Thursday, May 25, 2017

ፍኖተ እግዚአብሔር--- ክፍል ፱



© መልካሙ በየነ

ግንቦት 18/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ተጽሕፈ እም አሐዱ ሊቅ ኢትዮጵያዊ ኅሩይ ወመፈክራዊ
ጌታው አለቃ ኅሩይ
===========================

፲፪ኛ አንቀጽ
የመለኮት ንባቡ አንድ ትርጓሜው ብዙ እንደሆነ ይናገራል::
መለኮት ንባቡ አንድ ሲሆን፣ ትርጓሜው ብዙ ነው ፩ኛ ብርሃን ይሆናል:: ማስረጃ:- አግናጥዮስ:- ንባብ:- “እኁዛን እሙእንቱ በፅምረተ ፩ መለኮት ዘውእቱ ብርሃን ዘይሰርቅ እምኔሁ ሥላሴ” እንዳለ:: ሃይማኖተ አበው ምዕ ፲፩ ÷ ፰-፱ ጥያቄ:- በዚህ አንቀጽ ብርሃን የተባለ መለኮት ከሦስት የሚከፈል ከሆነ፣ አንዱን ልብስ ሦስት ሰዎች ከሦስት እንዲለብሱ፣ ሦስቱ አካላት አንዱን ብርሃን ከሦስት ተካፈሉት ሊባል ይገባልን? መልስ:- እኛስ በአብ አካል ያለች ብርሃን በወልድ አካልና በመንፈስ ቅዱስ ያለች አንዲት ብርሃን ናትና፣ “በአንድ መለኮት አንድ አድራጊነት፤ የተገናዘቡ ናቸው፤ ይህም መለኮት የአካል ሦስትነት የሚገኝለት አንድ ብርሃን ነው” ብሎ አግናጥዮስ ስለነገረነ፤ ከሦስት የማይከፈል አንድ ብርሃን በሦስቱ አካላት እንዳለ እናምናለን:: ማስረጃ:- ዮሐንስ ዘአንጾኪያ ፶፩ኛ ንባብ:- “አብ ብርሃን ወልድ ብርሃን መንፈስ ቅዱስ ብርሃን ዳዕሙ ውእቱ ፩ ብርሃን ዘኢይትከፈል ወኢይትዌለጥ በህላዌ መለኮት” ትርጉም:- “አብ ብርሃን ነው ወልድ ብርሃን ነው መንፈስ ቅዱስ ብርሃን ነው፤ ነገር ግን በመለኮት ሕላዌ የማይለወጥ የማይከፈል አንድ ብርሃን ነው” ብሏል:: (ሃይ. አበው ክፍል ፩) ሃይማኖተ አበው ምዕ ፻፲፬÷፭፡፡ ፪ኛ ሕይወት ይሆናል ማስረጃ:- አግናጥዮስ ዘአንጾኪያ:- ንባብ:- “ኢተአምርኑ ከመ ለእመ ትቤ መለኮት ሞተ፣ ትከውን ቀታሊሆሙ ለሥሉስ ቅዱስ እስመ ባሕርየ ሥላሴ ፩ ውእቱ ዘውእቱ ፩ መለኮት” ትርጉም:- “መለኮት ሞተ ብትል አንተ የሥሉስ ቅዱስ ገዳያቸው እንድትሆን አታውቅምን? የሥላሴ ባሕርይ አንድ ነውና፤ ይኸውም አንድ /ሕይወት/ መለኮት ነው” ብሏል:: (ሃይ. አበው ክፍል ፩) ሃይ. አበው ምዕ ፲፩ ÷ ፲፫-፲፬ በዚህ አንቀጽ መለኮት የተባለ ባሕርይ ሦስቱን አንድ የሚያደርግ አንድ ሕይወት እንደሆነ ያስተውሏል:: ሕይወት የተባለ መለኮት በአካል ከሦስት የሚከፈል ከሆነማ አንዱ ቢሞት ሦስቱ ሞቱ እንደምን ባላሰኛቸውም ነበር? አንድ ቢሆን አይደለምን? በሕይወት ከሚመሳሰሉ ብዙ ሰዎች አንዱ ቢሞት ሁሉም ሞቱ ያሰኛልን:: ፫ኛ አገዛዝ ይሆናል:: ማስረጃ:- ነቢዩ ዳዊት ንባብ:- “ውስተ ኩሉ በሐውርት መለኮቱ” ትርጉም:- “አገዛዙ በሀገሮች ሁሉ ነው” እንዳለ:: መዝሙር ፻፪÷፳፪ ፬ኛ ጌትነት ይሆናል:: ማስረጃ:- ጳውሎስ ንባብ:- “ወከመዝ ይትአመር ኃይሉ ወመለኮቱ ዘለዓለም” ትርጉም:- “የዘለዓለም የሚሆን ኃይሉ ጌትነቱም እንዲህ ይታወቃል” እንዳለ:: (ሮሜ ፩÷፳) ቅዱስ ጴጥርስም ንባብ:- “ዘበኃይለ መለኮቱ ወኀበ ለነ ኩሎ ምግባረ ዘይወስድ ኀበ ሕይወት ወጽድቅ” ትርጉም:- “በጌትነቱ ኃይል ወደ ሕይወትና ወደ ጽድቅ የሚወስድ ምግባርን የሰጠን” ብሏል:: (፪ኛ ጴጥ ፩÷፫) ኄሬኔዎስም ፫ኛ:- ንባብ:- ቅዱስ ጳውሎስ “እስመ ዘሐመ ተሰቅለ በድካም፤ ሕያው ውእቱ በኃለ እግዚአብሔር” ትርጉም:- “ደክሞ የተሰቀለውና የሞተው በእግዚአብሔር ኃይል ሕያው ነው” ያለውን (፪ኛ ቆሮ ፲፫ ÷፬-፭) ሲተረጉም:- ንባብ፦ “ወሐይወ በኃይለ እግዚአብሔር ዘውእቱ መለኮት” ትርጉም:- “በእግዚአብሔር ኃይል ተነሣ፣ ይኸውም መለኮቱ ነው” ብሏል:: (ሃይ. አበው ክፍል ፩) ሃይ. አበው ምዕ ፯ ÷ ፴ በዚህ መለኮት የተባለ ጌትነት ወይም ሥልጣን እንደሆነ ማስተዋል ነው:: ፭ኛ ክብር ይሆናል:: ማስረጃ:- ሐዋርያው ጴጥሮስ ንባብ:- “ከመ በእንተ ዝንቱ ትኩኑ ሱቱፋነ ለመለኮተ ዚአሁ” ትርጉም:- “ስለዚህ ነገር የክብሩ ተካፋዮች ትሆኑ ዘንድ ለምግባር ለትሩፋት ሁሉ” ፪ኛ ጴጥሮስ ፩÷፬ ባለው መረዳት ነው:: ፮ኛ ባሕርይ ይሆናል:: ማስረጃ:-(፶፪ኛ) ዲዮናስዮስ ሊቀ ዻዻሳት ዘአንጾኪያ:- ንባብ:- “ይሴለሱ በአካላት ወይትወሐዱ በመለኮት” እንዳለ አንቀጽ ፪ እይ:: ፯ኛ አምላክነት ይሆናል:: ማስረጃ (፶፭ኛ)/ዮሐንስ ዘአንጾኪያ ንባብ:- “ይገብር መንክራተ በመለኮቱ፤ ወይትዌከፍ ሕማማተ በትስብእቱ” ትርጉም:- “በአምላክነቱ ተአምራትን ያደርጋል፣ በሰውነቱ መቀበል” አንዳለ (ክፍል አንድ) እመልክተ ሲኖ. በ፲፩ኛው አንቀጽ፤ ነገሩን ኋላ በ፲፪ኛ አንቀጽም እናመጣዋለን ያልነው ይህ ነው::ሲኖዲቆን ይህ ሁሉ አንድ  የሚሆኑበትና የሚገናዘቡበት ነው እንጂ፤ የሚለያዩበት አይደለም:: ይህን ያህል ስህተት የሚያመጣ የመለኮትን የምሥጢሩን ስልት አስተውሎ አለመመልከት ነው:: መለኮት በአካላት የሚለይ ቢሆንስ፣ ሦስቱ ባልተጠሩበትም ነበረ:: ወላዲ፣ ተወላዲ፣ ሰራጺ ማለት በግብር፤ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ማለት  አካል፤ ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ ማለት በከዊን፤ የሚለያዩባቸው ስሞች ስለሆኑ፤ እየራሳቸው ተጠሩባቸው እንጂ ሦስቱ ሁሉ አልተጠሩባቸውም፤ አምላክ፣ መለኮት፣ ከዊን ማለት ነው:: እግዚአብሔር ማለት ግን በባሕርይ አንድ የሚሆንበት በሕልውና የሚገናዘቡበት በመሆኑ ሦስቱ ተጠሩበት:: ሐተታ:- ሦስቱ መለኮት ለማለት፤ ሳዊሮስ ዘገብሎን በተረፈ ቄርሎስ “እስመ ፫ቱ ኁልቈ መለኮቱ” ያለውን የሚጠቅስ ቢኖር፣ መልሱ ምሥጢሩን ባይመለከት ነው እንጂ ቢመረምረውስ ይህን ምስክር አድርጐ ባልተነሣም ነበር፤ አሁን በአርእስቱ እንደተናገርነው፤ሦስቱ ስለተጠሩበት “፫ ኍልቊ መለኮቱ” አለ:: የሚዋሕዱበት አንድ እንደሆነ ሲያስረዳ መለኮቱ ብሎ በአንድ አንቀጽ ተናገረው:: እንደእነሱ አነጋገር ቢሆን ኖሮ ግን “መለኮታቲሆሙ” ባለ ነበረ እንጂ፣ መለኮቱ ባላለም ነበር:: ምሥጢሩም አትናቴዎስ ዘእስክንድር:- ንባብ:- “አምላክ ውእቱ አብ፣ አምላክ ውእቱ ወልድ፣ አምላክ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ፤ ወኢይትበሀሉ ሠለስተ አማልክተ፤ አላ ፩ አምላክ” ትርጉም:- “አብ አምላክ ነው፣ ወልድ አምላክ ነው፣ መንፈስ ቅዱስ አምላክ ነው፤ ነገር ግን አንድ አምላክ ይባላሉ እንጂ፣ ሦስት አምላክ አይባሉም” (ሃይ. አበው ክፍል ፬) ሃይማኖተ አበው ዘአትናቴዎስ ምዕ ፳፭ ÷ ፬  ብሏል:: ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ ማለት በከዊን የሚለያዩበት በህልውና የሚገናዘቡበት እንደሆነ ከዚህ አስቀድመን በ፪ኛው አንቀጽ ተናግረናል:: ይህውም ሕያዋን የሚያሰኛቸው ሕይወት ነው፤ ሕይወትም እንደሆነ “ንግበር ሰብአ በአርአያነ” ባለው በሰው ይታወቃል:: ሰው አእምሮው ንባቡ እስትንፋሱ የተለየው እንደሆነ ሞተ ይባላል፤ ካልተለየው ግን ሕያው ነው ይባላል እንጂ ሞተ አይባልም:: የእግዚአብሔር የባሕርዩን ከዊን ከሚመሰክሩ መጻሕፍት አንድ ደገኛ መጽሐፍ ሰው ነውና:: ማስረጃ:- ቅዱስ ቁርሎስ ዘእስትጉቡዕ ንባብ:- “ወኮንኩ መጽሐፎ ለክርስቶስ” ትርጉም:- “የክርስቶስ መጽሐፍን ሆንኩ” ንባብ:- “ወየአምር መጽሐፈ እግዚአብሔር” ትርጉም፦ “የእግዚአብሔር መጽሐፍ ሰው ያውቃል” እንዳለ፤ በ፲፩ኛው አንቀጽ ነገሩን ኋላ በ፲፪ኛ አንቀጽም እናመጣዋለን ያልነው ይህ ነው::
፲፫ኛ አንቀጽ
ሥላሴ ዓለምን በአንዲት ቃል እንደፈጠሩ
“ለሥላሴ በየራሳቸው ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ አላቸው ካልተባለ፣ ሥላሴ በአካል ፍጹማን ናቸው አያሰኝም” ለተባለው ጥያቄ መልሱን ከነምስክሩ በ፲ኛው አንቀጽ አስረድተናል፤ ከዚያ የቀረውንም በዚህ አንቀጽ እንናገራለን:: ለሦስቱ አካላት በየራሳቸው ቃል አላቸው ማለት እንዳይገባ ቃላቸውም አንድ ወልድ ብቻ እንደሆነ የሚያስረዳ ነገር በሥነ-ፍጥረት እናሳያለን:: እግዚአብሔር በዕለተ እሑድ “ለይኩን ብርሃን” ካለ ጀምሮ፤ በዕለተ ዓርብ፣ “ንግበር ሰብአ በአርአያነ” እስኪል ድረስ በነቢብ የፈጠረው ፍጥረት ብዙ ነው:: በማንኛቸው ቃል ተፈጠረ ይባላል በአብ በተለየ ቃሉ እንዳይባል ፍጥረት የተፈጠረ በወልድ ቃልነት እንደሆነ መጻሕፍት በብዙ አንቀጽ ይመሰክራሉ:: ከብዙም በትቂቱ የሚያስረዳ ዮሐንስ ወንጌላዊ:- ንባብ:- “ቀዳሚሁ ቃል ውእቱ” ትርጉም:- “አስቀድሞ ቃል ነበረ” ብሎ ተነሥቶ ንባብ:- “ወቦቱ ኩሉ ኮነ ወዘእንበሌሁሰ አልቦ ዘኮነ ወኢምንትኒ እምዘኮነ” ትርጉም:- “ሁሉም በእርሱ ሆነ ያለ እርሱ ግን የሆነ የለም ምንም ከሆነው ሁሉ” ብሏል:: ዮሐ ፩÷፪-፫ ቅዱስ ጳውሎስም:- ንባብ:- “ወአሐዱ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘኩሉ በእንቲአሁ ወንሕነኒ ቦቱ” ትርጉም፦ “አንድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉ በእርሱ የሆነ፣ እኛም በእርሱ” ብሏል:: ፩ቆሮ ፰÷፮ ዳግመኛም ንባብ:- “ወበድኀሪሰ መዋዕል በወልዱ ዘረሰዮ ወራሴ ለኩሉ፤ ወቦቱ ፈጠሮ ለኩሉ” ትርጉም:- “እርሱ በኋለኛው ዘመን በልጁ ነገረን፤ ሁሉን ወራሽ ባደረገው፣ ዓለሙንም ሁሉ በፈጠረበት” ብሏል:: ዕብ ፩÷ ፪ ከአረጋዊ መንፈሳዊ ማስረጃ ንባብ:- “ወዓዲ ይሰመይ ወልድ በእንተ ዘተፈጥረ ቦቱ ኩሉ፤ ወካዕበ ወልድ ይሰመይ ቃለ፣ እስመ አእምሮቱ ለእግዚአብሔር ውእቱ” ትርጉም:- “ዳግመኛ ሁሉ በእርሱ ስለተፈጠረ ወልድ ይባላል፤ ወልድም ቃል ይባላል፣ የእግዚአብሔር መታወቂያው ነውና” ብሏል:: /ድርሳን ፳፪/ አትናቴዎስም ዘእስክንድርያ ፲፩ኛ ወደ አክኒጦስ በጻፈው መጽሐፍ አክኒጦስ የቆጵሮስ ኤጲስ ቆጶስ ነበር ። ሃ.አ በው ምዕ ፳፱ ÷፩ ገጽ ፺ ንባብ:- “ኢንፈልጦ ለወልድ እምቃል፣ ከመ ካልእ ውእቱ፤ ወባሕቱ ንብል እስመ ቃል ውእቱ ወልድ ዘቦቱ ኩሉ ኮነ” ትርጉም:-  ወልድን ከቃልነቱ ልዩ አድርገን አናወጣም፤ ወልድ ዓለም ሁሉ የተፈጠረበት ቃል ነውና፣ ወልድ ቃል ነው እንላለን እንጂ” ብሏል:: (ድርሳን ፲፭) ይህን የመሰለ በየአንቀጹ የተናገረው ብዙ ነው:: ደግሞ ይህን ተመልክተን በወልድ ቃልነት ብቻ ተፈጠረ እንዳንል፤ አብን ከፈጣሪነት ማውጣት ይሆናል፤ በዚኸውም ቃል አልፈጠረም እንዳንል ገንዘቡ ባልሆነ በሌላ ቃል ተናገሮ ፈጠረ ማለት ለልቦና አይረዳም:: ይህ ካልሆነ ብለን አብን ከፈጣሪነት እንዳናወጣውም በየአንቀጹ መጻሕፍት ይመሰክሩብናል:: ማስረጃ:- ሙሴ እስራኤልን /ንባብ/ “አኮኑ ዝንቱ አብ ፈጠረከ፤ ፈጠረከሂ ወገብረከ” ትርጉም:- “ይህ አብ የፈጠረህ አይደለምን? ፈጥሮ ወገን ያደረገህ አይደለምን?” ብሎታልና ዘዳ ፲፪÷፮ በዚህ አንቀጽ “ንግበር ሰብአ በአርአያነ ወበአምሳሊነ” ያለው የአብ ቃል እንደሆነ ያስረዳል:: ነቢይም ንባብ:- “ወበቃለ እግዚአብሔር ፀንዓ ሰማያት፣ ወእምእስትንፋሰ አፉሁ ኲሉ ኃይሎሙ” ትርጉም:- “በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ተሠሩ፤ ሃ. አበው ምዕ ፴፩ ÷ ፵፩ ሠራዊቶቻቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ” ብሏል:: መዝ ፴፫ ÷፮ ዮሐንስ ወንጌላዊ በቅዳሴው ንባብ:- “ወኩሎ ተግባረከ ፈጠርከ በቃልከ” ትርጉም “ፍጥረትህን ሁሉ በቃልህ ፈጠርህ” ብሏል:: አትናቴዎስም ዘእስከንድርያ ንባብ:- “ፈጠረ አብ ኩሎ ፍጥረተ በቃሉ፣ ዘውእቱ እምነ መለኮቱ ወበመንፈሱ ቅዱስ” ትርጉም:- “አብ ፍጥረቱን ሁሉ ከባሕርይው በተገኘ በቃሉና በቅዱስ መንፈሱ ፈጠረ” ብሏል:: (ሃይ. አበው ፲፫ ክፍል) ሃ.አ በው ምዕ ፴፩ ÷ ፵፩ ሠለስቱ ምዕትም ፫ኛ በፀሎተ ሃይማኖት ንባብ:- አብን “ገባሬ ሰማያት ወምድር ዘያሰተርኢ ወዘኢያስተርኢ” ትርጉም:- “ሰማያትና ምድርን የሚታየውንም የማይታየውንም የፈጠረ” ወልድንም ንባብ:- “ዘቦቱ ኲሉ ኮነ ወዘእንበሌሁሰ፣ አልቦ ዘኮነ ወኢምንትኒ ዘበሰማይኒ ወዘበምድርኒ” ትርጉም:- “ሁሉ በእርሱ የተፈጠረ በሰማይም በምድርም ያለ እርሱ የተፈጠረ ምንም የለም” ብለዋል::  ይህን የመሰለ በየአንቀጹ የተነገረው ብዙ ነው:: ነገር ግን መጻሕፍት ፍጥረት ሁሉ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ገንዘብ በሚሆን በአንድ ቃል ተፈጠረ ሲሉ፣ ሦስቱን አካላት በአንድ መለኮት የማያገናዝቡ ሰዎች በየራሳቸው ሦስት ቃሎች አሉ ባሉ ጊዜ፣ በማናቸውም ቃል ተፈጠረ ይሉት ይሆን ወይስ በሠርግ፣ በዱለት፣ በገበያ የተሰበሰበ ሰው፣ ሁሉም በየቃሉ እየተናገረ፣ በአንድነት ሲጮህ እንዲሰማ፣ ሦስቱ አካላት በየቃላቸው አንድ ጊዜ ሲናገሩ ተሰሙ ይሉ ይሆን፣ መጻሕፍት በመሰከሩ ነው እንጂ፤ በጉሥዓተ ልብ አይደለምና፣ ይህ ከብዙ ስህተት የሚያደርስ ስለሆነ፣ ይህን ነገር ጠንቅቀን እናስተውል::
ይቀጥላል፡፡
ይቆየን፡፡

No comments:

Post a Comment