፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ዛሬ ከገጽ ፲፫- ፲፭ ድረስ ያሉ ስህተቶችን በማስረጃ እንመለከታለን፡፡
በፎቶ ከስር ስለማያይዝላችሁ ሙሉውን ማንበብ ትችላላችሁ እኔ ግን ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ብቻ ነው ትኩረት የማደርገው፡፡
ገጽ ፲፫ መጨረሻ መስመር ላይ ጀምሮ ገጽ ፲፬ መጀመሪያው መስመር ላይ
የሚቋጨውን የካሳሁን ምናሉን የክህደት ትምህርቶች እንመልከት፡፡ “ጌታ ሰው ሆኖስጋ ለብሶ በስጋ ርስት የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ፡፡ ከአብ የባሕርይ ልደት ተወልዶ ሳለ ለአበው
ለነቢያት ለሚመጡ ለሐዋርያት ለምዕመናን በኩር ሆኖ ልጅነት የሚያድል መሆኑ በጊዜው ፅንስ ነው” ይላል፡፡ ይህ አስተምህሮ አርዮሳዊነት መሆኑ ለሁሉም የታወቀ ነው፡፡
ከተዋሕዶ በኋላ በሥጋ ርስት በመለኮት ርስት እያልን አንዱን ለሁለት ልንከፍለው እንዴት እንችላለን? ክርስቶስ የሚለው ስም እኮ
በፍጹም ተዋሕዶ ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ቢሆን የወጣለት ስም ነው፡፡ “መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ” ማለት ምን ማለት ነው? እስኪ እናስተውል ወገኖቼ! በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ የሆነው አምላክ
መንፈስ ቅዱስን በመላ የሚቀበለው ቃል ሥጋን በተዋሐደ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ተለይቶት ነበርን? ይህን ድንቅ የሆነ የሥጋዌውን ነገር
ለመናገር የሥላሴን ምሥጢር ማወቅ መረዳት በቀደመ ነበር፡፡ የሥላሴ አንድነታቸው እና ሦስትነታቸው እንዴት እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንዱ በአንዱ ላይ ሕልዋን ሆነው የሚኖሩ እንጅ ተለያይተው የሚኖሩ አይደሉም፡፡ ሁላችን እንደምናውቀው በከዊን አብን “ልብ” ወልድን “ቃል” መንፈስ ቅዱስን “እስትንፋስ” እንላለን፡፡ የአብ “ልብነት” ከወልድ “ቃልነት” ከመንፈስ ቅዱስም ሕይወትነት (እስትንፋስነት) አይቀድምም አይከተልምም፡፡ በተመሳሳይ የወልድ “ቃልነት” ከአብ “ልብነት” እና ከመንፈስ ቅዱስ “እስትንፋስነት” አይይቀድምም አይከተልምም፡፡ የመንፈስ ቅዱስም “ሕይወትነት” (እስትንፋስነት) ከአብ “ልብነት” ከወልድ “ቃልነት” አይቀድምም አይከተልምም፡፡ ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ ለአብ እና ለወልድ እስትንፋሳቸው ነው ማለት የባሕርይ ሕይወታቸው ነው ማለት ነው፡፡ በቅብአት እምነት ውስጥ ግን “ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ” ይላሉ፡፡ እንግዲህ “ወልድ” ማለት ልጅ ማለት እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ልጅነቱም ከአብ የባሕርይ ልጅነት ነው፡፡ ይህ “ወልድ” የሚለው ስም አብ “አብ” ከተባለበት መንፈስ ቅዱስም “መንፈስ ቅዱስ” ከተባለበት ስሙ አይቀድምም አይከተልምም፡፡ ስለዚህ “ወልድ” የሚለው ስም የተገባው የሆነ ከድንግል ማርያም ከተወለደ ጊዜ ጀምሮ አይደለም ከርሷ በተወለደ ጊዜስ “ወልደ ማርያም” ተብሎ የቀደመ ልጅነቱን “ወልደ አብ” ነቱን አወቅንበት እንጅ “ወልድ” መባሉስ ጥንት የለውም፡፡ ከድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜስ “አማኑኤል”፣ “ኢየሱስ” ፣“ክርስቶስ” ተባለ እንጅ “ወልድ” የተባለውስ ከዓለም መፈጠር አስቀድሞ “ባሕርይ ዘእምባሕርይ አካል ዘእምአካል” ከአብ በተወለደ ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ “ወልድ” የመንፈስ ቅዱስን ሕይወትነት ያገኘው ዛሬ ከድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ ሳይሆን ጥንት ከአብ ተወልዶ “ወልድ” ተብሎ በተጠራበት ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ “ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ” ቢባል ክህደት ነው አንጅ እምነት አይባልም፡፡ ምክንያቱም “አብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነውና፤ ወልድም በአብና በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነውና፤ መንፈስ ቅዱስም በአብና በወልድ ህልው ነውና” እንዳሉ የቀደሙ አባቶቻችን በሃይማኖተ አበው ዘዲዮናስዮስ ምእራፍ ፻፩ ቁጥር ፲ ላይ፡፡ ስለዚህ ይህ ህልውና ቀድሞ ከዓለም መፈጠር አስቀድሞ ያለ በመሆኑ እና ወልድ ከዚህ ህልውናው የተለየበት ጊዜ ስለሌለ “ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ” ቢባል ክህደት ነው፡፡ “መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ፡፡ ከአብ የባሕርይ ልደት ተወልዶ ሳለ” ማለትን ከማን እንደተማሩት አይታወቅም፡፡ አብ በመለኮቱ ቅድመ ዓለም ያለ እናት ወለደው እንጅ ድኅረ ዓለምም ዳግመኛ በሰውነቱ ከእናት አልወለደውም፡፡ በሰውነቱስ ከአብ ዳግመኛ ተወልዶ ቢሆን ኖሮ “ወልደ አብ” መባል “ወልደ ማርያም” ከመባል በበለጠበት ነበር፡፡ ነገር ግን ቅድመ ዓለም “ወልደ አብ” የተባለው ድኅረ ዓለም “ወልደ ማርያም” ቢባል እኩል ነው አንጅ አይበላለጥም፡፡ እንዲያውም ሊቃውንቱ ሲያመሰጥሩ “ቀዳማዊ ልደቱ በደኃራዊ ልደቱ ታወቀ” ይላሉ፡፡ ይህ ማለት “ወልደ አብ” መባሉ “ወልደ ማርያም” በመባሉ ታወቀ ተገለጠ ማለት ነው፡፡ ሃይማኖተ አበው ዘቴዎዶጦስ ምእ ፶፫ ቁ ፲፫ ላይ “ወልድ ዋሕድ ከአብ መወለዱ እንዴት እንደሆነ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱ እንዴት እንደሆነ አትጠይቀኝ፡፡ እርሱ በባሕርዩ ከአብ ተወልዷልና ለራሱ በአደረገው ተዋሕዶም ከድንግል ማርያም ተወልዷልና አምላክ ነው ሰውም ነው” ይላል፡፡ ሊቁ “ለራሱ በአደረገው ተዋሕዶም ከድንግል ማርያም ተወልዷልና አምላክ ነው ሰውም ነው” አለ እንጅ የቅብአት ምንፍቅና አራማጆች እንደሚሉት “መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ፡፡ ከአብ የባሕርይ ልደት ተወልዶ ሳለ” አላለም፡፡ ይህን የሚያምኑ ሰዎች እንዲመልሱልኝ የምጠይቃቸው ነገር ቢኖር አብ ወልድን በመለኮቱ ስንት ጊዜ ወለደው ትላላችሁ? የሚል ነው፡፡
ገጽ ፲፭ ላይ “በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ የግድ የማይታመም የማይሞት ሆኖአል
ሲል ነው፡፡ ወእንዘ ምድራዊ ኮነ ሰማያዊ ማለቱም፡፡ ሥጋ በርስቱ ምድራዊ ሲሆን ከቃል ጋር ተዋሕዶ መንፈስ ቅዱስ ቢቀበል ሰማያዊ ሆነ ሲል ነው” ይላል፡፡ ዋናው ዓላማ “በመንፈስ ቅዱስ ከበረ” ለማለት ስለፈለጉ ነው ይህን ያህል
ቃል እያጣመሙ የሚገኙት፡፡ ሥጋ ክቡር አምላክ የሆነው በተዋሕዶ ነው፡፡ መለኮት ሥጋን ሲዋሐድ ሥጋ ክቡር አምላክ ሆኗል፡፡ የመለኮት
ገንዘቦች በሙሉ ለሥጋ ሆነዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የሥጋ ገንዘቦች በሙሉ ከኃጢአት በቀር ለመለኮት ገንዘቡ ሆነዋል በዚህም መሠረት
ሰው ሆኗል፡፡ ለዚህም እኮ ነው “ፍጹም አምላክ
ፍጹም ሰው” የምንለው ክርስቶስ ኢየሱስን፡፡
ወልድ ሥጋን ሲዋሐድ መንፈስ ቅዱስ ተለይቶት ነበር ቢባል ክህደት ነው፡፡ ታዲያ መንፈስ ቅዱስ ያልተለየው ወልድ ሥጋን ሲዋሐድ በተዋሕዶ
መንፈስ ቅዱስን ገንዘቡ ማድረግ እንዴት አይቻልም ይባላል? ሥጋ የመንፈስ ቅዱስን ህይወትነት የአብን
ልብነት ገንዘቡ ያደረገው በተዋሕዶ እንጅ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ አነሣለሁ አሁንም፡፡ ሥጋ
የመንፈስ ቅዱስን ሕይወትነት ሕይወቱ ለማድረግ ተቀባ ካላችሁ የአብን ልብነት ልቡ ለማድረግ ምን አደረገ ልትሉ ነው? በአጭር ቃል
ወልድ ሥጋን በተዋሐደ ጊዜ በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ የመንፈስ ቅዱስን ሕይወትነት በሰውነቱ ተቀበለ ካላችሁ የአብን ልብነት ገንዘቡ
ያደረገው መቼ ነው?
እኛ
“ወልድ ዋሕድ በተዋሕዶ ከበረ” የምንል የተዋሕዶ ልጆች ግን መለኮት ሥጋን ሲዋሐድ የአብ ልብነት የመንፈስ ቅዱስ ሕይወትነት ለሥጋ
ገንዘቦቹ ሆኑ እንላለን፡፡ ምክንያቱም ከልብ እና ከእስትንፋስ የተለየ ቃል ሥጋን አልተዋሐደምና ነው፡፡ ለዚህም ማስረጃ አለን ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ በድርሳኑ ድርሳን ፪ ቁጥር ፻፶፭ ላይ እንዲህ ይላል “…አብን በልብነት መንፈስ ቅዱስን በእስትንፋስነት ገንዘብ
ለማድረግ ሥጋ ቃልን ተዋሐደ” ስለዚህ ሥጋ የአብን
ልብነት የመንፈስ ቅዱስን እስትንፋስነት ገንዘቡ ያደረገው ቃል ስለተዋሐደው እንጅ መንፈስ ቅዱስ በቅብአትነት ስላከበረው አይደለም
ማለት ስለዚህ ነው፡፡
ይቀጥላል፡፡
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ኅዳር ፰
/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
No comments:
Post a Comment