Monday, June 12, 2017

“ጩኸታችንን በአደባባይ የጮኹልን የተዋሕዶ ልጆች”


© መልካሙ በየነ
ሰኔ 05/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ትናንትና ሰኔ 04/2009 ዓ.ም የአማራ ብዙሀን መገናኛ ድርጅት የከተሞች መድረክን በምሥራቅ ጎጃም መዲና በደብረ ማርቆስ ከተማ አድርጓል፡፡ የዚህ መድረክ ዋና ዓላማ በከተማ አስተዳድሩ ውስጥ ያሉትን ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ከህብረተሰቡ በመሰብሰብ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት እዛው መልስ እንዲሰጡበት ማድረግ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በርካታ ጉዳዮች የተነሡ ሲሆን በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት የተፈጠረው ከፍተኛ ችግርም አንገብጋቢ መሆኑ ከህብረተሰቡ ተነሥቷል፡፡ 
https://youtu.be/GcbXQQa9sqs

“ቀድሞ መምህር ነበርሁ” አሉ ወ/ሮ ፈንታ “አሁን ግን በጥሮታ ከሥራየ ተሰናብቻለሁ፡፡ እኔ የማነሣው ጉዳይ እስካሁን ከተነሣው ችግር ሁሉ የተለየ ነው” አሉ፡፡ “ስለመብራት ችግር አነሣን መልካም፤ ስለ ውኃ ችግር አነሣን መልካም፤ ስለመኖሪያ ቤት ችግር አነሣን መልካም፤ ስለቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓታችን ችግር አነሣን መልካም ይህ ሁሉ መነሣቱ ጥሩ ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ችግር ተፈታ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ሃይማኖታችንን እንዴት እናድርጋት፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፡፡ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ ተማሪዎች መንፈሳዊ ትምህርትን የሚማሩበት ግቢ ጉባዔ ተዘግቶባቸዋል፡፡ ከሀገረ ስብከቱ ጀምሮ እስከ ወረዳ አጥቢያዎች ድረስ በሙሉ የተሰገሰጉ የሊቀ ጳጳሱ የእህት ልጅ የወንድም ልጅ የአጎት ልጅ የአክስት ልጅ የአገር ልጅ ናቸው፡፡ ታዲያ ለማን አቤት እንበል፡፡ በሃይማኖታችን ዙሪያ ችግር አለብን ብለን እንዳናማክር ሁሉም የስጋ ዘመዶቻቸው ናቸው፡፡ የንስሐ አባት እንኳ እስካሁን የለንም ማንን እንያዝ? መድረክ ላይ ወጥተውም ጎጃም ሌባ የማርቆስ ህዝብ ሌባ ነው እያሉ ከመሳደብ ውጭ ይህን አታድርጉ ከዚህ ተቆጠቡ ብለው አላስተማሩንም፡፡ ቤተክርስቲያን የህዝብ ናት የምትመራበት ቃለዓዋዲም አላት በዚህም መሠረት ሕዝበ ክርስቲየኑ የሰበካ ጉባዔ ይመርጣል ነገር ግን በምን ምክንያት እንደሆነ ሳይታወቅ አባታችን ሰበካ ጉባኤውን አፍርሰው በዘመዶቻቸው ይተካሉ፡፡ ታዲያ የት ሄደን እንጸልይ፡፡ ለምን ብለን ስንጠይቅ ከነፍስ ልጅነት አባርርሻለሁ እንባላለን፡፡ አሁን እንዲያውም አባታችን አይነሡብን እያላችሁ አስፈርሙ ብለው እያስፈራሩ እንዲፈረም እያደረጉ ነው፡፡ ልጆቻችን ወደ አልባሌ ቦታ እንዲሄዱ እያደረጉብን ነው፡፡ ዛሬ ይህን የምናገረው ህዝቡ አገሩ ይወቀው ብየ ነው እንጅ ጉዳዩን ከወረዳ እስከ ጠቅላይ ቤተክህነት ድረስ አሳውቀናል፡፡ በከተማችን ሽብር እየፈጠሩ ነው፡፡ ተነሡ እያሉ ህዝቡን እያነሣሡ ነው፡፡ ስለዚህ አንፈልጋቸውም ይነሡልን አንፈልጋቸውም” አሉ፡፡ በዚህ ንግግራቸው ሁሉም የአዳራሹ ህዝብ በጭብጨባ ነው ደስታውን የገለጸው፡፡ የአባታችን የአቡነ ማርቆስ ጉዳይ በዚህ መልኩ በቀጥታ ስርጭት ሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውን ሁሉ ተከታትለውታል፡፡ ይህ ችግር የቤተክርስቲያናችን ችግር ብቻ ሳይሆን የከተማውም ችግር ነው፡፡ ቤተክርስቲያናችን በዚህ መልኩ ከተረበሸች ይህ ያጨበጨበው ህዝበ ክርስቲያን ሁሉ ብጹእነታቸውን ከተቃወመ ከፍተኛ ብጥብጥ መፈጠሩ ለማንም የተገለጠ ነው፡፡ ለዚህም ነው የዞኑ ጸጥታ ዘርፍ አስተዳድር ህዝቡ የሚያነሣውን ቅሬታ በአስቸኳይ ፍቱ ብሎ ለብጹእነታቸው በደብዳቤ የገለጠው፡፡

መጋቤ አእላፍ ጥበቡ ዕድሉን አገኙ የድምጽ ማጉያው ተሰጣቸው፡፡ “ ሰንበት ትምህርት ቤቱ ላይ የተነሣው ጉዳይ ትክክል ነው ተዘግቶባቸዋል፡፡ እንደሃይማኖት አባትነት ለቅዱስ ጴጥሮስ የተሠጠ ቃል ትወደኛለህ በጎቼን ጠብቅ ግልገሎቼን ጠብቅ ጠቦቶቼን ጠብቅ የሚል ነው፡፡ አይጦች ነው የምንባለው አብሮ አደግ ጋኔን ይዞታል ነው የምንባለው፡፡ ይህን የሚሉን ግን ለዘመዶቻቸው ቦታ ለማመቻቸት ሲፈልጉ ነው፡፡ ከሃገረ ስብከት እስከ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ድረስ የሁለት ወረዳዎች አጠቃላይ የቤተሰብ እና አብሮ አደግነት ነው የተከማቸው፡፡ በእውቀታቸው አይደለም የተመደቡት የእህት የወንድም የአጎት የአክስት ልጅ ነው፡፡” አሉ፡፡ መድረክ መሪው ከወ/ሮ ፈንታ ጋር ተመሣሣይ ስለሆነ ለሌላ እድል እንስጥበት አላቸው፡፡ እርሳቸው ግን ውስጣቸውን መግለጥ ስለፈለጉ “በማይመሳሰል መልኩ አቀርበዋለሁ” አሉ፡፡ ከዚያም ቀጠሉ “ሚሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊ የሚል መጽሐፍ በዚህ ዓመት ታትሟል፡፡ የታተመው ምስካበ ቅዱሳን ቆጋ ገዳም ነው፡፡ ወልደ አብ የሚባል መጽሐፍም አለ በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ የሚል ትምህርት የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡ ይህንን ችግር የመገናኛ ብዙሃኑ ይፈተዋል ብየ አይደለም ግን ወዴት እያመራን ነው፡፡ ወደፊት የአገራችን ራእይ ምንድን ነው የሚሆነው፡፡ ይህ ችግር በቅዱስ ሲኖዶስ የተያዘ ነው፡፡ ሚያዝያ 30/2009 ዓ.ም ያስተማሩት ትምህርት ቅስቀሳ ነበር ጎጃም ተጠመቅ ተብለሃል ተነሣ እያሉ ሲቀሰቀሱ ነበር፡፡ …ጳጳስ ስለሆንኩ እንደፈለግሁ አደርጋለሁ የሚሉ ናቸው፡፡ አባታችን እንዳይነሡብን እያሉ እንዲፈርሙ ተደርጓል፡፡ አብማ ማርያም ላይ በግድ ፈርሙ ተብሏል አንፈርምም ያሉ ካህናት እና ዲያቆናት በስጋት ላይ ናቸው፡፡” በማለት ተናገሩ፡፡ ይህንን በመናገራቸው አሁንም የህዝበ ክርስቲያኑ ደስታ በጭብጨባ ተገልጧል፡፡ በዚህ መልኩ ብጹእ አባታችን ላይ የሚታዩትን ችግሮች ለህዝብ አደረሱ፡፡ እኛ በተለያዩ መንገዶች የጮኽናቸው ጩኸቶች ፍሬ አፍርተው  ወ/ሮ ፈንታ እና መጋቤ አእላፍ ጥበቡ በአደባባይ ለዓለም እንዲገለጥ አድርገዋል፡፡ ይህን በማድረጋቸውም ታሪክ የሚዘክራቸው ምርጥ የሃይማኖታችን አርበኞች ብለናቸዋል፡፡

ይህ ከላይ የተነሣው የሀገረ ስብከቱ ችግር እንዲፈታ መንግሥት ምን ሠርቷል የሚለውን ጥያቄ አቶ አብርሃም እንደ ዞን ጸጥታ ዘርፍ ሆነው መልስ ሰጥተዋል፡፡ “ለሰላም እና ጸጥታ ጠንቅ የሆነ አሠራር ስላለ ይህን አሠራር ከማረም አኳያ ለመመመካከር ጥረት አድርገናል፡፡ ባደረግነው ጥረት ውስጥ ግን ሊሳካልን አልቻለም፡፡ ያልቻለበትም ምክንያት በጣም ሳብ ጎትት የበዛበት ነው፡፡ ወይንም የእኛ አሠራር ባህል ችግሩ አለ የሚባለው *ኤሪያ* ላይ ስለሌለ ነው፡፡ መደማመጥ የለም፤ መግባባት የለም፤ ለመነጋገር ፈቃደኛነት የለም፡፡ ይኼ ባለበት ነባራዊ ሁኔታ እኛ *ኢንተርቬን* አድርገን ልንፈታው የምንችለው ሆኖ አላገኘነውም፡፡ ስለሆነም የመጨረሻ እንግዲህ የዞናችን ጸጥታ ከአቅሙ በላይ በመሆኑ  ምክንያት ከዚህ በኋላ ለሚደርሰው ችግር ተጠያቂ አይደለሁም ብሎ *ዲክላር* አድርጎበታል በደብዳቤ፡፡ በርግጥ ይኼ መፍትሔ ነው ወይ ሌላ ነገር ነው፡፡ ስለሆነም እኔ መፍትሔ ብየ የምወስደው የቤተክርስቲያኑ አካላት ጉዳዩን አይተው ፈጣን ምላሽ እንዲሰጡ ማድረግ ያስፈልጋል ብየ ነው የማስበው፡፡ እንግዲህ አሁን በዚህ መልእክቱን በማድረስ በኩል ትልቅ ሚና ይኖረዋል የሚል አስተያየት ነው ያለኝ፡፡ ችግሩ ግን ትክክል ነው ከመንግሥት ድርሻ አኳያ ጣልቃ ገብተን እርምጃ የምንወስድበት እድል ስለሌለን ህገ መንግሥቱን አክብረን ግን ደግሞ ቤተክርስቲያኗ በራሷ ምላሽ ትሰጣለች ብለን እየጠበቅን ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ አመሰግናለሁ፡፡” በማለት አቡነ ማርቆስ እየፈጠሩት ያለው ችግር ከዞኑ አቅም በላይ እንደሆነ ገልጧል፡፡ ስለዚህ የቤተክርስቲያናችንን ችግር አባቶቻችን እንዲፈቱልን አሁንም ወደፊትም እንጠይቃለን፡፡ ምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት የሁሉ ትኩረት ሊሆን ያሻዋል!

ከታች ያለውን ቪዲዮ ግን ሁላችሁ ተመልከቱልኝ ዞኑ ከተናገረው ውጭ ያለውን የሁለቱን የተዋሕዶ ልጆች ቃል በቃል ስላልገለበጥኩት በዛ ያለ መልእክት ስላስተላለፉ አዳምጡት፡፡
=====================================
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት #comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡

No comments:

Post a Comment