Sunday, May 28, 2017

ፍኖተ እግዚአብሔር--- ክፍል ፲



© መልካሙ በየነ

ግንቦት 21/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ተጽሕፈ እም አሐዱ ሊቅ ኢትዮጵያዊ ኅሩይ ወመፈክራዊ
ጌታው አለቃ ኅሩይ

ክፍል ፩
ሦስቱን በአንድ ልብ እንዲያውቁ፣ በአንድ ቃል እንዲናገሩ፣ በአንድ እስትንፋሰ የሕይወት ሥራ እንዲሠሩ የሚያደርጋቸው፣ ሦስቱን የሚያገናዝብ መለኮት አንድ ቢሆን ነበረ፤ መለኮት በአካል የሚለይ ሦስት ከሆነ ግን፣ ለሦስቱ በየራሳቸው ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ አላቸው ማለት ግድ ነው:: እንዲህም ከሆነ መጻሕፍት የተናገሩት ቃል ሁሉ ሐሰት ሆነ ማለት ነው:: እኛስ በአካል ሦስት በመለኮት አንድ ብለው አብን ልብ፣ ወልድን ቃል፣ መንፈስ ቅዱስን እስትንፋስ በማለት መጻሕፍት የመሰከሩት እውነት እንደሆነ አውቀን ተረድተን እናምናለን፤ ይህንም የሚያስረዳ አቡሊድስ:- “ወልድሂ ቃሎሙ ለአብ ወመንፈስ ቅዱስ፤ ወመንፈስ ቅዱስሂ መንፈሶሙ ውእቱ ለአብ ወወልድ፤ ወበዝንቱ አእመርነ ከመ ፩ዱ ውእቱ መለኮተ ስላሴ፣ ወሎቱ ንሰግድ:: ወአበዊነሂ እለ ተጋብኡ በኒቅያ ይቤሉ እመቦ ዘይፈልጥ መለኮቶ ለእግዚአብሔር አብ እም ወልድ ወእም መንፈስ ቅዱስ ውጉዘ ለይኩን ብለዋል” ትርጉም፡- “ወልድም ለአብ ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ነው፤ መንፈስ ቅዱስም ለአብ ለወልድ  እስትንፋሳቸው ነው፤ የሦስቱ አካላት መለኮት አንድ እንደሆነ በዚህ አውቀን ለርሱ እንሰግዳለን ። በኒቂያ የተሰበሰቡ አባቶቻችንም አንዱን የእግዚአብሔር አብን መለኮት ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ የሚለይ እንደኛ በአብ ትእዛዝ እንደተፈጠሩ የሚናገር ፤ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ከዚህ ከአንዱ ከአብ ባሕርይ አልተገኙም የሚል ቢኖር ውጉዝ ይሁን” ብለዋል።  (አንቀጽ ፴፭ኛ ፩ እይ) ሃ. አበው ምዕ ፴፱ ÷ ፰ ዮሐንስ ዘእስክንድርያም:- ንባብ:- “አአምን በ፩ዱ አምላክ፤ ወአአምር ተዋሕዶተ ሥላሴ፤ ወሥላሴ በተዋሕዶ፤ ወተዋሕዶትኒ በእንተ ፩ መለኮት ዘ፫ አካላት በአሐቲ ክብር፤ ወሥላሴኒ ዓዲ በእንተ ተዋሕዶተ አምላክኒ ዘ፫ አካላት ዘውእቶሙ:- አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ:: እስመ ምሥጢረ ሥላሴ ይትሌለይ በአካላት ወኢይትሌለይ በመለኮት፣ ወለእመኒ ንስምዮሙ ለ፫ አካላት በ፫ አስማት ኢንሬስዮሙ ሠለስተ አማልክተ፤ ወኢይከውን ዝንቱ፤ አላ ፩ አምላክ፤ ዘውእቱ አብ ምስለ ወልዱ ወመንፈስ ቅዱስ እምቀዲሙ እንበለ ፍልጠት::” ትርጉም:- “በአንድ አምላክ አምናለሁ፤ አንድነት በሦስትነት፣ ሦስትነትም በአንድነት እንዳለም አውቃለሁ፤ አንድነትም በአንዲት ክብር ያሉ የ፫ቱ አካላት መለኮት አንድ ስለሆነ ነው:: ዳግመኛም በአምላካችን ተዋሕዶ ላይ የሚነገር ሦስትነትም አካላት ሦስት ስለሆኑ ነው:: እኒሁም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ናቸው:: የሥላሴ ምሥጢር በአካል ይለያያል፤ በመለኮት ግን አይለይምና፣ ሦስቱን አካላትም በሦስት ስሞች ብንጠራቸው፣ ሦስት አማልክት አናደርጋቸውም:: ሦስት አማልክት ማለት አይገባምና፣ አንድ አምላክ ናቸው እንጅ:: ይኸውም ከጥንት ጀምሮ ያለመለየት ከልጁና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ የነበረ አብ ነው ብሏል::” /ሃይ. አበው ድርሳን ፩/ ሃ. አበው ምዕ ፺ ÷ ፭ ዳግመኛም ንባብ:- “እንዘ ሊሉያን እሙንቱ ይከውኑ ፩ እስመ መለኮተ ሥላሴ ፩ ወበሰለስቲሆሙ ሀሎ ፩ መለኮት::” ትርጉም:- “ልዩ ሲሆኑ በአንድነት ይኖራሉ:: የሦስቱ መለኮት አንድ ነውና፣ በሦስቱም አካላት አንድ መለኮት አለና ብሏል::” /ሃይ.አበው ድርሳን ፩/ (ዝኒ ከማሁ ቁ. ፲፫)፡፡ ፴፭ኛ ዮሐንስ ዘእስክንድርያም ንባብ:- “ንሕነሰ ነአምን ከመ ወልድ ይትዋሐድ በመለኮት ምስለ አብ ወመንፈስ ቅዱስ:: ወእመቦ ዘኢየአምን ከመ ፩ መለኮት ንሕነ ናውግዞ” ትርጉም:- “እኛስ ወልድ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ በመለኮት እንዲዋሐድ እናምናለን:: መለኮት አንድ እንደሆነ የማያምን ቢኖር ግን እኛ እናወግዘዋለን” (ዝኒ ከማሁ ምዕ ፺ ÷ ፲፭ )ብሏል:: ኪራኮስም ፴፮ኛ ንባብ:- “ወእሙንቱ ይነብቡ በዘያብህም ልሳናቲሆሙ እንተ ኢኮነት ግሥጽተ:: አኮ ከመዝ ሃይማኖትነ ለነሰ ለርቱዓን፤ አላ ፩ አምላከ ንሰብክ፣ ወ፩ ሕላዌ ወ፩ መለኮተ፣ ወ፩ ኃይለ፤ ወኢንብል ከመ በዝየ ሱታፌ ለ ፫ አካላት፣ በከመ ይቤ ዮሐንስ ዘይሰመይ ተዐቃቢ ዘይትሜካህ በእበዱ ምስለ እለ ይብሉ ሠለስቱ አማልእክት ወሠለስቱ ሕላዌ ዘሠለስቱ አካላት:: አኮ ዝንቱ ንባበ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን::” ትርጉም:- “ያልተሠራች ያልተቀጣች አንደበታቸውን ምላሽ የሚያሳጣ ነገርን ይናገራሉ:: የቀና እምነትን የምናምን የእኛ ግን፣ እምነታችን አንድ አምላክ ብለን ነው እንጅ፣ ሦስት አማልክት ብለን አይደለም:: በአንድ ኃይል ያለ አንድ ባሕርይ አንድ መለኮት እንደሆነ እናስተምራለን:: በዚህ አንቀጽ መለኮትን አንድ ነው እንዳልነ፣ ልዩ ልዩ የሚሆኑ አካላትን አንድ የምንል አይደለንም:: በስንፍናው የሚመካ ተዐቃቢ የሚባል ዮሐንስ ሦስት አማልክት ከሚሉ ሰዎች ጋራ የሦስቱን አካለት በባሕርይ ሦስት እንዳለ፣ መለኮትን አንድ በማለታችን አካላትን አንድ አንልም:: ይህ የቅድስት ቤተክርሰቲያን አነጋገር አይደለምና” ብሏል:: (ሃይ. አበው መልዕክት ፩) ሃ.አ በው ምዕ ፺ ፩ ÷ ፲-፲፩፡፡ ዳግመኛም:- ንባብ፦ “ንትዐቀብ ከመ ኢንምሀር በልሳናቲነ በዝንቱ መካን ከመ ንብል ሠለስቱ አማልክት ወ፫ ሕላውያት እስመ ዘይብል ዘንተ ናሁ ተሀበለ ያስተጋብዕ ሎቱ ብዙኃነ አማልክተ::” ትርጉም:- “ሦስት አካላት በማለታችን ሦስት አማልክት ሦስት ሕላውያት የማለትን ትምህርት ለአንደበታችን ልማድ ከማድረግ እንጠበቅ:: ይህን የሚል ሰው እነሆ ብዙ አማልክትን ይሰበስብ ዘንድ ይደፍራልና” ብሏል:: (ዝኒ ከማሁ ቁ. ፲፮)፡፡  ዮሐንስ ዘአንጾኪያ ፵፯ኛ ንባብ:- “ንህነሰ ናሰትት የታተመው “ናዓትት” ይላል ቃሎሙ ለአላውያን እለ ይትአመኑ ብዙኃነ አማልክተ ወሕላውያተ ፍሉጣነ ለ፩ እግዚአብሔር ዘኢይትከፈል በሕላዌ መለኮት:: ወናወግዝ ዓዲ እለ ይብሉ ሠለስቱ መለኮት እንተ ዘአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ::” ትርጉም፦ “እኛስ በመለኮት ባሕርይ ለማይለይ ለአንድ እግዚአብሔር ልዩ ልዩ ሕላውያትን የሚሰጡ ብዙ አማልክትን የሚያመልኩ የአላውያንን ትምህርታቸውን እንነቅፋለን:: ዳግመኛም የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ የሚሆን መለኮትን ፫ የሚሉትን እናወግዛለን” ብሏል:: (ሃይ. አበው ክፍል ፩) ሃይማኖተ አበው ምዕ ፶፫ ÷ ፬ ዳግመኛም:- ንባብ:- “ወሶበሂ ንቤ ሠለስቱ አካላት በበአካላቲሆሙ ንቤ ፩ ባሕርየ ፍጹመ፣ ወ፩ ሕላዌ ወ፩ መንግሥት ወ፩ እበይ ወ፩ ክብር ይትበሀሉ በእንተ እሉ ሠለስቱ አካላት አብ ብርሃን ወልድ ብርሃን መንፈስ ቅዱስ ብርሃን እንዘ ፩ ብርሃን ዘኢይትከፈል ወዘኢይትዌለጥ በሕላዌ መለኮት:: ወዓዲ ንብል አብ ሕይወት ወልድ ሕይወት መንፈስ ቅዱስ ሕይወት እንዘ ፩ ሕይወት:: ወካእበ ይተበሀል አብ ፩፤ ወልድ ፩ መንፈስ ቅዱስ ፩ ወለለ ፩ እምአካላት ፩ ሕላዌ ወ፩ አምላክ እሙንቱ:: ወኢይትበሀሉ ፫ አማልክተ አኮ ዘንተአመን በ፫ እደው ወ፫ አማልክት ወኢበ ፫ መለኮት:: አላ ንትአመን በ፫ አካላት ወ፫ ገጻት እንተ ፩ ባሕርየ መለኮት” ትርጉም:- “፫ አካላት በየአካለቸው አሉ ብንል፣ ፍጹም ባሕርይን ፩ ፣ ሕልውናንም አንድ ብለን፣ ፩ መንግሥት አንድ እበይ /ጌትነት/ አንድ ክብር ነው እንላለን:: አካላት ፫ ስለሆኑ በመለኮት ሕላዌ /አኗኗር/ የማይከፈልና የማይለይ አንድ ብርሃን ሲሆን፣ አብ ብርሃን፣ ወልድ ብርሃን፣ መንፈስ ቅዱስ ብርሃን ይባላሉ:: ዳግመኛም በመለኮት አኗኗር አንድ ሕይወት ሲሆኑ አብ ሕይወት፣ ወልድ ሕይወት፣ መንፈስ ቅዱስ ሕይወት ነው እንላለን:: ዳግመኛም አብ አንድ ይባላል፣ ወልድ አንድ ይባላል፣ መንፈስ ቅዱስ አንድ ይባላል:: ከአካላትም እያንዳንዱ አንድ ሕላዌ አንድ አምላክ ናቸው:: ሦስት አማልክት ግን አይባልም:: መገናዘብ እንደሌላቸው ሰዎች አድርገን በሦስት ሰዎች በሦስት አማልክት፣ በሦስት መለኮት፣ የምናምን አይደለንም:: ባሕርየ መለኮት አንድ በሚያድርጋቸው በሦስት አካለት፣ በሦስት ገጻት እናምናለን እንጂ”  ሃ. አበው ዘዮሐንስ ምዕ ፻፲፬ ÷ ፬-፮  ብሏል:: ዳግመኛም:- ፶፫ኛ ዲዮናስዮስ ዘአንጾኪያ:- ንባብ:- “ወንትአምን በዝንቱ ሕላዌ፣ ወንሰግድ አሐተ ስግደተ፤” ብሎ ተነሥቶ /አንቀጽ ፩ እይ/ “ንህነሰ ንሰብክ ከመዝ ወንሰግድ ለ፩ አምላክ ባሕቲቱ፣ ወንትአመን ከመ ፩ መለኮት ዘሠለስቱ አካላት፣ ወኢንበውእ ውስተ ከፊለ መለኮት ወመንግሥት:: አላ ንብል ፩ ሕላዌ፣ ወ፩ መንግሥት፣ ወአሐቲ ሥምረት፣ ወ፫ አካላት ወ፫ ገጻት እንበለ ተዘርዎ::” ትርጉም “እኛስ እንዲህ እናስተምራለን፤ ለአንድ አምላክ ብቻም እንሰግዳለን:: የ፫ አካላት መለኮትም አንድ እንደሆነ እናምናለን:: መለኮትንም መንግሥትንም ወደ መክፈል አንገባም:: አንድ ሕልውና፣ አንድ መለኮት፣ አንድ መንግሥት፣ አንድ ፈቃድ፣ ያለመለያየትም፣ ሦስት አካላት፣ ሦስት ገጻት እንላለን እንጂ ብሏል:: (እመልዕክተ ሲኖዲቆን) ዳግመኛም:- ንባብ:- “ውእቱሰ ፩ አምላክ ወአኮ ፫፡ ፩ እግዚእ ወአኮ ብዙኃን:: ወክብረ ምልክናሂ ልዑል ለመለኮት፤ ወበመለኮት ምልክና፤ ወቅድስት ሥላሴ ይእቲ ትትመለክ፤ ወትትአመር በ፫ አካላት:: ወተዋሕዶተ መለኮቶሙ ርሑቅ እምኩሉ ክፍለት፤ ወእመኩሉ ፍልጠት::” ትርጉም:- “እርሱስ አንድ አምላክ ነው እንጂ ፫ አማልክት አይደለም፤ አንድ ጌታ ነው እንጅ ሦስት ጌቶች አይደለም:: ከፍ ያለ የአምላክነት ክብርም ለመለኮት ነው፤ መግዛትም በመለኮት ነው:: ልዩ ሦስትነትም በሦስት አካላት እንዳለች ታውቋል፤ በአንድነትም ትመለካለች:: የመለኮታቸውም አንድነት ከመከፈል ከመለየትም የራቀ ነው”ብሏል:: (፳፫ኛ እመልዕክተ ሲኖዲቆን) ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙም:- “ወኢይትሀበሉ ኅጉላን ያብኡ ውስተ ቅድስት ሥላሴ ፍልጠተ መለኮት” ብሏል:: (አንቀጽ ፩ እይ ሃይ. አበው ፪) ሱኑትዮስ ዘእስክንድርያ:- ንባብ:- “ዘኢየአምን ወዘኢይትአመን ከመ ፩ መለኮቶሙ፤ ወ፩ ህላዌሆሙ፤ እንተ ሠለስቲሆሙ፣ ወ፩ ቃሎሙ፣ ወ፩ ምግባሮሙ ውጉዘ ለይኩን::” ትርጉም:- “ሦስት ሲሆኑ መለኮታቸው አንድ፣ ሕልውናቸውም አንድ፣ ቃላቸውም አንድ፣ ምግባራቸው አንድ እንደሆነ የማያምንና የማያሳምን የተለየ ይሁን” ብሏል:: (ሃይ. አበው ክፍል ፩) ሃይማኖተ አበው ምዕ ፻፲ ÷ ፵፩ ፵፱ኛ አትናቴዎስ ዘአንጾኪያም:-  “ወሶበሂ ንቤ ፩ እግዚእ ወ፩ ህላዌ ወ ፩ መለኮት” አንድ ጌታ አንድ አኗኗር አንድ መለኮት ባልን ጊዜ  ብሏል:: (አንቀጽ ፪ እይ) ሃይማኖተ አበው ምዕ ፻፮ ÷ ፰ ባለቤቱም ጌታ በኦሪት:- ንባብ:- “ኢታምልክ ባዕደ አምላከ ዘእንበሌየ” ብሏል:: ትርጉም:- “ከእኔ በቀር ሌላ ባዕድ አምላክ አታምልክ” አለ:: ዘጸ.፳÷፫፤ አንድ አድርጎ በአንድ አንቀጽ “ዘእንበሌየ” አለ እንጂ ከሦስት ለይቶ “ዘእንበሌነ” አላለም:: ዳዊትም:- ንባብ:- “ወኢትስግድ ለአምላክ ነኪር፤ እስመ አነ ውእቱ እግዚአብሔር አምላክ፤ ዘአውጻእኩከ እምድረ ግብፅ” ትርጉም:- “ለባዕድ አምላክ አትስገድ፣ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝና ከግብጽ ምድር ያወጣውህ አለ እግዚአብሔር” ብሏል:: መዝ. ፹፩÷፱ አንድ አድርጎ በአንድ አንቀጽ “አነ አምላክከ” አለ እንጅ፤ ከሦስት ከፍሎ አብዝቶ “ንሕነ አማልክቲከ” አላለም፤ ሙሴም በኦሪት:- ንባብ:- “ስማዕ እስራኤል ፩ እግዚአብሔር አምላክከ”:: ትርጉም:- “እስራኤል እግዚአብሔር አምላክህ አንድ እንደሆነ ስማ ዕወቅ” ብሏል:: ዘዳ ፮÷፬ ጌታም በወንጌል ንባብ:- “አነ ወአብ ፩ ንሕነ” ትርጉም፦”እኔና አብ አንድ ነን” ብሏል:: ዮሐ ፲:፴  ዳግመኛም ንባብ:- “ለግብርየ እመኑ አንትሙ፤ ከመ ታእምሩ ወትጠይቁ፤ ከመ አነ በአብ፣ ወአብ ብየ” ትርጉም:- “በሥራየ እመኑ ታውቁ ትረዱም ዘንድ፣ አብ በእኔ እንዳለ፤ እኔ በአብ” ብሏል ዮሐ ፲÷፴፰:: ይህ ሁሉ ቃል መለኮትንና አምልኮትን ከሦስት የማይከፍል ሦስቱን አካላት የሚያዋሕድና የሚያገናዝብ እንደሆነ የሚያስረዳ ነው:: ይህንም የመሰለ በየአንቀጹ የተነገረው ብዙ ነው፤ ነገር ግን ሁሉን ልንጽፈው አይቻለንምና ከባሕሩ ገብቶ በየአንቀጹ መመልከት ነው::
ይቀጥላል፡፡
ይቆየን፡፡

No comments:

Post a Comment