Friday, December 25, 2015

ዘጠኙስ ወዴት አሉ? (ሉቃ 17÷17)------ክፍል 3

© በመልካሙ በየነ
ታህሳስ 15/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
እስከመጨረሻው የጸናውን ለማወቅ ወደ ራስቅል ኮረብታ ወደ ቀራንዮ እንውጣ፡፡ ዮሐ19÷25 ጀምራችሁ ተከተሉኝ፡፡ ነገር ግን በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ (እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም) የእናቱም እህት (ሰሎሜ የእናቱ የእመቤታችን እኅት ናት፡፡ ሃና ከሞተች በኋላ የቀለዮጳን ሚስት አግብቶ ወልዷታል)፣ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም (ማርያም ባውፍሊያ) መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር፡፡ ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀመዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን አንች ሴት እነሆ ልጅሽ አላት፡፡ ከዚህ በኋላ ደቀመዝሙሩን እናትህ እነኋት አለው፡፡ ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀመዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት ይላል፡፡ እንግዲህ ከ12 ቱ ደቀመዛሙርት መካከል መስቀሉ ስር የተገኘው ዮሐንስ ወንጌላዊ ብቻ ነው፡፡ መከራ ላይ እንዲህ ነው ሁሉም ይሸሻል ሁሉም ይርቃል፡፡ አበርክቶ ሲመግብ የተመገበው ሁሉ ዛሬ ላይ የለም፡፡ 5 ገበያ ሕዝብ 4 ገበያ ሕዝብ ከበረከቱ የተመገበው ዛሬ የለም፡፡ ያ መልኩን ለማየት፣ ፈውሱን ለመቀበል፣ከበረከቱ ለመሳተፍ ይከተለው የነበረው ሁሉ ዛሬ ሸሽቷል፡፡ ከዋለበት የዋሉት ካደረበት ያደሩት ሃብት ንብረታቸውን ቤት ልጆቻቸውን ሥራቸውን ሁሉ ትተው የተከተሉት ደቀመዛሙርቱም ራሳቸው በፍርሐት ተይዘው ሸሹት፡፡
እነዚህ 10 ለምጻሞችም እንዲሁ ናቸው፡፡ በዘመናቸው ለምጽ የወጣበት ሰው ኃጢአተኛ ነውና ከከተማ ርቆ ይጣላል፡፡ እንግዲህ እነዚህም እንዲሁ ናቸው፡፡ ዓለም ንቋቸው ሰው ጠልቷቸው የሰው ፍቅር ርቋቸው ከዓለም ሁሉ ተገልለው ለብቻቸው ከከተማ ዳር አውጥተው የጣሏቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን አምላካችን ክብር ምስጋና ይድረሰውና ኃጢአተኛን የማይጠላ እውነተኛ አምላክ ስለሰው ፍቅር ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከንጽሕተ ንጹሐን ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ ሕሙመ ሥጋን በተአምራት ሕሙመ ነፍስን በትምህርት እየፈወሰ ሲመጣ እነዚህንም ተገናኛቸው፡፡ ዓለም የናቃቸውን ሰው የጠላቸውን እርሱ ቀረባቸው፡፡ እነርሱም ተገቢ የሆነውን ልመና አቀረቡ፡፡ “እየጮኹ ኢየሱስ ሆይ አቤቱ ማረን” አሉ፡፡ እርሱም የኃጥአንን ለመና ሰማ ከዚያም “ኺዱ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ” አላቸው፡፡ ካሕናት እንዲህ ያለ ትልቅ ክብርና ጸጋ አላቸው፡፡ አምላክ ሲሆን እዚያው ላይ ማንጻት ሲቻለው እንዴት ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ ይላቸዋል? ንስሐ ግቡ ራሳችሁን ለካሕናት አሳዩ የማሰር እና የመፍታት ሥልጣንን የሰጠኋቸው ናቸውና፡፡ እነርሱም የአምላክን ቃል አክብረው ራሳቸውን ለካህናት ሊያሳዩ ሄዱ  እነሆም ሲሄዱ ነጹ፡፡ ይህን ከለምጽ መንጻታቸውን ግን ለየግል ጥቅማቸው ተጠቀሙበት፡፡ ዛሬም እንዲሁ ነው ንስሐ እንገባለን ከደዌ ዳኛ ከአልጋ ቁራኛ እንፈወሳለን ሥጋውን እንበላለን ደሙን እንጠጣለን ነገር ግን ይህን ሁሉ ቸርነት ለኃጢአት እንጠቀምበታለን፡፡ ዲቁና፣ ቅስና፣ ቁምስና፣ ጵጵስናን አምላክ ያድለናል እኛ ግን ላልሆነ ነገር እንጠቀምበታል፡፡ መንጻታቸው ከሰው ጋር እንደሰው የሚያስቆጥራቸው ስለሆነ በዚያው እንደነጹ ያነጻቸውን አምላክ ተመስገን ሳይሉ እንደወጡ ቀሩ፡፡ ነገር ግን ከእነርሱም አንዱ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ በታላቅ ድምጽ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፡፡ እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግንባሩ ወደቀ እርሱም ሳምራዊ ነበር፡፡ ኢየሱስም መልሶ ዐሥሩ አልነጹምን ዘጠኙስ ወዴት አሉ? ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም አለ፡፡ እርሡም ተነሣና ሂድ እምነትህ አድኖሃል አለው፡፡ እንግዲህ የነጹት ዐሥር ነበሩ መንጻቱን አምኖ ያነጻውን ለማመስገን የመጣ ግን አንድ ቅዱስ ብቻ ነው፡፡ ቅድስናው አምላክ መስክሮለታል “ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር” ብሎ ቅዱስ ማለት ልዩ ማለት ነው፡፡ ከሌሎች አስተሳሰብና አመለካከት ተለይቶ ተገኝቷል፡፡ አንድ ሲሆን በዘጠኙ ሃሳብና ምክር ሳይታለል ያዳነኝ ከለምጽም ያነጻኝ አምላኬን ሳላመሰግነው የትም አልሄድም ብሎ ተመልሶ ስለተደረገለት ምስጋና አቅርቧል፡፡
የቀሩቱ ዘጠኞቹ ግን የተደረገላቸውን ድንቅ ነገር ተጠቅመው ተመለሰው ወደ ዓለም ገብተዋል፡፡ ታጥቦ ጭቃ የሚባለው እንዲህ አይነቱ ተግባር ነው፡፡ ስለዚህ አምላካችን ያደረገልንን ውለታ ዘንግተን ዘጠኙስ ወዴት አሉ? ከመባል ይሰውረን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን፡፡

ዘጠኙስ ወዴት አሉ? (ሉቃ 17÷17)------ክፍል 2

© በመልካሙ በየነ
ታህሳስ 14/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
…እስኪ ወደ መከራው ሰዓት እንሂድ፡፡ ማቴ 26÷20 ላይ እንዲህ ይላል “በመሸም ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀመዛሙርት ጋር በማእድ ተቀመጠ ይላል፡፡ እንግዲህ አሁን 5 ሺህ ሕዝብ የለም 4 ሽህ ሕዝብም የለም አሁን የቀሩት ከዋለበት የሚውሉት ካደረበት የሚያድሩት ደቀመዛሙርቱ ብቻ ናቸው፡፡ ከእነዚህ 12 ቱ መካከልስ እስከ መጨረሻው የሚጸና እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ የሚሄድ ማነው? አሁን እዚህ ላይ እራት እየበሉ ሁለት ነገሮች ተከውነዋል፡፡ የመጀመሪያው ነገር ይሁዳ አይሁድ የመዘኑለትን ሰላሣ ብር በከረጢቱ ይዞ አብሯቸው መቀመጡ ነው፡፡ ሌላኛው ነገር ደግሞ የጴጥሮስ “ሁሉም ባንተ ቢሰናከሉ እኔ ከቶ አልሰናከልም” ያለው መልስ ነው፡፡ እንግዲህ እዚህ ላይ ይሁዳ የሚስቱ ወንድም የሆነውን ቀማኛ እና ሽፍታ በርባንን እንዲፈቱለትና ኢየሱስ ክርስቶስን ደግሞ እንዲይዙት ከአይሁድ ጋር ምክሩን ጨርሶ የሚያሲዝበትን ምቹ ጊዜ ይፈልግና ያመቻች ነበር፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም ይህን ያውቅ ስለነበር እንዲህ አለ “እውነት እላችኋለሁ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል” በዚህ ሰዓት ደቀመዛሙርቱ ሁሉ እጅግ አዝነው “ጌታ ሆይ እኔ እሆንን” እያሉ ይጠይቁት ነበር፡፡ እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው “ከእኔ ጋራ እጁን በወጭቱ ያጠለቀ እኔን አሳልፎ የሚሰጥ እርሱ ነው” ሲል ይሁዳ ራሱን ያውቅ ነበርና “ መምህር ሆይ አኔ እሆንን አለ ኢየሱስም መልሶ አንተ አልህ” አለው፡፡ ጌታ በልማዱ ስድስቱን አቁሞ ስድስቱን አስቀምጦ ይዞ ይበላሉ ይመገባሉ፡፡ ዛሬ የቆሙ ነገ ይቀመጣሉ ወጥ የሚያወጣው በተራ ነው፡፡ ጌታ እያወጣ ይበላል አውጡልኝ አይልም ስድስተኛው ለአምስቱ ለራሱም እያወጣ ይበላል፡፡ በዚህ ቀን ከተቀመጡት አንዱ ይሁዳ ነበር  ወጥ ማውጣትም ተራው ነበርና ከእኔ ጋር እጁን በወጭቱ ያጠለቀ እኔን አሳልፎ ይሰጠኛል” ሲል ይሁዳ እርሱ እንደሆነ አልጠፋውም ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ እንጀራውንና ጽዋውን በየተራ አንሥቶ ባርኮ መግቧቸዋል፡፡ የሐዲስ ኪዳንን የቁርባን ሥርዓት አስተምሯቸዋል፡፡ እንግዲህ የይሁዳ ልብ እንደሸፈተ ነውና ከደቀመዛሙርቱም መካከል አንዱ ቀነሰ ማለት ነው፡፡ ይሁዳ ውሎውና አዳሩ ከአይሁድ ጋር ሆነ የአባቱን ቤት የጌታውን ጋጣ ዘነጋ፡፡ የይሁዳ ዓይን በሰላሣ ብር ተሸፈነ ፈጣሪውን ለወጠው፡፡ ከ12ቱ ደቀመዛሙርት መካከል 11ዱ ቀሩ ማለት ነው፡፡
ሌላው የሚገርመው ነገር የጴጥሮስ መልስ ነው፡፡ ጴጥሮስ እንዲህ አለ “ሁሉም ባንተ ቢሰናከሉ እኔ ከቶ አልሰናከልም” እንግዲህ ጴጥሮስ በራሱ ተመክቶ ነገ የሚሆነውን የሚደረገውን ነገር ስላላወቀ ከሁሉም ይልቅ ጌታውን አብልጦ እንደሚወደውና ከእርሱም እንደማይሸሽ ፈጥኖ ተናገረ፡፡ ኢየሱስም እንዲህ አለው “እውነት እልሃለሁ በዚች ሌሊት ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ጴጥሮስ ግን አሁንም በራሱ እንደተመካ ነበር “ከአንተ ጋራ መሞት እንኳ የሚስፈልገኝ ቢሆን ከቶ አልክድህም አለ” አምላኩ የሚነግረውን እንኳ ማመን አቃተው፡፡ እስከሞት ድረስም እንደሚታመን በራሱ አንደበት ተናገረ፡፡ በእውነት ግን ጴጥሮስ በዚያች ሌሊት እስከሞት ድረስ ይታመን ይሆን? እናንተ ማቴ 26ን በሙሉ እያነበባችሁ ተከተሉኝ አሁን ይሁዳ መምህር ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን ብሎ ስሞ ለአይሁድ አሳልፎ ሰጥቷቸዋል፡፡ እነርሱም ወደሊቀ ካህናቱ ቀያፋ ወሰዱት፡፡ በዚህ ጊዜ ያ ማንም ቢክድህ አልክድህም እስከሞት ድረስ እከተልሃለሁ ያለው ጴጥሮስ እስከዚህ ግቢ ድረስ በሩቅ ሆኖ ነበር የሚከተለው፡፡ የአይሁድ ጭፍሮችን ፈራ ነገር ግን ደግሞ አልክድህም ያለው ቃል አሰረው ስለዚህ በሩቅ ሆኖ መከተሉን መረጠ፡፡ ቁጥር 69 ላይ ቅዱስ ጴጥሮስ ከቤቱ ውጭ በዐጥሩ ግቢ ተቀምጦ ነበር አንዲት ገረድም ቀርባ አንተ ደግሞ ከገሊላው ከኢየሱስ ጋር ነበርህ አለችው፡፡ እርሱ ግን የምትዪውን አላውቀውም ብሎ በሁሉ ፊት ካደ፡፡ በተድላና ደስታ ዘመን ምንም መከራ ሳይኖር እስከሞት ድረስ እታመናለሁ ብሎ በአፍ መናገር እስከሞት ድረስ መታመን ማለት አይደለም፡፡ አሁንም ደግሞ ሌላኛዪቱ እንዲህ ጠየቀቸው አሁንም አላውቀውም ብሎ ካደ፡፡ አሁንም ለሦስተኛ ጊዜ አነጋገርህ ይገልጥብሃልና በእውነት አንተ ከእርሱ ወገን ነህ አሉት ሰውየውን አላውቀውም ብሎ ለሦስተኛ ጊዜ ካደ፡፡ ከዚህ በኋላ ዶሮ ጮኸ የዚያን ጊዜ ያ ኢየሱስ ክርቶስ የነገረው ቃል ትዝ አለውና መራራ ልቅሶን አለቀሰ፡፡ አሁን በዚህ በመከራው ሰዓት የ5 ገበያ ሕዝብ የለም ቢኖር እንኳ ለመስቀል እንጅ እንዳይሰቀል ለመከልከል አይደለም፡፡ ሌሎችም ደቀመዛሙርት እንዲሁ በየፊናቸው ልብሳቸውን ጥለው ሁሉ የሸሹ አሉ፡፡ (ማር 14÷51-52) ታዲያ እስከመጨረሻ የጸናው ማነው?

ይቀጥላል…

Tuesday, December 22, 2015

ዘጠኙስ ወዴት አሉ? (ሉቃ 17÷17)--- ክፍል 1

© በመልካሙ በየነ
ታህሳስ 12/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
      የቃሉ ተናጋሪ መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን ቃሉን የተናገረውም ለአንድ ከለምጹ ለነጻ ሰው ነው፡፡ ይህ ቃል የተነገረበት ምክንያት ከላይ ከቁጥር 12 ጀምረን የምናገኘው ይሆናል፡፡ “ወደ አንዲት መንደርም ሲገባ በሩቅ የቆሙት ዐሥር ለምጻሞች ተገናኙት እነርሱም እየጮኹ ኢየሱስ ሆይ አቤቱ ማረን አሉ፡፡ አይቶም ኺዱ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ አላቸው፡፡ እነሆም ሲሄዱ ነጹ፡፡ ከእነርሱም አንዱ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ በታላቅ ድምጽ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፡፡ እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግንባሩ ወደቀ እርሱም ሳምራዊ ነበር፡፡ ኢየሱስም መልሶ ዐሥሩ አልነጹምን ዘጠኙስ ወዴት አሉ? ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም አለ፡፡ እርሡም ተነሣና ሂድ እምነትህ አድኖሃል አለው” ይላል እስከ ቁጥር 19 ድረስ ያለው ቃል፡፡ ስለቃሉ የቃሉ ባለቤት እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይሁንልን፡፡
እንግዲህ ከዚህ ቃል የምንረዳው እና የምንማረው ነገር ምንድን ነው? እስከ ፍጻሜ ድረስ መጽናት የሚያስገኘውን ዋጋ እንረዳለን፡፡ አበርክቶ ሲመግብ ሲከተለው የነበረው ህዝብ በኋላ መከራን በመስቀል ላይ ሲቀበል  ሸሽቷል፡፡ የ5 ገበያን ሕዝብ በ 5 እንጀራ እና በ2 ዓሣ እስኪጠግቡ ድረስ አበርክቶ አብልቶ 12 መሶብ ፍርፋሪ ሲነሣ የነበረው የሕዝብ ብዛት የሚገርም ነበር፡፡ ማቴ 14÷21 ላይ “ከሴቶችና ከልጆችም በቀር የበሉት 5 ሽህ ወንዶች ያህሉ ነበር” ይላል እናንተ ቃሉን ከላይ ከቁጥር 16 ጀምራችሁ አንብቡት፡፡ በዚህ የበረከት ሰዓት ሴቶችና ሕጻናት አብረው ተሳትፈዋል ነገር ግን ወንዶች ብቻ ናቸው እንደተመገቡ ተደርጎ የተቆጠሩት ምክንያቱም ሴቶች ሲመገቡ ወንዶች ካዩአቸው ያፍራሉ ሕጻናትም ከሚመገቡት ይልቅ የሚደፉት፣ የሚጥሉት እና የሚያበላሹት ይበዛልና ከቁጥር ውስጥ አልተካተቱም፡፡ እዚህ ላይ እንግዲህ በወንዶች ብቻ ብንወስደው 5 ሺህ ህዝብ እንደተከተለው ልብ ይሏል፡፡ እንደዚሁ ያለ ተመሣሣይ ታሪክ አለ ማቴ 15÷34-38 ድረስ ተመልከቱት፡፡ ቁጥር 38 ላይ ያለውን ልጻፍላችሁ እንዲህ ይላል “የበሉትም ከሴቶችና ከልጆች በቀር አራት ሺህ ወንዶች ነበሩ” ይላል፡፡ እንግዲህ እዚህ ላይ ደግሞ ሰባት እንጀራን እና ጥቂት ዓሣን አበርክቶ 4 ሺህ ሕዝብ በበረከቱ መግቧል፡፡ እዚህ ላይ ልብ በሉ እየተከተለው ያለው ህዝብ ምን ያህል እንደሆነ? ለምን ይህ ሁሉ ሕዝብ ይከተለዋል የሚለው መልስ የሚመለሰው በመከራው ጊዜ ነው፡፡ መልኩን ለማየት ይከተለው የነበረው በአይሁድ አጥንቱ እስኪቆጠር ድረስ ተደብድቦ፣ የእሾህ አክሊል ደፍቶ ቀራንዮ ላይ በመልዕልተ መስቀል ላይ ሲሰቀል ለንጊኖስ ጎኑን በጦር ሲወጋው ያን ጊዜ ይሸሹታል፡፡ ምክንያቱም ደም የሸፈነውን ፊቱን መመልከት አይፈልጉምና፡፡ ሲያበረክት ለመመገብ የተከተሉትም ተርቦ ፍሬ አልባ ወደ ሆነችው ዕጸ በለስ ሲቀርብና ፍሬ ሲያጣባት ያን ጊዜ በለስን ሲረግም ይሽሹታል አንድም በመስቀል ላይ ሆኖ ተጠማሁ ሲል የራሱን ጥማት የማያረካ እኛን እንዴት ይመግበናል ብለው ይሸሹታል፡፡ (ማቴ 21÷19፣ ማቴ 27÷48፣ ዮሐ 19÷28) ፈውስን ሽተው የተከተሉትም እንዲሁ በአይሁድ እጅ በፈቃዱ ተይዞ ሲሰቀል ፈያታዊ ዘጸጋም (ዳክርስ) ራስህን አድን እያለ ያልተገባን ንግግር ሲናገር ሲሰሙ ይኼስ ራሱንም ማዳን አልተቻለውም እንኳን እኛን ሊያድን ብለው ትተውት ይሸሻሉ፡፡ (ማቴ 27÷42) ይሸሻሉ የምላችሁ በልባቸው ነው እንጅ በአካልማ ድሮ ነው ችግራቸው ሲፈታ  የሸሹት፡፡ የሰው ልጅ የሚገርመው ታሪኩ እዚህ ላይ የሚጀምር ነው፡፡ ሲያዝ እና ሲለቀቅ በጣም ትልቅ የሆነ ልዩነትን ያሳያል፡፡ በህመም ወቅት እጅግ ከባድ መከራና ሃዘን በደረሰበት ወቅት የሚሰማው አምላኩን የማክበርና በአምላኩ ትእዛዝ የመሄድ ስሜትና በኋላ ይህ ሁሉ አልፎ የደስታ ጊዜ ሲተካለት የሚኖረው ስሜት ይለያያል ስለዚህም አብሮ ፈጣሪውን በደስታው ይለውጠዋል፡፡ በመከራው ጊዜ፣ በፈተናው ጊዜ በስቃዩ ጊዜ፣ በህመሙ ጊዜ፣ በረሃቡ እና በማጣቱ ጊዜ ስእለት የማይሳልበት ቤተክርስቲያን የለም፡፡ አምላክ መሐሪ ነውና ይቅር ይለዋል፣ ይምረዋል በበረከት በደስታ በፈውስ በጥጋብ ይጎበኘዋል ያን ጊዜ የተሳለውን ስእለት እንኳ አይመልስም ኖኅ እንደላከው ቁራ በዚያው እንደወጣ ይቀራል፡፡ ከላይ እየተመለከትነው የሚገኘው ይህንን መሰል ድርጊት ነው፡፡ በዚህ በበረከቱ ሰዓት 5ም 4ም ሺህ ሕዝብ ተሳታፊ ሆኗል፡፡ አሁን ይህ ሕዝብ መከራው ላይስ ይሳተፍ ይሆን?

ይቀጥላል….

Friday, December 18, 2015

‹‹እኛን ያዳነን ከሦስቱ ልደታት የበለጠው ልደት ነው››

© በመልካሙ በየነ
ታህሳስ 8/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
አምላካችን ፍጥረትን መፍጠር የጀመረው እሁድ ዕለት ሲሆን ከሥራው ሁሉ ያረፈው ደግሞ በ7ኛው ቀን ቀዳሚት ሰንበት ነው፡፡ የፍጥረት መጀመሪያው ሰማይና ምድር የፍጥረት መጨረሻው ደግሞ አዳም ነው፡፡ አዳም እንዴት ተወለደ? የአዳም ልደት ከኅቱም ምድር ነው፡፡ እግዚአብሔርም አለ “ሰውን በመልካችን እንደምሳሌያችን እንፍጠር… እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፣ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” ዘፍ1፥26-27 የአዳም ልደት እንዲህ ያለ ነው፡፡ ይህ ልደት በሰው ዘር ውስጥ የዓለማችን ቁጥር አንድ ልደት ነው፡፡ ከምድር አፈር አዳም የተወለደበት ልደት ግሩም ነው፡፡ የአዳም ልደት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በአዳም መወለድ ብቻ የቀረ ነው፡፡ ከአዳም በኋላ በዚህ መልኩ የተወለደ ሰው የለም፡፡ ይህ ልደት ለእኛ ምን ጠቀመን? ምንም አልጠቀመንም ለመዳናችን ሳይሆን ለመጥፋታችን መነሻ ነበር፡፡ አዳም ትእዛዝን የሻረ ሰው ከሆነ በኋላ እንጅ አፈር ትቢያ እንደነበረ አልነበረምና፡፡
ሌላው እና አስገራሚው ልደት የሴቲቱ የሔዋን ልደት ነው፡፡ የሔዋን ልደት ደግሞ ከአዳም ልደት የተለየ ልደት ነው፡፡ “እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ከባድ እንቅልፍን ጣለበት አንቀላፋም ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወስዶ ስፍራውን በሥጋ ዘጋው” ዘፍ2፥21 አዳም ከኅቱም ምድር እንደተገኘ ሔዋን ደግሞ ከኅቱም ገቦ (ጎን) ተገኝታለች፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ሶሪያዊ “ኦ ዝ መንክር ነሥአ አሐደ አፅመ እም ገቦሁ ለአዳም ወለሐኮ እምኔሁ ብእሲተ ወኵሉ ፍጥረተ ዕጓለ እመሕያው”  ከአዳም ጎን አንዲት ዐጽም መንሳት ምን ይደንቅ? ከእርሱ ሴትን ፈጠረ የሰው ፍጥረትንም ሁሉ ፈጠረ በማለት የሔዋንን ልደት ያስረዳል፡፡ (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ) የሔዋን ልደትስ ለእኛ መዳን ምን ጠቀመን? እንደ አዳም ሁሉ ለመጥፋታችን እንጅ ለመዳናችን የሚጠቅም ልደት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሔዋን ባደረገችው አመጽ የገነት ደጅ ተዘጋ ስለሚል ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም፡፡ ዘፍ 3 ን ስናነብብ የምንመለከተውም የጥፋታችንን ውጥንና ፍጻሜ ነው፡፡ እንግዲህ እነዚህ ሁለቱ ልደታት እኛን ማዳን አልተቻላቸውምና ሌላ ልደት አስፈለገ፡፡
ሦስተኛው የሰው ልጅ ልደት የቃየን ልደት ነው፡፡ የቃየን ልደት በዘር በሩካቤ የተወለደው ልደት ነው፡፡ ከአፈር የተፈጠረው አዳምና ከአዳም ጎን የተፈጠረችው ሔዋን ሁለቱ ባደረጉት ሩካቤ ቃየን ተወለደ፡፡ በዘር በሩካቤ የተወለደ የመጀመሪያው ሰው ቃየን ነው፡፡ በእርግጥ ሔዋን መንታ ወልዳለች ሉድ የቃየን መንትያ ናት፡፡ ከዚህ በኋላ ደግሞ አቤልና አቅሌማ ተወልደዋል፡፡ (ዘፍ4 ን ተመልከት) አሁን እኛ የምንወለደው ልደት እንዲህ ያለውን ልደት ነው፡፡ ከአባትና ከእናት በዘር በሩካቤ የምንወለደው ልደት ይህ ሦስተኛው ልደት ነው፡፡ የአዳም የሥጋ አባትና እናት ማነው?  የሔዋንስ? የቃየንስ? የሥጋ አባትና እናት መቁጠር የምንጀምረው ከአዳም አባትነትና ከሔዋን እናትነት ነው፡፡ ታዲያ ይህ ልደት ለእኛ መዳን ምን ጠቀመን? ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ፣ ዳንኤል፣ ዘካርያስ፣ ሕዝቅኤል፣ አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ… እነዚህ ሁሉ በዚህ መልኩ የተወለዱ ቅዱሳን ናቸው ግን ጽድቃቸው ወደ ገነት ማስገባት አልተቻለውም፡፡ ምክንያቱም በአዳም በኩል የመጣው ኃጢአት መርገም ለእነርሱም ተርፎ ስለነበር፡፡ ታዲያ ለገነት ለመንግሥተ ሰማያት ያበቃን ልደት የትኛው ልደት ነው?

ለገነት ያበቃን ልደት አዳም ከኅቱም ምድር፣ ሔዋን ከኅቱም ገቦ፣ ቃየን በዘር በሩካቤ እንደተገኙ ሁሉ በዘር በሩካቤ የተገኘችው እመ ብርሃን ድንግል ማርያም ያለ ዘር ያለ ሩካቤ በኅቱም ድንግልና የለአባት ጸንሳ የወለደችው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ነው፡፡ የአዳም መርገም ያልነካት ንጽሕት ዘር ድንግል ማርያም ቅድመ ጸኒስ፣ ጊዜ ጸኒስ፣ ድኅረ ጸኒስ፣ ቅድመ ወሊድ፣ ጊዜ ወሊድ፣ ድኅረ ወሊድ ድንግል ናት፡፡ ያለዘር ያለሩካቤ ጸንሳ የወለደችው ልደት ከእነዚህ ሦስቱ ልደታት ሁሉ የበለጠ ልደት ሆነልን፡፡ በሔዋን ምክንያት የተዘጋው ገነት በድንግል ማርያም ምክንያት ተከፈተልን፡፡ ለድኅነታችን ምክንያት፣ የአዳም ተስፋ፣ የነቢያት ትንቢት የተፈጸመላት፣ አምላክን ጸንሳ ለመውለድ በቅታ፣ ነጽታ የተገኘች መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለባት ንጽሕት ዘር ድንግል ማርያም ከእናቷ ሃና እና ከአባቷ ኢያቄም መወለዷ ለእኛ ጠቅሞናል፡፡ ምክንያቱም ከእነዚህ ልደታት ሁሉ የበለጠውን ትልቁን ልደት አምጥታልናለችና፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ አርጋኖን በተሰኘ መጽሐፉ ድንግልን ሲያመሰግን እንዲህ ይላል “እግዚአብሔር ከሰው ልጅ የማይተባበሩ ሦስት ልደታትን ተወለደ፡፡ እኔም አውቄ አደነቅሁ፡፡ ባራተኛው እንጅ የበጎ ዕረፍት አላገኘሁም፡፡ አዳም ከኅቱም ምድር የተወለደ በተፈጥሮ ነው፡፡ እኔን ግን የጠቀመኝ የለም፡፡ ሔዋንም ከአዳም ግራ ጎን ተወለደች እርሷም በተፈጥሮ ነው፡፡ ለእኔ ግን የጠቀመችኝ የለም፡፡ ቃየንም እንደ ሰው ሁሉ በዘር በሩካቤ ተወለደ የጠቀመኝ የረባኝ የለም፡፡ ስንኳንስ እኔን ራሱንም አልጠቀመም፡፡ እሊህ ሦስቱ ልደታትም ለማንም ለማን አይረቡም አይጠቅሙምም፡፡ ክርስቶስ ግን ያለዘር ያለሩካቤ ከድንግል ተወለደ ለሁሉ የሚረባ ለሁሉ የሚጠቅም ሆነ፡፡ ለዚህ ልደት መስገድ መገዛት ይገባል፡፡ ክብር ምስጋና ለዚህ ልደት ይገባል፡፡ ጌትነትና ገናንነት፣ ኃያልነት፣ አዚዝነት፣ እልልታ፣ ግርግርታ ለዚህ ልደት ይገባል፡፡ (አርጋኖን ዘሰኑይ ምእራፍ 2 ቁጥር 4-7)

Tuesday, December 15, 2015

‹‹ለሃሜት አሳልፈው ሰጡን›› (ክፍል 2)

© በመልካሙ በየነ
ታህሳስ 5/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
…እኔ በመኪናም ይሁን በእግሬ ስጓዝ አብረውኝ የሚጓዙ ሰዎችን ንግግር ማዳመጥ ደስ ይለኛል፡፡ ምክንያቱም ስለምማርበትና ሰውም ስለምመክርበት እኔም ስለምመከርበትና ስለምገሰጽበት ነው፡፡ እናም ስጓዝ የሰማሁትን ላካፍላችሁ ወደድሁ መልካም ንባብ!
በክፍል 1 (http://melkamubeyene.blogspot.com/2015/12/1.html) እንደተመለከትነው የኤማሑስ መንገደኞች አርስ በርሳቸው የሚነጋገሩት ነገር የተቀደሰ በመሆኑ የጉዞ ጉባኤ ብንለው ደስ ይለኛል፡፡ በስሜ ሁለት እና ከዛ በላይ ሆናችሁ ብትሰበሰቡ በዚያ መካከል እኔ እገኛለሁ ያለን አምላክ በእነዚህ በሁለቱ መንገደኞችም መካከል ተገኘ፡፡ የዚያን ጊዜ ወቅታዊው ጉዳይ የክርስቶስ በአይሁድ መገረፍ፣ መደብደብ፣ መሰቀል፣ መሞት፣ መነሣት ነበር እነዚህም የሚነጋገሩበት ጉዳይ ወቅታዊ ስለነበረው ነገር ነበር፡፡ እኔም የሰማኋቸው ሰዎች እንዲሁ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያነጣጠሩ ናቸው፡፡ አንድ የታወቀ ገዳም አስተዳዳሪ ናቸው ከሆነ ሰው ጋር ሲሄዱ “በ5 ሚሊዮን ብር ዕዳ የተከሰሰ የሃገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ እንዴት ሌላ ሹመት ይሰጠዋል?” ይላሉ፡፡ ያ እሳቸው የሚሉት ሰው ያሉትን ያህል እዳ ይኑርበት አይኑርበት ማን ያውቃል? ሊኖርበት እንደሚችል ሁሉ ላይኖርበትም ይችላል፡፡ ነገር ግን ተበርዘናል የአሁኑ ወቅታዊ ጉዳይ የሆነው ተሐድሶ ከገንዘብ ጋር ንክኪ እየፈጠረ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሰላም እንዳይኖር እየፈጠረ ያለው ችግር ለሃሜት አሳልፎ እንደሰጠን እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ዝም እንዳንል ዝም የሚያስብል ጉዳይ የለንም እንዳንናገርም ተናጋሪዎች ተሳዳቢዎች ሃሜተኞች ተንኮለኞች ምቀኞች ወዘተ እንባላለን፡፡ ታዲያ ወዴት ልናዘነብል እንችላለን?
ተሐድሶዎቹ ዓላማቸው ብዙ ዕቅዳቸው ረዥም ነው፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ በቀላሉ ሰርጎ መግባት አይቻልም መጀመሪያ ክፍተታችንን ማዎቅ አለባቸው ያንን ያወቁትንና ያጠኑትን ክፍተት ደግሞ ውሻ በቀደደው.. እንዲሉ ይገቡበታል ምክንያቱም ጅቦች ናቸውና፡፡ ቤተክርስቲያንን ለመቆጣጠር የሰበካ ጉባኤ አባልና ስራ አስፈጻሚ፣ ዲያቆን፣ ሰባኪ፣ ቄስ፣ ዘማሪ፣ ከፍ ብሎም ቆሞስ፣ ኤጲስ ቆጶስ፣ ጳጳስ፣ ሊቀ ጳጳስ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ ላይ በየቦታው በየአጥቢው ብጥብጥ ሲፈጠር የምንመለከተው፡፡ ሁሉም የሰበካ ጉባኤ ጸሐፊ፣ ሰብሳቢ፣ ገ/ያዥ መሆን ይፈልጋል ሁሉም የቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ መሆን ሂሳብ ሹም መሆንን ይሻል፡፡ ሁሉም የአንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያን መሪ አስተዳዳሪ መሆን ይፈልጋል ድሮ አባቶቻችን ይሸሹት የነበረውን ሥልጣንና ሹመት የዛሬዎቹ ደግሞ አብዝተው ይፈልጉታል፡፡ ድሮ ጳጳስ ለመሆን የተመረጠ አባት “አይገባኝም” ብሎ ይሸሽ ነበር የዛሬዎቹ ግን ስለሚገባኝ “ጵጵስና እንድትሾሙኝ” የሚል ማመልከቻም ሳያስገቡ አይቀሩም፡፡ ታዲየ ይሄው  እኛም እኮ ለሃሜት ተላልፈን ተሰጠን አማናቸው አይደል፡፡ ሳይገባቸው እንደተገባቸው አድርገው የሚቀርቡ ሰዎች ለብዙ መከራና ስቃይ እየዳረጉን ነው፡፡ ግዴለሽነትን፣ ምን አገባኝነትን፣ ማን አለብኝነትን አስተማሩን፡፡ በመናፍቁ ዘንድ ያለውን ሥርዓት አልባነት እኛ ውስጥም ጨመሩት፡፡ አሥራትና በኩራቱን ታወጣለህ የሆነ አስተዳዳሪ ነኝ ባይ አልያም ሂሳብ ሹም ነኝ ባዩ የራሱን ፎቅ ይሠራበታል፡፡ አንተም አሥራት ማውጣትህን ታቆማለህ ምክንያቱም ግለሰቦች ናቸዋ እየበለጸጉበት ያለው፡፡ ግን ትክክል ሥራ ሠርቻለሁ ትክክለኛ እርምጃ ወስጃለሁ ብለህ ታምናለህ? በፍጹም አያሳምንም፡፡ አሥራት በኩራት አውጣ ያለህ ፈጣሪ ነው ያወጣኸውን ገንዘብ የወሰደው ደግሞ ሰው ነው ላንተ ዋጋህን የሚከፍልህ ፈጣሪ እንጅ ሰው አይደለም ስለዚህ በሁለት መንታ ሃሳቦች መካከል ይጥሉሃል ማለት ነው፡፡ ከዚያስ ግዴለሽ ትሆናለህ “አሥራት ባወጣ የሚበላው እገሌ” እያልክ ትሸሻለህ፡፡ ታዲያ አንተ ለሃሜት ተላልፈህ አልተሰጠህም?

ሳንወድ በግድ ለሃሜት ተላልፈን እየተሰጠን ነው፡፡ ቤተክርስቲያናችን የምትፈልገው እንደ ኤማሑስ መንገደኞች ያሉ ሰዎችን ነው፡፡ ስለዚህ እንደነርሱ ልንሆን ይገባል፡፡ እነርሱ አይሁድ እንዲህ አድርገው ሰቀሉት እንዲህ አድርገው ገደሉት ካሉ በኋላ መጨረሻ ላይ “ወንሕነሰ ነአምን ቦቱ ከመ ውእቱ ሀለዎ ያድኅኖሙ ለእስራኤል” እኛ ግን እርሱ እስራኤልን ያድናቸው ዘንድ እንዳለው እናምናለን ብለው ነው የራሳቸውን አቋም የገለጹ፡፡ ዛሬ ግን እገሌ እንዲህ አደረገ፣ እገሊት እንዲህ አደረገች ከማለት ባለፈ እኔ ብሆን እንዲህ አደርግ ነበር የሚል የቀና መንፈስ የለንም፡፡ ይልቁንም እነርሱ በሳቱበት እንስታለን በወደቁበትም እንወድቃለን እንጅ፡፡ ስለዚህ ከሁለቱ የኤማሑስ መንገደኞች ከሉቃስና ኒቆዲሞስ ልንማር ያስፈልገናል ማለት ነው፡፡

‹‹ለሃሜት አሳልፈው ሰጡን›› (ክፍል 1)

© በመልካሙ በየነ
ታህሳስ 1/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ትምህርታችንን በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 24 እንጀምራለን፡፡ “ወይእተ ዕለተ እንተ የሐውሩ ፪ቱ እምውስቴቶሙ ሀገረ እንተ ትርኅቅ እምኢየሩሳሌም  መጠነ ፷ ምዕራፍ እንተ ስማ ኤማሑስ”   በዚያን ቀን ከርሳቸው ሁለቱ ከኢየሩሳሌም ስሳ ምዕራፍ ያህል የሚርቅ ኤማሑስ ወደምትባል አገር ሲሄዱ (ሁለቱ የተባሉት ሉቃስና ቀለዮጳ ናቸው ሉቃስን ዘውእቱ  ቀለዮጳ ይለዋል ብሎ ሉቃስና  ኒቆዲሞስ ናቸው ይላል) “ወይትናገሩ በበይናቲሆሙ በእንተ ኩሉ ዘኮነ”  ስለተደረገው ነገር ሁሉ ሲጫወቱ “ወእንዘ እሙንቱ ይትናገሩ ወይትኃሠሥዎ ለዝንቱ” ይህን ሲነጋገሩ ሲመራመሩ “ቀርቦሙ እግዚእ ኢየሱስ ወሖረ ምስሌሆሙ” ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ቀርቦ ከርሳቸው ጋራ ሄደ፡፡ “ወተእኅዘ አዕይንቲሆሙ ከመ ኢያእምርዎ” እንዳያውቁት ዓይናቸው ከእውቀት ተገታ “ወይቤሎሙ እግዚእነ ምንትኑ ዝንቱ ነገር ዘትትናገሩ በበይናቲክሙ እንዘ ተሐውሩ ትኩዛኒክሙ” እያዘናችሁ ስትሄዱ እርስ በርሳችሁ የምትነጋገሩት ይህ ነገር ምንድን ነው አላቸው፡፡ “ወአውስአ ፩ዱ እምኔሆሙ ዘስሙ ቀለዮጳ” ከርሳቸው አንዱ ቀለዮጳ የሚባለው መለሰ “ወይቤሎ አንተኑ ባሕቲትከ ነግድ ዘኢሀለውከ በኢየሩሳሌም” አንተ ብቻህን በኢየሩሳሌም አልነበርህምን? “ወኢያእመርከኑ ዘኮነ በውስቴታ በዝንቱ መዋእል” በዚህ ወራት በርሷ የተደረገውን አላወቅህምን አለው፡፡ “ወይቤሎሙ እግዚእ ኢየሱስ ምንትኑ ውእቱ” ጌታም ምንድን ነው አለው፡፡ “ወይቤልዎ በእንተ ኢየሱስ ናዝራዊ” የናዝሬቱን የኢየሱስን ነገር ይነግሩት ጀመር፡፡ “ብእሲ ጻድቅ” ደግ ሰው “ወነቢይ” ዐዋቂ የሆነ “ዘኮነ ከሃሌ በቃሉ ወበምግባሩ በቅድመ እግዚአብሔር ወበቅድመ ሰብእ” በተናገረው ነገር በሚሠራው ሥራ በእግዚአብሔር ዘንድ በሰውም ዘንድ ማድረግ የሚቻለው “ወዘከመ አግብእዎ ሊቃነ ካህናት ወመኳንንቲነ” የካህናት አለቆችና አለቆቻችን አሳልፈው እንደሰጡት “ወሰቀልዎ” ሰቀሉት  “ወንሕነሰ ነአምን ቦቱ ከመ ውእቱ ሀለዎ ያድኅኖሙ ለእስራኤል” እኛ ግን እርሱ እስራኤልን ያድናቸው ዘንድ እንዳለው እናምናለን፡፡ /ሉቃ 24 13-21/
የኤማሑስ መንገደኞች ሉቃስና ኒቆዲሞስ እየተነጋገሩ ይሄዱ የነበረው ስለኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ ያለበደሉ፣ ያለኃጢአቱ ለሰው ፍቅር ሲል ለመስቀል ሞት ተላልፎ መሰጠት ስለነበር ኢየሱስ ክርስቶስ ከእነርሱ ጋር አብሮ መጓዝ ጀመረ፡፡ በጉዞው መካከልም ስለምን እንደሚነጋገሩ ጠየቃቸው ፍቅራቸው እጅግ ብዙ ስለነበር ኢየሱስ ክርስቶስ የሚባለውን አምላክ አይሁድ ተመቅኝተው እንዴት እንደገደሉት ነገሩት፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ፣ ደግ፣ ለድሆች የሚራራ፣ ለበሽተኞች መድኃኒት፣ ለተራቡት እውነተኛ ምግብ ለተጠሙት ደግሞ እውነተኛ መጠጥ እንደሆነ እነርሱ በጣም የሚወዱት አምላክነቱን የማይጠራጠሩ እንደሆኑ አስረዱት፡፡ ከማን ጋር እንደሚነጋገሩ ባወቁ ኖሮ ዝቅ ብለው ወድቀው በሰገዱለት ነበር ነገር ግን ማን እንደሆነ ስላላወቁ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲያምን ሊያስተምሩት ነበር የሞከሩ፡፡ ምንም እንኳ በኋላ አምላካቸው ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን የሚያውቁ ቢሆኑም ማለት ነው፡፡ እነዚህ የተቀደሱ የኤማሑስ መንገደኞች አይሁዳውያንን ለማማት ያበቃቸው የክርስቶስ ፍቅር ነው (በእርግጥ ይህ ሐሜት አይደለም ምክንያቱም አይሁድ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የሠሩትን እውነተኛ የግፍ ሥራ ስለነበር የሚነጋገሩ) ስለስሙ በሚነጋገሩት ተጓዦች መካከል አምላክ ተገኝቶ ባረካቸው፡፡ ሰውና ሰው ሲገናኝ የሰውን ጥፋት ያቅዳል፣የሌላውን ውድቀት ይመኛል፣ ሰውን እንዴት ማጥፋት እንደሚቻል ይወያያል፣ ሰውን በሌለበት በተሳለ ምላስ በሐሜት ይበላል እንጅ በእውነት የክርስቶስ ፍቅር፣ የእመብርሃን ፍቅር፣ የመላእክት ክብር፣ የቤተክርስቲያን ጉዳይ አገብሮት አንዳች ነገር የሚተነፍስ የሚነጋገር ሰው ከቶ የለም፡፡ እኔ በመኪናም ይሁን በእግሬ ስጓዝ አብረውኝ የሚጓዙ ሰዎችን ንግግር ማዳመጥ ደስ ይለኛል፡፡ ምክንያቱም ስለምማርበትና ሰውም ስለምመክርበት እኔም ስለምመከርበትና ስለምገሰጽበት ነው፡፡ እናም ስጓዝ የሰማሁትን ላካፍላችሁ ወደድሁ መልካም ንባብ…

ይቀጥላል፡፡

Wednesday, December 9, 2015

ኃጢአትየ ዘበንእስየ ወእበድየ ኢትዝክር ሊተ፡፡ /የልጅነቴን ኃጢአትና መተላለፍ አታስብብኝ/ መዝ 24÷7

© በመልካሙ በየነ
ሕዳር 29/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ልበ አምላክ የተባለው ቅዱስ ዳዊት  በመዝሙሩ አምላኩን ሲማጸን “የልጅነቴን ኃጢአትና መተላለፍ አታስብብኝ፡፡ አቤቱ ስለቸርነትህ ብዛት እንደ ምሕረትህ አስበኝ” እያለ ይጸልያል፡፡ የቅዱስ ዳዊት መዝሙር በቁም ላሉት ዕድሜን የሚያረዝም፣ ከሰይጣን ፈተና የሚጠብቅ፣ በበረከትና በምሕረት የሚያኖር ስለሆነ ሁልጊዜም እንጸልየዋለን፡፡ ይህ መዝሙር ለሁሉም የሚገባ ስለሆነ ለሙታን  ፍትሐትም ሳይቀር እንጸልየዋለን፡፡ ሁልጊዜም በቅዳሴ ጊዜ ከዳዊት መዝሙር ሶስት መስመሮችን ወቅቱን የሚዋጁ ዕለቱን የሚመለከቱ ምስባኮች በሚያምረውና በሚመስጠው የዲያቆኑ ድምጽ በሚማርክ ዜማ ይሰበካሉ፡፡ የዳዊት መዝሙር ለማንኛውም አገልግሎት የሚውል ልዩ ጸሎት ነው፡፡ ትንቢትን አቅርቦ የመናገር ጸጋ የበዛለት ነቢዩ ዳዊት ይህንን ልዩ የሆነውን ምስጋናና ጸሎት ለመንፈስ ልጆቹ ሁሉ ሰጥቶናል፡፡ እኛም የተሰጠንን ይህን ልዩ ጸሎት እየተገለገልንበት እየተጠቀምንበት እንገኛለን፡፡
ዳዊት ከትልልቅ ወንድሞቹ ይልቅ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ሆኖ በመገኘቱ ከእረኝነት ወደ ንግሥና ወንበር የተቀመጠ ነቢይ ነው፡፡ ይህ ነቢይ አባቱ እሴይ እናቱ ደግሞ ሁብሊ ይባላሉ፡፡ ሰባት ልዩ ልዩ ሀብታት  ማለትም ሀብተ ትንቢት፣ ሀብተ ክህነት፣ ሀብተ መዊእ፣ ሀብተ ፈውስ፣ ሀብተ በገና፣ ሀብተ መንግሥት እና ሀብተ ኃይል ተሰጥተውታል፡፡ ይህ ጻድቅ ነው እንግዲህ  ከላይ በአርእስቱ ላይ የጻፍነውን የጸሎት ክፍል ያስተማረን፡፡ ዳዊት “የልጅነቴን ኃጢአትና መተላለፍ አታስብብኝ” አለ፡፡  እስኪ ሁላችንም ወደ ልጅነታችን ወደ ሕጻንነታችን እንመለስ በእውነት ያንን ሁሉ ኃጢአታችንን አምላክ ቢቆጥርብን ኖሮ ዛሬን መኖር እንችል ነበር? በደል ሳይመስለን የሰራነው ያ ሁሉ በደል ቢታሰብብን የዛሬዋን ጸሐይ ለመሞቅ እንታደል ይመስላችኋል? ኃጢአት ሳይመስለን የፈጸምነው ያ ሁሉ ኃጢአት ቢቆጠርብን ሰማይን ቀና ምድርን ዝቅ ብለን ለማየት እንታደል ነበርን? በፍጹም፡፡ አምላካችን ምሕረቱ ብዙ፣ ቸርነቱ ምጡቅ ስለሆነ ያንን በደል አልቆጠረብንም አላሰበብንም፡፡ በልጅነቱ ከእንስሳት ጋር ያልረከሰ፣ ሰውን በሽንገላ ከንፈር ያልተናገረ፣ ሰውን ያልበደለ ማነው? በእርግጥ ልጅነት ማለት ምን ማለት ነው? ለሚለው ጥያቄ ተገቢ ምላሽ መስጠት ይገባል፡፡ ጥንተ ፍጥረት አዳም የ30 ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ሄዋንም የ 15 ዓመት ቆንጆ ሆና በአምላክ አምሳያ ከተፈጠሩ እና በገነት መኖር ከጀመሩ በኋላ 7 ዓመት ከ 1 ወር ከ 17 ቀን ሲሞላቸው ሰይጣን አታለላቸውና ከገነት ተባረሩ፡፡ እስከዚያ ቀን  ድረስ ኃጢአት አልሰሩም ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ይህንን አብነት በማድረግ አንድ ሕጻን ከ 7 ዓመት ጀምሮ መጾም፣ መስገድ፣ መጸለይ፣ መመጽወት  አለበት ንስሐ መግባትም አለበት ማለት ነው፡፡ ያ ማለት ግን ከዚያ በፊት መደረጉ ኃጢአት ሊኖረው አይችልም ምክንያቱም ለሚቀጥለው ሕይወታቸው ልምምድ ስለሆነ ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን ከ 7 ዓመት ጀምሮ የሚሠራ ኃጢአት ይታሰብብናል ይቆጠርብናል ማለት ነው፡፡
በልጅነታችን ብዙ በድለናል፣ ብዙ ኃጢአት ሰርተናል፣ ለቤተሰቦቻችን አልታዘዝም ብለናል፣ ቤተሰቦቻችንን ሰርቀናል፣ አባት እናቶቻችንን አላከብር ብለናል ወዘተ እሱ ሁሉ ኃጢአት ነው፡፡ አስቡት እንግዲህ ንስሐ መግባት የጀመርን አሁን ነው ያውም እየገባን ከሆነ ማለቴ ነው በአብዛኛው ግን የኃጢአት ክምር ከምረናል፡፡ እንግዲህ ዳዊት ይህንን ሁሉ አታስብብን ይላል፡፡ ምክንያቱም ዛሬ ላይ ሆነን በልጅነታችን የሰራነውን ኃጢአት ሁሉ ማስታወስ ስለማንችል፡፡ ነገር ግን ዳዊት ይህንን የልጅነቴን ኃጢአት አታስብብኝ ማለቱ የማውቀውንም የማላውቀውንም አታስብብኝ አትቁጠርብኝ ማለቱ ነው፡፡ ይህን ጸሎት ስትጸልዩ የልጅነታችሁን በደል ታስባላችሁ ያንን ያሰባችሁትን ያወቃችሁትን በደል አምላክ እንዳይቆጥርባችሁ ትማጸናላችሁ፡፡ ከዚያ ትዝ ካለን ኃጢአት ውጭ ያለውን ደግሞ እንዲሁ እንዳይቆጥርብን እንለምነዋለን፡፡ የልጅነት ኃጢአት የሚሠራ ፈጣሪን በማስታወስ አይደለም፡፡ ፈጣሪን የምንፈራበት ይህን ባደርግ እንዲህ እሆናለሁ እንዲህ እደረጋለሁ በሚል ስጋት ውስጥ ሆነንም አይደለም የምንሠራው፡፡ በማን አለብኝነት የምንሠራው ነውና አሁንም ፈጣሪን ዘንግተን በድፍረት የምንሰራውን ኃጢአት አታስብብን ምክንያቱም አስተሳሰባችን በአእምሮ እንዳልጎለመሱ ሕጻናት ስለሆነ፡፡

አምላካችን የልጅነታችንን ኃጢአትና መተላለፍ አያስብብን፡፡ አቤቱ ስለቸርነቱ ብዛት እንደ ምሕረቱም ያስበን፡፡

Wednesday, December 2, 2015

ሥጋ ወደም

© በመልካሙ በየነ
ሕዳር 22/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ዲያብሎስ እጅግ በጣም አብዝቶ ማራቅ የሚፈልገው ከምሥጢራት ሁሉ የበላይ ከሆነው “ከምሥጢረ ቁርባን” ነው፡፡ ምሥጢራት ሁሉ የሚደመደሙት በሥጋ ወደሙ ነው፡፡ መሥጢረ ጥምቀት፣ ምሥጢረ ንስሓ፣ ምሥጢረ ተክሊል የሚፈጸሙት በቁርባን ነው፡፡ ይህንን የሚያውቅ የውሸት አባት ዲያብሎስ የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር ከሥጋ ወደሙ ያርቅሃል፡፡ አንተ ግን “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም ከቶ አይጠማም” ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን አምናለሁና ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የነሳውን ሥጋና ደም እመገባለሁ በለው፡፡ /ዮሐ6፥35/ የዘላለም ሕይወትን መውረስ እንደምትፈልግም አሳወቀው፡፡ “ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል” /ዮሐ6፥41/ ስለዚህ ለዘላለም በመንግሥተ ሰማያት ለመኖር ከሰማይ የወረደውን እንጀራ እበላለሁ ብለህ ጠላትህን አሳፍረው፡፡ ጠላት ግን በድፍረት እንድትቀርብ ሊፈትንህ ይችላል፡፡ የምትቀበለውን ሥጋና ደም የዕሩቅ ብእሲ ሥጋና ደም ነው ብሎ ሊያታልልህም ይሞክራል፡፡ አንተ ግን አትስማው የምቀበለው ሥጋና ደም በዕለተ አርብ የተቆረሰውና የፈሰሰውን  ሥጋና ደም ነው በለው፡፡ ሥጋና ደሙም መለኮት የተዋሐደው ነፍስ የተለየው እንጅ ጠላት እንደሚለው መለኮት የተለየው አይደለም፡፡ ጠላት ውጊያውን አሁንም አያቆምም “ንስሓ ሳትገባ ሳትዘጋጅ ተቀበል” ይልሃል፡፡ እርሱን ከሰማኸው የይሁዳ እጣ ፈንታ አንተ ላይም ይደርሳል፡፡ ሳይዘጋጁ ከኃጢአት ሳይነጹ ቢቀበሉት ግሩም ፍዳን የሚያመጣ የሚባላ እሳት ነው፡፡ ይሁዳ በጸሎተ ሐሙስ ከሌሎች ሐዋርያት ጋር ከቁርባኑ ሥርዓት ተካፋይ ነበረ፡፡ ነገር ግን በልቡ የነበረው ጌታን በ30 ብር የመሸጥ ኃጢአት እንደወጣ እንዲቀር አድርጎታል፡፡ /ማቴ26፥14-29/፣ /ማቴ27÷3-9/ ሥጋና ደሙ ግሩም ፍዳ የሚያመጣ ነው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ስለዚህ በንጽሕና በትሕትና ንስሓ ገብቶ ሊቀበሉት ይገባል፡፡ በዚህ መልኩ ለሚቀበለው የዘላለም ሕይወትን የሚያወርስ ጥበብን የሚገልጽ ምሥጢርን ሁሉ የሚያድል ነው፡፡ ለዚህም ነው ካህኑ በቅዳሴ ሰዓት “ንጹሕ የሆነ ከቁርባኑ ይቀበል ንጹሕ ያልሆነ ግን አይቀበል ለሰይጣንና ለመልእክተኞቹ በተዘጋጀው በመለኮት እሳት እንዳይቃጠል በልቡናው ቂምን የያዘ ልዩ አሳብም ያለበት ቢኖር አይቅረብ እጄን ከአፍአዊ ደም ንጹሕ እንዳደረግሁ እንዲሁም ከሁላችሁ ደም ንጹሕ ነኝ፡፡ ደፍራችሁ ወደ ክርስቶስ ሥጋና ደም ብትቀርቡ ከእርሱ ለመቀበላችሁ መተላለፍ የለብኝም በደላችሁ በራሳችሁ ይመለሳል እንጅ፡፡ በንጽሕና ሆናችሁ ባትቀርቡ እኔ ከበደላችሁ ንጹሕ ነኝ” ብሎ እጁን የሚታጠበው፡፡ ዲያቆኑም ተቀብሎ “ይህን የቄሱን ቃል ያቃለለ ወይም የሳቀና የተነጋገረ ወይም በቤተክርስቲያን በክፋት የቆመ ቢኖር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዳሳዘነው በእርሱም እንደተነሣሣ ይወቅ ይረዳ ስለበረከት ፈንታ መርገምን ስለኃጢአት ሥርየት ፈንታ ገሃነመ እሳትን ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቀበላል” ይላል፡፡ ይህ አዋጅ የሚታወጀው ከክርስቶስ ሥጋና ደም ርቀን እንድንቆም ወይም የበይ ተመልካቾች እንድንሆን ተፈልጎ ወይም ለማስፈራራት ተብሎ አይደለም ንስሓ ገብተን፣ የበደልነውን ይቅር ብለን፣ የቀማነውን መልሰን፣ ተዘጋጅተን በንጽህና ሆነን እንድንቀበል ነው እንጅ፡፡ በድፍረት በኃጢአት እንደተጨማለቁ ተዘሎ የሚበላና የሚጠጣ አይደለም ፍዳ መቅሰፍት ያመጣልና፡፡ ጠላት ግን ይህንን አዋጅ እያሳሰበና እንደተመቸው እየተረጎመ “ሥጋ ወደሙን ለመቀበል የበቃህ አይደለህም” ብሎ ከሥጋ ወደሙ ያርቅሃል፡፡ የአዋጁ ዋና መልእክት ንስሓ ገብታችሁ፣ ከንስሓ አባታችሁ ጋር ጨርሳችሁ ቅረቡ የሚል ነው፡፡ በዚህ ድል ስትነሳው ደግሞ “አንተ ገና ወጣት ነህ ሽማግሌዎች እንኳን ሳይቆርቡ ያንተ ቁርባን ምንድን ነው” ይልሃል፡፡ አንተ ምክሩን አትቀበል “ሽማግሌዎች የራሳቸው ነፍስ ነው ያላችው እኔም እንደዚሁ የራሴ ነፍስ ነው ያለኝ  ስለዚህ እነርሱ ስላልቆረቡ እኔ መቁረብ የለብኝም? በወጣትነት ዘመንህ ፈጣሪህን አስብ ተባልኩ እንጅ ሽማግሌዎች የሚሠሩትን እያየህ እንደእነርሱ ሁን አልተባልኩም፡፡ በእርግጥ በጎ ሥራ ሲሠሩ ልመስላቸው ግድ ነው መጥፎ ሲሠሩ ግን ልመስላቸው አልሻም፡፡ እነርሱ የሚቆርቡበት የራሳቸው ጊዜ ሊኖራቸው ይችላል የእኔ ጊዜ ግን ዛሬ ብቻ ነው” ብለህ አሳፍረው፡፡ ይህን ሁሉ ብለህ ስታሸንፈው ደግሞ እንደለመደው ከንቱ ውዳሴን ይጨምርብሃል፡፡ ቆራቢ እንድትባል ብቻ መቁረብን ያለማምድሃል፡፡ ከዚያ በኋላ ልምድ ያደርግብህና ሳትዘጋጅ ንስሓ ሳትገባ በድፍረት መቅረብን ያለማምድሃል፡፡ ስለዚህ በጣም ጥንቃቄ ልታደርግ ያስፈልጋል፡፡ ሥጋና ደሙን ለመቀበል የግድ ንስሓ መግባት ከንስሓ አባት ጋር መወያየትን ይጠይቃል፡፡ የዘላለም ሕይወትን ለማግኘት ስትሻ የዘላለም ቅጣት እንዳይመጣብህ ተጠንቀቅ፡፡

Friday, November 27, 2015

ምኑን ልከራየው????


© በመልካሙ በየነ
ሕዳር 16/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ቤት የለኝ አልሠራሁ መሬቱ የመንግሥት፣
መኖር ደግሞ አለብኝ ተጠልየ በቤት፣
ታዲያ የት ልኑረው ወዴት ብየ ልግባ፣
የራሴ ማስገቢያ ስለሌለኝ ታዛ ሆዴ እጅጉን ባባ፣
ዓይኔ ራሰ በእንባ፡፡
እንባዬን ጠርጌ ቀና ስል በድንገት፣
 “ይከራያል” የሚል  አየሁኝ ከርቀት፣
ችግር ያበሰለኝ ማደሪያ አጥቼ፣
እየተንሰፈሰፍኩ ቤቱን ተጠግቼ፡፡
የሚከራየውን አሳዩኝ አልኳቸው፣
አሳዩኝ ዶርሚቱን ከነመመሪያቸው፣
መመሪያ ቁጥር አንድ…
አምሽቶ መግባት መስከር መወላገድ፣
ቆሻሻ መጣል እንጀራ መጋገር ማድቤትን ማቆሸሽ ሴት ልጅን ማሳደድ፣
አምጥቶ  ማሳደር ጓደኛና ዘመድ፣
ሳያንኳኩ መግባት ሳልፈቅድ ወጥቶ መሄድ፣
ከዶርም ያባርራል ሳትወድ በግድ፡፡
መመሪያ ቁጥር ሁለት…
ሽንት ቤት ውስጥ ገብቶ ደቂቃን ማባከን፣
ሳልፈቅድ መጠቀም መብራት እና ውኃን፣
ያስወጣል ከግቢ ካልጠበቅህ ይህንን፡፡
… እናም መመሪያውን ተጋበዝኩትና ፣
ዶርሚቱን አየኋት ፈቀዱልኝና፡፡
ዶርሚቱ እንዲህ ናት…
የግድግዳ ቀለም ምንም ያልነካካት፣
ክፍተቱ የበዛ መስኮትና በር የተገጠመላት፣
አንድ አልጋን መዘርጋት የማይቻልባት፣
ኮርኒስ የሚባለው ያልተሰበከባት፣
ምንም ምን የሌላት፣
ፈጣሪ የሰጠን  ጭቃ እንኳ በአግባቡ ያልተለጠፈባት፣
መመሪያ እና ደንብ ክልከላ እና ዛቻ የተንሰራፋባት፣
ለአቅመ ኪራይ የማትበቃ ባዶ ሆና አገኘኋት፡፡
እ ኔ-- ም… ውስጤ ተክኖ ልቤ አዝኖ ተክዞ፣
ዋጋዋ ስንት ነው? ብየ ጠየቅኋቸው ዓይኔ በእንባ ፈዞ፡፡
“ሶስት መቶ ነው ለአንድ ከሆነ፣
ስድስት መቶ ነው ለሁለት ከሆነ፣
ዘጠኝ መቶ ነው ለሦስት ከሆነ፣”
እያሉ ሲጠሩት የብሩን ጋጋታ፣
በጣም ተገርሜ “ኪራይ ነው ወይስ ሽያጭ” አልኳቸው በእርጋታ፡፡
ምን ይላል! ይሄ ሰው፣
በሦስት መቶ ነው ቤቴን የምሸጠው?
ይልቅስ ከያዝከው፣
“ይከራያል” የሚለውን ጽሑፍ አሁን ልገንጥለው፣
አሉኝ ቀና ብለው::
እኔም ተገርሜ እጅግ ተደምሜ፣
በቤት አልባነቴ እኔን ተቀይሜ፣
እከራይ ነበር ዶርምስ ቢኖርዎ፣
አሁን ያሳዩኝ ግን ዶርም አይደለም ከቶ ቅር ካላልዎ፡፡
እናም! ያኔ ዶርም ሰርተው “ይከራያል” ሲሉ፣
መጥቼ እይዛለሁ መመሪያን ሲያቀሉ፡፡
አሁን ግን! ዶርም የሎት ምኑን ልከራየው???
ያው ቤት አልባነቴን ይዤው እኖራለሁ፡፡

(ማስታወሻነቱ፡ በዶርም አጥረት ሳይሆን በዶርም ውጥረት፤ በዶርም ማጣት ሳይሆን በዶርም ቅጣት ላለሁት ለእኔ እና ለመሰሎቼ ይሁን)

Wednesday, November 18, 2015

አገሬ ኢትዮጵያ!!




© በመልካሙ በየነ
ሕዳር 8/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
አገርም ቢሏችሁ ከአገር በላይ ቅድስናን ከንጽሕና፣ ውበትን ከቁንጅና፣ ጀግንነትን ከፍልስፍና… ጋር አቆራኝታ እጆቿን ወደ ፈጣሪ ዘርጋታ የኖረች፣ እየኖረች ያለች ወደፊትም የምትኖር ፈጣሪ ውብ አድርጎ የሠራት አገር ናት ኢትዮጵያ፡፡ ይች አገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስማቸው ተመዝግቦ ከምናገኛቸው ቦታዎች መካከል አንዷ ናት፡፡ ገነትን ከሚያጠጧት አራት አፍላጋት መካከል አንዱ የኢትዮጵያው ግዮን ወይም አባይ እንደሆነ ዘፍጥረት ላይ እናነብባለን፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ለገነት ማጠጫ የሚሆን ትልቅ ወንዝ ለገነት የታጨ ቅዱስ ሕዝብ ያላት አገር ናት ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በተለያዩ መሪዎቿ የተለያዩ ስሞችን ተቀብላለች፡፡ አቢሲኒያ፣ ኢትዮጵያ እየተባለች ተጠርታለች፡፡ በአቢስ አቢሲኒያ በኢትዮጲስ ኢትዮጵያ ተብላ የተጠራችው አገራችን ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ካገኘች በኋላ የመሯት መሪዎቿ “አዲሲቷ፣ አሮጊቷ” የሚል ቅጥያ ከመቀጠል ውጭ ስመ ተፋልሶ አላደረጉባትም፡፡ ኢትዮጵያ ስትነሣ ዓለምን የሚያስደንቀው የአኩስም ሐውልት፣ የላሊበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት፣ የጎንደር ፋሲለደስ ቤተ መንግስት፣ በሐረር የጀጎል ግንብ፣ በጎጃም የጣና ሐይቅና በደሴቱ ያሉ ገዳማት፣ የሰው ልጅ መገኛ መሆኗን የሚመሰክረው የሉሲ ድንቅነሽ አጽም፣ የተለያዩ ቋንቋዎችና ባህሎች ተስማምተው የሚኖሩባት፣ ገነትን የሚያጠጣው የአባይ ወንዝ ወዘተ… ትዝ የሚላቸው ፈረንጆቹ ብቻ ናቸው፡፡ እኛ ግን “በቅርብ ያለ ጠበል …” እንዲሉ ከምንም አንቆጥራቸውም፡፡ እኛ የራሳችን ሃብትና ንብረት እንዴት ትዝ አላለንም? በእርግጥ በዚህ ዘመን በአሁኑ ሰዓት ስለብዙ ነገሮች እነዚህ ሁሉ ሃብቶቻችን ትዝ እንዳይሉን ከባድ ተጽእኖዎች አሉብን፡፡ ከእነዚህ ተጽእኖዎችም መካከል የመጀመሪያው የገዢው መንግሥት ተጽእኖ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከመሸለም ከማድነቅ ይልቅ መቅጣት የሚቀናው ማኅበረሰብ ማፍራታችን ነው፡፡
ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘመናት የተለያዩ አስተሳሰቦችንና አመለካከቶችን ያነገቡ አንዳንዶች ለራሳቸው ጥቅም ጥቂቶቹም ለአገራቸው ለወገናቸው ጥቅም ሲሉ የኖሩ መሪዎችን አይታለች ተቀብላም አስተናግዳለች፡፡ ማን ነው ለአገሩ የሞተው መሪ? ማን ነው በጠላት እጅ መሞትን የናቀው? ቴዎድሮስ አይደለም እንዴ? ነው፡፡
 “መቅደላ አፋፉ ላይ ጩኸት በረከተ
የሴቱን አናውቅም ወንድ አንድ ሰው ሞተ” የተበላው ለማን ነው? የወንዶች ወንድ፣ የጀግኖች  ጀግና፣ ህዝቡን አሳልፎ ያልሰጠ፣ በጠላት እጅ በነጭ እጅ ላለመሞት ወስኖ የአገሩን የወደፊት ራእይ ሰንቆ፣ አደራውን ለቀሪው ትውልድ አስረክቦ በያዘው ሽጉጥ ራሱን ያሳለፈ የመቅደላው ጀግና የኢትዮጵያው ጀግና ቴዎድሮስ ዘ ኢትዮጵያ ፡፡ በአገራችን ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያና የመጨረሻ የሆነውን መድፍ ነጮቹን ቀጥሮ ጋፋት ላይ ያሠራ ብቸኛው መሪ፡፡ ታዲያ ምን ዋጋ አለው አንዱ ጀግና የሞተለትን ጉዳይ አንዱ ፈሪ ቀበቶውን አላልቶ ሱሪውን አውልቆ ይቀበለዋል፡፡ በቴዎድሮስ የጀመረው ጀግንነትና የአገር ፍቅር በዚያው መጠን ቀጥሎ ዮሐንስ አራተኛ ለአገሩ ለወገኑ ሲል ባደረገው ጦርነት በሱዳኖች አንገቱን ተቆረጠ፡፡ የአገር ገዢዎች ለአገር መልማትም ሆነ መጥፋት ምክንያቶች ናቸው፡፡ እንግዲህ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለአገር ፍቅር ለወገን ብሎ ራስን አሳልፎ በመስጠት  በኩል ቆራጥ መሪዎች እነዚህ እንደነበሩ ማሳያዎቼ  ናቸው፡፡ እነዚህ መሪዎች ጀግናዎቼ ናቸው በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥም ስማቸውን መስማት የምሻው የእነዚህን ምርጦች ነው፡፡ ምክንያቱም የሞቱለት ዓላማ ትልቅ ስለሆነ እና ለወደፊት ማስቀመጥ የፈለጉት ራእይ ምን እንደሆነ ሳስብ የሚገርም ስለሆነ ነው፡፡ በጠላት እጅ አልሞትም መሞቴ ካለቀረ ግን በራሴ እጅ ሞትን እመርጣለሁ ብሎ በባእድ መገዛትን ተጸይፎ መሞትን ያህል ወኔ የያዘ መሪ አይገርም ማን ይግረም ታዲያ፡፡  ምናልባት ልብ ልንለው የሚያስፈልገው ነገር  ከእነዚህ በፊት እና በኋላ ሌሎች ምርጦች የሉም ለማለት አይደለም፡፡ እነዚህ ሁለቱ ለአገራቸው ለወገናቸው ራሳቸውን ለሞት አሳልፈው ስለሰጡ በልጠውብኝ እንጅ ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ስልጣኔ በር ከፋች የነበሩት ምኒልክም ለአገራችን ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ አልዘነጋሁትም፡፡ የመጀመሪያው ተሽከርካሪ መኪና የኢትዮጵያን ምድር የረገጠው፣ ስልክ ተዘርግቶ መደዋወል የተጀመረው፣ የፖስታ አገልግሎት የተጀመረው ዘመናዊ ስልጣኔ ኢትዮጵያን የነካካት መቼ  ነው? በዘመነ ምኒልክ አይደለም እንዴ? አረ ነው ምን መዋሸት ያስፈልገዋል፡፡ ከአውስትራሊያ ጋር በመገናኘት አሁን ለአገራችን ህዝብ በተለይ ለገጠራማው ክፍል ዋስትና እየሆነ ያለውን ባህር ዛፍ ወደ አገራችን ያመጡት ማን ሆኑና፡፡ በዘመናዊ መሳሪያ ከራስ ጸጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ  ድረስ ተከናንቦ ኢትዮጵያን ለመውረር የመጣውን የኢጣሊያ ጦር በጀግንነትና በወኔ አድዋ ላይ ድራሹን ያጠፉት የአበሻ መሪ ማን ሆኑና፡፡ ጠላትን በመጣበት እግሩ አሳፍረው የመለሱ ድንቅ ኢትዮያዊ መሪ ምኒልክ ሁለተኛ፡፡ የዛሬዪቱን አንገቷን የተቆረጠችውን ሳይሆን ያችን ባለወደቧን ኢትዮጵያ ቅርጽና ግዛቷን እንድትይዝና በዚያ ካርታ እንድትታወቅ ያደረጉ መሪ ናቸው፡፡ በታሪካችን ውስጥ የሚገርመው ነገር ያለፈውን መሪ በበጎ ማንሣት አልተለመደም እንጅ ስንት በጎ ነገር ነበረን መሰላችሁ፡፡ ሃይለ ሥላሴን በብዛት የምናነሣቸው በበጎው አይደለም፡፡ ምንም እንኳ ከላይ ያየኛቸውን መሪዎች ያህል ለአገራችን ስልጣኔ አስተዋጽኦ ባያበረክቱም በተለያዩ ተጽእኖዎች ተነሣስተው የቻሉትን ያህል ግን አድርገዋል፡፡ የአፍሪካ ኅብረትን ከመመሥረት ባለፈ በመዲናችን አዲስ አበባ ጽ/ቤት እንዲኖረው ያደረጉ እሳቸው ናቸው፡፡ ዘመናዊ ትምህርት የሰይጣን ትምህርት ነው በሚል አስተሳሰብ ታንቆ የነበረውን የአገራችን ሕዝብ አሳምነው ዘመናዊ ትምህርትን ወደ ኢትዮጵያ ያመጡ ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን ከፍተው ዘመናዊ ትምህርትን ያስጀመሩ እሳቸው ናቸው፡፡ ምንም ያህል ብንተቸውም በበጎ ጎኑ ባናነሣውም  የመጀመሪያውን የተጻፈ ሕገ መንግሥት ለአገራችን ያስተዋወቁ ብቸኛ መሪ ናቸው፡፡ አገራችን አሁን ከአደጉት አገራት ተርታ ያለችውን ጀርመን ለመጀመሪያና ለመጨረሻ ጊዜ ስንዴ የለገሰች በጃን ሆይ ዘመን ነው፡፡ ለአገራችን የመጀመሪያ የሆነውን የጽሕፈት መኪና ወደ አገራችን ያመጡ ጃንሆይ ናቸው፡፡ ይህ ማለት ግን አገራዊ ስህተት አልሰሩም ማለት አይደለም፡፡ ማንም መሪ የሚሠራውን የአገር ስህተት ሰርተዋል፡፡ በተለይ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለሁለተኛ ጊዜ በወረረ ጊዜ አገር ለቅቀው መሄዳቸውና ያም አልበቃቸው ብሎ ጦርነቱ ካለቀ በኋላ አገር ውስጥ ተመልሰው አገርን በአርበኝነት ሲጠብቅ የነበረውን ጀግና በላይ ዘለቀን መስቀላቸው ዓበይት ስህተቶች ናቸው፡፡ ከጃን ሆይ ቀጥሎ የመጣው ወታደራዊ መንግሥትም አዲስ አስተሳሰብን “ሶሻሊዝም” የሚባለውን ለአገራችን አስተዋውቋል፡፡ እድገት የሚመጣው በኅብረት ነው የሚል አመለካከት ነበረው፡፡ መፈክሩም “ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚል ነበር በዚህ መፈክር ውስጥ የሚመጣብን ኢትዮጵያ በዓለም ስልጣኔ ላይ ቁንጮ ስትሆን ማየትን ነው፡፡ ዛሬ በቆረጠው ምትክ እንኳ የማይተክለው ደን ኢንተርፕራይዝ ብለን ያቋቋምነው ተቋም ሲቆርጠው የሚውለው ደን በማን ዘመን የተተከለ ነው እንላለን? በማይናወጥ መሠረት ላይ የታነጹት የቀበሌ ቢሮዎች እንዲሁም የቀበሌ ቤቶች በተጨማሪም ትምህርት ቤቶች መቼ የታነጹ ናቸው? አሁን ከገነባናቸው ይልቅ በደርግ ዘመን የተሠሩት ናቸው ጥንካሬ ያላቸው፡፡ እንደ እድል ሆኖብን አንድ መንግሥት ሄዶ ሌላው ሲመጣ ያለፈው መንግሥት የሠራቸውን ነገሮች ሁሉ ማፍረስ እንወዳለን፡፡ መታሰቢያውን እንደመስሰዋለን፣ ይጠቀምባቸው የነበሩ ቢሮዎችን፣ መሥሪያ ቤቶችን እናፈርሳቸዋለን፣ ታሪክን ዜሮ ብለን እንደገና እንጀምራለን፡፡ አሁን ላይ በተለያዩ ኃላፊነት ቦታዎች የተቀመጡ ሰዎች በማን ትምህርት ፖሊሲ እንደተማሩ ራሳቸው እኮ ያውቁታል፡፡ ነገር ግን ያለፈ ታሪክን በበጎ ስለማንመለከት ለዚህ ነው ደርግን በበጎው የማናነሣው፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ አሁን እየመራን ወዳለው መንግሥት ደርሰናል፡፡ የአሁኑ መንግሥት ከክፋቱ ይልቅ በጎነቱ ጎልቶ እንዲታይ የአገራችን መገናኛ ብዙኃን ትልቅ ድርሻ ይይዛሉ፡፡ ክረምት ላይ የተቀረጸውን አረንጓዴ ሰብል በበጋው እያሳዩ በመስኖ የተመረተ ምርት ነው ይሉናል፡፡ ስልጣኔውም እየመጠቀ ስለሆነ ይህንን ነገር ለአገራችን ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለዓለም እንዲደርስ ስለተደረገ ውጮቹ ኢትዮጵያ አድጋለች ተመንድጋለች እያሉ ባላዩት ባልሰሙት ነገር ላይ ይመሰክራሉ፡፡ በጣም የሚገርመኝ የዚህ መንግሥት አገራዊ ስህተት ሁሉን አቀፍ የሆኑትን ብሄራዊ በዓላት እና የሃይማኖት በዓላትን ከማክበር ይልቅ ጥቃቅን የሚባሉ ነገሮችን ለወር ለሁለት ወር ከዛም ለረዘመ ጊዜ ሲያከብር ማየታችን ነው፡፡ በእውነት ኅሊና ላለው ሰው የአድዋን ጦርነት ያሸነፍንበትን የካቲት 23 ከማክበርና ብአዴን የተመሰረተበትን ህዳር 11፣ ኢህአዴግ ደርግን ያሸነፈበትን ግንቦት 20 ከምናከብር ትልቅ ስሜት ሊሰጠን የሚችለው የትኛው ነው? በየካቲት 23 ስም የተሰየመ ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል፣ መንገድ፣ አደባባይ የት አለ? ግንቦት 20 የሚለውን ስያሜ ግን ለብዙ ነገሮች ሰጥተነዋል፡፡ ግንቦት 20 የሚባል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በምሥራቅ ጎጃም ዞን አዋበል ወረዳ እንዳለ አውቃለሁ፡፡ የካቲት 23 የሚባል ትምህርት ቤት ግን አላውቅም፡፡ የውጭን ጠላት አሸንፎ ዓለም አቀፋዊ እውቅናና ዝና ያጎናጸፈን የትኛው ነው? ሌላው የገዣችን ትልቅ ስህተት ካለፉት በጎ ነገሮችን መማር አለመቻሉ ነው፡፡ በእርግጥ ያን ጊዜ ድሮ የነበሩት መሪዎቻችን እንዲህ በቀላሉ ዓለምን መድረስ የሚችሉበት ሥልጣኔ የነበራቸው ስላልሆኑ እንጅ በጎ ስራ ስላልሰሩ አይደለም እውቅና ያላገኙት፡፡ አንድ ዛፍ ተክሎ ሺህ ጊዜ በሚዲያ መቅረብና ማቅረብ፣ አንድ ሽንኩርት አብቅሎ ሺህ ጊዜ ሚዲያ ላይ መውጣት እና ማውጣት የተጀመረው አሁን ቅርብ ጊዜ ነው፡፡ በእውነት ግን! ባህር ዛፍ ተከለ ተብሎ በሚዲያ ከመታየት ይልቅ ባሕር ዛፍን ወደ ኢትዮጵያ ያመጣው ሰው ማን እንደሆነ ፎቶውን እንኳ ብናሳይ አይበልጥም ነበር? የዘመናዊ ትምህርትን ጥራትና ሽፋን፣ የትምህርት ቤቶቻችንን ቁጥር እያነጻጸርን ሺህ ጊዜ እስኪሰለቸን ከሚነግሩን ይልቅ ዘመናዊ ትምህርት ኢትዮጵያ ውስጥ ማን እንዳስጀመረው? ሲጀመር የነበረው የህዝቡ አቀባብል ምን ይመስል እንደነበር ምነው በነገሩን፡፡ ባለፉት ዘመናት ለአገራቸው ለወገናቸው ሲሉ ውድ ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡ ጀግኖቻችን አድራሻቸው የት አለ? መታሰቢያ ሀውልታቸው የት ቆመ? በቅርቡ ከ1983 ዓ.ም ወዲህ ማለቴ ነው በየክልሉ የሰማዕታት ሃውልት እየተባለ ሲቆምላቸው (አይቁምላቸው ማለቴ አይደለም) ለቴዎድሮስ እና ለገብርዬ፣ለዮሐንስና ለምኒሊክና፣ ለበላይ ዘለቀ የትኛው ክልል ላይ ነው መታሰቢያ ሐውልት የቆመላቸው ምናልባት አሁን ካልፈረሰ በወረዳ ደረጃ ተሰርቶላቸው ሊሆን ይችላል፡፡ የትኛው ትምህርት ቤት፣ የትኛው ሆስፒታል፣ የትኛው አደባባይ ነው በስማቸው የተጠራ? የሚገርመው ነገር አሁን በቅርቡ ላለፉት ባለራዕይ መሪ ስንት ትምህርት ቤት፣ ስንት መንገድ፣ ስንት አደባባይ፣ ስንት ስታዲየም፣ ስንት ሆስፒታል፣ ስንት ፓርክ ነው በስማቸው የተሰየመ? ብቻ ታሪክ ይቀሰን! የእነ ቴዎድሮስ የእነ ዮሐንስ የእነ በላይ ዘለቀ ደም ይክሰሰን፡፡ ድሮ እነርሱ ደርግን የጣሉት በትጥቅ ትግል ነበር ምክንያቱም አስተሳሰቡና ርእዮቱ ለኢትዮጵያ ተገቢ ነው ብለው ስላላመኑ፡፡ ዛሬ ግን የትጥቅ ትግል የሚጀምርን ሰው አሸባሪና ኪራይ ሰብሳቢ ከማለት ውጭ ለአገሩ ለወገኑ ለሕዝቡ አስቦ ነው ብለን መቼ ተረዳን፡፡ አስተሳሰባችን አመለካከታችን ከጫካ አስተሳሰብና አመለካከት መቼ ተለየ? ለዛም እኮ ነው ከእኛ በላይ ፖሊሲ፣ ከኛ በላይ መሪ፣ ከኛ በላይ ካድሬ፣ ከኛ በላይ ሕገ መንግሥት የትም የለም ብለን የምንከራከረው፡፡ የተማረ ሰው መለያው “ይህ ስህተት ነው” ሲሉት ስህተቱን መመልከት መቻሉ ነበር የዚህኛው የኛ ገዢ ግን መማሩ ያልጠቀመው ይመስላል፡፡ አልተማረም እንዳንል ውጭ አገር ድረስ ሄደው ዲግሪ፣ ማስተርስ፣ ዶክትሬት ጭነው ተመልሰዋል ተማሩ እንዳንላቸው ደግሞ ዋይታችንን ችግራችንን ብሶታችንን አልተረዱልንም፣ አመለካከትና አስተሳሰባቸውን አልቀየሩልንም፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያን በነበረችበት ስልጣኔ ላይ ሳይሆን አፍርሰው እንደገና ወደ ስልጣኔ ጎዳና ስላመጧት በርካታ ጊዜያትን ሊወስድ እንደሚችል እናስባለን፡፡ ነገር ግን ሁል ጊዜ ጅማሬ የለም መጨረሻ ሊኖረው ያስፈልጋል፡፡ ከ83 ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ጅማሬ ላይ ነን ሊባል አይገባውም ነበር፡፡ የጅማሬ ራዕያችን መቼ ነው አውን ሆኖ የምንመለከተው?
ሌላው የአገራችንን ታሪክ ከማድነቅ ይልቅ እንድንዘነጋውና እንድረሳው ትዝ እንዳይለን ያደረገን ጉዳይ ከመሸለም ይልቅ ለቅጣት የሚፈጥን ማኅበረሰብ ማፍራታችን ነው፡፡ በየቤታችን አስተዳደጋችን እንዲሁ ነው፡፡ ታሪክን እያስተማሩ ለአገር ፍቅር እንዲኖረን ከማድረግ ይልቅ “አንተ ወሬኛ” እየተባልን ታሪክን ለመማር እና ለመስማት ተሸማቀቅን አድገናል፡፡ ተረት ንገሩን ስንላቸውም የቀበሮና የበግ ተረት ነው የሚተርቱልን፡፡ እኛም እሱኑ ለመድነውና ቀበሮና በጎች ሆነን ቀረና፡፡ በጀመርነው የጥንቱ ስልጣኔ እና ትልቅነት ላይ አንዳች ነገር መጨመር ያልተቻለን ከማበረታታት ይልቅ ማሸማቀቅና ማስፈራራትን ባህላችን አድርገን በመኖራችን ነው፡፡ ለብዙ ዘመን በበጎ ስራህ ስትነሣ፣ ስትመሰገን፣ ስትወደስ፣ እንደ እርሱ አድርጋችሁ ሥሩ እየተባለ አርአያነትህ ሲጎላ፣ ህዝቡም አንተን ሲከተልህ ትኖራለህ መቼም ከሰው ልጅ ስህተት አይጠፋምና አንድ ቀን ታጠፋለህ ለብዙ ዘመን ይዘኸው የነበረው ስምና ዝናህ ከመ ቅጽበት ይለወጥና ትታሰራለህ ወይም ትቀጣለህ፡፡ አውሮፕላን ብትሠራ፣ መርከብ ብትገጣጥም፣ አዲስ ጥበብ ብታመጣ ማንም አያደንቅህም ሊቀጣህና ሊወግርህ የተዘጋጀው ግን አያሌ ነው፡፡ ሃይለ ሥላሴ በላይ ዘለቀን ለምን ሰቀሉት? ርስታቸውን ቀማቸው ወይስ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አደረገባቸው? አረ ምንም፡፡ ጀግንነቱ በህዝቡ ዘንድ ስለገነነ እና በርካቶች ስለተከተሉት ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ምቀኝነታችን ያስቸግረናል፡፡ ምቀኛ መሪዎች ደግሞ ተፈራርቀውብናል፡፡ እነሱ የሚሰሩት ብቻ ትክክል ይመስላቸዋል፣ ያለፉት መሪዎች የሰሩት ሁሉ ደግሞ ስህተት ይመስላቸዋል ለዛ ነው ታሪካችን እንዲህ ዘቅጦ የቀረው፡፡ ስንት ሽህ ጊዜ በጎ ነገር ብትሠራ መልካም ነገር ቢኖርህ ለሎች ሁሉ አርአያ ብትሆንም ሽልማት አታገኝበትም እውቅናን አትጎናጸፍበትም፡፡ በአንጻሩ ግን ትንሽ ስህተት ብትሰራ ከሰምንት ሰዓት የሥራ ሰዓት ውስጥ 10 ደቂቃ ብትሸርፍ ሽራፊ ደመወዝ ይሰጥሃል፡፡ የጽሑፍና የቃል ማስጠንቀቂያ ማስፈራሪያና ዛቻ እንዲሁም አዲስ ስም ከኪራይ ሰብሳቢነት እስከ አሸባሪነት እና ትምክህተኛነት ድረስ ያሉት ስድቦች ይዘንቡብሃል፡፡ መሪዎችህም የሚደሰቱት በመሸለም ሳይሆን በመቅጣት ነው ምክንያቱም አስተዳደጋቸውና አስተሳሰባቸው ነዋ፡፡ ማበረታታት የሚባለው ነገር ተዘንግቷል፡፡ አዲስ ፈጠራ ፈጥረህ ስልክ በነጻ መደወል ብትጀምር ፈጠራህን የሚያበረታታ ፍርድ ቤት የለም 25 ዓመት ጽኑ እስራት የሚል እንጅ፡፡ ታዲያ በዚህ ሂደት ታሪክህን ማጥናት እንዴት ልትደሰት ትችላለህ?
አገራችንን አምላክ ይጠብቅልን፡፡


Thursday, November 12, 2015

እውነተኛ ሰላም

© በመልካሙ በየነ
ሕዳር 2/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

…ይህ ሰላም ዘላለማዊ ዕረፍትን የሚያጎናጽፍ ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ልዩ ሃብት ነው፡፡ በቅዳሴው ጸሎት ካህኑ “ሰላም ለሁላችሁ” ብሎ የሚጸልይልን ይህን ሰላም ነው፡፡ ለዚህም ነው “ከመንፈስህ ጋራ” ብለን ያንን እውነተኛ ሰላም እናገኝ ዘንድ የምንማጸነው፡፡ ነቢዩ ዳዊት በመዝ 28÷ 11 ላይ “እግዚአብሔር ሕዝቡን በሰላም ይባርካል” የሚለውን መዝሙር ይዘን እኛም በቅዳሴ ጸሎታችን ውስጥ “የሰላም ንጉሥ ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ሰላምን ስጠን ሰላምንም አጽናልን” እያልን እውነተኛ ሰላማችን እንድትጸናልን ሰላማዊ የሆነውን የሰላም ንጉሥ በየዕለቱ እንለምነዋለን፡፡ ይህ ሰላም ለአገር፣ ለወገን፣ ለፍጡራን ሁሉ የሚያስፈልግ መሆኑን በመረዳት በቅዳሴ ጸሎታችን ላይ በተደጋጋሚ እናነሣዋለን፡፡ ይህ በተደጋጋሚ የምንማጸነው ሰላም ከዲያብሎስ፣ ከፍርሃት፣ ከጭንቀት፣ ከመከራና ከሃዘን ጠብቆ ሙሉ ደስታን የሚያጎናጽፍ ልዩ መሣሪያ ነው፡፡ ብዙዎች ልባቸው በጭንቀትና በፍርሃት በሚሸበርበት ጊዜ የአንተ ውስጣዊ ሰላምህ አይናጋም፡፡ በጦርነት መካከል ተሰልፈህ የመሸነፍ ስሜት ጠፍቶ የማሸነፍ ወኔ ትጎናጸፋለህ፡፡ በዚህም የተነሣ ውስጣዊ መረበሽ፣ መጨነቅ ብን ብሎ ይጠፋልህና እውነተኛ ሰላም በፊትህ ትፈስሳለች፡፡ በከባድ አደጋዎች መካከል የብዙዎች  ልብ በፍርሃትና በጭንቀት ቀልጦ ዋይታ ሲበዛባቸው አንተ ግን ምንም እንደማያውቅ ሕጻን ንጹሕ ሰላምን ተሸፋፍነህ በደስታ ትቦርቃለህ፡፡ በከንቱ በመጨነቅ እና በማልቀስ አንዳች ነገር መፍጠር እንደማትችል እውነተኛ ሰላምን የሠጠህ አምላክ ያስተማረህ ወንጌል በሕይወትህ ትርጉም እያገኘ ፍሬ ሲያፈራ አንተም ፍሬውን ስትመገብ ይበልጥ ደስታህ ይጨምራል፡፡ ብዙዎች እንቅልፍ በማጣት ሲባዝኑ አንተ በንጹሕ እረፍት መካከል ትሰማራለህ፡፡ “እግዚአብሔር እረኛየ ነው የሚያሳጣኝም የለም በለመለመ መስክ ያሰማራኛል በእረፍት ውኃ ዘንድም ይመራኛል” /መዝ22÷1/ የሚለውን የቅዱስ ዳዊት ዝማሬ በእውነተኛ ሰላም መካከል ትዘምራለህ፡፡ የአገሬን ጥፋት አታሳየኝ እያለ ይለምን የነበረው በእግዚአብሔር ጥበብ ለድውያን የሚሆን ዐጽቀ በለስን ቆርጦ እንዲያመጣ የተላከውና ዐጽቀ በለሷን ይዞ መጥቶ ከዛፍ ሥር እንዳረፈ በዚያው ለ66 ዓመት ያህል በእንቅልፍ አሳልፎ የአገሩን ጥፋት ከማየት የሰወረውን አቤሜሌክ ወደ አንተ ያመጣዋል፡፡ እርሱም እውነተኛ ሰላምን በሚገባ በተግባር ያረጋግጥልሃል ይተረጉምልሃልም፡፡ ያ እውነተኛ ሰላም ታላቅ የሆነ መንፈሳዊ ኃይል አለው፡፡ “ስለዚህ ኤልሳቤጥ የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ጽንሱ በማኅጸን ዘለለ” /ሉቃ 1÷41/ እውነተኛ ሰላም እንዲህ በማኅጸን ያለውን ጽንስ ሳይቀር ደስ የሚያሰኝና የሚያዘልል ነው፡፡  ያ ሰላም በየዋህነትና በንጽሕና ከእግዚአብሔር ጋር በመሆን የሚገኝ ነው፡፡ ያን ሰላም ዮሐንስ እንዲህ ገልጾታል “ ሰላምን እተውላችኋለሁ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም”/ዮሐ14÷27/ እውነተኛ ሰላም ከእግዚአብሔር የሚገኝ  ዓለምም ከምትሰጠው ሰላም እጅጉን የተለየ ለመሆኑ ይህ ቃል ምስክር ነው፡፡ ዓለም የምትሰጠው ሰላም የሐሰት ነው፡፡ የጠፋው ልጅ ታሪክ ይህንን በሚገባ ያስረዳናል፡፡ በአባቱ ቤት የነበረው እውነተኛ ሰላም ሆኖ ሳለ ወደ ዓለም ገባ፤ ዓለምም ገንዘቡን በሚገባ ከጨረሰች በኋላ ሰላም ነፈገችው፡፡ በዚህም የተነሣ እንደገና ተመልሶ ወደ ቀድሞው ሰላም ወደ አባቱ ቤት ገባ፡፡/ሉቃ15÷11-24/ ይህ ልጅ እውነተኛ ሰላም የሚገኘው በአባቱ ቤት ብቻ መሆኑን ተረዳ፡፡ ከእግዚአብሔር ስትርቅ የምታጣው ይህንን ዓይነት ሰላም ነው፡፡ እግዚአብሔር ይህን ሰላም እንድታጣ ከተወህ ወጥተህ መግባት አትችልም፤ ለሴኮንዶች ያህል እንኳ እረፍት አታገኝም፡፡ ድምጽ በሰማህ ኳ ባለ ቁጥር ትሸበራለህ፡፡ ያ እውነተኛ ሰላም በገበያ መካከል ገብተህ ድምጽ ሳትሰማ የምትወጣበት ነበርና አሁን ግን እርሱን በማጣትህ ትጨነቃለህ፣ ፍርሃት ይበዛብሃል፣ ተቅበዝባዥ ትሆናለህ፡፡ ስለዚህ ወደ እውነተኛው ሰላም ወደ አባትህ ቤት ልትመለስ ያስፈልጋል፡፡ በኃጢአት የቆሸሸ ማንነትህን በንስሓ አጥበህ ወደ አባትህ ቤት ልትመለስ የምትችልበት ዕለት ዛሬ ብቻ ስለሆነ እውነተኛ ሰላምን ወደሚሰጠው አባትህ ቤት ተመለስ፡፡ እውነተኛ ሰላም ለእግዚአብሔር ክብር እንድትመሰክር ሊወግሩህ ድንጋይን በያዙ ሰዎች መካከል ወይም ሊፈጩህ በተዘጋጁ ወፍጮዎች መካከል ቆመህ እውነቱን እንድትገልጥ ትረዳሃለች፡፡ የፍርሃት ካባን ታወልቅልህና የቅዱስ ጊዮርጊስንና የቅዱስ እስጢፋኖስን ሰማእትነት እስክትቀበል ድረስ ታጸናሃለች፡፡ ለሚወግሩህም ሰዎች “ይህን ኃጢአት አትቁጠርባቸው” የሚል ፍጹም ፍቅር የተሞላበት ልመና እንድታቀርብ ውስጥህን በንጹሕ ፍቅር ታትምሃለች፡፡ /የሐዋ 7÷60/ ስለዚህ ያንን እውነተኛ ሰላም ገንዘብህ ልታደርገው ይገባል፡፡ ከኃጢአትህ ተመልሰህ በንጽሕናና በቅድስና በየዋህነትም ሆነህ ብትገኝ እውነተኛ ሰላም ወደ አንተ ትመጣለች፡፡ እንደ እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ትእዛዙን ጠብቀህ ብትጓዝ እውነተኛ ሰላም ከአንተ ጋር ትጓዛለች፡፡ ስለዚህ ከእግዚአብሔር ጋር በመታረቅ እንደእርሱ መልካም ፈቃድ በመጓዝ ከቤቱ ሳትርቅ በእውነተኛ ሰላም ልትኖር ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ይህን የማታደርግ ከሆነ እውነተኛ ሰላም እጅጉን ትርቅሃለች፡፡

Wednesday, November 11, 2015

“አይምሰላችሁ!!!”

© በመልካሙ በየነ
ሕዳር 2/2008 ዓ.ም
ደብረማረቆስ፣ ኢትዮጵያ
ወገኖቻችን መጠንቀቅ እንዲገባቸው ልንጠነቀቅና ልናስተውል የሚገባንን ነገር ለመንገር ብዕሬን አነሣሁ፡፡ የሚቀበል ይቀበላል የማይቀበል ደግሞ አይቀበልም አለመቀበሉንም ሆነ መቀበሉን ግን በነጻነት አስተያየት መስጫው ላይ መተው ይቻላል፡፡ ይህን ካልኩ በኋላ ወደ መልእክቴ እገባለሁ፡፡
ዘመኑ ቀርቧልና ንስሐ ግቡ እያለች ልጆቿን በምግባርና በትሩፋት የምትጠብቅ እናት ቅድስት ቤተክርስቲያን በአሁኑ ሰአት ባስተማረቻቸው ልጆቿ እና ምንም በማያውቋት ጥላቻ ከባድ ፈተና ላይ ናት፡፡ ነገር ግን እስካሁን ካሳለፈቻቸው በርካታ ፈተናዎች የበለጠ ስላልሆነ በጥበብና በማስተዋል እንደምታልፍ ጥርጥር የለኝም፡፡ ነፋስ በነፈሰ ቁጥር ባለማስተዋል የምንነፍስ፣ በበረሩበት የምንበር፣ በሄዱበት የምንሄድ፣ በገቡበት የምንገባ፣ በወጡበት የምንወጣ እግዚአብሔርን ከመደገፍ ይልቅ የሰው ምርኩዝ የምንመረኮዝ በርካታዎች ነን፡፡ ከንቱ ሰማዕትነት ለመክፈልም የምንጣደፍ የሆነ ያልሆነውን የምንዘባርቅ መረጃዎችን ከማገላበጥ መጻሕፍትን ከማንበብ ይልቅ የሰዎችን አባባልና ወሬ የምናመላልስ “አባ እገሌ እንዲህ ብለው” ፣ “እማ እገሊት እንዲህ ብለው”፣ “እዚህ ገዳም እንዲህ ተብዬ”፣ “አባ እገሌ ራዕይ አይተውልኝ” ወዘተ አያልን ባለማስተዋል የተበላን በርካታዎች እንደሆንን ልንዘነጋው አይገባም፡፡ “የአባ እገሌ” ሃሳብ ከመጽሐፉ ጋር አልገጥም ይላል “የእማ እገሊት”ም ራዕይ እንዲሁ መጽሐፍ ቅዱሱን ይጋጨዋል ነገር ግን የምንወዳቸው የምናከብራቸው “አባ አባ፣ እማ እማ” የምንላቸው ዝቅ ብለን ጉልበታቸውን የምንስማቸው ናቸውና የተናገሩት እነርሱን ለሚቃወም ሁሉ ዘብ እንቆምላቸዋለን፡፡ አንድ ሰው የሆነ ውለታ ሊውልልህ ይችላል ያ ውለታው ግን እምነትህን እንድትለውጥ የሚያደርስ ተጽእኖ ሊኖረው አይገባም፡፡ ውለታ የዋለልህ በመሆኑም ብቻ “በዚህ ምድር  እንደእርሱ ያለ ሰው ፈጽሞ አይገኝም”፣ “አረ በፍጹም እርሱ እንዲህ አይነት ነገር አያደርግም” ወዘተ እያልክ ልትሞግትለት ጥፋቱን እራሱ አምኖ እንኳ “በፍጹም ይህን ያደርጋል ብዬ አልገምትም ዝም ብሎ አምኖ ይሆናል እንጅ” እያልክ ልትከራከር ሁሉ ትችላለህ፡፡ ግን አይደለም…
አይምሰላችሁ! አትሞኙ! የጠመጠመ ሁሉ ካህን አይደለም፤ ድምጽ ያለው ሁሉ ዘማሪ አይደለም፤ ጥቅስ የጠቀሰ ሁሉ ሰባኪ አይደለም፣ ደብተር የያዘ ሁሉ ተማሪ አይደለም፣ ቾክ የያዘ ሁሉ መምህር አይደለም፣ ጋወን የለበሰ ሁሉ ሃኪም አይደለም፣ በተሸከርካሪ ወንበር የተቀመጠ ሁሉ ኃላፊ አይደለም፡፡ በቃ! ይህንን ደፍረን እንናገረዋለን! እየሆነ ያለው ነገር እሱ ስለሆነ፡፡ ተሐድሶ መናፍቃን አይደለም ይህንን ማድረግ ቀርቶ ሌላም ሌላም ለማድረግ እቅዱ ስላላቸው ማለት ነው፡፡ ነገር ግን በግልሰቦች ደረጃ ወርደን ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዞ ሳይለያቸው ድሮ እንመጻደቅባቸው እንዳልነበር ሁሉ አሁን አብዛኛው ሰው ንቆ ሲተዋቸው “ፓስተር እገሌ” ለማለት መቅደማችን በራሳችን የመተማመኑ ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ያስገባዋል፡፡ በመኪና የሄደ ሁሉ ሹፌር ሊሆን አይችልም፤ በአውሮፕላን የበረረ ሁሉ ፓይለት ሊሆን አይችልም፣ ትምህርት ቤት የገባ ሁሉ ተማሪ ሊሆን አይችልም፣ ዩኒቨርሲቲ የተማረ ሁሉ ሊመረቅ አይችልም፡፡ ስለዚህ በቤተክርስቲያን ያደገ ሁሉም እንዲሁ የቤተ ክርስቲያን ልጅ ሊሆን አይችልም፡፡ እዚህ ላይ ማስተዋል ይገባናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለብዙ ጊዜ እንዲቆይ በዚያ እንዲያድግ ምክንያት የሆነው ምንድን ነው? እናትነቷን ፈልጎ ነው ወይስ ሌላ ጥቅም ፈልጎ? የሚለው መመለስ አለበት፡፡ በርካታ አርቲስቶችን መመልከት ትችላላችሁ፡፡ ኮፒ ራይትን ማስቆም ባለመቻሉ ዛሬ ያወጡት ዘፈን ነገ በዓለም ሁሉ ይደመጣል አንድ ካሴት እንደሸጡ ሁሉም ሰምቶ ይሰለቸዋል ይህ በመሆኑ ምንም ህይወታቸውን የሚለውጥ ገንዘብ ማግኘት አልተቻላቸውም፡፡ በዚህ የተነሣ አብዛኞቹ ወደ ሃይማኖቱ ገብተው እምነታቸውን እንደሽፋን ተጠቅመው “ዘፋኝነተን አቁሜ ዘማሪ ሆኛለሁ” እያሉ “አርቲስት ዘማሪ እገሌ” እየተባለ መዝሙር አይሉት ዘፈን ቅጡን ያጣ አድርገው እያሳተሙ ሲቸበችቡት ይውላሉ፡፡ ታዲያ እነዚህ ሰዎች ነገ ያ የኮፒ ራይት መብት ቢጠበቅላቸው ወደ ዘፈናቸው ላለመመለሳቸው ምን ዋስትና አለ? ምንም፡፡
እግዚአብሔር ያደረገልንን ውለታ ለግለሰቦች አሳልፈን የምንሰጥ ግለሰቦች አሳልፈን የምንሸጥ የአምላካችንን ስም ከማመስገን ይልቅ የግለሰቦችን ስም እየጠራን ያኑርልን የምንል ከንቱዎች፡፡ ምንም ያህል ነገር ከሰው ቢደረግልን ያን እንዲያደርግልን የረዳንን አምላክ ወዴት እንዘነገዋለን? አምላካችን ሲሰደብ ኢየሱስ አማላጅ ሲባል ቅዱሳኑ ሲሰደቡ አያማልዱም ሲባሉ ስናጨበጭብ የነበርን ሰዎች ዛሬ አንድ ግለሰብ እንዲህ ሆነ እንዲህ ተደረገ ሲባል አካኪ ዘራፍ እንላለን፡፡ ለመሆኑ መቅደም የነበረበት ለማን ነው? ለአምላካችን ወይስ ለግለሰቦች? እኔ በጣም ይገርመኛል ምን ዓይነት አዚም እንደተጫነን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ጴጥሮስ የውስጣቸው ቅድስና ለልብሳቸው ብሎም ለጥላቸው ሲሆን በጥላቸው ድውይ ሲፈውሱ አላነበብንም እንዴ?ሺህ ጊዜ  አንብበነዋል፡፡ ታዲያ በሮም አደባባይ ቁልቁል ሲሰቀሉ ምን ተነፈስን? ምንም፡፡ ምክንያቱም የአምላክ ፈቃድ ነዋ!!! ታዲያ ዛሬስ??????????

Wednesday, October 21, 2015

የእግር ስንፍና

ሰነፍ እግር የሚገሰግሰው ለኃጢአት ሥራ ነው፡፡ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ የሚለውን የዳዊት መዝሙር አይወድም፡፡/መዝ121÷1/ ሰነፍ እግር በክፉዎችና በኃጢአተኞች ምክር ይጓዛል፤ የበደልንም ጫማ ይጫማል፡፡ የሚገሰግሰውም ወደ ሰዶምና ገሞራ ከተማ ነው፡፡ ለክርክር እና ለሙግት ይቸኩላል፡፡ እግዚአብሔር ከሚጠላቸው ስድስት ነገሮች መካካል አንዱ ወደ ክፉ የሚሮጥን እግር ነው፡፡/ምሳ6÷18/ ሰነፍ እግር የሚረግጠውን አያስተውልም፤ የት ለመድረስ እንደሚፈጥንም አያውቅም፡፡ሰነፍ እግር ቀራንዮ ድረስ የሚሄደው በክርስቶስ ምራቁን ሊተፋ አልያም ሊሳለቅ ነው፤ በመስቀሉ አጠገብም የሚቆመው በልብሱ ዕጣ ለመጣጣል ነው፡፡ ሰነፍ እግር እንደ ቃየን እግር የሚቅበዘበዝ ይሆናል፡፡ በባዶ ሜዳ በድንጋጤ የሚሮጥ መድረሻውን የማያውቅ ተንከራታች ይሆናል፡፡ ሰነፍ እግር ለጸሎት መቆምን አብዝቶ ይጠላል፡፡ ሰነፍ እግር ከምጽዋት ይልቅ ስርቆት፣ ከስግደት ይልቅ ክፋት፣ ከጸሎት ይልቅ ትዕቢት፣ ለነፍሴ ከማለት ይልቅ ለኪሴ፣ ንስሓ ከመግባት ይልቅ ኃጢአት መሥራት፣ ከልጅነት ይልቅ ባርነት፣ ከሕይወት ይልቅ ሞት ይመርጣል፡፡ የሚጓዘውም በኃጢአተኞች መንገድ ነው፡፡ የሚሮጠውም ከነዓን ለመግባት ሳይሆን በእስራኤላውያን ላይ አደጋ ለመጣል ነው፡፡ የእስራኤላውያን እግር ባሕረ ኤርትራን በደረቅ ሲሻገረው እርሱ ግን በኤርትራ ባሕር ውስጥ ይሰጥማል፡፡ ሰነፍ እግር ናቡከደነጾር ላቆመው ምስል ይንበረከካል፤ ጥበበኛ እግር ግን ሠለስቱ ደቂቅን ይከተላል፡፡ ሰነፍ እግር በጦርነት መካከል ይቆማል፤ ብልህ እግር ግን ሰላምን ይፈልጋል፡፡ ሰነፍ እግር ድንግል ማርያምን የሚከተላት በግብጽ በረሓ ለማሳደድ ነው፡፡ ሰነፍ እግር እስጢፋኖስ ሲወገር ድንጋይ ያመላልሳል፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲፈጭ ደብረ ይድራስ ሊበትነው ይቸኩላል፡፡ ወንድሜ አንተ ግን እግርህን ጠብቅ፤ ስንፍና በእግርህ ዘንድ እንዳይመጣ ነቅተህ ጠብቅ፡፡ የጽድቅን ጫማ እንዲጫማ ወደ ጽድቅ ገበያ ውሰደው፡፡ ጉዞው እንደ ዮሐንስ ያለ ጉዞ እስከ ቀራንዮ ተራራ ድረስ የሚጸና ይሆን ዘንድ አበርታው፡፡ እንደ ማርያም መግደላዊት እሾኹን እንቅፋቱን ሌሊቱን የሮማን ወታደር ሳይፈራ የጌታን መቃብር የሚመለከት አድርገው፡፡ ትንሣኤውን ለዓለም ሁሉ የሚያበሥር እግር እንዲሆን ምከረው፡፡ የሐዋርያትን እግር እንዲከተል አሰልጥነው፡፡ እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ ወንጌልን ለመስበክ የሚዞር ጠንካራ እግር ይሆንልህ ዘንድ ምከረው፡፡ መጥፎ ነገር ለማርዳት ሳይሆን ጥሩውን ነገር ለማብሠር አፍጥነው፡፡ እግርህ የምሥራች የሚናገር ያማረ እንዲሆን ጸሎትህ አይቋረጥ፡፡ እንደ አረጋዊው ዮሴፍ ልጅ ሰውን ለማስደንገጥ አይፍጠን፡፡ ወደ ግብጽ በተሰደደች ጊዜ ይህ ወልደ ዮሴፍ እየሮጠ ደረሰባቸውና እዚህ ተቀምጣችኋልን የሔሮድስ ወታደሮች መጥተዋልና ተነሡ ባላቸው ጊዜ እመቤታችን እጅግ ደነገጠች ዕንባዋንም አፈሰሰች፡፡ ይህን ያህል በረሀ የተንከራተትሁ ከሞት ላላተርፍህ ነውን ብላ አለቀሰች፡፡ ሕጻኑ ኢየሱስ ክርስቶስም አመጣጥህ መልካም ነበር ነገር ግን እናቴን አስደንግጠሃታልና በፍርድ ቀን አስነሥቼ እስክፈርድብህ ድረስ ድንጋይ ተንተርሰህ ተኛ አለው በዚያው ድንጋይ ሆኖ ቀረ፡፡ ይህ እግር አስደንጋጭ እግር ነው በመሆኑም ተገቢውን ቅጣት አገኘ፡፡ አንተ ግን ከእንደዚህ አይነቱ እግር የተለየ እግር ሊኖርህ ይገባል፡፡

© በመልካሙ በየነ
ጥቅምት 10/2008 ዓ.ም

ደብረማረቆስ፣ ኢትዮጵያ

Wednesday, October 14, 2015

ስሞት እንዳትቀብሩኝ

“… ሰው ነኝ! አዎ ሰው ነኝ! ሰውስ ብላችሁ ሰው መሰልኳችሁ! ዓለምን የዞርኩ፣ ዓለምን ያጣጣምኩ፣ ሁሉን የቀመስኩ፣ ሁሉ ያልቀረኝ፣ ሁሉን የሠራሁ፣ በነፈሰበት የነፈስኩ፣ በወረደበት የወረድኩ፣ በዘነበበት የዘነብኩ፣ በበረሩበት የበረርኩ ሁሉን የሆንኩ ሰው ነኝ፡፡ ያኔ ገና “ሀ” ብዬ ራሴን ለማይገባ ሱስ እጄን ሳነሣ ተው ባይ አጣሁ፤ እኔም በዛው ገፋሁበትና በጫት የጀመርኩት ሱስ በሲጋራ፣ በሲሻ እና በመጠጥ አጎለመስኩት፡፡ በፊት በፊት የሰፈር ጓደኞቼ የነበሩት ትምህርት ቤት የመማር ዕድል ሲያገኙ እኔ ግን ወላጆቼ ማስተማር ስላልቻሉ ነበር ወደ ጎዳና የወጣሁት፡፡ በእርግጥ ጎዳና መውጣቴ ለሱስ ዳረገኝ የሚል ጸጸት የለብኝም ምክንያቱም ትልልቅ የሚባሉት አገራችን በብዙ ዋጋ ውጭ አገር ድረስ ልካ ያስተማረቻቸው የአገር መከታና አለኝታ ይሆናሉ የተባሉ “ምሁራን” ሳይቀሩ የሱስ ተጠቂዎች ናቸው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ የአገራችን ትልልቅ ዲፕሎማቶች እንዲሁም የሚኒሰትር መስሪያ ቤት ተጠሪዎች ሁሉ ሱስ አጥቅቷቸው እንደኔ ሆነው ሳያቸው እጽናናለሁ፡፡ ሲጋራው ጫቱ ሁሉም አይቀራቸውም እኔ የጎዳና ተዳዳሪው እና እነርሱ አንድ እኩል የሚያደርገን ነገር ሱስ ብቻ ነው፡፡
ዛሬ እነዚያ የሰፈሬ ልጆች ትልልቅ ሰዎች ሆነው ትልልቅ ከሚባሉ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ናቸው፡፡ እኔ ደግሞ በሱስ ብዙ ዘመናትን ያሳለፍኩ ከንቱ ሰው እንደሆንኩ አስባለሁ፡፡ ይህ ከንቱነቴ ይበልጥ የሚያስለቅሰኝ የእኔ እኩዮች የሰፈሬ ልጆች ሲያገኙኝ ሰላም ለማለት ተጠይፈውኝ እንደማያውቁኝ ሲያልፉኝ ነው፡፡ በጣም አለቅሳለሁ በጣምም አነባለሁ እጅግም አዝናለሁ እንዴት የሰፈሬ ልጆች ይጠየፉኛል? ቢያንስ አብረን አፈር ፈጭተን ጭቃ አቡክተን አኩኩሎሽ ተጫውተን ያደግነውን እንዴት ይዘነጉታል? ወይስ የእኔ በሱስ መውደቅ የእነርሱን ክብር የሚነካ መስሎ ታይቷቸው ይሆን? ይህን ሳመላልስ ኅሊናዬ በጣም ይደማል እጅግ አዝናለሁ፡፡ ለነገሩ ልክ ናቸው እንደእኔ ያለ ከንቱ እንደነርሱ ላለ ትልቅ ሰው ጓደኛ መሆን ክብራቸውን የሚነካ ሊሆን ይችል ይሆናል፡፡
እኔ ከዚያ ሱስ መውጣት አልቻልኩም በእርግጥ እንድወጣም የሚመክረኝ ሰው የለኝም፡፡ በጣም የምበሳጨውም በዚህ ነው፡፡ ሰው ሕይወቴን ለመቀየር ባይጥር ምክር መለገስ ምን ይከብደዋል? ምን ወጭ ያስወጣዋል? እኔ በኃጢአት ባሕር እንደምዋኝ በኃጢአት ማዕበል እንደምናጥ አውቀዋለሁ፡፡ ዛሬ ከአንዷ ነገ ደግሞ ከሌላኛዋ ጋር፤ ብቻ ካገኘዋት ጋር ሁሉ አንሶላ ተጋፍፌያለሁ፡፡ ያ በሽታም ሳይኖርብኝ አይቀርም ስላልተመረመርኩ ነው እንጅ፡፡ በጣም ጎስቁያለሁ ከውሻ ጋር እየተሻማሁ እመገባለሁ ዞሮ ያየኝ ሰው አለመኖሩ ውስጤን ያሳዝነዋል፡፡ መንግሥትስ ቢሆን ምን አረገልኝ? ተው ጫት አትቃም፣ ሲጋራ አታጭስ፣ ዝሙት አትፈጽም በማለት ፈንታ በጥቃቅን በምናምን አደራጀሁ እያለ አይደል እንዴ ሴቶችን የሚቀያይርልን፡፡ ዝሙት አትፈጽም ብሎ ከመምከር ይልቅ ኮንዶም ተጠቀሙ እያለ ነው ማስታወቂያ የሚሰራልን፡፡ ዛሬ ሴተኛ አዳሪዎች ስንት ናቸው? እንደእኔ ካገኛት ጋር የሚተኛው ወንድስ ስንት ነው? ጫት መቃሚያ ቤቶች የሚዘጉት እኮ ግብር አልከፍል ሲሉ እንጅ ወጣቱን ሱሰኛ ስላደረጉት አይደለም፡፡ ታዲያ እንደዚህ አይነት መንግሥት ባለበት አገር ላይ እኔ ራሴን ማዳን ካልቻልኩ በቀር ማን ዞሮ ያየኛል? የሰውን ኅሊና ከመገንባት ይልቅ ሕንጻ መገንባት ላይ ትኩረት ባደረገች አገር ውስጥ ከሱስ ነጻ መሆን ይከብዳል፡፡

አብሮ አደጎቼ ሆይ! ዛሬ እንዲህ ስጎሰቁል፣ መካሪ ሳጣ፣ አይዞህ ባይ ረዳት ሲርቀኝ፣ ሰው የመሆን ህልሜ ሲዳፈን አይታችሁ ጨከናችሁ አይደል? ተውት ለእኔስ እግዚአብሔር አለኝ እመብርሃን ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም እናቴ አለችኝ፡፡ ዛሬ እና ነገ የእኔን ማንነት አንድ ሆኖ አታዩትም፡፡ ያንን ሱሰኛ ጓደኛችሁን ዳግም በዚያ ሁኔታ ላታዩት እስከወዲያኛው ይሰናበታል፡፡ ይኼው በቃ! ማል ካላችሁኝ ማልሁላችሁ ሲጋራዬን ሰባብሬ፣ ጫቴን አሽቀንጥሬ፣ ዝሙቴን መዳራቴን ሁሉ ትቼ ንስሐ ገብቼ ከአምላኬ ጋር ታርቄ ልኖር ወስኛለሁ፡፡ በቃ አለቀ! ታሪኬን እቀይራለሁ ሲጋራ ማጨሴን ጫት መቆርጠሜን ዳግም ላልመለስባቸው ላልደርስባቸውም ወረወርኳቸው፡፡ ነገር ግን ሰው ስሆን ያኔ ሰው ሆኜ ስሞት ያኔ እንዳትቀብሩኝ ምክንያቱም በቁሜ ቀብራችሁኝ ስለነበር፡፡ ያን ያህል አይዞህ ባይ ባጣሁበት፣ ከውሻ ጋር ተሻምቼ በተመገብኩበት ማደሪያ አጥቼ ግድግዳ ተደግፌ በማነጋሁበት ሌሊት፣ በሲጋራ ሳንባዬ በነደደ ሰዓት ልባችሁን አጨክናችሁብኝ አልነበር? ሰላም እንዳትሉኝ ተጠየፋችሁኝ አይደል? በእርግጥ አልቀየማችሁም ነገር ግን ስሞት እንዳትቀብሩኝ እናዘዝላችኋለሁ፡፡ የሰው ልጅ ትልቁ ሰውነት በቁም መረዳዳት ብቻ ነው ሲሞቱ አልቅሶ መቅበር አይደለም ስለዚህ በቁሜ ስሞት ለቀበራችሁኝ አብሮ አደጎቼ ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ሆኜ ስሞት ለቅሶ ደረሱ ለመባል ያህል ቀብሬ ላይ መጥታችሁ እንዳትቀብሩኝ፡፡ እንዳታለቅሱልኝ፡፡ አደራ በሰማይ አደራ በምድር፡፡ አበቃሁ…”

Monday, October 12, 2015

ፍርሐት


©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
…ሌላው ከእግዚአብሔር እንድንርቅ ምክንያት የሆነው ፍርሐት ነው፡፡ ዓላውያን ነገሥታት፣ ከሐድያንና መናፍቃን ሲነሡ ስለ እግዚአብሔር አምላክነት ለመመስከር ፍርሐት አለ፡፡ እነዚህ ሊገድሉህ ቢችሉ እንኳን ሥጋህን እንጅ ነፍስህን ሊገድሏት አይችሉም፡፡ እነዚህን መፍራት እንደማይገባም በወንጌል እንዲህ ተገልጿል “ሥጋህንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ” /ማቴ10÷28/ አንተ መፍራት ያለብህ ገሃነም ሊያስገባህ የሚችልውን ኃጢአት ነው፡፡ ሰው ቢዝትብህም፣ ቢያስፈራራህም፣ ቢያስጨንቅህም ፍርሐት ከእግዚአብሔር ሊያርቅህ አይገባውም፡፡ መግደላዊት ማርያም ሴት ሳለች ሴትነቷ ከእግዚአብሔር ፍቅር የሚያርቅ ፍርሐት አላመጣባትም፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስን መቃብር ይጠብቁ የነበሩትን የታጠቁ ወታደሮች ከምንም አልቆጠረቻቸውም ፍርሐት የለባትም ነበርና፡፡ በማለዳ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር ሄደች ሌሊቱ አላስፈራትም፡፡/ማቴ28÷1-10/ ሌሎች ፍርሐት ሲያርቃቸው እርሷ ግን ትንሣኤውን ለማየት የመጀመሪያ ሆነች፡፡ ሰለስቱ ደቂቅን የሚነድደው እሳት 49 ክንድ ያህል ከፍ ከፍ ሲል አላስፈራቸውም፡፡ የናቡከደነጾር ንጉሥ መሆን አላሸበራቸውም፡፡ እግዚአብሔር ብቻ አምላክ እንደሆነ መሰከሩ፡፡ ከፊታቸው የሚነድደው እሳት ወላፈኑ ልባቸውን አላስደነገጠውም፡፡ ንጉሥ ናቡከደነጾር ላቆመው ምስል እንዲሰግዱ በብዙ ነገሮች አስፈራራቸው፡፡ እነርሱ ግን ምንም አይነት ፍርሐት የለባቸውም ነበር፡፡ ንጉሥ ሆይ አንተ ላቆምከው ምስል በፍጹም አንሰግድም አንተንም እኛንም ዓለምን በፈጠረ እግዚአብሔር እናመልካለንና አሉት፡፡ በዚህም የተነሣ ወደ እቶኑ እጃቸውን ታስረው ተጣሉ ቅዱስ ገብርዔል መጥቶ እሳቱን እንደ ውኃ አቀዘቀዘላቸው በእሳቱ መካከልም እየተመላለሱ እግዚአብሔርን አመሰገኑት፡፡/ዳን3÷1-ፍጻ/ እነዚህን ሕጻናት የሚነድደው እሳት አላስፈራቸውም፡፡ እግዚአብሔር እንደሚያድናቸው ፍጹም እምነት ነበራቸው፡፡ እግዚአብሔር ፈቃዱ ሆኖ ከእሳቱ ባያወጣን ማለትም ሰማእትነትን እንድንቀበል ቢተወን እንኳን አንተ ላቆምከው ምስል አንሰግድም ብላው ፍጹም እምነታቸውን አሳዩ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚቆረጥበት ስለት የሚፈጭበት ወፍጮ ሲቀርብለት አልፈራም በእግዚአብሔር ጸና እንጅ፡፡ ንጉሡ ዱድያኖስ እስኪያፍርና እስኪፈራ ድረስ እየሞተ እየተነሣ ስለ እግዚአብሔር አምላክነት መሰከረ፡፡ ንጉሡ እጅግ ተጨነቀ፤ ገደልኩት አረፍኩት ሲል ተነሥቶ ይመጣበታል፡፡ አሁንም እኔን ከሞት ባስነሳ አንተንም በፈጠረ ዓለምን ሁሉ ካለመኖር ወደ መኖር ባመጣ አምላክ በእግዚአብሔር እመን እያለ ይገስጸዋል፡፡ንጉሡ ግን መስማትን እንቢ አለ፡፡ይህን የተቀደሰ ምስክርነት ለመጠበቅ አንተም የፍርሐትን ጫማ አውልቀህ ልትጥል ያስፈልጋል፡፡ እስከመጨረሻው ድረስ ፍርሐትን አርቀህ ከተከተልህ የድል አክሊልን ትቀዳጃለህ፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስን ልብ በል፡፡ ሌሎች ሐዋርያት ፈርተው ሲሸሹ እርሱ ግን እስከ ቀራንዮ ድረስ ፍርሐቱን አስወግዶ ተከተለው፡፡ በመስቀሉ አጠገብ በመገኘቱም ድንግል ማርያምን የምታህል እውነተኛ ቅድስት እናትእነኋት እናትህ ተብሎ ከአምላኩ ለመቀበል በቅቷል፡፡/ዮሐ19÷27/ አንተም እንደዚህ ባለው ጭንቅ ቀን እንኳን ሳይቀር ልትታመን ያስፈልጋል፡፡ በሰላም እና በደስታ ጊዜ ሁሉም ተከታይ ነው በመከራ ጊዜ ግን ሁሉ አይደለም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ምግቡን እያበረከተ ሲመግብ ይመገብ የነበረው ያ ሁሉ ሕዝብ እስከ ቀራንዮ ድረስ መስቀሉን ተሸክሞ ሲወድቅ ሲነሣ ሊያሳርፈው የተከተለ አልነበረም፡፡ ፍርሐትን ከልብህ አውጥተህ ወዲያ ጣለው፡፡ ያየኸውን ሁሉ ፈርተህ ከእግዚአብሔር ርቀህ ልትኖር አትውደድ፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል ያለ ፍርሐት ልትመሰክር አደራ አለብህ፡፡ ልምን ይህን ትናገራለህ? የሚልህ ቢነሣ ለእግዚአብሔር የሚገባ ስለሆነ ተናገርሁ ብለህ መልስለት፡፡ ስለ እምነትህ የሚገባውን ሁሉ ልታደርግ ከእግዚአብሔር ዘንድ መብት ተሰጥቶሃል፡፡ ይህን መብትህን እንዳትጠቀም የሚኮረኩምህ ከሃዲ ቢነሣ እጅህን አትስጠው የፍርሐት ስሜትም አይሰማህ፡፡ የነቢዩ ሙሴ መንድም አሮን የፈራውን ፍርሐት ከልብህ አርቀው፡፡ ሙሴከእግዚአብሔር ጋር 6 ቀን ቃል በቃል እየተነጋገረ 34 ቀን እየነገረ ሲያስጽፈው ለ40 ቀን በሲና ተራራ በቆየ ጊዜ ሕዝበ እስራኤል አሮንን ከግብጽ ያወጣን ሙሴ ም እንደሆነ አናውቅምና ተነሥተህ በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን አሉት፡፡ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ከእኔ ሌላ አማልክት አይሁኑልህ፡፡/ዘጸ20÷3/ የሚለውን አምላካዊ ትዕዛዝ ለመሻር ወሰኑ፡፡ እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ለማምለክ የግድ ሙሴ አብሯቸው መኖር ነበረበት እንዴ? አሮን ሕዝቡን ፈራ ገንዘብ ወዳጆች ናቸውና በሚስቶቻችሁ በወንዶችና በሴቶች ልጆቻችሁም ጆሮ ያሉትን የወርቅ ቀለበቶች ሰብራችሁአምጡልኝ አላቸው፡፡ ነገር ግን ሰይጣን አነሣሥቷቸዋልና ለወርቃቸውም አላዘኑም፡፡ ሕዝቡም እንደታዘዙት ወርቃቸውን ወደ አሮን አቀረቡት፤ እርሱም በመቅረጫ ቀረጸው ቀልጦ የተሠራ ጥጃም አደረገው፡፡ ቁጡዓን የሆኑትን ሕዝበ እስራኤል የፈራው አሮን የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ተላለፈ፡፡ እንዲህም አላቸው እስራኤል ሆይ እነዚህ ከግብጽ ምድር ያወጧችሁ አማልክት ናቸው አላቸው፡፡ ለዚያም ምስል መሥዋዕት እየሰዉ እየበሉና እየጠጡ እየዘፈኑም ሰገዱ፡፡በዚህም የተነሣ እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ላይ ተቆጣ፡፡ /ዘጸ32÷1-ፍጻ/ ይህ አይነት ፍርሐት ከእግዚአብሔር ያርቃል፡፡ ለጣዖት ሲሰግዱ መሥዋዕት ሲሰው በፍርሐት የሚመለከት ሰው ከእግዚአብሔር ለመራቅ የወሰነ ሰው ነው፡፡ ይህን አይነቱን ፍርሐት ማስወገድ ተገቢ ነው፡፡ ጭንቅ ሲመጣብህ ፈተና ሲደርስብህ መጽናት ከቻልክ ብቻ ነው የዘላለም ርስት ወራሽ የምትሆነው፡፡ ሐዋርያት ልብሳቸውን ጥለው እስከ መሮጥ ድረስ ያደረሳቸው ፍርሐት ነው፡፡ቅዱስ ጴጥሮስ ኢየሱስ ክርስቶስን 3 ጊዜ ለመካድ ያበቃው ፍርሐት ነው፡፡ ምንም እንኳን በኋላ ኃይልን ለብሰው አንገታቸውን ለስለት ጀርባቸውን ለግርፋት እስከመስጠት ድረስ የደረሰ ፍጹም ጽናት የተሰጣቸው ቢሆንም መጀመሪያ ላይ ግን ፍርሐት ነበረባቸው፡፡/ማር14÷50-52/፣ /ማር14÷66-71/ በአርግጥ እንደዚህ አይነቱ ፍርሐት ጊዜያዊ ፍርሐት በመሆኑ በንስሓ የመመለስ ዕድል ይሰጣል፡፡ የአሮንም ሆነ የሐዋርያት ፍርሐት ለጊዜው ነው፡፡ እንደ ነቢዩ ኢሳይያስ ያለ ፍርሐት ማለት ነው፡፡ንጉሡ ዖዝያን የማይገባውን ሥራ በቤተ መቅደስ ገብቶ አጥናለሁ ሲል ንጉሥ በመሆኑ ፈራው በዚህም የተነሣ ለምጽ ወጣበት ትንቢት ተነሣው፡፡ በኋላ ግን ተመልሶለታል ጊዜያዊ ፍርሐት ነበርና፡፡/ኢሳ6÷1-8/ ነገር ግን ያ በትንሹ የጀመረ ፍርሐት እያደገ ንስሓን በር ጭምር የሚዘጋ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ለጊዜው ነው በሚል አስተሳሰብ ኃጢአት መሥራት አይገባም፡፡ የመመለሻ ዕድሜ ይኑረን አይኑረን የምናውቀው ነገር ስለሌለ ዘሬ ፍርሐትን ልናስወግድ ያስፈልጋል፡፡ እስከ መጨረሻው መጽናት ያስፈልጋል፡፡ እስከ መጨረሻው የሚጸና እርሱ ይድናል ይላልና፡፡/ማቴ2413/ እዚህ ላይ የቅድስት ሶስናን ታሪክ እንመልከት፡፡ ሶስና መልከ ቀና ስለነበረች በሐፀ ዝሙት የተነደፉ ረበናት ወይም ሥርዓት አስተማሪ ነን ባዮች በአትክልት ቦታ ውስጥ ሰውነቷን ስትታጠብ ሄደው እሺ በእጄ በይን እንቢ ካልሽ ግን ከጎረምሳ ጋር ስትዳራ አገኘናት ብለን በድንጋይ እናስወግርሻለን አሏት፡፡ ነገር ግን ይህን ኃጢአት አድርጌው እግዚአብሔር ከሚፈርድብኝ ሳላደርገው ሞት ቢፈረድብኝ ይሻለኛል ብላ በድንጋይ ነመወገርን ሳትፈራ ጮኸች፡፡ እነርሱም አብረው ጮኹ ከወንድ ጋር ስትዳራ አገኘናት ብለው አዕሩገ እስራኤል ተሰብስበው ተወግራ እንድትሞት ፈረዱባት፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ዳንኤልን ልኮ አዳናት፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም ነገር ሠሪዎችን እንደ አክርማ ሰነጠቃቸው፡፡/መጽሐፈ ሶስናን ተመልከት/

Thursday, October 8, 2015

መልካም ምኞት አገላለጻችን ከየት ወዴት?

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ባለፈው ቃል በገባሁላችሁ መሠረት ቃሌን ለመጠበቅ ኢትዮጵያዊውን የመልካም ምኞት አገላለጽ እና አሁን እየተበረዘ ስላለበት ሁኔታ እንመለከታለን፡፡ ኢትዮጵያዊነታችን ከሌላው ዓለም ሁሉ ልዩ የሚያደርገን በርካታ ነገር እንዳለው የታመነ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት በደስታ በሐዘን የአንዱን ሌላው የሚጋራበት የባህል ማዕከል ነው፡፡ ሌላው ዓለም ምናልባት ሃዘንህን የተጋራ ደስታህንም እንዲሁ የተጋራ ሊመስል ቢችልም የመልካም ምኞት አገላለጹ ግን ሙሉ በመሉ ደስታህን እንዳልተጋራልህ ያሳያል፡፡ አንተ ስትደሰትም ሆነ ስታዝን ሌላው ሰው የሚጋራልህ ከሆነ እርሱ ኢትዮጵያዊነት መሆኑ አያጠራጥርም፡፡
ኢትዮጵያዊነት ደስታህ ደስታየ ነው ሲል “እንኳን ደስ አለህ!” ይልሃል አንተም “አብሮ ደስ ይበለን” ብለህ ትመልሳለህ፡፡ ይህ መልካም ምኞት መግለጫችን ደስታህ ደስታየ መሆኑን የሚጠቁም ነው፡፡ “አብሮ ደስ ይበለን” የሚለው ምላሽም እርሱን የሚያጎላ ነው ሁላችንንም ደስ ይበለን የሚል ስለሆነ፡፡ ሌላው “እንኳን አደረሰህ” የሚለው ሲሆን “እንኳን አብሮ አደረሰን” የሚለውን ምላሽ ያስከትላል፡፡ ያንተ መድረስ ለእኔ የእኔም መድረስ ላንተ ምኞታችን ነው ለዚህም ነው “እንኳን አደረሰህ” ስትባል “እንኳን አብሮ አደረሰን” የምትለው፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን ሁላችንንም እንኳን አደረሰን ብለን የምንመልሰው የሌሎቹንም ለዚያ ቀን መድረስ ስለምንመኝ ስለምናስብ ነው፡፡ መልካም ምኞት አገላለጻችን አንድን ወገን ብቻ የሚገልጽ አይደለም፡፡ ሌሎች ዓለማት ግን መልካም ምኞታቸው አንድ ወገን ተኮር ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነታችን ልዩ የሚያደርገን መልካም ምኞታችን ሁለት ወገን ተኮር መሆኑ ነው፡፡
አንድ ወገን ተኮር መልካም ምኞታቸው ኢትዮጵያዊነታችንን እየተፈታተነው ይገኛል፡፡ ውጮቹ “CONGRATULATION” ይላሉ መላሹም “THANK YOU” ይላል፡፡ “እንኳን ደስ አለህ” ሲባል “አመሰግናለሁ” ብሎ ይመልሳል ማለት ነው፡፡ የእኔ ደስታ አንተን አይመለከትም “እንኳን ደስ አለህ” ላልከኝ ግን “አመሰግናለሁ” ማለት ነው እንግዲህ፡፡ ኢትዮጵያዊነት ግን ደስታህ ደስታየ ነው እና አይመለከትህም አልልህም “አብሮ ደስ ይበለን” ብሎ ይመልሳል፡፡ ሌላው የምንመለከተው “የእንኳን አደረሳችሁ” መልእክታቸውን ነው፡፡ ውጮቹ “HAPPY NEW YEAR”፣ “HAPPY X_MASS”፣ “HAPPY EASTER” ወዘተ በማለት መልካም ምኞታቸውን ይገልጻሉ፡፡ እነዚህ መልካም ምኞቶች እኛ አገር ውስጥ ዋጋ የላቸውም፡፡ “መልካም አዲስ ዓመት”፣ “መልካም ገና”፣ “መልካም ፋሲካ” የሚል ቀጥተኛ ትርጉም ይይዛሉ፡፡ ታዲያ መላሹ “አመሰግናለሁ” ብሎ ይመልስ? ወይስ “እንኳን አብሮ” አደረሰን ይበል? ኢትዮጵያዊነት መቸም “አመሰግናለሁ” ብቻ ብሎ መልካም ምኞቱን ለሌሎችም ሳያጋራ ውጦ አይቀርም፡፡ ኢትዮጵያዊነት በመጀመሪያ “መልካም አዲስ ዓመት” አይልም “መልካም ገና” እና “መልካም ፋሲካ” ብሎም መልካም ምኞት አይገልጽም፡፡ የእኛ ያልሆነውን ነገር በፈረንጆቹ ተጽእኖ ከኢትዮጵያዊነታችን ጋር ቀላቀልነው እንጅ እኛ የምንለው “እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሰህ” ነው፡፡ መላሹም “አመሰግናለሁ” ሳይሆን “እንኳን አብሮ አደረሰን” የሚል ይሆናል፡፡ በሌላ አነጋገር እኔ ብቻ ሳልሆን አንተንም እንኳን አደረሰህ እያለው ነው፡፡ ፈረንጆቹ ግን “አመሰግናለሁ” ይሉሃል ምክንያቱም ያንተ ለዛ ቀን መድረስ አለመድረስ ምናቸውም አይደላማ!፡፡ ሌሎችንም በእነደዚህ ያለ ሁኔታ ነው እንኳን አደረሳችሁ የምንባባለው፡፡ ለገና በዓል “እንኳን ለጌታችን ለመድኃታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በሰላም አደረሰህ” እንዲሁም ለትንሣኤ በዓል “እንኳን ለጌታችን ለመድኃታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በሰላም አደረሰህ”  እንባባላለን መላሹም ከላይ እንደተመለከትነው “እንኳን አብሮ አደረሰን” ይላል፡፡

አሁን አሁን ግን በርካታ ኢትዮጵያዊነት ለዛችንን እያጣን ያለንበት ሁኔታ ነው፡፡ “እንኳን ለልደትህ በሰላም አደረሰህ” በማለት ፋንታ “HAPPY BIRTH DAY” ማለት የሚቀናው ኢትዮጵያዊ እየተበራከተ ነው፡፡ “መልካም ልደት”፣ “መልካም አዲስ ዓመት”፣ “መልካም ገና”፣ “መልካም ፋሲካ” ወዘተ እያልን የፈረንጆቹን አንድ ወገን ተኮር የሆነ መልካም ምኞት መግለጫ መጠቀም መጀመራችን ታሪካችንን የሚፈታተን እና ማንነታችንን የሚያበላሽ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነታችን ከሌላው የዓለም ክፍል ሁሉ ልዩ ያደርገናል፡፡ የአመጋገብ፣ የአለባበስ፣ የአነጋገር፣ የአረማመድ ልዩ ባህል አለን፡፡ ስንመገብ ዘመድ ጎረቤቱ ተሰብስቦ በአንድ መሶብ ከብቦ አንዱ አንዱን እያጎረሰ ይመገባል፡፡ ይህ ልዩ ፍቅርን የሚያሳይ ነው የሚጎርሰው ሰው ቆርሶ መጉረስ አልችል ብሎ አይደለም የምናጎርሰው ፍቅራችንን ለመግለጽ እንጅ፡፡ መተሳሰብ መረዳዳታችንን ለማሳየት የምንጠቀምባቸው ባህሎቻችን ናቸው፡፡ስለዚህ በሌሎቹ ተጽእኖ ስር ከመውደቅ ራሳችንን እንጠብቅ የሚል መልእክት አስተላልፋለሁ፡፡