Friday, November 10, 2017

መሠረተ ሐይማኖት ወይስ መሠረተ ክህደት? ክፍል ፫


፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ዛሬ ከገጽ ፭ እስከ ፮ ያሉትን ስህተቶች በማስረጃ አስደግፈን እንመለከታለን፡፡ በፎቶ ከስር አብሬ ስለማያይዝላችሁ ሙሉውን ማንበብ ትችላላችሁ እኔ ግን በቤተክርስቲያናችን ትምህርት ልዩነት ያለውን ብቻ በማስረጃ እያስደገፍሁ እጽፍላችኋለሁ፡፡



#እናምናለን_ምሥጢረ_ቅባት የሚል መዝሙር በጭፈራ መልኩ ሲዘመር የሚያሳይ መረጃ ከጉንደወይን ደርሶኛል፡፡ #በወልደ_አብ_መናፍቅ_አፈረ በማለት ቅዱስ ሲኖዶስ ያወገዘውን መጽሐፍ ደግፈው ሲጨፍሩ አድረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ #በሃያ_ስምንት_መብላት_ተወገዘ ይላሉ፡፡ “ወልደ አብ” የታተመባትን ቆጋ ገዳምን #ቆጋ_ገዳም_የሃይማኖት_አገር በማለት ሲያሞካሹም ተደምጠዋል፡፡ #ሁለተኛ_ሻወር_መውሰድ_ቀረ በማለትም ጥምቀትን #ሻወር ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ #አክሲማሮስ_የቅባት_ምስክር በማለትም ሊቁ ኤጲፋንዮስ የጻፈልንን መጽሐፍ ለክህደታቸው #ምስክር ነው ሲሉ ተሰምተዋል፡፡ ተዋሕዶ ነን የሚሉ ካህናትንም በዚያ አካባቢ መከራ እንደሚያጸኑባቸውም በዕለቱ ትምህርት የሰጡት ሰው ተናግረዋል፡፡ ይህ ጉዳይ በዝምታ መታየት የለበትም፡፡ በቤተክርስቲያናችን ስም እየተሰባሰቡ ቤተክርስቲያናችንን ለማፍረስ እየሠሩ ያሉ ስለሆነ ጉዳዩን ወደ ህጋዊ አካል ማድረስ ቢቻል ጥሩ ነው ባይ ነኝ፡፡

 


ከዚህ በተጨማሪም አቡነ ማርቆስ ከቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ እንደተመለሱ የተቃወሟቸውን ካህናት ክህነታቸውን በመያዝ እርሳቸውን ደግፈው ያልሄዱትን ደግሞ ካሉበት ኃላፊነት ቦታ በማንሣት ተራ ካህን አድርገዋቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ሊቀ ልሳናት ኢሳይያስ ጤናው ከአዋበል ወረዳ ቤተክህነት ሥራ አስኪጅነት፣ መሪጌታ ቤዛ ጥላሁንን ከአዋበል ቤተክህነት ጸሐፊነት፣ መልአከ ሰላም ጌታቸውን ከአነደድ ወረዳ ቤተክህነት ሥራ አስኪጅነት፣ ሊቀ ብርሃናት ተስፋ ባየውን ከጎዛምን ወረዳ ቤተክህነት ሥራ አስኪጅነት አንሥተው ተራ ካህናት አድርገዋቸዋል ተብሏል፡፡ እኔን ተቃውማችሁ አዲስ አበባ ድረስ ሄዳችኋል በሚል የመጋቤ አእላፍ ጥበቡን ክህነታቸውን ይዘውባቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እርሳቸውን ደግፈው አዲስ አበባ ለሄዱት ደመወዛቸውን በእጥፍ አሳድገውላቸዋልም ተብሏል፡፡



ወደ ርእሰ ጉዳያችን ስንመለስ ገጽ ፭ ላይ እንገልጣለን፡፡ ካሳሁን ምናሉ እንዲህ ይላል “ማስመርያም እንደሰጠ መንፈስ እግዚአብሔር ዘላዕሌየ ዘበዕንቱአሁ ቅብአኒ እዜ ንወሙ ለነዳያን ፈነወኒ ወእሰብክ ግዕዛነ ለፄውዋን፡፡ ብሏታል መንፈሰ እግዚአብሔር በላዬ ላይ ሥለራሱም ቀባኝ ለነዳያን እነግራቸዋለሁ ተገስተው ለተማረኩት እሠብክ ዘንድ ላከኝ፡፡ ዕሳ ም.1፣1” ይለዋል ቆርጦ በመቀጠል የተካነው ካሳሁን፡፡ ፕሮቴስታንቶች “ማለደ” የሚል ቃል ፍለጋ ዓይናቸው እስኪጠፋ ድረስ መጽሐፍ ቅዱስን ያገላብጣሉ፡፡ ቅባቶች ደግሞ “ቀባ” የሚል ቃል ፍለጋ ትውስታቸውን ተነጥቀዋል፡፡ መጀመሪያ ጥቅሱ የት እንደሚገኝ በትክክል መጠቆም ነበረበት “ዕሳ” የሚባል መጽሐፍ አናውቅም ኢሣይያስ ለማለት እንደሆነ ግን ቃሉ ያለበትን ቦታ ስለምናውቀው የግድ እንረዳለታለን፡፡ በነገራችን ላይ ይህን ቃል ቅዱስ ገብርኤል ለድንግል ማርያም እንደነገራት አድርጎ ነው የጻፈው ሙሉውን ስታነቡት ታገኙታላችሁ፡፡ ይህንን ቃል ግን ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን አልነገራትም፡፡ ይዌድስዋ መላእክት ላይ እንዲህ ተጽፎ አናገኝም፡፡ ቃሉ የተጻፈው ኢሳይያስ ትንቢት ላይ በስድሳ አንደኛው ምእራፍ ነው፡፡ የጠቀሰው ቃል የሚገኘው ኢሣ ፷፩፥፩ ላይ ሲሆን ቃሉና የቤተክርስቲያናችን አንድምታ ትርጓሜ እንደሚከተለው ነው፡፡ “መንፈሰ እግዚአብሔር ላዕሌየ ዘቀብአኒ ዘበእንቲአሁ አስተፍሥሆሙ ለነዳያን ፈነወኒ” ስለሱ ነዳያን ትሩፋንን ደስ አሰኛቸው ዘንድ በኔ ያደረ መንፈሰ ረድኤት ላከኝ ይላል ኢሳይያስ፡፡ ወእፈውሶሙ ለቁስላነ ልብ፣ በቁስለ መከራ የተያዙትን አድናቸው ዘንድ፤ ወእስብክ ሎሙ ግዕዛነ ለፂውዋን፣ ለተማረኩት ነጻነትን አስተምራቸው ዘንድ ማለት ሚጠትን አስተምራቸው ዘንድ ላከኝ፡፡ ወይርአዩ እውራን፤ እውራነ ልቡና እስራኤል ያዩ ዘንድ ላከኝ፡፡ ወእስምዮ ለዓመተ እግዚአብሔር ኅሩየ፤ ዕለተ ሚጠትን የተመረጠ እለው ዘንድ ወለዕለተ ፍዳ ኅሪተ፤ ዕለተ ፍዳም ያላት ዕለተ ሚጠት ናት የባቢሎን ሰዎች ፍዳን ስለተቀበሉባት ዕለተ ፍዳ አላት፡፡ ወአስተፍሥሆሙ ለልህዋን፤ ሰባ ዘመን ያዘኑትን ደስ አሰኛቸው ዘንድ፡፡ ወአሀቦሙ ክብረ ለእለ ይላህውዋ ለጽዮን፣ ኢየሩሳሌምን አጥተው ላዘኑ ሰዎች ክብረ ሥጋን እሰጣቸው ዘንድ፡፡

ወህየንተ ሐመድ እፍረተ ትፍሥሕት ለእለ ይላህው፣ ትቢያ ይበንባቸው ስለነበረ ፈንታ ላዘኑ ሰዎች ደስ የሚያሰኝ ሽቱን እሰጣቸው ዘንድ፤ ወልብሰ ክብር ህየንተ መንፈስ ትኩዝ፣ ሰባ ዘመን ስለአዘነ ልብ ፈንታ ደስ አሰኘው ዘንድ ፈነወኒ፣ ላከኝ፣ አንድም መንፈሰ እግዚአብሔር ላዕሌየ ዘቀብአኒ ዘበእንቲአሁ አስተፍሥሆሙ ለነዳያን ፈነወኒ፣ ያዋሐደኝ በህልውናዬ ያለ የእግዚአብሔር የባሕርይ ህይወቱ መንፈስ ቅዱስ፣ አንድም ሳይናበብ መንፈሰ እግዚአብሔር ላዕሌየ፤ በእኔ ህልውና ባለ መንፈስ ቅዱስ ያዋሀደኝ እግዚአብሔር አብ ምእመናንን አስተምር ዘንድ ላከኝ፣ አንድም መንፈስ ዘዚአየ በህላዌ ለሊሁ ኀደረ ላእሌየ ብሎ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ ተረጉሞታልና ብሎ የእግዚአብሔር አብ የባህርይ ህይወቱ መንፈስ ቅዱስ ላዕሌየ በእኔ ህልው ነው፣ ወዘበእንቲአሁ ቀብዐኒ፣ ስለማስተማርም ያዋሐደኝ መንፈስ ቅዱስ ምእመናንን አስተምራቸው ዘንድ ላከኝ” የሚል ሆኖ ሳለ ካሳሁን እና መሰሎቹ ግን ይህን ቃል ይዘው “ቀባኝ” በሚለው ቃል ላይ ብቻ ተንተርሰው ሲተኙ ይታያሉ፡፡ ሳዊሮስም ሃይማኖተ አበው ላይ ይህንን ቃል ይተረጉመዋል ይተረጉማል ሃይማኖተ አበው ዘሳዊሮስ ክ ፱ ቁ ፲፰ እንዲህ ይላል “ስለዚህ ነገር ከዚህ በኋላ ለድኆች የምሥራች እነግራቸው ዘንድ ያዘኑትን አረጋጋቸው ዘንድ ለተማረኩት ነጻነትን እሰብክላቸው ዘንድ ዕውሮች ያዩ ዘንድ ስለዚህ ላከኝ አለ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ገንዘቡ ሆነ መባሉ ቃል ሰው ስለሆነ ነው ሰውማ ባይሆን ኖሮ እግዚአብሔር በእግዚአብሔር ህልው እንደሆነ መንፈስ ቅዱስ በባሕርየ መለኮት ገንዘቡ ነውና እንደምን ገንዘቡ ሆነ ይባላል አብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ  ህልው መሆኑን እንደተናገረ”፡፡

ገጽ ፮ ላይ ስንገልጥ ደግ እንዲህ የሚል እናገኛለን፡፡ “ሠሪው መንፈስ ቅዱስ ነው ሥጋን የፈጠረው እሱ ነውና ቀብቶ ያነፃም ሲዋሐድ ነውና ቃል ከርሷ የነሳውን ሥጋ በአብ ፈቃድ በወልድም ፈቃድ በመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ አንድ ባህሪይ አንድ መለኮት አደረገው እንጅ እንዳለ ቄረሎስ ሊቀ ጳጳስ  ዘእስክንድርያ” ይላል፡፡ ቄርሎስ ይህንን የተናገረው በስንተኛው ድርሳኑ በስንተኛው ምእራፍ በስንተኛው ክፍል በስንተኛው ቁጥር ነው ብለን ብንጠይቀው የብራና ስለሆነ ምእራፍ እና ቁጥር የለውም ነው የሚለን ይህ ቀልደኛ ሰው፡፡ “ሠሪው መንፈስ ቅዱስ ነው” የሚለው ያስማማናል ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ላይ የፈጠረ የከፈለ ያዋሐደ መንፈስ ቅዱስ ነው ይላል፡፡ ረቂቅ ምሥጢሮችን ለመንፈስ ቅዱስ ሰጥቶ መናገር የመጻሕፍት ልማድ ስለሆነ ነው እንጅ በመፍጠር በመክፈል በማዋሐድ የተለያዩ ሆነው አይደለም፡፡ ያማ ከሆነ ፈጣሪ የሚባለው መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው የሚል ክህደትን ያመጣል እኮ፡፡ ስለዚህ በመጀመሪያ መስማማት ያለብን በመፍጠር አንድ መሆናቸውን ነው፡፡ አንድ ናቸው ካልን ወልድ ራሱ የፈጠረውን ሥጋ ተዋሐደ ማለታችን ነው፡፡ እኛ ማስረጃ ይዘን ነው ይህን የምንለው ሃይማኖተ አበው አበው ዘኤፍሬ ምእራፍ ፵፯ ክፍል ፩ ቁጥር ፪ ላይ “ድንግል ፈጣሪዋን ወለደችው፤ እርሱም እናቱን ፈጠራት፤ ከርሷም፣ እርሱ የፈጠረውን ሥጋ ተዋሐደ” ብሏል፡፡ ስለዚህ ወልድ የተዋሐደው ሥጋ በእርሱ የተፈጠረ እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ “ቀብቶ ያነፃም መንፈስ ቅዱስ ነው” የሚለው አባባል ግን ስህተት ነው፡፡ “በመንፈስ ቅዱስ ቅባትነት ከበረ” ለማለት ነው እንግዲህ ይህን ያህል የሚደክመው፡፡ ወልድ ራሱ ያከብራል ይቀድሳል እንጅ በሌላ አይከብርም አይቀደስምም፡፡ ይህንንም በማስረጃ ነው የምገልጥላችሁ ስምዐት ፻፳፬ ቁጥር ፴፬ ላይ “ወካዕበ ይቤ እስመ ክርስቶስ ኢተቀብዐ በእንተ መፍቅድ ዘቦቱ አላ ለሊሁ ቀባዒ ውእቱ…፤ ዳግመኛ ክርስቶስስ ክብር መሻት ኖሮበት አልከበረም እርሱ ራሱ አክባሪ ነው እንጅ…” ይላል ሃይማኖተ አበው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሃይማኖተ አበው ስምዓት ምእራፍ ፻፳፬ ክፍል ፪ ቁጥር ፲፬ ላይ “ወከመዝ ነአምሮ ለሊሁ ተቀብዐ ከመ ሥርዓተ ትስብእት ወዳእሙ ውእቱ ዘይቀብዕ ርእሶ በመንፈሱ ባሕቲቱ፤ በተዋሕዶ እንደከበረ እናውቃለን ግን በገዛ ሥልጣኑ ራሱን የሚያከብር እሱ ነው”፡፡

፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ኅዳር ፩ / ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍




No comments:

Post a Comment