© መልካሙ በየነ
ግንቦት 28/2009
ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ተጽሕፈ እም አሐዱ ሊቅ ኢትዮጵያዊ
ኅሩይ ወመፈክራዊ
ጌታው አለቃ ኅሩይ
ክፍል ፪

ክፍል ፫
በኃይል፣ በክሂል፣ በሥልጣንም
በሚሠራ በባሕርይ ሥራ በሦስቱ አካላት መለያየት እንደሌለ የሚያስረዳ ነገር፤ ከሙታን ተለይቶ መነሣት የክርቶስ አካል ብቻ ግብር
ሲሆን፣ ማስነሣት የሦስቱ አካላት የባሕርይ ግብር ነው:: ስለዚህ ከሦስቱ አካላት ለሰው ሁሉ የሚሰጥ ሕይወት በአንድነት በሚሠራ
በባሕርይ ግብር እንደሆነ መጻሕፍት ያስረዳሉና:: ቄርሎስ:- ንባብ፦ “ ፩ ሕላዌ ዘሥሉስ ቅዱስ ኲሉ ዕበይ ወኲሉ ክብር ይደሉ ለባሕቲቶሙ፣
ወኲሉ ዘኮነ በአምላክነ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፣ ወለእመኒ ተብህለ በእንተ አብ ከመ ውእቱ ማሕየዊ፤ ዘእንበለ ኑፋቄ፤ እስመ
ለዝንቱ ግብር ወልድኒ ይገብር፤ ወዓዲ ይገብሮ መንፈስ ቅዱስ፤ ወለእመኒ ወልድ ሕይወት በእለ ይፈቅድዎ ለሕይወት፣ እስመ ኢይገብር
ዘንተ ዘእንበለ ፈቃደ አቡሁ፣ ዘይትዔረዮ፤ እስመ ቦቱ ለርእሱ ዘአብ ወላዲሁ፣ ወለሊሁኒ ይቤ ክሡተ ኢይገብር ግብረ ምንተኒ ዘእምኀቤየ
አላ እገብር ግብሮ ለአቡየ ዘሀሎ ብዬ፤ ወለእመ ተብህለ በእንተ መንፈስ ቅዱስ ከመ ውእቱ ማሕየዊ ዘእንበለ ኑፋቄ ይገብር ዘንተ
እስመ መንፈሰ ሕይወት ውእቱ፤ ንሕነሰ ንብል እስመ ሕይወት ውእቱ በህላዌሁ እግዚአብሔር አብ:: ወወልድ ዋሕድ ዘተወልደ እምኔሁ፤
በዝንቱ አምሳል ሶበ ይትበሀል ከመ አብ አንሥኦ ለክርስቶስ፣ ንሕነሰ ንረክብ ከመ ለሊሁ አንሥአ ርእሶ፣ ወይቤሎሙ ለአይሁድ ንሥትዎ
ለዝንቱ ቤተ መቅደስ ወአነ አነሥኦ በሠሉስ መዋዕል” ትርጉም፦ “በአካል ልዩ የሚሆን የሥላሴ ባሕርይ አንድ ነው፣ ፍጹም ጌትነት
ፍጹም ክብርም ለሦስቱ ብቻ ይገባል፤ ፍጥረት ሁሉ በአምላካችን በአብና በወልድ በመንፈስ ቅዱስም ተፈጠረ:: አብ ያለ ጥርጥር ያለ
መለየት ማሕየዊ እንደሆነ ምንም ቢነገር ይህን ሥራ /ማዳኑን/ ያለመለየት ወልድ ይሠራዋልና፣ ወልድም ሕይወትን በሚሹ ሰዎች የሕይወትን
ሥራ ቢሠራ በማስነሣት ሕይወት በሚተካከለው መተካከል በአካል ነው በአባቱ ፈቃድ ነው እንጅ ያለ አባቱ ፈቃድ ይህን አይሠራምና::
የወለደው የአብ ገንዘብ የእርሱ ገንዘብ ስለሆነ፤ እርሱም እራሱ በሕልውናየ ያለ አባቴ የሚሠራውን እሠራለሁ እንጅ እኔ ከራሴ ብቻ
አንቅቼ ምንም አልሠራም ብሎ ገልጾ ተናግሯልና፣ መንፈስ ቅዱስም ማሕየዊ እንደሆነ ቢነገር ያለ መለየት ይህን ይሠራል የሕይወት መንፈስ
ነውና፣ እኛ ግን እግዚአብሕር አብ በባሕርዩ ሕይወት እንደሆነ እንናገራለን:: ከእርሱ የተወለደ አንድ ልጁም በዚህ አምሳል/ማሕየዊ/
በመባሉ አብ ክርስቶስን አስነሣው ቢባል እኛ እርሱ ራሱ ራሱን እንዳስነሣ ከመጻሕፍት እናገኛለን:: አይሁድን “ይህን መቅደስ አፍርሱት
እኔ በሦስተኛው ቀን አስነሣዋለሁ ብሏቸዋልና” እንዳለ:: /ክፍል ፶ ለኀበ ነገሥት ሄራን/ ዳግመኛ:- ንባብ፦ “እግዚእነ ክርስቶስ
ያነሥአነ ለኩልነ እስመ ሕያው ውእቱ በእንተ አቡሁ እስመ ዘተወልደ እምአብ ሕያው ዘለዓለም ወበእንተዝ ደለዎ ሎቱኒ ዓዲ ይኩን ሕይወተ፤
እስመ ዘተወልደ እምሕይወት ማሕየዊ” ትርጉም፦ “ጌታችን ክርስቶስ ሁላችንን ያስነሣናል አባቱ ሕያው ስለሆነ እርሱም ሕያው ነው፤
ለዘለዓለም ሕያው ከሚሆን ከአብ ስለተወለደ ስለዚህም ሕይወት ይሆን ዘንድ ዳግመኛም ለእርሱ ተገባው፤ ሕይወት ማሕየዊ ከሚሆን ከአብ
ተወልዷልና” ብሏል:: /ክፍል ፶/ ኪራኮስም ፴፮ኛ ንባብ፦ “ንሕነሰ ፅኑዐን በጽድቅ ወንሰብክ እንዘ ንትአመን በሥሉስ ቅዱስ እለ
ሕልዋን ቅድመ፣ ወይሄልው ለዓለም፣ ንጹሐን ፫ አካላት ፍፁማን፣ ዘውእቶሙ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ ሕላዌሆሙ ወ፩ መለኮቶሙ
ወ ፩ ግብሮሙ ወአሐቲ ሥምረቶሙ ወአሐቲ ክሂሎቶሙ ሕልዋን በዘዚአሆሙ:: ወአኮ አብ በርእሱ ባሕቲቱ ዘይገብር ዓዲ አኮ ወልድ ዘይገብር
በርእሱ ባሕቲቱ ወአኮ መንፈስ ቅዱስኒ በርእሱ ባሕቲቱ ዘይገብር፣ አላ ዳዕሙ ለዘፈቀደ አብ ይፈጽምዎ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ወምግባሮሙኒ
፩ እስመ ፩ ውእቱ መለኮቶሙኒ፤ አካላት ዕሩያን በአርአያ ወአምሳል ወመልክዕ” ትርጉም፦ “በእውነት የፀናን እኛ ቅድመ ዓለም በነበሩ
ለዘለዓለም በሚኖሩ በልዩ ሦስት አካላት አምነን፣ ፍጹማን የሆኑ ሦስቱ አካላት፣ ከመለየት ከመለወጥ ንጹሐን እንደሆኑ እናስተምራለን::
እኒሁም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ናቸው:: በሕልውና አንድ፣ በባሕርይም አንድ፣ በግብርም (አምላካዊ ግብር) አንድ፣ በፈቃድም አንድ፣
ሁሉን ማድረግ በመቻልም አንድ እንደሆኑ እናስተምራለን:: /በዘዚአሆሙ/ በሚገናዘቡበት በልብነት፣ በቃልነት፣ በእስትንፋስነት በየራሳቸው፣
በወላዲነት በተወላዲነት በሠራጺነት የሚኖሩ ናቸው:: አብ በተለየ አካሉ ብቻውን ሥራ የሚሠራ አይደለም፣ ወልድም በተለየ አካሉ ብቻውን
ሥራ የሚሠራ አይደለም፤ አብ ያሰበውን ወልድና መንፈስ ቅዱስ ይሠሩታል እንጅ፣ ግብራቸውም አንድ ነውና፤ ሦስቱ አካላት በግብርና
በመመሳሰል በቅርጽም የተካከሉ ናቸው” ብሏል:: /ክፍል ፩/ ከዚህ በላይ እንደተነገረ ከሦስቱ አካላት ለዓለሙ ሁሉ የሚሰጥ የዘለዓለም
ሕይወት በአንድነት በሚሠራ ግብር ከሆነ፣ ይህን የሚያደርጉበት ኃይል ክሂል ሥልጣን ከሦስት የተከፈለ ነው ማለት አይገባምና፣ ይህን
በአስተዋይ ልቡና መመልከት ያሻል:: አንዳንድ ሰዎች በሚናገሩት በሦስቱ አካላት ላይ የሚገኝ ዕሪና ብቻ ነው እንጅ ሕልውናም ዋሕድና
/መገናዘብም አንድነትም/ አይገኝበትም ይላሉ:: እንዲህም ማለታቸው መጻሕፍት ስለ ዕሪና እና ስለ ሕልውና ስለዋሕድናም የተናገሩትን
ምሥጢር አስተውሎ ባለመመልከት ነው:: ዕሪና የሚነገር በአካል ላይ በሚወድቅ ምሥጢር ነው:: ሕልውናም የሚነገር በከዊን ላይ በሚነገር
ምሥጢር ነው:: ዋሕድናም የሚነገር ስለ ባሕርይ ነው:: ወይም ስለ ጠባይዕ በሚነገር ምሥጢር ነው:: ስለዚህ ከዚህ በላይ ዘርዝረን
ያሳየናቸውን ነገሮች ማሳሳትን የሚያመጣ ስልት ስልታቸውን ለይቶ ሳያውቁ የሃይማኖትን ነገር ማስተማር፣ መጻሕፍትንም መጻፍ ምሥጢረ
ሥላሴን ያፋልሳል:: መጻሕፍትንም ያጣላል:: ሰሚንና ተመልካቹንም ገደል ይሰዳል:: ማቴ ፲፭÷፲፬ ስለዚህ ጠንቅቆ ማስተዋል ይገባል::
የዚህን ነገር በሰፊው ልናስረዳ በቻልን ነበር:: ነገር ግን በብዙ ዘመን አንፈጽመውም:: ባስልዮስ ዘቂሣርያ:- ንባብ፦ “ወይእዜኒ
ናሕፅር ነገረ ወንፈጽም ዘንተ ክፍለ ወንኅድግ ኩሎ አእምሮ ለእግዚአብሔር ዘይመውዕ ኩሎ ግብራተ” ትርጉም፦ “ነገርን በማሳጠር ይህን
ምሥጢር ፍጹም ዕውቀትንም ሥራን ሁሉ፣ ድል መንሣት ለሚቻለው ለእግዚአብሔር እንተው” ብሎ እንደተነገረን /ሃይማኖተ አበው ክፍል
፩/ ነገራችንን በማሳጠር እንወሰን::
ይቀጥላል፡፡
ይቆየን፡፡
No comments:
Post a Comment