Tuesday, November 28, 2017

“በቅባት ካህን የተጠመቀ ልጅነት የለውም” ብጹእ አቡነ ዘካርያስ




                       ፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠

ይህን ሸር ያላደረገ ሰው #የማርያም_ጠላት ታዲያ ምን ሸር ልታደርጉ ነው!
የምሥራች ነው ደግሞ እኮ!
****************
ብጹእነታቸው አቡነ ዘካርያስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን ምሥራቅ፣ ደቡብ ምሥራቅና መካከለኛው አሜሪካ ኒዮርክ ሊቀ ጳጳስ በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ስላለው ሃይማኖታዊ እና አስተዳደራዊ በደል ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ብጹእ አቡነ ዘካርያስ ከአቡነ ማርቆስ በፊት ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት ብጹእ አቡነ ጴጥሮስ በፊት የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ነበሩ፡፡ ብጹእነታቸው አቡነ ዘካርያስ ምሥራቅ ጎጃምን እያስተዳደሩ በነበሩበት ጊዜ ቅባቶች ላይ ቆራጥ አቋም የነበራቸው እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን በዚያን ወቅት ቅባቶች በጾም ጊዜያት ላይ ብቻ ክርክር ያነሡ ስለነበር ልዩነታቸው እንደ አሁኑ ጎልቶ አለመታየቱ ብጹእነታቸው በሰፊው አልሄዱበትም ነበር፡፡ እንዲያውም በተፈጠረው ወቅታዊ ችግር ቅባት እና ተዋሕዶ በአንድነት ሲቀድሱ ሁሉ ዝም ይሉ እንደነበር እና በዚህም የተነሣ ከዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም ጋር እና ከምእመናን ጋር ቅሬታ ውስጥ ገብተው እንደነበር ለሁሉም የታወቀ ነው፡፡ ምክንያቱ ባልተገለጠ መንገድ ከሀገረ ስብከቱ ገንዘብ ሲጠፋባቸው ሀገረ ስብከቱን ለቀው እንደሄዱም ይታወቃል፡፡ ብጹእነታቸው ግን የገንዘቡን መጥፋት አምነው ጠፍቶብኛል ያሉትን ገንዘብም ከልጆቻቸው አሰባስበው ለሀገረ ስብከቱ እንደሚመልሱ በወቅቱ ለአሜሪካን ድምጽ አሳውቀው ነበር፡፡ በቃላቸውም መሠረት አምና ፳፻፱ ዓ.ም አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር ለሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ለብጹእ አቡነ ማርቆስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በተገኙበት አስረክበዋል፡፡ ሆኖም ግን ይህ ገንዘብ ለሀገረ ስብከቱ መግባት አለመግባቱን የሚያውቅ ምእመን የለም፡፡ ገንዘቡ ምን ሥራ ላይ እንደዋለም ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የተባለ ነገር የለም፡፡




ብጹእነታቸው አቡነ ዘካርያስ በዚህ መልኩ በምእመናን ቅሬታ ቀርቦባቸው በዚያ ላይ ገንዘብም ጠፍቶባቸው ተደራራቢ ችግር ውስጥ ሳሉ ነበር ሀገረ ስብከቱን ለቀው የወጡ፡፡ እርሳቸው ሀገረ ስብከቱን ከለቀቁ ወዲህ ምሥራቅ ጎጃምን የተረከቡት ብጹእ አቡነ ጴጥሮስ ነበሩ፡፡ አቡነ ጴጥሮስም የአቡነ በርናባስን እረፍት ተከትሎ ወደ ባሕር ዳር ተዛውረው አቡነ ማርቆስ ምሥራቅ ጎጃምን ተረከቡ ማለት ነው፡፡ ከብዙ ዓመታት በኋላ ብጹእነታቸው አቡነ ዘካርያስ አምና ፳፻፱ ዓ.ም የጠፋባቸውን ገንዘብ መልሰው ቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ተገኝተዋል፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ በምእመናን ቅሬታ የቀረበባቸው አቡነ ማርቆስ ምሥራቅ ጎጃምን እንዲለቁ ከፍተኛ ተሳትፎ ያደረጉት አቡነ ዘካርያስ ናቸው፡፡ አቡነ ማትያስ የአቡነ ማርቆስ ጉዳይ እንዳይነሣ ቢከለክሉም አቡነ ዘካርያስ ግን የ“ወልደ አብ” ጉዳይ በተነሣበት አጀንዳ ላይ በከፍተኛ ደረጃ ተከራክረዋል፡፡ ብጹእነታቸው እስከመሰደብ ድረስም እንደደረሱ በስብሰባው የነበሩ አባቶች ተናግረዋል፡፡ ብጹእ አቡነ ማርቆስ አቡነ ዘካርያስን “አንተ ሌባ እኔ እንዳንተ ገንዘብ የምዘርፍ መሰለህ” ያሏቸው ሲሆን ብጹእነታቸው አቡነ ዘካርያስም በትእግስት “እኔስ ገንዘብ ቢጠፋብኝም መልሻለሁ ደግሞስ ይህ የቀኖና እንጅ የሃይማኖት ችግር መሰለዎ እንዴ፡፡ እርስዎ ግን የሃይማኖት ችግር ነው ያለብዎ” ብለው የመለሱላቸው ሲሆን በዋናነት በመድረኩ ላይ ከፍተኛ ተሳታፊ የነበሩ እንደነበሩ አባቶች ይናገራሉ፡፡ እንዲያውም አቡነ ማርቆስን ደፍሮ የሚናገራቸው በጠፋበት ሰዓት እርሳቸው ያለምንም ፍርሐት ስለተዋሕዶ ሃይማኖታችን ሲሉ በዚያ መልኩ በመናገራቸው ከስብሰባው ሲወጡ እጃቸውን እየሳሙ “አባታችን ረዥም ዕድሜን ያድልዎ” እያሉ ብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት እንደመረቋቸው ነው አባቶች የተናገሩት፡፡
ብጹእነታቸው አቡነ ዘካርያስ “ወልደ አብ” እንዲወዘግ ከፍተኛ ትግል ያደረጉ አባት ናቸው፡፡ “ወልደ አብ” የተወገዘውም እርሳቸው ለጠቅላይ ቤተክህነት እና ለሊቃውንት ጉባዔ መጽሐፉን አያይዘው በጻፉት ደብዳቤ እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ለአቡነ ማርቆስም በተደጋጋሚ ደብዳቤ በመጻፍ ይህ የቅባት ክህደት ሥር እንዳይሰድ ምክር ሲለግሱ ነበር ሆኖም ግን ሰሚ አላገኙም፡፡ በዘንድሮው የጥቅምት ሲኖዶስ በርካታ ጥያቄዎቻችን የተፈቱ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በተለይ በምሥራቅ ጎጃም አካባቢ ስላለው የቅባት