፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ዛሬ ከገጽ ፲፱ ጀምረን ያሉ ስህተቶችን በማስረጃ እንመለከታለን፡፡ በፎቶ ከስር ስለማያይዝላችሁ ሙሉውን
ማንበብ ትችላላችሁ እኔ ግን ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ብቻ ነው ትኩረት የማደርገው፡፡
****************
·
እንኳን ለኃያሉ
መልአክ ለቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ በዓል በሰላም በፍቅር በአንድነት አደረሳችሁ፡፡ የመልአኩ ረድኤት በረከት አይለየን አሜን፡፡
***************
ካሳሁን ምናሉ ገጽ ፲፱ ላይ እንዲህ ይላል “ይህ ፈጣሬነት እውነት መስጠት ግብሩ የሆነ ቃል ፣ ፍጡርነት
ተወካፌነት ርስቱ ከሆነ ስጋጋራ ብዋሐድ፣ ፈጣሪነቱን ዕውቀቱን ወሐቢነቱን ሳይለቅ በስጋ ርስት ፍጡር ያሐራዊ ተወካፌ ሲሆን ጊዜ
ሳይሻ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ከአብ ቢወለድ በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ መጣሪ ወሐቢ አዋቂ ሐዲስ አምላክ ሆነ” ይላል፡፡ ይህንን
አስመልክቶ በሰፊው የ “ወልደ አብን” ክህደቶች በተመለከትንበት ባለፈው ዓመት አብራርቻለሁ፡፡ ሆኖም ግን አዲስ ለሆኑትም በድጋሜ
ቢጻፍ ስለማይጎዳ እንደ አስፈላጊነቱ እንጽፋለን፡፡ ከዚህ የክህደት ትምህርት በመነሣት መጠየቅ የሚገባን እና ማብራራት የሚያስፈልገን
ነገር ይኖራል፡፡ በዚህም መሠረት፡-
፩ኛ. ቅባቶች መለኮት ከሥጋ ጋር ሲዋሐድ ፍጹም ተዋሕዶ እንዳላደረገ
አድርገው ነው እየተናገሩ ያሉት፡፡ ተዋሕዶ ከዚህ በፊትም እንደገለጽነው ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ
የሆነበት የሥጋ ገንዘቦች በሙሉ ከኃጢአት በቀር ለመለኮት፤ የመለኮትም ገንዘቦች በሙሉ ለሥጋ የሆኑበት ሰው አምላክ አምላክም ሰው
የሆነበት ረቂቅ ድንቅ ምሥጢር ነው፡፡ አሁን ከተዋሕዶ በኋላ አንዱን ለሁለት መክፈል መሰንጠቅ መተርተር አይቻልም አንድ ነውና፡፡
ታዲያ አንዱን ለሁለት ከፍለን “በስጋ ርስት ፍጡር ያሐራዊ (ደኃራዊ ለማለት ፈልጎ ነው) ተወካፌ ሲሆን…” የሚለው አነጋገር ክህደት
አይደለምን? አካላዊ ቃል ሥጋ ማርያምን ሲዋሐድ እኮ ሥጋን አምላክ አድርጎታል ታዲያ አምላክ የሆነውን ሰው እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስን
“በሥጋው ደኃራዊ ተወካፌ ነው” ማለት ምን የሚሉት ቅዠት ነው፡፡ አካላዊ ቃል ሥጋን ሲዋሐደው ደሐራዊ የነበረውን ሥጋ ቀዳማዊ አምላክ
አድርጎታል፡፡ እሳት ከብረት ጋር ሲዋሐድ እሳቱ ብረቱን ያግለዋል እንጅ እሳቱ በብረቱ የተነሳ ቁረት አያገኘውም፡፡ መለኮትም ሥጋን
ሲዋሐደው ሥጋ ቀዳማዊ አምላክ ሆነ እንጅ መለኮት የሥጋ ንዴት ተወካፌነት ኃጢአት ተላልፎበት በመንፈስ ቅዱስ ቅብዓትነት የተወገደለት
አይደለም፡፡ ከተዋሕዶ በኋላ በዚህ ርስት በዚህ ርስት የሚለው የቅባቶች አንዱን አምላክ የመክፈል ጠባይእ ፍጹም ክህደትን ያመጣል፡፡
፪ኛ. ወልድ ከአብ ሁለት ጊዜ ተወልዷል የሚለው አስገራሚው ክህደታቸው
ነው፡፡ ወልድ ቅድመ ዓለም ከአብ አካል ዘእም አካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ በመለኮት ተወልዷል፡፡ ዳግመኛም ጊዜው ሲደርስ ከእመሕይወት
ከድንግል ማርያም በሥጋ ተወልዷል፡፡ በመለኮት አብ ወለደው በሥጋ ድንግል ማርያም ወለደችው ሁለቱ ልደታት እነዚህ ብቻ ናቸው፡፡
ቅባች ግን ሌላ ሦስተኛ ልደትን ይጠቅሳሉ ይኸውም “ጊዜ ሳይሻ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ከአብ ቢወለድ” ብሎ ካሳሁን ጽፎት
እንደምናገኘው “ወልድ ከአብ ሁለተኛ ተወልዷል” ማለታቸው ነው፡፡ እዚህ ላይ አብ በማኅጸነ ማርያም ወልድን በሥጋ ወለደው የምትለዋ
የቅባቶች ኑፋቄ መነሻ እና አጋዥ መጽሐፍ የላትም፡፡ ዛሬም በድንግል ማርያም ማኅጸን ከአብ ተወልዷል ካሉ የሚከተሉትን ጥያቄዎች
መጠየቅ ግድ ይለናል፡-
·
ያለባሕርዩ
መለኮት በሥጋ፣ ሥጋ በመለኮት መውለድ ይቻለዋልን? አዎ ካላችሁ አብ በሥጋ እንደወለደው ድንግል ማርያምም በመለኮት ወለደችው ያሰኝባችኋል፡፡
አዎ ልክ ነው ካላችሁ ወልድ በመለኮት ሁለት ጊዜ ተወለደ ያሰኛልና ስህተት መናገራችሁን አስተውሉ፡፡
·
“ወልድ በማኅፀነ
ማርያም ከአብ ተወልዷል” ካላችሁ ለሰማያዊ ልደቱ እናት እንደሌለችው ሁሉ ለምድራዊ ልደቱም አባት የሌለው እንደሆነ ሊቃውንቱ ያስተማሩት
ትምህርት ወዴት ይጣላል? እዚህ ላይ ለቀዳማዊ ልደቱ መለኮታዊት እናትም ሆነች ሥጋዊት እናት የለችውም ማለት ነው፡፡ ለምድራዊ ልደቱም
እንደዚሁ መለኮታዊም ሆነ ሥጋዊ አባት የለውም ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት የአብ አባትነት ቀድሞ ዘመን ሳይቆጠር የነበረ አሁንም ያለ ወደፊትም የሚኖር ነው ማለት ነው፡፡ አባትነት እንደ ቀበሌ መታወቂያ
በየዘመኑ የሚታደስ አይደለም፡፡ አብ ዳግመኛ በሥጋ ከድንግል ማርያም ልጁን አልወለደውም ይህንንም የምንለው በማስረጃ አስደግፈን
ነውና ማስረጃውን እናስቀምጣለን፡፡ እነዚህን የሊቃውንቱን ትምህርቶች ምን ብላችሁ ትተረጉሟቸዋላችሁ?
፩. ሃይማኖተ አበው ዘጎርጎርዮስ ም ፷ ቁ ፳ ላይ “ዛሬ ግን ከድንግል ብቻ ተወለደ ድንግልናዋንም ባለመለወጥ አጸና ድንቅ የሚሆን መጽነስዋ የታመነ ይሆን ዘንድ ቅድመዓለም ከአብ እንደተወለደም
ለማመን መሪ ይሆን ዘንድ” በማለት ድኅረዓለም ከድንግል ማርያም ብቻ እንደተወለደ ከአብ እንዳልተወለደ ይናገራል፡፡
፪. ሃይማኖተ አበው ዘጎርጎርዮስ ም ፴፭ ቁ ፲፯ “በምድራዊ ልደቱ አባት አለው
አትበሉ በሰማያዊ ልደቱም እናት አለችው አትበሉ እርሱ በምድር አባት የሌለው ነው በሰማይም እናት የሌለችው ነው”
፫. “ዘአልቦቱ እም በሰማያት ወአብ በዲበ ምድር ፤ በሰማይ እናት በምድርም
አባት የለውም” አንቀጸ ብርሃን ዘቅዱስ ያሬድ ኢትዮጵያዊ፡፡
፬. ሃይማኖተ አበው ዘሄሬኔዎስ ም ፯ ክ ፪ ቁ ፳ “ከንጽሕት ድንግል ማርያም
በኋላ ዘመን እንደተወለደ እንደሚነግሩን ቀድሞም ከአብ እንደተወለደ እንዲሁ ከአባት ያለእናት ከእናት ያለአባት ለመወለድ መጀመሪያ
እርሱ እንደሆነ ለፍጥረት ሁሉ ይነግሩናል”
፭. ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ ም ፸፫ ቁ ፬-፭ “ወልድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
በማይመረመር ተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነውና ቀዳማዊ ሲሆን ከዘመናት አስቀድሞ ከአብ የተወለደ ነው ዳግመኛም ከድንግል በሥጋ የተወለደ
ነው ተብሎ ስለርሱ እንዲህ ይነገራል፡፡ የመለኮቱ መገኘት ከድንግል አይደለም፤ ከአብ ከተወለደ በኋላ ጥንታዊ (ቀዳማዊ) ልደትን
ሊወለድ አልወደደም ከአብ ጋር ከዘመን ሁሉ አስቀድሞ የነበረ ጥንት የሌለው ቀዳማዊ ስለሚሆን ስለእርሱ ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ጥንታዊ
ልደትን ሁለተኛ እንደሻ ይነገር ዘንድ ይህ ሐሰት ክህደትም ነው፤ ዳግመኛ በሥጋ እንደተወለደ ስለእርሱ እንዲህ ይነገራል እንደሰው
ሁሉ አስቀድሞ ቅርጽ የተፈጸመለት ሰው ተገኝቶ ከዚህ በኋላ ቃል ያደረበት አይደለም በእመቤታችን ማሕጸን እርሱ ብቻ አንድ አካል
አንድ ባሕርይ ሆነ እንጅ በሥጋም ይወለድ ዘንድ ወደደ በሥጋ መወለድንም ለእርሱ ብቻ ገንዘብ አደረገ” …..እዚህ ላይም በማስተዋል አንብቡት “ከአብ ከተወለደ በኋላ ጥንታዊ (ቀዳማዊ)
ልደትን ሊወለድ አልወደደም ከአብ ጋር ከዘመን ሁሉ አስቀድሞ የነበረ ጥንት የሌለው ቀዳማዊ ስለሚሆን ስለእርሱ ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ
ጥንታዊ ልደትን ሁለተኛ እንደሻ ይነገር ዘንድ ይህ ሐሰት ክህደትም ነው” ይላል ሊቁ ቄርሎስ፡፡ ስለዚህ አብ በማኅጸነ ማርያም ወልድን
ወልዶታል ማለት ሐስት ክህደትም ነው ቄርሎስ እንደተናገረው፡፡
፮. ሃይማኖተ አበው ዘኤጲፋንዮስ ም ፶፬ ቁ ፲፩ “አብ ጥንት ፍጻሜ የሌለው
ቃልን ዓለምን ከመፍጠሩ አስቀድሞ ወለደው በኋላ ዘመንም በግብረ መንፈስ ቅዱስ ንጽሕት ከምትሆን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም
በሥጋ ተወለደ”… ይህንን አጻጻፍ ልበ ብላችሁ አስተውሉት፡፡ አብ በማኅጸን ወልዶት ቢሆን ኖሮ “በኋላ ዘመንም በግብረ መንፈስ ቅዱስ
ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ወለደው” ለማለት የቀና የተመቸ አጻጻፍ ነበር ነገር ግን አብ በማኅጸነ ማርያም ከአብ
አልተወለደምና “ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ተወለደ” ብሎ ሊቁ ኤጲፋንዮስ ከላይ ባለው መልኩ ጻፈልን፡፡
፯. ሃይማኖተ አበው ዘሳዊሮስ ም ፹፬ ቁ ፰ “ሁለት ልደት እንዳለው በእግዚአብሔር
ቃል እንዲሁ ልናምን ይገባናል አንዱ ቅድመዓለም ከአብ ያለ እናት የተወለደው የማይመረመር ልደት ነው፡፡ ሁለተኛውም በኋላ ዘመን
ከንጽሕት ድንግል ማርያም ያለአባት የተወለደው የማይመረመር የማይነገር ልደት ነው፡፡ ነገር ግን ቃል ሥጋ እንደሆነ ባሕርያችንንም
ባሕርይ እንደአደረገ በዓይናችን እንዳየነው በእጃችንም እንደዳሰስነው ይህን ብቻ እናውቃለን”
እነዚህ ሰባት ማስረጃዎች በዋናነት ሁለት መሠረታዊ ነጥብ የያዙ ናቸው፡፡
፩. ለሰማያዊ ልደቱ እናት ለምድራዊ ልደቱ ደግሞ አባት እንደሌለው የሚገልጹ
መሆናቸው፡፡
፪. የጌታ ልደታት ሁለት መሆናቸውን እነርሱም ቅድመዓለም ከአብ በመለኮት
ድኅረ ዓለም ከእመቤታችን በሥጋ የተወለዳቸው ልደታት ብቻ መሆናቸውን፡፡ እዚህ ላይ “አብ በማኅጸነ ማርያም በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ
ወለደው” የሚለው የቅብዓቶች ሦስተኛ ልደት ደጋፊ የሌለው ከንቱ ፍልስፍና መሆኑን ተረድተንበታል፡፡
·
“ሕይወቱ መንፈስ
ቅዱስን ተቀብሎ ከአብ ቢወለድ በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ መጣሪ (ፈጣሪ ለማለት ነው) ወሐቢ አዋቂ ሐዲስ አምላክ ሆነ” የሚለው ሌላኛው ክህደታቸው ነው፡፡ ቃል ሥጋን የተዋሐደ አርጅቶ አፍጅቶ
ሐዲስ ለመሆን አይደለም፡፡ በመጀመሪያ የጌታን ሰው መሆን ድንቅ ምሥጢር እና ጥበብ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ይኸውም ምሥጢረ ሥጋዌ
ነው፡፡ በየትኛውም የሥጋዌ ትምህርት ላይ “ሐዲስ አምላክ ሆነ” አይልም አይባልም ሊባልም አይገባውም፡፡ መለኮቱ አያረጅም አያፈጅም
ታዲያ “ሐዲስ” ልንለው እንዴት እንደፍራለን? እርሱ እኮ ከዘመናት በፊት የነበረ ዘመናትን ያሳለፈ አሁንም ያለ ወደፊትም የሚኖር
ዘመናት ያልቀደሙት ዘመናትን አሳልፎ የሚኖር አምላክ ነው ታዲያ ሰው አምላክ ቢሆን አምላክ ሰው ቢሆን “ሐዲስ አምላክ” ሊባል እንዴት
ይቻላል? ይህንን ትርጓሜ ያመጣችሁት ከሥነ ፍጥረት መጽሐፍ ከመጽሐፈ አክሲማሮስ ነው፡፡ አክሲማሮስ ለመላእክት የጻፈውን እናንተ
ለአካላዊ ቃል እየቀጸላችሁ ትተረጉሙታላችሁ ይህ ፈጽሞ የተሳሳተ ነው፡፡
ከላይ በዚህ መልኩ የጠየቅሁትን ጥያቄ መመለስ የሚችል ሊያስረዳ የሚችል
የቅባት አማኝ ካለ አስተያየቱን በነጻነት ሊተውልን ይችላል፡፡
#ይቀጥላል
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ኅዳር ፲፪
/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
No comments:
Post a Comment