Thursday, November 9, 2017

መሠረተ ሐይማኖት ወይስ መሠረተ ክህደት? ክፍል ፪





፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ዛሬ ከመጀመሪያው ገጽ ከምእራፍ አንድ ጀምረን እንመለከታለን፡፡ በፎቶ ከስር አብሬ ስለማያይዝላችሁ ሙሉውን ማንበብ ትችላላችሁ እኔ ግን በቤተክርስቲያናችን ትምህርት ልዩነት ያለውን ብቻ በማስረጃ እያስደገፍሁ እጽፍላችኋለሁ፡፡


ምእራፍ አንድ ምሥጢረ ሥጋዌን መማር ይገባል ብሎ በሚጀምረው ገጽ አንድ ላይ ካሳሁን ምናሉ እግዚአብሔር አምላክ ለአዳም ስለሰጠው ተስፋ እንዲህ ይጽፋል፡፡ “በሶስት ዕለት ወበመንፈቅ ዕለት እመፅዐ ሐቤከ ወእትወለድ እምወለተ ወለትከ ወዕከውን ሕፃነ በዕንቲአከ በአሀንከ ውስተ መርህብከ ወትቤዘወከ በመስቀልየ ወበሞትየ” ይላል፡፡ ይህን ተስፋ እግዚአብሔር አምላክ ለአዳም አልሰጠውም፡፡ የፊደል ግድፈቱን እንተወውና ያልተባለን እንደተባለ አድርጎ በጨረፍታ የሰማውን ብቻ በመሰለኝ ነው የጻፈው፡፡ “በሶስት ዕለት ወበመንፈቅ ዕለት” ተብሎ ነገር ሰምተንም ዓይተንም አናውቅም፡፡ መጽሐፍም እንዲህ ብሎ አልጻፈም፡፡ አልሆንም ደግሞም አይሆንም እንጅ ቢሆን እንኳ “ሦስት” በግዕዝ  ሠሉስ ተብሎ “በሠሉስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት” ይል ነበር እንጅ “በሶስት ዕለት ወበመንፈቅ ዕለት” ሊል አይችልም፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የአዳምን ንስሐ ተቀብሎ የገባለት ቃል ኪዳን እንዲህ የሚል ነው “በኃሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ፤ አምስት ሽህ ከአምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ…” የሚል ነው፡፡ እግዚአብሔር ለአዳም የሰጠው ተስፋ የአምስት ሽህ አምስት መቶ ዘመን እንጅ የሦስት ሽህ አምስት መቶ ዘመን አይደለም፡፡ ቅዳሴ ማርያም እና ውዳሴ ማርያም አንድምታን እንዲሁም መጽሐፈ አክሲማሮስን፣ መጽሐፈ ቀሌምንጦስን ተመልከቱ፡፡
 
ካሳሁን ምናሉ የተባለው ሰው እግዚአብሔር ለአዳም የሰጠውን ተስፋ ሲተረጉም “ሶስት ዕለት ያለው ሶስት ሺህ ነው፡፡ መንፈቅ ዕለት ያለው ሶስት መቶ ነው” ይላል፡፡ በዚህም መሠረት አዳም ድህነት የተፈጸመለት ከጌታ ልደት በፊት እንደሆነ ነው የሚናገረው፡፡ ከአምስት ሽህ አምስት መቶ ዘመን ላይ ሦስት ሺህ ሦስት መቶ ዘመን ስንቀንስ ሁለት ሽህ ሁለት መቶ ዘመን ይተርፋል፡፡ በዚህ ስሌት መሠረት አዳም የዳነው ከጌታ ልደት ሁለት ሽህ ሁለት መቶ ዘመን  ቀድሞ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ፍጹም ክህደት ነው፡፡ አንድ ዕለት የተባለ ሽህ ዘመን ነው ከተባለ መንፈቅ የሚባለው ግማሽ ማለት በመሆኑ አምስት መቶ ዘመን ይባላል እንጅ ሦስት መቶ ሲባል ስምተንም ዓይተንም አናውቅም፡፡ ምናልባት በዚያ ሰፈር ሦስት እና አምስት ተቀያይረው እንዳይሆን እንጅ፡፡ በጣም የሚገርማችሁ በዚሁ ገጽ ይህንኑ በተመለከተ ዘመናትን ከዘመናት ደምሮ አምስት ሽህ አምስት መቶ ዘመን ይሆናሉ ብሎ ይደመድማል፡፡ ምኑን ምኑን ደምሮ እንደዚህ እንዳደረሰው አይታወቅም እስኪ እናንተም ደምሩለትማ፡፡ በዚህ ገጽ አንድ እውነት የተገኘው “በእግዚአብሔር ዘንድ አንድ ዕለት ማለት በእኛ አንድ ሽህ ዘመን ነው” የሚለው ብቻ ነው፡፡

ገጽ ሁለት ላይ ቅዱስ ኤፍሬም ያላለውን ነገር ብሏል ብሎ በድፍረት ጽፏል፡፡ “እስመ በፈቃዱ ወበሥምረተ አቡሁ ወመንፈስ ቅዱስ መጽአ ወአድኃነነ” ያለውን ሲተረጉም ምን አለው መሰላችሁ “በፈቃድ የአባትንም ማውደድ ነውና በመንፈስ ቅዱስም መጥቶ አዳነን” ብሎ ተርጉሞታል፡፡ የማክሰሰኞ ውዳሴ ማርያምን እባካችሁ አውጡና አንብቡት ምንድን ነው የሚለው? ቅባቶች “መንፈስ ቅዱስ ብቻ” የሚሉ ስለሆኑ ሁሉን ነገር ለመንፈስ ቅዱስ ሲሰጡ ነው የሚታየው፡፡ በፈቃድ አንድ ናቸው እያልን “በፈቃድ የአባትንም ማውደድ ነውና በመንፈስ ቅዱስም መጥቶ አዳነን” አይባልም ነውርም ክህደትም ነውና፡፡ ትክክለኛ ትርጓሜው “በእርሱ ፈቃድ በአባቱም ፈቃድ በመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ መጥቶ አዳነን” የሚል ነው፡፡ ወልደ እግዚአብሔር አዳምን ለማዳን ከድንግል ማርያም ሲወለድ ፈቃዳቸው የሁሉም እንጅ መንፈስ ቅዱስ ውረድ ተወለድ ብሎ ወልድን ስላስገደደው የመጣ አይደለም፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ተገፍቶ የመጣ ሳይሆን በፈቃዱ የመጣ አምላክ ነው አዳምን ነጻ ያወጣው፡፡
ይቆየን፡፡

፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ጥቅምት ፴ / ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment