: ዮሐንስ አፈወርቅ ሲተረጉም:-
ንባብ፦ “እስመ መንፈስ ቅዱስ ውእቱ ዘፈጠረ ውስተ ከርሠ ድንግል ሥጋሁ ለቃል፤ ውእቱ እምግብረ ስምረቱ ለመንፈስ ቅዱስ” /ትርጉም/
“በድንግል ማሕፀን ሥጋን የፈጠረ መንፈስ ቅዱስ ከፈቃዱ ሥራ የተገኘ ነው” ብሏል:: ዳግመኛ:- ንባብ፦ “ፈጠረ ሎቱ እግዚአብሔር
መቅደሰ ሕያወ በመንፈስ ቅዱስ” ትርጉም፦ “እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ ሕያው መቅደስ ሥጋን ፈጠረለት” በታተመው ሃይማኖተ አበው
ያለው ዘር ትንሽ ይለያል በምሥጢር ግን አንድ ነው ብሏል:: (ክፍል ፩)
ሃ. አበው ምዕ ፷፮÷፮ ይህን የመሰለ በየአንቀጹ የተናገረው
ብዙ ነው፤ ይህን በመመልከት በአብ አካል ብቻ ወይም በመንፈስ ቅዱስ አካል ብቻ ባለ ሥልጣን ተፈጠረ እንዳይባል፣ ወልድ በገዛ ሥልጣኑ
ሥጋውን ፈጥሮ እንደተዋሐደ መጻሕፍት ይመሰክራሉ:: /ማስረጃ/ ዘቂሣርያ ባስልዮስ ፲፪ኛ ንባብ፦ “ወኢንብል እስመ አብ ፈጠረ ሎቱ፤
ከመ ኢንረስዮ ነኪረ እምነ መለኮቱ፤ አላ ለሊሁ ፈጠረ ለርእሱ፣ እስመ ቦቱ ምልክና ምስለ አብ በኩሉ ግብር” ትርጉም፦ “አብ ብቻ
ሥጋን ፈጠረለት አንልም፤ ከመለኮቱ ልዩ እንዳናደርገው እርሱ እራሱ ሥጋን ፈጠረ እንላለን እንጅ፣ በሥራ ሁሉ ከአብ ጋራ ሥልጣን
አለውና” ብሏል:: (ድርሳን ፩ ማር ኤፍሬም) ሃ. አበው ዘባስልዮስ ምዕ ፴፬÷፲፩ ንባብ፦ “ወእምኔሃ ነሥአ ሥጋ ዘውእቱ ፈጠረ፤
ወለሊሁ ፈጠረ ዘነሥአ” ትርጉም፦ “እርሱ የፈጠረውን ሥጋ ከእርሷ ነሣ፤ የነሣውንም ሥጋ እርሱ ፈጠረ” ከታተመው ሃይማኖተ አበው
ዘር በቃል አገባቡ ይለያያል ብሏል:: (ድርሳን ፩) ሃ. አበው ዘ ኤፍሬም ምዕ ፵፯÷፬ አውክንድዮስም ንባብ፦ “ወኢተሳተፎ መኑሂ
በፈጢረ ሥጋሁ አላ ለሊሁ ፈጠረ ለባሕቲቱ” ትርጉም፦ “ሥጋውን በመፍጠር ማንም አጋዥ አልሆነውም፤ እርሱ ብቻ ሊዋሐደው፣ እርሱ ፈጠረው
እንጂ” ብሏል:: (መልዕክት ፩) ሃ.አበው ምዕ ፵፬÷፫ አትናቴዮስም ዘእስክንድርያ:- ንባብ፦ “ወሥጋሁሰ ለእግዚእነ ግቡር ውእቱ
እስመ ለሊሁ ገብሮ ለርእሱ” ትርጉም፦ “የጌታችን ሥጋስ ፍጡር ነው፤ እርሱ ለራሱ ፈጥሮታልና” ብሏል:: (ሃ.አበው) ክፍል ፲፬:
ይህን የመሰለ የተናገሩ ሊቃውንት ብዙ ናቸውና፣ በየአንቀጹ እየገቡ መመልከት ነው:: ኃይል፤ ክሂል፤ ሥልጣን፤ በአካል ከሦስት የሚለይ
ከሆነ፤ ይህ ሁሉ ንባብ በምን ምሥጢር ተስማምቶ ይገኝ ይሆን? እኛስ አባቶቻችን እንደነገሩን፣ ይህን ሁሉ ንባብ በምሥጢር በማስማማት፤
ወልድ በአካሉ ባለች በገዛ ሥልጣኑ ሥጋውን ፈጥሮ ተዋሐደ ብለን እናምናለን:: አምነን በወልድ አካል ያለች ኃይል፣ ክሂል፣ ሥልጣን፣
በአብና በመንፈስ ቅዱስ አካል ያለች አንዲት ናትና:: መጻሕፍት አንድነታቸውንና ሕልውናቸውን ለመንገር አብ ፈጠረው፤ መንፈስ ቅዱስ
ፈጠረው እርሱ፤ እራሱ ፈጠረ ያሉትን የመጻሕፍትን ቃል አስማምተን፤ ኃይል፣ ክሂል፣ ሥልጣን፣ ከሦስት የማይከፈል አንድ እንደሆነ
እናምናለን::
ይቀጥላል፡፡
ይቆየን፡፡