Monday, June 5, 2017

አስቸኳይ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ!


© መልካሙ በየነ
ግንቦት 22/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ


ጠፋህብን ጠፋህብን ያላችሁኝ ሁሉ አረ አለሁ ምን እጠፋለሁ! ይኼው መጣሁላችሁ፡፡ ብዙ መረጃዎች ከእጄ ላይ ገብተዋል! ያውም በድምጽ በምስል በቪዲዮ!!! አሁን ግን አስቸኳይ ስለሆነው ጉዳይ ብቻ ነው የማወራችሁ!
ብዙዎች የወንጌል አባት ናቸው በማለት ይሟገቱላቸዋል፡፡ ለምሥራቅ ጎጃም ሐገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማርቆስ፡፡ በእውነት የወንጌል አባት ናቸው በማለት የሚሟገቱላቸው ወገኖች ምናልባትም በጥቅማጥቅሞች ታጥረው የሚገኙ የሥጋ ዘመዶቻቸው አልያም በገንዘብ የመምሪያ ኃላፊ የሆኑ ሆድ አደሮች መሆን አለባቸው፡፡ የወንጌል አባት ናቸው የምትሉ ሰዎች ቆም በሉ እና ይህን ቪዲዮ ተመልከቱት፡፡ ከዚህ ቪዲዮ ላይ በዋናነት ማሳየት የምፈልገው አስቸኳዩ ነገር ሁለት ነገር ነው፡፡ አንደኛ የወንጌል አባት ናቸው የምትሉ ወገኖች ስለእስጢፋኖስ ብንማር አይገባንም በማለት ስለግብርና አንዱን አዛውንት አስነስተው ቃለ መጠይቅ ማድረጉ ትርጉሙ ምን ይሆን?
ቀጣዩ እና አስቸኳዩ ነገር ከዚህ ቃለመጠይቅ ከሚደረግላቸው አዛውንት በስተቀኝ በኩል የመጀመሪያው ሻሽ ጠምጥመው ቁጭ ያሉትን (አክሊል ከደፉት ካህን በስተግራ ያሉትን) መምህር የሚመለከት ነው፡፡
መምህሩ መምህር ሰሎሞን አሥራቴ ይባላሉ፡፡ አቡነ ማርቆስ ስለቅባት እምነት በይፋ ሲያስተምሩ መድረክ ላይ እያሉ የተቃወሙ የተዋሕዶ አርበኛ ናቸው፡፡ ታዲያ እነኚህ አባት አቡነ ማርቆስን በግልጽ በመቃወማቸው የስራ ዕገዳ ተደርጎባቸዋል፡፡ የሥራ ዕገዳው ከታች በፎቶ የምትመለከቱት ነው፡፡ ዋና ነገሩ እንዲህ ይነበባል፡፡
ቁጥር፡134.09
ቀን፡ 07/09/09
ለደ/ብ/ሠፈረ ገነት ቅድስት ስላሴ ወገብርኤል ሠ/ጉ/ጽ/ቤት
ጉንደ ወይን
ጉዳዩ፡ ከስራ እገዳን በተመለከተ
ከላይ በጉዳዩ እንደተገለጸው በናንተ ደብር (ቤተክርስቲያን) በሠባኬ ወንጌልነት ሲያገለግሉ የቆዩት መ/ር ሰሎሞን አስራቴ ከእርሳቸው የማይጠበቅ ስራ እየሰሩና ህዝቡን አስተምረው ሰላም ያሰፍናሉ ሃይማኖት ያስጠብቃሉ ሲባሉ መጽሐፍ አንዲት ጥምቀት እያለ ጥምቀት ሁለት ነው ወይም ዳግም ጥምቀትን እያስፋፉ በወረዳም ሆነ ከወረዳ ውጭ መርዝ ከሚረጩ ጋር ተባባሪ ሁነው በተጨባጭ ስለተገኙ ከግንቦት 01/09/09 ዓ.ም ጀምሮ ከአገልግሎት ስለታገዱ እናንተም ከዛሬ ጀምራችሁ ስታስገለግሉ ብትገኙ ቤቱ በሰ/ጉ/ ላይ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን እናስታውቃለን፡፡
“ከመንፈሳዊ ሰላምታ ጋር”
ግልባጭ፡ //
ለመ/ር ሰሎሞን አስራቴ
ጉንደ ወይን
ለምስ/ጎ/ሃ/ስ/ጽ/ቤት
ደ.ማ
ሊቀኅሩያን መምህር ዕዝራ አሰፋ
የጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ ቤተ ክህነት ዋና ስራ አስኪያጅ
ይላል፡፡
እዚህ ላይ ቆም ብለን እናስተውል፡፡ ይህን የእግድ ደብዳቤ የጻፈው የወረዳ ቤተ ክህነቱ ሥራ አስኪያጅ ይህን ለመጻፍ ዋና ምክንያቱ ምንድን ነው? ብለን እንመልከተው፡፡ ዋና ምክንያቱ ግንቦት 19/09/09 ዓ.ም ኆህተ ሰማይ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ወእስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ምረቃ ላይ እነኝህ መምህር አቡነ ማርቆስን በግልጽ ስለተቃወሙ ነው፡፡ ደብዳቤው የተጻፈው በ07/09/09 ዓ.ም ይላል ዕገዳው ደግሞ ከ01/09/09 ዓ.ም ጀምሮ ይላል፡፡ ነገረ ሰሪ መቸም አያምርበትም የተምታታ ነገር ሆኖባቸዋል፡፡ ተቃውሞውን ያደረጉት በ19/09/09 ደብዳቤው የተጻፈ የተባለው ደግሞ በ07/09/09 ሥራ የታገዱት ደግሞ ከ01/09/09 ጀምሮ ድብልቅልቅ ያለ ነገር!
ዋናው ነጥብ መምህር ሰሎሞን አሥራቴ ከሥራ ታግደዋል ደመወዝ ተከልክለዋል፡፡ አከራይተዋቸው የነበሩት የጉንደወይኑ መርጌታ መሠረትም ከዶርም አስወጥተዋቸዋል፡፡ አሁን ለጊዜው ከዶርም እንደተባረሩ ያረፉት ያረጋል አዱኛ ከሚባሉ እንግዳ ተቀባይ ሰው ዘንድ ነው፡፡  ስለዚህ መምህሩን በተቻለን መጠን ሁላችንም እንርዳቸው እያልኩ አስቸኳይ ስለሆነ ይህን መልእክት አስተላለፍኩላችሁ እንጅ አቡነ ማርቆስ ያስተማሩትንም ሙሉ የክህደት ትምህርት እና መምህር ሰሎሞንን ደብድቡት በጥፊ በሉት ያሉበትን መረጃ እለቅላችኋለሁ፡፡ እርሳቸውን እግር በእግር እየተከታተልናቸው ነው፡፡ አሁን ወደ ሞጣ ሂደዋል ሁላችሁም ሞባይላችሁን በአግባቡ ቅረጹበት መረጃውን ላኩልን፡፡
መምህር ሰሎሞን “አንዲት ጥምቀት” ኤፌ 4÷4 የሚለው የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ጠፍቷቸው አይደለም፡፡ አካባቢው የቅብአት እምነት የተንሰራፋበት ነው፡፡ መምህር ሰሎሞን ግን ወልድ ዋሕድ በተዋሕዶ ከበረ ብሎ የሚያምን የእነአትናቴዎስ የእነ ቄርሎስ ደቀመዝሙር የእኛ ደግሞ መምህር ናቸው፡፡ ታዲያ የቅብአት ምንፍቅናን ከልባቸው የሚጠየፉት መምህር ሰሎሞን እያስተማሩ ወልድ ዋሕድ በተዋሕዶ ከበረ ብለው ያመኑትን በፍትሀ ነገሥት አንቀጽ 3 ቁጥር 24 መሠረት ያጠምቃሉ፡፡ ተምሮ አውቆ በሃይማኖቱ እኛን መምሰል ያለበት ሰው ሁሉ ግድ ነው የእኛ ሥርዓት ይፈጸምለታል፡፡ በዚህ መሠረት ነው መምህሩ ሐዋርያዊ ተልእኳቸውን እየተወጡ የሚገኙት፡፡ አቡነ ማርቆስ ግን ይህንን ነው ዳግም ጥምቀት ሁለተኛ ተጠመቁ የሚሉ ማኅበራት አሉ በማለት ማኅበረ ቅዱሳንን በማጥላላት ላይ የሚገኙት፡፡ አባ ማርቆስ መሰላቸው እንጅ እኮ ይህ ጉዳይ የማኅበረ ቅዱሳን ጉዳይ አይደለም የእምነት የሃይማኖት ጉዳይ ነው፡፡ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን በሚያዝዘው ፍትሐ ነገሥቱ በሚለው መሠረት ይፈጸማል እንጅ ማኅበር አልያም ግለሰብ ስላለ የሚፈጸም ወይም የሚከለከል ጉዳይ አይደለም፡፡ አሁን መምህር ሰሎሞን አሥራቴን የምታውቋቸው ሁሉ በቻላችሁት መጠን እንድትረዷቸው በማሰብ ብቻ ነው ይህን መረጃ መልቀቅ ያሰፈለገኝ፡፡ መምህር ሰሎሞን አስራቴ ለአቡነ ማርቆስ ቅሬታ ሊያቀርቡ ማርቆስ ዛሬ ገብተዋል ነገር ግን አቡነ ማርቆስ በሀገረ ስብከታቸው የተነሣውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በሦስቱ እነሴዎች በመዞር ፊርማዎችንም በማሰባሰብ ላይ ስለሆኑ ማግኘት አልቻሉም፡፡ ጎንቻ! እነብሴ ሳር ምድር! ሞጣ! የደጋግ ክርስቲያኖች ቦታ! እንዲህ ዝም ብለህ የአቡነ ማርቆስን ወንጀል ስትተባበር እንዳትገኝ!!! ከነገ ጀምሮ ግን ወደ ዋናው የአቡነ ማርቆስ ሙሉ ንግግር እገባለሁ፡፡ በትእግስት ጠብቁኝ!!!
ሌላም ብዙ ሰበርም ጥግንም ዜና አለኝ፡፡
-       የአቡነ ማርቆስ መኪና በአንድ ግርማ እስቲያውቅ በሚባል አእምሮ በሽተኛ በሹፌሩ በኩል ያለው መስታወት ተመቷል፡፡
-       ዲማን የማስጠላት ሰፊ ሥራዎችን ተሠርቷል፡፡
-       ማኅበረ ቅዱሳንን የማጥላላት ሥራ ሰርተዋል፡፡
-       መምህር ሰሎሞን አስራቴን ደብድቡት ብለው መድረክ ላይ ሰብከዋል፡፡
ይህ ሁሉ በአንድ ጀንበር ግንቦት 19/09/09 ዓ.ም የተደረገ ነው፡፡ መረጃውን በቪዲዮ በማስረጃ አስደግፈን እንልካለን ይጠብቁን፡፡

No comments:

Post a Comment