እምነት እና እርሱን ተከትሎ ስላለው የጥምቀት ሁኔታ ውሳኔ ተላልፎበታል፡፡ በዚህ በጥምቀቱ ጉዳይ ብዙ ምእመናን ሲከራከሩበት የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም ግን “ወልደ አብ” የተባለው የክህደት መጽሐፍ የቅባትን መሰረተ እምነት በግልጽ ሳለወጣ ኑፋቄያቸው በሚገባ ታውቋል፡፡ ስለሆነም በቅባት ካህናት የተጠመቁ ምእመናን ሁሉ መጠመቅ አለባቸው የሚል ውሳኔ ተላልፏል፡፡ ብዙዎችን ያከራክር የነበረውም የጥምቀቱ አስፈላጊነት ሳይሆን የልጅነት ጥምቀት ወይስ የቄድር ጥምቀት የሚለው ነበር፡፡ ነገር ግን ቄድር የሚያስፈልገው በተዋሕዶ እምነት አምኖ ተጠምቆ ከዚያ በኋላ ክዶ ቆይቶ ዳግም ወደ እምነቱ ሲመለስ እንጅ ከመጀመሪያውኑ በከሃድያን በመናፍቃን የተጠመቁ ግን ልጅነት ስለሌላቸው የልጅነት ጥምቀት ያስፈልጋቸዋል ተብሎ ተወስኗል፡፡ ለዚህ ውሳኔ መተላለፍ ምክንያት የነበረው የአቡነ ማርቆስ ንግግር ነበር፡፡ እርሳቸው በሲኖዶሱ ስብሰባ ላይ “ጎጃምን ተጠመቁ የሚሉ መናፍቃን አሉ” ብለው ሀሳብ በማንሳታቸው ሊቃውንቱ እነ አቡነ እንድርያስ እነ አቡነ ቀውስጦስ አነ አቡነ ዘካርያስ በሰፊው ተከራክረውበታል፡፡ ጎጃም ተጠመቅ አልተባለም ቅባት ግን ተጠመቅ ተብሏል፡፡ ጎጃም ማለት ቅባት ማለት አይደለም ቅባት ማለት ግን በጎጃም የሚገኝ ኑፋቄ ነው፡፡ የጎጃም መገለጫ ደግሞ ቅባትነት አይደለም ሊቅነት እንጅ፡፡ ብዙ ሊቃውንት የፈለቁበት ሀገር ነው ጎጃም፡፡ ዝም ብለን ሳይሆን ጠቅሰን የምንናገራቸው እነ አቡነ ቴዎፍሎስ የደብረ ኤልያስ ልጅ ናቸው (በትውልድ ማለቴ ነው እንጅ የዓለም አባት ነበሩ ለቤተክርስቲያናችን ሁለተኛው ፓትርያርክ ነበሩ)፣ እነ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ (ትውልዳቸው እነማይ ወረዳ ዲማ ነው፡፡ ኮኩሐ ሃይማኖት እና መድሎተ አሚንን ጽፈው እስካሁን ድረስ መናፍቃንን የሚረቱ ብርቅየ አባት ናቸው፡፡) እነ አለቃ አያሌው ታምሩ (ትውልዳቸው እነማይ ነው) በርካታዎችን መጥቀስ እንችላለን፡፡ ታዲያ በእነአቡነ ቴዎፍሎስ፣ በእነ መልአከ ብርሃን አድማሱ በእነ አለቃ አያሌው አገር ጎጃም መናፍቅ ሊቀልድበት ይገባልን? በፍጹም!
ይህን የሲኖዶሱን ውሳኔ አሁንም ድረስ ያልተቀበሉት አቡነ ማርቆስ አጣሪ ኮሚቴው ላይ ደግነታቸውን እንዲመሠክሩላቸው በአበል የሰበሰቧቸውን የሀገረ ስብከቱን ካህናት ሰብስበው ዲማ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ እና ማኅበረ ቅዱሳንም እንዳይንቀሳቀስ የአቋም መግለጫ ቢጤ አውጥተዋል፡፡ ሆኖም ግን ብጹእነታቸው አቡነ ዘካርያስ ኅዳር ፬/ ፳፻፲ ዓ.ም ለሚመሩት ሀገረ ስብከት ለምእመናን እና ለካህናት የቅዱስ ሲኖዶሱን ሃሳብ በደብዳቤ ገልጠውላቸዋል፡፡ ደብዳቤው እንዲህ ይላል!
                     *****************************************
                                                ቁጥር፡-1603/2010
                                                ቀን፡- 04/03/2010
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን ምሥራቅ፣ ደቡብ ምሥራቅና መካከለኛው አሜሪካ የኒዮርክ ሀገረ ስብከት ውስጥ የምትገኙ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን መምህራን ሰባኪያነ ወንጌል ካህናትና ዲያቆናት ምእመናን ወምእመናት ወወራዙት (ወጣቶች) ወመሐዛት (ታዳጊዎች) በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ፡፡ የቅድስት ድንግል እመቤታችን ረድኤት አይለያችሁ አሜን፡፡
እጽሕፍ ለክሙ ደቂቅየ ልጆቼ ሆይ እጽፍላችኋለሁ ይኸውም “ሚሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊ” የሚል በግዕዛዊ አነጋገሩ በሃይማኖታዊ ምሥጢሩ እጅግ በጣም ስህተት ኑፋቄ ክህደት የሞላበት ስለሆነ ከወልደ አብ መጽሐፍ ጋር ተመሳሳይ ስለሆነ ይኸውም የተወገዘ እና የተከለከለ ስለሆነ እንዳትቀበሉት እያሳሰብኩ ብታገኙትም በሽፋኑ እና በውስጡም ያሉ ስዕሎችን እያነሣችሁ በእሳት ማቃጠል ትችላላችሁ፡፡ የተዋሕዶ ሃይማኖታችን ጠላት ነውና የቅባቶች የፀጎች የካቶሊኮች መጽሐፍ ነውና ከዚህም ሌላ ስለጥምቀት ከሊቃውንቱ አንዳንዶቻችሁ ጥያቄ አቅርባችኋል፡፡ ጥምቀት የተዋሕዶ ሃይማኖት አንዲት ናት፡፡ እርሷም አትለወጥም አትከለስም አትታደስም ዘላለማዊት አንዲት ጥምቀት ናት፡፡ በተዋሕዶ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት የተጠመቁ ክርስቲያኖች ሌላ ጥምቀት የላቸውም፡፡ ዘላለማዊት አሐቲ ጥምቀት ናትና ነገር ግን ክርስቶስ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ ወልድ ተፈጠረ መለኮት ተፈጠረ የሚሉ ቅባቶች ፀጎች ያጠመቋቸው ሰዎች ጥምቀት አይባልም፡፡ ፀጎች ቅባቶች ምንም እንኳ ከተዋሕዶ አባች ጳጰሳት ክህነቱን ቢቀበሉትም ራሳቸው ወልድ ፍጡር የሚሉ አርዮሳውያን ስለሆኑ ክህነታቸው ልጅነት አያሰጥም፡፡ ለምሳሌ ወልደ አብ የተባለውን መጽሐፍ የጻፈው የቆጋው መነኮስ ገብረ መድኅን የዲቁናውን የቅስናውን ክህነት የተቀበለው ከብጹእ አቡነ ማርቆስ ቀዳማዊ ሊቀ ጳጳስ ዘጎጃም ነው፡፡ እርሱም የተዋሕዶ ልጅ ነኝ ብሎ ምሎ ተገዝቶ ነበር የተቀበለው አሁን ግን በመጽሐፉ እንደገለጸው ክርስቶስ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ ወልድ ተፈጠረ መለኮት ተፈጠረ ብሎ የሚያምን ስለሆነ በርሱና ርሱን በመሰሉ ካህናት ነን በሚሉ የተጠመቁ ሁሉ ሃይማኖትም ልጅነትም ስለሌላቸው በተዋሕዶ ሃይማኖት ጥምቀት መጠመቁ ግድ ነው፡፡ የሚጠመቁትም በሊቀ ጳጳስ በኤጲስ ቆጶስ በካህን ነው፡፡
ለዘተወልደ እምጻውቲኒ ዳግመ ያጥምቅዎ የተባለውም ስለዚህ ስለሆነ ትርጉሙም በሳምሳጢ ጳውሎስ በአርዮስ ወገኖች የተጠመቀ ቢኖር ርትዕት በሆነችው ተዋሕዶ ሃይማኖት ይጠመቅ “ዲድስቅልያ” ባቀረባችሁት ጥያቄ መሠረት መልሴ ይህ ነው፡፡
                                  እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን
                       የቅድስት ድንግል ቡርክት ማርያም ረድኤት አይለየን አሜን፡፡
                                      አባ ዘካርያስ
                  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን ምሥራቅ፣     ደቡብ ምሥራቅና መካከለኛው አሜሪካ የኒዮርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ፊርማ
ግልባጭ//
     - ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት
     - ለብጹእ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት
     - ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት
                         **************************************
ብጹእነታቸው አቡነ ዘካርያስ ከሊቃውንቱ ከምእመናኑም የቀረበላቸውን ጥያቄ በሚገባ ከላይ በተጻፈው መልኩ መልስ ሰጥተዋል፡፡ ይህ መልስ በዘንድሮው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ በሰፊው የተነጋገሩበት ጉዳይ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ቅባቶች ይጠመቁ የሚባለው ተዋሕዶን አምነው በተዋሕዶ ትምህርት መሠረት መኖር ከፈለጉ ብቻ ነው፡፡ በጅምላ ተጠመቁ የተባለበት የሚባልበትም አጋጣሚ አይኖርም ሊኖርም አይገባውም፡፡ ሰው ያመነውን ይከተላል ያመነውን ያስፈጽማል፡፡ ቅባቶችም የራሳቸውን ውሳኔ ማሳወቅ አለባቸው፡፡ በቤተክርስቲያናችን ስር ተወሽቀው ግን ምንፍቅናቸውን እንዲዘሩ አንፈቅድም፡፡ ይህንን ደብዳቤ አይተው “ዳግም ጥምቀት የሚፈቅዱ ሊቀ ጳጳስ” እያሉ የሚተቹ ቅባቶች አይጠፉም ነገር ግን ክህነት የሚሰጡት አባት ክህነት የላቸውም ብለውናል፡፡ ታዲያ ክህነት በሌለው ሰው ተጠምቀህ እንዴት አንድ ብለህ ትቆጥራለህ? ይህ መልእክት ለመዳን ለሚፈልግ ነፍስ የሚያረካ ነው መዳን ለማይፈልግ ነፍስ ግን ወዮለት ወዮታ አለበት፡፡
አቡነ ዘካርያስ ከዚህ በፊትም የ “ወልደ አብን” በምሥራቅ ጎጃም መታተም አስመልክተው ለሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ደብዳቤ መጻፋቸው ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን ምንም ምላሽ አላገኙም ነበር፡፡ ወልደ አብንም ከሊቃውንት ጉባዔ እና ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በፊት አውግዘው ደብዳቤውን አሰራጭተዋል፡፡ አሁንም “ሚሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊ” የሚለውን መጽሐፍ በግንቦቱ ሲኖዶስ ለማስወገዝ እየሠሩ ናቸው፡፡ ብጹእነታቸው አቡነ ዘካርያስ፣ አቡነ ማርቆስ ሀገረ ስበከቴ ላይ በሕገ ወጥ መንገድ መጥተው ያሰባሰቡትን ሃያ ሰባት ሺህ ሦስት መቶ ሃያ ዶላር ለሀገረ ስብከቴ እንዲመልሱ ሲሉም ለጠቅላይ ቤተክህነት ጽፈዋል፡፡
ጎጃም ተጠመቅ ተባልህ እያሉ አቡነ ማርቆስ ቅባቶች እንዳይጠመቁ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከጠቅላይ ቤተክህነት አንድ እልባት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በቅባት ካህናት የተጠመቁ ሰዎች አማኒ ለመሆን ማለትም የተዋሕዶ ልጆች ለመሆን በተዋሕዶ ካህናት መጠመቅ አለባቸው ይህ ምንም የሚያሻማ ነገር የለውም፡፡ ነገር ግን እንዴት መፈጸም እንዳለበት ዝርዝር ነገር ከጠቅላይ ቤተክህትም መተላለፍ እንዳለበት መጠቆም እንፈልጋለን፡፡ ዲማ በአቡነ ማርቆስ እና በቅባቶች መንጋጋ ውስጥ እንዲገባ ያደረገው ይህንን የአባቶቻችንን ውሳኔ ተግባራዊ በማድረጉ ብቻ ነው፡፡ ዲማ እንዳትሄዱ ዲማ የሄደን ሰው አወግዛለሁ እስኪባል ድረስ ልዩ ትኩረት ያሳረፉበት ለዚሁ ነው፡፡
                         ****************
ከዚህ ጽሑፍ ጋር የተያያዘውን ማስረጃ ተመልከቱት!
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ኅዳር ፲፱ / ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment