Monday, June 5, 2017

ፍኖተ እግዚአብሔር--- ክፍል ፲፫




© መልካሙ በየነ
ግንቦት 29/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ተጽሕፈ እም አሐዱ ሊቅ ኢትዮጵያዊ ኅሩይ ወመፈክራዊ
ጌታው አለቃ ኅሩይ

፲፭ኛ አንቀጽ
ምዕዳንና አኲቴት
ንባብ፦ “እንከሰ የአክል ኅዳጠ ዘተናገርነ እምብዙኅ እስመ ለለባዊ ኅዳጥ የአክሎ፣ ወለዘኢኮነሰ ለባዊ ወኢያርትዐ ልቡናሁ ኀበ ነገረ ጽድቅ እመ ውኅዘ ቃለ መጻሕፍት ከመ ማየ ፈለግ፣ ወለእመኒ ዘንመ ከመ ዝንቱ ክረምት፣ ኢይከውን በኀቤሁ ከመ አሐቲ ነጥበ ጠል ወኢይርሕስ ሥርወ ልቡናሁ፤ ወኢያለመልም አዕፁቂሁ ወኢይሠርፅ ቈፅሉ:: ወእምከመ ኢለምለመ ዐፅቅ፣ ወኢሠረፀ ቈፅል ኢይትረከብ ፍሬ፤ ወለእመ አልቦ ፍሬ ምንትኑ ረባሑ ለተይህዶ” ትርጉም፦ “እንግዲህስ ከብዙ በጥቂቱ የተናገርነው ቃል ይበቃል፤ ለአስተዋይ ልቦና ጥቂት ቃል ይበቃልና፤ አስተዋይ ላልሆነ እግረ-ልቦናውንም ወደ እውነት ነገር ላላቃና ሰው ግን፣ የመጻሕፍ ቃል እንደ ወንዝ ውኀ ቢፈስ፣ እንድ ክረምት ዝናብምም በዝቶ ቢዘንም፣ በእርሱ ዘንድ እንደ አንዲት ጠብታ አይሆንም:: ልቦናውም ምሥጢር አይረዳም፤ ሕሊናውም አይመለስም፣ ሃይማኖቱ አይቀናም:: ሕሊናውም ካልተመለሰ፣ ሃይማኖቱ ካልቀና፣ ፍሬ ክብር ካልተገኘ፣ አማኒ የመባል ጥቅሙ ምንድን ነው?” ንባብ፦ “ኦ አሐውየ ፍቁራን ንፍራህ ወንኅዝን፤ ከመ ኢይብጻሕ ላዕሌነ ቃል ነቢይ ዘይቤ ዐፀደ ወይን ኮነ ለፍቁር በብሔር ጥሉል፤ ወእምዝ ጸሕናክዎ ይፈረይ አስካለ ወፈረየ አሥዋከ” ትርጉም፦ “የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ እንፍራ፣ አንዘንም:: ለወዳጄ የወይን ቦታ ነበረው በሰባ ኮረብታ ላይ:: ከዚህ በኋላ ፍሬ ያፈራል ብዬ ተስፋ አደረግሁ:: ነገር ግን እሾህን /መጻጻ ፍሬን/ አፈራ” ብሎ ነቢዩ የተናገረው ቃል /ኢሳ ፭:፩-፪/ በእኛ እንዳይደርስብን እንፍራ እንዘንም:: ንባብ፦ “ወዓዲ ቃለ እግዚእነ ዘይቤ ቦ ዘወድቀ ውስተ ሦክ ወበቊሎ ጠበቆ ሦክ ወሐነቆ” ትርጉም፦ “ዳግመኛም ጌታችን በእሾህ ላይ የወደቀ ከበቀለ በኋላ እሾህ ያጫነቀው ያጣበቀውም ዘር አለ” ብሎ የተነናገረው እንዳይደርስብን:: ማቴ ፲፫:፯ ንባብ፦ “ወዓዲ ቃለ ጳውሎስ ዘይቤ እመሰ አውጽአት ሦከ ወአሜከላ ዘቅርብት ለመርገም ወደኃሪታ ለአንድዶ” ትርጉም፦ “ዳግመኛም ምድር እሾህን አሜከላን ያበቀለች እንደሆነ፣ ለመርገም የቀረበች ናት፤ ፍጻሜዋም መቃጠል ይሆናል” ብሎ ጳውሎስ የተናገረው ቃል እንዳይደርስብን:: ዕብ ፮÷፰ ንባብ፦ “ኦ አኃው ንሑር በተዐቅቦ በዛ ፍኖት ሠናይት፤ እስመ ፍኖት ሠናይት ጥቀ ፀባብ ወመቅዓን ወፅዕቅት ይዕቲ፣ እንተ ትወስድ ውስተ ሕይወት:: ለእለ ይበውዕዋ በትሕትና ወበፍርሃት ወለዕለሰ ይበውዕዋ በትዕቢት ታውድቆሙ ውስተ ጸድፈ ሞት” ትርጉም፦ “ወንድሞች ሆይ በዚች በቀናች ጎዳና በጥንቃቄ ሆነን እንሂድ፤ ይህች እጅግ ጭንቅና ጠባብ የሆች በጎ ጎዳና በፍርሃትና በትሕትና ሆነው የሚገቡባትን ሰዎች ወደ ሕይወት የምትወስድ ናትና:: በትቢዕትና በድፍረት ሆነው የሚገቡባትን ግን ሞት ሰውን እየገደለ ወደሚጥልባት ወደ ገሃነም የምታወርድ ናትና::” ንባብ፦ “እንከሰ ናርትዕ አእጋሪነ ውስተ ፍኖተ ሰላም እንተ ይእቲ አሚን፣ ከመ ፩ መለኮት በ፫ አካላት” ትርጉም፦ “እንኪያስ እግረ ልቡናችንን ወደ ሰላም ጎዳና እናቅና፣ ይህችውም የሦስቱ አካላት መለኮት አንድ እንደሆነ ማመን ናት:: ወእግዚአብሔር አምላከ ሰላም የሀበነ ሰላመ፤ በብሂለ ዋሕድ መለኮቱ፤ በእግረ ልቡና ንትልዋ ለአሠረ ሠናይት ፍኖቱ፤ ለበዊዕ በጽድቅ ቤተ አሐቲ መንግሥቱ፤ ዘብዙኀ ማኀደረ ክብር ወምዕራፍ ቦቱ፤ ወኬንያሁ ለሊሁ ውእቱ” ትር ጉም “የሰላም አምላክ እግዚአብሔር ሰላምን ይስጠን ፤ አንድ ነው እያልን በመለኮቱ፤ በእግረ ልቦናችን እንከተላት መልካም ፍለጋ ያላት መንገዱን በእውነት ለመግባት ወደ አንዲቱ ቤተመንግሥቱ፤ ብዙ መኖሪያና ክብር ማረፊያም ያለባቱ፤ ሠሪዋ የተጠበበባት እርሱ ነው ባለቤቱ፤ ማለት ነው። ንባብ፦ “ኦ አኃው አንብብዋ ለዛቲ መጽሐፍ በተዓቅቦ ወበኅድዓት፣ እመኒ ኅዳጥ በንባብ፤ ብዝኅት ይእቲ በረባሕ፣ ወበቁዔት” ትርጉም፦ “ወንድሞች ሆይ ይችን መጽሐፍ በጥንቃቄና በጸጥታ ተመልከቷት፤ በንባብ ጥቂት ብትሆን፣ ረብሕ ጥቅም በመሆን ብዙ ናትና።” አሞንዮስና አውሳብዮስ እግዚአብሔርን እንዳመሰገኑት እኛም ከአንድነቱና ከሦስትነቱ ምሥጢር ጥቂት ስለ ገለጽን፣ ለእግዚአብሔር ያቀረብነው ምስጋና:- ንባብ፦ “አኮቴት ለእግዚአብሔር ሠዋሪ፣ ወከዳኒ፣ ነባቢ ወከሃሊ፣ ሕያው ወማሕየዊ፣ ወመዋዒ፣ ዘአንቅሐ አልባቢነ ኀበ ዝክሩ፣ ወመርሐ ልሳናቲነ ኀበ አኩቴቱ ወስብሐቲሁ፣ ንሰብሖ እንከ በእንተ ዘወሀበነ እምነ ሠናይት ኂሩቱ፤ ወናእኩቶ እንበይነ ዘፀገወነ እምዕበየ ጸጋሁ፤ ወንቀድስ ስሞ ክቡረ ድልወ በእንተ ዘከሰተ ለነ እምነ ምሥጢራተ ሃይማኖት በተዋሕዶተ ባሕርዩ ለሊሁ፤ ወትሥልስተ አካላቲሁ ወገጻቲሁ ወመልክዑ ወንሰብሖ ስባሔ ፍጹመ:: በእንተ ዘወሀበነ ቦቱ:: ስብሐት ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ለዓለመ ዓለም” ትርጉም፦ “ባሕርዩን በባሕርዩ ለሚሰውር፣ በመምህራን አድሮ ምሥጢርን ለሚናገር፣ ሁሉንም ለማድረግ ለሚቻለው፣ ለራሱ ሕያው ሆኖ ሌላውን ሕያው ለሚያደርግ፣ ሕሊናትን ድል ለሚነሣ፣ ልቡናችንን እርሱን ወደማሰብ ላነቃቃ፣ አንደበታችንንም ጌትነቱን ወደማመስገን መርቶ ላደረሰን እግዚአብሔር ምስጋና ይገባል:: በቸርነቱ ከሚሰጠው ከበጎው ሀብት ወገን ስለሰጠን እናመስግነው:: በለጋስነቱም ከሚያድለውም ክብር ወገን ስለሰጠን እናመስግነው:: ክቡር ስሙንም በሚገባ ምስጋና እናመስግን:: ከሃይማኖት ምሥጢር ወገን በባሕርይ አንድነቱን በአካልና በገጽ ሦስትነቱን፣ አንድ አድራጊ ሕልውናውንም ስለገለጸልን፣ ይህንም ሁሉ ስለ አደረገ፣ ፍጹም ምስጋና እናመስግነው:: ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ክብር ምስጋና ይግባው ለዘለዓለም አሜን::”
መፍትሔ ቃላት
ሁከት - ሁልጊዜ የሚከናወን የባሕር እንቅስቃሴ፡፡
ሃይማኖተ አበው - የመጽሐፍ ስም፣ ስለ ምሥጢረ ሥላሴ፣ ስለ ምሥጢረ ሥጋዌ የቀድሞ ሊቃውንት ያስተማሩትን ትምህርት የያዘ የቤተ ክርሰቲያን መጽሐፍ፡፡
ሕልው- ነዋሪ፣ ቋሚ፡፡
ለባዊያ- የሚያስቡ፡፡
ሕላዌ -አኗኗር፡፡
ሕያዋን - በማይለወጥ ሕይወት የሚኖሩ ሕይወት ያላቸው፡፡
መለኮት- የእግዚአብሔር የአንድነት መገለጫ እና የግዛትና የጌትነት መጠሪያ ስሙ፡፡
መልክእ -መልክ፡፡
መቅድመ ወንጌል- የመጽሐፍ ስም፣ የአራቱ ወንጌላት መቅድም፣ አሞንዮስ፣ አውሳብዮስ በሚባሉ ሊቃውንት እንደተጻፈ የሚነገርለት ስለ ጥንተ ተፈጥሮ ስለ ሰው ጠባይና በተፈጥሮው ስለተሰጠው ነጻነት በሰፊው የሚናገር፡፡
መንፈስ ቅዱስ- ከሦስቱ አካላት የሦስተኛው አካል የመንፈስ ቅዱስ መጠሪያ ስም፡፡
ማሕደር- ማደሪያ፣ ቤት፡፡
ምሥጢረ ሥላሴ- ስለ እግዚአብሔር አንድነት ሦስትነት ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረው ትምህርት፡፡
ምዕዳን - ምክር፡፡
ሥላሴ- አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ፡፡
ሥልጣን- የበላይነት፣ አገዛዝ፡፡
ርጥበት - ውኃ ያለበት የባሕር አካል፡፡
ስመ አካል- የአካል ስም፡፡
ስመ ኩነት- የመሆን፣ የአኳኋን ስም፡፡
ስመ ግብር- የግብር ስም፡፡
ሰራጺ- የመንፈስ ቅዱስ የግብር ስም፣ ከአብ የወጣ የተገኘ፡፡
ሰብእ-  ሰው፡፡
ስፍሀት- ስፋት፡፡
ቅሉ-ቢሆን፣ ጨምሮ፣ ከዚያም በላይ፣ ለነገሩ፡፡
ቅጥነተ ሕሊና- የረቀቀ አስተሳሰብ፣ ረቂቅ አእምሮ፣ ጥልቅ አስተሳሰብ፣ ምርምር፣ ርቃቄ፡፡
ባሕርይ- ትርጉሙ ብዙ ነው እንደ ሁኔታው ይለያያል፣ በምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት እግዚአብሔር በባሕርይው አንድ ነው፡፡
ተረክቦ- መገኘት፡፡
ተወላዲ- የወልድ የግብር ስም፣ ከአብ የተወለደ፡፡
ተድኅሮ -ወደ ኋላ መቅረት፡፡
ተፈልጦ- መለየት፡፡
ትርጉም- በግዕዝ የተጠቀሰው ንባብ ፍች (በአማርኛ) ማለት ነው፡፡
ትስብዕት- ሰው መሆን፣ የሰውነት ባሕርይ፣ ሰውነት፡፡
ትንሣኤ ዘጉባኤ- ጌታችን ሁለተኛ ሲመጣ ሁሉም ሰው ተነሥቶ በአንድነት በፊቱ የሚቆምበት የትንሣኤ ጊዜ፡፡
ኃይለ ዘርዕ- እንደ ሰው አራቱን ባሕርያት ነሥቶ ተወልዶ በየደረጃው ማደግ፡፡
ኃይለ እንስሳ- እንደ ሰው መብላት፣ መጠጣት፣ መተኛት፣ መነሣት፡፡
ኃይለ ንባብ- እንደ ሰው ደረጃ በደረጃ አፍ እየፈቱ አከናውኖ የመናገር ችሎታ፡፡
ኃይል- ብርታት፣ ኃይል፡፡
ኃዳሪ-አዳሪ፣ ኗሪ፣ በውስጥ የሚኖር፡፡
ነባብያን- የሚናገሩ፡፡
ንባብ- ነገር፣ የመናገር ችሎታ፡፡
ንባብ -በግዕዝ፣ ቃል በቃል ከአንድ መጽሐፍ የተወሰደ ጥቅስ ማለት ነው በዚህ መጽሐፍ፡፡
አሐቲ ጠባይዕ- የሕይወትነት ጠባይ፡፡
አማልእክት- አምላኮች፡፡
አሠረ ፍኖት- ፈለግ፣ ፍለጋ፣ የመንገድ ፈለግ ወይም ኮቴ፡፡
አስማት- ስሞች፡፡
አስራጺ- የአብ የግብር ስም፣ መንፈስ ቅዱስን የሰረጸ ወይም ያስገኘ፡፡
አቃኒም- አካላት፡፡
አብ- ከሦስቱ አካለት የአንዱ መጠሪያ ስም፤ በዚህ ስም ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ አይጠሩም፡፡
አእምሮ- ዕውቀት፣ ማስተዋል፡፡
አኮቴት- ምስጋና፡፡
አንቀጽ- መክፈያ፣ የመጽሐፍ ክፍለ ሐሳብ ተጠናቆ ሌላ ሲጀመር እንደ ንዑስ ምዕራፍ ወይም ክፍል የሚያገለግል።
እዝነ ልቡና- የውስጥ የአእምሮ ግንዛቤ፣ አእምሮ ላይ የተመሠረተ፣ በደንብ የሚሰማ ውሳጣዊ አካል፡፡
ከዊን - መሆን፡፡
ከዊነ ልብ- ልብ መሆን፣ የልብን ቦታ መያዝ፣ ወይም የአእምሮን የዕውቀትን ቦታ መተካት፣ ይህ ስም የአብ የከዊን ስሙ ነው።
ከዊነ ቃል- የወልድ የከዊን ስሙ ነው፣ ቃል መሆን፣ በቃልነት መገለጥ ማለት ነው፣ ወልድ ለአብም፣ ለመንፈስ ቅዱስም፣ ለራሱም ቃል ነውና፡፡
ከዊነ እስትንፋስ - የመንፈስ ቅዱስ የግብር ስሙ ነው፣ ለአብና ለወልድ እስትንፋስ፣ ሕይወት ሆኖ በራሱም ሕያው ነውና፡፡
ከርሠ መቃብር - የመቃብር ሆድ፡፡
ክሂል- ችሎታ፡፡
ወላዲ- የአብ የግብር ስም፣ ወልድን የወለደ በመሆኑ “ወላዲ” ይባላል “ወላጅ” ማለት ነው፡፡
ወልድ- ከሦስቱ አካላት የሁለተኛው አካል የወልድ መጠሪያ ስም፡፡
ዋሕድና- አንድነት፡፡
ዋዕይ- ሙቀት፡፡
ዕሪና- እኩልነት፣ መተካከል፡፡
ዝኒ ከማሁ- ይህም እንደዚያው ነው፡፡ ምንጩ መገኛው ከላይ ከተጠቀሰው ጋር አንድ ነው ማለት ነው፡፡
ዮሐንስ ተአቃቢ- እግዚአብሔርን በአካልም በመለኮትም ሦስት ብሎ ያስተምር የነበረ ዘጠኝ መለኮት ይላል የሚባል መናፍቅ ስም ነው። ትምህርቱ በደብረ ሊባኖስ ገዳም እና በዋልድባ አካባቢ ተስፋፍቶ ነበር። አሁን ግን የጠፋ ይመስላል። ምንጩ ግን ትግራይ ነው ይባላል። ስሜን ሽዋ ነው የሚሉም አሉ።
ደብር- ተራራ፡፡
ገጽ- አካል፣ መልክ፡፡
ገጻት- አካላት፡፡
ፍኖት መብዕሰ- ያልተስተካከለ ወጣ ገባ መንገድ፡፡

ተጽሕፈ እም አሐዱ ሊቅ ኢትዮጵያዊ ኅሩይ ወመፈክራዊ
ጌታው አለቃ ኅሩይ
ተፈጸመ፡፡

No comments:

Post a Comment