፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ዛሬ ከገጽ ፲፭ ምእራፍ ሦስት ጀምረን ያሉ ስህተቶችን በማስረጃ እንመለከታለን፡፡ በፎቶ ከስር ስለማያይዝላችሁ ሙሉውን
ማንበብ ትችላላችሁ እኔ ግን ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ብቻ ነው ትኩረት የማደርገው፡፡
****************
·
እንድማጣ ኢየሱስ
የሚገኘው የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባዔ ተማሪዎች የመማሪያ አዳራሽ በድንጋይ ተደብድቦ የመስኮት እና የበሮቹን መስታወት
መርገፋቸው ተነገረ፡፡
·
ይህንን ድርጊት የፈጸመው
ቄስ በህግ ሊጠየቅ ይገባል ብለዋል ተማሪዎቹ፡፡
***************
ምእራፍ ሦስት ድንግልን ስለ ማንፃትና ስለመክፈል ብሎ የሚጀምረው የካሳሁን
ምናሉ የክህደት ትምህርት እንዲህ በማለት ይቀጥላል “የመንፈስ ቅዱስ ግብር ምንድን ነው ቢሉ መንፃት መክፈል መዋሐድ መፍጠር ቅብዕ
መሆን ነው” ይላል፡፡ ይህን በተመለከተ ባለፉት ተከታታይ ትምህርቶች በሰፊው ስለተመለከትን በድጋሜ አናየውም፡፡ በዚህ የምንጨምረው
ነገር ቢኖር ከመንፈስ ቅዱስ ግብሮች መካከል አንዱ “መዋሐድ” ተብሎ የተጠቀሰውን ክህደት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለለቢሰ ሥጋ በድንግል
ማርያም ማኅጸን አላደረም፡፡ በየትኛው ትምህርት በየትኛው መጽሐፍ ነው “መንፈስ ቅዱስ የማርያምን ሥጋ ተዋሐደ” የሚል ገጸ ንባብ
የሚገኘው? ይህ ፍጹም ክህደት ነው፡፡
፩ኛ. ማስረጃ፡ ወንጌላዊው ዮሐንስ “ቃል ሥጋ ኮነ” በማለት ተናግረ
እንጅ “መንፈስ ቅዱስ ሥጋ ኮነ” አላለንም፡፡፡፡
፪ኛ. ማስረጃ፡ “የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን
ከህግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ” ገላ ፬÷፬ ይላል እንጅ መንፈስ
ቅዱስን ላከ አላለንም፡፡ ወይስ መንፈስ ቅዱስ ልጁ ነው ትሉን ይሆን?
፫ኛ. ማስረጃ፡ “አሐዱ ዘእምቅድስት ሥላሴ ርእዮ ትሕትናነ አጽነነ ሰማየ
ሰማያት መጽአ ወኃደረ ውስተ ከርሰ ድንግል፤ ከቅድስት ሥላሴ አንዱ ወልድ መዋረዳችንን አይቶ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ባሕርዩን ዝቅ
አደረገና መጥቶ በድንግል ማኅጸን አደረ” ይላል ሊቁ አባ ኤፍሬም በሐሙስ ውዳሴ ማርያም፡፡ ታዲያ መንፈስ ቅዱስ የድንግልን ሥጋ
ቢዋሐድ ኖሮ “አሐዱ ዘእምቅድስት ሥላሴ” ማለቱን ትቶ “ክልዔቱ” ባለ ነበር፡፡
፬ኛ. ማስረጃ፡ ሃይማኖተ አበው ዘኪራኮስ ምእራፍ ፺፩ ቁ ፲፯ ላይ “ወኢንብል ከመ ሠለስቱ አካላት ተሠገው በሥጋ ወኢሥላሴ በአሐዱ
አካል ከመ ይሠገው አላ አሐዱ አካል እም ሠለስቱ አካላት ዘውእቱ እግዚአብሔር ቃል ጥበቡ ለአብ ወኃይሉ ብርሃነ ጽድቅ ዘያበርህ
እምብርሃነ አብ ብሩህ አምላክ ዘኢይትዌለጥ እምአምላክ ዘበአማን ዘተወልደ እመለኮተ አብ፤ ሦስቱ አካላት ሥጋን እንደ ተዋሐዱ አንናገርም
ወይም ሰው ይሆኑ ዘንድ ሥላሴ አንድ አካል ሆኑ አንልም ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ሰው ሆነ እንላለን እንጅ ይኸውም የአብ ጥበቡ
ኃይሉ የሚሆን ከብሩህ አብ ብርሃን የተገኘ የሚያበራ የእውነት ብርሃን ከባሕርይ አምላክ የተገኘ የማይለወጥ አምላክ ከአብ አካል
ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ የተወለደ እግዚአብሔር ቃል ነው” አለ እንጅ “እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው” አላለንም፡፡ ታዲያ
ካሳሁን ምናሉ ከየት የተማረውን ከየት ያነበበውን ነው “የመንፈስ ቅዱስ ግብሩ መዋሐድ ነው” ብሎ በድፍረት የጻፈው? ጤነኛነቱ በራሱ
አጠራጠረኝ ስለእውነት የመንፈስ ቅዱስ ግብሩ “መዋሐድ” እንዴት ሊሆን ይችላል፡፡
ገጽ ፲፮ ላይ “ዕንሆ ምስጢረ ስጋዌ ንዴት በቅብዐት አጠፋለት ማለት
ነውና ሲዋሐድ ባይቀባ ንዴት ይወድቅበት ነበርና ንዴት ሳይወድቅበት አስቀድሞ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስ ቢአድርበት ያገኘው የነበረው
ንዴት ስለቀረለት ጠፋለት ይላል እንጅ” በማለት ይጽፋል፡፡ እግዚአብሔር ይቅር ይበላቸው ሌላ ምንም አይባልም፡፡ በመለኮት ከአብ
ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድነት ያለው አካላዊ ቃል ከድንግል ማርያም ሥጋን ሲዋሐድ መለኮቱን ሰማይ ትቶ የመጣ ይመስላችኋል እንዴ?
አብ እና መንፈስ ቅዱስስ ከድንግል ሥጋን ከተዋሐደው አካላዊ ቃል የተለዩበት ጊዜ አለን? ይህ ፍጹም ክህደት ነው፡፡ ሕይወቱ የሆነው
መንፈስ ቅዱስ ንዴትን የሚያጠፋለት አካላዊ ቃል ራሱ ንዴትን ማጥፋት የማይችል ሆኖ ነውን? በመለኮት መበላለጥ ያለባቸው አስመስሎ
በመጻፉ ሁላችሁም ትታዘቡታላችሁ ብየ አስባለሁ፡፡
“ዳግመኛ በዚህ ድርሳን እግዚአብሔር
ሕያው አምላክ የሆነ ሥጋን በመንፈስ ቅዱስ ፈጠረ ዓለምንም በእርሱ አዳነ ብንል ዐላዋቆች ይነቅፉናል” ሃይማኖተ አበው
ዘዮሐንስ አፈወርቅ ም ፷፰ ክ ፳፰ ቁ ፵፫ በማለት ቃል ራሱ የፈጠረውን ሥጋ እንደተዋሐደ ያስረዳናል፡፡
ሃይማኖተ አበው ዘኤፍሬም
ም ፵፯ ቁ ፭ ግን እንዲህ ይላል “የድንግልን ሥጋ መረጠ ሰው መሆኑን ሊያስረዳ ፍጹም አካሉን በማኅጸኗ ፈጠረ ከእርሷ ሥጋን የተዋሐደ
እጠቀምበታለሁ ብሎ አይደለም” ይላል፡፡
የቅባት ባህሎችን በጥቂቱ እስኪ እንመልከታቸው፡፡
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ገጽ ፯፻፹ ላይ የቅብዓት
ባህል ፫ ክፍል አለው ይላሉ፡፡ መጀመሪያ በፋሲል ዘመን የተነሡት እነዘኢየሱስ መጽሐፍ “አንደየ ርእሶ” ይላልና “ቃል በተዋሕዶ
ዜገ ከሥጋ ሲዋሐድ የባሕርይ ክብሩን አጣ ለቀቀ ሲቀባ ወደ ጥንተ ክብሩ ተመልሶ በሰውነቱም በአምላክነቱም አንድ ወገን በቅብዓት
የባሕርይ ልጅ ሆነ ብለዋል” ይላሉ፡፡
ሁለተኛው ባህላቸው በአንደኛው ዮሐንስ ዘመን የተነሡት እነ አካለ ክርስቶስ
“ዜገ” የሚለውን የእነ ዘኢየሱስን ትምህርት ነቅፈው አጸይፈው መጽሐፍ “እስመ ተዋሕዶ አእተታ ለምንታዌ ይላልና ሥጋ በተዋሕዶ አንድ
አካል ሆነ እንጅ የአምላክነት ክብር አላገኘም፡፡ ሲቀባ ግን ክብር ተላልፎለት ተፈጥሮ ተገብሮ ጠፍቶለት በቅብዓት የባሕርይ ልጅ
የባሕርይ አምላክ ሆነ ብለዋል”
ሦስተኛው ባህላቸው በዐጼ ቴዎድሮስ ዘመን የተነሡት እነአለቃ ጎሹ ናቸው፡፡
እነዚህ ደግሞ በቅብዓት ብቻ ማለትን ነቅፈው “መጽሐፍ በሁለቱም ሁሉ በተዋሕዶ ከበረ በቅብዓት ከበረ ይላልና ቅብዓት ያለተዋሕዶ
ተዋሕዶም ያለቅብዓት ብቻ ብቻውን አያከብርም በተዋሕዶና በቅብዓት በአንድነት የአምላክነት ክብር ከብሮ የባሕርይ ልጅ ሆነ ብለዋል”
ይላሉ፡፡ የቅባት ሦስቱ ባህሎች እነዚህ ናቸው፡፡ እነዚህ የአሁን ቅባቶችም በእነዚህ በሦስቱም ባሕሎች ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡
ይህንን ማፍረስ የሚችሉ በርካታ መጽሐፋዊ ጥቅሶችን ማቅረብ ይቻላል ሆኖም
ግን የራሱ ጊዜ እና ቦታ ስላለው በጊዜው በቦታው የምናየው ይሆናል ለዛሬ ግን የተወሰኑ ጥቅሶችን ላቅርብላችሁ፡፡
፩. “ከአብ የተገኘ ቃል ከተዋሐዳት ካከበራት ከሥጋ ጋር አንድ እንደሆነ መጠን” ድርሳነ ቄርሎስ ፶፮÷፲፭
፪. “ዘአንገሦ ለሥጋ አዳም በመንፈስ ቅዱስ ወረሰዮ ቅዱሰ ወማሕየዌ፤
በመንፈስ ቅዱስ ሕይወትነት የአዳምን ባህርይ ያከበረዉ የባሕርይ አምላክ ያደረገዉ እርሱ ነው” ሃይማኖተ አበው ዘአልመስጦአግአያ
ም ፪ ቁ ፭ እርሱ የሚለው ማንን ነው?
፫. “መኑ ውእቱ ዝንቱ ዘሐደሶ
ለሥጋ እምነ ኀጉል ወተወክፎ እሙስና፤ ሥጋን ከብልየቱ ያደሰው ከመለወጥ አድኖ የተዋሐደው ይህ ማነው” ሃይማኖተ አበው ዘእልመስጦአግያ ም ፬ ቁ ፲፩
#ይቀጥላል፡፡
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ኅዳር ፲፩
/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
No comments:
Post a Comment