Wednesday, November 15, 2017

መሠረተ ሐይማኖት ወይስ መሠረተ ክህደት? ክፍል ፭



፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ዛሬ ገጽ ፱ እና ፲ ላይ ያሉ ስህተቶችን በማስረጃ እንመለከታለን፡፡ በፎቶ ከስር ስለማያይዝላችሁ ሙሉውን ማንበብ ትችላላችሁ እኔ ግን ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ብቻ ነው ትኩረት የማደርገው፡፡

ካሳሁን ምናሉ ገጽ ፱ ላይ እንዲህ ይላል “ቃልም ለቃልነቱ ቃል ነው፡፡ ሥጋ ለስጋነቱ ስጋ ነው ነገር ግን ቃልም ስጋም በእንድ ሆኑ ማለት ነው” ይላል፡፡ ገጽ ፰ እና ፱ ላይ መለኮት እና ሥጋ በተዋሕዶ አንድ እንደሆኑ ከሃይማኖተ አበው ጥቅሶችን እየጠቃቀሰ ለማስረዳት ሞክሯል፡፡ ሆኖም ግን በተዋሕዶ ምንታዌነት ብቻ ተወገደ እንጅ ሰው አምላክ፤ አምላክም ሰው አልሆነም ብሎ የሚያምን ስለሆነ “በተዋሕዶ ከበረ” አይልም፡፡ እንዲያውም “በተዋሕዶ ከበረ” ማለት ዐራት ኑፋቄ አለበት ብለው “በወልደ አብ” መጽሐፋቸው ላይ በሰፊው ክደውበት ታይተዋል፡፡ ተዋሕዶ ማለት ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ የሆነበትና የሥጋ ገንዘብ ለቃል የቃልም ገንዘብ ለሥጋ የሆነበት ሰው አምላክ አምላክም ሰው የሆነበት  የማይመረመር ከአእምሮ በላይ የሆነ የማይደረስበት ምጡቅ የማይጨበጥ ረቂቅ የሆነ ድንቅ ምሥጢር ነው፡፡ ሰው አምላክ ከመሆን በላይ መክበር አለን? ከወዴትስ ይገኛል? ስለዚህም በተዋሕዶ ከበረ ብለን እናምን ዘንድ እንገደዳለን ማለት ነው፡፡ “በተዋሕዶ ከበረ” የሚል ጥቅስ ከወዴት ይገኛል ካላችሁ በቦታውና በርእሱ ስንገናኝ እዘረዝርላችኋለሁ፡፡ በርካታ ጥቅሶችን አሳያችኋለሁ፡፡ ከዚህ በፊትም የገለጥሁላችሁ መሆኑን ልብ በሉ፡፡


አሁን ካሳሁን ከተዋሕዶ በኋላ ስላለው ጉዳይ ሲገልጽ “ቃልም ለቃልነቱ ቃል ነው፡፡ ስጋም ለስጋነቱ ስጋ ነው ነገር ግን ቃልም ስጋም በእንድ ሆኑ ማለት ነው” ይላል፡፡ ይህ ተዋሕዶን አይገልጥም፡፡ ተዋሕዶ ማለት እኮ ከሁለት ግብር አንድ ግብር ከሁለት አካል አንድ አካል የሆነበት ምሥጢር ነው ብለናል፡፡ ታዲያ ከተዋሕዶ በኋላ “ቃል በቃነቱ ቃል ነው ሥጋም በሥጋነቱ ሥጋ ነው” ብሎ መናገር ክህደት አይደለምን? ራሱ ካሳሁን ለተዋሕዶ ምሳሌ ብሎ ባስቀመጠው ነፍስና ሥጋ እስኪ ውሰዱት፡፡ ነፍስ እና ሥጋ በአንድ ተዋሕደውልን ሳለ ነፍሳችን በነፍስነቱ ነፍስ ነው ሥጋችንም በሥጋነቱ ሥጋ ነው ልንለው ልንለያየው እና ልንገነጣጥለው እንዴት እንችላለን? በፍጹም አይሆንም አይደረግምም፡፡





እዚሁ ገጽ ላይ ይቀጥልና “የቃል ገንዘብ ምንምን ነው ቢሉ ሳድስ ቀለም ንጉስ ባዕል ረቂቅ ምሉዕ ስፉሕ ህያው ልዑል ክቡር አምላክ ነው፡፡ የሥጋ ገንዘብ ግዕዝ ቀለም ሐየሰ ወረሰ ተለአለ ነግሠ ከብረ ነው” ይላል፡፡ ምሥጢረ ተዋሕዶን ስንነጋገር ሦስት ነገሮች ላይ ትኩረት መስጠት ይኖርብናል፡፡ በነገራችን ላይ ጌታ የተዋሐደው ሥጋ ተፈጥሮ የቆየን ሥጋ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ በሦስት ክፍሎች ስንከፋፍለው ስለ ሥጋ እና ስለመለኮት ባህርይ ለመነጋገር ያህል እንጅ ሥጋ ተፈጥሮለት ቆይቶ ያንን የተዋሐደ አይደለም፡፡ የቃላት አጠቃቀማችንን ለማብራራት ሲባል ብቻ ነው ለሦስት ክፍሎች ከፋፍየ የማሳያችሁ፡፡

፩ኛ. ቅድመ ተዋሕዶ፡፡ ይህ ጊዜ ሥጋ በሥጋነቱ መለኮትም በመለኮትነቱ ያለበት ጊዜ ነው፡፡ ከተዋሕዶ አስቀድሞ ያለው ጊዜ ነው፡፡ መለኮት ረቂቅ ነው ስፉሕ ነው ምሉዕ ነው ንጉሥ ነው ህያው ነው ባዕለ ጸጋ ነው አምላክ ነው ወዘተ እንላለን ይህ ሁሉ ገንዘቡ ነውና፡፡ ይህ ችግር የለውም፡፡ ሥጋንም እንዲሁ ነዳይ (ደሃ) ነው ተወካፊ (ተቀባይ) ነው ግዙፍ ነው ውሱን ነው ጠባብ ነው  ፍጡር ነው ወዘተ እንላለን ይህ ሁሉ ገንዘቡ ነውና፡፡ ይህ ምንም ህጸጽ የለበትም፡፡ እዚህ ጊዜ ላይ የሥጋ ገንዘብ ለቃል፤ የቃልም ገንዘብ ለሥጋ ስላልሆነ ሥጋ በሥጋነት ገንዘቡ መለኮትም በመለኮትነት ገንዘቡ ቢጠራ ምንም ችግር የለውም፡፡ እንዲያውም “ነው” ተብሎ ነው የሚገለጸውም፡፡ ሥጋም (ሰውም) ሥጋ (ሰው) ነው ይባላል፡፡ አምላክም አምላክ  ነው ይባላል፡፡ ልብ በሉ አሁንም ሥጋ ቀድሞ ተፈጥሮ ያንን ተዋሐደው ማለት አይደለም፡፡

፪ኛ. ጊዜ ተዋሕዶ ነው፡፡ ይህ መለኮት እና ሥጋ የተዋሐዱበት ድንቅ ምሥጢር የተፈጸመበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ነው የሥጋ ገንዘብ ለቃል፤ የቃልም ገንዘብ ለሥጋ የሆነው፡፡ የቃል ገንዘብ ለሥጋ የሥጋ ገንዘብም ለቃል ሲሆን በተዓቅቦ  (በመጠባበቅ) ነው፡፡ የሥጋ ገንዘቦች በሙሉ (ከኃጢአት በቀር) ለቃል ሆኑ የቃልም ገንዘቦች በሙሉ ለሥጋ ሆኑ እንጅ የሥጋ ገንዘቦች ጠፍተው ለቃልየቃል ገንዘቦችም ጠፍተው ለሥጋ አልተሰጡም አልተለወጡም፡፡ በዚህም መሠረት ዘመን የማይቆጠርለት መለኮት የሥጋን ገንዘብ ገንዘቡ አድርጎ ዘመን ተቆጠረለት፡፡ ረቂቅ ስፉህ ምሉዕ የነበረው መለኮት የሥጋን ገንዘብ ገንዘቡ አድርጎ ግዙፍ እና ጠባብ ሆነ በሦስት ክንድ ከስንዝር ተወሰነ፡፡ ረሃብ እና ጥም የማይስማማው መለኮት የሥጋን ገንዘብ ገንዘቡ አድርጎ ተራበ ተጠማ በላ ጠጣ ተባለ፡፡ ዘመን የሚቆጠርለት ሥጋ የመለኮትን ገንዘብ ገንዘቡ አድርጎ ቀዳማዊ አምላክ ዘመን የማይቆጠርለት ሆነ፡፡ የሚሞት የሚበሰብስ ሥጋ የመለኮትን ገንዘብ ገንዘቡ አድርጎ ህያው አምላክ ዘላለማዊ ገዥ ሆነ፡፡ ፍጡር የሆነው ሥጋ የመለኮትን ገንዘብ ገንዘቡ አድርጎ ፈጣሪ አምላክ ሆነ፡፡ ይህ ሁሉ የተፈጸመው በተዋሕዶ ምስጢር ነው፡፡ ለዚህም ነው ሰው አምላክ ሆነ አምላክ ሰው ሆነ ማለታችን፡፡ ሰው አምላክ ከመሆን በላይ ምን መክበር አለና ነው “በተዋሕዶ ከበረ” ማለት ኑፋቄ ሊሆን የሚችለው? በተዋሕዶ ይህ ሁሉ አልተደረገም ካላችሁ ምንፍቅናችሁ ያኔ ይገለጣል፡፡

እዚህ ላይ ተዋሕዶው ያለመለየትያለመቀላቀልያለመለወጥ፣ ያለመደመር፣ ያለማደርያለመጎራበት በፍጹም ተዋሕዶ በተዓቅቦ (በመጠባበቅ) ነው፡፡ እዚህ ላይ “ነው” ተብሎ መነገር ይቀርና “ሆነ” በሚል ቃል ይነገራል፡፡ በዚህም መሠረት “ሰው ነው አምላክ ነው” መባል ቀርቶ “አምላክ ሆነ ሰው ሆነ” ይባላል ማለት ነው፡፡

፫ኛ. ድኅረ ተዋሕዶ፡፡ ይህ ከተዋሕዶ በኋላ ያለ ጊዜ ነው፡፡ አምላክ ሰው ሆኗል ሰውም አምላክ ሆኗል፡፡ ከዚህ በኋላ መለኮቱ እንዲህ አደረገ ሥጋው እንዲህ አደረገ ብሎ መለያየት መከፋፈል ክህደት ነው፡፡ እሳትና ብረት ተዋሕደው የጋለ ብረት ይሆናል፡፡ በዚህ የጋለ ብረት ላይ ይህ ብረት ነው ይህ እሳት ነው እንደማንል ሁሉ ክርስቶስን (ሥግው ቃል) ንም እንዲሁ ሥጋው ይህ ነው መለኮቱ ይህ ነው አንልም ምክንያቱም ሥጋና መለኮት አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆኗልና ነው፡፡ “በ” የምትል ፊደል ጨምረን “በመለኮቱ”፣ “በሥጋው” እያልን እንገልጻለን እንጅ “በ” ን አጥፍተን “መለኮቱ”፤ “ሥጋው” ማለት ግን ክህደት ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱ የሰማይ እና የምድርን ያህል የምሥጢር ልዩነት አላቸው፡፡ “ሥጋው ተራበ” ማለት እና “በሥጋው ተራበ” ማለት በጣም ይለያያል፡፡ “ሥጋው ተራበ” ስንል ሥጋ ና መለኮት መዋሐዳቸውን አያመለክትም አያሳይም፡፡ ለምሳሌ እኔ ሥጋየ ተራበ እንደምለው ዓይነት ነው የሚሆነው፡፡ “በሥጋው ተራበ” ስንል ግን መለኮት እና ሥጋ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነዋል ማታችን ነው፡፡ ይህ አንድ አካል አንድ ባሕርይ የሆነ አምላክ በሥጋው ተራበ እንላለን፡፡ ይህም ማለት በአጭር ቃል “በሥጋው ተራበ” ማለት “መለኮት የተዋሐደው ሥጋ ተራበ” ማለታችን ነው፡፡

ስለዚህ የቃል ገንዘብ በሳድስ የሥጋ ገንዘብ በግዕዝ ፊደላት ይገለጻሉ የሚለው አነጋገር መጀመሪያ በዚህ መልኩ ተዋሕዶን መዘርዘር ሳያስፈልግ አይነገርም፡፡ ከተዋሕዶ በኋላ ሳድስ ቀለም ለቃል ግዕዝ ቀለም ለሥጋ ማለት አይቻልም፡፡ “ከበረ” የሚለው ቃል እኮ ሰው አምላክ ሆነ አምላክ ሰው ሆነ የሚለውን ድንቅ ምሥጢር ለማሳየት ካልሆነ በቀር ለቃል የሚቀጸል ቃል አይደለም፡፡ ሰው አምላክ ከመሆን በላይ ምን መክበር አለና ነው “በተዋሕዶ ከበረ” ቢባል ስህተት የሚሆነው? የቻላችሁ መልሱልኝ ያልቻላችሁ ደግሞ ሊቅ የምትሏቸውን ወገኖቻችሁን ጠይቁ፡፡

በጣም ያሳዘነኝ ገጽ ፲ ላይ የተጻፈው ነው፡፡ ቃሉ እንዲህ ይላል “ወልደ አብ ወልደ ማርያም በመንፈስ ቅዱስ ከበረ ይህቺ ናት ሐይማኖት” ይላል፡፡ “ከበረ” የሚለው ቃል በግዕዝ ቀለም ስለሆነ የተገለጸው ለቃል አይቀጸልም ስትለን አልነበረም እንዴ ምን ነካህ ታዲያ “በመንፈስ ቅዱስ ከበረ” ብለህ የምትደመድመው? “ወልደ አብ ወልደ ማርያም በተዋሕዶ ከበረ ሃይማኖት ይቺ ናት” ማንም ያልቀየራት ማንም ያልበረዛት ቀጥተኛ ሃይማኖት፡፡ አምላክ ምኑ ይከብራልና ነው “በተዋሕዶ ከበረ” የምትሉ እያሉ አባ ማርቆስን (ምሥራቅ ጎጃም ሊቀጳጳስ) ጨምሮ ሲሟገቱን ነበር እነርሱ ግን “በመንፈስ ቅዱስ ከበረ” ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሆነ አልገባቸውም መሰል፡፡ ታዲያ አምላክ ምኑን ይከብራልና ነው “በመንፈስ ቅዱስ ከበረ” የምትሉን? እኛ በተዋሕዶ ከበረ ስንል “ሰው አምላክ” ከመሆን የበለጠ ክቡርነት የለውምና ነው፡፡ እናንተ ግን “በመንፈስ ቅዱስ ከበረ” የምትሉን “ወልድ እንደ አብ እንደ መንፈስ ቅዱስ አምላክ ገዥ ፈጣሪ የሆነው በመንፈስ ቅዱስ ቅብዓትነት ነው” ለማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ፍጹም ክህደት ነው፡፡ እስኪ ልጠይቃችሁ ለነገሩ መልስ አትሰጡኝም እንጅ፡፡ ወልድ ቅብዓተ መንፈስ ቅዱስን ባይቀበል ኖሮ አምላክ አይሆንም ነበርን? አዎ እንደምትሉኝ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ለዚህም እኮ ነው አርዮሳውያን ናችሁ ማለታችን፡፡ አባቶቻችን “በመንፈስ ቅዱስ ከበረ” የሚለውን ትምህርት አውግዘውታል፡፡ “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በእርሱ አጋዥነት ድንቅ ተአምራትን ያደርግ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ ከበረ የሚለው፤ ርኩሳን አጋንንትን በማውጣት ጊዜም ኃይልን ተአምራትን ከመንፈስ ቅዱስ ይቀበላል፤ በሰውም የአምላክነትን ሥራ ይሠራል የሚለው፤ መንፈስ ቅዱስ የባሕርዩ ነው፤ የአምላክነትንም ሥራ እርሱ ራሱ ይሠራል የማይል ቢኖር ውጉዝ ይሁን” ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ ፸፫÷፵፱ ይላል፡፡ እዚህ ላይ እነዚህን ፬ ነጥቦች ማንሣት እንችላለን፡፡
፩. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በእርሱ አጋዥነት ድንቅ ተአምራትን ያደርግ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ ከበረ የሚለው ቢኖር ውጉዝ ይሁን፡፡
፪. ርኩሳን አጋንንትን በማውጣት ጊዜም ኃይልን ተአምራትን ከመንፈስ ቅዱስ ይቀበላል የሚለው ቢኖር ውጉዝ ይሁን፡፡
፫.  በሰውም የአምላክነትን ሥራ ይሠራል  የሚለው ቢኖር ውጉዝ ይሁን፡፡
፬. መንፈስ ቅዱስ የባሕርዩ ነው  የማይል ቢኖር ውጉዝ ይሁን፡፡ የሚሉ ናቸው፡፡

ስለዚህ “ወልደ አብ ወልደ ማርያም በመንፈስ ቅዱስ ከበረ” የሚለው ኑፋቄ የተወገዘ ትምህርት ነው፡፡ ስለዚህ “ወልደ አብ ወልደ ማርያም በመንፈስ ቅዱስ ከበረ ይህቺ ናት ሐይማኖት” ማለት ሀሰት ነው፡፡ ትክክለኛዋ የአባቶቻችን ጥንታዊቷ ቀጥተኛ ሃይማኖት “ወልደ አብ ወልደ ማርያም በተዋሕዶ ከበረ ነው ሃይማኖቲቱም ይህቺ ናት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ”
ይቀጥላል፡፡
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ኅዳር ፯ / ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment