© መልካሙ በየነ
ሰኔ 08/2009
ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
አባታችን አቡነ ማርቆስ በሀገረ ስብከቱ እየተሠራ ላለው አዲሱ ህንጻ
በየወረዳው እየዞሩ ገንዘብ በማሰባሰብ ላይ በነበሩበት ወቅት እግር መንገዳቸውን አንዳንድ ጉዳዮችን እንደ ቋሚ አጀንዳ ይዘው የራሳቸውን
መልእክት ሲያስተላልፉ ነበር የከረሙት፡፡ በአምበር ከተማም ተገኝተው እንደተለመደው የግል መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ከአንድ
የመርኃ ግብር ተከታታይ በወረቀት ጥያቄ ተላከላቸው ለዚያም ጥያቄ መልስ ሲሰጡ በጣም በሚያሳፍር መልኩ እንደነበር ይህን ቪዲዮ ስሙት፡፡
“በ28 በ29 ማለት ሃይማኖት ቀን መቁጠር ይሆናል ወይ፡፡ ሃይማኖት
ወልደ አብ ወልደ ማርያም ተወለደ ማለት ነው” ብለው ይጀምራሉ፡፡ የልጁ ጥያቄ ስለ ቅብአት እና ስለተዋሕዶ ልዩነት የጠየቃቸው ይመስላል፡፡
በእውነት ከአንድ ሊቀጳጳስ የገና በዓል በ28 በ29 እያሉ ቀን መቁጠር ሃይማኖት ይሆናልን ሲል መስማት ያሳዝናል፡፡ ቀን መቁጠርን
የምታስተምር በባሕረ ሃሳብ ጥበብ የመጠቀች ቤተክርስቲያናችን ይህን ተብላ ስትሰደብ መስማት እጅግ ያስለቅሳል፡፡ በእውነት ቀን መቁጠር
የሃይማታችን መገለጫ ካልሆነ “ዓርብ እና ረቡዕ” መጾማችንን ትተን ለምን “ሰኞ እና ማክሰኞ” አንቀይረውም ነበር፡፡ የዐቢይ ጾም
መግቢያ መውጫ በባሕረ ሐሳብ በወጣለት የቀን አቆጣጠር ካልተከበረ ሥርዓት አላፈረስንም ወይ፡፡ የገና በዓልስ ቢሆን በ28 በሚከበርበት
በ28 በ29 በሚከበርባቸው ዓመታትም በ29 ማክበር እንዳለብን የተቀመጠ ሥርዓት አይደለም ወይ፡፡ ያውስ ቢሆን ቅዱስ ሲኖዶስ ይህ
ነው ብሎ ሳይወስን አንድ ሊቀ ጳጳስ ብቻውን ሥርዓት ሊሠራ ይቻለዋል ወይ፡፡
ሌላው ደግሞ በጣም የሚገርመው “ካራ ጸጋ ተዋሕዶ ቅብአት እያሉ መርዝ ረጩ ቃላት ሃይማኖት ይሆናል ወይ፡፡ ሃይማኖት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ማለት ነው በሥላሴ ማመን ነው” የሚለው አገላለጻቸው ነው፡፡ እምነታችን በሥላሴ ማመን ነው በጣም ጥሩ፡፡ እምነታችን ወልደ አብ ወልደ ማርያም ተወለደ ነው በጣም ጥሩ፡፡ እምነታችን መጾም መጸለይ መቁረብ ነው በጣም ጥሩ፡፡ ግን እዚህ ላይ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ እምነታችን በሥላሴ ማመን ነው ስንል ሥላሴን ምን ብለን ነው የምናምናቸው? እንደ ፕሮቴስታንቱ ነው እንደ ካቶሊኩ ነው እንደ ጆቫው ነው ወይስ እንደማን ነው የምናምነው? መጾም መጸለይ መቁረብ ነው ሃይማኖት ብለውናል የማንን ሥጋ በላን የማንንስ ደም ጠጣን ልንል ነው የምንቆርበው? መጀመሪያ እኮ ሃይማኖት ያስፈልጋል ምሥጢረ ሥጋዌን አርቅቆ መማር ያስፈልጋል፡፡ ምሥጢረ ሥጋዌ ነው ዋናው የሃይማኖቶች መከፋፈል ላይ ምክንያት የሆነው፡፡ ሌላው ሃይማኖት አንዲት ናት ብለውና በጣም ትክክል ነው፡፡ ግን ያች ሃይማኖት ማናት? ካራ ተዋሕዶ ቅባት ጸጋ እያሉ መርዝ ይረጫሉ በእውነት ይህ ሃይማኖት ይሆናል ወይ ብለውናል፡፡ ስም የሌለው ሃይማኖት አለ ወይ? አንዲት ናት ያሉን ሃይማታችን ስሟ ማነው? ካራ ነውን? ቅባት ነውን? ተዋሕዶ ነውን? ጸጋ ነውን? ቃል ሃይማኖት ይሆናል ወይ ብለውናል ታዲያ እርስዎ ጵጵስናዎ በማን በኩል ነው ስም በሌለው ሃይማኖት ነውን አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ነው የሚል ማኅተሙም፡፡ አባቶቻችን እርስዎ እንደሚሉት ሁሉ “የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን” ብቻ ማለት አልጠፋቸውም ነበር፡፡ ነገር ግን ኦርቶዶክስ ነኝ ብሎ ሁለት ባሕርይ የሚል ወልድ ፍጡር የሚል ሃይማኖት በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ በጥምቀት ከበረ የባህርይ አምላክ ሆነ የሚሉ አሉ ስለዚህ ከእነዚህ ለመለየት ሲባል “ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን” ተብላ ተዋሕዶ የሚል ጭማሬ ተሰጣት፡፡ ይህ የእምነታችን ስም ነው እምነታችንም “ወልድ ዋሕድ በተዋሕዶ ከበረ” የሚል ነው፡፡ እርስዎ ግን “ወልደ አብ ወልደ ማርያም ተወለደ” ነው ብለው ሸሽተውታል፡፡ እንዴት ነው የጠወለደው በተዋሕዶ ነው በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ነውን በጥምቀት ነውን ይህን አጥርተው መናገር ነበረብዎ እርስዎ ግን ስድብ ስለሚቀናዎ በስድብ ነበር መልሱን የመለሱት፡፡
የሊቃውንት ጉባዔ ያወጣው ጋዜጣ አለ በማለት የተናገሩት አለ፡፡ ጋዜጣው
የሚያወራው የልደት በዓል በ29 እና በ28 የሚለው ነገር በቅዱስ ሲኖዶሱ መልስ ቢሰጥበት የሚል የአንድ ሰው አስተያየት የያዘ ነውው፡፡
የታተመውን በዜና ቤተክርስቲያን እንጅ በሊቃውንት ጉባዔ አይደለም፡፡ የሊቃውንት ጉባዔ እንዲህ አለ በማለት ያልተባለውን መናገር
ያሳፍራል፡፡ የሆነው ሆነና የእምነታችን መሠረቱ ምንድን ነው ለሚለው ጥያቄ መልስ መስጠት ይገባዎት ነበር፡፡
አዳምጡትና አስተያየታችሁን ስጡን፡፡
,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,
https://youtu.be/PleZb54qzgM
,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,
https://youtu.be/PleZb54qzgM
No comments:
Post a Comment