Monday, June 5, 2017

“ስለ እስጢፋኖስ አይገባንም (ገ ላልቶ ይነበብ)”-- አቡነ ማርቆስ



© መልካሙ በየነ

ግንቦት 23/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ


ስለ ሊቀዲያቆናት ቀዳሜ ሰማእት ቅዱስ እስጢፋኖስ መድረክ ላይ ቆሞ መናገር አይገባም (ገ ይላላ)፡፡ ዕለቱ ዕለተ ቅዳሜ ግንቦት 19/2009 ዓ.ም ኆህተ ሰማይ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ወእስጢፋኖስ አዲስ ህንጻ ቤተክርስቲያን ምረቃ ነው፡፡ አቡነ ማርቆስ በቦታው ተገኝተዋል፡፡ በዚህ ቦታ የመገኘት ዋና ምክንያቱ ቅዳሴ ቤቱን ለመባረክ አይደለም፡፡ በምሥራቅ ጎጃም ሐገረ ስብከት የተነሣባቸውን የምእመናን ተቃውሞ ይደግፉኛል ብለው ለሚተማመኑባቸው የጎንቻ ምእመናን ለማሳወቅ ነው፡፡ እርሳቸው በሦስቱ እነሴዎች ማለትም በጎንቻ ሲሶ እነሴ (ጉንደ ወይን) በሁለት እጁ እነሴ (ሞጣ) እና በእነብሴ ሣር ምድር (መርጡለ ማርያም) እየተዟዟሩ የህዝበ ክርስቲያኑን ይሁንታ በመለመን ላይ ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት የጎንቻን ህዝብ በሙሉ ከዚህ ከሚባረከው አዲሱ ህንጻ ቤተክርስቲያን እንዲገኝ ካደረጉ በኋላ የራሳቸውን መልእክት በሚገባ አስተላልፈዋል፡፡
ስለእስጢፋኖስ ቀዳሜ ሰማእትነት ሊቀ ዲያቆንነት ብነግራችሁ አይገባችሁም በማለት ለህዝቡ ይገባዋል (ገ ይላላ) ያሉትን የግብርና ሙያ ለአንድ አዛውንት ቃለ መጠይቅ በማድረግ ሲያስተምሩ ታይተዋል፡፡  እርሳቸው የተሾሙት የግብርና ሙያን ሊያስተምሩ ነውን?  የወንጌል አባት ናቸው በማለት የሚክቧቸው ወገኖችም ወንጌል ከቀዳሜ ሰማእት ከሊቀ ዲያቆን እስጢፋኖስ ይልቅ መሬት እንዴት እንደሚታረስ አብልጦ ከመሰከረ መረጃውን አሳዩን፡፡
ካህናቱን ስለእርሻ እንዳልጠይቃቸው የእነርሱ እርሻ የምእመናንን አእምሮ ማለስለስ እንጅ መሬትን ማለስለስ አይደለም፡፡ በዚያም ላይ እግዚአብሔር በጎቸን ጠብቀሀልን ብሎ እንጅ መሬትን ስለማለስለስ አይጠይቃቸውም፡፡ ይህንን የሚጠየቁ ገበሬዎች ናቸው በማለት ነው አንዱን አዛውንት እያስጨበጨቡ የጠሯቸው፡፡ አይ የወንጌል አባት! ካህኑን ሌላ ምእመኑን ሌላ የሚጠይቅ እግዚአብሔር ነው ያለን ማለት ነው ለካ፡፡ ካህኑን ስለእረኝነቱ ገበሬውን ስለ ሞዴል አርሶ አደርነቱ ነው የሚጠይቀው ብለውን አረፉት እኮ፡፡ ብራብ አላበላኸኝም፤ ብጠማ አላጠጣኸኝም፣ እንግዳ ብሆን አልተቀበልከኝም፤ ብታረዝ አላለበስከኝም፤ ብታሰር አላስፈታኸኝም፣ ብታመም አልጠየቅኸኝም ብሎ ይጠይቃል እንጅ መሬትህን ስንት ጊዜ አረስከው ብሎ ይጠይቃል የሚል ትምህርት ተምረንም ሰምተንም አናውቅም፡፡
አዛውንቱ ሲመጡ “አጨብጭቡላቸው” በማለት ህዝቡን በማይቋረጥ ጭብጨባ እንዲያጅቧቸው አደረጉ፡፡ የሆነ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ የመጣ ነው የሚመስለው፡፡ “ተጨብጭቦላቸው አያውቅም ነበር የዓመቱን ነው ዛሬ የተጨበጨበላቸው” በማለትም ህዝቡን ፈገግ አደረጉ፡፡ ልብ በል ወገኔ ንቃ! ይህ አካሄድ የቤተክርስቲናችን አካሄድ አይደለም ሥርዓትም አይደለም፡፡ ይህ የመናፍቃን ድብቅ ተልእኮ ነው፡፡ መናፍቃኑ መድረክ ላይ ወጥተው ስለቅዱሳን ከመናገር ይልቅ የሆነ ያልሆነ ዋዛ ፈዛዛ ነገርን በመናገር በማሳቅ ጊዜን የሚያባክኑ ከንቱዎች ናቸው፡፡ እርሳቸውም ስለእስጢፋኖስ ከመናገር ከመማማር ይልቅ ስለግብርና እንማር በማለት ይህን መድረካችን ላይ መፈጸማቸው ተልእኳቸውን እንድናጤን በር ከፋች ነው፡፡ ለማንኛውም ቪዲዮውን ተመልከቱት፡፡ አስተያየታችሁንም ለግሱን!!!

No comments:

Post a Comment