Sunday, November 19, 2017

ደጀን በፀረ ተሐድሶ ትግል ውስጥ



፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
የደጀን አበ ብዙኃን አብርሃም ቤተክርስቲያን
እልህ አስጨራሹን የዓባይን በረሃ አቋርጠው የጎጃምን ንጹሕ ዓየር “ሀ” ብለው የሚተነፍሱባት ደጀን ከተማ ዛሬ ኅዳር ፲/፳፻፲ ዓ.ም ፀረ ተሐድሶ ዘመቻዋን በጥንታዊው ደብረ አሚን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት አዳራሽ ውስጥ በይፋ ጀምራለች፡፡ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በተጀመረው በዚህ የመጀመሪያው የፀረ ተሐድሶ ዘመቻ ጉባዔ ላይ ከ አምስት መቶ ያላነሱ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደተሳተፉበት ተነግሯል፡፡ አዳራሹ ከመሙላቱ የተነሣ በመስኮቶች እና በበሮች አካባቢ ቆመው ይመለከቱ የነበሩ ምእመናን በቁጥር አያሌ እንደነበሩም ተጠቁሟል፡፡ ደጀን ኮራንብሽ ደብረ አሚን እውነትም የእምነት ተራራ ስምን መልአክ ያወጣዋል አሉ፡፡ አባ ሙሴን የመሰሉ ብርቅየ አባት ያስተማሩበት ዐረፍተ ዘመን ሲገታቸውም በዚያው ሥጋቸው ያረፈባት ደጀን በመናፍቃን አትወረርም አትወረስም፡፡



የደጀን ደብረ አሚን ቅዱስ ጊዮርጊስ

ከፍተኛ ቁጭትን የፈጠረው የዚህ የዛሬው ጉባዔ በተለይም በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ከተቀበረበት ጉድጓዱ አስነሥተው ሕይወት የዘሩበትን “ቅባት” የተባለ የካቶሊክ ቅርንጫፍ በግልጥ ለምእመናን እውቅና ተፈጥሮበታል፡፡ ይህንን በተመለከተ ለምእመናን እውቅና ሲፈጠር ውስጣቸው ላይ የነበረው ሃማኖታዊ ቁጭት ገንፍሎ እንደወጣባቸው ተነግሯል፡፡ ደጀን ደብረ አሚን ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰንበት ትምህርት ቤት ዛሬ ታሪክ የሚዘክረውን ታላቅ ሥራ ሠርቷል፡፡ በደጀን ወረዳ ቤተክህነት ሥር የሚገኙ የተወሰኑ ጥቂት ወፍ ዘራሽ ቅባቴዎች ያሉባቸው አካባቢዎች ተለይተው ታውቀዋል፡፡ የተወገዘውን “ወልደ አብ” የተባለ የክህደት መጽሐፍ በማከፋፈል እና በማስተማርም በኩል እየሠሩ ያሉ መሪጌቶች ተለይተው ታውቀዋል፡፡ ቆንቸር፣ ሳሳበራይ፣ ምንጅ፣ ጎረፍ፣ የትኖራ በቁጥር ጥቂት የሚባሉ ወፍ ዘራሽ ቅባቴዎች እንዳሉ ታውቋል፡፡ ከጉንደ ወይኑ የ “ወልደ አብ” መጽሐፍ አከፋፋይ ጋር በመገናኘት የቅባት መጻሕፍትን እንደሚያከፋፍሉም መረጃው ተይዟል፡፡ ይህ የዛሬው ጉባዔ ለነዚህ ሁሉ የማስጠንቀቂያ ደወልም ነው ተብሎለታል፡፡
በጉባዔው ላይ የከተማዋ ወረዳ ቤተክህነት ሥራ አስኪጅ፣ የደጀን ደብረ አሚን ቅዱስ ጊዮርጊስ እና የደጀን አበ ብዙኃን አብርሃም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ እንዲሁም የአጥቢያው አገልጋይ ካህናት እና ዲያቆናት የተገኙ ሲሆን ወጣቱ አዛውንቱ ህጻናትም ሳይቀሩ በቦታው እንደተገኙ ታውቋል፡፡ ይህን የመሰለ ታላቅ ታሪካዊ ጉባዔ በጠባብ አዳራሽ መደረጉ ግን ብዙዎችን አላስደሰተም ነበር፡፡ ዐውደ ምሕረቱ የራሳችን በሆነበት ቤተክርስቲያን ላይ ሁሉም ተቀምጦ ቢመለከተው መልካም በሆነ ነበር ብለዋል፡፡

በዚህ ጉባዔ ላይ ከአንዴም ሁለቴ ከዚያም በላይ ለጠቅላይ ቤተክህነት እና ለቅዱስ ሲኖዶስ በፍላሽም በሲዲም ቀርቦላቸው አልመለከተው ያሉትን የአቡነ ማርቆስን የስህተት አስተምህሮዎች ለምእመናን በፕሮጀክተር ታግዞ ቀርቦላቸዋል፡፡ ይህንን የአቡነ ማርቆስን የስህተት አነጋገሮች ሲሰሙ ውስጣቸው በቁጭት የበገነው የደጀን ነዋሪዎች ከዚህ በኋላ ማንም ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን ሊደፍራት እንደማይገባ ሁላችንም ዘብ ልንቆምላት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ ገና ካሌንደር ነው፣ ሰኔ ጎልጎታ ልብ ወለድ ነው፣ ተዝካር ምዋርት ነው፣ ተዋህዶ ቅባት ካራ ጸጋ ማለት አያስፈልግም፣ ዳግም ጥምቀት የለም (ቅባቶች መጠመቅ የለባቸውም) ወዘተ የሚለውን የአቡኑን የቪዲዮ ማስረጃ ያለማንም ከልካይነት በግልጽ ለምእመናን እንዲታይ ተደርጓል፡፡
የደጀን ወረዳ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ በቅባት እና በተዋሕዶ ጉዳይ ላይ ያላቸውን አቋም እንዲገልጹ እና ጥጋቸውን እንዲይዙ በምእመናን ፍጥጥ ተደርገው የተጠየቁ ሲሆን በእናቴ ጉንደወይን በአባቴ ግን ከጉንደ ወይን ውጭ ነኝ በማለት ጉንደወይንን በሙሉ ቅባት አስመስለው ሲናገሩ ተስተውለዋል። በዚህ መልኩም ለማድበስበስ ሞክረው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ምእመናን ማጽዳት የምንጀምረው ከእናንተ ጀምረን ነውና እውነቱን ያውጡ ብለው አፋጠዋቸዋል፡፡ ሥራ አስኪያጁም ነገሩ የከረረ መሆኑን ሲያዩ እኔ ተዋሕዶ ነኝ ብለው ተናግረዋል፡፡ ታዲያ ተዋሕዶ ከሆኑ የቅባት እምነትን እያስፋፉ ያሉትን ሊቀ ጳጳስ አይነሡብን ብላችሁ ጠቅላይ ቤተክህነት ለምን ሄዳችሁ ብለው ምእመናን አሁንም ያፋጠጧቸው ሲሆን አዲስ አበባ አልሄድሁም በሚል ክደው መልሰዋል፡፡ ለምን ይዋሻሉ አዲስ አበባ ሄደዋል አባ ማርቆስ አይነሡብንም ብለዋል ብለው አሁንም አፋጠጧቸው መውጫ ቀዳዳ ያጡት ሥራ አስኪያጅም ፀበል ነው የሄድሁ እንጅ አዲስ አበባ አልሄድሁም በለዋል፡፡ እዚህ መፋጠጥ ውስጥ ከዚህ በላይ መግባት የለብንም መሄድ አለመሄድዎን በሚገባ እናጣራለን ወደፊትም የሚሆነውን እናያለን በሚል ፋይሉን መዝጋታቸው ተረጋግጧል፡፡ የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪ የሆኑትም ከዚህ በኋላ ቅባት የተባለን መናፍቅ ቅጽራችን አናስደርስም ብለዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ምእመናን እናንተ በምትሉት እንጓዛለን በሚልም የጋራ ድምዳሜ ላይ የተደረሰ ሲሆን አላግባብከሀገረ ስብከቱ የተጣለውን ገንዘብም እንደማይከፍሉ የጋራ አቋም ይዘዋል፡፡ ለምንፍቅና መደገፊያ የቤተክርስቲያናችንን ገንዘብ አንልክም በሚል ተወስኗል፡፡
ደጀን ደብረ አሚን ታሪካዊ ሥራ ሠርቷል፡፡ የዚህን ጉባዔ ዜና የሰሙ ሁሉ በሀሴት ልባቸው ሲመላ ሳይ ጊዜ ደስ አለኝ፡፡ ማንም መድረኮቿ ላይ ወጥቶ የሚፈነጥዝባት አደባባይ አይደለችም ቤተክርስቲያናችን የራሷ ሥርዓት ያላት የራሷ አስተምህሮ ያላት እንጅ፡፡ ይህ ጉባዔ ቢቻል በሁለት ሳምንት ባይቻል ግን በየወሩ መደረግ አለበት መቋረጥ የለበትም የሚል አስተያየት የሠጡት መእመናን ውስጣቸውን የሚኮረኩር አንዳች ኃይል እንደፈነቀላቸው ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ይህንኑ የመሰለ ጉባዔ በብቸና በመልአከ ብርሃን አድማሱ ልጆችም ተደርጓል፡፡ ዓርብ የጀመረው ይህ ጉባዔ ከዲማ በመጡ ሊቃውንት ሲደምቅ ሰንብቷል ተብሏል፡፡ ሀገረ ስብከታችን የመናፍቃን መከማቻ እየሆነ ስለመጣ ለሀገረ ስብከት ይከፈል የነበረውን ገንዘብ አንልክም የሚል የጋራ አቋም ላይ መድረሳቸውን የአለቃ አያሌው ልጆች ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ጎረቤታም ወረዳዎች በተሐድሶ መናፍቃን ላይ የጋራ አቋም መያዛቸውም ለሌሎች የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ወረዳ ቤተክህነቶች የማንቂያ ደወል ነው፡፡

፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ኅዳር ፲ / ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment