Wednesday, June 7, 2017

“ትኩረት የሚያሻው ሀገረ ስብከት” ምሥራቅ ጎጃም

© መልካሙ በየነ

ግንቦት 30/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ


ምሥራቅ ጎጃም ሐገረ ስብከት የጥንታውያን እና የታሪካውያን አድባራት እና ገዳማት መገኛ  የቅኔ እና የዜማ እንዲሁም የትርጓሜ መጻሕፍት መፍለቂያ ቦታም ጭምር ነው፡፡ ለዓለም ሳይተዋወቁ ዓለም በመላ የሚጎበኛቸው ከዋክብት የሆኑ ገዳማት እና አድባራትም በብዛት  ይገኙበታል፡፡ ሐዲስ ዓለማየሁ ዓለምን ባስደመመበት “ፍቅር እስከ መቃብር” መጽሐፉ ላይ  የጠቀሳቸው ገዳማት እና አድባራት የሀገረ ስብከታችን ገጸ በረከቶች ናቸው፡፡ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ተወልደው ያደጉበት  ደብረ ኤልያስ እንዲሁም የቅኔ ሊቃውንት መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ እና  አለቃ አያሌው ታምሩ ተወልደው ያደጉበት ዲማ፤ መስዋእተ ኦሪት ከተከናወነባቸው አምስቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ የሆነቸው አብርሃ ወአጽብሐ በወርቅ እና በዕንቍ አስውበው የገነቧት መርጡለ ማርያም (የማርያም አዳራሽ) ከምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት በርካታ ገጸ በረከቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን ይህ ሀገረ ስብከት ይህን ያህል የሊቃውንት መፍለቂያ ቢሆንም የጀግንነት ታሪክ በበላይ ዘለቀ በኩል የተላበሰ አርበኝነት የግሉ የሆነ ህዝብ ያለበት ቢሆንም ይህን ታሪኩን ጥላሸት የሚቀባ፡
 “ዘንድሮ ጎጃም ላይ ቅብአት ረከሰ፤
 ከራሳችን አልፎ መቅደስ ውስጥ ፈሰሰ” የተባለለት የቅብአት እምነት መኖሩ ያሳፍራል፡፡ ምሥራቅ ጎጃም ውስጥ በጥቂት ቦታዎች በአንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ  “ተዋሕዶ እና ቅብአት” የሆኑ ካህናት በአንድነት የሚያገለግሉበት ሀገረ ስብከት ነው፡፡ “ብርሃን እና ጨለማ” “እምነት እና ክህደት” “ነጭ እና ጥቁር” “መንፈስ ቅዱስ እና መንፈስ ርኩስ” “እግዚአብሔር እና አጋንንት” “ፍቅር እና ጥል” አዎ እነዚህ ሁሉ በአንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያገለግላሉ ይገለገላሉ፡፡

እስከ አሁን በነበረው የእነዚህ እምነቶች በአንድ መቆየት የጎላ ልዩነት አይታይም ነበር፡፡ “ተቀባት” እና “ተዋሐዳት” ከሚል የጨዋ ክርክር የዘለለ “ቅብአት” ማለት እንዲህ ነው የሚል ሊቅም አልነበራቸውም፡፡ በእኛ በኩል የነበሩት እነመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ግን “መድሎተ አሚን” በተሰኘው መጽሐፋቸው ለካቶሊካውያን መልስ በሰጡበት ላይ ቅባትን ከዚያ ጋር አያይዘው መልስ ሰጥተውበታል፡፡ በ1990ዎቹ አካባቢ ለፍትህ ሚኒስቴር “ሃይማኖታችን ይታወቅልን” ብለው ጥቂት የቅብአት መናፍቃን በደብዳቤ መጠየቃቸው የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን በወቅቱ  “መሥራቹ ማነው? ምን ያህል ተከታይ አለው?” ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎችን መመለስ አልቻሉም ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም “እምነታችሁ ይፈቀድላችኋል በነጻነት ማምለክ ትችላላችሁ ይህ ሕገ መንግሥታዊ መብታችሁ ነው፡፡ ነገር ግን ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምንም ነገር ይዛችሁ መሄድ አትችሉም” አሏቸው፡፡ በዚህም የተነሣ ድምጻቸውን አጥፍተው ጥቂት የሚባሉ ገዳማትን እና አድባራትን ውስጥ ለውስጥ ለመቆጣጠር ቻሉ፡፡ በተለይ በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል ደብረ ማርቆስ ወረዳ ቤተክህነት የሚያስተዳድረው አባ ዐሥራት ገዳም አንዱ ሲሆን በጎንቻ ሲሶ ወረዳ ቤተክህነት ሥር ያለው ቆጋ ኪዳነ ምህረት በሌላ ጎን ተጠቃሽ ነው፡፡

ቆጋ ኪዳነ ምህረት በዋናነት የቅባት መናፍቃን የመሸጉባት ገዳማችን ናት፡፡ ይህንን ተልእኳቸውን በመፈጸም ላይ ያሉት ገዳማውያን ነን ባዮችም ከሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ልዩ ድጋፍ የሚደረግላቸው ናቸው፡፡ ለዚህም ማሳያው “ወልደ አብ” እና “ሚሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊ” የሚሉ መጻሕፍት የታተሙት በዚሁ ገዳም ስም መሆኑ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማርቆስ ኆህተ ሰማይ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ወ እስጢፋኖስ የተባለ አዲስ ህንጻ ቤተክርስቲያን ጉንደ ወይን ከተማ ውስጥ ግንቦት 19/2009 ዓ.ም በባረኩበት ወቅት ስለ ጎንቻ ሲናገሩ “በዚህም ቢሄድ ቆጋ ነው በዚያም ቢሄድ ጎንቻ ነው” በማለት ጎንቻ የቅዱሳን መፍለቂያ ነው ሲሉ ተሰምተዋል፡፡ “እዚህ ቆጋ ጓሮ እንዲህ ያለ ጉድ” በማለትም የቅብአት እምነት አማኞችን ተጠመቁ የሚሉትን ገስጸዋል፡፡ ቆጋን ያህል ቦታ እያለ እንዴት የቅብአት እምነት ተከታዮችን ተጠመቁ ይላሉ እንዲህ የሚሏችሁን ስም ዝርዝራቸውን ስጡን በማለት በግልጽ መናገራቸው ለቅብአት እምነት ያላቸውን ድጋፍ የገለጹበት መሆኑን መረዳት አይከብድም፡፡ ስለዚህ ለቅብአት እምነት እንዲህ በይፋ በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ተቀምጠው የክህደት መጽሐፍ እንዲጽፉ ኃይል እና ብርታታቸው የሀገረ ስብከታችን ሊቀጳጳስ ለመሆናቸው ምንም ጥርጥር የለውም፡፡

ሌላው ምሥራቅ ጎጃም ልዩ ትኩረት የሚያሻው ሐገረ ስብከት ነው የምንለው ቤተክርሰቲያኒቱን በዘመድ አዝማድ ቁጥጥር ስር እንድትወድቅ ማድረጋቸው ነው፡፡ በዚህ ሀገረ ስብከት ለመቀጠር የሚያስፈልጉ መስፈርቶች በዋናነት፡
1.  ለሊቀ ጳጳሱ የሥጋ ዘመድ ሆኖ መገኘት…. ተማረም አልተማረም ተማረችም አልተማረችም፡፡
2.  በጥቅማጥቅም መቆራኘት…..ለምሳሌ ዲማን ታሪክ አልባ ለማድረግ የተጠቀሙት መምህር ላእከ ማርያም በአቡነ ጴጥሮስ ዘመነ ጵጵስና የተወገዘ ሰው መሆኑ፡፡ ይህ ሰው የመምህሩን የመምህር ዘሚካኤል ይሁኔን ሚስት የደፈረ ሰው ሲሆን በዚህም ተጸጽቶ ንስሐ ያልገባ ነው፡፡ ይህን ሰው ዲማ ላይ እንዲመደብ በማድረግ የዲማን ሰላም ነስተውት መክረማቸው የታወቀ ነው፡፡
3.  የሰፈር ልጅ ሆኖ መገኘት……ከቤት አልፎ በጣም ቢበዛ የተማሩበትን ቦታ ልጆች ይሰበስባሉ፡፡ መርጡለ ማርያም የተማሩበት ቦታ ስለሆነ ጎንቻም የተወለዱበት ቦታ ስለሆነ እነዚህ በጣም በቅርበት ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ 
4.  ገንዘብ መክፈል…..ዘመድ ካልሆንህ በጥቅማ ጥቅም ካልተቆራኘህ የሰፈር ልጅ ካልሆንህ ያለህ የመጨረሻው አማራጭ ሙስና ነው፡፡
በእነዚህ ዐራት ምክንያቶች በየአጥቢያው አለቃ እና የሰበካ ጉባኤ አባላት እያደረጉ መመደባቸው ቤተክርስቲያናችን በቅኝ ግዛት እንድትወድቅ አድርጓታል፡፡ በዚህ አሠራራቸውም አብዛኛው ምእመን ከዳር ቆሞ የሚመጣውን በጎ ዘመን በመናፈቅ ላይ ያለ ነው፡፡ ህዝቡ እና የንስሀ አባቶች ላይ ያለመግባባቶች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ በዚህም የተነሣ ልዩ ትኩረት የሚያሻው ሀገረ ስብከት ነው፡፡ አባታችን በ19/09/09 ዓ.ም “ጎንቻን ተነሥ ተደፍረሃል” እያሉ ለጦርነት ሲቀሰቅሱት መዋላቸው ሌላው አስፈሪውን የመከፋፈል ስትራቴጅ መከተላቸውን ያመለክታል፡፡ ይህንንም በቪዲዮ አድርጌ ከዚህ በፊት ይፋ ማድረጌ ይታወቃል፡፡


የምእመናንን ይሁንታ ለማግኘት አባታችን በዋናነት ትኩረታቸው “ጎጃም ተጠመቅ ተባለ” የሚለው ብሂላቸው ነው፡፡ “ዩኒቨርሲቲ የገቡ ተማሪዎች ጎጃም ስለሆናችሁ ዳግም ተጠመቁ ተባሉ” በማለት ያልተደረገውን ተደረገ ያልሆነውን ሆነ ሲሉ መክረማቸው ትዝብት ውስጥ ከቷቸዋል፡፡ እኔም አንዱ ጎጃሜ ነኝ ዩኒቨርሲቲንም አልፌበታለሁ ጎጃሜ በመሆኔ ግን ተጠመቅ ያለኝ ማንም የለም፡፡ ልብ በሉ በተለይ ኤፌ 4÷4ን ይዛችሁ “አንዲት ጥምቀት” እያለ ለምን ተጠመቁ ትላላችሁ የምትሉን  ክርስቲያኖች ነገሩን ከላይ ብቻ አትመልከቱት ገባ ብላችሁ ምሥጢሩን መመርምሩ፡፡ ኤፌ 4÷4 ላይ ያለው “አንዲት ጥምቀት” የሚለው ቃል የማይታበል ማንም የማይሽረው በማንም የማይለወጥ መለኮታዊ ቃል ነው፡፡ ተጠመቁ የተባሉት ጎጃሞች ሳይሆኑ ቅብአቶች ናቸው፡፡ ጎጃም እና ቅብአትን ለያይታችሁ ተረዱት፡፡ “ተጠመቁ ተባልን” የሚሉት ቅብአቶች አቡነ ማርቆስ በመሠረቱት “ማኅበረ ሐዋርያት” በተባለው “የደብረ ወርቅ፣ የጉንደ ወይን፣ የሞጣ እና የመርጡለ ማርያም” የቅብአት እምነት ተከታይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሰላይነት በቀረበው ሪፖርት መሠረት ነው፡፡ “ማኅበረ ሐዋርያት” ማለት እንደ ግቢ ጉባኤ ሁሉ በየዩኒቨርሲቲዎች የተዋቀረ የራሱ ዓላማ እና ርእይ ያለው ከላይ ከጠቀስኩላችሁ ዐራት ቦታዎች የተውጣጣ ነገር ግን ሁሉን የማይወክል “ማኅበረ ቅብአት” ነው፡፡ የዚህ ማኅበር መንቀሳቀሻ ገንዘብ ከብጹእነታቸው እንደሚገኝ ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡ በአጠቃላይ ጎጃም እና ቅብአት የሚለውን ለያይተን መመልከት አለብን፡፡ የዋሐንን ለመሳብ “ጎጃም ተጠመቅ” ተባለ እያሉ የሚነዙት ክፉ ወሬ ተቀባይነት የለውም፡፡

የዘመድ አዝማድ መሠብሰቢያ የሆነው ሀገረ ስብከታችን ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት ያሻዋል፡፡ እነማን ናቸው ዘመዶች የሚለውን ዝርዝር ከፎቶው ተመልከቱት (የተወሰነ የቆየ መረጃ ስለሆነ ምናልባትም የቦታ መቀያየር እና የሥልጣን እና የማዕርግ መለያየት ሊኖረው ይችላል) በሐገር ልጅነት እንደሚቀጥሩ እና ቅባትን እንደሚደግፉ ደግሞ በቪዲዮው ላይ ተመልከቱት፡፡ የሁሉ ዓይን ወደ ምሥራቅ ጎጃም ይሁን!!!
=====================================
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት #comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡

No comments:

Post a Comment