Wednesday, November 15, 2017

ጣት የሚጠቡ ሕጻናትን ያደረገን ልዑክ



፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
መሠረተ ሐይማኖት ወይስ መሠረተ ክህደት? የሚለውን ተከታታይ ትምህርት ወደፊት የምንመለስበት ይሆናል፡፡ ዛሬ ማወቅ ስላለባችሁ ጉዳይ መረጃ ልሰጣችሁ መጥቻለሁ፡፡
***ብጹእ አቡነ ዲዮስቆሮስን ስለሁኔታው እናናግራቸው መልእክት እንጻፍላቸው፡፡ 00251933074614 የእጅ ስልካቸው ነው***
ነገሬን ፳፻፱ ዓ.ም  በጻፍኋት ትንሽየ ግጥም ለጀምር፡፡
በጉ እረኛ ሆነ
=========
በግ መሆናችንን አምነው ተቀብለው፣
እረኛ ሊሆኑን በእኛ ላይ ተሹመው፣
ዘመነ ግልንቢጥ ጉድ ዘመን ዘመነ፣
እረኛው ተኛና በጉ እረኛ ሆነ፡፡
ትላለች ሲገርመኝ ሲደንቀኝ እረኝነታቸውን ዘንግተው በበጎቻቸው ሲጠበቁ ባይ ጊዜ የጻፍኋት አነስተኛዋ ግጥም!!!

 
ምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት በብጹእ አቡነ ማርቆስ ከተያዘበት ህዳር ፳፻፬ ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ ምእመናን እረፍት አላገኙም፡፡ ነገሩ “እንደፈለገው” ተብሎ የሚተው ጉዳይ አይደል የሃይማኖት ነገር ነውና በትዕግስት ህጋዊውን ሃይማኖታዊ ሂደት ተከትሎ ለሰባት ጊዜያት በኮንትራት መኪናዎች አዲስ አበባ ድረስ በመሄድ አቤቱታቸውን ለቅዱስ ሲኖዶስ አመልክተዋል፡፡ በተለይ ከባለፈው ፳፻፱ ዓ.ም ጀምሮ የመረረ ትግል ውስጥ የገባው የሀገረ ስብከቱ  የመእመናን አንድነት ዘንድሮ ጥቅምት ውስጥ ባደረገው ሰባተኛ ጉዞው የማያዳግም መፍትሔ አገኛለሁ ብሎ ጠብቆ ነበር፡፡ ሆኖም ግን በፓትርያርክ አባ ማትያስ “የአባ ማርቆስ ጉዳይ እንዳይነሣ” በሚለው ግትር አቋም የቅዱስ ሲኖዶሱን ልዕልና በመጋፋት ጉዳዩ እንዳይታይ ተደርጎ ነበር፡፡ ይህንን የፓትርያርኩን አቋም የሰማው የሀገረ ስብከቱ ምእመናን አንድነትም ትእግስቱን በማስፋት ለስምንተኛ ጊዜ አስራ አምስት ተወካዮችን ለመላክ ተገዷል፡፡ ይህ ስምንተኛው ጉዞ በጣም ፈታኝ የነበረ እና በር ተዘግቶባቸው ለብዙ ሰዓታት በፀሐይ ላይ በመቆም ብዙ የደከሙ ቢሆንም አምላክ ፈቅዶ ሊቃነ ጳጳሳት ለእረፍት ሲወጡ በአቡነ ሳዊሮስ (የቅዱስ ሲኖዶስ ፀሐፊ) መሪነት አበው ሊቃነ ጳጳሳትን በግል በማናገር የያዙትንም ማስረጃ በማሳየት መረጃውን ለማድረስ ሞክረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ይህ ጉዳይ ይመለከተዋል የተባለውን የፌዴራል የመንግሥት አካልንም በማነጋገር ጥሩ የተባለለትን ውይይት አድርገዋል፡፡

ይህ ለስምንተኛ ጊዜ የመጣውን ተወካይ ዓይተውና ተመልክተው ለቅዱስ ሲኖዶሱ ሳያነሡት ቢቀሩ ውስጣቸውን ሰላም እንደሚነሣቸው የተረዱት ብጹእ አቡነ ሳዊሮስ “የምሥራቅ ጎጃም ጉዳይ ሊታይ ይገባል” ብለው ሃሳባቸውን አቀረቡ፡፡ በዚህን ጊዜ አቡነ ማርቆስ “የእኔ ከሳሽ ማኅበሩ ነው፡፡ ምእመናን አልከሰሱኝም” ብለው ለመከራከር ሞከሩ፡፡ ሆኖም ግን አቡነ ሳዊሮስና ሌሎችም ሊቃነ ጳጳሳት ለማኅበሩ ያላቸውን አመለካከት እንዲያስተካክሉ እና የከሰሳቸውም ማኅበሩ ሳይሆን ምእመናን እንደሆኑ እየተተካኩ ሃሳባቸውን ሰነዘሩ፡፡ አቡነ ማርቆስም ይህ ሃሳብ እንደማያዋጣቸው ሲያዩት ነገሩን ለማድበስበስ “ጎጃም ይጠመቅ እያሉ ዳግም ጥምቀትን የሚያስተምሩ ናቸው” ማለት ጀመሩ፡፡ የዚህን ጊዜ እውነቱን በሚገባ የሚያውቁት እነ አቡነ ቀውስጦስ እነ አቡነ እንድርያስ መጻሕፍትን እየጠቀሱ አፋቸውን ማስያዝ ጀመሩ፡፡ በተለይ “ወልደ አብ” የተባለው መጽሐፍ የያዘውን ክህደት በሚገባ የመረመሩት አባቶች ይህን እምነት በሚያምኑ ካህናት የተጠመቁ አማኝ ሊሆኑ ስለማይችሉ መጠመቅ አለባቸው በማለት ተከራክረዋል፡፡ በአብዛኛው የዘንድሮው የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ በርካታ ቁልፍ ነገሮች ላይ ውሳኔ የሰጠ ነበር፡፡ ከእነዚህ ውሳኔዎችም መካከል ለጠቅላይ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ ኃላፊነት የተሰጠው የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት አጣሪ ኮሚቴ ጉዳይ ነው፡፡ ብጹእ ሥራ አስኪያጁ ኃላፊነቱን ወስደው አጣሪ ኮሚቴ መድበው ወደ ቦታው በመላክ ሙሉውን የማጣራቱን ሂደት በቪዲዮ ቀርጸው እንዲያቀርቡ ተወሰነ፡፡ በዚህ ውሳኔ መሠረትም ብጹእነታቸው አቡነ ዲዮስቆሮስ ሦስት ልዑካንን መርጠው አሳወቁን፡፡ የተመረጡት አጣሪ ኮሚቴዎችም፡
፩. ርእሰ ደብር መሐሪ ኃይሉ……የጠቅላይ ቤተክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ
፪.መጋቤ ጥበብ ምናሱ ወልደ ሐና……የአልባሳት ማደራጃና ምርት ሥርጭትድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ
፫. መጋቤ ሐዲስ ሐዋዝ የማነ ብርሃን ……. የሰበካ ጉባዔ ማደራጃ መምሪያ ምክትል ኃላፊና የብጹእነታቸው ልዩ ፀሐፊ  ነበሩ፡፡ ሆኖም ግን ምክንያቱ ባልታወቀበት ሁኔታ ወደ መጨረሻው ሰዓት አካባቢ ርእሰ ደብር መሐሪ ኃይሉን በማስቀረት የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ባልደረባ ነው የተባለውን መምህር አብርሃም ገረመውን መተካታቸው ተሰማ፡፡ ይህ ሁሉ ሲደረግ የምሥራቅ ጎጃም ምእመናን በትእግስት ሲጠብቁ የነበረው “ሙሉው የማጣራት ሂደት በቪዲዮ ተቀርጾ ይቅረብ” የሚለውን ትእዛዝ ተፈጻሚነቱን በመተማመን ነበር፡፡ በቪዲዮ ከተቀረጸ ማንም ከምድር ተነሥቶ እንዲህ ነው ማለት አይችልምና ነው፡፡ ሆኖም ግን ነገሮች ሁሉ ታላቁን ህዝብ በመናቅ ጣቱን እንደሚጠባ ሕጻን ማታለል ነበር የተጀመረው፡፡ ይህ የሃይማኖት ጉዳይ ነውና እስከመገረፍ ትደርሳለህ፡፡ ይህ የሃይማኖት ጉዳይ ነውና እስከሞት ትታመናለህ፡፡ ታዲያ የምን ድብብቆሽ ነው? ቤተክርስቲያኒቱ ለሳምንታት ያህል አበል ከፍላ የምትቀልባችሁ እኮ ለምእመናን የመፍትሔ አካላት ትሆናላችሁ ብላ እንጅ ገንዘብ የምታወጣበት ጉዳይ አጥታ አልነበረም፡፡ ይህን ትልቅ አደራ እና ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው በሽርፍራፊ ሳንቲም መደለል (መገዛት) ዕቃነት ነው፡፡ ዕቃ ነው ለማንም በማንም በገንዘብ የሚገዛው፡፡
ብጹእነታቸው አቡነ ዲዮስቆሮስ ይህንን ተልእኮ አልሰጧችሁም እናውቃለን፡፡ አንድ አጣሪ ኮሚቴ ተብሎ የሚመጣ አካል ከሁለቱም ቡድኖች ከስብሰባው በፊት ማግኘት የለበትም፡፡ መጀመሪያ ማግኘት ካለበትም ገለልተኛ የሆነን አካል ነው፡፡ እነዚህ ግን በመጀመሪያ ያገኙ አቡነ ማርቆስን እና በሥራቸው ያሉ የሀገረ ስብከቱን ሠራተኞች ነበር፡፡ ዓርብ ዕለት ህዳር ፩/፳፻፲ ዓ.ም ደብረ ማርቆስ የመግባታቸውን ዜና ስንሰማ አላመንም ነበር፡፡ ዛሬ መጥተዋል ሲሉን ነገ ይገባሉ ሲሉን ማጣራቱ ቅርብ ጊዜ ይጀምራል ሲሉን እውነቱን ማግኘት ተስኖን ስንወዛገብ እሁድ ዕለት ህዳር ፫ ከሞጣ ከጉንደወይን አካባቢ በመኪና እየተጫነ ደብረ ማርቆስ የሚሰፍረውን የአባ ማርቆስ ደጋፊዎችን ስንመለከት አጣሪ ኮሚቴው ደብረ ማርቆስ እንደገባ እርግጠኖች መሆን ጀመርን፡፡ በዚህም መሠረት አጣሪ ኮሚቴው እንዲያየው የምንፈልገውን ነገር ሁሉ በወግ በወጉ አዘጋጅተን “ኑ” የሚለውን ጥሪ መጠባበቅ ጀመርን፡፡ በሀገረ ስብከቱ የሚገኙ ምእመናን አጣሪ ኮሚቴው ስለመምጣት አለመምጣቱ ምንም የሚያውቁት ነገር አልነበረም፡፡ መረጃዎችን አዘጋጅተን እንጠብቅ እንጅ መቼ እንደሚጠራ ስላላወቅን ከወረዳዎች የሚመጡትን ምእመናን ደብረ ማርቆስ እንዲመጡ ማድረግ አልተቻለም ነበር፡፡ “መቼ እንምጣ” የሚለው የወረዳዎች ጥያቄ  በአጣሪዎች የውኃ ሽታ መሆን የተነሣ መልስ አላገኝ አለ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ነበር ሰኞ ህዳር ፬ ቀን ከቀኑ ስምንት ሰዓት እንድትገኙ የሚል ድንገተኛ መልእክት የተላለፈው፡፡ የምእመናን ተወካዮችም “ይህ ጉዳይ የሀገረ ስብከቱ ጉዳይ ነው፡፡ ወረዳ ላይ ያሉ ምእመናንም መገኘት አለባቸው፡፡ እኛ አምስት ሰዎች ምሥራቅ ጎጃምን ወክለን ልንሰበሰብ አንፈልግም፡፡ ጉዳዩ ሃይማኖታዊ ጉዳይ ትልቅ አጀንዳ ነው፡፡ ሁሉም መገኘት አለባቸው ያ ካልሆነ ግን በስብሰባው አንገኝም” አሉ፡፡ ይህ ውሳኔ ትክክለኛ ውሳኔ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉዳዬ ብሎ አጣሪ ኮሚቴ ይመደብበት ያለውን ሀገረ ስብከት በሰባት መኪና ሲመላለስ የኖረውን ምእመን በአምስት ሰዎች መወከል ማለት ምን ማለት ነው? ይጣራ ቢባል ኖሮስ ምኑን ሊያጣሩት ነበር የገመቱ? በዚህም የተነሣ አጣሪ ኮሚቴው አጣብቂኝ ውስጥ ወደቀ፡፡ ታዲያ ምን እናድርግ አሉ፡፡ ምእመናን ይገኙ መረጃዎቻችንን እናቅርብ ቪዲዮ ቀራጭም ይፈቀድልን ተባለ፡፡ በዚህም ጥያቄ መሠረት በነጋታው ህዳር ፭ ከሁለት ሰዓት ጀምሮ ጉዳዩ እንዲታይ እና መቶ የምእመናን ተወካይ እንዲሳተፉበት ተወሰነ፡፡
መምህር አብርሃም ገረመው

ይህ ውሳኔ በተላለፈበት ዕለት ህዳር ፬/ ፳፻፲ ዓ.ም በርእሰ ደብር መሐሪ ኃይሉ  ምትክ የመጡት መምህር አብርሃም ገረመው በደብረ ፀሐይ መልእልተ አድባር ቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን (መንበረ ጵጵስና) ከአቡነ ማርቆስ እና ከደጋፊዎቻቸው ጋር የመጡበትን ዓላማ በመዘንጋት ሲዘባጥሩ አምሽተዋል፡፡ “ብዙ መሥራት የሚችሉ አእምሮን ማደስ የሚችሉ፡፡ ለሁሉ አብነት የሚሆኑ ደግሞ አባት የዚሁ ሀገረ ስብከት ለእናንተ አባት መሪ የሆኑ እግዚአብሔር ነው የሰጣችሁ በዚህም ደስ ይበላችሁ ምእመናን፡፡ ከዚህ የበለጠ ትልቅ ነገር የለም ቦታውን ጊዜውን የሚዋጁ አባት ማለት ነውና ስለዚህ ሰው ሞኝ ነው ባለው ነገር መጠቀም አለመቻል ማለት ነውና፡፡ ስለዚህ ለዚህ ሁሉ መንገድ ይህንን ሁሉ ይህንን ሁሉ ጸጋ ይህ ሁሉ ሀብት ይህ ሁሉ በረከት ባለበት የምሕረት አደባባይ ዛሬ እኔ ደግሞ ታናሹ ደካማ የምሆነው ደግሞ ይህን እንድመሰክር እግዚአብሔር ስለፈቀደልኝ እግዚአብሔርን ብታመሰግኑልኝ ደስ ይለኛል፡፡ በደንብ አ መ ስ ግ ኑ ት፡፡ እግዚአብሔርን የተመሰገነ ይሁን” በማለት ደጋፊዎቻቸውን ከልክ ባለፈ ሁኔታ ሲያስጨበጭቡ ማምሸታቸው በጣም ያስገርማል፡፡ አጣሪ ኮሚቴ ተብሎ ችግር አለበት ከተባለ ወገን ጋር ተገናኝቶ ካልተቀበላችሁ ብሎ ማላዘን ምን የሚሉት እብደት ነው? በእውነት ከልቤ አዝናለሁ፡፡ ቆዩ እንጅ ቤተክርስቲያኒቱ የሚያስብላት ሰው አጥታ ነው ይህን የመሰለውን ሰው አበል ከፍላ የላከችው ግን፡፡ ይህ በጣም ያስወቅሳል አቡነ ዲዮስቆሮስ እንዲህ ተደረገ ሲባሉ በጣም እንደተበሳጩ ሰምተናል፡፡ ይህ እኮ ለሕጻናት ማባበያ እና መሸንገያ ካልሆነ በቀር ለእኛ ያውም ሃይማኖታዊ ጉዳይ ለያዘ ሰው በፍጹም አይሆንም በፍጹም፡፡

ይህንንም ክፍተት እንዳለ ይዘን በተቀጠረው ዕለት በሰዓቱ ተገኝተናል፡፡ የአቡነ ማርቆስ ደጋፊዎች በሌሊቱ ሳይፈተሹ ቁጥራቸው ሳይታወቅ አዳራሽ ገብተው ተሰግስገዋል፡፡ የምእመናን ተወካዮችም በቦታው በተባለው ሰዓት ተገኝተዋል፡፡ የሚገባው አንድ መቶ ሰው ብቻ ነው ተባለ እሽ አሉ ምእመናን፡፡ ካሜራ መያዝ አይቻልም ሞባይላችሁን አምጡ ተባሉ እሽ ይሁን አሉ፡፡ ፕሮጀክተር ላፕቶፕ የቪዲዮ ማስረጃ ምናምን የሚባል ነገር ማቅረብ አይቻልም አሉ፡፡ ታዲያ የቪዲዮ የድምጽ የሰነድ ማስረጃዎች ካልታዩ ምኑን ነው ልታጣሩት የመጣችሁ በሚል የተፈቀደለት መቶ ሰውም አንገባም ብሎ ቀረ፡፡ በዚህም የተነሣ የማጣራቱ ሂደት በአቡነ ማርቆስ ደጋፊዎች በሙሴ በትር የኤርትራን ባሕር ከፍለው እንደተሻገሩ እስራኤላውያን “ንሴብሖ” በሚለው መዝሙር ብቻ ተደምድሞ አረፈው፡፡ የምእመናን ሞባይል ከአዳራሽ ውጭ እያሉ ሁሉ እየተቀሙ ለተወሰነ ደቂቃም ሲኒማ አዳራሹ አጥር ግቢ ውስጥ እየታሰሩ ሲንገላቱ መዋላቸው “እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ” አሰኝቶናል፡፡ ሲጀመር ይህ ጉዳይ ሃይማኖታዊ እንጅ ፖለቲካዊ ጉዳይ ስላልሆነ ስብሰባው መደረግ የነበረበት በራሷ በቤተክርስቲያኒቱ ቅጽር ግቢ ውስጥ ነበር፡፡ ምሥራቅ ጎጃም አሥራ ስምንት ወረዳዎችን የያዘ ሀገረ ስብከት በመቶ ሰዎች እንዴት ሊወከል ይችላል? የሚገርመው ደግሞ መቶ ሰው ቢገባም መናገር የሚችለው አምስት ሰው ብቻ ተብሎ መወሰኑ ነው፡፡ ያ ሁሉ የቪዲዮ የድምጽ እና የሰነድ ማስረጃ አይታይም ሲባል ታዲያ ምኑን ልታዩ ነው የመጣችሁ እናንተ ብታጣሩም የምትወስኑትን ስለምናውቅ አንገባም  አንሳተፍምም በማለት ምእመናን የያዙት አቋም ትክክለኛ ነው፡፡ አሁንም ወደፊት አምላክ የፈቀደውን ነገር ሁሉ በቤተክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት ያለተስፋ መቁረጥ እናካሂዳለን፡፡

አጣሪ ተብሎ የተላከው አብርሃም ገረመው ዐውደ ምሕረት ላይ ምን እንደተናገረ ከዚህ በታች የተያያዘውን ቪዲዮ ከፍታችሁ ተመልከቱ፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ቪዲዮ ለአቡነ ዲዮስቆሮስ እንዲደርስ አዲስ አበባ ተልኳል፡፡ https://youtu.be/JxFvQQD1cKg
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ኅዳር ፮ / ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment