Tuesday, November 7, 2017

መሠረተ ሐይማኖት ወይስ መሠረተ ክህደት? ክፍል ፩




፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ቅባቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ኃፍረታቸውን የገለጡበት እጃቸውን የፈቱበት የመጀመሪያው የክህደት መጽሐፋቸው በሐምሌ ፲/ ፳፻፩ ዓ.ም በካሳሁን ምናሉ (0910581997) አዘጋጅነት የታተመው “መሠረተ ሃይማኖት” የተሰኘው ባለ ዐሥራ ሁለት ምእራፎች ባለ ሃምሳ አምስት ገጾች አነስተኛ መጽሐፍ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ከሽፋን ገጹ ጀምሮ በፊደል ግድፈቶች የተሞላ ነው፡፡ ምናልባትም ይህ የፊደል ግድፈት አንድም ከአዘጋጁ አንድም ከኮምፒዩተር ጸሐፊው ሊመጣ ይችላል፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን መጽሐፍ ሲታተም የጽሑፉ ረቂቅ በሚገባ ተገምግሞ እና በድጋሜ ታይቶ ስህተቶች ግድፈቶች ተለቅመው ነው መዘጋጀት ያለበት፡፡ የዚህ መጽሐፍ ደራሲ ግን ምናልባትም የዚህ ዓይነቱ ክህደት በመጽሐፍ ሲታተም የመጀመሪያውም ስለሆነ በፍርሐት መካከል ስለሆነ የፊደል ግድፈቶችን ለቅሞ አላስተካከላቸውም፡፡ በውስጥ ገጾችም ስትመለከቱ እንዲሁ በፊደል ግድፈቶች የተሞላ ነው፡፡ በነገራችን ላይ “ወልደ አብ” ም ሆነ “ሚሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊ” የተባሉት በቅርቡ የታተሙትም ቢሆኑ የፊደል ግድፈታቸው በጣም የበዛ ነው፡፡ ነገሩማ ክህደት እየተጻፈ በፊደል ግድፈቶች ማን ይጨነቃል ብላችሁ ነው እኛ ዓይን ስላየነው እንጅ፡፡






“ኦርቶዶክስ ይእቲ እርትዕተ ሐይማኖት በመንፈስ ቅዱስ” ይልልሃል አቶ ካሳሁን ምናሉ፡፡ “እርትዕተ” ማለት ምን ማለት ነው በሉልኝማ ይህን ሰው፡፡ “ኦርቶዶክስ ይእቲ ርትዕት ሐይማኖት በመንፈስ ቅዱስ” ለማለት ፈልጎ ነው፡፡ በመቅድም ገጹ ላይ እንዲህ ብሏል “አንባቢያን ሆይ የጎደለውን ሞልታችሁ የተጣመመውን አቅንታችሁ ሰው ሆኖ የማይሳሳት የለምና እኔም ብሳሳት ኮንፒተሩም ቢአልፈው አረሞ (አርሞ ለማለት ነው አሁን ይሔም) የማንበብ የናንተው ፈንታ ነው” በማለት የማረም እና የማስተካከሉ ስራ ግዴታችን እንደሆነ ገልጦልናልና እያረምና እያስተካከልን የጎደለውን እየሞላን የጠመመውን እያቀናን እንመለከትለታለን ማለት ነው፡፡ ያን ካላደረግንማ የራስህ ፈንታ ነው ብሎናል እኮ፡፡ እኔን ግን የገረመኝ ስንቱን ጎደሎ ሞለተን ስንቱን ጠማማ አቅንተን እንገፋዋለን የሚለው ነው፡፡ መጽሐፉ እኮ በሙሉ ጎደሎ እና ጠማማ ነው፡፡ “ሰው ሆኖ የማይሳሳት የለምና” የምትለው አባባል አልተመቸችኝም ምክንያቱም ካሳሁን ምናሉ እኮ ከመሳሳት አልፈህ ክህደት ውስጥ ገብተሃል፡፡ “ሰው ሆኖ የማይክድ የለምና” ብትል ትንሽ እስማማልህ ነበር አንተን አብነት በማድረግ፡፡ ስለዚህ በፊደል ግድፈቶች ላይ ከዚህ በኋላ አንነጋገርም ማለት ነው፡፡
መጽሐፉ የያዛቸው ዐሥራ ሁለቱ ምእራፎች እነዚህ ናቸው፡፡
፩. ምእራፍ አንድ ምሥጢረ ሥጋዌ መማር ይገባል
፪. ምእራፍ ሁለት አምላካችን መድሐኒታችን ከሰማያት ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም መወለዱን
፫. ምእራፍ ሦስት ስለ ማንጻትና መክፈል ማዋሐድ
፬. ምእራፍ ዐራት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መዋሃድ በስንት አይነት ነው?
፭. ምእራፍ አምስት የጌታችን የፅንዓ ተዋህዶ ነገር እንዴት ነው
፮. ምእራፍ ስድስት የምስጢረ ቅብዓት ነገር ዕንዴት ነው
፯. ምእራፍ ሰባት መንፈስ ቅዱስን ትቶ አብ እና ወልድን ብቻ ስራ መስራት አይችሉም በአንድ ነው የሚሰሩት
፰. ምእራፍ ስምንት ሐተታ ምስጢረ ቅብዓት
፱. ምእራፍ ዘጠኝ ልደተ ክርስቶስ መከበር ያለበት ታህሳስ 29 ቀን ብቻ ነው
፲. ምእራፍ ዐሥር አርባ ቀን የነቢያ ጾም
፲፩. ምእራፍ ዐሥራ አንድ ምንም የማያወላውል ጥምቀት አንዲት ስለመሆኑ
፲፪. ምእራፍ ዐሥራ ሁለት ሁለት ልደት አንድ ባሕርይ አንድ መለኮት ስለሚለው
በዚች አነስተኛ የክህደት መጽሐፍ ቅስጥ የተካተቱት ዐሥራ ሁለቱ ምእራፎች እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ናቸው፡፡ ይህን ይዘን አስኪ ወደ መቅድም ገጹ እናምራ!
መቅድም በሚለው ገጹ ላይ ካሳሁን ምናሉ ይህን የክህደት መጽሐፍ ለመጻፍ ስላነሣሣው ጉዳይ እንዲህ ይገልጣል፡፡ “ይህንን መጽሐፍ ለመጽሐፍ (ሲቃናለት ለመጻፍ) ያነሳሳኝና ያሳሰበኝ አብይ (ሲቃናለት ዐቢይ) ጉዳይ እናት ለሆነችው ለቀናች ሃይማሆት (ሲቃናለት ሃይማኖት) ለቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ሳይገባኝ እንዲገባኝ አድርጎ ሚስጢረ ስጋዌን (ሲቃናለት ምሥጢረ ሥጋዌን) በመጠኑ ስለመገለፀልኝ (ሲቃናለት ስለገለጠልኝ የጎደለው ሲሞላለት ፈጣሪየን አመሰግነዋለሁ)፡፡ ዋናው ነገር ይህን መፅሐፍ ለመፃፍ ያነሳሳኝ ምክንያት ሁለት ጥምቀት አለ ስለሚሉና በዘመነ ዮሐንስ ልደተ ክርስቶስ በ28 ቀን ስለሚከበረው ነው፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ህዳር 16 ቀንና ህዳር 19 ቀን በሁለቱም አገላለፅ ጾሙ ይጀመራል ስለሚለው ነው፡፡ በአራተኛ ደረጃ ጰራቅሊጦስ ከዋለ በአንደኛው ቀን ይጾማልና ወይም ጰራቅሊጦስ በዋለ በስድስተኛው ቀን ይጾማል ስለሚለው ነው” ይላል፡፡ እነዚህን ጉዳዮች ማንሣቱ የሚያስመሰግነው ቢሆንም ከመጽሐፍ ውጭ የሆኑ ቃሎችን እየጠቀሰ ለማሳመን መሞከሩ ግን ያስወቅሰዋል፡፡ ይህንንም በዚሁ በመቅድም ገጹ ላይ እንዲህ በማለት በግድ እመኑኝ ሲል ይታያል፡፡ “እዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙ ሐይለ ቃሎች ከሰማንያ አሐዱ መጻሕፍት ውስጥ ነው፡፡ ግን አንዳንዶች ከቀደምት ብርአና (ሲቃናለት ብራና) መፃህፍ (ሲቃናለት መጽሐፍ) ስለሆኑ ምዕራፍና ቁጥር ስለሌላቸው ምንም ልትጠራጠሩ አያስፈልግም ምክንያቱም ጥንት አባቶችንን (ሲቃናለት አባቶቻችን) ሲጽፉ በምልክት ብቻ እንዳይጠፋባቸው አልፈው አልፈው ገጽ ብቻ ነው የሚጠቀሙት ማለት ነው፡፡ ዋናው ነገር ቃለ እግዚአብሔር መጥቀሱ ነውና” ይልልሃላ፡፡ ሰውን ለማታለል እና ለማጭበርበር አንዳንዴም ጥራዝ ነጠቅ ወሬዎችን የመጽሐፉ አካል ለማድረግ በመቅድም ገጹ እውነት ናቸው ብለን እንድንቀበለው በማባበል መልኩ ይለምነናል፡፡ “ዋናው ነገር ቃለ እግዚአብሔር መጥቀሱ ነውና” ብሎ እንዲያውም ወሬውን ሁሉ “ቃለ እግዚአብሔር” ነው ለማለት ይጣጣራል፡፡ ይህ ገለጻው እኔ የጻፍሁት ምእራፍ እና ቁጥር ባይኖረውም እውነት ነው ብላችሁ እኔን አምናችሁ ተቀበሉኝ የሚል የልመና እና የማባበል ንግግር ነው፡፡ የቅባትን ምንፍቅና ጥንታዊ ነው ለማለትም “ብራና” በማለት ለማታለል ሞክሯል፡፡ ብራና ማለት የጻፉበትን የሚቀበል መጻፊያ ነው፡፡ ጥንታዊነት በብራና አይለካም አይመዘንምም፡፡ የድሮ አባቶቻችን ወረቀት ስላልነበረ በብራና ይጽፉ ነበር ማለት የአሁን አባቶች በብራና ላይ መጻፍ አይችሉም ማለት አይደለም፡፡ ዛሬም ድረስ በብራና ላይ የሚጽፉ አባቶቻችን አሉ፡፡ ስለዚህ በብራና ስም ጥንታዊ ነኝ ብሎ ማጭበርበር ተገቢ አይደለም፡፡
ካሳሁን ምናሉ! አሁን ደግሞ ስለሚወቀስበት ነገር እንዲህ ብሏል “የናንተ የሆነ አሐዳዊ መጽሐፍ የላችሁ ጳጳስ የላችሁ እዚህ በሃይማኖት በኩል አናሳ የምንባለው ግፍና መከራ ዛሬ እንሆ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ ለመጀመሪያ ጊዜ ይኸው መሠረተ ሐይማኖት መጽሐፍ ታትሞ በገበያ ላይ ዋለ” ይላል፡፡ ካሳሁን ምናሉን አንዴ አመስግኑልኝ በእውነት ነው የማመሰግንህ፡፡ እዚህ አንቀጽ ላይ እውነቱን ተናግረህ ስለሆነ የጻፍኸው አመሰግንሃለሁ፡፡ የዛሬ ቅባቶች ተሐድሶአዊ ባሕርይን ተላብሰው ነው የመጡት፡፡ አንደኛ ሃይማኖት ስም የለውም ተዋሕዶ ካራ ጸጋ ቅባት ፕሮቴስታንት ካቶሊክ አድቬንቲስት ጆቫ እስልምና ወዘተ ማለት አይገባም ይላሉ፡፡ ስም የሌለው ሃይማኖትን ነው እየሰበኩ ያሉት፡፡ ፍጥጥ አድርገህ አንተ እኮ ሃይማኖትህ ቅባት ነው ስንላቸው ደግሞ ፀሐዩ ያቀልጠናል ብለው ፈርተው ይሁን አይሁን እንጃ “ቅባት ምሥጢር እንጅ ሃይማኖት አይደለም ሃይማታችን ኦርቶዶክስ ነው” ይላሉ፡፡ ካሳሁን ምናለ አንተ ግን እውነቱን ተናግረህ “ቅባት ሃይማኖት ነው ብለሃል” በዚህም አመሰግንሃለሁ፡፡ “በሃይማኖት በኩል አናሳ” ይሉናል በማለት እንቅጩን ነው የተናገረው፡፡ “የናንተ የሆነ አሐዳዊ መጽሐፍ የላችሁ ጳጳስ የላችሁ እዚህ በሃይማኖት በኩል አናሳ” እየተባልን ግፍና መከራ ደርሶብናል ያለው ካሳሁን ምናሉ ዛሬ ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖለት ለመጀመሪያ ጊዜ የእጅ መፍቻ የኃፍረት መግለጫ የሆነውን “መሠረተ ሐይማኖት” የተባለ የክህደት መጽሐፍ አሳትሞ ለገበያ ማቅረቡን ነው የገለጸው፡፡ እንግዲህ ቅባቶች አንድ ብለው መጽሐፍ መቁጠር የጀመሩ ከዚህ በኋላ ነው ማለት ነው፡፡ በነገራችን ላይ እኮ አሁንም ቢሆን “ጳጳስ የላችሁም” መጽሐፍ ግን ሦስት ደርሳችኋል፡፡

ካሳሁን በመቀጠልም ለምን “መሠረተ ሐይማኖት” ብሎ እንደሰየመው ምክንያቱን ይዘረዝራል፡፡ “መሠረቱን እስከ ዛሬ ድረስ በምንም አይነት ያለቀቀ ስለሆነ መሠረተ ሃይማኖት አልኩት፡፡ ያለቀቀበት ምክንያት ነቢያት ትንቢት የተናገሩት እንዳለ ይሁንና ሐዋርያት በዲዲስቅልያ አንቀጽ 29 ልደተ ክርስቶስን ከ29 ውጭ መውጣት የለበትም በአራቱ ዘመን ታህሳስ 29 ቀን መከበር አለበት፡፡ ዳግመኛም ወልድ በተለየ አካሉ ለተዋሐደው ስጋ መንፈስ ቅዱስ በመላ ተቀብሎ ከአብ የባሕርይ ልደት ቢወለድ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ የባሕርይ አምላክ የባሕርይ ልጅ ሆነ፡፡ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ ብለን ስለምንሄድ መሰረተ ሐይማኖት አልኩት” ይለናል፡፡ ይህ አገላለጹ የፍልስፍና ሰዎች “HASTY GENERALIZATION” የሚሉት ነው፡፡ ለምሳሌ  በአሜሪካን ሀገር  አንድ ኢትዮጵያዊ የሆነ ወንጀል ሰርቶ ቢያዝ “ሁሉም ኢትዮጵያውያን ወንጀለኞች ናቸው” ብለው ይደመድማሉ እነዚህ ሰዎች ለድምዳሜያቸው የተጠቀሙት መረጃ በጣም ኢምንት የሆነ ነገር ነው፡፡ ይህ ካሳሁን የተባለው ሰውም እንዲሁ ነው፡፡ ልደት ታህሳስ ፳፱ ቀን ብቻ ነው መከበር ያለበት ብሎ ሌላ ሃይማኖት እንደመሠረተ ነው የሚያስበው፡፡ ለምን ታህሳስ ፳፰ ተከበረ ብሎ ከመመርመር ይልቅ ያላነበበውን መጽሐፍ እየጠቀሰ ማወናበድ ነው የተያያዘው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የራሱ ርእስ እና ቦታ ስላለው በዚያው ቦታ እንነጋገራለን፡፡ በነገራችን ላይ ይኼ እንደመግቢያ ስለሆነ አንድ በአንድ ወደፊት እንመለስበታለን፡፡
ይቀጥላል፡፡

፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ጥቅምት ፳፱ / ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment