Thursday, May 25, 2017

ለቤተክርስቲያናችን ዘበኞች ራሳችን እንሁን!



© መልካሙ በየነ

ግንቦት 17/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ቤተ ክርስቲያናችን ይህን ያህል ዘመን ስትኖር በፈተናዎች አልፋ ነው፡፡ አርዮስ ወልድ ፍጡር ብሎ በመነሣቱ አልተናወጠችም እለ እስክንድሮስን ወልዳለችና፡፡ ቀጥሎም መቅዶንዮስ መንፈስ ቅዱስ ሕጹጽ ብሎ ተነሣ በዚህም አልተናወጠችም  ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙን፣ ኔክታሪዎስን እና  የእስክንድርያው ጢሞቴዎስን ወልዳለችና፡፡ ንስጥሮስ ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ አይደለችም ወላዲተ ሰብእ ናት በማለቱ ቤተክርስቲያናችን አልተናወጠችም ቄርሎስን ወልዳ አሳድጋለችና፡፡ ልዮን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ባሕርይ አንድ አካል ነው በማለቱ ቤተክርስቲያናችን አልተናወጠችም ጥርሱን ለውልቃት ጽሕሙን ለመነጨት ቆርጦ ለሃይማኖቱ ተጋዳይ የሆነ ዲዎስቆሮስን ወልዳለችና፡፡ እንግዲህ በእነዚህ ሁሉ ዘመናት ፈተናዎች ከቤተክርስቲያናችን አልራቁም ነበር፡፡ ዛሬ እዚህ ቦታ እንዲህ ተደረገ እዚህ ቦታ እንዲህ ተፈጠረ ስንል አዲስ የቤተክርስቲያናችን ፈተና ነው ብለን አይደለም፡፡ ትንቢቱ መፈጸሙ ግድ ነው ትንቢቱ ሐሰት አይደለምና ታዲያ ለበጎቻቸው ግድ የማይላቸው እረኞች እንደሚነሡ የተነገረ ትንቢት ነው፡፡ በእውነተኛ አባቶች ተመስለው ሊነጥቁን የሚመጡ እረኛ መሳዮች እንዳሉ መጽሐፉ ነግሮናል፡፡ ሐሳዊ መሲህ እንደሚነሣ እኔ ክርስቶስ ነኝ በማለት የተመረጡትን እንኳ እስከ ማሳት የሚደርስ ልዩ ልዩ ምትሐታዊ ተአምራትን እንደሚያደርግ የተነገረ ነገር ነው፡፡ ታዲያ ትንቢቱ መፈጸሙ እንደማይቀር የተረዳ የታወቀ ነው፡፡ እኛን ግን ያንገበገበን ይህ ትንቢት በእኛ ዘመን በመፈጸሙ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በፊት አይተነው የማናውቀውን እንግዳ ነገር እየተመለከትንም ስለሆነ ነው፡፡ የልማቱ እና የጥፋቱ፣ የጽድቁ እና የኩነኔው፣ የእውነቱ እና የሐሰቱ መሸጋገሪያ ዘመን ላይ መሆናችን ብቻ ነው የሚያብሰለስለን፡፡
በጣም የምናከብራቸው በጣምም የምንወዳቸው ጳጳሳት እና ሊቃነ ጳጳሳት እነ አቡነ ቀሌሜንጦስ፣ እነ አቡነ ቀውስጦስ፣ እነ አቡነ እስጢፋኖስ፣ እነ አቡነ ቄርሎስ እነ አቡነ ገብርኤል ወዘተ የዚህ ትንቢት ሰለባዎች የሆኑ ይመስለኛል፡፡ የተመረጡትን እስኪያስቱ ድረስ ድንቆች ተአምራትን ያደርጋሉ እንዳለ ወንጌል፡፡ የተመረጡት የተባሉት እነዚህ ናቸው ዛሬ ግን እረኝነታቸውን ወደ ጎን ትተው  ከበጎቻቸው ጋራ ፍጥጫ ላይ ናቸው፡፡ ለተሐድሶዎቹ የእግር እሳት ሆነውባቸው የነበሩት አቡነ ቀውስጦስ በዚህ ሁኔታ መገኘታቸው የሚያሳዝነኝ ሲሆን አምላክ ወደ ልቡናቸው እንዲመልሳቸውም ለእኔ ከማልቀስ ውጭ ሌላ አማራጭ ያለ አይመስለኝም፡፡ እርሳቸው ማለት እኮ በመናፍቃኑ ዘንድ በቅጽል ስማቸው “ቀውስ” “ጦስ” ተብለው ነበር የሚጠሩት፡፡ አዎ ለመናፍቃኑ “ቀውስ” ነበሩባቸው ምን ቀውስ ብቻ “ጦስ” ም እንጅ፡፡ ታዲያ ዛሬ ያ የእረኝነት ተልእኳቸው የት ገባ? የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ላይ ችግሮች እንዳሉ ብዙዎች ጽፈዋል ብዙዎችም ተችተዋል፡፡ እኔ ግን ከጅምሩ ስህተት ነው የምለው ሲኖዶሱን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለማድረግ የሚያስችላቸውን ህግ ባወጡበት ጊዜ ነው፡፡ ኤጲስ ቆጶሳት ሲመለመሉ በየክልሉ ኮታ መሰጠቱ በራሱ ችግር ፈጣሪ ነበር፡፡ ለሸዋ፣ ለጎንደር፣ ለጎጃም፣ ለጋምቤላ፣ ለኦሮምያ ወዘተ የሚለው ኮታ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካልሆነ በቀር ለሲኖዶሳችን ተገቢነቱ ጥያቄ ውስጥ ነው፡፡ ይህ በሰውነት አስተሳሰብ እንጅ በእግዚአብሔርነት አስተሳሰብ ላይ ያልተመሠረተ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ጵጵስና የብሔር ተዋጽኦ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በእግዚአብሔር ምርጫ ላይ የተመሠረተ መሆን ነበረበት፡፡ የቀደሙ አባቶቻችን በሠሩልን ሕግ እና ሥርዓት መሠረት ለዚህ ለከበረው መዓርግ ብቁ የሆኑትን ኤጲስ ቆጶሳት ለእግዚአብሔር ማቅረብ ተገቢ ነው፡፡ እነዚህ የሚቀርቡት ኤጲስ ቆጶሳት ግን ከአንድ ክልልም ሊሆኑ ከአንድ ሰፈርም ሊሆኑ ይችላሉ እርሱ ችግር ስላልሆነ፡፡ ይህን የምላችሁ በእውነተኛዪቱ እምነት ህግና ሥርዓት ጵጵስና ተጨማሪ አደራ እንደሆነ እና ለዚህ አደራ ብቁ አይደለሁም ብለው በሚሸሹበት ዘመን ሆኘ ነው፡፡ ጵጵስናን ለተጨማሪ “ቢዝነስ” መጠቀም የሚፈልጉ ሰዎች በበዙበት እና ለምን እኔ አልተመረጥኩም በሚባልበት በዛሬው ዘመን ሆነን ካሰብነው ግን “ጎጠኝነት” የሚያስብል ነው፡፡ ሐዋርያትን እስኪ ተመልከቷቸው የትኛውን አህጉር ነው የሚወክሉት? ዮሐንስ እና ያዕቆብ ወንድማማቾች ናቸው የዘብዴዎስ ልጆች፡፡  እንድርያስና ጴጥሮስ ወንድማማቾች ናቸው፡፡ አያችሁት ከአንድ ቤትም ሁለት ሁለት መረጠ እኮ፡፡ እንደእኛ ህግ ግን መሥፈርቱን አሟላም አላሟላም የሆነ ክልልን ወክሎ እንዲመረጥ እናደርጋለን፡፡ ለዚህም የጋምቤላውን አባ ተክለ ሃይማኖትን ማንሣቱ በቂ ምስክር ነው፡፡ አምላክ ፍርዱን ይስጣችሁና! በእውነት በጋምቤላ ክልል አንድ መነኩሴ ብቻ ነው ያለ እንዴ ብቻውን እንዲወዳደር የተደረገው? ለማንኛወም ይህን ጉዳይ በዚሁ ልተወውና ወደ ርእሰ ጉዳየ ላምራ፡፡
ዘመኑ ዘመነ መናፍቃን ዘመነ ከሐድያን ነው፡፡ ክህደቱ እና ምንፍቅናው ደግሞ ከቤተክርስቲያናችን ውጭ ሳይሆን እዛው ውስጧ መቅደሷ ውስጥ ገብቷል፡፡ ታዲያ ከበሩ እስከ መቅደሱ ድረስ ቅጽረ ቤተክርስቲያናችንን የመጠበቅ ሥራ ዘብ የመቆም ተግባር መፈጸም ያለብን እኛ ብቻ ነን፡፡ ይህን ማድረግ ያለብን ደግሞ ገነት መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ብቻ ሳይሆን ታሪክም እንዳይወቅሰን ነው፡፡ እነ እለእስክንድሮስን እነ ቄርሎስን እነ ዲዎስቆሮስን በታሪካችን ውስጥ የምናነሣቸው ለቤተክርስቲያናችን አምድ ጽንዕ ምሰሶ ሆነው በዘብነታቸው ታሪካዊ ገድልን ስለፈጸሙ ስለተጋደሉ ነው፡፡ ስለዚህ መልካሙን ገድል ስለቤተክርስቲያናችን ስንል ልንፈጽም ይገባናል፡፡ አመጣጣቸው እኛን በእጅጉ ሊፈትን በሚችል መልኩ ነው፡፡ ቀሚሳቸውን ለብሰው አስኬማቸውን ጭነው ቅናተ ኀቄ ታጥቀው መስቀላቸውን ጨብጠው ነው፡፡ ምንም ይሁን ምን ግን ተኩላ በበግ ቆዳ ተሸፍኖ ስለመጣ ብቻ በግ ሊባል አይችልም፡፡ መስቀሉ፣ ቆቡ፣ ቅናቱ፣መቋሚያው፣ ቀሚሱ ወዘተ ሁሉ ነገር ገበያ ላይ በስፋት ይሸጣል፡፡ ስለዚህ ማንም ገዝቶ ሊጠቀምበት እንደሚችል ጠንቅቀን ልናውቅ ይገባናል፡፡ ለእናታችን ቅድስት ቤተክርስቲያን ዘብ እንቁምላት ብለን ከተነሣን ከዚህ እንጀምር፡፡ በቀሚሳችን አይቀልዱብን፣በአስኬማችን አይነግዱብን፣ በመስቀላችን አያስመስሉብን ሁሉም ንብረቶቻችን ክብር ይኑራቸው፡፡
ይህንን የተሐድሶአውያኑን ቀስት በዘብነታችን መመከት የምንችለው በምን መልኩ ነው የሚለውን ጉዳይ አጥርተን እንመልከተው፡፡ ዘብነታችን ምን መልክ መያዝ አለበት ካልን፡-
v  ዘብነት 1. ሁሉም የአብነት ትምህርትን በሚችለው አጋጣሚ ሁሉ መማር አለበት፡፡ የሚችል ሰው ጉባዔ ቤት ገብቶ ሁሉንም የቤተክርስቲያናችን እውቀት ማወቅ አለበት፡፡ ያልቻለ ሰው ደግሞ ዘመናችን ቴክኖሎጅው የተራቀቀበት ዘመን ስለሆነ ሁሉንም የአብነት ትምህርቶችን በድምጽም ሆነ በምስል እየቀረጸ ከቤቱ ቁጭ ብሎ ጊዜ ሰጥቶ ማጥናት እና መማር ይችላል፡፡ ያጠናውን ነገር በአግባቡ መያዙን ለማረጋገጥ ከአብነት መምህራን ጋር ተገናኝቶ ስህተቱን በማረም ሙሉ መሆን ይቻላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ማኅበረ ቅዱሳን በሚያቀርባቸው የአብነት ትምህርቶች ውስጥ በመሳተፍ ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም መማር ይቻላል፡፡ አሁን ድራማ ፊልም ጨዋታ ምናምን የሚባል አሸንክታብ ጥለህ መገኘት አለብህ፡፡
v  ዘብነት 2. በነጻ ማገልገል፡፡ ይህኛው ዘብነት ዘብነት 1 በኋላ የሚመጣ ጸጋ ነው፡፡ የአብነት ትምህርቶችን ከተማርክ በኋላ ክህነት ማምጣት ከቻልህ ክህነት ታመጣለህ ማምጣት የማትችል ከሆነ ግን ትምህርትህን ብቻ ይዘህ ቤተክርስቲያን ውስጥ ትገባለህ፡፡ ታዲያ አገልግሎትህ ፍቅረ ንዋይ የሌለበት ለነፍስህ ብቻ ብለህ ይሁን፡፡ በቃ በነጻ አገልግል፡፡ በነጻ ማገልገል ስትጀምር ለ ”ቢዝነስ” ብሎ ቆቡን ያጠለቀው መሸሽ ይጀምራል፡፡ የምንኩስናው ቦታ ከተማ እንዳልሆነ መረዳት ይጀምራል፡፡ የምንኩስናው ቦታ በጾም በጸሎት የሚታገሉበት በረኃ ነው፡፡ እዚያ የአራዊቱን ድምጽ ፈርቶ የአጋንንቱን ፈተና ሸሽቶ ከተማ ለከተማ ቀሚሱን እያዝረከረከ የሚዞረውን አስመሳይ መነኮስ ሁሉ ቀልብ ያስገዛልሃል፡፡ በቃ አገልግሎት በነጻ ይሁን፡፡ ጳጳስም በለው የመምሪያ ኃላፊም በለው ሥራ አስኪያጅም በለው ቀዳሽም በለው ምንም በለው ምን በነጻ ያለገንዘብ አገልግል ተብሎ የነጻ አገልግሎት መስጠት ከተጀመረ ያን ጊዜ ቆቡን እየጣለ አዲስ “ቢዝነስ” ይጀምራል፡፡ ቤተክርስቲያናችንን ለቅቆ ይሄድልናል፡፡ ለአገልግሎት ሳይሆን ለፊርማ ብሎ ሰዓታት እና ማኅሌት የሚቆመው፣ ኪዳን የሚያደርሰው ቅዳሴ የሚቀድሰው ሁሉ በነጻ አገልግል ሲባል በሉ ደህና ሁኑ ብሎ ከቤታችን መውጣት ይጀምራል፡፡  
v  ዘብነት 3. የያገባኛልነት ስሜትን መላበስ፡፡ ሁሉም ሰው ለቤተክርስቲያኑ ክብር ያገባዋል ይመለከተዋልም፡፡ ስለዚህ ቃጭል እያቃጨለ ስለ ጊዮርጊስ ስለ ማርያም እያለ የስእላትን ክብር ዝቅ በማድረግ በየመንገዱ በስእላት የሚነግደውን ነጋዴ ሁሉ እያነቁ ለፖሊስ ማስረከብ አለብን፡፡ የቤተ ክርስቲያን ማሰሪያ ተዘከሩን እያለ ተሰርተው በተመረቁ አብያተ ክርስቲያናት ሳይቀር ለልመና መናኸሪያ ለመናኸሪያ የሚዞረውን ነጋዴ ሁሉ እያነቁ መያዝ ነው፡፡ ስእላችን ክብር ይኑረው፣ ስማችን ክብር ይኑረው፣ ለማኞች ናቸው አንባል፡፡ ይህ ይቆጨን፡፡ ባለቤት የሌላት እስከምትመስል ድረስ ሁሉም ተነሥቶ የሚነግድባት ቤተክርስቲያናችን ታሳስበን እንጅ፡፡ ሁላችንም ያገባናል ሁላችንም ይመለከተናል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ የሚባል ደንቀራ መወገድ አለበት ይመለከተናል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተሸነፈ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስህተት ሰራ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወራጅ ቀጠና ገባ ወዘተ እየተባለ ሲነገር እንዴት አይሰቀጥጠንም፡፡ ስእላትን አስፋልት ላይ አንጥፈው የሚሸጡ፣ ከደብረ ሊባኖስ ከግሸን ተባርኮ የመጣ መስቀል እያሉ በሞንታርዶ የሚጮኹብንን እያነቅን ለፖሊስ እንስጣቸው፡፡ የራሷ የቤተክርስቲያናችንን ሱቅ እንከፍትላታለን፡፡
v  ዘብነት 4.  የቶማስን እምነት መያዝ፡፡  ዘንድሮ መጠርጠር ጥሩ ነው፡፡ ቶማስ ኢየሱስ ክርስቶስን የተወጋ ጎንህን ካልዳሰስሁ አላምንም ብሎታል፡፡ በቃ! ይህ ለዘንድሮ ሰዎች ለእኛ ጥሩ ትምህርት ነው፡፡ ቀሚሱን ስለለበሰ አስኬዋውን ስለደፋ ብቻ መነኩሴ ነው ብለህ አትታለል፡፡ ውስጡን ማንነቱን ዳሰው ካልዳሰስኸው አትመን፡፡ እርሳቸው ጳጳስ ናቸው አይሳሳቱም አትበል ንስጥሮስ ፓትርያርክ እንደነበረ አትዘንጋ፡፡ እኛ ከሰበክንላችሁ ወንጌል ውጭ የሰማይ መልአክም ቢሰብክላችሁ አትቀበሉ ብሎናል ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ በቃ መልአክ መስሎ ከሰማይ ቢወርድም አንሰማም!!!
v  ዘብነት 5. ከቤተክርስቲያን አለመራቅ፡፡ ብዙዎቻችን እኔን ጨምሮ ከቤተክርስቲያን ርቀናል፡፡ መቅደሳችን ውስጥ ገብተው ሲቀድሱ ላለማየት ሸሽተኛል፡፡ ይህ ግን መፍትሔ አይደለም፡፡ ሕጓን ሥርዓቷን እንማር ሁላችንም ሰንበት ትምህርት ቤት እንግባ፡፡ ልጆቻችንን እየያዝን እንማማር፡፡ ታሪካችንን እምነታችንን እናጥና፡፡ ሥርዓቷን ሕጓን እንማር፡፡ ከዚህ የወጣ ካየን ግን እንታገል፡፡
ሌሎችን የዘብነት ባሕርያት ለእናንተ ተውኩት፡፡ ለመወያያ ያህል ስለሆነ እናንተም በየቤታችሁ ተወያዩበት፡፡ ከዚያም አስተያየታችሁን ግለጹ፡፡ እንግዲህ በዚህ መልኩ ቤተክርስቲያናችንን ልእልናዋን ማስጠበቅ አለብን፡፡ ህዝቡ ባለቤት መሆን  ዘብ መቆምም ካልቻለ ከዚህ የባሰ ነገር እንደሚገጥመን አትጠራጠሩ፡፡ ማንም የሚፈነጭባት ሆነች እኮ! ባለቤት የሌላት መሰለች እኮ! እንዴ ምንድን ነው ዝምታችን!!!

No comments:

Post a Comment