፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
·
የምሥራቅ ጎጃም ሐገረ ስብከትን ሃይማኖታዊ እና
አስተዳደራዊ ችግሮች እንዲያጣራ ከጠቅላይ ቤተክህነት የተመደበው ልዑክ ደብረ ማርቆስ ገብቷል፡፡ ይህንንም ተከትሎ በርካታ ምእመናን
ወደ ቦታው በመምጣት ላይ ናቸው፡፡
ዛሬ ገጽ ፯ ላይ ያሉትን ስህተቶች
በማስረጃ አስደግፈን እንመለከታለን፡፡ በፎቶ ከስር አብሬ ስለማያይዝላችሁ ሙሉውን ማንበብ ትችላላችሁ እኔ ግን በቤተክርስቲያናችን
ትምህርት ልዩነት ያለውን ብቻ በማስረጃ እያስደገፍሁ እጽፍላችኋለሁ፡፡
ካሳሁን ምናሉ በገጽ ፯ ላይ እንዲህ ይላል፡፡ “መንፈስ ቅዱስ ምን ምን አድርጓአል ቢሉ ማንጻት
መክፈል ማዋሐድ መፍጠር ቅብዕ መሆን ነው” ይላል፡፡ እዚህ ላይ በዋናነት ማንሣት የምሻው “ቅብዕ” የሚለውን ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ
በማኅጸነ ማርያም ቅብዕ ሆኗልን? የሚለውን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት
“ቅብዕ” የሚለውን ቃል ትርጓሜ መመልከቱ የተሻለ ነው፡፡ ለዘሬ የምንመለከተው በመጠኑ ይሆናል፡፡ ራሱን የቻለ ርእስ
ስላለው እዚያ ላይ በሰፊው የምናትተው ይሆናል፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ገጽ ፺፬ ላይ ያለውን ቅብዓት (ቅባት) ከልዩ ልዩ እንጨቶች ተቀምሞና ተነጥሮ የሚወጣ ፈሳሽ ዓይነት ዘጸ ፴÷፳፪-፴፪፡፡
የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነው፡፡ ፩ኛ ዮሐ፪÷፳፡፳፯፡፡ ከዚያም ሲጨርስ “ቀባ” ን ተመልከት ይላል ስለዚህ የ “ቀባ”ንም ትርጉም መመልከት
ይኖርብናል ማለት ነው፡፡ “ቀባ” መቀባት በመጽሐፍ ቅዱስ ለ፫ ዓይነት ነገር ያገለግላል፡፡ ፩ኛ. ለአገልግሎት፡- ሰዎችና ዕቃዎች ለእግዚአብሔር ሥራ ሲለዩ ይቀቡ ነበር፡፡ በብሉይ
ኪዳን ዘመን የመገናኛው ድንኳንና ዕቃው ተቀብቷል፡፡ ዘጸ ፴÷ ፳፪-፳፱፤ ዘጸ ፴÷፴፤ ፩ኛ ሳሙ ፱÷፲፮፤ ፩ኛ ሳሙ ፲÷፩ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቷል (በመንፈስ ቅዱስ ተሞላ ሐዋ ፲÷፴፰)፤
፪ኛ ቆሮ፩÷፳፩-፳፪፤ ፩ኛ ዮሐ፪÷፳፡፳፯ ላይም ተገልጿል፡፡ ፪ኛ.
ለአክብሮት፡- ተጋባዦች ለአክብሮት ይቀቡ ነበር፡፡ ሉቃ ፯÷፵፮ ፤ማር ፲፬÷፰፤ ማር ፲፮÷፩ ፫ኛ. ለሕክምና፡- ቁስለኞችና ሌላም በሽታ ያለባቸው በዘይት ይቀቡ ነበር፡፡ ማር ፮÷፲፫፤
ሉቃ ፲÷፴፬፤ ያዕ ፭÷፲፬ በማለት ይገልጻል፡፡ ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሽፈራው
መጽሐፈ ግስ ወሰዋስው መርኆ መጻሕፍት በተሰኘ መጽሐፋቸው ገጽ ፻፺፱ ላይ ቀብዐ
ቀባ
ካሉ በኋላ ማስረጃ ይሰጣሉ፡፡ በዘተሰብአ ተቀብዐ ፤
ተዋሐደ ተቀብዐ ተዋሐደ ተብሎ ተተርጉሟል፡፡ ከመዝ ይትቀብዑ እምቅዱስ
ቅብዕ በኀበ ምቅባዕ እን ቆስጠ ፴፱ ወፈነወ ኢየሱስሀ ወአቅደመ ቀቢዖቶ አዘጋጀ ብለው ቀብዐ ያለውን ግስ አዘጋጀ ብለው
ይተረጉሙታል፡፡ በዚህ ግስ እርባታ ላይ ቀብዐ የሚለው ግስ ቀባ ከሚለው የአማርኛ ትርጉም በተጨማሪ አዘጋጀ አዋሐደ ተብሎ
እንደሚተረጎም ማስረጃዎችን አስቀምጠዋል፡፡ ሌላው አለቃ ኪዳነ ወልድ
ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በተሰኘው መጽሐፋቸው ገጽ ፯፻፸፱ እና ገጽ ፯፻፹ ላይ በዝርዝር
ያስቀመጡትን እንመልከት፡፡ ቀቢዕ፤ ዖት፤ (ቀብዐ፡ ይቀብዕ፡
ይቅባዕ፡፡ ዕብ፡ ቃባዕ፡ ሐገገ፡ ዐደመ ፡ መልአ ፡ ሤመ) ብለው፤ ሲተረጉሙ መቅባት፣ መቀባት፣ መላላክ፣ መለቅለቅ፣ ለመሾም፣
ለማክበር፣ ለማሳመር ለመፈወስ ይላሉ፡፡
ወደ ቅብአት እምነት አስተምህሮ
ስንመለ “ወልድ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” የሚል መሠረተ እምነት ነው የምናገኘው፡፡ ይህ ደግሞ በተዋሕዶ ትምህርት መሠረት
ፍጹም ክህደት ነው፡፡ ካሳሁን ምናሉ “መንፈስ ቅዱስ ምን ምን አድርጓአል ቢሉ ማንጻት
መክፈል ማዋሐድ መፍጠር ቅብዕ መሆን ነው” በማለት እውነቱን ከሀሰት እምነቱን ከክህደት ማሩን ከመራራው ጋር ቀላቅሎ ያስቀመጠው
“ወልድ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” ለማለት እንደመግቢያት ቢያገለግለኝ
ብሎ እንጅ በምንም መጽሐፍ ተጽፎ አይገኝም፡፡ “ቅባት” ለሚለው ቃል እንደአገባቡ የተለያየ ትርጉም ቢኖረውም ቅባቶች የሚሹ “ቀባ”
አከበረ “ተቀብዐ” ከበረ የሚለውን ስለሆነ “ቅብዕ” ክብር የሚል ትርጉም ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ በዚህም መሠረት “ቅብዕ” ቀጥተኛ
ትርጉሙ ክብር ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ ፍጥጥ ያለ ጥያቄ አነሣለሁ የቅብዓት ምሥጢር ገብቶኛል ያለ ሊቅ ሊያስረዳኝ ይችላል፡፡
መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ሆነ
ስትሉ ወልድ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ እንደ አብ እንደ መንፈስ ቅዱስ ገዥ አዛዥ ፈጣሪ ሆነ ማለታችሁ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስን
ባይቀበል ኖሮ እንደ አብ እንደ መንፈስ ቅዱስ አይገዛም አያዝዝም ነበር ይላል ወልደ አብ መጽሐፋችሁ ላይ፡፡ እዚህ ላይ የምጠይቃችሁ
የሚከተሉትን ጥያቄዎች ነው፡፡
፩ኛ. መንፈስ ቅዱስ ለወልድ
ክብር የሆነው በአካል ነውን? አዎ ካላችሁ መንፈስ ቅዱስን በአካሉ ክብር ያደረገው ወልድ ሥጋን ተዋሐደ ስትሉ መንፈስ ቅዱስም ሥጋን
ተዋሕዷል ያሰኝባችኋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአካላት ተዋሕዶ ተፈጽሟልና ከአካላት ሦስትነት ወደ ሁለትነት ይቀንስባችኋልና አይስማማም፡፡
በአካል ክብር አልሆነውም ካላችሁ ታዲያ በምን ክብር ሆነው?
፪ኛ. መንፈስ ቅዱስ ለወልድ
ክብር የሆነው በመለኮቱ ነውን? አዎ ካላችሁ የመንፈስ ቅዱስ መለኮት ከወልድ መለኮት ይበልጣል ያሰኝባችኋል፡፡ አይደለም በመለኮት
ክብር አልሆነውም ካላችሁ በምን ክብር ሆነው ትላላችሁ?
፫ኛ. መንፈስ ቅዱስ ክብር
የሆነው ወልድ ለተዋሐደው ሥጋ ነውን? አዎ ካላችሁ ወልድ በአምላክነት ሥልጣኑ ሥጋን ማክበር (አምላክ ማድረግ) አይችልም ወይ? አሁንም አዎ ካላችሁ ትምህርተ
መለኮት ተፋለሰባችሁ፡፡ ማክበር ይቻለዋ ካላችሁ ደግሞ “በመንፈስ ቅዱስ ቅብዓትነት ከበረ” የሚለው ትምህርታችሁ ፉርሽ ሆነ፡፡
በርግጥ ከላይ ለጠየቅሁት ጥያቄ ሊመልስልኝ የሚችል የቅብአት እምነት
ተከታይ ሰው አይኖርም፡፡ እነርሱ በብዛት በመሳደብ እና በማሸማቀቅ ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ ነው የሚጣጣሩት፡፡ ምንም በሉ ምን ቅብአት
ምንፍቅና እንደሆነ በሚገባ ለምእመናን እውቅና መፍጠር ችለናል፡፡ እዚህ ላይ ስንከራከር የሚታዘበንም ሰው የትኛው ነው ትክክል የሚለውን
ጥያቄ እየመለሰ ይገኛል፡፡ በዚያውም ላይ “ቅብዓት” የሚባል ነገር በሀገረ ስብከቴ ውስጥ የለም ያሉትን የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት
ሊቀ ጳጳስ ትዝብት ውስጥ ይጥላቸዋል፡፡
መንፈስ ቅዱስ “ቅብዕ” ሆነ ካላችሁ እስኪ እነዚህን ጥቅሶች አብራሩልን፡፡
ስምዐት ፻፳፬ ቁጥር ፴፬ ላይ “ወካዕበ ይቤ እስመ ክርስቶስ ኢተቀብዐ በእንተ መፍቅድ ዘቦቱ አላ ለሊሁ ቀባዒ ውእቱ…፤ ዳግመኛ ክርስቶስስ ክብር መሻት
ኖሮበት አልከበረም እርሱ ራሱ አክባሪ ነው እንጅ…”
ይላል ሃይማኖተ አበው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሃይማኖተ አበው ስምዓት ምእራፍ ፻፳፬ ክፍል ፪ ቁጥር ፲፬ ላይ “ወከመዝ ነአምሮ ለሊሁ ተቀብዐ ከመ ሥርዓተ ትስብእት ወዳእሙ ውእቱ ዘይቀብዕ ርእሶ በመንፈሱ ባሕቲቱ፤ በተዋሕዶ እንደከበረ እናውቃለን
ግን በገዛ ሥልጣኑ ራሱን የሚያከብር እሱ ነው”፡፡ ምን ይኼ
ብቻ “በመንፈስ ቅዱስ ከበረ የሚለው ቢኖር የተወገዘ ይሁን” የሚል ቀጥታ የተጻፈ ቃል አሳያችኋለሁ ርእሱ ላይ ስንደርስ፡፡
ይቀጥላል፡፡
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ኅዳር ፬
/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
No comments:
Post a Comment