Thursday, November 23, 2017

መሠረተ ሐይማኖት ወይስ መሠረተ ክህደት? ክፍል ፲



፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ዛሬ ከገጽ ፳፩ ጀምረን  ያሉ ስህተቶችን በማስረጃ እንመለከታለን፡፡ በፎቶ ከስር ስለማያይዝላችሁ ሙሉውን ማንበብ ትችላላችሁ እኔ ግን ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ብቻ ነው ትኩረት የማደርገው፡፡
ካሳሁን ምናሉ “መሠረተ ሐይማኖት” በተሰኘው የክህደት መጽሐፉ  ገጽ ፳፩ ላይ “ቃልን በስጋ ርስት ትሑት ነዳይ ካላልነው፡፡ ማወራረስ አይቀርብንም ተዋሕዶ አይጎላብንም ቢሉ፡፡ አይጎላብንም በቅርብዓት እንመላዋለን፡፡ በቅብአት እንዴት እንመላዋለን ቢሉ፡፡ ይህ ስጋ ሲፈጠር ንዴት ትሕትና ያድርበት ነበር፡፡ ይህ አንዴት ትህትና ያድርበት የነበረ ስጋ ከቃል ሲዋሐድ ጊዜ ሳይሻ መንፈስ ቅዱስ ቢያድርበት ንዴት ትሕትና ቀረለት” ይላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ብዙ ጊዜ ስለተነጋገርን መድገሙ አስፈላጊ መስሎ አልታየኝም፡፡ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ እንዳንልማ የተወገዘ ሃይማኖት ነው  “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በእርሱ አጋዥነት ድንቅ ተአምራትን ያደርግ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ ከበረ የሚለው፤ ርኩሳን አጋንንትን በማውጣት ጊዜም ኃይልን ተአምራትን ከመንፈስ ቅዱስ ይቀበላል፤ በሰውም የአምላክነትን ሥራ ይሠራል የሚለው፤ መንፈስ ቅዱስ የባሕርዩ ነው፤ የአምላክነትንም ሥራ እርሱ ራሱ ይሠራል የማይል ቢኖር ውጉዝ ይሁን” ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ ፸፫÷፵፱ ስለዚህ በመንፈስ ቅዱስ ከበረ ማለት ክህደት ነው፡፡



የሚገርማችሁ ነገር የጌታን ምሥጢረ ሥጋዌ የተረዱበት ሁኔታ በሥጋዊ ዓይን እይታ ብቻ ነው፡፡ ጌታ ሲዋሐድ ምን ጎድሎበት ነው በመንፈቅ ቅዱስ ቅብዓትነት እንመላዋለን እያሉ እንደ ውኃ ቀጅ ምሥጢር የሚያፋልሱ፡፡
ካሳሁን “ይህ ሁሉ በቅብዓት ጠፋለት እንላለን፡፡ በቅብዓት ጠፋለት ማለቱ ስለምን ነው፡፡ በተዋሕዶ አይጠፋምን” ይላል፡፡ ካሳሁን ይህ ሁሉ የሚለው “የግድ መራብ የግድ መጠማት የግድ መታመም” እንደሆነ ይገልጻል፡፡  “ንዴት” የሚላቸው እነዚህን ነው፡፡ እንግዲህ እንደ ካሳሁን ገለጻ ከሆነ ቃል ከሥጋ ጋር ሲዋሐድ ንዴት አደረበት ማለትም የግድ መራብ የግድ መጠማት የግድ መታመም ተላለፈበት፡፡ ይህን የተላለፈበትንም ንዴት ለማጥፋት መንፈስ ቅዱስ ቀባው ያንጊዜ ንዴት ጠፍቶለት የባሕርይ አምላክ የባሕርይ ገዥ ሆነ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከዚህ በፊትም በማስረጃ እንዳሳየሁት ስህተት ክህደት ኑፋቄ ነው፡፡
ካሳሁን ይህንን ሲያብራራ “መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ ከአብ የባሕርይ ልደት ቢወለድ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ የባሕርይ አምላክ የባሕርይ ልጅ ሆነ በቅብዓት መንፈስ ቅዱስ ከበረ” ይላል፡፡ ይህ “በመንፈስ ቅዱስ ከበረ” የሚለው እምነት የተወገዘ እንደሆነ ከላይ  ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ ፸፫÷፵፱ ማስረጃ አድርጌ ገልጫለሁ፡፡ አብ ስንት ጊዜ ነው የወለደው? ወልድስ ከአብ ስንት ጊዜ ነው የተወለደው? ይህንን መመለስ አይችሉም፡፡ ወልድ የአብ የባሕርይ ልጁ የሆነ የባሕርይ አምላክ ነው፡፡ ታዲያ ዛሬ ድጋሜ የባሕርይ አምላክ እና የባሕርይ ልጅ ለመሆን ከአብ መወለድ እና በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ መክበር አለበትን? መቸም በሥጋ ርስት እንደሚሉ የታወቀ ነው፡፡ ከተዋሕዶ በኋላ የሥጋ የመለኮት የሚባል ርስት ምንድን ነው? ሥጋን የባህርይ ልጅ የባሕርይ አምላክ ያደረገው እኮ የቃል ከሥጋ ጋር መዋሐድ ነው፡፡ በተዋሕዶ ከበረ ማለትም ስለዚህ ነው፡፡

ካሳሁን የራሱን ኑፋቄ ሸሽጎ በማያውቀው የተዋሕዶ ምሥጢር ውስጥ ገብቶ ሲዳክር ይታያል “ዕንዲህ ስላሴ ያደረጉትን ነቢያት ሐዋርያት ያስተማሩትን ሊቃውንት የተረጎሙትን ይህን ትቶ በተዋሕዶ ከበረ ወልድ ቅብዕ ማለት ብዙ ኑፋቄ አለበት” ይላል፡፡ መጀመሪያ “በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” ብሎ ያስተማረ ነቢይ ሐዋርያ ሊቅ የት ይገኛል እስኪ ጥቀስ፡፡ መጀመሪያ ቢያንስ አንድ ማስረጃ ማቅረብ አለብህ እኮ፡፡ “በተዋሕዶ ከበረ” የሚለውን እምነት ከመንቀፍህ በፊት “በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” የሚል አብነት ሊሆንህ የሚችል ሊቅ ሐዋርያ መጥራት መቻል ነበረብህ ግን ከየት ታመጣለህ፡፡ መቸም ያንተ ነገር ሊቅ ብለህ አልፎንሱ ሜንዴዝን እንዳትጠራብን እና እንዳታስቀን፡፡ ሊቃውንትማ አወገዙት እኮ “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በእርሱ አጋዥነት ድንቅ ተአምራትን ያደርግ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ ከበረ የሚለው፤ ርኩሳን አጋንንትን በማውጣት ጊዜም ኃይልን ተአምራትን ከመንፈስ ቅዱስ ይቀበላል፤ በሰውም የአምላክነትን ሥራ ይሠራል የሚለው፤ መንፈስ ቅዱስ የባሕርዩ ነው፤ የአምላክነትንም ሥራ እርሱ ራሱ ይሠራል የማይል ቢኖር ውጉዝ ይሁን” ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ ፸፫÷፵፱ በማለት፡፡ በተዋሕዶ ከበረ የሚለው ቀጥተኛ ሃይማኖት እንደሚያስረዳን አካላዊ ቃል ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ አንድነት ሳይለይ እጅ ከመላ ሰውነት ሳይለይ ዕቃ አንሥቶ እንዲመለስ ሥጋን ተዋህዶ ሥጋን የባሕርይ አምላክ የባሕርይ ገዥ የባሕርይ ልጅ አድርጎ አዳምን ከሲዖል ባርነት ነጻ አደረገ ነው ዋና ምሥጢሩ፡፡ ይህንንም ዝም ብለን የምንናገረው ሳይሆን ሊቃውንትን ጠቅሰን ነው፡፡
በተዋሕዶ ከበረ ለሚለው እምነታችን ጥቂት ጥቅሶችን ላስቀምጥላችሁ፡፡  
፩. “ዘአንገሦ ለሥጋ አዳም በመንፈስ ቅዱስ ወረሰዮ ቅዱሰ ወማሕየዌ፤ በመንፈስ ቅዱስ ሕይወትነት የአዳምን ባህርይ ያከበረዉ የባሕርይ አምላክ ያደረገዉ እርሱ ነው” ሃይማኖተ አበው ዘአልመስጦአግአያ ም ፪ ቁ ፭
፪. ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ ላይ እንዲህ ተጽፎ እናገኘዋለን፡፡ ስምዐት ፻፳፬÷፴፬ “ወካዕበ ይቤ እስመ ክርስቶስ ኢተቀብዐ በእንተ መፍቅድ ዘቦቱ አላ ለሊሁ ቀባዒ ውእቱ ወዐርገ ኀበ ሥልጣነ መለኮቱ እንዘ ሰብእ ውእቱ ወለሊሁ እግዚአብሔር አምላክ ተብህለ በእንቲአሁ ከመ ውእቱ ተለዐለ ፈድፋደ በእንተ ትህትና ወሕጸጽ እንተ ዘትስብእት ወንዴት ወለሊሁ ጸገዎ ስመ ዘላዕለ ኩሉ ዝንቱ ዘኮነ በህላዌ ከመ አምላክ ከመ ያልዕለነ ለነሂ ዓዲ ኀበ ሀሎ ዝኩ፤ ዳግመኛ ክርስቶስስ ክብር መሻት ኖሮበት አልከበረም እርሱ ራሱ አክባሪ ነው እንጅ ሰው ቢኾንም በባህርይ ክብሩ ከበረ እርሱ ራሱ እግዚአብሔር አምላክ ነው ሥጋ ትሁት ሕጹጽ ነዳይ ስለሆነ ተለዐለ ተብሎ ተነገረለት ከሁሉ በላይ የሆነ ስምንም እሱ ራሱ ሰጠው ተባለ ይህም የሆነ በባህርይ ተዋሕዶ ነው አምላክ እንደሆነ እኛንም እሱ ወደ አለበት ያቀርበን ዘንድ”
፫. “ወከመዝ ነአምሮ ለሊሁ ተቀብዐ ከመ ሥርዓተ ትስብእት ወዳእሙ ውእቱ ዘይቀብዕ ርእሶ በመንፈሱ ባሕቲቱ፤ በተዋሕዶ እንደከበረ እናውቃለን ግን በገዛ ሥልጣኑ ራሱን የሚያከብር እሱ ነው” ሃይማኖተ አበው ስምዓት ምእራፍ ፻፳፬ ክፍል ፪ ቁጥር ፲፬ ላይ፡፡
፬. “መኑ ውእቱ ዝንቱ ዘሐደሶ ለሥጋ እምነ ኀጉል ወተወክፎ እሙስና፤ ሥጋን ከብልየቱ ያደሰው ከመለወጥ አድኖ የተዋሐደው ይህ ማነው” ሃይማኖተ አበው ዘእልመስጦአግያ ም ፬ ቁ ፲፩
፭. “አነ እቄድስ ርእስየ፤ እኔ ራሴን አከብራለሁ” ዮሐ ፲፯÷፲፱
፮. “በቃል ክብር መክበር ለሥጋ ተገባዉርሳነ ቄርሎስ ፸፮÷
፯. “ከአብ የተገኘ ቃል ከተዋሐዳት ካከበራት ከሥጋ ጋር አንድ እንደሆነ መጠንርሳነ ቄርሎስ ፶፮÷፲፭
፰. “ሰዉ መሆንን ከወደደ ሰዉ አለመሆንን ከጠላ ሰዉ መሆንን ስለወደደ ከአብ በሚገኝ ክብር ከበረ ተባለ ከአብ የተገኘ ክብርም አካለ ቃል ነዉ ክብርነቱ ለተዋሐደዉ ሥጋ ነዉ፡፡ርሳነ ቄርሎስ ፶፮÷፫- ፬
፱. “በመንፈስ ቀዱስ አዋሐጅነት ከአብ በተገኘ ክብር ከብሯልና ከአብ የተገኘ ክብርም አካለ ቃል ነውከሌላ ክብር አይሻም ቃልን ከበረ የሚል አንቀጽ የለምና መሢህ የሚለዉ ክብር ነዉ ክብር ማለትም ከተዋሕዶ በፊት ክብር ያልነበረዉ ሥጋ አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመሆን ከቃል ጋር ሲዋሐድ የባህርይ ክብርን በተዋሕዶ ገንዘብ ማድረጉን መናገር ነዉርሳነ ቄርሎስ ፵፯÷፱-፲፡፡
፲.  “ይህ ክብር በጸጋ በኅድረት እንዳልተሰጠው በዚህ ይታወቃል፤ በአንድ የመለኮት ባሕርይ ተዋሕዶ ነው አንጅ ለወልድ የአባቱ ልዑል ጌትነት ገንዘቡ ነውና” ሃይማኖተ አበው ዘባስልዮስ ም ፴፫ ቁ ፳፱
፲፩. “ዳግመኛ በዚህ ድርሳን እግዚአብሔር ሊዋሐደው ሥጋን እንደ ፈጠረ ተናገረ የመላእክት ፈጣሪ ሥጋ ያልነበረው እውነተኛ ፀሐይ ከንጹሕ ሥጋ ተወለደ ነቅፎ አልተወውም ንፁህ አድርጎ ፈጥሮ ፍጹም አምላክ አደረገው እንጅ” ሃይማኖተ አበው ዘዮሐንስ አፈወርቅ ም ፷፰ ክ ፳፱ ቁ ፵፬
፲፪.  “በሥጋ ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም ከአብርሃም ከዳዊት ከተገኘ ባህርይዋም ኃጢአት የሌለበት በነፍስ በሥጋ ፍጹም የሚሆን አካልን ሊዋሐደው ፈጠረ ከማርያም የነሣውን ሥጋ ከኃጢአት ከዘር የራቀ አደረገው ከማኅጸን ጀምሮ በማይመረመር ግብር በአንድ ባሕርየ መለኮት ከእርሱ ጋር አንድ አደረገው” ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ ም ፸ ቁ ፳
በነገራችን ላይ በተዋሕዶ ከበረ ለሚለው እውነተኛ ሃይማኖት ምስክሮቻችን እነዚህ ብቻ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ በርካታ ጥቅሶችን ማንሣት ይቻላል፡፡ እኛ ቢያንስ እነዚህን ወደ ዐሥራ ሁለት የሚጠጉ ማስረጃዎችን አስቀምጠናል ቅባቶች እስኪ “በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” የሚል አንድ ጥቅስ አምጡልን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ገብታችሁ “ቀባ” የሚል ቃል ፍለጋ ድከሙ እስኪ፡፡ የናንተ ነገር ዳዊትን ተቀብቶ በእሥራኤላውን ላይ ንጉሥ ሆነ የሚለውን ጥቅስ እንዳታመጡብን እና እንዳንስቅባችሁ፡፡
በጣም የሚያሳዝነው ነገር አንድነትን ያጸናውን ተዋሕዶን እየከፋፈሉ የንስጥሮስ የልዮን ባህል ውስጥ ይገባል ሲሉ ስናይ በጣም እናዝናለን፡፡ አንድነት ውስጥ ንስጥሮስ ምን ሊሠራ ይመጣል አንድነት ውስጥ ልዮን ምን ቦታ አለውና ሊነሣ ይችላል፡፡ ይህ አንድም ምሥጢረ ተዋህዶን ጠንቅቆ ካለማወቅ አንድም ልዮን እና ንስጥሮስ ይከተሉት የነበረውን ክህደት በሚገባ ካለማወቅ የመጣ ይመስለኛል፡፡ ንስጥሮስ ማን እንደሆነ ባለፈው ክፍል ዓይተናል፡፡ ልዮን የሮሜ ሊቀ ጳጳስ ነበረ ነገር ግን “ሥጋ ከመለኮት ያንሣል” በማለት ካደ፡፡ ንስጥሮስ ደግሞ የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ ነበረ ነገር ግን “ወልድ ከነቢያት እንደ አንዱ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ በዮርዳኖስ ባደረበት ጊዜ በጸጋ አምላክ ሆነ” እንዲሁም “ሕስወኬ ትሰመይ ቅድስት ድንግል ወላዲተ አምላክ ወአማነ ትሰመይ  ወላዲተ ሰብእ” በማለት ካደ፡፡ ንስጥሮስ እና ልዮን ክህደታቸው እንደዚህ ሆኖ ሳለ ምሥጢረ ተዋሕዶን ከእነዚህ ባሕል ውስጥ መጨመር ከንቱነት ነው፡፡ ተዋሕዶ ውስጥ “ሁለት አካል ሁለት ግብር ሁለት ባሕርይ” የሚል ክህደት የተወገዘ ነው ታዲያ በየትኛው ሂሳብ ነው እነዚህ ክህደቶች የተዋሕዶ ሊሆኑ የሚችሉት? ለቅባት እምነት ተከታዮች ግን እነዚህ የልዮን እና የንስጥሮስ ባህሎች የእምነታቸው ክፍሎች ናቸው፡፡
ካሳሁን ይቀጥልና “በተዋሕዶ ሦስቱም አከበሩት ማለት ሶስቱም ሰው ሆኑ ያሰኛል ተዋሕዶ ማለት ቃል ከስጋ ስጋ ከቃል ጋራ አንድ ሆነ ማለት ነውና” ይላል፡፡ በሥላሴ ዘንድ የአካል ሦስትነት እንጅ አንድነት የለባቸውም እኮ ካሳሁን ምነው ምሥጢረ ሥላሴን ዘነጋኸው፡፡ ታዲያ እንዴት ነው ሦስቱም ሥጋ ለበሱ የሚሰኘው? አሁንም ይቀጥልና “ወልድ ብቻውን ያለ አብ ያለ መንፈስ ቅዱስ በተዋሕዶ ከበረ ማለት ስላሴን ሶስት መለኮት ዘጠኝ አካላት ያሰኛል” ይላል፡፡ ይህ ሰው በጣም ዞሮበታል፡፡ ወልድ ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ ተለይቶ ብቻውን የኖረበት ጊዜ አለ እንዴ? እስኪ ልጠይቅህማ! የቃል ተዋሕዶ በባሕርይም በአካልም አይደለምን? ነው እንደምትል አልጠራጠርም፡፡ አይደለም ካልህ እዚሁ ላይ እንፈጽማለን፡፡ ነው ካልኸኝ ግን ሥላሴ በባሕርይ አንድ ናቸውና የባሕርይ ተዋሕዶ ካለ ሦስቱም ሥጋ ለበሱ ያሰኝብሃል ይህንን ምን ብለህ ተረጎምኸው? ካስሽ! ምሥጢረ ተዋህዶ ላንተ ስለተሰወረብህ ሁሉም እንደዚያ እንዳይመስልህ ብዙ ሊቃውንት ያሉባት ቤተክርስቲያን ናት ያለችን፡፡ ሊቃውንቱ በሰፊው አመስጥረው አብራርተው ግልጥልጥ አድርገው ነው የሚያስረዱን፡፡ ሦስቱም ሥጋ ለበሱ እንዳንል ሦስቱም ያደሩበት ምሥጢር አላቸው፡፡  
እዚህ ላይ አባ ጳውሊ ለሮማውያን የመለሱትን መልስ ቀጥተኛ ላስቀምጥ እወዳለሁ፡፡ አባ ጳውሊ ሲመልስ ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ሲያበሥራት መንፈስ ቅዱስ ባንቺ ላይ ይመጣል የአብም ኃይሉ ይጋርድሻል ካንች የሚወለደውም ቅዱስ ነው የልዑል የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል ብሎ ሦስቱም አካላት በማኅጸነ ማርያም እንደ አደሩ ተናግሯል፡፡ ማደራቸውም አብ ለአጽንዖ መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ ወልድ ለለቢሰ ሥጋ ነው እንጅ ሦስቱ ኹሉ ለለቢሰ ሥጋ ያደሩ አይምሰልህ፡፡
በዚህ ጊዜ መለኮት ርቀቱን ለቆ ሳይገዝፍ ሳይለወጥ ትስብእትም ግዘፍነቱን ለቆ ሳይረቅ ሳይለወጥ እንደ ነፍስና እንደ ሥጋ በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ኾነ፡፡ ወልድ ለለቢሰ ሥጋ ማለት ይህ ነው አብ ለአጽንዖ ማለትም ሰማይና ምድር የማይወስኑትን ምሉዕ ስፉሕ ረቂቅ መለኮትን እመቤታችን በጠባብ ማኅጸን እንድትችለው አጸናት ማለት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ ማለትም ትስብእትን ከአዳም መርገም አንጽቶ ቀድሶ ለተዋሕዶተ መለኮት የበቃ አደረገው ማለት ነው፡፡ በቃ ተዋሕዶ ይኸው ነው፡፡ ሦስት መለኮት ዘጠኝ አካላት የሚያሰኝ ነገር የለውም ክህተት ራሱ አይገኝም እኮ ተዋሕዶ ውስጥ ስንዱዋ እመቤት ውስጥ!
ቅባቶች ባህል ላይ ግን አብ ድጋሜ ወለደው መንፈስ ቅዱስ ቀባው ከዚያ ተወለደ ሲባል ሦስቱም ሥጋ ለበሱ ያሰኛል ይኼ ሰፊ ክፍተት ነውና፡፡ ወልድ አምላክ ገዥ የሖነው በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከብሮ ነው ሲሉ የባሕርይ ሳይሆን የጸጋ አምላክ ማድረጋችሁ ነውና ክህደት ነው ብንል ሰፊ ክፍተት ነው፡፡ እናንተም እያነበባችሁ ለመታዘብ ሞክሩ በዚያውም የቅብዓት አስተምህሮ ኑፋቄነቱ ምን ጋር ነው የሚለውን እያስተዋላችሁ ተመልከቱ፡፡፡

#ይቀጥላል

፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ኅዳር ፲፬ / ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment