Monday, November 27, 2017

”በሃይማኖታችን አንደራደርም” ደጀን ደብረ አሚን



፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ደጀን ከተማ በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሥር የምትገኝ አነስተኛ ከተማ ናት፡፡ ደጀን የከተማዋም የወረዳዋም መጠሪያ ስም ነው፡፡ ጎጃምን ማየት የሚፈልግ ሁሉ የዓባይን ድልድይ ተሻግሮ በመጀመሪያ የሚያገኛት ደጀንን ነው፡፡ ዋና ዓላማየ ደጀንን ማስተዋወቅ አይደለም፡፡ ደጀን ደብረ አሚን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ላይ ትናንትና እሁድ ኅዳር ፲፯/ ፳፻፲ ዓ.ም ፀረ ተሐድሶ ጉባዔ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዚህ ለሁለተኛ ጊዜ በተዘጋጀው ጉባዔ ላይ የደብሩ አስተዳዳሪ የደብሩ አገልጋይ ካህናት ዲያቆናት እና በርካታ ህዝበ ክርስቲያን ተገኝቶ ነበር፡፡ በምሥራቅ ጎጃም ሐገረ ስብከት እንዲህ ያለ ጉባዔ ሲዘጋጅ ደጀን የመጀመሪያዋ መሆኗ ነው፡፡ ይህ ጉባዔ ያስፈለገበት ምክንያት፡-

፩ኛ. ሳምንት የተዘጋጀው ጉባዔ አዳራሽ ውስጥ ስለነበረ መከታተል እየፈለገ በቦታ ጥበት ምክንያት ያልታደመውን ህዝበ ክርስቲያን ለማሳየት፡፡
፪. በመጀመሪያው ጉባዔ ከሕዝበ ክርስቲያኑ የተነሡ ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው ሀሳቦችን ውሳኔ ለመስጠት፡፡
፫. የፀረ ተሐድሶ ኮሚቴውን ህጋዊነት ለማሳወ፤ በህዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ ጥቆማ ተደርጎ ምርጫው ተካሂዶ ከሰበካ ጉባዔው ፈቃድ እንዲያገኝ ለማስደረግ፡፡
፬. ደጀን ደብረ አሚን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን እና አበ ብዙኃን አብርሃም ቤተክርስቲያን  ውስጥ ሳይታወቁ እያገለገሉ ያሉ የቅባት ካህናትንና ዲያቆናትን መሪጌቶችን ወዘተ ለይቶ ከጠቅላይ ቤተክህነት በተላለፈው መመሪያ መሠረት ለማስወገድ
፭. ምሥራቅ ጎጃም ሐገረ ስብከትን እያመሳት ያለውን የቅባት ኑፋቄ በማጋለጥ የክህደት መጻሕፍትንም በሚሰራጩ ላይ ክስ ለመመስረት ጥቆማ እንዲካሄድ ወዘተ ለማድረግ ነበር፡፡
በዚህም መሠረት ጉባዔው ከቀኑ ፱ ሰዓት ጥቂት ደቂቃዎች ቀደም ብሎ በፀሎት ተጀምሯል፡፡ ደጀኖች ለምሥራቅ ጎጃሞች አርአያነታቸውን በይፋ አሳይተዋል፡፡
ደጀን ላይ በቤተክርስቲያን ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ሥራ እየሠራ የሚገኘው መምህር ጌታቸው ተፈሪ የፀረ ተሐድሶውን ዋና ዓላማ ከዘረዘረ በኋላ ተሐድሶ መናፍቃን እነማን እንደሆኑ፣ ትምህርታቸው ምን እንደሚመስል በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲሁም በሐገራችን ያላቸውን እንቅስቃሴ በሚገባ ዘርዝሮ አብራርቶ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አድርጎ አቅርቧል፡፡ ሙሉውን ውይይት ከዩቱዩብ ላይ እንድታገኙት በራሴ አድራሻ እጭነዋለሁ ተከታተሉን፡፡
መምህር ጌታቸው ተፈሪ ለመርኃ ግብሩ የተመደበለትን ሰዓት እንደጨረሰ ለቀጣዩ መርኃ ግብር ፈጻሚ መድረኩን ለቋል፡፡ በቀጣይነት በህዝቡ በተነሣው ጥያቄ መሠረት ስለ “ቅባት እና ተዋሕዶ” ልዩነት እንዲገልጹ ከዚያ ውጭ እንዳያስተምሩ ተብለው ለቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ መድረኩን ሰጧቸው፡፡ አስተዳዳሪው አባ ማርቆስ የመደቧቸው የጉንደ ወይን ተወላጅ ናቸው፡፡ ደግመው ደጋግመው ሲጠየቁ የሚመልሱት ነገር ቢኖር ይኸው ነው “በጎንቻነቴ አላፍርም” የሚል፡፡  ሰው በተወለ፤ደበት ቦታ ማፈርም አይገባውም ማፈር ካለበትስ ማፈር ያለበት “ወልድ ፍጡር” በሚለው ክህደቱ ነው፡፡ አባ ሳሙኤል ይባላሉ፡፡ ይህን ስም ያገኙት ፍርድ ቤት ነው፡፡ በቀድሞ ስማቸው አባ ወልደ ሥላሴ ይባላሉ፡፡ ደብረ ማርቆስ፣ ረቡዕ ገበያ አካባቢ ያ ሰዎች የሚያውቋቸው አባ ወልደ ሥላሴ በሚለው ስማቸው ነው፡፡ ዛሬ ደጀን ሲገቡ ግን ፍርድ ቤት በመሄድ ስማቸውን አባ ሳሙኤል ብለው አስቀይረውታል፡፡ ስም የማስቀየራቸው ጉዳይ ባይገባንም ባያገባንም ባይመለከተንም ማለት ነው፡፡ ያገባን ይመለከትን ይሆናል ግን…፡፡
“ወስክ ለነ አሚነ፤ እምነትን ጨምርልን” በሚል ርእስ መነሻነት የሆነ መጽሐፍ እያነበቡ ትንሽ ማብራራት ጀመሩ፡፡ ግን ፈርተዋል ውስጣቸው ሰላም አይደለም፡፡ መምህር ጌታቸውን በተለይ የፈሩት ይመስላሉ፡፡ “ጌችየ ና ጠጋ በለኝ” አሉትና ከርቀት ቦታ አስጠርተው አጠገባቸው እንዲቀመጥ አደረጉ፡፡ የሚናገሩትንም ነገር እንዲያረጋግጥላቸው ዐሥሬ “አይደል ጌችየ” ይላሉ፡፡ እምነት ብዙ ነው ሃይማኖት ግን አንዲት ናት አሉ፡፡ ተዋሕዶ ተወልዷል እያሉ ብዙ ጊዜ ተናገሩ፡፡ እምነቲትም ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ናት አሉ ወደው ሳይሆን ፈርተው፡፡ ትንሽ ቆዩና ሰው ባመነው ነገር ሁሉ ይድናል ብለው ጣልቃ አስገቡ፡፡ ህዝበ ክርስቲያኑ እያንዳንዷን ነገር እየመዘገበ እየያዛት ነው፡፡ በጣም ተጠንቅቀው ነው የሚናገሩት በጣም ሲበዛ፡፡ “ ወልድ ዋሕድ በተዋሕዶ ከበረ” ሳይሆን “ተዋሕዶ ተወለደ” ነው የሚሉ፡፡ ምእመናን ግን “ተዋሕዶ” የሚለውን ስም ከአባ ሳሙኤል በመስማታቸው ብቻ ሳይወዱ ቢናገሩትም በመጠኑ ደስታ ፈጥሮባቸዋል፡፡ “ተዋሕዶ ተወለደ” ቅባቶችም የሚሉት ብሒል ነው፡፡ በነገራችን ላይ መንፈሳዊ ኮሌጅ ገብተው ስለወጡ የማስተማር ዘዴያቸው ያው እንደሌሎቹ ሁሉ “ከቃሉ ጋር ናችሁ ከእኔ ጋር ናችሁ” ወዘተ በሚሉ አዝማቾች የተደገፈ ነበር፡፡

አባ ሳሙኤል የተሰጣቸውን ርእስ ትተው ሰዓታቸውን ለመጨረስ ብቻ የሆነ ያልሆነውን ሲናገሩ ምእመናን ርእሳቸውን ለምን ይለቃሉ በሚል አስተያየት ይጎርፍ ጀመር፡፡ የምእመናን ዓላማ የነበረው አስተዳዳሪውን በትክክል እምነታቸውን ለይተው ቅባት ከሆኑ ለማስወገድ ነበር ይህ ደግሞ የጠቅላይ ቤተክህነቱ መመሪያ ነው፡፡ ምእመናን የአባ ሳሙኤልን ትምህርት መስማት ስላልፈለጉ እንዲጨርሱ መልእክት አስተላለፉ በዚያም መሠረት ሰዓት አልቋል ያጠናቁ ተብለው የተሰጡትን ርእስ አንድ ነገር ሳይነኩ ከመድረክ ወረዱ፡፡

ከዚህ በኋላ ውሳኔ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት እንዲደረግ ሊቀ ዲያቆን ደሳለኝ (ደሴ) መድረኩን ተረከበ፡፡ ከዚያ በፊት ግን ከምእመናን የቀረቡ አስተያየቶች እንዲነበቡ ተደረገ፡፡ ምእመናን የተሰማቸውን ሁሉ በጥያቄ መልኩ በወረቀት እየጻፉ አስተላለፉ፡፡ ከተነሡት ነጥቦችም መካከል፡
፩. አባ ሳሙኤል እርስዎ የቤተክርስቲያናችን አስተዳዳሪ ነዎት፡፡ ተወልደው ያደጉት ጉንደወይን ነው የመነኮሱትም የክህደት መጻሕፍት አሳታሚዋ ቆጋ ኪዳነ ምሕረት ገዳም ነው፡፡ እርስዎ ተጠምቀዋል ወይስ አልተጠመቁም?
፪. “ንቁም በበሕላዌነ፤ በያለንበት እንቁም” ብለው ቅዱስ ገብርኤል መላእክትን ያረጋጋበትን ቃል “እምነትን ጨምርልን” በሚለው ትምህርትዎ ላይ ተናግረዋል፡፡ በያለንበት ሲሉ በየትኛው እምነት ማለትዎ ነው?
፫. አባ ሳሙኤል ሃይማኖት አንዲት ናት ብለው ሲናገሩ ቆይተው ሰው ባመነበት ነገር ይድናል ብለው የደመደሙት ምን ለማለት ፈልገው ነው?
፬. እንዲያስተምሩ መርኃ ግብር የተሰጠዎ ስለ ቅባት እና ተዋሕዶ ስለምሥጢረ ሥላሴ ሊያስተምሩ ነበር ለምን ርእስዎን ቀየሩ?
፭. ቅባት የሆንን ሰዎችን እንደ ባሶሊበኖች በኮንትራት መኪና ወስዳችሁ አስጠምቁን፡፡
፮. አባ ማርቆስ ለደጀን ለቤተክርስቲያናችን ስድስት ሽህ ብር ተሰጥቷቸዋል የሚባል ወሬ እየሰማን ነው ይህ ምን ያህል እውነት ነው? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች ዋና ዋናዎች ነበሩ፡፡

ከዚህ በኋላ እነዚህ ጥያቄዎች መልስ እንዲሰጥባቸው ተደረገ፡፡ አስተዳዳሪው መመለስ ያለባቸው አሁን ነው የሚል እና መርኃ ግብራችንን ስንጨርስ ነው መናገር ያለባቸው የሚል ሁለት ሃሳብ ተነሣ፡፡ በዚህም መሠረት ለምእመናን ሃሳቡ ተዘርግቶ አባ ሳሙኤል በመጨረሻ እንዲናገሩ ስለወሰነ አባ ሳሙኤል ሳይመልሱ ተቀመጡ፡፡
ሊቀ ዲያቆን ደሳለኝ ውሳኔ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች ዘረዘረ፡፡ ውሳኔ እንዲሰጥባቸው የተፈለጉ ጉዳዮችም፡
፩. ሀገረ ስብከታችን ለተሐድሶ እና ለቅባቶች እንዲሁም ለዘመድ አዝማድ መሰብሰቢያ ስለሆነ ራሳችን ከቤተክርስቲያናችን ገንዘባችንን እየላክን ቤተክርስቲያናችንን ለሚያፈርሱ አካላት ድጋፍ ማድረግ የለብንም፡፡ ስለዚህ ከወረዳችን ወደ ሀገረ ስብከት የሚላከው ሃያ % ክፍያ መቆም አለበት ወይስ የለበትም?
፪. ፀረ ተሐድሶ ኮሚቴ እንዲዋቀር የአባላት ምርጫ ማካሄድ፡፡
፫. የቅባት  ካህናት እና ዲያቆናት ተለይተው በስም ዝርዝር እንዲቀርቡ እና ትምህርት ተሰጥቷቸው አምነው የሚመለሱት እንዲመለሱ አምነው መመለስ የማይችሉት ከቤተክርስቲያናችን እንዲለዩ ማድረግ፡፡
፬. ይህ ጉባዔ ድጋሜ መካሄድ አለበት ወይስ የለበትም ይካሄድ ከተባለ በየስንት ጊዜ፡፡
ወዘተ የሚሉ ሃሳቦች ውሳኔ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት ህዝበ ክርስቲያኑ የሚመጣውን ሁሉ ስለሃይማኖታችን እንቀበላለን፡፡ በሃይማኖታችን ድርድር አናውቅም ወልድ ዋሕድ በተዋሕዶ ከበረ ስንል በኖርንበት ቤተክርቲያን ቅባት የሚባል እምነት ሊመራን አይገባም፡፡
ህዝበ ክርስቲያኑ በእያንዳንዱ ርእሰ ጉዳይ ላይ ሰፊ ማብራሪያ እየሰጠ የውሳኔ ሃሳቡንም አቅርቧል፡፡ በዚህም መሠረት ውሳኔዎች በሙሉ ድምጽ የተወሰኑ ሲሆን የተጠየቁ ጥያቄዎችም ምላሽ አግኝተዋል፡፡
በዚህም መሠረት፡
፩. ሀገረ ስብከታችን ለተሐድሶ እና ለቅባቶች እንዲሁም ለዘመድ አዝማድ መሰብሰቢያ ስለሆነ ራሳችን ከቤተክርስቲያናችን ገንዘባችንን እየላክን ቤተክርስቲያናችንን ለሚያፈርሱ አካላት ድጋፍ ማድረግ የለብንም፡፡ እኛ ተዋሕዶዎች ነን እኛ ተዋሕዶዎች ደግሞ ለቅባቶች ገንዘብ አንሰጥም፡፡ ስለዚህ ከወረዳችን ወደ ሀገረ ስብከት የሚላከው ሃያ % ክፍያ መቆም አለበት፡፡ በዚህ ጉዳይ ሰበካ ጉባዔውም የተጣለብን ሰባ አምስት ሺህ ብር ነው ብሎ ገልጦ እንደማይከፍል አሳውቋል፡፡
፪. ፀረ ተሐድሶ ኮሚቴ እንዲዋቀር የአባላት ምርጫ ተካሂዷል፡፡ በዚህም መሠረት ሰባት አባላት ያለው የፀረ ተሐድሶ ኮሚቴ ከካህናት እና ከምእመናን የተውጣጣ ሆኖ ተሰይሟል፡፡ ይህ ኮሚቴ ህጋዊ እውቅና አግኝቶ እንዲንቀሳቀስ ሰበካ ጉባዔው እውቅና እንዲሰጠው ይደረጋል፡፡
፫. የቅባት  ካህናት እና ዲያቆናት ተለይተው በስም ዝርዝር እንዲቀርቡ እና ትምህርት ተሰጥቷቸው አምነው የሚመለሱት እንዲመለሱ አምነው መመለስ የማይችሉት ከቤተክርስቲያናችን እንዲለዩ ማድረግ፡፡ ደጀን ውስጥ የሚያገለግሉ ካህናት ዲያቆናት መምህራን ሁሉ ከየት እንደመጡ በፀረ ተሐድሶ ኮሚቴው መረጃ ተሰብስቦ ቅባት መሆናቸው ከተረጋገጠ በመረጃ እየተደገፈ እንዲቀርብ እና እንዲወገዱ ይደረጋል፡፡ አንድም ቅባት በቤተክርስቲያናችን ውስጥ እንዲያገለግል አንፈልግም፡፡ ቤተክርስቲያናችንን እኛ እናስተዳድራታለን፡፡ የተወገዙ መጻሕፍትን እያሰራጩ የሚገኙ አካላትም እየተያዙ ህጋዊ ክስ እንዲመሠረትባቸው ይደረጋል፡፡
፬. ይህ ጉባዔ ድጋሜ መካሄድ አለበት ወይስ የለበትም ይካሄድ ከተባለ በየስንት ጊዜ ይካሄድ የሚለው ሃሰብ በጣም ብዙ ሃሳብ የቀረበበት የነበረ ሲሆን በወር ሁለት ጊዜ በየሁለት ሳምንቱ መካሄድ አለበት ተብሎ ተወስኗል፡፡
እነዚህ ውሳኔዎች በሙሉ ድምጽ ከተወሰኑ በኋላ የተጠየቁ ጥያቄዎች ተመልሰዋል፡፡
፩. አባ ሳሙኤል እርስዎ የቤተክርስቲያናችን አስተዳዳሪ ነዎት፡፡ ተወልደው ያደጉት ጉንደወይን ነው የመነኮሱትም የክህደት መጻሕፍት አሳታሚዋ ቆጋ ኪዳነ ምሕረት ገዳም ነው፡፡ እርስዎ ተጠምቀዋል ወይስ አልተጠመቁም? የሚለውን ጥያቄ የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ አባ ሳሙኤል እርግጥ ነው ተወልጀ ያደግሁት ጎንቻ ነው፡፡ በጎንቻነቴ ደግሞ አላፍርበትም፡፡ አሁንም አባልነቴ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ነው፡፡ ቆጋ አመንኩሸዋለሁ ቆብ ጭኘለታለሁ የሚል ካለ ይምጣ፡፡ እኔ እኮ ይህን ለቅቄ ገዳም መሄድ እችላለሁ፡፡ በማለት በማኩረፍ ዓይነት መልሰዋል፡፡ ጥምቀት አንዲት ናት በቃ፡፡ ብለዋል ሆኖም ግን እውነቱን እስካላሳወቁን ድረስ ቤተክርስቲያናችንን ሊያስተዳድሩ አይችሉም በሚል ምእመናን አቋም ይዘዋል፡፡ የመለሱት መልስ በሙሉ አባ ማርቆስ የሚናገሩት ስለሆነ ወደፊትም ገና ይጠየቃሉ ወይም ይባረራሉ፡፡
፪. “ንቁም በበሕላዌነ፤ በያለንበት እንቁም” ብለው ቅዱስ ገብርኤል መላእክትን ያረጋጋበትን ቃል “እምነትን ጨምርልን” በሚለው ትምህርትዎ ላይ ተናግረዋል፡፡ በያለንበት ሲሉ በየትኛው እምነት ማለትዎ ነው? የሚለውን ሲመልሱ እኔ ለማለት የፈለግሁት ብለው በመላእክት ዘንድ የነበረውን ታሪክ ተናግረዋል፡፡
፫. አባ ሳሙኤል ሃይማኖት አንዲት ናት ብለው ሲናገሩ ቆይተው ሰው ባመነበት ነገር ይድናል ብለው የደመደሙት ምን ለማለት ፈልገው ነው? ይህንን ሲመልሱ ሃይማት አንዲት ናት ግን የቀን አቆጣጠሩ ላይ ስታትስቲክ ነውና ልዩነት አለ፡፡ ብለው አባ ማርቆስ ሃያ ስምንት ሃያ ዘጠኝ ማት ካሌንደር ነው ያሉትን አሻሽለው አለዝበው ለመናገር ሞክረዋል፡፡ በዚህን ጊዜ በዝምታ ማለፍ ያልቻለው መምህር ጌታቸው ተፈሪ አባታችን ይህ የስታትስቲክስ ወይም የካሌንደር ልዩነት አይደለም የሃይማኖት ልዩነት እንጅ ብሎ ተናገረ፡፡
፬. እንዲያስተምሩ መርኃ ግብር የተሰጠዎ ስለ ቅባት እና ተዋሕዶ ስለምሥጢረ ሥላሴ ሊያስተምሩ ነበር ለምን ርእስዎን ቀየሩ? የሚለውን ሲመልሱ ስለምሥጢረ ሥላሴ የማታውቁ ካላችሁ ሥላሴ አንድም ሦስትም ናቸው፡፡ መለኮታዊ ባሕርያቸውን ግን እኔ ፍጡሩ መርምሬ አላውቅም፡፡ የሚል አጭር መልስ መልሰዋል፡፡ ተዋሕዶን በተመለከተም ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም ሥጋዋን ተዋህዶ ተወለደ ማለት ነው ብለው አባ ማርቆስ “ሃይማኖቱ ወልደ አብ ወልደ ማርያም ተወለደ” ነው ብለው ያስተማሩትን ደግመውታል፡፡ እምነታችን “ወልደ አብ ወልደ ማርያም በተዋሕዶ ከበረ” ነው አለቀ፡፡ እርሳቸው ግን ፈርተው ነው ያለፉት፡፡
፭. ቅባት የሆንን ሰዎችን እንደ ባሶሊበኖች በኮንትራት መኪና ወስዳችሁ አስጠምቁን፡፡ የሚለውን ትልቅ ሃሳብ ወደፊት መልስ የሚሰጥበት ይሆናል፡፡ እንጠመቅ ብሎ የመጣን ሰው እናስጠምቃለን፡፡
፮. አባ ማርቆስ ለደጀን ለቤተክርስቲያናችን ስድስት ሽህ ብር ተሰጥቷቸዋል የሚባል ወሬ እየሰማን ነው ይህ ምን ያህል እውነት ነው? የሚለውን እውነት ነው ተብሏል፡፡ አባ ማርቆስ ይህን የምታዩትን ህንጻ (የንዋየ ቅድሳት ማስቀመጫ ባለ አንድ ፎቅ ግንባታ ነው) ልናሠራ የመሠረት ድንጋይ ሊያኖሩልን መጡ፡፡ ከዚያም መድረኩን ይዘው ገንዘብ አሰባሰቡልን፡፡ በመጨረሻም የመጣሁበትን ገንዘብ ክፈሉኝ አሉ ስንት ነው አልናቸው ስድስት ሽህ ብር አሉን አራት ሽህ ብር ለምነውልን ነበር ሁለት ሺህ ብር በፊት ከሰበሰብነው ላይ ቀንሰን ስድስት ሺህ ብር ሰጠናቸው ሄዱ ብለው ህንጻ አሠሪ ኮሚቴው ተናግሯል፡፡
ይህን በመሰለ መልኩ ጉባዔው ደስ በሚል መልኩ ተካሂዶ መርኃ ግብሩ ተፈጽሟል፡፡ ከዚህ በኋላ የተወሰኑ ሃሳቦችን ለመለዋወጥ ሞክረናል፡፡ በተለይ ወደፊት ምን ማድረግ አለብን የሚለውን ጉዳይ በመጠኑም ቢሆን ለመነጋገር ሞክረናል፡፡
************************
በቀጣይ ምን ማድረግ ይገባናል!
፩. የተመረጠው ፀረ ተሐድሶ ኮሚቴ የሰበካ ጉባዔውን እውቅና እንዲያገኝ እና ህጋዊ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ፡፡ ከዚያም በአጎራባች ቀበሌዎች ከደጀን ከተማ ወጣ ብሎ #ጉባያ #የትኖራ #ሰብሸንጎ #ተዝካረ_ማርያም እና ሌሎች ቦታዎችም ላይ ተመሳሳይ መርኃ ግብሮች እንዲካሄዱ ማመቻቸት፡፡
፪. አጎራባች ወረዳዎች ይህንን ተሞክሮ አስፍተው እንዲሠሩበት ማድረግ፡፡ በተለይ በዚህ ሃሳብ ላይ ተመሳሳይ አቋም ያላቸው #እነማዮች መርኃ ግብር እንዲያደርጉ መነጋገር፡፡ መርኃ ግብሮችን ስናካሂድ አንድነት ጉባዔ ማድረግ፡፡ #ደጅን ሲያዘጋጅ ሌሎች ጎረቤት ወረዳዎችን መጥራት #እነማዮች ሲያካሂዱም #ከደጀን ተሰባስበን መሄድ፡፡ ይህ ግንኙነታችንን ያጠናክራል አንድነታችንን ያፀናል ለሌሎችም ማንቂያ ይሆናል፡፡
፫. #ታህሳስ_ስምንት የአቡነ ተክለ አልፋ በዓል #ዲማ_ቅዱስ_ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን በድምቀት ይከበራል፡፡ ይህንን ምክንያት አድርገን #ታህሳስ_ሰባት ዲማ ተገናኝተን ስለ ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ዙሪያ በጥልቀት ብንወያይ የሚሉ ናቸው፡፡
በዚህ መሠረት ወደፊትም ጉባዔዎች ይካሄዳሉ የተኛህ ንቃ ማለት አሁን ነው፡፡ ተሐድሶ መናፍቃን “ተሐድሶ የለም” እያሉ ነው ለዚህ ደረጃ የደረሱት፡፡ ዛሬ የምሥራቅ ጎጃም ቅባታዊ ተሐድሶ ደግሞ “ቅባት የለም ቅባት ምሥጢር እንጅ ሃይማት አይደለም” እያሉ ነው እየቀሰጡ የሚገኙት፡፡ እኛ አሁንም ወደፊትም የምንታገለው ቤተክርስቲያናችን ውስጥ ሆነው የቅባት ምንፍቅናን የሚዘሩት ሰዎች ላይ ነው፡፡ ወጥተው ከቤተክርስቲያኒቱ ተለይተው እንደሌሎች እምነቶች የራሳቸውን ትምህርት ማስተማር መብታቸው ነው፡፡ በቤታችን ግን አንፈቅድም፡፡ በዚህ ዙሪያ ሰፊ ተጋድሎ ይጠብቀናል፡፡ ትናንትና ወደ ደጀን ስንሄድ አዋበል ወረዳ ባለች አንዲት ቀበሌ ላይ ሰንጋ ታርዶ እየጠበሱ ሲበሉ ስናይ በጣም አዝነናል፡፡ የጾም መያዣቸው ነው ያደጉበት ነው እነዚህ ሰዎች አይፈረድባቸውም ጾሙ የሚገባው ኅዳር ዐሥራ ዘጠኝ ነው እየተባሉ ያደጉ ሰዎች ናቸው፡፡ ታዲያ ይህ እውቀት በማጣጡ የተነሣ የጠፋውን መንጋ መሰብሰብ አይጠበቅብንምን? ይህ ቅባት የጠባለውን ምንፍቅና በመጠኑም ቢሆን ለህዝቡ እውቅና እየፈጠርን ስለሆነ ሁላችሁም ለተዋሕዶ ሃይማኖታችን ዘብ እንቁም፡፡ ቅባቶች በአባ ማርቆስ ሰብሳቢነት የአቋም መግለጫ ማውጣታቸውን እንዳትዘነጉ፡፡ ሙሉውን የአቋም መግለጫ ከዚህ ሊንክ ተከታተሉት፡፡ https://www.youtube.com/watch?v=iXQoaIzlgkU ማኅበረ ቅዱሳን እና ዲማ በምሥራቅ ጎጃም ሐገረ ስብከት እንቅፋት እንደሆነባቸውና እነዚህ ሁለቱ ከፍተኛ ቁጥጥር ሊደረግባቸው እንደሚገባ ነው የመከሩ፡፡ አዳምጡት አደራ!
የተያያዘውን ቪዲዮ ተመልከቱት የተቀነጫጨበ ነው አጭር እንዲሆን ለማድረግ በማሰብ፡፡ ሙሉውን በዩቲዩብ አድራሻየ ላይ አስቀምጥላችኋለሁ፡፡ ዩቲዩብ ላይ ገብታችሁ Melkamu beyene ብላችሁ ፈልጉ፡፡
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ኅዳር ፲፰ / ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment