© መልካሙ በየነ
ሰኔ 23/2009
ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
- በተከታታይ ሦስት ክፍሎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲን ፓትርያርኮችን ታሪክ ሳስነብባችሁ መቆየቴ ይታወቃል፡፡ ዐራተኛው ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ አምስተኛው አቡነ ጳውሎስ ስድስተኛው አቡነ ማትያስ ናቸው፡፡ ነገር ግን በዐራተኛው እና በአምስተኛው መካከል መከፋፈል ስለመጣ አቡነ መርቆሬዎስ ሳይሞቱ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ሆነው ተሾሙ፡፡ ይህም ስደተኛው እና የሐገር ውስጥ ሲኖዶስ መባባልንና መከፋፈልን አምጥቷል፡፡ በዚህም የተነሣ ታሪኩ ያን ያህል አስተማሪ እና ገንቢ ባለመሆኑ ወደ ሌሎች ሊቃውንት መሻገርን መርጫለሁ፡፡
- ከዚያ በኋላ ውይይት የሚያስፈልገውም ጉዳይ ስለሆነ አስተያየት መስጫው ላይ ሃሳባችሁን አካፍሉን፡፡
- የቅዱሱ ሊቅ ዐጽም አደጋ ላይ ነው፡፡
መልአከ ብርሃን አድማሱ ሁሉንም
ትምህርታቸውን ከዲማ ከተማሩ በኋላ በተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውረው አስተምረዋል ታላቅ ታሪክንም ፈጽመዋል፡፡ መልአከ ብርሃን በቁም
ጽሕፈት በጣም የታወቁም እንደነበሩ ይነገራል፡፡ መልአከ ብርሃን ከትውልድ ሀገራቸው ዲማ ለመጀመሪያ ጊዜ በግንቦት ፲፪ ቀን ፲፱፻፬
ዓ.ም ለቀው ደብረ ሊባኖስ ገዳም ሂደው የጻፉትን የአርባዕቱን ወንጌል ንባብ በዚያ ሸጠው ለስንቃቸው እና ለጉዟቸው የሚሆን ገንዘብ
ይዘው ወደ አዲስ አበባ አቀኑ፡፡
አዲስ አበባ ቅድስት ሥላሴ
ቤተክርስቲያን አካባቢ ከነበሩት ወልደ ሥላሴ ከሚባሉት የብሉይ ኪዳን
መምህር ዘንድ ትርጓሜ ዳዊትን፤ መጻሕፍተ ሰሎሞንን እና ትንቢተ ኢሳይያስን ከቀጸሉ በኋላ በወጡ በዓመታቸው ወደ ትውልድ
ሀገራቸው ዲማ በግንቦት ወር በ፲፱፻፭ ዓ.ም ተመለሱና ከመምህር ወልደ
ጊዮርጊስና ከመምህር እንግዳሽት ዘንድ ቅኔና ልዩ ልዩ መጻሕፍትን ተምረዋል፡፡ ከዚያም ወደ ደሴ በ፲፱፻፮ ዓ.ም ሄደው ከመልአከ
ገነት አፈወርቅ ፍትሐ ነገሥትን እንዲሁም ከቀለም ቀንዱ መምህር አካለ ወልድ ዘቦሩ ሜዳ ዘንድ በመሄድ ሐዲሳትንና መጻሕፍተ ሊቃውንትን
ተማሩ፡፡ ከዚያም በ፲፱፻፱ ወደ ጎጃም ደምበጫ ተመልሰው ከብሉዩ ሊቅ
ከመምህር አለቃ ገብረ ኤልያስና ከቅኔው ሊቅ ከመልአከ ሰላም ገብረ ማርያም ዘንድ ብሉያቱን ሲቀጽሉ ቅኔውን ሲያስፋፉ እስከ ፲፱፻፲፰ ዓ.ም ድረስ በዚያ ቆዩ፡፡
ከዚህ በኋላ ወደ ትውልድ
ሀገራቸው ዲማ በመመለስ እስከ ፲፱፻፳፬ ዓ.ም ድረስ በቅኔ መምህርነት ሲያገለግሉ ቆዩ፡፡ መልአከ ብርሃን እስከዚህ ዘመን ድረስ
መተዳደሪያቸው መጻሕፍትን በቁም ጽሕፈት በማዘጋጀት እርሱን በመሸጥ በሚያገኙት ገንዘብ ነበር፡፡ በ፲፱፻፲፰ ዓ.ም አካባቢ የልጆቻቸውን
እናት ወ/ሮ አለሚቱ እሸቴ (በኋላ እማሆይ አለሚቱ እሸቴ) ን አግብተው ሰባት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ ከዚህ በኋላ በ፲፱፻፳፭ ዓ.ም
ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው በዚያ መኖር ጀመሩ፡፡
************************************************************
የመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ታላላቅ ሥራዎች፡-
*************************************************************
- ቤተክርስቲያናችን በመናፍቃን ስትደፈር እንደ ውርደት ይቆጥሩት ስለነበር ሌላው ዝም ቢል እንኳ እኔ ግን ዝም አልልም በማለት አቶ ዘመንፈስ የተባለ መናፍቅ “ተግሳጽና ምክር” በሚል ምንፍቅናውን ሲዘራ “ኰኲሐ ሃይማኖት”ን ዳግመኛም ዶ.ር አባ አየለ ተክለሃይማኖት የተባለ ካቶሊካዊ መነኩሴ “የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ስለ ክርስቶስ ባሕርያት የምታምነው ትምህርት” ብሎ ክህደትን ሲጽፍ “መድሎተ አሚንን” በመጻፍ ተገቢውን ምላሽ በመስጠት እንዲያፍሩ አድርገዋል፡፡ በዚህም በተለይም በመድሎተ አሚን የካቶሊካውያኑ ቅርንጫፎች የሆኑትን “ቅብዐትን” እና “ጸጋን” ድራሻቸው እንዲጠፋ በማድረጋቸው ታሪክ ሲዘክራቸው ይኖራል፡፡ ነገር ግን በመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ መልስ የተቀበሩትን እነዚህን ምንፍቅናዎች ዛሬ በአዲስ መልኩ በአቡነ ማርቆስ እንዲያንሰራሩ ተደርጓል፡፡
- የመጨረሻ ልጃቸውን “ምኅርካ ክርስቶስ አድማሱን” ከሞት አስነሥተዋል፡፡ ትናንት የነበርህ አምላክ ዛሬም እንዳለህ አምናለሁ፡፡ “አዝዝ በቃልከ ይሕየው ወልድየ ፤ ልጄ እንዲድን በቃልህ እዘዝ” በማለት ነበር ልጃቸውን ከሞት ያስነሡት፡፡ ይህ ሙትን የማንሣት ቅድስና በአንድ ጀንበር የሚመጣ እንዳልሆነ የታወቀ ነው፡፡ ምርጥ የጸሎት አባት ሊቅ ቅዱስ እንደሆኑ በዚህ መረዳቱ አይከብድም፡፡
- ጥሩ የንባብ ችሎታ ነበራቸው፡፡ መልአከ ብርሃን ምግብ እየተመገቡ እንኳ በአንድ እጃቸው መጽሐፍ ይዘው ያነብቡ ነበር፡፡ “እባክዎ ዓይንዎ ይጎዳል” ሲሏቸውም “ለመጽሐፍ መመልከቻ ያልሆነ ዓይን ይፍረጥ” ይሉ እንደነበር ይነገራል፡፡ የሚገርመው ነገር መልአከ ብርሃን አድማሱ ለንባብ የሚመች የተለየ ቦታ ሳይኖራቸው ሳሎን ላይ ቁጭ ብለው በተመስጦ ያነብቡ ነበር፡፡ በጣም የሚያዘወትሩት የሃይማኖት መጻሕፍትን ቢሆንም የታሪክ እና የምርምር ጽሑፎችን የግለሰብ ታሪክ መዛግብትን ልብወለዶችንም ያነቡ ነበር፡፡
- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከራሷ ልጆች ሊቃነ ጳጳሳትን መሾም አለባት፡፡ ከግብጽ በሚመጡ ሊቃነ ጳጳሳት አገልግሎታችንን መፈጸም አልቻልንም፡፡ በቋንቋችን የሚያስተምሩ ሊቃነ ጳጳሳትን ከሐገራችን ልጆች መሾም አለብን የሚለውን ታላቁን ሀሳብ ከማመንጨት ጀምረው ጉዳዩን ዳር እስከማድረስ ድረስ ታላቅ የሆነ ተጋድሎን ፈጽመዋል፡፡ ይህም ተጋድሏቸው ዛሬ ፍሬ አፍርቶ ከመጀመሪያው ፓትርያርክ አቡነ ባስልዮስ እስከ አሁኑ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ድረስ ደርሷል፡፡
- በቤተክህነቱ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳድር ላይ በመማክርት አባልነት አገልግለዋል፡፡ ከዚያም ይህ አስተዳድር ቀርቶ በመልአከ ብርሃን አድማሱ የታሪክና ድርሰት ክፍል ሹም የሊቃውንት ጉባዔ ፕሬዝዳንት በመሆን አገልግለዋል፡፡
- በ፲፱፻፵፱ ዓ.ም - ፲፱፻፶፱ዓ.ም በንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነው ተሹመው በቤጌ ምድር፣ በወሎ እና በትግራይ ጠቅላይ ግዛቶች በመዘዋወር ከባድ እና አስቸጋሪ የሚባሉትን የፍርድ ውሳኔዎች ሁሉ በሚገባ ያለ አድልዎ በቀላል ጥበባዊ ዘዴ ወስነዋል፡፡ ከዚህም አገልግሎታቸው በኋላ በ፲፱፻፶፱ዓ.ም በጥሮታ ከዚህ ሥራ ለቅቀዋል፡፡
- በልዩ ልዩ ድርጅቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ በኢትዮጵያ ሬዲዮና በብሥራተ ወንጌል ሬዲዮ ጣቢያዎች እየተገኙ መንፈሳዊ ትምህርቶችን ያስተላልፉ ነበር፡፡ ከተለያዩ አቅጣጫዎችም የሚቀርቡላቸውን ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች በመመለስም ይታወቃሉ፡፡
- በጠቅላይ ቤተ ክህነት መጽሐፍትን እንዲመረምሩ እና እንዲተረጉሙ፣ በቤተክርስቲያናችን የሚነሡትን ዐበይት ችግሮችም እንዲመለከቱ ከጥሮታ በኋላ ወደ ጠቅላይ ቤተክህነት ተጠሩ፡፡ በዚህም አጋጣሚ ብዙ ሊቃውንትን የማግኘት እድሉን አገኙ፡፡ የኢትዮጵያ ሊቃውንት ታሪክ አልባ እንዳይሆኑ ሥራቸውም ተቀብሮ እንዳይቀር በማሰብ እነርሱን የሚዘክር መጽሐፍ “ዝክረ ሊቃውንት” በሚል ለኅትመት አብቅተዋል፡፡ ይህ መጽሐፍም የታተመው እርሳቸው ከዐረፉ በኋላ በ፲፱፻፷፫ ዓ.ም ነው፡፡
- ስለኢትዮጵያ ባህልና ታሪክ ጥናትና ምርምር ለሚያደርጉ ሰዎችም የበኩላቸውን ከፍተኛ ድጋፍ ያደርጉ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት “የኢትዮጵያ የጥንት ቅርስ ጥበቃ ድርጅት” ባደረገው እንቅስቃሴ ላይ ተሳትፈው በጎጃም ጠቅላይ ግዛት አካባቢ ባሉ አድባራትና ገዳማት ያሉ መጻሕፍትን በድርጅቱ ከሚጠበቀው በላይ መረጃውን በማሰባሰብ አቅርበዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር በየአብያተ ክርስቲያናቱ የሚገኙትን መጻሕፍት በማይክሮ ፊልም በሚያነሣበት ወቅት በጎጃም ጠቅላይ ግዛት በብቸና አውራጃ ያሉትን ምርጥና ጥንታውያን መጻሕፍትን በማስነሣት በኩል ከፍተኛ ሚና ነበራቸው፡፡ በዚህም ሥራ ተሳታፊ ነበሩ፡፡
- በዐቢይ ጾም ወቅት በኢትዮጵያ ሬዲዮ በመገኘት ተከታታይ ትምህርቶችን ሰጥተዋል ይህ ተከታታይ ትምህርታቸውም “ሐዲስ ሰውነት” በሚል መጽሐፍ ታትሟል፡፡
- መጻሕፍትን መመርመር ይወዱ ነበር፡፡ መጻሕፍትን ዝም ብለው ከመቀበል ይልቅ የያዙትን ፍሬ ነገር በሚገባ መረዳትን ይመርጡ ስለነበር ያገኙትን ሁሉ መጽሐፍ መመልከት ይወዱ ነበር፡፡ በዚህም በጣም አስቸጋሪ እና በቀላሉ ለመረዳት የሚከብዱ ቃላትን በመተርጎም ይታወቁ ነበር፡፡ ለዚህም መድሎተ አሚንን እና ኮኩሐ ሃይማኖትን ያነበበ ሰው ሁሉ ምስክር ይሆናል፡፡
- ዲማ ጊዮርጊስ ለተቋቋመው የጀግኖች ማኅበር አባል ሆነውም አገልግለዋል፡፡
- ትጉህ፣ ትእግስተኛ፣ ለቤተክርስቲያን ተቆርቋሪ፣ የጸሎት አባት፣ ቅድስናን ከሊቅነት ጋር ያስተጻመሩ፣ ለሚጠይቃቸው ሁሉ መልስ የሚሰጡ ታላቅ አባት፣ አስተዋይ፣ ሐገር ወዳድ፣አርቆ አሳቢ፣ በጥልቀት መርማሪ፣ እግዚአብሔርን ፈሪ፣ ሰውን አክባሪ፣እውነትን ደፋሪ፣ ሰውን ሁሉ አስደሳች፣ የሰውን ክብር ጠባቂ ነበሩ፡፡
- ታዋቂውን ሊቅ አለቃ አያሌውን ወደ አዲስ አበባ ወስደው በማስተማርም ለቤተክርስቲያናችን ሌላ እርሳቸውን የሚተካ ታላቅ ሊቅ አበርክተዋል፡፡ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ የታላቁ ሊቅ አለቃ አያሌው አጎታቸውም ናቸው፡፡ ስለ አለቃ አያሌውም በትህትና ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ሲናገሩ “እኔን ማንም ይተካኛል እኒህን ዓይነ ሥውር ሊቅ ግን ተንከባከቧቸው እርሳቸውን የሚተካ መምህር ወደፊት አይገኝምና” እንዳሉም ይነገራል፡፡
*************************************
የተሰጣቸው መዓርግ እና ሹመት፡-
*************************************
- በአቡነ ፊልጶስ ተመርጠው አድማሱ ጀንበሬ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀበሉት ሹመት “መጋቤ ምሥጢር” የሚል ነበር፡፡ ይህ የሹመት ስም ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጣቸው ለአድማሱ ጀንበሬ ሲሆን ሹመቱ በእንደዚህ ዓይነት ሰው መጀመሩ ዕድለኛ የሆነው ተሿሚው ሳይሆን ራሱ ሹመቱ ነውም ተብሏል፡፡ ይህ ሹመትም ለመጀመሪያ ጊዜ ለእርሳቸው ከተሰጠ በኋላ ሌሎችም እየተጠቀሙበት ይገኛል፡፡ ከአድማሱ ጀንበሬ በፊት “መጋቤ ምሥጢር” የሚል ሹመት የለም ነበር ማለት ነው፡፡
- በ ፲፱፻፳፯ ዓ.ም ደግሞ በንጉሠ ነገሥቱ መልካም ፈቃድ የተቀበሉት ሁለተኛው ሹመት “ሊቀ ጠበብት” የሚል ነበር፡፡ ይህን ሊቀ ጠበብትነት መዓርግ ይዘው ከአዲስ አበባ ወደ ሀገራቸው ዲማ ተመልሰዋል፡፡
- በ ፲፱፻፴፫ ዓ.ም ደግሞ በታላቁ ብቸና ጊዮርጊስ “መልአከ ብርሃን” ተብለው ተሾሙ፡፡ እስካሁንም ድረስ የሚጠሩት በዚሁ ስማቸው ነው፡፡ በመጽሐፎቻቸውም ውስጥ የሚጠቅሱት ይህንኑ መዓርግ ነው፡፡
መልአከ ብርሃን ተብለው የተሾሙበት ብቸና ጊዮርጊስ ደብር |
*****************
ዜና እረፍት፡-
*****************
መጋቤ ምሥጢር ሊቀ ጠበብት
መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ የሀገራችንን ሊቃውንት ስም ለማስታወስ እና ሥራቸው ከመቃብር በላይ እንዲሆን ለማድረግ እንቅልፍ
አጥተው ታሪከ ሊቃውንትን አሰባስበው “ዝክረ ሊቃውንት” የተሰኘው መጽሐፋቸውን በማዘጋጀት ላይ ሳሉ ነበር በድንገተኛ የአእምሮ ድካም
(ስትሮክ) ሀምሌ ፳፬ ቀን ፲፱፻፷፪ ዓ.ም ይህ መጽሐፋቸው ሳይታተም ያረፉት፡፡ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ ቤተሰቦቻቸው
እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበትም በእግዚአብሔር ወልድ ቤተክርስቲያን ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡ “ፍሬ ሊቃውንት” የተባለው
የማኅበረ ቅዱሳን መጽሐፍ ግን ቀብራቸው ቅድስት ሥላሴ ተፈጽሟል ይላል፡፡ ይህ ሊታረም የሚገባው ይመስለኛል፡፡
ታላቁ ሊቅ አለቃ ተገኝ ታምሩ
ዘደብረ ኤልያስ በመልአከ ብርሃን አድማሱ ፵ ቀን መታሰቢያቸው ላይ ይህንን ግጥም አስፍረዋል፡፡
ታላቁ ሊቅ አለቃ ተገኝ ታምሩ ዘደብረ ኤልያስ በመልአከ ብርሃን አድማሱ ፵ ቀን መታሰቢያቸው ላይ ይህንን ግጥም አስፍረዋል፡፡ |
==========================
“ቤተክርስቲያን
ሆይ ኦርቶዶክሳዊት፣
ጠበቃሽ
ተረታ ሐምሌ ሃያ አራት፡፡
መጋቤ
ምሥጢራት የሊቆቹ ዋልታ፣
መልአከ
ብርሃን መዓርገ ጌታ፣
ትምህርትን
ጋባዡ በሰፊ ገበታ፣
የመጻሕፍት
ምንጭ ማፍለቅ እማይገታ፣
አንደበተ
ዕንቁ አፈወርቅ አለኝታ፣
የህግ
መሐንዲስ የሃይማኖት ካርታ፣
ለተጋፊው
ሁሉ መናፍቅ ወስላታ፣
በሚያስደንቅ
ትግል እንዲያ ሲበረታ፣
በሐምሌ
ሃያ አራት ደከመው ተረታ፡፡”
==========================
***********************************************
መካነ መቃብራቸው አሁን ያለበት ሁኔታ፡-
************************************************
እኒህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ
ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ኩራት ዐይናማው ሊቅ የተቀበሩበት ቤተ ክርስቲያን ቅጽር ግቢውን አስተካክላለሁ በሚል ሃሳብ ከዐረፉ ከ፵፯
ዓመት በኋላ የሊቁን መካነ መቃብር አፈራርሶታል፡፡ በዚህም የተነሣ ዐጽማቸው በአደባባይ መውጣቱ የማይቀር ነው፡፡ በእውነት ለእነኝህ
ለራሳቸው ላልኖሩ ስመ ጥር ሊቅ ይህ ነበር ወይ የሚገባቸው? አሁን በቦታው የተመለከቱት ሰዎች እንደሚነግሩን ከሆነ መቃብራቸው ፈራርሶ
ከወሰዳችሁ ውሰዱልን ካልወሰዳችሁ ግን እኔ ራሴ ወዲያ ብየ ሥራየን እሠራለሁ በማለት ላይ እንደሆነ ነው፡፡ መውቀስ ካስፈለገም በመጀመሪያ
ደረጃ የሚወቀሰው የቤተክርስቲያኑ የሰበካ ጉባዔ ነው፡፡ ከዚያም የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ከዚያም ወረዳ ቤተክህነቱ ከዚያም ሐገረ
ስብከቱ እያለ እስከ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ድረስ ይዘልቃል፡፡ በእውነት ለቤተክርስቲያን ሲሉ እረፍት አጥተው የደከሙት ሊቅ ይህ ነበር
ወይ ዋጋቸው? የኢትዮጵያ ሊቃውንት እንዲታሰቡ ሥራቸውም ከመቃብር በላይ ከፍ ከፍ እንዲል ሌት ከቀን ሲሰሩ አእምሯቸው ደክሞ ያረፉት
ሊቅ በእውነት እርሳቸውን የሚዘክር አንድ ሰው ይጥፋ? ምቀኝነታችን ካልሆነ በቀር በእውነት ለእኒህ ቅዱስ ሊቅ ገድል እና ተአምር
መጻፍ በስንክሳሩስ እንዲገቡ ማድረግ የለብንም ነበር ወይ? ስንክሳሩን ስታነቡ እኮ ምን እንዳደረጉ ሳይታወቅ ስማቸው ብቻ ተጽፎ
የሚገኙ ቅዱሳን አሉ፡፡ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ግን ሙት አንሥተዋል እኮ የሚታይ የሚዳሰስ የሚጨበጥ የእምነት ሥራ ነው፡፡
ገድላቸውስ ቢሆን ቀላል የሚባል ነው እንዴ? እስኪ ለቤተክርስቲያናችን ሲሉ የተጋደሉትን ከላይ የተጻፈውን ደጋግማችሁ አንብቡት፡፡
ሙት ማንሣት ተአምር አይደለም ወይ? ታዲያ እኒህ ቅዱስ ሊቅ መታወስ ሲገባቸው ከአንድ ተራ ምእመን ባነሠ መልኩ እንዲህ መቃብራቸው
ፈራርሶ የማንም መጫወቻ ሲሆን ማየትን ያህል ውርደት አለ ወይ? እስካሁን
ድረስ በሕይወት ሳሉ የጻፏቸውን መጻሕፍት ደጋግሞ በማሳተም የሚገኘውን ገንዘብ ማነው የሚጠቀምበት? ቤተክርስቲያናችን አይደለችም
ወይ? ከዚህ በታች በፎቶ የምትመለከቱት መጽሐፍ ከአቡነ ባስልዮስ እስከ አቡነ ጳውሎስ ድረስ ቤተክርስቲያናችን ደጋግማ ማሳተሟን
ያሳያል፡፡ አሁን በቅርቡም በአቡነ ማትያስ ዘመነ ፕትርክና ደግሞ ታትሟል፡፡ ከዚህ መጽሐፍ ሽያጭ የሚገኘውን ገቢ ቤተክርስቲያናችን
ከተጠቀመችበት ለዐጽማቸው እረፍትን ልትነሣቸው ትችላለች ወይ? በፍጹም አትችልም፡፡ ታዲያ የመታሰቢያ ሐውልት ሊሠራላቸው ሲገባ ዐጽማቸው
እንኳ እረፍትን እንዳያገኝ መቃብራቸው መፈራረስ ነበረበት ወይ? ደግሞ ነገ እኮ በኤክስካቫተር ተቆፍሮ ዐጽማቸው የማን እንደሆነ
እንኳ ሳይታወቅ ተዳፍኖ ይቀርም ይሆናል፡፡ ይህንን ዜና ግን ፈጣሪየ እንዳያሰማኝ እለምነዋለሁ፡፡
ስለዚህ አሁንም አልረፈደምና
ወደ መፍትሔው መሄድ አለብን፡፡ ዐጽማቸውን በክብር የሚያፈልስ ጠንካራ ኮሚቴ መቋቋም አለበት፡፡ ይህ ኮሚቴ ደግሞ ተወልደው ባደጉበት
እውቀትን በቀሰሙበት በታላቁ ዲማ ገዳም አባቶች መመራት እንዳለበት ይሰማኛል፡፡ የሊቁ ፍልሰተ አጽምም ወደ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከሚሆን ይልቅ ወደ ትውልድ
ሐገራቸው ወደ ታላቁ ገዳም ወደ ዲማ ቢሆን መልካም ነው እላለሁ፡፡ ዲማዎች በዚህ በኩል ያላቸውን አስተያየት እየጠየቅሁ ያለሁ ቢሆንም
ይህ ተግባር የሁላችን ነውና ለታላቁ ገዳም ለዲማም በክብር ላይ ክብርን የሚያድለው ዐጽመ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ እንደሚጠቅመው
አምናለሁ፡፡ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የደከሙት መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ቅድስናቸው እና በረከታቸው ለሁላችን ይደርስ ዘንድ ከአዲስ አበባ ወደ ጎጃም ቢመጡ ምኞቴ
ሰማየ ሰማያትን የነካ ነው፡፡ አመናችሁም አላመናችሁም ይህንን ዜና ከሰማሁ ጀምሮ እንቅልፍ የለኝም (ምንም ጠብ የሚል መፍትሔ ባላፈልቅም)
ትናንትና ደግሞ በይበልጥ እንባየን አፈሰስኩ፡፡ መድሎተ አሚንን ኮኩሐ
ሃይማኖትን ለማንበብ በጀመርሁ ቁጥር ከማለቅስ ምነው ዲማ መጥተው ከበረከታቸው በተካፈልሁ እያልሁ እመኛለሁ፡፡ አዲስ አበባዎችም
በዚህ በኩል ትብብር ብታደርጉልንና የታላቁን ጻድቅ አጽም መላ ኢትዮጵያን እየባረከ ወደ ዲማ እንዲመጣ ብታደርጉልን እላለሁ፡፡ ይህ
ኮሚቴ በቅርቡ ሥራ እንዲጀምር ለማድረግ ሊቃነ ጳጳሳትም የበኩላቸውን ትብብር ቢያደርጉ መልካም ነው እላለሁ፡፡ ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን
ከታዋቂ አርቲስቶች እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ የተቀበሩበት ቦታ ነው፡፡ በሁሉም ዘንድ የታወቀ ነው፡፡ የብዙ ሊቃነ ጳጳሳትም
አጽም በዚያ እንደሚገኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ስለዚህ መልአከ ብርሃንን ወደዚያ ማፍለስ ብዙም ጥቅም ያለው መስሎ አይታየኝም፡፡ ዲማ
በከፍታው ላይ ሌላ ከፍታን የሚጨምሩለት ሊቅ ናቸውና ፍልሰተ ዐጽማቸው ከእግዚአብሔር ወልድ ቤተክርስቲያን ወደ ታላቁ ገዳም ዲማ
መሆን አለበት ባይ ነኝ፡፡ ይህንን ፍልሰታቸውን ለመፈጸም ደግሞ በገንዘብ በኩል የማንንም እርዳታ እንደማንጠይቅ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
እስኪ ከዲማ የፈለቃችሁ የዲማ ሊቃውንትም በዚህ ሃሳብ ላይ የበኩላችሁን አስተያየት ለግሱን፡፡
***************************************************************************
ፍልሰታቸው ወደ ዲማ እንዲሆን የምምኘው ስለሚከተሉት ነገሮች ነው፡-
**********************************************************************
፩. ዲማን ይበልጥ ታዋቂ
እንዲሆን ስለሚያደርጉት፡፡
፪. ዲማ ተወልደው ያደጉበት
መንፈሳዊውን እውቀት ሁሉ የቀሰሙበት ቦታ በመሆኑ፡፡
፫. ተዳፍኖ የቀረው ታሪካቸው
በሁሉ ዘንድ ታዋቂ እንዲሆን፡፡
፬. ከአዲስ አበባ ጀምሮ
እስከ ጎጃም ዲማ ድረስ ያሉትን ቦታዎች ሁሉ በቅዱሱ ዐጽማቸው እንዲባርኩት፡፡
፭. የጎጃም ሰው ዲማ እየሄደ
ከቅዱሱ ዐጽማቸው በረከትን እንዲሳተፍ፡፡
፮. የእርሳቸውን ታሪክ እየተማረ
የጎጃም ሊቃውንት ከእውቀት ጋር የተፈተለ ቅድስናን እንዲላበሱ ስለሚረዳ፡፡
፯. ዲማ ለእርሳቸው ዐጽም
ማረፊያ ሊሆን የሚችል ለቅድስናቸውም ለሊቅነታቸውም የሚመጥን ታላቅ ገዳም በመሆኑ፡፡ እና በእነዚህ መሰል ምክንያቶች ነው፡፡
=====================================
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት #comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡
No comments:
Post a Comment