Friday, June 16, 2017

እንደ ሳሙኤል እውነትን ግለጥ!



 © መልካሙ በየነ
ሰኔ 09/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ


ቤተክርስቲያናችን  በፈተናዎች መካከል ያለፈች እንደሆነች ያልተረዱ ሰዎች አሁንም ድረስ በቪዲዮም በኦዲዮም በምስልም ማስረጃዎችን እየተመለከቱ ማመን ተስኗቸዋል፡፡ ምናልባትም እነዚህ ሰዎች፡-
   1ኛ. በቀደሙት አባቶቻችን እይታ ስለሚመለከቱ ነው፡፡ የቀደሙት አባቶቻችን ንጽሕ ጠብቀው በጾም በጸሎት ተወስነው በትህትና የኖሩ የእግዚአብሔርን እንጅ የሰውን ፍላጎት ለመጠበቅ ያላጎበደዱ ናቸው፡፡ አሁን የምንመለከተው ግን በተቃራኒው ሆኗል፡፡ ልብ በሉ አሁንም ቢሆን ግነ በቀደሙት አባቶቻችን መንገድ የሚጓዙ አባቶች አሉን፡፡ እነዚህን አባቶቻችንን አይጨምርም አሁን የምላችሁ ጉዳይ፡፡ ቀሚሳቸው፣ ቆባቸው ሲታይ ከድሮ አባቶቻችን ጋራ ተመሳሳይ ነው የለበሱት ሰዎች ግን ለየቅል ናቸው፡፡ ስለዚህ ዲያቆን ስለሆነ፣ ቄስ ስለሆነ፣ ጳጳስ ስለሆነ ወዘተ እንዲህ አይደረግም በውሸት ነው ስም ለማጥፋት ነው ወዘተ ወዘተ የሚለው አነጋገር ምናልባትም እያዩ እንዳላዩ እየሰሙ እንዳልሰሙ የሆኑ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡
ቪዲዮው አለ ምስሉ አለ ድምጹ አለ መረጃ ማለት ከዚህ በላይ ምን አለ፡፡ ቆራርጣችሁ ነው የሚልም ቪዲዮ እንዴት እንደሚሰራ የማያውቅ ሰው አለ፡፡ በእውነት ማን ይሙት እስኪ ምን ቢቆራረጥ ምን ኤዲት ቢደረግ አንድ ቪዲ ስድብ ሊሆን ይችላል፡፡ በምን መልኩ ቢቀናበር ነው የወንጌልን ትምህርት ቆራርጦ ስድብ ማድረግ የሚቻለው፡፡
2ኛ. ምን ችግር አለው እገሌስ እንዲህ ያደርግ የለም እንዴ የሚሉ ወገኖች ናቸው፡፡ ኃጢአት ዲያቆኑ ወይም ቄሱ ወይም ደግሞ ጳጳሱ ወይም ፓትርያርኩ ስለሠራት ጽድቅ አትሆንም፡፡ ኃጢአት ኃጢአት የምትሆነው ኃጢአት ስለሆነች እንጅ በሠራት ሰው የምትወሰን አይደለችም፡፡ እነዚህ ሰዎች የመጽሐፉን ሳይሆን የሚደረገውን ነገር ነው እንደትክክል የሚቆጥሩት፡፡ ምን ችግር አለው በሚል ከንቱ አስተሳሰብ ውስጥ ራሳቸውን የቀበሩ ናቸው፡፡ ምናልባትም ሳያውቁ ያለቁ ናቸው ማለት ነው፡፡
ስለዚህ የውሸት እና የአሉባልታ ተባባሪ ከመሆን ወጥተን እንዲህ አይደረግም የሚለውን የሞኝ አስተሳሰብ ትተን ቤተክርስቲያናችንን እናስከብራት፡፡ ፓትርያርኩ የፈቀዱለት አባ ኃይለማርያም እኮ ነው የዓለም ፕሮቴስታንቶችን ከነጫማቸው ክህነት የሌለው ሰው መግባት ከማይገባው መቅደስ አስገብተው በእግራቸው ያስጠቀጠቁት፡፡ ታዲያ ፓትርያርኩ ስለፈቀዱ መቅደሳችን በማንም መረገጥ አለበት ነው የምትሉ ካላችሁ የራሳችሁ ውሳኔ ነው የሚሆነው የመጽሐፉ ግን እንደዛ አይደለም፡፡ እንዲያውም የሥርዓት መጽሐፋችን እኮ “ከመናፍቃን ጋራ አትጸልይ” ነው የሚለው ታዲያ እነሱ ስላደረጉት ኃጢአት መሆኑ ይቀራልን አይቀርም፡፡ ስለዚህ በየዋኅነት እና በሞኝነት ከእነርሱ በላይ እያልን ልንበላ አያስፈልግም፡፡ እኔ ስለራሴ አንተም ስለራስህ ነፍስ ነው የምትጠየቀው ምናልባት እነርሱ ( ካህና ጰጳሳት ፓትርያርኩ) ግን ስለሁሉ ይጠየቃሉ፡፡ ይህ እኮ እረኝነት ነው፡፡ ምናልባት እረኛው ቢተኛ በጎች ተኩላን መለየት ይገባቸዋል እንጅ እረኛቸው ስለተኛ ብቻ ጠላታቸው ከሆነ ተኩላ ጋራ ሊጫወቱ አይገባም፡፡ ተኩላው የሚያጠቃው በቅድሚያ በጎችን ነውና ስለዚህ እንደበግነታችን እረኞቻችንን ልንለይ ያስፈልገናል፡፡
ይህ እውነት ነው፡፡ እውነት ደግሞ በምንም በማንም ታፍና እና ተደብቃ የማትቀር እንቁ ናት፡፡ እንደ ንጋት ኮከብ ሁሌ የምታበራ ብርሃን ናት እውነት፡፡ ይህችን እውነት ደፍሮ ለመከተል የግል ውስጣዊም ውጫዊም ጥንካሬ እንዳለ ሆኖ የአባቶቻችንን የነቢያትን የሐዋርያትን የመምህራንን የእውነት ጉዞ መከተል ግን ቅድሚያ መሰጠት አለበት፡፡ ዲዎስቆሮስ አለቃህን ልዮንን አትፈራምን ሲሉት ምን ነበር ያለው በርግጥ ልዮን አለቃየ ነው ነገር ግን አለቃየ የሚሆነው በእምነት ሲመስለኝ ብቻ ነው፡፡ ሳጥናኤል አለቃቸው የነበረ መላእክት ሳጥናኤል አለቃቸው ስለሆነ ብቻ እንዳልተከተሉት ሁሉ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ እምነታችንን እናስቀድም፡፡
አንዳንዶች ደግሞ በጣም በሚያሳዝን መልኩ ከ “ቅናት እና የግል ቂም” ጋር ያያይዛሉ፡፡ ምን አገናኘን እምነታችን ላይ እንጅ ክርክራችን እኛ ምን አገባን የፈለጉትን ቢሆኑ፡፡ ደግሞስ ምን የሚቀናበት ነገር አላቸውና ነው የምንቀናባቸው፡፡ ጠባችን ክርክራችን ለምን በቤተክርስቲናችን ስም እንደዚህ ይደረጋል የሚል ብቻ ነው፡፡ እና በዚህ ሃሳብ ላይ ያላችሁ ሰዎች አመለካከታችሁን ከግለሰብ ወደ ቤተክርስቲያን ፍቅር ቀይሩት ከፍ አድርጉት፡፡
እውነትን ከሳሙኤል እንማር፡፡ የሆነውን ሁሉ ሳንፈራ ሳንደብቅ እንገልጠው፡፡ ካህኑ ዔሊ አፍኒንና ፊንሐስ የሚባሉ ሁለት ምናምንቴ ልጆች ነበሩት፡፡ ዔሊ ክህነት ከምስፍና ጋር አስተባብሮ ለ40 ዘመን አስተዳድሮ ስለደከመ እነዚህን ልጆቹን ከበታቹ ሾማቸው፡፡ እነዚህ የዔሊ ልጆች ግን ሦስት ዐበይት ኃጣውእ ሠሩ፡፡
v ሙሴና አሮን በሠሩት ሥርዓት መሠረት በቀዳማይ ሰዓተ ሌሊት በርቶ በቀዳማይ ሰዓተ መዓልት ይጠፋ የነበረውን ፋና ከባዶ ቤት ሲበራ ቢያድር ምን ይጠቅማል? ብለው አስቀሩ፣
v እስራኤላውያን መሥዋዕት በሚሠው ጊዜ ገና ስቡ ሳይጤስ የወደዱትን ሥጋ እየነጠቁ ይበሉ ነበር፣
v ሴቶችን በቤተመቅደስ ውስጥ ያስነውሩ ነበር፡፡
ካህኑ ዔሊ ልጆቹ ይህን ሁሉ ሥራ እንደሚሠሩ ሲያውቅ ልጆቼ ሆይ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ኃጢአተኛ በማድረጋችሁ ስለእናንተ የደረሰኝ ወሬ መልካም አይደለምና ይህ አይሆንም፡፡ ሰውስ ሰውን ቢበድል እግዚአብሔር ይፈርድለታል ሰው ግን እግዚአብሔርን ቢበድል ስለእርሱ የሚለምን ማን ነው? አላቸው፡፡ ነገር ግን ምክሩ ቸልተኛ ምክር ነበር፡፡
እንደዚያ ያለውን የከፋ ኃጢአት እየሠሩ እያለ ከስልጣን ልሻራቸው አለማለቱ ቸልተኝነቱን ያሳያል፡፡ ካህኑ ምክሩ ከእኔ ይውጣልኝ እንጅ ቢመለሱ ባይመለሱ ምን አገባኝ የሚል የቸልተኝነት አስተሳሰብ ተጠቂ ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን ሦስት ዐበይት ኃጣውእ ልጆቹ ማድረጋቸውን (መሥራታቸውን) እያወቀ ከእግዚአብሔር ይልቅ ለልጆቹ አድልቶ ከበታቹ እንደሾማቸው ልሻራቸው ሳይል ቀረ፡፡ እነርሱም አባታቸው በቸልተኝነት የመከራቸውን ምክር ቸል አሉት አልተቀበሉትም፡፡ የቸልተኛ ልጆች ናቸውና እንደ አባታቸው እነርሱም ቸልተኞች ሆኑ፡፡ እግዚአብሔር ሊገድላቸው ወዷልና የአባታቸውን ቃል አልሰሙም እንዲል፡፡
በዚያን ጊዜ ታቦተ ጽዮንን ያገለግል የነበረው ብላቴናው ሳሙኤል በቤተ መቅደስ ተኝቶ ሳለ ሳሙኤል ሳሙኤል ብሎ እግዚአብሔር ጠራው፡፡ ሳሙኤል ግን ካህኑ ኤሊ የጠራው መስሎት ወደ ዔሊ ሄዶ እነሆኝ የጠራኸኝ አለ፡፡ ዔሊም ሂድና ተኛ እኔ አልጠራሁህም አለው፡፡ አሁንም ለሁለተኛ እና ለሦስተኛ ጊዜ እንዲሁ ሆነ ዔሊም ከዚህ በኋላ የሚጠራህ ከሆነ ተናገር ባሪያህ ይሰማል በል አለው፡፡ ሳሙኤልም ለዐራተኛ ጊዜ እግዚአብሔር ሲጠራው ዔሊ እንዳዘዘው አደረገ፡፡ እግዚአብሔርም ለሳሙኤል “ልጆቹን አፍኒንና ፊንሐስን ከበደል አልከለከላቸውምና እንድፈርድበት የነገርኹትን በዔሊ ላይ እፈጽምበታለሁ” አለው፡፡ በተጨማሪም የእስራኤልን መሸነፍ (መመታት)፣ የታቦተ ጽዮንን መማረክ፣ የአፍኒንና ፊንሐስን የዔሊንም ሞት ነገረው፡፡ ሲነጋ ዔሊ እግዚአብሔር የነገረህን አንዲት ሳታስቀር ንገረኝ ብሎ ሳሙኤልን ጠየቀው፡፡ ሳሙኤልም አንዲት ሳያስቀር ሁሉንም ነገር ነገረው፡፡ በቃ እውነት እንዲህ መገለጥ አለባት፡፡ የምን መደባበቅ የምን መሸፋፈን ነው፡፡ ዔሊ ግን እርሱ እግዚአብሔር ነውና የወደደውን ያድርግ አለ፡፡ አሁንም ይመጣብሃል የተባለውን መቅሰፍት በቸልታ ተመለከተው፡፡ ከመመለስ ይልቅ ቸልተኝነትን መረጠ፡፡ የወደደውን ያድርግ እንጅ እኔ አልመለስም ልጆቼንም አልሽራቸውም አለ፡፡ በቃ ካልሰማ ካልተመለሰ ለአንዱ አምላክ ነግሮ መፍትሔውን መጠባበቅ ነው፡፡
እግዚአብሔርም እንደተናገረው እስራኤላውያን በፍልስጥኤማውያን ተመቱ 4 ሺህ የሚያህሉ ሰዎችም ተገደሉባቸው፡፡ ይህ የሆነብን ታቦተ ጽዮንን ስላልያዝን ነው ብለው ታቦተ ጽዮንን እንዲልክላቸው ወደ ካህኑ ዔሊ መልእክተኛ ላኩ፡፡ የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ታቦተ ጽዮንን ይዘው መጡላቸው፡፡ እስራኤላውያን ታላቅ ደስታ አደረጉ እልልታቸውም ደመቀ፡፡ ፍልስጥኤማውያንም እስራኤላውያን የሚደሰቱት በታቦተ ጽዮን መምጣት ምክንያት መሆኑን ሲያውቁ ወዮልን ወዮታ አለብን አሉ በግብጽ የሠራችውን ተአምር ያውቃሉና፡፡ ነገር ግን ተጽናንተው እስራኤላውያንን ገጠሙ እና አሸነፉ፡፡ አፍኒንና ፊንሐስን ገደሉ ታቦተ ጽዮንን ማረኩ፡፡ አንድ ብንያማዊ ልብሱን ቀዶ አመድ ነስንሶ ወደ ከተማ ተመልሶ የሆነውን ሁሉ ለዔሊ ነገረው፡፡ ዔሊም የዘጠና ዓመት ሽማግሌ ነበርና ደንግጦ ከመንበሩ ወድቆ አንገቱ ተሰብሮ ሞተ፡፡ /1ኛ ሳሙ4÷1-18 ተመልከት/ ለዚህ ሁሉ ከባድ ችግር ዋናው ምክንያት የዔሊ ቸልተኝነት ነበር፡፡ እግዚአብሔር በግልጥ እየነገረው ቃሉን ቸል ማለቱ ይህን መቅሰፍት አምጥቷል፡፡ እግዚአብሔር እንድትሠራው ያዘዘህን አለመሥራት አትሥራ ያለህንም መሥራት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ተመልከት፡፡ ስለዚህም እንዲህ አይነቱን የዔሊን መሰል ቸልተኝነት ልታስወግደው ይገባል፡፡ ከዚያ ውጭ ግን በአንድም በሌላም ነገር ተመክረህ ካልሰማህ ተዝቆ የማያልቀውን መከራ እግዚአብሔር ያሸክምሃል፡፡
ዛሬ ሰኔ 9 የነቢዩ ሳሙኤል የእረፍቱ መታሰቢያ ነው፡፡
=====================================
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት #comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡

No comments:

Post a Comment