Sunday, November 26, 2017

ጾመ ነቢያት መቸ ይገባል?



፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
“መሠረተ ሐይማኖት ወይስ መሠረተ ክህደት? የሚለው ተከታታይ ጽሑፍ ይቀጥላል፡፡ ለዛሬ ስለጾመ ነቢያት ትንሽ እንነጋር እስኪ፡፡ እዚህ ላይም በቅባች እና በተዋሕዶ ልጆች መካከል ልዩነት አለ፡፡ ቅባቶች እንብላ ተዋሕዶዎች እንጹም የሚል ክርክር አለ እርሱን በጥቂቱ እንመልከት፡፡

ጾመ ነቢያት የገና ጾም በመባልም ይጠራል፡፡ ነቢያት እግዚአብሔር ለአዳም የሰጠውን ተስፋ እየጠበቁ አምላክ ይወርዳል ይወለዳል ብለው የጾሙት ነው፡፡ ይህ ጾም በሦስቱ ዘመናት ማለትም በዘመነ ማቴዎስ፣ በዘመነ ማርቆስ እና በዘመነ ሉቃስ ኅዳር ፲፮ ይጀምርና ታህሳስ ፳፱ ይፈሰካል፤ በዘመነ ዮሐንስ ግን ኅዳር ፲፭ ቀን ጀምሮ ታህሳስ ፳፰ ቀን ይፈሰካል፡፡  በአራቱም ዓመታት ፵፫ ቀናትን ይጾማል፡፡ ነገር ግን ከአራት ዓመት አንድ ጊዜ ኅዳር ፲፭ የሚገባው ጾም ስለሚረሳ ሁልጊዜ ኅዳር ፲፭ ይጀምራል፡፡ በዚህ የተነሣ በሦስቱ ዘመናት ፵፬ ቀናት በዘመነ ዮሐንስ ደግሞ ፵፫ ቀናት ይጾማሉ፡፡ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ የጾሙ ቀናት በ ፩ ቀን ይቀንሳል፤ በሦስቱ ዘመናት ፵፬ ቀናትን የምንጾመው ለጾም ማድላት ተገቢ ስለሆነ ነው፡፡ ይህንንም ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭ ቁጥር ፭፻፹፬  ላይ “ዳግመኛም ቢቻላችሁ ከዚህ አብዝታችሁ ጹሙ በማለታቸው ይህን ሕግ እነሆ ወሰኑ በጾሙ ምክንያት ጠብ ክርክር ቢሆን መጾም ይገባል፡፡ ከመብላት በጣም ይሻላል” ብለው አዘዙን። በጾም ወቅት እንብላ እና እንጹም የሚል  ክርክር ከተፈጠረ መጾም ይሻላል ምክንያቱም ከመብላት በጣም ይሻላልና ብለው በአንድ አረፍተ ነገር አሠሩልን። ከዚህ ወዴት እንሸሻለን? እንብላበት እና እንጹምበት የሚሉ ሰዎች ቢከራከሩ እንጹምበት ያለው እንዲረታ እወቁ።

ስለዚህ ነቢያቱን አርአያ አብነት አድርገን እግዚአብሔር በተስፋ በበረከት ያኖረን ዘንድ፣ በጎውን የልቦናችንን መሻት ሁሉ ይፈጽምልን ዘንድ፣ እንደ ቅዱሳን አባቶቻችን በቃሉ እንኖር ዘንድ እንጾመዋለን እንጅ ርቀን አንቆምም፡፡ በዚህ ጊዜ ርቀን ከቆምን ልጅነትንም ህይወትንም እናጣለን፡፡ ይህም ጾም በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭ ቁጥር ፭፻፷፰ ላይ “ከእነርሱም የሚያንስ እንደ ረቡዕና እንደ ዓርብ የሚሆን አለ፡፡ ይኸውም ከልደት አስቀድሞ የሚጾም ጾም ነው፡፡ መጀመሪያው የኅዳር እኩሌታ ፋሲካው የገና በዓል ነው” በማለት መዝግቦት እናገኘዋለን፡፡ ሆኖም ግን አንዳንድ ወገኖች የጾሙን መግቢያ እና መውጫ ሲከራከሩበት እናያለን፡፡ ነገር ግን ይህ ቀኖና ቤተክርስቲያን እንጅ ዶግማ ባለመሆኑ የሚያከራክረን ጉዳይ ሊሆን አይገባውም፡፡ ፍቅረ እግዚአብሔርን በማሰብ ወደ ፍቅር ተመልሰን ለጾም በማድላትና ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን በማሰብ በፍቅር እንድናደርገው አባቶች ይመክሩናል፡፡ ስለዚህ በተሠራልን ሥርዓት እንመራ ዘንድ እመክራለሁ፡፡
በዚህ ጾም የሚነሣው መሠረታዊ ጉዳይ ነቢያቱ ዐርባ ቀናትን ብቻ ነው የጾሙት ይህ በትርፍነት የተጨመረው ዐራት ወይም ሦስት ቀን ከየት መጣ የሚል ነው፡፡ ለዚህ መልሱ አንደኛ ከላይ እንዳየነው ፍትሐ ነገሥቱ የዚህን ጾም መግቢያ ሲገልጽ የኅዳር እኩሌታ ስላለ ነው፡፡ የህዳር እኩሌታ ደግሞ ህዳር ፲፭ እንጅ ህዳር ፲፱ አይደለም፡፡ ሁለተኛ ስንክሳሩ ኅዳር ፲፭ “ወበዛቲ ዕለት ጥንተ ጾመ ስብከተ ጌና ዘውእቱ ልደቱ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት ዘሠርዕዎ ክርስቲያን ያዕቆባውያን ዘግብጽ፤ በዚችም ቀን የስብከተ ጌና ጾም መጀመሪያ ነው፡፡ ይህም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለተወለደበት በግብጽ የሚኖሩ ያዕቆባውያን የሠሩት ነው” በማለቱ የህዳር እኩሌታ የሚለው በግልጽ ኅዳር ፲፭ ነው እንላለን፡፡ ስንክሳሩ ኅዳር ፲፱ን “ወበዛቲ ዕለት ኮነ ጾመ ስብከተ ጌና ዘሮም ወአፍርንጊ ወሶርያ ወአርማንያ ዘእንበለ ግብጽ ወኢትዮጵያ ወኖባ፤ በዚችም ዕለት የሮም፣ የአፍርንጊ፣ የሶርያ፣ የአርማንያ ክርስቲያን ከግብጽ ከኢትዮጵያና ከኖባ በቀር የስብከተ ጌና ጾምን የሚጀምሩበት ነው” ይለዋል፡፡ ሦስተኛ ሐዋርያው ፊልጶስ ኅዳር ፲፮ በሰማእትነት ካሳረፉት በኋላ ሥጋውን ሊያቃጥሉ ሲነሡ መልአከ እግዚአብሔር ሥጋውን ሰወረባቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ደቀመዛሙርቱ ከዕለቱ ጀምረው ፫ ቀናትን እንደጾሙ  በኅዳር ፲፰ ሥጋውን ሰጣቸውና ቀበሩት፡፡ ስለዚህም ሦስቱ ጾም ጾመ ፊልጶስ ተብሎ ተጨመረ፡፡ አራተኛ በዓለ ልደት ረቡዕና ዓርብ ቢውል ይበላበታልና ለዚያ ማካካሻ ወይም ምትክ የምትሆን ጾም የገሐድ ጾም አንድ ቀን ከጾመ ፊልጶስ በፊት ተጨመረችና ኅዳር ፲፭ ቀን እንዲጾም አዘዙን፡፡ ጌታ የጾመው ጾም ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ሆኖ ሳለ ፶፭ ቀናትን እንደምንጾመው ያለ ነው፡፡ የመጀመሪያውን ሳምንት ጾመ ሕርቃል የመጨረሻውን ሳምንት ደግሞ የሕማማት ሳምንት በማለት እንደምንጾመው ሁሉ ይህንንም እንዲሁ አደረግን፡፡ ይህም የአባቶቻችን ትእዛዝ የአባቶቻችን ሥርዓት ነውና እኛም ተቀበልነው፡፡ አስቀድመን እንደተናገርነው በጾም ምክንያት ክርክር ቢነሣ መጾም ከመብላት እጅግ ይሻላል እንዳሉን እንጾመው ዘንድ ይገባናል፡፡ አምስተኛ አብርሃም ሶሪያዊ ከህዳር ጾም አስቀድሞ እንዲጾም አዝዟልና ነው፡፡ በስምዖን ጫማ ሰፊው አማካኝነት ተራራውን ያፈለሱበትን ድንቅ ተአምር ማሰቢያ አድርገው ይጾሙታልና ጾመ አብርሃም ሶሪያዊ ተብሎም ተጨመረ ይላሉ፡፡

በዚህም አልን በዚያ ጾሙ የሚገባው ኅዳር ፲፭ ቀን ነው፡፡ በቅባቶች ዘንድ ግን ጾሙ በኅዳር ፲፱ ነው የሚጀምረው ይህ ደግሞ የትመጣቸው ከሮም እንደሆነ ስንክሳሩ ያስረዳናል፡፡

፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ኅዳር ፲፭ / ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment