፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ዛሬ ከገጽ ፳ ጀምረን ያሉ ስህተቶችን በማስረጃ እንመለከታለን፡፡ በፎቶ ከስር ስለማያይዝላችሁ ሙሉውን
ማንበብ ትችላላችሁ እኔ ግን ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ብቻ ነው ትኩረት የማደርገው፡፡
ካሳሁን ምናሉ “መሠረተ ሐይማኖት” በተሰኘ የክህደት መጽሐፉ
ገጽ ፳ ላይ እንዲህ ይላል “ስጋ በርስቱ ከበረ ብዕለ
እንዳይባል በተዋሕዶ ከበረ ማለት ነው፡፡ በተዋሕዶ ከበረ ማለትም በህድረት ከበረ ማለት ነውና እንደ ንስጥሮስ ሁለት አካል ማድረግ ነው ስለዚህ ስጋ ከቃል
ከተዋሐደ በኋላ ክቡር ባዕል መባል ይገባዋል ዕንጅ፡፡ ክብረ ብዕለ መባል አይገባውም፡፡ በተዋሕዶ ከበረ ማለት እንዴት ነው ቢሉ፡፡
ሁለት አካል ማድረግ ነውና ከንስጥሮስ ባህል ይገባል ማለት እንዴትና፡፡ ተዋሕዶ አንድነትን ይፀናል እንጅ፡፡ ሁለትነትን ያመጣልን
እንጅ ቢሉ፡፡ በተዋሕዶ ከበረ ወልድ ቅብዕ ማለት ስም ሰጥቶ ግብር መንሳት ነው” ይላል፡፡
በነገራችን ላይ ማንም ሰው የመሰለውን የማመን ነጻነቱ ከፈጣሪው የተቸረው
ጸጋ ነው ማንም አይነጥቀውም ነገር ግን አንዱ በሌላው ገብቶ የማይመለከተውን ነገር ሲዘባርቅ ዝም ማለት አይገባም፡፡ መጀመሪያ ስለሆነ
ነገር ከመጻፍ በፊት ስለሚጻፈው ነገር ማወቅ ያስፈልጋል ከላይ ከላይ ከሆነ አጉል ነው፡፡ እኛ ቅባቶች እንዲህ ይላሉ ስንል መጽሐፋቸውን
ጠቅሰን ነው እነርሱ ግን በመሰላቸው ሄደው ነው፡፡ መጻሕፍትን መሠረተ እምነትህን መሠረት አድርገህ ነው የምትተረጉማቸው ስትተረጉማቸው
ደግሞ ሊቃውንቱ ምን አሉ ሐዋርያት ምን አሉ ነቢያቱ ምን አሉ ቅዱሳን አበው ምን አሉ ታዲያ እንዴት ይስማማል እንዴት ይታረቃል
ብለህ የማስታረቅ ሥራ ትሠራለህ፡፡ ይህን ለማድረግ ግን መሠረተ እምነት (ዶግማ) ሊኖርህ ይገባል አሁን ትልቁ ጥያቄ የዶግማው ጉዳይ
ነው፡፡ ተዋሕዶን ስናነሣ ወይም “ወልድ ዋሕድ በተዋሕዶ ከበረ” ብለን ስናምን የቃል ከሥጋ መዋሐድ እንበለ ውላጤ (ያለመለወጥ)፣
እንበለ ትድምርት (ያለ መጨመር) እንበለ ቱሣሔ (ያለመቀላቀል)፣ እንበለ ኅድረት (ያለ ማደር)፣ ያለመጎራበት፣ ያለመመለስ፣ ያለመከፈል
ወዘተ ነው፡፡ እዚህ ላይ ማንሣት የፈለግሁት ነገር ውዳሴ ማርያም እሁድ ላይ “ደመረ መለኮቶ” የሚለውን ቃል ነው፡፡ ይህን ቃል
ድማሬ አለበት አንልም፡፡ መነሻ መሠረታችን ዶግማችን እንበለ ድማሬ ነውና፡፡ ስለዚህ ይህንን ማስማማት ማስታረቅ የሊቃውንቱ ሥራ
ነው የሚሆነው፡፡ ታርቆ ተስማምቶም የተተረጎመልን ለዚሁ ነው፡፡ መለኮቱን ጨመረ ቀላቀለ ተብሎ አልተተረጎመም ተዋሐደ ተብሎ እንጅ፡፡
ዮሐንስ ወንጌልንም ማንሣት ይቻላል “ቃል ሥጋ ኮነ” ይላል “ኮነ” ን ይዘን “ሆነ” ብንለው “ቃል ተለውጦ ሥጋ ሆነ” ያሰኘናል
ስለዚህ ይህንን ቃል “ተለወጠ” ተብሎ እንዳይተረጎም አስቀድመን በመሠረተ እምነታችን ውስጥ “እንበለ ውላጠየ (ያለመለወጥ” ብለናል፡፡
ስለዚህ ይህን ቃል በተዋሕዶ መሠረተ እምነት ነው ልንተረጉመው የምንችለው ማት ነው፡፡ በርካታ ጥቅሶችን ማንሣት ይቻላል ግን ለጊዜው
በዚህ ይብቃን፡፡
ወደ ቅባቶም ስንመጣ የራሱ መሠረተ እምነት አለው መጻሕፍትንም የሚተረጉመው
በዚያው መንገድ ነው፡፡ ተዋሕዶ ኑፋቄ ነው ብለው ስለተነሡ “በተዋሕዶ ከበረ” ማለትን ይነቅፉና “በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ”
ብለው ያምናሉ፡፡ ቅባትን ኑፋቄ ነው የምንለው በተዋሕዶ እይታ ላይ ሆነን ነው፡፡ ተዋሕዶ ደግሞ መሠረቶቿ የሐዋርያት የሊቃውንት
መጻሕፍት ናቸው፡፡ እነዚህ መጻሕፍት የሚተባበሩበትን ይዛለችና መናፍቃንን ስትረታቸው ትኖራለች፡፡
“ስጋ በርስቱ ከበረ (ከብረ ለማለት ፈልጎ ነው) ብዕለ እንዳይባል በተዋሕዶ
ከበረ ማለት ነው” ይላል፡፡ ይህ ሰው ቃሉን የግድ ማጣመም የፈለገው “በተዋሕዶ ከበረ” ብሎ ላለማመን ነው፡፡ “ብዕለ ከብረ” ብየ
ከፈታሁትማ “በተዋሕዶ ከበረ” ሊያሰኘኝ ነው ስለዚህ “በተዋሕዶ ከበረ” ላለማለት ቃሉን በሌላ መፍታት አለብኝ እያለን ነው፡፡ አስተውሉ
ትግሉን ማምለጫ ፍለጋውን፡፡
“በተዋሕዶ ከበረ ማለትም በህድረት ከበረ ማለት ነውና እንደ ንስጥሮስ
ሁለት አካል ማድረግ ነው” ይላል ካሳሁን ምንም በማያውቀው የተዋሕዶ ምሥጢር ውስጥ እየሰጠመ፡፡ ልብ በሉ ተዋሕዶ ከሁለት አካል
አንድ አካል ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ሆነ የሚባልለት ድንቅ ምሥጢር ኅድረት የሚሆነው በምን መልኩ ነው፡፡ “ቅባት ያለ ተዋሕዶ
ተዋሕዶም ያለቅባት አይረቡም” ብለው የሚያምኑ አርዮሳውን ናቸው እንግዲህ ይህንን የሚናገሩት፡፡ “ቅባቱ ያለተዋሕዶ አይረባም” የምትሉ
ሰዎች ይህ ተዋሕዶ የምትሉት ኅድረት ነውን? ከተዋሕዶ በኋላ መከፋፈል አይገባም በሥጋ ርስት በመለኮት ርስት አትበሉ ብለን ስንከራከራቸው
ጊዜ የአባየን ወደ እምየ እንደሚባለው ኅድረትን ከራሳቸው አውጥተው ለተዋሕዶ ሲሰጡ ነው የታዩት፡፡ይህ ፈጽሞ የማይሆን ነገር ነው፡፡
ንስጥሮስ ምን አይነት ሰው ነው ባህሉስ ምን ነበር እስኪ በአጭሩ እንመልከት፡፡ ንስጥሮስ ሁለት መሠረታዊ ክህደቶች አሉበት፡፡ እነዚህም፡-
v
ከተዋሕዶ በኋላ
መለያየት እንዳለ ያምን የነበረውን ዲያድርስ የሚባለውን መናፍቅ አስተምህሮ ያምን ነበር፡፡ የዚህ መሠረታዊው ክህደት ሁለት ባሕርይ
የሚል ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከተዋሕዶ በኋላ አንዱን ወልደ ዳዊት አንዱን ደግሞ ወልደ እግዚአብሔር ነው በማለት ያምን ነበር፡፡
v
ሁለት ባሕርይ
የሚል እምነት ስለነበረው ከእግዚአብሔር አብ የተወለደው ወልደ እግዚአብሔር ከድንግል ማርያም የተወለደው ደግሞ ወልደ ዳዊት ነው
ብሎ ያምን ስለነበር እመቤታችን ክብር ይግባትና የወለደችልን እሩቅ ብእሲ ሰውን ነው እንጅ አምላክን አይደለም ይል ነበር፡፡ በዚህም
ድንግል ማርያምን “ወላዲተ ሰብእ” በማለት ክህደቱን ጀምሯል፡፡
እነዚህን ክህደቶቹን በአደባባይ በማስተማር እርሱን መሰሎችን መሰብሰብ ጀመረ፡፡
ለዚህ ክህደቱም ይደግፋል ብሎ ይጠቅስ የነበረው “ቃል ሥጋ ሆነ” ዮሐ ፩÷፲፬ የሚለውን ቃል ነበር፡፡ ይህንን ቃል ለራሱ እንዲመች
አድርጎ “መለወጥ አለበት” በማለት ኑፋቄውን ቀጥሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ፊልጵ ፪÷፭-፮ ላይ “በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ
ዐሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይኹን እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር
አልቆጠረውም” የሚለውን ቃል ይዞ በራሱ ለራሱ እንዲመች አድርጎ በመተርጎም “ቃል በሥጋ አደረ” ብሎ ኅድረትን ደግፎ ያስተምር ነበር፡፡
ስለዚህ ይህ ንስጥሮስ በውስጡ ብዙ ምንፍቅናዎችን የያዘ ትምህርት በዐደባባይ ያስተምር ነበር፡፡ ይህንን የክህደት ትምህርቱን የሰሙ
ሊቃውንት በተለያዩ ጊዜያት ተገቢውን መልስ እየሰጡ ይመክሩት ነበር፡፡ ለዚህ ለንስጥሮስ ክህደት ተገቢውን ምላሽ ከሰጡት አባቶች መካከል በእስክንድርያ ፳፬ኛ ፓትርያርክ የተሾመው ቅዱስ ቄርሎስ
ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ይህ ታላቅ አባት የቃልና የሥጋን ተዋሕዶ በሚገባ ከምሳሌ ጋር በማስረዳት ውላጤ እና ኅድረት የሚሉትን የንስጥሮስ
ክህደቶች በሚገባ አጋልጧል፡፡ የጌታን አምላክነት የድንግል ማርያምን
ወላዲተ አምላክነት ነቅፎ ያስተምር የነበረው ንስጥሮስ በቅዱስ ቄርሎስ አፈጉባኤነት በተመራው ጉባኤ ኤፌሶን በ፪፻ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን
ተወግዞ ተለይቷል፡፡ ንስጥሮስ “ሕስወኬ ትሰመይ ቅድስት ድንግል ወላዲተ አምላክ ወአማነ ትሰመይ ወላዲተ ሰብእ” በማለት ክዶ ነበርና ሊቃውንቱ እርሱን አውግዘው “በአማን
ወላዲተ አምላክ፤ በእውነት አምላክን የወለደች” ናት በማለት ድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክ ብለው አንቀጸ ሃይማኖት ጽፈውልናል፡፡
ንስጥሮስ የሚምነውን እምነት ከቀጥተኛዋ የተዋሕዶ እምነት ጋር ማመሳሰል
ራስን ማታለል ነው፡፡ ቅባት ግን በንስጥሮስ ባሕል የሚገኝ እምነት እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ለዚህም ማስረጃ ማስቀመጥ እችላለሁ፡፡
ወልደ አብ ገጽ ፻፳፯ ላይ “እንደ ዘርአ ብእሲ የሆነው ወልድ ነው
ማለት እንዴት ነው ቢሉ፡፡ ከአባት ዘር ከእናት ደም ተከፍሎ ተዋሕዶ እንዲፈጠር ወልድም ከእግዝእትነ ማርያም በግብረ መንፈስ ቅዱስ
ከተከፈለ ደመ ድንግልና ጋራ ተዋሕዶ ተፈጥሯልና፡፡ እንደ ዘርአ ብእሲ የሆነ ወልድ ነው ማለት ስለዚህ ነው” ብለው ያምናሉ፡፡ ስለዚህ
መለኮት ከሥጋ ጋራ ተዋሕዶ ከተፈጠረ በኋላ ድንግል ማርያም ወለደችው ይላሉ፡፡ ይህ ማለት ድንግል ማርያም የወለደችው ፈጣሪን ሳይሆን
ከሥጋ ጋራ ተዋሕዶ የተፈጠረን ሰው እንደሆነ ያስተምራሉ፡፡ ይቅር ይበለንና እንደዚህ ያለውን ክህደት ሲጽፉ እና ሲያስተምሩ ግን
እንደ ንስጥሮስ በጉባኤ ስላልተለዩ ምናልባትም ትክክል ነን ከንስጥሮስ ክህደት እንለያለን ይሉን ይሆናል፡፡ ግን ማታለያ ካልሆነ
በቀር ንስጥሮሳውያን እንደሆኑ በዚህ እንረዳለን፡፡ “ወልድን ተፈጠረ” ብለው የሚያስተምሩ ቅባቶች ንስጥሮስ መባል ሲገባቸው “በተዋሕዶ
ከበረ” ብሎ ማመንን ንስጥሮሳዊ ነው ማለት ፍጹም ስህተት ነው፡፡
“ስለዚህ ስጋ ከቃል ከተዋሐደ በኋላ ክቡር ባዕል መባል ይገባዋል ዕንጅ፡፡
ክብረ ብዕለ መባል አይገባውም” ይላል ካሳሁን፡፡ ይህ ሁሉ ዳርዳርታ “በተዋሕዶ ከበረ” ስላልን “ከብረ” መባል አይገባውም “ክቡር”
እንጅ ለማለት ነው፡፡ በመጀመሪያ “በተዋሕዶ ከበረ” ማለት ምን ማለት እንደሆነ ካሳሁንን ጨምሮ ሙሉ የቅባት አማኞች አያውቁትም፡፡
ተዋሕዶን ስንመለከት ለሦስት ከፍለን ማየት እንደሚያስፈልግ ከዚህ በፊት ስለገለፅሁ ያንን ተመልከቱት፡፡ ለዛሬ ግን የምንጨምረው
“ከብረ” የሚለው ቃል ስህተት የሚሆነው “በተዋሕዶ ከበረ” ሲባል ብቻ ነው ወይ በሉልኝማ፡፡ “በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” ስትሉ
“ከብረ” ማለታችሁ አይደለም እንዴ? ለመንቀፍ ብቻ ያልሆነን ነገር መለጠፍ ጥሩ አይደለም፡፡ ከተዋሕዶ በኋላ ማንን ከማን ገንጥለን
ነው እንዲህ ሆነ እንዲህ ሆነ የምንለው? “ከበረ” የሚለው እኮ ሰው አምላክ መሆኑን ለመግለጽ ብቻ የምንጠቀምበት ቃል ነው፡፡ ለሰው
አምላክ ከመሆን የበለጠ ምን ክብር አለውምና ነው ታዲያ፡፡
“በተዋሕዶ ከበረ ማለት እንዴት ነው ቢሉ፡፡ ሁለት አካል ማድረግ ነውና
ከንስጥሮስ ባህል ይገባል ማለት እንዴትና፡፡ ተዋሕዶ አንድነትን ይፀናል እንጅ፡፡ ሁለትነትን ያመጣልን እንጅ ቢሉ፡፡ በተዋሕዶ ከበረ
ወልድ ቅብዕ ማለት ስም ሰጥቶ ግብር መንሳት ነው” ብሎ ምንም ፍሬ የለሽ ጽሑፍ ጽፏል፡፡ መጀመሪያ ይህ ሰው በተዋሕዶ ከበረ ማለት
ምን ማለት እንደሆነ አላወቀውም እኮ፡፡ “በተዋሕዶ ከበረ ማለት እንዴት ነው ቢሉ” ብሎ “በተዋሕዶ ከበረ ማለትን ሊተረጉም ነው
ብለን ስንጠብቀው “ሁለት አካል ማድረግ ነውና ከንስጥሮስ ባህል ይገባል ማለት እንዴትና” ብሎ ይሸውዳል፡፡ “ተዋሕዶ አንድነትን
ይፀናል እንጅ፡፡ ሁለትነትን ያመጣልን እንጅ ቢሉ፡፡ በተዋሕዶ ከበረ ወልድ ቅብዕ ማለት ስም ሰጥቶ ግብር መንሳት ነው” ይላል፡፡
ስለ ተዋሕዶ ለመናገር ተዋሕዶን መማር ማወቅ ይገባል፡፡ ተዋሕዶ ምን እንደሆነ ሳያውቁ ግን እንዲህ ነው ይህን ይመስለኛል ወዘተ
ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ “በተዋሕዶ ከበረ” ብሎ ማመን አንድነትን ያፀናል እንጅ ሁለትነትን አያመጣም፡፡ ተዋሕዶ አንድነትን ያመለክታል
እንጅ ሁለትነትን አያመለክትም፡፡ ይልቅስ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ ማለት ንስጥሮሳዊነት ነው፡፡
ሳዖል ተቀብቶ በእስራኤላውያን ላይ ንጉሥ ሆነ ዳዊትም ተቀብቶ ነገሠ
ሰሎሞንም እንዲሁ ተቀብቶ ነገሠ፡፡ ይህ ለመንገሥ የሚደረግ መቀባት ነው፡፡ ንግሥናቸው ግን የጸጋ እንጅ የባሕርይ አልነበረም፡፡
ክርስቶስንም ተቀብቶ አምላክ ሆነ ብሎ መናገር የጸጋ አምላክ ማድረግ ነው፡፡ በባህርዩ ይቀባል ይከብራል እንዳይባል አምላክ ነው
ማን ይቀባዋል ማንስ ያከብረዋል፡፡ ክርስቶስ አምላክ የሆነው በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ነው ብሎ ማመን ክርስቶስን የጸጋ አምላክ ብሎ
ማመን ነውና ንስጥሮሳዊነት ማለት ይህ ነው፡፡
#ይቀጥላል
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ኅዳር ፲፫
/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
No comments:
Post a Comment