Monday, October 31, 2016

“እመ አምላክ ድንግል ማርያም”

© መልካሙ በየነ

ጥቅምት 21/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
እመ አምላክ (የአምላክ እናት) ድንግል ማርያም፡፡ ይህ አገላለጽ ከእናታችን ከቅድስተ ቅዱሳን ከወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም ውጭ ለማንም ለማን የማይነገር ብቸኛ አገላለጽ ነው፡፡ እናትነትን ከድንግልና ጋራ አስተባብራ የምትገኝ ሴት ከድንግል ማርያም ውጭ በየትኛውም ዓለም ውስጥ አትገኝም፡፡ እም ወድንግል ቢሉ የአዳም ተስፋ ምክንያተ ድኅነታችን የገነት በር የተከፈተባት እናታችን ብቻ ናት፡፡ ይህ ነገር ከሰው ኅሊና በላይ ነው፡፡ አእምሯችን ምጡቅ ሥራችን ረቂቅ ነው የሚሉ ጠቢባን ሁሉ ይህንን ነገር ሊረዱት አይችሉም፡፡ ምክንያቱም እናት እና ድንግል ሲባል መስማት ለጆሮም እንግዳ ነውና፡፡ ሌሎች ሴቶች ድንግል ከተባሉ እናት፤ እናት ከተባሉም ድንግል መባል አይችሉም፡፡ በምንም ተአምር ይህንን ማስተባበር አይችሉም፡፡ ከዓለም መፈጠር በፊት በአምላክ ኅሊና ተስላ የነበረች ንጽሕት ዘር እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ግን ይህንን አስተባብራ ከፍጥረታት ሁሉ ልቃ ተገኘች፡፡ አስቡት ይህንን ድንቅ ምሥጢር! ይህ ነገር እኮ ከእኛ ኅሊና በላይ ወደ ላይ ብንወጣ የማናገኘው፣ ወደ ታች እመቀ እመቃት ወደ ጥልቁ ብንወርድ የማንረዳው፣ ወደ ዓለም ዳርቻ ሁሉ ብንበርር የማንገነዘበው  ምጡቅ ነው፡፡ ለዚህም ነው የእናታችን ምስጋና የበዛለት አባ ኤፍሬም “ኦ ዝ ነገር” በማለት በአንክሮ የሚናገረው፡፡ እውነት ነው ነገሩ ይረቃል፣ ነገሩ ይደንቃል፣ ነገሩ ይከብዳል፣ ነገሩ ለመረዳት ያስቸግራል፣ ነገሩ እጹብ እጹብ ብቻ የሚባል ነው፡፡

ሴቶች ልጅ በመጽነሳቸው ደስ ይላቸዋል በመውለዳቸው ደግሞ አብልጠው ደስ ይላቸዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ ደግሞ ወንድ ይወለድላችኋል ሲባሉ ደስ ይላቸዋል፡፡ አያችሁት የእናታችንን ደስታ! በመልአኩ ብሥራት ትጸንሻለሽ መባል ምንኛ ያስደስታል!!! ይህንንማ ሌሎች ሴቶችስ የሚያገኙት አይደለምን ቢሉ፡፡ ሌሎች ሴቶች ትወልዳላችሁ ቢባሉ ነቢይ ነው በዚያ ይደሰታሉ፡፡ ሌሎች ሴቶች ትወልዳላችሁ ቢባሉ ሐዋርያ ነው በዚያ ይደሰታሉ፡፡ ሌሎች ሴቶች ትወልዳላችሁ ቢባሉ ቅዱስ አባት ቅድስት እናትን ነው በዚያ ይደሰታሉ፡፡ ሌሎች ሴቶች ትወልዳላችሁ ቢባሉ ጳጳስ ሊቀጳጳስ ካህንን ነው በዚያ አብዝተው ይደሰታሉ፡፡ እናታችን ግን ትወልጃለሽ ብትባል የሰማይ እና የምድር ጌታን እርሷንም የፈጠራትን አምላክ ነው፡፡ ይህ ያስደስታል! በዚህም ላይ ድንግልናን ከእናትነት ጋራ ማስተባበር ምንኛ ያስደስት፡፡ ይህ ድንቅ ነገር የተደረገው ለእናታችን ለድንግል ማርያም ብቻ ነው፡፡ ፈጣሪን ጸንሶ መውለድ ምንኛ ረቂቅ ምሥጢር ነው? ይህ ረቂቅ ምሥጢር በድንግል ማርያም ሲደረግ ስናይ እናታችንን አብዝተን ወደድናት አብዝተንም አደነቅናት አብዝተንም ተስፋችን አልናት፡፡ አብዝተን ስንደነቅ አብዝተን ስንወዳት አብዝተን ተስፋችን ነሽ ስንላት ግን ቅንጣት ታህል የምንጨምርላት ነገር ኖሮ አይደለም ነገሩ ቢረቅብን ነው እንጅ፡፡ በእውነት በእናታችን ፍቅር ተነድፈን አፋችን ለዘለዓለም ድንግል እናቴ ድንግል እናቴ አማልጅኝ ሲል ቢኖር ምንኛ በታደልን! ከእናታችን ፍቅር ርቀው የሚኖሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ፍቅሯ ጣዕሟ ባይገባቸው ነው፡፡ ቢገባቸውማ እናቴ ለማለት ቅጽበት ባልወሰደባቸውም ነበር፡፡ አምላካችን ፈጣሪያችን ከእናቱ ከእናታችን ከድንግል ማርያም ረድኤት በረከት ያሳትፈን፡፡


Friday, October 28, 2016

“ሳይሆኑ እንዲሆኑ መምከር”

© መልካሙ በየነ

ጥቅምት 18/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
==============================================

“መሆን ደስ ይላል መምሰል ግን ያስጠላል” ይሉኝ ነበር አንድ አባት፡፡ ለጊዜው ነገራቸው አልገባኝም ነበር እየቆየ በሕይወቴ ውስጥ ሳየው ግን ገባኝ፡፡ ብዙዎች ያውቁኛል፤ ምን ማወቅ ብቻ ያደንቁኛልም እንጅ፡፡ ያወቁኝ እና ያደነቁኝ ግን በማወቄ ሳይሆን በመታወቄ ነበር፡፡ ለመታወቅ ደግሞ መሆን ላያስፈልግ ይችላል፡፡ አረ ልክ ነው መምሰል ለመታወቅ በቂ ነው፡፡ አሁን ገና አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ ለመታወቅማ መምሰልም ላያስፈልግ ይችላል አሉ፡፡ አወ ልክ ነው፡፡ በዚያ ቀደምለት አንዱ ለመታወቅ ሲል ታዋቂዎችን ሲገርፍ ነበር አሉ፡፡ በታዋቂ ሰዎች ትክሻ ላይ ተንጠልጥለህ ታዋቂነትህን ለመጎናጸፍ በቻልከው መጠን በስድብ መወረፍ ነው አሉ፡፡ ታዋቂዎችን ካልተሳደብክ አትታወቅም፡፡ ብታመሰግናቸው ማንም አያውቅህም ምክንያቱም እልፍ ህዝብ ያመሰግናቸዋልና፡፡ ስለዚህ በቻልከው መጠን ብዙ ተከታይ ያላቸውን ሰዎች በስድብ ናዳ ትቀጠቅጣቸዋለህ ለጊዜው እብድ ሊሉህ ቢችሉም ከጊዜ በኋላ ግን ታዋቂ ትሆናለህ፡፡ ይሁዳ እንዲህ ስመ ገናና ሆኖ ዓለም ሁሉ ሲጠራው የሚውለው እኮ ጽድቅ ስለሰራ አይደለም ጌታውን ስለሸጠ እንጅ፡፡ በእርሱ ምትክ የተተካውን ሐዋርያ ማትያስን ማን ይጠራዋል? በዓለም ዘንድ የይሁዳን ያህል እውቅና ያገኘ አይመስለኝም፡፡ መንገድ ዳር ሄደህ ይሁዳ ማነው ብትል ጌታውን በ30 ብር የሸጠ ሰው ነው ይሉሃል፡፡ ማትያስ ማነው ብትል ግን ማንም አይመልስልህም፡፡ ይሁዳ ሁሉን አዋቂ በሆነው በሁሉም ዘንድ ስሙ በደረሰው አምላክ ላይ ስለተነሣሣ ነው ታዋቂ የሆነው፡፡ ዛሬም ይህንን ፈለግ ይዘው ሆነው ሳይሆን መስለው የሚኖሩ ሰዎች የራሳቸውን ታዋቂነት ለመጨመር ብቻ ያልተደረገውን ተደረገ እያሉ ያለማስረጃ አደባባይ ላይ በስድብ የሚቀጠቅጡ ሰዎች አሉ፡፡

እኔ አስመሳይ የለመለመ ዛፍ ነኝ፡፡ ቅጠል አለኝ ፍሬ ግን የለኝም፡፡ ለተራበ አጓጓለሁ ነገር ግን ከእኔ ፍሬን አያገኝብኝም፡፡ ምናልባት ለጥላነት ሊጠቀምብኝ ይችል ይሆናል፡፡ ብዙ ዛፎች የቅጠሌን ማማር ተመልክተው እንደአንተ እንድናምር ምን እናድርግ ይሉኛል፡፡ እኔም ፍሬ ያለኝ መስየ እንደ እኔ ቅጠላቸው እንዲያምር እመክራቸዋለሁ፡፡ ከዚህም በበለጠ እኔ ማፍራት ያልቻልኩትን ፍሬ እንዴት እንደሚያፈሩ ሁሉ እመክራቸዋለሁ፡፡ ያልሆንኩትን ሁኑ እያልኩ ስመክር ውስጤ ይረበሻል፡፡ አዋቂ አይደለሁም በዚህ መካሪነቴ ግን ብዙዎች ያውቁኛል፡፡ አልጾምም ሰዎች እንዲጾሙ ግን እመክራለሁ፡፡ አልሰግድም ሌሎች እዲሰግዱ ግን እመክራለሁ፡፡ አልጸልይም ሌሎች እንዲጸልዩ ግን አስተምራለሁ፡፡ አልመጸውትም ሌሎች እንዲመጸውቱ ግን እወተውታለሁ፡፡ አልቆርብም ሌሎች እንዲቆርቡ ግን አስተምራለሁ፡፡ ንስሐ ገብቼ አላውቅም ሌሎች እንዲገቡ ግን ሥርዓት አስተምራቸዋለሁ፡፡ እኔ እቅማለሁ አጨሳለሁ ሌሎች እንዳይቅሙ እንዳያጨሱ ግን አስተምራለሁ፡፡ እኔ ከመጠን በላይ እጠጣለሁ እሰክራለሁም ነገር ግን ሌሎች እንዳይሰክሩ አስተምራለሁ፡፡ አያችሁኝ ሳላችሁኝ! እኔ ማለት ነጠላየ በጣም የነጣ ልቡናየ በኃጢአት ብዛት የገረጣ ሰው ነኝ፡፡ የማስበው ኃጢአትን ነው፡፡ አፌ ይሰብካል ነጠላየ ይመሰክራል ውስጤ ማንነቴ ግን የሲዖልን ደጅ የሚያንኳኳ ነው፡፡ በአፌ እመርቃለሁ በልቤ እረግማለሁ፡፡ የእኔ ክርስትና ከነጠላ የዘለለ አይደለም፡፡ በልቤ የሸፈትኩ ወንበዴ ነኝ፡፡ በዝሙት አልጋ ውስጥ ተደብቄ እኖራለሁ፡፡ በዋዘኞች ወንበር ላይ ተቀምጨ አንቀላፋለሁ፡፡ ፍርዴ ደሃን ያስለቅሳል፤ እጀ ደምን ያፈሳል፡፡ እግሬ ለስርቆት ይገሰግሳል፤ ልቤ ኃጢአትን ያመላልሳል፡፡ በሰዎች ሃብትና ንብረት ዓይኔ ይቀላል፤ በወንድሜ ላይ እቀናለሁ በእህቴ ላይ አመነዝራለሁ፡፡ እናቴን እደበድባለሁ አባቴን እገድላለሁ፡፡ እንደዚህ ባደርግም ግን ስለ ጽድቅ እመክራለሁ፡፡ ምክንያቱም ታዋቂነትን ስለምሻ፡፡

ባልሆንኩበት ጠባይ ሌሎች እንዲሆኑ እመክራለሁ፡፡ እኔ ኃጢአተኛ ነኝ ስለጽድቅ እመክራለሁ፤ እኔ አልጾምም ጹሙ ብየ ግን እመክራለሁ፡፡ በጣም የሚገርሙኝ ግን እኔን ምከረን የሚሉኝ ሰዎች ናቸው፡፡ እኔ ለራሴ መቸ ሆንኩና ነው መካሪ የምሆነው? በእርግጥ የእኔን ድፍረት ተመልክተው እንደሚሆን እገምታለሁ፡፡ እኔ ከፈጣሪየ ጋር ሳልታረቅ ሰዎችን ታረቁ የምል ከንቱ ፍጥረት ነኝ፡፡ እናንተ ቅጠሌን አትመልከቱ ፍሬ አልባ ነኝና፡፡ እናንተ የምትሹ ፍሬ ማፍራትን ነው እኔ ግን ቅጠል ብቻ ነኝ፡፡ ታዲያ እኔ ያላፈራሁትን ፍሬ ታፈሩ ዘንድ እንዴት ልመክራችሁ እችላለሁ?


  

Friday, October 21, 2016

“አጽናኑ ሕዝቤን አጽናኑ” ኢሳ 40÷1

© መልካሙ በየነ

ጥቅምት 10/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
በመጀመሪያ ይህንን እንደ ርእስነት እንድጠቀምበት በውስጥ መስመር ለላከልኝ ፀገየ ባዩ አመሰግናለሁ፡፡
“አጽናኑ ሕዝቤን አጽናኑ” ኢሳ 40÷1 ይህንን ቃል የተናገረው አምላካችን እግዚአብሔር ነው፡፡ ቃሉ የተነገረው በዘመኑ ለነበሩት የሕዝብ መሪዎች ለሆኑ ነቢያት እና ካህናት ቢሆንም ፍጻሜው ግን በዘመናችን ላሉ የሃይማኖት አባቶች ሁሉ ነው፡፡ እዚህ ላይ በዋናነት ሁለት ነገሮችን ማንሣት ተገቢ ነው ብየ አምናለሁ፡፡ የመጀመሪያው እግዚአብሔር ሕዝቤ የሚላቸው እነማንን ነው የሚለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ማጽናናት ምንድን ነው የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ እግዚአብሔር በመጀመሪያ ከፍጥረት ሁሉ አክብሮ እና አብልጦ ሲፈጥረን የመንግሥቱ ወራሾች የሥሙ ቀዳሾች እንድንሆን እንጅ በከንቱ እንድንጠፋበት አይደለም፡፡
የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚባለው በእግዚአብሔር አምላክነት የሚያምንና በእግዚአብሔር ትእዛዝ የሚመራ ነው፡፡ ለዚህም ማስረጃችን እግዚአብሔር ሙሴን አሥነስቶ  እስራኤላውያንን ከግብጽ ባርነት ነጻ ሊወጣቸው በወደደ ጊዜ የግብጹን ፈርዖን “ህዝቤን ልቀቅ” ብሎታል፡፡ እነዚህ በግብጽ ባርነት ውስጥ አገዛዝ የከበዳቸው እስራኤላውያን በእግዚአብሔር አምላክነት የሚያምኑ እና በእግዚአብሔር ትእዛዝና ሥርዓት የሚመሩ ነበሩ፡፡ ለዚህም ነው እግዚአብሔር “ህዝቤ” የሚላቸው፡፡ ከዚህ በኋላ የነጻነት ጉዞውን በሙሴ መሪነት ጀመሩ፡፡ የኤርትራን ባህር ከፍሎ አሻገራቸው፡፡ አሁን ሲና ተራራ ላይ ደርሰዋል ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ለቃል ሊነጋገር ወደ ተራራው ወጥቷል፡፡ ሙሴ በጣም እንደዘገየባቸው ሲረዱ ሕዝበ እስራኤላውያን “ሙሴ አመሌ አመሌ ሲል እሳት አቃጥሎት ሞቶ እንደሆነ አናውቅማና አምላክ ሥራልን” ብለው ወንድሙ አሮንን አስቸገሩት፡፡ አሁን ህዝበ እስራኤላውያን አምላካቸው እግዚአብሔር እንደሆነ ዘንግተዋል፡፡ የሚገርመው ነገር “አምላክ ሥራልን” ማለታቸው ነው፡፡ እግዚአብሔር ባህረ ኤርትራን ከፍሎ አሻግሮ፣ መና ከደመና እያወረደ መግቦ ውኃ ከጭንጫ እያፈለቀ አጠጥቶ፣ ዋዕየ ፀሐይን በደመና ከልሎ እየመራቸው ለዚህ ደርሰዋል እነርሱ ግን ይህንን ሁሉ ውለታ ዘነጉ፡፡ አሮንም ከግብጽ ስትወጡ ይዛችሁት የመጣችሁትን  ንብረታችሁን ሰብስቡ አላቸው፡፡ ለገንዘባቸው ቀናዒ ናቸውና አንሰጥህም ይሉኛል ጊዜ አገኛለሁ እስከዚያ ድረስም ወንድሜ ይመጣልኛል አርፋቸዋለሁ ብሎ ነበር፡፡ እነርሱ ግን ወዲያውኑ ገንዘባቸውን ሰብስበው “አምላክ ሥራልን” አሉት፡፡ አርሱም ጉድጓድ አስምሶ እሳት አስነድዶ ወርቅ ብራቸውን ከዚያ ላይ ጣለው የጥጃ ምስል ሆኖ ወጣላቸው፡፡ አምላካችን ይኼ ነው ብለው ዘፈኑለት ሰገዱለት መስዋእት ሰውለት፡፡ በዚህ ጊዜ  እግዚአብሔር “ሙሴ ህዝብህ በደለኝ” አለው፡፡  ቅድም “ህዝቤ” ያላቸውን አሁን “ህዝብህ” አለው ጠብ ተጀመረ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ህዝብነት ዝም ብሎ የሚኖር የባሕርያችን አይደለም ማለት ነው፡፡ ጠቅለል ሲል ህዝብ ማለት በእግዚአብሔር የሚያምን፣ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የሚጠብቅ፣ በእግዚአብሔር ሥርዓት የሚኖር ማለት ነው፡፡

ሁለተኛው ጉዳይ “ማጽናናት” የሚለው ነው፡፡ ይህ ህዝብ ያዝናል፣ ይተክዛል፣ ይራባል፣ ይጠማል፣ ይሰደዳል፣ ይገደላል፣ ሃብት ንብረቱ ይዘረፋል፣ በበሽታ ይሰቃያል፣ ይታሰራል፣ ይንገላታል ወዘተ፡፡ በዚህ ጊዜ እንባውን አባሽ፣ መካሪ፣ አይዞህ ባይ ይሻል፡፡ ማጽናናት ሃዘንን ማስረሳት ነው፡፡ ማጽናናት ችግሩን መፍታት ነው፡፡ ማጽናናት አይዞህ አለንልህ ብቻህን አይደለህም ብሎ ከጎኑ መቆም ነው፡፡ ማጽናናት ሲራብ ማብላት ሲጠማ ማጠጣት ሲታረዝ ማልበስ ነው፡፡ ማጽናናት የጠፋበትን ሃብትና ንብረት መተካት ነው፡፡ ማጽናናት ማለት የሚያድርበትን የሚያርፍበትን ጎጆ መቀለስ ነው፡፡ ማጽናናት ማለት ከኃጢአት ባርነት መመለስ ነው፡፡ ማጽናናት ማለት ንስሐን ማስተማር ነው፡፡ ማጽናናት ማለት የተስፋ ቆራጭነትን ስሜት ማጥፋት ነው፡፡ ማጽናናት ማለት ተስፋን ማለምለም ነው፡፡

እግዚአብሔር “አጽናኑ ሕዝቤን አጽናኑ” ኢሳ 40÷1 ሲል ከላይ በተመለከትነው መልኩ ነው፡፡ እነዚህ የእግዚአብሔር ህዝቦች በሥጋቸውም በነፍሳቸውም እግዚአብሔርን ሲያመልኩ እንዲኖሩ፣ በፍቅር በደስታ ምድርን እንዲሞሏት፣ መከራ ጭንቀታቸውን እንዲረሱ፣ ኃጢአታቸውን ትተው ወደ ጽድቅ እንዲመለሱ አድርጉ ማለቱ ነው፡፡


አባቶቻችን ዛሬም እኛ ከሃዘናችን፣ ከመከራችን፣ ከስቃያችን ሁሉ እንድንጽናና ምክራችሁ ትምህርታችሁ ያስፈልገናል፡፡ ማጽናናት እንደማስለቀስ እንደማሳዘን ቀላል አይደለም፡፡ ልቡ የተሰበረን ህዝብ አጽናኑ፣ የእኛ ተስፋ ነገ ብቻ ነው፡፡ ነገ አዲስ ቀን ነው ነገ ይችን ምድር ተሰናብተን ለዘለዓለም የምንሄድበት ቀን ነው፡፡ ነገ እንደ ሥራችን ገነት ወይም ሲዖል የምንገባበት ነው፡፡ ዕድሜ ዘመናችንን በምድር ላይ አናሳልፍም፡፡ እርስ በርሳችን አንጠላላ፣ እርስ በርሳችን አንገዳደል፣ አርስ በርሳችን አንወቃቀስ፣ እርስ በርሳችን ቂም በቀል አንያዝ ሁላችንም ነገ ከመቃብር በታች ነን፡፡ ይች ምድር አትጥበበን ነገ ጥለናት የምንሄድ ሰዎች ነን፡፡ ሁላችን በፍቅር እንተያይ፡፡ አባቶቻችን ካህናት፣ ጳጳሳት ሆይ “አጽናኑ ሕዝቤን አጽናኑ” ይላል እግዚአብሔር፡፡ ሃዘናችንን አስረሱን፣ ኃጢአት በደላችንን በንሥሐ እጠቡት፣ ፍቅር ማጣታችንን በፍቅር ግዙት፣ መገዳደላችንን ደም መፋሰሳችንን በመስቀላችሁ ሰላም አቁሙት፣ እናንተ የመጽናናት መንገድን ምሩን እኛም እስከ ገነት ድረስ እንከተላችሁ፡፡ ያለእናንተ እኛ ምንድን ነን? ያለእናንተ ማን ሊያጽናናን ይችላል? ያለ እናንተ ማን ሊደርስልን ይችላል? ለሞቱት እረፍትን እና ምሕረትን ላሉት ፍቅር አንድነትን ከፈጣሪ ዘንድ ለምኑልን፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ለዘለዓለም እንድንኖር እርዱን፡፡ ይህን ካላደረጋችሁ ግን በኃጢአት ወድቀን  “ህዝቤ” ያለንን “ህዝብህ” ብሎ ለጠላት አሳልፎ ይሰጠናል፡፡ ለጠላት “ህዝብህ” ከመባላችን በፊት እናንተ ከፈጣሪያችን ጋር አገናኙን አጽናኑን፡፡ አጽናኙ መንፈስ እስኪመጣልንም ድረስ በኢየሩሳሌም እንጠብቃለን፡፡ “አጽናኑ ሕዝቤን አጽናኑ” ኢሳ 40÷1

Saturday, October 15, 2016

“ሁለት ክብደት በአንድ ሚዛን”

© መልካሙ በየነ

ጥቅምት 5/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
ሰውየው መዛኝ ነው፡፡ የሚገርመኝ ግን እርሱ ራሱ የተመዘነ አይመስለኝም፡፡ በእርግጥ በእኛ አገር እንዲህ ዓይነቱ አሠራር የተለመደ ብቻ ሳይሆን የተዋሐደ ነው፡፡ ሳትመዘን መመዘን ትችላለህ ያ ማለት እኮ ሳትማር ማስተማር ትችላለህ፣ ሳትሰለጥን ታሰለጥናለህ ማለት ነው፡፡ ሳይመዘን የሚመዝነው  ሰውየ “ሚዛን በ 50 ሚዛን በ 50” እያለ ይጮኸል፡፡ ይህን ጩኸቱን የሰማ ሰው ዳግም በዚያ በኩል የሚያልፍ አይመስለኝም፡፡ ሰውየው ከሚጮኸው በላይ የምትጮኽ መሣሪያ ከሚዛኑ አጠገብ አለች፡፡ እርሷ ታዲያ መጮኋን አታቋርም ትላዝናለች፡፡
መዛኙ “ሚዛን በ 50 ሚዛን በ 50” እያለ ይጮኸል፡፡ አንድ ኩንታል ሊሞላው ጥቂት ኪሎዎች የሚቀረው ሰውየ ራሱን ሊመዝን ተጠጋ፡፡ ባለሚዛኑ 50ዋ እንዳትቀርበት እንጅ ሰውየውን መመዘን አልፈለገም፡፡ ሚዛኑን የሚሰብርበት ነው የመሰለው፡፡ ሆኖም ግን መዛኝ ነውና የውስጡን ስሜት ዋጥ አድርጎ የሰማይ ስባሪ የሚያህለውን ሰውየ ወደ ሚዛኑ እንዲወጣ ጠቆመው፡፡ መዛኙ አሁንም “ሚዛን በ 50 ሚዛን በ 50” እያለ ይጮኸል፡፡ አንድ ቀጫጫ ሰው የመዛኙን ጩኸት ሰምቶ ሊመዘን ቀረበ፡፡ የሰማይ ስባሪ የሚያህለው ሰውየ ሚዛኗ ላይ እንደቆመ ነው፡፡ ጎንበስ ብሎ ማነበብ ስላልቻለ “ስንት ኪሎ ነኝ” ብሎ መዛኙን ጠየቀው፡፡ መዛኙም “ሚዛን በ 50 ሚዛን በ 50” ነህ አለው፡፡ ሰውየው ተናደደ፡፡ እኔ ግን በመዛኙ አልፈረድኩበትም ምክንያቱም አፉ “ሚዛን በ 50 ሚዛን በ 50” ከማለት ውጭ ሌላ አልለመደለትምና ነው፡፡ ልማድ ክፉ ነው በጣም ክፉ በሽታ ነው፡፡ እንዲያውም ሰው ተጣልቶ ሲሳደብም “ሚዛን በ 50 ሚዛን በ 50” የሚል ነው የሚመስለኝ፡፡ ልማድ በሽታ ነው ሲባል ብዙ ነገር ትዝ ይለኛል፡፡ ሲጋራ ማጨስ ልማድ የሆነባቸው ሰዎች ሲጋራ ካላገኙ ያዛጋሉ፡፡ የሚገርመው ነገር የሲጋራ ጢስ ሆድ የሚሞላ አለመሆኑ ነው፡፡ ሰው ጢስ ቀረብኝ ብሎ ሲያዛጋ ስታዩ “አይ ልማድ” ማለታችሁ አይቀርም፡፡ ጫት የሚቆረጥሙትንም እንዲሁ ነው የምታዘባቸው፡፡ ፍየሎቻችን የናቁትን ቅጠል ሰዎች ሲያመነዥኩ ሳይ “አይ ልማድ፤ ልማድ እኮ ክፉ በሽታ ነው” እላለሁ፡፡ ወደ ነገሬ ልመለስና ሰውየው 96 ኪሎ ነው፡፡ ሚዛኗ ሰውየውን የፈራችው ትመስላለች 96ን ጽፋ ትርገበገባለች፡፡ መዛኙ 96 ኪሎ ነህ አለው፡፡ ተመዛኙ ሰውየም ከሚዛኗ ከመቅጽበት ወርዶ 50 ሳንቲሙን ወርውሮለት ሄደ፡፡
ቀጭኑ ተመዛኝ ወደሚዛኑ ወጣ፡፡ መዛኙ “ሚዛን በ 50 ሚዛን በ 50”  እያለ ደጋግሞ ይጮኸል፡፡ ቀጫጫው ሚዛኗ ላይ የወጣው በአንድ እግሩ ነው፡፡ ቀጫጫው በአንድ እግሩ እንደቆመ “መዛኝ ስንት ኪሎ ነኝ” አለው፡፡ መዛኙም 45 ኪሎ ነህ አለው፡፡ ከሚዛኗ ወረደ እና 15 ሳንቲም ወረወረለት፡፡ መዛኙ ግራ ገባው “ምንድን ነው ይኼ” አለው ተመዛኙን፡፡ ተመዛኙም “የቅድሙ ትልቁ ሰውየ 96 ኪሎውን በ50 ሳንቲም ተመዝኖ እኔ 45 ኪሎውን ለዚያውም በ1 እግሬ ቆሜ ተመዝኘ 15 ሳንቲም አነሰህ” አለ፡፡ መዛኙ በጣም ተበሳጨና “ቀጫጫ በል 354 ሳንቲም ጨምር” አለው፡፡ ተመዛኙም ያልሰማ መስሎ ትቶት ሊሄድ ሲል መዛኙ አንቆ ያዘው፡፡ ተመዛኙ “በአንድ እግሬ ቆሜ 45 ኪሎ ለተለካሁት እና በ2 እግሩ ቆሞ 96 ኪሎ ለተለካ ሰው እኩል ታስከፍላለህ እንዴ” አለው፡፡ መዛኙም “ስትፈልግ ተኝተህም መመዘን ትችል ነበር እርሱ ያንተ ሂሳብ ነው የእኔ ሂሳብ ደግሞ 50 ሳንቲም ነው” አለው፡፡ ተመዛኙም ነገሩ ስለከረረበት ተጨማሪውን 35 ሳንቲም ወርውሮለት ሄደ፡፡
በአንድ ሚዛን ሁለት ክብደት ሲመዘን ሳይ ገረመኝ፡፡ እንዳትስቁብኝ ግን ሚዛን እንኳን ይህን ሌላስ ይመዝን አይደል እንዴ ምን ያስገርምሃል እንዳትሉኝ፡፡ በሁለት እግሩ ቆሞ የተመዘነ እና በአንድ እግሩ ቆሞ የተመዘነ ሰው እኩል ሂሳብ መክፈላቸው በጣም ያስገርማል እንጅ፡፡ በአንድ ሚዛን ስለተመዘኑ ብቻ እኩል ክፍያ መክፈላቸው ያስገርማል፡፡ በዚህ ህግ መሠረት ሳይሆን ይቀራል ፍርድ የሚፈረደው፡፡ በአንድ ዓይነት ወንጀል ሳይሆን በአንድ ዳኛ ስለተዳኙ ብቻ እኩል መቀጣታቸው አያስገርምም፡፡ በሬ የሰረቀ እና መርፌ የሰረቀ ሰው እኩል ሲፈረድባቸው አይደንቅም፡፡ በእርግጥ ይኼ ሰማያዊ ፍርድ ስላልሆነ ፍትሐዊ ይሆናል ማለት አይቻልም፡፡ በሥራ ቅጥርስ ገጥሟችሁ አያውቅም፡፡ በአንድ ተቋም ስለተማራችሁ ብቻ እኩል የምትቀጠሩበት ጉዳይ አይገርማችሁም፡፡ 5 ዓመት 3 ዓመት ወይም 2 ዓመት የተማረ ሰው በአንድ ተቋም ስለተማሩ ብቻ እኩል ደመወዝ ሲከፈላቸው ይገርመኛል፡፡ ቢያንስ እኮ ያጠናኸው የትምህርት መስክ እና ያስመዘገብከው ውጤት ግምት ውስጥ መግባት ነበረባቸው፡፡ ግን የለም!

በአንድ ሚዛን ተመዘን እንጅ የግድ እኩል ትከፍላለህ፡፡ በአንድ ዳኛ ተዳኝ እንጅ እኩል ይፈረድብሃል፣ በአንድ ሃኪም ታከም እንጅ አንድ አይነት መድኃኒት ይታዘዝልሃል፣ በአንድ ተቋም ተማር እንጅ እኩል ትቀጠራለህ፣ በአንድ መምህር ተማር እንጅ እኩል ውጤት ታገኛለህ፡፡ ይኼ የተለመደ ሆኗል፡፡  በእርግጥ አንድ ሚዛን ሁለት ክብደት መለካቱን ስመለከት ከዚህም ባለፈ ያየሁት ነገር አለ፡፡ ሁለት ሰዎች በአንድ ህግ እኩል ሳይሆኑ ሲቀሩ ታያለህ፡፡ ለምሳሌ ለእኔ የሚሰራ ህግ ላንተ ላይሰራ ይችላል፡፡ እኔ በተዳኘሁበት ህግ አንተ ላትዳኝ ትችላለህ፡፡ ሰው የገደለ ወንጀለኛ በሙሉ አንድ ዓይነት ፍርድ አይጠብቃቸውም፡፡ አንዳንዱ መግደልን እንደመብትም የተሰጠው ይመስላል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ እድሜ ልኩን እስር ቤት ይጣላል አንዳንዱም ከ10 ዓመት በኋላ ይወጣል ብቻ ይለኛኛል፡፡ በአንድ ወንጀል እኩል አለመዳኘት እንደዚህ ነው፡፡ አንድ ሚዛን ሁለት ክብደት እንደለካው ማለት ነው፡፡ ብቻ ብዙ ነገር አለ እናንተም ጨምሩበት!!!!

Wednesday, October 5, 2016

የሚጠት ወይስ የምጽአት ዋዜማ?

© መልካሙ በየነ

መስከረም 25/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
“ሚጠት” መመለስ ነው “ምጽአት” ደግሞ መምጣት ነው፡፡ መከራ፣ ስቃይ፣  እንግልት፣ ረሃብ፣ ጥም፣ እርዛት፣ ሰሚ ማጣት  ያሰድዳል፡፡ መሰደድ ፍርሐት አይደለም፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል  አረጋዊው ዮሴፍን ልጇን ኢየሱስ ክርስቶስን እና  እናቱ ድንግል ማርያምን ይዘህ ወደ ግብጽ ሂድ ብሎታል፡፡ አምላክ ሁሉን ማድረግ ይችላል፤ ንጉሡ ሔሮድስን በተቀመጠበት ዙፋን ላይ ጸጥ ማድረግ ይችላል፤ 14 እልፍ የቤተልሄም ሕጻናት እንዳይሞቱ ማድረግ ይችላል ግን መከራ ሲመጣባችሁ ፈተና ሲገጥማችሁ ክፉ ንጉሥ ሲነሣባችሁ እኔ ያደረግሁትን አድርጉ ለማለት አርአያነቱን ለማሣየት ተሰደደ፡፡ አሁን ወደ ግብጽ እየተሰደዱ ናቸው፡፡ የስደታቸው ምክንያት ደግሞ የክፉው ንጉሥ የሔሮድስ አሰቃቂ ግድያ ነው፡፡ ለዚህ ነው መሰደድ ፍርሐት አይደለም ያልኩት፡፡ ሕጻኑ ያለጊዜው ደሙ አይፈስም ስለዚህ ነው መሰደድን የመረጠው፡፡ ሆኖም ግን ጊዜው በደረሰ ጊዜ ደሙ የሚፈስበት ቀን ሲደርስ ራሱ በፈቃዱ ለገዳዮቹ እጁን ሰጥቷል፡፡ እዚህ ላይ የምንገነዘበው ነገር ለሚገድሉት እጁን ሰጠ እንጅ ልግደላችሁ አላለም፡፡ ለዚህ ነው ክርስትና ውስጥ እንሞታለን እንጅ አንገድልም እንደማለን እንጅ አናደማም እንቆስላለን እንጅ አናቆስልም የምንለው፡፡ ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና በዚህ በዘመነ ሄሮድስ ሁለት ምርጫዎች ብቻ ናቸው ያሉት፡፡ የመጀመሪያው በንጉሡ እጅ መሞት ሌላኛው ደግሞ መሰደድ ናቸው፡፡ እንግዲህ ሁለተኛው ምርጫ ነው ለአረጋዊው ዮሴፍ የተነገረው እርሱም እንደተነገረው ወደ ግብጽ ተሰደደ፡፡ ከዚያም ምን ቢገዙ፣ ምን ቢነዱ፣ ምን ቢጨክኑ ከሞት እጅ ማምለጥ አይቻልምና ይህ ጨካኝ ንጉሥ ሔሮድስ ሞተ ያን ጊዜ “ተመየጢ ተመየጢ ተመየጢ ሱላማጢስ” ተባለች፡፡ አወ አሁን በቤተልሔም መገደል የለም፣ ያ ጨካኙ ንጉሥ ከመቃብር በታች ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ቤተልሄም መመለስ አለባቸው “ሚጠት” ማለት ይህ ነው፡፡ ሰው የሚሰደደው አገሩን ጠልቶ አይደለም ችግር ሆኖበት እንጅ፤ ስለዚህ ያ ችግር ሲፈታ መመለሱ አይቀርም፡፡ የንጉሡ ሞት ለሚጠት ዋዜማ ነበር፡፡
እስራኤላውያንም በግብጽ የባርነት ታሪክ ውስጥ ብዙ እንደተቸገሩ እናውቃለን፡፡ ዛሬ “የግብጽ ፒራሚድ” እያልን ግብጽን የምናነሣት ያኔ ድሮ እስራኤላውያን ራሳቸውን እንደ እባብ እየተቀጠቀጡ ባቦኩት ጭቃና ሲሚንቶ የተገነባ ነው፡፡ ራሄል የመውለጃዋ ቀን ደረሰ ነገር ግን ማንም ሊያሳርፋት አልቻለም ነበር፡፡ ምጧ ደረሰ ጭቃ እያቦካች ነው፡፡ አሁንም እየተደበደበች ምጧን ዋጥ አድርጋ ጭቃ ታቦካ ጀመረች፡፡ አልቻለችም እዛው ጭቃው ላይ ወለደች፡፡ ከዚያም ልጆችሽን ከጭቃው ጋር እርገጫቸው ደማቸው ጭቃችንን ያጠነክርልናልና ተባለች፡፡ አስቡት ይህን ግፍ፡፡ ይህ ግፍ ለእስራኤላውያን “ሚጠት” ዋዜማ ነበር፡፡ እንባዋን ወደ ሰማየ ሰማያት ረጨች አምላክ እንባዋን ተቀበለ ድንቅ መሪ የሆነውን ሙሴ አዘጋጀ ከዚያም ግብጽን ዳግም ባሪያ ሆነው ላይኖሩባት ተሰናብተው ወደ ርስት ሀገራቸው ተመለሱ፡፡ ይህ የእስራኤላውያን ሚጠት ነው፡፡
በተመሳሳይ ወደ ፋርስ ባቢሎን በባርነት በተሰደዱ ጊዜ ኤርምያስ ሳይቀር አብሮ ተሰዷል፡፡ በዚህ ወቅት ሀገሪቱ ተፈታለች ሰው የሚባል ፍጡር ጠፍቶባታል፡፡ ይህ የሚሆነው ለ70 ዓመታት ያህል ነበር፡፡ ከዚህ ጥፋት በእግዚአብሔር ጥበብ የተሠወሩት የኤርምያስ ደቀመዛሙርት ባሮክና አቤሜሌክ ብቻ ናቸው፡፡ ሌላው ህዝብ ግን የአገሩን ጥፋት በዓይኑ ተመልክቷል፤በባርነት ተሰዷል፡፡ አቤሜሌክ ለድውያን የሚቀባ መድኃኒት ሊያመጣ ተላከ ባሮክም መቃብረ ነገሥትን እንዲጠብቅ ተደረገ፡፡ የሚገርመኝ የአቤሜሌክ ጉዳይ ነው፡፡ መድኃኒቷን ቆርጦ ሲመጣ ደከመውና ከጥላ ሥር አረፍ አለ በዚያው 66 ዓመት ተኛ ሲነቃ እንቅልፉ በደንብ አልለቀቀውም ነበር፡፡ ተነሥቶ መንገዱን ሊቀጥል ሲል መንገዱ ሁሉ ጠፋበት አገሪቱ ጠፍታለች ሰው አይኖርባትም በኋላ ግን መልአኩ ከባሮክ ጋር አገናኝቶታል፡፡ ከዚያም መድኃኒቷን ለኤርምያስ በንስር አሞራ ላኩለት፡፡ ያኔ ለሚጠት ዋዜማ ነበር 4 ዓመት ብቻ ነበር የቀራቸው፡፡
አገራችን እንግዳ ተቀባይ፣ በማንም ወራሪ ጠላት ያልተንበረከከች የጀግኖች መፍለቂያ፣ የፍቅር አገር ናት፡፡ ለራበው የሚያበላ፣ ለጠማው የሚያጠጣ፣ ለበረደው የሚያለብስ፣ ለጠላት እጁን የማይሰጥ፣ ለማንም የውጭ ኃይል የማይንበረከክ ጀግና የሚፈልቅባት ቅድስና የማይጠፋባት፣ ጥበብ የሚመነጭባት፣ ጠላት የሚያፍርባት፣ በገንዘብና በብልጭልጭ ነገር የማይታለል ህዝብ ያላት አገር ናት፡፡  ዘመናዊ መሣሪያ ታጥቆ የመጣውን የጣሊያን ጦር በቆራጥ የአገር ፍቅር እንዴት እንዳንቀጠቀጠ ህዝባችንን አይተናል፡፡ ዛሬ ወንድም ወንድሙን ገድሎ ጀግና ተብሎ ማዕርግ እንደሚጨመርለት ያለ ወኔ አይደለም የጥንቱ ጀግንነት፡፡ ዛሬ  እንደ ሔሮድስ፣ እንደ ሂትለር እጃችን በደም ጨቅይቷል፡፡ ወንዞቻችን ደም እያጎረፉ ናቸው፣ ሴቶቻችን ተገዳዮችን እያረገዙ ናቸው፣ የቻሉት ስደትን መርጠው እየተሰደዱ ናቸው ያልቻሉትም በአገራችን መቃብራችንን አድርግልን ብለው ፈጣሪያቸውን እየተማጸኑ ናቸው፡፡ ይህ ዘመን ለሀገራችን ከባድ የሀዘን፣ የዋይታ፣ የለቅሶ፣ የስቃይ ዘመን እየሆነ ነው፡፡ ታዲያ “ሚጠት” ነው ወይስ “ምጽአት” ነው እየቀረበን ያለው፡፡
“ምጽአት” የጌታ ለዘላለም ፍርድ ወደዚህ ዓለም መምጣት ነው፡፡ የምጽአት ዋዜማዎች በርካቶች ናቸው ከእነዚህ ውስጥ ግን በማቴ 24 ላይ “ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣሉ” ይላል፡፡ ዛሬ በእኛ ላይም እንደዚያ እየሆነ ነው፡፡ ጦርን የጦርንም ወሬ በርቀት ሳይሆን በቅርበት እየሰማን ነው፤ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ እየተነሣ ነው፡፡ ለአገራችን አስከፊ የሚሆነው ህዝብ በህዝብ ላይ ከተነሣ ብቻ ነው፡፡ መንግሥት በመንግሥት ላይ፤ መንግሥት በሕዝብ ላይ ቢነሣ ምንም ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም የሚያመጣው ተጽእኖ ከባድ አይሆንም ህዝብ የሌለው መንግሥት ምንም ሊያደርግ ስለማይቻለው፡፡ ህዝብ በህዝብ ላይ ከተነሣ ግን ተጽእኖው ከበድ ያለ ይሆናል፡፡ ህዝብ በህዝብ ላይ ከተነሣ ቋንቋ፣ ቀለም፣ ዘር፣ ጎሳ፣ ጎጥ፣ የደም ዓይነት ሁሉ የጥላቻ ምንጭ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ መንግሥትንም እንዳይቆም ያደርገዋል ሀገርንም ያፈራርሳል፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን “ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣሉ” የሚለው ቃል የምጽአት ዋዜማ ነው፡፡ አገራችንን እንደቀደመ ክብሯ ለማስቀጠል ካስፈለገን ህዝብ በህዝብ ላይ መነሣት የለበትም፡፡ በዘር፣ በጎሳ፣ በብሄር፣ በቋንቋ አንከፋፈል አንድ እንሁን፡፡ መከፋፈል ካለብን ወድደን ባመጣነው ነገር ብቻ እንጅ ተፈጥሮ በቸረን ነገር ሊሆን አይገባውም፡፡ ከሆነ ዘር፣ ከሆነ ብሄር፣ ከሆነ እምነት፣ ከሆነ ቋንቋ ተናጋሪ በሆነ ብሔር የተፈጠርነው ፈልገን አይደለም ይህ የፈጣሪ ሥራ ብቻ ነው፡፡ አገራችን ደግሞ በህብረ ብሔሯ ዓለምን የምታስቀና ናት፡፡ ስለዚህ ይህን ህብረ ብሔር አንድ ማድረግ ካልቻልን መለያየታችን ሞታችንን ያፋጥነዋል፡፡

ለዚህ ነው አሁን በአገራችን እየተፈጸመ ባለው ግድያ የእናቶች ለቅሶ ከፍ ብሎ ሲሰማ ሳስተውል ዋዜማነቱ ወደ ቀደመ ክብራችን ወደ ቀደመ ኃያልነታችን ወደ ቀደመ አልደፈርም ባይነታችን ወደ ቀደመ ጀግንነታችን ልንመለስ ይሆን ወይስ “ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣሉ” እንዳለው ምጽአት ቀርቦ ይሆን ብየ እንዳስብ የተገደድኩት፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ወይ ለ “ሚጠት” ወይ ለ “ምጽአት” ዋዜማ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ አምላከ ቅዱሳን ለአገራችን ሰላምን እንዲሰጥልን ሁላችንም እንጸልይ መፍትሔው ከፈጣሪ ብቻ ነው፡፡ አሁን ደግሞ የፈቃድ ጾም ቢሆንም ነገ መስከረም 26 ጀምሮ የጽጌ ጾም ይጀመራል እስኪ ለዚሁ ዓላማ ብለን ዘንድሮ እንጹመው ሱባኤ እንያዝ፡፡ ሌላው እምነትም በራሱ ለዚሁ ብሎ በእምነት ሥርዓቱ የሚገባውን ያድርግ፡፡

Friday, September 30, 2016

“አባታችን ስንለው ልጆቼ የሚለን እረኛ አግኝተናል”

መስከረም 18/ 2009 ዓ.ም


እረኛ እንደመሆን ከባድ  አደራ የለም፡፡ አደራው ከእግዚአብሔር ዘንድ ሲሆን ደግሞ ይበልጥ ያከብደዋል፡፡ ለጴጥሮስ የተሠጠው የእረኝነት ሥልጣን በጎችን እንዲጠብቅ ብቻ ሳይሆን በሚገባ እንዲያሰማራ ጭምር ነበር፡፡ መጠበቅ ቀላል ነው ማሰማራት ግን ከባድ ነው፡፡ የለመለመ ሣር በሌለበት፣ የእረፍት ውኃ በማይገኝበት ቦታ መጠበቅ ቀላል ነው፡፡ ነገር ግን በጎቹ ይከሳሉ፣ ይጠቁራሉ፣ ይደክማሉ፣ ይራባሉ፣ ይጠማሉ በመጨረሻም ይሞታሉ፡፡ ይህ እረኝነት ችግር አለበት፡፡ ተኩላ ሊነጥቃቸው ቢመጣ ስለበጎቹ ራሱን አሳልፎ አይሰጥም፡፡ ስለዚህ ነው ይህን እረኝነት ችግር አለበት የምንለው፡፡ እረኝነት መጠበቅ ብቻ ሳይሆን በአግባቡ ማሰማራትንም ይጠይቃል፡፡  ይህን ለማድረግ ደግሞ የበጎቹን ባሕርይ በሚገባ ማዎቅ ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም የምናሰማራበትን ቦታ ለመምረጥ የበጎቹን ፍላጎት መረዳት ግድ ይላል፡፡ ውኃ የጠማቸውን በጎች ከለመለመ ሳር ውስጥ፣ የተራቡ በጎችን ደግሞ በእረፍት ውኃ ዘንድ ብናሰማራቸው ምንም ዋጋ የለውም፡፡ ምክንያቱም ለጠማው ውኃ፤ ለራበው ደግሞ ሳር እንጅ ሌላ ፍላጎት እንደማይኖራቸው የታወቀ ነውና፡፡ ስለዚህ ነው እንግዲህ እረኝነት ከባድ አደራ ነው የምንለው፡፡ እውነተኛው እረኛ ስለበጎቹ ራሱን አሳልፎ ይሰጣል፡፡ ተኩላ ሊነጥቃቸው ቢመጣ በመጀመሪያ እረኛው ከተኩላው ጋር ይታገላል፡፡ እረኛው በትግሉ ከተሸነፈ ከዚያ በኋላ ነው እንግዲህ በጎቹን ተኩላ ሊነጥቃቸው የሚችለው፡፡ ከዚያ ውጭ ግን በጎቹ በማንም አይነጠቁም፡፡ እረኝነት ይህ ነው ከእግዚአብሔር ስንቀበለው ደግሞ እጅግ በጣም ከባድ ነው፡፡
በዚህ አስከፊ ዘመን እርስ በርሳችን ደም ስንፋሰስ ሰላም ስትርቀን ወንድሞቻችን ሲሞቱ፣ ሕጻናት ሳይቀር ሲጨፈጨፉ፣ እናቶች በልጆቻቸው አስከሬን ላይ ቁጭ በሉ እየተባሉ ሲደበደቡ የሚያጽናናን አባት ማጣታችን ልባችንን ሰብሮት ነበር፡፡ እንዲያውም ይባስ ብሎ ፓትርያርኩ ከምእመናን በተሰበሰበ ሽራፊ ሳንቲም በሚንቀሳቀሰው የቤተክርስቲያናችን ቴሌቪዥን ላይ ብቅ እያሉ ማን የጻፈላቸውን እንደሆነ ባናውቅም ከአንድ እረኛ የማይጠበቅ መግለጫ መሰል ንግግራቸውን ሲያነበንቡብን በጣም እጅግ አዝነን ነበር፡፡ ኤልያስ ስለ ናቡቴ ከንጉሡ አክአብና ንግሥት ኤልዛቤል ጋር የተጋጨው፣ ዮሐንስ መጥምቅ የወንድምህን ሚስት ልታገባት ህግ አይፈቅድልህም በማለት ከንጉሥ ሔሮድስ ጋር የተጋፈጠው፣ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለ አንዲት ደሃ መበለት ከንግሥት አውዶክስያ ጋር የተከራከረው እና መከራን የተቀበለው፣ አቡነ ጴጥሮስ ኢትዮጵያ ለፋሽስት ባህል እምነት  እንዳትገዛ በማውገዛቸው በጥይት የተገደሉ  እረኝነታቸው እውነተኛ ስለነበር ነው፡፡ ዛሬ ግን ፓትርያርኩ የሚሰጡት መግለጫ እረኝነታቸውን የማያሳይ ምእመናንን ይበልጥ ውስጣቸውን እየጎዳቸው ያለ ነገር ነው፡፡ እረኝነት የሞቱ በጎቹን እየፈታ መቅበር ከዚያም ነፍሳቸውን ማርልን ብሎ ማስተጋባት ብቻ አይደለም እንዳይሞቱ መጠበቅ ጭምር እንጅ፡፡
ለብዙ ዘመናት አባት የሌለን ልጆች ነን ስንል ነበር፡፡ ፓትርያርኩ የሚሰጡት መግለጫ የቅዱስ ሲኖዶሱ እየመሰለን አባቶቻችንን ስንጠላቸው ኖረናል፡፡ ግን አይደለም፡፡ አባት አለን ልጆች መሆን ብቻ ነው የሚጠበቅብን፡፡ በደመራ በዓል ላይ የምእራብ ጎጃም፣ የአዊ እና የመተከል አህጉረ ስብከቶች ሊቀጳጳስ  የሆኑት አቡነ አብርሃም የብዙ ንጹሐን ወገኖቻችን ደም በፈሰሰባት በባህር ዳር ከተማ መስቀል አደባባይ ላይ ተገኝተው ከአንድ መልካም እረኛ የምንጠብቀውን ስንናፍቀው የኖርነውን የተመኘነውን የአባት ፍቅር ሰጥተውን ተመለከትን እና በጣም ደስ አለን፡፡ አባታችን እንደሚከተለው ነበር በህዝብና በመንግሥት መካከል በመሆን የሰላም ንግግር ያደረጉት፡፡
ከዚህ የተረዳነው ትልቁ ነገር የፓትርያርኩ መግለጫ የቤተክርስቲያናችን አለመሆኑን ነው፡፡ እርሳቸውንማ ግማደ መስቀሉ ያለው ግሸን መሆኑን ዘንግተው አዲግራት ላይ አየናቸው እኮ፡፡
የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንደሚባለው ከአንድ ማኅጸን ተወልደው በአንድ ቤት አድገው የምሥራቅ ጎጃሙ ሊቀጳጳስ አቡነ ማርቆስ  ከአሜሪካ ስልክ መትተው “መስቀል አብርሃ” ከሚለው መዝሙር ውጭ ሌላ እንዳይዘመር ሰንበት ትምህርት ቤቶችን አስጠነቀቁ አሉን፡፡ “አንመካም በጉልበታችን እግዚአብሔር ነው የእኛ ኃይላችን፤ መስቀል ኃይልነ መስቀል ጽንእነ መስቀል ቤዛነ” እየተባለ እንዳይዘመር አስጠነቀቁ ተባልን እኛም “መስቀል አብርሃ” ስንል ዋልን፡፡ አቡነ አብርሃም ደግሞ “ወታደሮች ከተሸከሙት መሣሪያ ይልቅ መስቀል ይበልጣል” በማለት በከበቧቸው ወታደርች መካከል ቆመው እውነቱን መሰከሩ፡፡ ልጆቼ ከቤታቸው በሰላም ሲገቡ ሳላይ ወደ መንበሬ አልሄድም ብለው ልጆቻቸው በሰላም መግባታቸውን አይተው በእግራቸው ወደ መንበራቸው ገቡ አሉን ደስ አለን፡፡

በዘመናችን መራራ የሆነውን እውነት ተጋፋጭ አቡነ አብርሃም ዳግማዊ አቡነ ጴጥሮስ ብላቸው እንዴት ደስ ባለኝ ነበር ዳሩ ግን እኔ ስም የማውጣት መብቱ የለኝም፡፡ ለአባታችን ረዥም ዕድሜ ዘመንን ይስጥልን፡፡ አባታችን ስንለው ልጆቼ የሚለን በማግኘታችንም ሁላችንም ኮርተናል ደስም ብሎናል፡፡ ነገር ግን በዚህ ንግግራቸው መከራ እና ስቃይ ሊደርስባቸው እንደሚችል የታመነ ነው፡፡ በርግጥ እርሳቸው ለዚህ እንደማይበገሩ እናምናለን ምክንያቱም እግዚአብሔር ህዝቡን እንዲጠብቁ አደራ ሰጥቷቸዋልና፡፡ ሆኖም ግን ጠባቂው እግዚአብሔር እንደሆነ ብናውቅም  የአባታችንን ጉዳይ ግነ በቅርበት መከታተል እንደሚገባን አሳስባለሁ፡፡

Monday, September 26, 2016

“ደርሰናል!”

© መልካሙ በየነ

መስከረም 16/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================

==============================================
እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም እና በአንድነት አደረሳችሁ! ይህን የምለው ግን ለ2009 ዓ.ም ማለቴ ለአዲሱ ዓመት የመጀመሪያየ ጽሑፍ ስለሆነ ነው እንጅ አዲሱ ዓመት ከገባ በጣም ቆይቷል እናም እንኳን አደረሳችሁ ለማለት በጣም ዘግይቻለሁ፡፡ የሆነው ሆኖ ግን አምላክ በወደደው እና በፈቀደው መጠን ደርሰናል፡፡ ለነገሩ ችግሩ ያለ ከእኔ ጋር ነው፡፡ እንኳን አደረሳችሁ የምንባባለው በዓላትን ጠብቀን ብቻ ነው እንዴ? አረ አይደለም፡፡ ብቻ ግን ልማድ የሆነብን ይመስለኛል፡፡ እንኳን አደረሳችሁ የምንባባለው በዓላትን ጠብቀን ብቻ ነው፡፡ በእርግጥ በርካታ ትውስታዎች  ያሉ በበዓላት ወቅት ስለሆነ እንኳን አደረሳችሁ መባባል ልማድ ቢሆንብንም አይገርምም፡፡ ግን እንጅ በዓል ባልሆኑባቸው ቀናትስ ለምን እንኳን አደረሳችሁ አንባባልም፡፡ በበዓላት ቀን ለመድረስ እኮ በዓላት ያልሆኑ ቀናትን ማለፍ ግድ ነው፡፡ ስለዚህ እንደእኔ በእነዚያ ቀናትም እንኳን አደረሳችሁ ብንባባል መልካም ነው እላለሁ፡፡ ለዚያም ነው አንኳን አደረሳችሁ የምላችሁ፡፡ ዛሬ ላይ መድረስ ቀላል አይደለም ምክንያቱም ለዚህ የደረስነው በራሳችን ፈቃድ ስላልሆነ ነው፡፡
የሆነው ሆኖ ግን ደርሰናል፡፡ ለዛሬም ደርሰናል ነገም እንደርስ ይሆናል የአምላክ ፈቃድ ነው፡፡ ግን የመድረሳችን ትርጉሙ ምን እንደሆነ መረዳት ያስፈልገናል፡፡ አምላክ ለዚህ ቀን ሲያደርሰን ምክንያት አለው እኛ ለዚህ ቀን ስንደርስ ግን ምክንያት የለንም፡፡ ስለዚህ ትልቁ ነገር መድረሱ ሳይሆን የደረስንበትን ምክንያት ማወቅ ነው፡፡ ባለፈው ኃጢአትን አደረግን፣ ባለፈው ሰውን ገደልን፣ ባለፈው ሰውን አማን፣ ባለፈው የሰው ንብረት ሰረቅን፣ ባለፈው በዝሙት ወደቅን ግን ዘንድሮ ደረስን ለምን? ትልቁ ጥያቄ ይኼ ነው፡፡ መድረስማ ደረስን እኮ ግን ምን ቀሪ ሥራ ቢኖረን ነው ለዚህ ቀን የደረስነው የሚለውን መመለስ ተገቢ ነው፡፡ መድረሳችንን ለመልካም ምኞት መግለጫ ብቻ አድርገነው ከቀረን ዋጋ የለንም፡፡ ቸርነቱ ለዚህ ካደረሰን ቸርነቱን ለኃጢአት ሳይሆን ለጽድቅ፣ ለክፉ ሳይሆን ለበጎ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ አምና በነበርንበት ኃጢአት ሳለን እንኳን አደረሳችሁ መባባላችን እንኳን ለኃጢአት አደረሳችሁ ማለታችን እንደሆነ መረሳት የለበትም፡፡ ስለዚህ ለዚህ ቀን መድረሳችንን ለምን እንጠቀመው የሚለውን መመለስ ትልቅነት ነው፡፡ ይህ በሁሉም ዘንድ ይስተዋላል አዲስ ዘመን ሲመጣ አዲስ እቅድ ይዘጋጃል፡፡ አንዳንዱ ለጽድቁ አንዳንዱም ለኃጢአቱ ፤ አንዳንዱ ለሕይወቱ አንዳንዱም ለሞቱ ያቅዳል፡፡ ግን የዚህ ዕቅድ ተግባራዊነት መመዘኛ የለውም፡፡ ደስ ሲለን ለሚቀጥለው ዓመት ልናሸጋግረው መብቱ የራሳችን ስለሆነ ቸል ማለት እናበዛለን፡፡
በቃ አሁን ምንም ጥርጥር የለውም 2009 ዓ.ም ላይ ደርሰናል፡፡ ስለዚህ ነገን ስለመኖራችን ባናውቅም በዚህ ዓመት ምን ልናደርግ አቅደናል? ለሕይወታችን ወይስ ለሞታችን? ለጽድቃችን ወይስ ለኃጢአታችን? ለመጾም ወይስ ለመብላት? ለመዘመር ወይስ ለመዝፈን? ለመቀደስ ወይስ ለመርከስ? ለመነሣት ወይስ ለመውደቅ? ለንስሐ ወይስ ለበደል? ብቻ የራሳችን እቅድ ስለሆነ ራሳችን ብቻ ነን መፈተሸ የምንችለው፡፡ ሁላችሁም እቅዳችሁን ፈትሹት እስኪ ለሕይወት ይጠቅማል? ከጠቀመ ቀጥሉበት ካልጠቀመ ደግሞ ሰርዙት፡፡ ምክንያቱም ለሞት ማቀድ ሳያስፈልግ መሞት ስለሚቻል፡፡ ንስሐ መግባት እንጅ ኃጢአት መሥራት እኮ አይከብድም፡፡ በሕይወት መኖር እንጅ መሞት እኮ ቀላል ነው፡፡ ስለዚህ በጎ እቅድ አቅደን ራሳችንን በሕይወት ማኖር ይገባናል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ፈቃደ እግዚአብሔርን መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡
አምላከ ቅዱሳን በሕይወት እንድንኖር ይርዳን!!!

Friday, September 9, 2016

“ዘመን ለዘመናት”

ጳጉሜን 4/ 2008 ዓ.ም

ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ 
=============================================
በመጀመሪያ ይህንን ገጽ ላይክ ያድርጉ facebook.com/beyenemlkm
==============================================

ዓለም ከተፈጠረችበት ዕለት ጀምሮ ያለውን ያለፈና የሚመጣ ዘመን በተለያዩ የቀን አቆጣጠሮች እንቆጥራለን። ከእነዚህ የዘመንና የቀን አቆጣጠር ስልቶች መካከል አንዱ ያልተበረዘውና ያልተከለሰው የእኛው የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ነው። የእኛ ዘመን አቆጣጠር ዓመትን በ ፲፫ ወር ይከፍላል። ፲፫ ኛዋ ወር ጳጉሜን ትባላለች። ይህች ወር የወርን ቀመር አታከብርም። ፩ ወር ፴ ቀናትን ይይዛል ይህች ጳጉሜን ግን ስትፈልግ ፭ ሲያሻት ደግሞ ፮ ትሆናለች።
ደስ የሚለው ነገር የቤት ኪራይ አይታሰብባትም በእርግጥ ደመወዝም አንቀበልባትም። ባትሰራ ደመወዝህ የሚቆረጥባት ብትሰራ ደግሞ ክፍያ የማታገኝባት ወር ...... ጳጉሜን። የውኃ፣ የመብራት፣ የስልክ ወጭ ግን ከምንጊዜውም በላይ የሚልቅባት ጭማሪ ወይም ትርፍ ወር ናት ……. ጳጉሜን። ይህች ወር መሸጋገሪያ ድልድይ ናት። አሮጌውን ዓመት ሽኝተን አዲሱን ዘመን የምንቀበልባት መሸጋገሪያ ናት። አሮጌው ዘመን ለሚመጣው አዲስ ዘመን ቦታውን ሲለቅ የመልቀቂያ ውሉ  መፈጸሚያና መፈራረሚያ ጳጉሜን ናት።
በባህላችን ዘመን ሲተካ እንኳን አደረሳችሁ እንባባላለን፡፡ እንቁጣጣሽ እየተባባልን መልካም ምኞት እናቀርባለን። አዲስ ዘመን ላይ ብዙ ተስፋ እንጥላለን አዲስ እቅድ እናቅዳለን፣ አዲስ መሠረት እንመሠርታለን። በመንፈሳዊውም ሆነ በሥጋዊው መንገድ እቅድ እናቅዳለን። ዘመኑን መኖር ስንጀምር የተወሰነውን እቅድ እንሰራዋለን፤ የተወሰነውን እንረሳዋለን፤ የተወሰነውንም ለሚቀጥለው ዓመት እናዞረዋለን። ዘመን ወደፊት አሻግሮ ሲያዩት የሚያልቅ አይመስልም፤ ነገር ግን ባላወቅነውና ባላሰብነው ሰዓት ፀሐይ ይጠልቅብናል ዘመን ያልቅብናል። ዘመን ማለት እንዲህ ነው፡፡ በጣም የሚገርመው ግን ላንተ የተሰጠ ዘመን ለእኔ አልተሰጠኝም ምናልባት ግን የሆነ ዘመን የጋራችን ሊሆን ይችላል። 
እንቁጣጣሽ የሚለውን ቃል እንደመልካም ምኞት መግለጫ የምንጠቀመው ዘመኑን በሚገባ ስለምናውቅና ስለምንረዳ ነው። እንቁጣጣሽ የሚለው ቃል የሁለት ቃላት ጥምርታ ነው የ "እንቊ" እና የ "ጣጣሽ" ማለት ነው። የዘመን መለወጫ ወር መስከረም በእኛ አገር ልዩ ወር ነው። ገደሉ፣ ሜዳው፣ ጋራው፤ ሸንተረሩ ሁሉ በተፈጥሮ አበባ የሚያምርበት የሚያጌጥበት የሚፈካበት ወር ነው። የአበቦች መዓዛ እንኳንስ ንቦችን ዝንቦችንም የሚስብበት ወቅት ነው። ስለዚህ ነው እንግዲህ እንቁ የሚያስብለው። ውኃው የሚጠራበት ጋራው የሚያሸበርቅበት እንቁ የሚሆንበት ነው። በሌላ ጎን ደግሞ መስከረም ማለት የተዘራው የማይደርስበት፣ የጎተራው የሚያልቅበት ወቅት ነው። በዓሉን ደግሞ ለማክበር በጉን ዶሮውን ማረድ ለምደናል። ጎተራችን አልቆ በግ እና ዶሮው  በሌለበት ሁኔታ አዲስ ዘመን ስንቀበል ደግሞ ቅር ያሰኘን ይሆናል። ነገር ግን ካልቻልን ምን ማድረግ እንችላላን? ምንም። በተለይ በዚህ ወቅት ደግሞ ከባድ ፈተና ነው። በጉን ከጓሮ ጎትተን አናቀርበው ነገር የለንም። ስለዚህ ምርጫችን መግዛት ብቻ ነው። ያንን ማድረግ ደግሞ አንችልም። ከዚህ በተጨማሪም ልጆች አዲሱን ዘመን ምክንያት አድርገው ልብስ ጫማ እንዲገዛላቸው ይጠይቃሉ፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ትምህርት ቤቶች የሚከፈቱበት ወር በመሆኑ ደብተር እስክብሪቶ እርሳስ ይፈልጋሉ። አቤት የዘመን መለወጭ ጣጣ! እውነትም ጣጣሽ ብንላት ሲያሳት እንጅ አይበዛባትም። ለዚህ ነው እንግዲህ " እንቁጣጣሽ " የምንባባለው። 
ዘንድሮ ደግሞ ማለቴ አዲሱ ዓመት 2009 ዓ.ም ለሀገራችን የደስታ የዘመን መለወጫ አልሆነልንም የሀዘን ሆነብን እንጅ፡፡ ወገኖቻችን በግፍ ደማቸው ፈስሷል፣ ወንድሞቻችን፣ እህቶቻችን ያለርኅራኄ በጭቃኔ ተገድለዋል፡፡ በዚህም አንገታችንን ደፍተናል፡፡ እንደእኔ ከሆናችሁ የዘንድሮው የዘመን መለወጫ በዓል ምንም አልመስልህ ብሎኛል፡፡ በዓል በዓልም አልሸተተኝም ውስጤ በዓሉን ለመቀበል ደስተኛ አይደለም፡፡ ብቻ ግን ዘመናትን የሚያቀዳጅ ፈጣሪ ይህንን ዘመን አሳልፎ መጭውን ዘመን እንድቀበል በሕይወት ስላኖረኝ አመሰግነዋለሁ፡፡
አዲሱን ዓመት የንስሐ፣ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የመልካም ነገር፤ የሰላም፣ የመረጋጋት፣ የመደማመጥ፣ የመተሳሰብ፣ ያድርግልን። ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ በሰላም ያሸጋግረን።
አሜን፡፡

Thursday, September 8, 2016

“ሰውነታችንን ካላስቀደምን ሰላምን አናመጣም”

ጳጉሜን 3/ 2008 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
========================
በመጀመሪያ ይህንን ገጽ ላይክ ያድርጉ facebook.com/beyenemlkm
========================
ሁላችን አሁን ከደረስንበት ደረጃ ከመብቃታችን በፊት ሰው ነበርን፡፡ ሰው ሳንሆን ቀድሞ ሃይማኖት የለንም፣ ሰው ሳንሆን ቀድሞ ብሔር የለንም፣ ሰው ሳንሆን ቀድሞ ዘር የለንም፣ ሰው ሳንሆን ቀድሞ ጎሳ የለንም፣ ሰው ሳንሆን ቀድሞ ጎጥ የለንም፡፡ ከዚህ ሁሉ ቀድሞ የነበረው ሰውነት ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ በስፋት ከሚያስተምሩ የቤተክርስቲያናችን ፈርጦች መካከል አንዱ የሆኑት ብርቅየ ሊቅ መጋቤ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ ናቸው፡፡ እርሳቸው ሰው እንሁን እንደ ሰው እናስብ እያሉ ሁልጊዜ ይሰብካሉ ያስተምራሉ ይመክራሉ ነገር ግን ሰሚ ጆሮ ያጡ ይመስላል፡፡ ሰው እንሁን ሰውነታችንን እናስቀድም ማለት ፖለቲካ አልያም ሃይማኖታዊ ስብከት አይደለም፡፡
ሰውነታችንን ስናስቀድም በሃይማኖት አንለያይም ምክንያቱም ሃይማኖት ሰው ከመሆናችን በኋላ የሚመጣ ጉዳይ ነውና፡፡ የኦርቶዶክ ተዋሕዶ፣ የፕሮቴስታንት፣ የእስልምና፣ የካቶሊክ ወዘተ እምነት ተከታዮች መሆን የጀመርነው ሰው ከመሆናችን በኋላ ነው፡፡ ስለዚህ በሃይማኖት ልዩነትን ፈጥረን አንዱ ለአንዱ ጠላት የሚሆነው ሰውነታችንን ስለማናስቀድም ብቻ ነው፡፡ አብያተ ክርስቲያናት ሲቃጠሉ እንመለከታለን፣ መስጊዶች ሲፈራርሱ እናስተውላለን ይህ ክስተት የሚፈጠረው ሰውነታቸውን ባላስቀደሙ ሰዎች ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ሃይማኖታቸውን ሰው ከመሆናቸው ያስቀደሙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ሃይማኖትን እንደልዩነት በመጠቀም ከሰውነት አንድነታችን መውጣት የለብንም፡፡ ምንም እንኳ በሃይማኖት ብንለያይም ሰው በመሆናችን ግን እንተባበራለን፡፡ ትብብራችን ደግሞ ቀድሞ ባገኘነው የሰውነት ጸጋ እንጅ በኋላ ባገኘነው የሃይማኖት ጸጋ መሆን አይገባውም፡፡
ሌላው ሰውነታችንን ስናስቀድም በሃገር፣ በዘር፣ በብሔር፣ በጎሳ፣በጎጥ ወዘተ አንለያይም፡፡ አገሬ፣ ዘሬ፣ ብሔሬ፣ ጎሳየ፣ ጎጤ ወዘተ ከማለታችን በፊት ሰው መሆናችን ይቀድማል፡፡ ሰው ስንሆን ያን ጊዜ አምላክ ባወቀ በሆነ አገር፣ በሆነ ብሔር፣ በሆነ ጎጥ፣ ከሆነ ዘር እንድንወለድ አደረገን፡፡ እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባው ጉዳይ ፈልገን የተወለድንበት አገር፣ ብሔር፣ ዘር፣ ጎሳ እንደሌለ ነው፡፡ የአምላክ ፈቃድ ሆኖ ከሆነ አገር፣ ከሆነ ብሔር፣ ከሆነ ጎጥ፣ ከሆነ ዘር ፈጠረን እንጅ እኛ የመረጥነው እንዳልሆነ እናስተውላለን፡፡ ስለዚህ በብሔር፣ በቋንቋ፣ በዘር ከመከፋፈላችን እና አንድነታችንን ከመበታተናችን በፊት ሰውነታችንን እናስቀድም፡፡ ሰውነታችንን ካስቀደምን በዘር፣ በጎሳ፣ በቋንቋ በብሔር አንከፋፈልም፡፡ ደግሞም እኮ ሁሉን ያደረገልንን አምላክ ልናመሰግነው ይገባል እንጅ በእነዚህ ነገሮች መለያየትን እንዴት እንቀበላለን፡፡ ዛሬ በብሔር በቋንቋ እና በዘር እንድንከፋፈል ያደረገን ሰውነታችንን ስላላስቀደምን ብቻ ነው፡፡ የትም ተወለድ የት፣ የትም ተፈጠር የት ሰው ነህ፡፡ ሰው በመሆንህ ደግሞ አንድነትን ታጠነክርበታለህ እንጅ ልዩነትን አትፈጥርበትም፡፡ ምክንያቱም ሰው ከሰው በምንም ሊለያይ አይችልምና፡፡
ሰውነታችንን ስናስቀድም ማንም ማንንም አይገድልም፤ ማንም በማንም አይሞትም አይገደልምም፡፡ አንዱ ባለስልጣን ሌላው ሎሌ፣ አንዱ ገዳይ ሌላው ተገዳይ፣ አንዱ ሰጭ ሌላው ተቀባይ፣ አንዱ ጠጋቢ ሌላው ተራቢ፣ አንዱ ረጋጭ ሌላው ተረጋጭ በመሆን መለያየት የመጣው ሰው ከመሆናችን በኋላ ነው፡፡ እንደ ሰው ስታሰብ ሌሎች ባንተ ላይ ሊያደርግብህ የማትፈቅደውን ነገር በሌሎች ላይ አታደርግም፡፡ ስለዚህ አንተን እንዲገድሉህ እንደማትፈቅድ ሁሉ ሌሎችን ለመግደል አትፈቅድም፡፡ አንተን ሲረግጡህ ሲጨቁኑህ እንደማትወድ ሁሉ ሌላውን አትረግጥም አትጨቁንም፡፡ ስለዚህ ነው ሰውነታችንን ማስቀደም አለብን የምንለው፡፡ አንተ ባማረ በተዋበ ባሸበረቀ በዕንቁ ባጌጠ ቪላ ቤት ላይ እየተንፈላሰስክ ሌላው መንገድ ላይ ወድቆ በብርድ ሲሰቃይ መመልከት እንደ ሰውነቱ ለማያስብ እንጅ እንደሰውነቱ ለሚያስብ ሰው እጅግ በጣም ከባድ ነው፡፡
እንደሰውነታችን ስናስብ ሰውን አንገድልም ምክንያቱም እኛን እንዲገድሉን ስለማንፈልግ፡፡ አሁን ግን እያስቀደምነው ያለ ጉዳይ ከሰውነታችን በኋላ የመጡ ጉዳዮችን ሆኗል፡፡ በቅርቡ ያየነው እና ያስተዋልነው የአገራችን ጉዳይ ሰውነታቸውን ካላስቀደሙ ወገኖች በተሰነዘረ ጥቃት የብዙዎች ደም ፈስሷል፡፡ ሁልጊዜ ሳስበው ከኅሊናየ አልወጣልህ ያለኝ ግን ማረሚያ ቤቶች ሲቃጠሉ ለማምለጥ ሞክረዋል ተብለው በጸጥታ ኃይሎች የተገደሉት ንጹሐን ወገኖቻችን ናቸው፡፡ በእውነት እንደሰውነት ለሚያስብ ሰው ማረሚያ ቤቱ ሲቃጠል ታሳሪዎች ምን ማድረግ ነበረባቸው? በእሳት ላለመቃጠል ከማምለጥ ውጭ ምን ተስፋ አላቸው? ከእሳቱ ከማምለጥ ውጭስ ምን ዓይነት እርምጃ መውሰድ ነበረባቸው? ሳስበው በጣም ይዘገንነኛል፡፡ በእሳት ተቃጥለው እንዲሞቱ መወሰን ሰው ከመሆን ውጭ ያለው የሚያስበው ከንቱ ሀሳብ ነው፡፡ እንደ ሰውነታችን ካሰብን በእርግጠኝነት እንዳይቃጠሉ እንተባበራቸው ነበር እንጅ አመለጡ ብለን ተኩሰን አንገድላቸውም ነበር፡፡
ሰውነት አንድ ያደርጋል፡፡ በመወለድ አንድ ሆነናል በመሞትም አንድ እንሆናለን፡፡ በመብላት አንድ ሆነናል በመጠጣትም አንድ እንሆናለን፡፡ ዘርን በመተካት አንድ ሆነናል በማሰብም አንድ እንሆናለን፡፡ ስለዚህ ከሁሉ አስቀድመን ሰው መሆናችንን እናረጋግጥ ከዚያ በኋላ ሃይማኖት፣ ብሔር፣ ቋንቋ፣ ጎሳ ከዚህ በኋላ የሚመጣ ጉዳይ ነው፡፡ ሰው ስንሆን ለሁሉ እንራራለን፣ ሰው ስንሆን ለሁሉ እናስባለን፣ ሰው ስንሆን ሁሉን እንመግባለን፣ ሰው ስንሆን ሁሉን እንታደጋለን፣ ሰው ስንሆን ሁሉን በፍቅር እንመለከታለን፣ ሰው ስንሆን አድልዎ አንፈጽምም፣ ሰው ስንሆን ለሁሉ እኩል እንጨነቃለን፡፡ ሰው ካልሆንን ግን የዚህ ተቃራኒ እንሆናለን፡፡ እኛ ጮማ እየቆረጥን ጠጅ እያንቆረቆርን ሌላው በረሃብ ሲያልቅ እንስቃለን፡፡ እኛ ባማረ ቤት ሞቆን እየኖርን የሚወጥሩት ሸራ እንኳን አጥተው መንገድ ላይ የሚያድሩትን ወገኖቻችንን አናስባቸውም፡፡ ስለዚህ እንደሰውነታችን እናስብ እንደሰውነታችን ካሰብን ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት ማንም ሊቀማን ማንም ሊነፍገን የማይችላቸው ሃብቶቻችን ይሆናሉ፡፡

Wednesday, September 7, 2016

“የወላጅ ቁንጥጫ ረሃብን አያጠፋም”

ጳጉሜን 2/ 2008 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

=======================
በመጀመሪያ ይህንን ገጽ ላይክ ያድርጉ facebook.com/beyenemlkm 
=======================

አንድ ነገር አሰብኩ፤ ያሰብኩትንም እንዲህ ጻፍኩት፡፡ ልጆች ሲርባቸው፣ ሲበርዳቸው፣ ሲታመሙ ወዘተ ያለቅሳሉ፡፡ የሚያለቅሱበትን ምክንያት በአግባቡ መለየት የወላጆች ድርሻ ነው፡፡ የሕጻንኛን ቋንቋ በሚገባ ያልተረዳ ወላጅ በማይመክርና በማያስተምር እንዲሁም በማይገስጽ መልኩ ልጆቹን ይቀጣል፡፡ ልጆቹም ለጥቂት ጊዜ ከማልቀሳቸው ዝም ይላሉ፡፡ ከማልቀሳቸው ዝም ስላሉለት ብቻ ግን ለልጆቹና ለራሱ ሰላም የፈጠረ የመሰለው ወላጅ ጅል ነው፡፡ ምክንያቱም ልጆቹ ከማልቀሳቸው ዝም ያሉ ችግራቸው ስለተፈታላቸው ወይም ጥያቄያቸው ስለተመለሰላቸው ሳይሆን ስለቆነጠጣቸው እና ስላስፈራራቸው እንደሆነ አልተረዳም ማለት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ወላጅ የወላጅነት ድርሻው ለስሙ አባት ወይም እናት ለመባል ብቻ ነው፡፡
ራበኝ አብላኝ ጠማኝ አጠጣኝ እያለ ረሃብ ጎድቶት የሚያለቅስብንን ህጻን እንደወላጅነታችን ማብላትና ማጠጣት ካልቻልን ያልቻልንበትን ምክንያት ማስረዳት ይጠበቅብናል እንጅ ቆንጥጠን ዝም ማስባል አይገባንም፡፡ ልጆቹ እኮ ያለቀሱብን ስለራባቸው እና ስለጠማቸው ነው፤ ታዲያ የእኛ ቁንጥጫ እና ኩርኩም ረሃብን የሚያስታግስ ይመስል ለምን ቁንጥጫና ኩርኩሙ አስፈለገ? በተገቢው መልኩ ልጆቻችን ያለቀሱበትን መረዳትና ተገቢውን መልስ መስጠት የወላጅነት ድርሻችን ነው፡፡ እንደወላጅነታችን ተገቢውን መልስ መስጠት ከእኛ የሚጠበቅ ነው፡፡ ለምን አለቀሱብን አትበሉ ሲርባቸው ያለቅሳሉ፣ ሲጠማቸው ያለቅሳሉ፣ ሲበርዳቸው ያለቅሳሉ፣ ግፍ ሲበዛባቸው ያለቅሳሉ፡፡ የወላጅ ቁንጥጫ ደግሞ ረሃብን አያስታግስምና ልጆች ለጊዜው ከማልቀሳቸው ቢቆጠቡም ቆይተው ግን ለቅሷቸውን በአዲስ መልኩ ይጀምሩታል፡፡ ስለዚህ ሁነኛው መፍትሔ የወላጅነትን ምግባር ተላብሶ የልጆችን እንባ ማበስ  ነው፡፡ ምክንያቱም የልጆች ጥያቄ ረሃብና ጥማት በዛብን የሚል እንጅ ማልቀስ አይደለም፡፡ ወላጆችም እንዳያለቅሱባቸው ከመደብደብ ባለፈ ለምን እንዳለቀሱባቸው መረዳት አይፈልጉም፡፡ ይህ ደግሞ ዘላቂ መፍትሔ የሚሆንበት አንዳች ነገር የለውም፡፡
በርካቶቻችን መፍትሔ የምንሰጠው ለችግሩ ሳይሆን ችግሩ ለወለደው ሌላ ችግር ነው፡፡ ጎርፍ ቤታችን ውስጥ ሲገባ የገባውን ውኃ ወደ ውጭ እየረጨን መጨረስ መፍትሔ እናደርጋለን፡፡ ከዚያም በጎርፉ የተበላሹ ዕቃዎቻችንን ፀሐይ ላይ በማስጣት ማድረቅ እንጀምራለን፡፡  ነገር ግን ይህ ሁሉ መፍትሔ ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም ነገ ጎርፉ ቤታችን ላለመግባቱ ምንም ዋስትና የለንምና፡፡ ስለዚህ ዘላቂ የሚሆነው መፍትሔ የጎርፉን አቅጣጫ ማስቀየር አልያም ቤትን ማስተካከል ብቻ ነው፡፡
በሀገራችን እየሆነ ያለውም እንደዚሁ ያለ ነው፡፡ ሰልፍ እንዳይወጡ በማስፈራራት ወይም የወጡትን በመደብደብ የህግ የበላይነትን አስከብረናል ሰላምንም አስፍነናል ማለት ያስቸግራል፡፡ ህዝቡ ሰልፍ እንዳይወጣ ማድረግ ወይም የተሰለፈውን መበተን በምንም መልኩ ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን አይችልም፡፡ ችግሩ እኮ ሰልፍ መውጣታቸው አይደለም ሰልፍ እንዲወጡ ያደረጋቸው ጉዳይ እንጅ፡፡ ሰልፍ እንዲወጡ ያደረጋቸው ምክንያት ሰልፉ ቢበተንም አብሮ አይበተንም፡፡ የተሰለፈውን ሰው ብናስፈራራው እና ብንገድለውም ሰልፉን ሊበትነው የሰውን ቁጥር ሊቀንሰው ይችላል እንጅ ችግሩን ሊፈታው አይችልም፡፡ ስለዚህ መፍትሔ ሊሆን የሚችለውን ነገር እንደተማረ፣ ለሀገር እንደሚያስብ፣ ለወገን እንደሚቆረቆር ሰው ሆነን በጋራ ልንፈታው ያስፈልጋል፡፡ ህጻናት ተርበው ሲያለቅሱ በወላጅ ቁንጥጫ ለጊዜው ዝም ቢሉም ረሃቡ ሲጸናባቸው ቁንጥጫውን ከምንም ሳይቆጥሩ አብልጠው እንደሚያለቅሱ ሁሉ ችግሩ ካልተፈታለት ይህ ህዝብም ሞትን ሳይሰቀቅ ወደፊት ማለቱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ የወገኖቻችን ደም ሳይፈስ ዘላቂ መፍትሔ የሚፈለግበትን መንገድ መፈለግ ይገባናል፡፡

Friday, August 26, 2016

“ከጎልያድ ሰይፍ የሚልቅ የዳዊት ጠጠር”


© መልካሙ በየነ

ነሐሴ 20/ 2008 ዓ.ም

ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
በጉልበቱ እና በኃይሉ የሚመካ ፍልስጥኤማዊ ሰው ነበረ፡፡ እርሱም ያልተገዘረ ሲሆን በእግዚአብሔር ህዝብ በእስራኤላውያን ላይ እጁን ጫነባቸው፡፡ እነርሱንም ለመግደል ይዝት እና ያስፈራራ ነበር፡፡ ንጉሡ ሣዖልም እነዚህን ፍልስጥኤማውያንን ድል ለሚያደርግለት ሽልማትን አዘጋጀ፡፡ ነገር ግን ይህን ግዙፉን በጉልበቱ እና በኃይሉ እንዲሁም በታጠቀው መሣሪያ የሚመካውን ጎልያድ ማንም እስራኤላዊ ሊያሸንፈው አልቻለም ነበር፡፡ ጎልያድ ላይ ዛቻ አለ፣ ጎልያድ ላይ ሰይፍ አለ፣  ጎልያድ ላይ ኃይል አለ፣ ጎልያድ ላይ ጉልበት አለ፣ ጎልያድ ላይ ማስፈራራት አለ፣ ጎልያድ ላይ የጦር መሣሪያ አለ፡፡ ለዚህም ነው ፍልስጥኤማውያን በዚህ ሰው ተመክተው በእስራኤላውያን ላይ የተገዳደሩ፡፡
አምላክ ይሁን ካላለ በቀር አንዲት ነገር አትደረግም፡፡ ጎልያድ የእግዚአብሔር ሰው አይደለም፡፡ የህዝበ እስራኤላውያንን ደም ለማፍሰስ የሚፈጥን እጅ የያዘ ግፈኛ ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ የህዝቡን ደም ከእጁ ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ የጎልያድ ዛቻ፣ የጦር መሣሪያ፣ ማስፈራራት፣ ኃይልና ጉልበት ሁሉ በእስራኤላውያን ዘንድ ቦታ የለውም፡፡ ምክንያቱም እስራኤላውያን የእግዚአብሔር ሰዎች ናቸውና፡፡ እነርሱ ዘንድ እምነት አለ፣ እነርሱ ዘንድ እግዚአብሔር አለ፣ እነርሱ ዘንድ ድል መንሳት አለ፣ እነርሱ ዘንድ ማሸነፍ አለ፣ እነርሱ ዘንድ ሞገስ አለ፡፡ ለጊዜው ጎልያዳውያኑ ደም ሊያፈሱ ይችላሉ፣ ለጊዜው ፍልስጥኤማውያኑ ሊገድሉ ይችላሉ፣ ለጊዜው ጎልያዳውያኑ ያሸነፉ ይመስላቸዋል፣ ለጊዜው ፍልስጤማውያኑ ኃይላቸው ከእነርሱ ጋር ይቆይ ይመስላቸዋል፣ግን አምላክ ከማን ጋር እንዳለ አያውቁም፡፡
ጎልያዳውያኑ! ዛሬ ግደሉን እንሞታለን፣ ዛሬ ደማችንን አፍስሱት፣ ዛሬ አስፈራሩን ዝም እንላለን፣ ዛሬ ተዋጉን ድል እንደረጋለን፣ ዛሬ ሥጋችንን አቃጥሉት እንቃጠላለን፣ ዛሬ በሰይፍ ቁረጡን አንገታችንን እናመቻቻለን፣ ዛሬ በጥይት ደብድቡን ደረታችንን እንሰጣለን፣ ዛሬ እሰሩን እጅ እንሰጣለን፣ ዛሬ አሸማቁን እንሸማቀቃለን፣ ዛሬ በኃይላችሁ ተመኩ፣ ዛሬ በጉልበታችሁ ተመኩ፣ ዛሬ በመሣሪያችሁ ተመኩ፣ ዛሬ በሚሆነው ሁሉ ነገር ስልጣን ይኑራችሁ፡፡ ግን አይቀጥልም፡፡ ምክንያቱም ጎልያዳዊነት የሚዝተው፣ ጎልያዳዊነት የሚያሸንፈው፣ ጎልያዳዊነት የሚገዳደረው የዳዊት ጠጠር እስኪለቀም ድረስ ብቻ ነው፡፡ ዳዊት ጠጠሩን ይሰበስባል፡፡ ከሁሉ የሚያንሰው ዳዊት ከሁሉ የሚበልጠውን ጎልያድ አሸንፈዋለሁ ብሎ ሊገጥመው ነው፡፡ ጎልያድ መገዳደር፣ መዛት፣ በጉልበቱ መመካት ልማዱ ነውና  ወንጭፉን ይዞ ጠጠሩን ለቅሞ የተጠጋውን ዳዊትን ውሻ የምትገድል መሰለህን ወንጭፍ ይዘህ የመጣህ አለው፡፡ ዳዊት ከጠጠሩ ጋር አብሮት ያለውን አምላክ ያውቃል፡፡ ለጎልያድ መለሰለት ውሻስ ጌታውን ያውቃል አንተ ግን ጌታህን የማታውቅ አህዛብ ነህ አለው፡፡ ዳዊት ዘንድ ፍርሐት የለም፡፡ ከጎልያዳዊ ሰይፍ ይልቅ ዳዊታዊ ጠጠር እንዲልቅ በውስጡ ያውቃልና፡፡
ዳዊት ጠጠሩን ከወንጭፉ ላይ አኖረ፡፡ ጎልያድ በዳዊት ድርጊት ሳቀ፣ ተደነቀ፣ ከእጀ የሚያስጥልህንም አየዋለሁ ብሎ ዛተ በራሱም ተመካ፡፡ ጎልያድ እስከዛሬ ድረስ ደም ያፈሰሰ፣ ደሀ የበደለ፣ ፍርድ ያጓደለ፣ በባርነት አገዛዝ ቀንበር ስር ህዝቡን ያስጨነቀ ዳዊት ስላልተነሣ ብቻ ነው፡፡ ዳዊት ሲነሣ ግን ጎልያድ ጎልያድነቱ ያከትምለታል፡፡ ዳዊት ጠጠሩን በወንጭፉ ላይ አስቀመጠና ወደ ጎልያድ ወረወረው፡፡ ጎልያድን ለተመለከተው ሰው እንኳን በጠጠር በጦርም የሚሸነፍ ሰው አይደለም፡፡ ጎልያድ በዚያ ዘመን በነበረ ማንኛውም መሣሪያ የሚሞት ሰው አይመስልም ነበር፡፡ ዛሬ ግን ትልቅነቱን እንድንረሳ በትንሽ ጠጠር ወደቀ፡፡ ዳዊት ጎልያድን በጠጠር ግንባሩ ላይ መትቶ ጣለው፡፡ ፍልስጥኤማውያን ወደቁ እጃቸውን በአፋቸው ላይ ጭነው ዝም አሉ፡፡ እስራኤላውያንም የድል ዝማሬን ዘመሩ፡፡ ዳዊት በጠጠር ከጣለው ጎልያድ ላይ ሰይፉን መዘዘና ቸብቸቦውን ቆረጠው፡፡ ከእስራኤላውያን ዘንድም ስድብን አራቀ፡፡ ዳዊታዊ ጠጠር እንዲህ ያለ ኃይል አለው፡፡
ዛሬ በሐገራችን ጎልያዳዊ አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ሰዎች በዝተዋል፡፡ በመሣሪያቸው ተመክተው ያስፈራራሉ፣ ያስራሉ፣ ያንገላታሉ፣ ይገድላሉ፡፡ ምድርን በህዝቦቿ ደም አረከሷት፡፡ የህዝቡን ጩኸት በመሣሪያ በዛቻና በማስፈራራት ለማፈን ጥረት ያደርጋሉ፡፡ በመንግሥት መገናኛ ብዙኀን ላይም ይህን ማስፈራሪያ አብዝተው ያስተጋባሉ፡፡ ግን ዕለት ዕለት ቁጣው እየጨመረ መጥቷል፡፡ ዳዊታዊ ቁጣ መጥፎ ነው፣ ዳዊታዊ አስተሳሰብ ከባድ ነው፣ ዳዊታዊ ጠጠር አስቸጋሪ ነው፡፡ እስከዛሬ ድረስ ስናርደው ዝም ያለን ዳዊታዊ ጠጠርን እየፈለገ ስለነበረ ነው፡፡
እባካችሁ እርስ በርሳችን እንሰማማ፡፡ እኛው ገዳዮች እኛው ተገዳዮች፣ እኛው አስጨናቂዎች እኛው ተጨናቂዎች፣ እኛው አሳዳጆች እኛው ተሳዳጆች፣ እኛው አቃጣዮች እኛው ተቃጣዮች ሆነን እስከመቼ እንቀጥላለን፡፡ ጎልያዊ ዛቻ፣ ጎልያዳዊ ማስፈራሪያ የዳዊትን ቁጣ ያስነሣል፡፡ ከሁሉ ታናሽ የሆነውን ብላቴና ያስቆጣል፡፡ ዳዊት እኮ ከእርሱ የሚበልጥ ስንት ሚሊዮን ህዝብ እያለ ነው ገና በ12 ዓመቱ ጎልያዳዊ ዛቻ የቀሰቀሰው፡፡ ስለዚህ ሌሎችን ብላቴኖችን የሚቀሰቅስ ጎልያዳዊ ማስፈራሪያችንን እና ትምክህታችንን እናስወግድና እንነጋገር፡፡ ትናንት የገነባናቸውን ዛሬ ካፈረስናቸው፣ ትናንት አደግን ተመነደግን ያልንባቸውን ዛሬ ከናድናቸው ብልጽግናችን ከቶ ወዴት አለ፡፡ እየሞተ ያለው የእኛው ወገን ነው እየገደለ ያለም የእኛው ወገን ነው፡፡ አልሸባብ አልመጣብን፣ አይሲስ አልደረሰብን፣ ቦኮ ሐራም አልተቃወመን ታዲያ ማንን ማን ይገድላል? የእግዚአብሔርን ህንጻ እያፈረስን እንደሆነ አይገባንም እንዴ? እኛ በምናፈርሰው የእግዚአብሔር ህንጻ እግዚአብሔር ተቆጥቶ ራሱ በራሱ ሥልጣን እኛን እንዲያፈርሰን እወቁ፡፡ አትጠራጠሩ ዳዊትን አስነስቶ ቸብቸቧችንን ያስቆርጠናል፡፡ እኛ ለገነባነው እና እኛ ለሠራነው ህንጻ መፍረስ ተጨንቀን አይደል እንዴ መሠረተ ልማቶች ፈረሱ በሚል ሰበብ ሰሪዎቹን እየገደልናቸው ያለን፡፡ ታዲያ እግዚአብሔርስ ገንባን ሳንለው የገነባንን የራሱ ንብረቶች የሆንነውን ህንጻዎች ስታፈርሱን ዝም ይል ይመስላችኋል፡፡ በፍጹም ዝም አይልም፡፡ ቃየን ይቅበዘበዛል ያገኘው ሁሉ ይገድለዋል፡፡ ጎልያድ ይዝታል ዳዊታዊ ጠጠር ግን ኃይልን ታደርጋለች፡፡
“ንኡስ አነ እምአኃውየ፣ እኔ ከወንድሞቼ ታናሽ ነኝ” ያለው ዳዊት “ወአሰሰልኩ ጽእለተ እምደቂቀ እስራኤል፤ ከእስራኤላውያን ልጆች ዘንድ ስድብን አጠፋሁ” በማለት የደስታ ዝማሬን ዘመረ፡፡ ዳዊት ሲዘምር ጎልያድ ወዴት ነበር? በጠጠር ወድቆ ሞቶ ነበር፡፡ ስለዚህ ከጎልያድ ሰይፍ የሚልቅ የዳዊት ጠጠር በህዝቡ ዘንድ እንዳለ አውቀን ህዝባችንን ለሚበልጥ ቁጣ ባናነሣሣው የሚል ምክር ለሚሰማኝ ሁሉ እመክራለሁ፡፡ አልሰማም ለሚል ግን ዳዊታዊ ጠጠር ተነሥቶ ጎልያዳዊ አስተሳሰብ ወድቆ “ወአሰሰልኩ ጽእለተ እምደቂቀ ኢትዮጵያ፤ ከኢትዮጵያውያን ልጆች ዘንድ ስድብን አጠፋሁ” የሚለውን የድል ዝማሬ ሊዘምሩበት ጊዜው ቅርብ ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ወደ ኋላ ዞራችሁ ያለፈውን መንግሥት ታሪክ መርምሩ፡፡ “ምክር ሰናዪት ለኩሉ ዘይገብራ፣ ለሚያደርጋት ለሚፈጽማት ሁሉ ምክር መልካም ናት”
አበቃሁ

Tuesday, August 23, 2016

“በአግባቡ ያልተጠገነ ስብራት”

ነሐሴ 17/ 2008 ዓ.ም

ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

በተለያዩ አጋጣሚዎች ሰዎች ለስብራት ይዳረጋሉ፡፡ በብዛት የሚስተዋለው ስብራት ግን አካላዊ ስብራት ነው፡፡ ይህ አካላዊ ስብራት በእግር፣ በእጅ፣ በአጥንት ላይ በብዛት ይስተዋላል፡፡ በብዛት የሚከሰተውም ከመውደቅ ጋር ተያይዞ ነው፡፡ በተለይ በክረምት ወራት ከላይ ዝናብ ሲዘንብ ምድር ውኃ መቋጠር ትጀምራለች፡፡ በዚህ ጊዜ ሙሉ በጋውን ሲዘልባት የነበረውን ሁሉ ዳዴ እያሰኘች ትነዳዋለች፡፡ አንዳንዱንም እግርህን አልቀበልም ብላ ሰማይ አድርሳ ታፈርጠዋለች፡፡ ያኔ ነው ነገር ተበላሽቶ ስብራት የሚባል ጣጣ የሚፈጠረው፡፡ ከዚያም እንደተሰበሩ አውቆ መጠገን የሚባለውን ፍልስፍና መዘመር ያስፈልጋል፡፡ ስለተሰበርን ብቻ መሰበርን እንደ ውርደት ቆጥረን ስብራታችንን አፍነን መያዝ የለብንም፡፡ ሆኖም ግን መጠገን እንደሚያስፈልገን ራሳችንን ካሳመንን በኋላ ጠጋኝ መፈለግ ግድ ይለናል፡፡ መጠገን እና መጠገን (ጠ ይጠብቃል) ጠጋኝ እና ጠጋኝ ሁሉም አንድ አይደሉም፡፡ አንዳንዱ ጊዜያዊ ጥገና ይሰጣል፣ አንዳንዱም ጥገና የሚመስል ነገር ያደርጋል፣ አንዳንዱ ደግሞ ሙሉ ጥገኛ ይሰጣል፣ አንዳንዱ ደግሞ ከጥገናም በላይ ሌሎችን አስፈላጊ ምክሮችን እና ተሞክሮዎችን ይለግሳል፡፡
ዛሬ እየጻፍኩት ያለው ወጌሻ ስለሆንኩ አይደለም ወይም ደግሞ እግሬ ወይም እጄ ተሰብሮብኝ አይደለም፡፡ አካላዊ ስብራትን ለመተርጎምም ፈልጌ አይደለም ሞራላዊ ስብራትን፣ አገራዊ ስብራትን፣ ህዝባዊ ስብራትን ለመናገር ፈልጌ ነው እንጅ፡፡ በሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ቦታዎች ብዙ የማንነት ጥያቄዎች ይመጣሉ፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች ግን በወቅቱ እንደ ጥያቄ ተመልክቶ ሊያስተናግዳቸው የቻለ ሰው አልነበረም አሁንም የለም፡፡ በመሆኑም በጥያቄ ላይ ሌላ ጥያቄ ሲደረብ ለነገ እየተባለ ሲገፋ ኖረና ዛሬ ላይ ከባድ ሀገራዊ ስብራትን ፈጠረ፡፡ የህዝቡ አቤቱታ እየጨመረ መጣ፡፡ የአንዱ ስብራት ለሌላውም ስብራት እየሆነ መጣ፡፡ በእርግጥ እስካሁን ድረስም ስብራታችሁ ስብራታችን አይደለም ያሉ አሉ፡፡ ሆኖም ግን ስብራታችን አገራዊ ስብራት ነው፡፡ ይህ ስብራት ደግሞ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ ለሁላችን ስብራት የሚሆንበት አንድ ቀን ይመጣል፡፡ ህዝቡ ለምን መቃወም አስፈለገው? የመቃወም አባዜ ተጠናውቶት ይሆን? አይደለም እናውቀዋለን ኢትዮጵያውያን ከመጠን በላይ ያለፈ ትእግስት ያላቸው ህዝቦች ናቸው ነንም፡፡ ከትእግስት መስመር አልፎበት የማንነት ስብራት ሲደርስበትና ስብራት ሲገጥመው ግን ወጌሻ ሆነን መጠገን ይገባናል፡፡ ምክንያቱም ግብር ከፋዩ ህዝብ ነው፣ መሠረተ ልማቱ የህዝብ ነው፣ በመንግሥት የአመራር ቦታዎች ላይ ያሉትም የህዝብ ናቸው ከህዝብ ናቸው፡፡ ሁሉም አንድ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስቴር መሆን አይችልም እንጅ እኮ እኛም ጠቅላይ ሚኒስቴር ለመሆን የሚጎድለን ነገር የለም ነበር፡፡ ግን ስልጣኑን ለሌላ አሳልፈን ሰጥተነዋል ምክንያቱም ሊመራን ወይም ሊያስተዳድረን ይችላል ያልነው አንድ ሰው ብቻ ስለሆነ፡፡ ዛሬ የሚገድለው እና የሚገደለው ህዝብ እንደ አንድ አገር ዜጋ እኩል ድርሻ ያላቸው ናቸው ለኢትዮጵያ፡፡ የሚገድለው ለአገሬ አስብላታለሁ ከሚለው በላይ እየሞተ ያለው ዜጋ ያስብላታል፡፡ ሆኖም ግን እንደ ባቢሎናውያን ለመሰማማት እና ለመደማመጥ አልቻልንምና የህዝቡ ጥያቄ በጥይት ሲመለስ ተመለከትነው፡፡ ይህ መልስ ምናልባትም ለሕዝቡ የማንነት ስብራት ጊዜያዊ መፍትሔ ሰጥቶ ህዝቡን እንዳይቃወም ልናደርግበት እንችል ይሆናል ዘላቂ መፍትሔ ግን አይሆንም፡፡ በረሃብ ተጎድቶ ዛሬ እንዳይጮኸብን ያለውን ህጻን ተቆጥተንም ሆነ አስፈራርተን እንዳይጮኽ ልናደርገው እንችላለን፡፡ ይህ ማለት ግን ልጁ መጮኹን ያቆመው ረሀቡ ስለጠፋለት አይደለም ስለፈራ እንጅ፡፡ ምናልባትም በዚህ ከቀጠልንበት አንድ ቀን ከሞት ሰይፍ ይሻላል እንዲሉ አበው ሰይፍ ሊመዝብን ይችላል፡፡ ህጻን መሆኑን አንመልከተው እርሱ ዘንድም ብሶት ታፍኗልና፡፡
“መንግሥት ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው” የሚባለው በእውነት የህዝብን ደም ሲያፈስ ነው ወይስ ደግሞ ጥያቄያችሁ ተገቢ ነው ወደ ፊት እናስተካክላለን እናንተ የምትሉትን ነገር እኮ እኛም ቀድመን ተረድተነዋል በማለት በሰላም ህዝቡን የሚያነጋግር ሲሆን ነው፡፡ የኃይል ጥቃት ጊዜያዊ ጥገና ነው፡፡ ምክንያቱም የህዝቡ ስብራት በአግባቡ እስኪጠገን ድረስ ስብራቱ በየጊዜው ማስቸገሩ አይቀርም፡፡ መንግሥት ጥሩ ወጌሻ መሆን ካልቻለ ከባድ ችግር ይፈጠራል፡፡ በአገራችን ላይስ ከህዝቡ በሚበልጡ ፖሊሶች እያስፈራራን እንደ ህጻን ልጅ ዝም እናስብላቸው ትናንትና ብራዚል ላይ የህዝቡን ስብራት በዓለም አደባባይ ሲያጋልጥ ምን አደረግን? ምንም ልናደርግ አንችልም የእኛን ሚዲያ ቀጥታ ስርጭት ልናቋርጠው እንችላለን የአትሌቱ ተቃውሞ ግን አልተቋረጠም ነበር፡፡ ሌሎች ታላለቅ ሚዲያዎች ቀጥታ ሽፋን ሰጥተውት ነበር እኮ፡፡ ታዲያ የህዝባችንን ጩኸት በእንደዚህ ዓይነት አጋጣሚዎች የሚገልጹ ዜጎች ካሉ የሀገራችንን ህዝብ ብናስፈራራው ምን ዋጋ አለው? እኛ እኮ ዝም  ካልን ቆየን በጣም ብዙ ጊዜ አለፈን፡፡ ህገ መንግሥቱ የመናገር መብት ስለሰጠ እንናገራለን ነገር ግን የማሰር ስልጣንን ስለሰጠ ደግሞ እንታሰራለን፡፡ እንደዚህ እየሆነ እስከመቼ? እዚህ ያለውን አስፈራርተን ዝም ብናስብለውም ስብራቱን ማከም የሚችልበትን አጋጣሚ ባገኘ ቁጥር ባለም አደባባይ ቅሬታውን ይገልጻል፡፡
ስለዚህ የጋራ መፍትሔ መፈለግ ያስፈልገናል፡፡ ህዝቡ ተቃውሞውን እንዲያቆም ጥያቄውን መመለስ ያስፈልጋል፡፡ የህዝቡ ደም እንዳይፈስ መንግሥት ያሰማራቸውን ደም አፍሳሾች መሰብሰብ አለበት፡፡ በእውነት መንግሥት ላይ አንዳችም ጥፋት ባይኖርበት ኖሮ መቶ ፐርሰንት መረጠን ያልነው ህዝብ በየወረዳው እና በየቀበሌው ለምን ይቃወመናል? አንዳንዴ እኮ ራስንም ዞር ብሎ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ዝንጀሮ በሌላው መላጣ የምትስቀው እኮ የራሷን መላጣ ዞራ ስለማታየው ብቻ ነው፡፡ የራሷን መላጣ ብታይ ግን በሌላው መላጣ የምትስቅበት አፍ እና አንደበት አይኖራትም ነበር፡፡ ስለዚህ የስብራቱ ጥገና ፍቱን መሆን አለበት፡፡ ጀምሮ ነካክቶ ስብራቱን አባብሶ ዞር ማለት ምንም ፋይዳ የለውም፡፡ እስከዛሬ ድረስ እኮ ተመልክታችሁታል፡፡ ምን ላይ ችግር እንዳለ፣ ምን ላይ ህዝቡ ቅር እንደተሰኘ መመርመር አለባችሁ፡፡ ትልልቅ አገራዊ ፕሮጀክቶች ሲቀረጹ ከመቀረጻቸው በፊት ህዝቡን ማወያየት ያስፈልጋል፡፡ ፕሮጀክቱ ብዙ ገንዘብ ከፈሰሰበት በኋላ ወደ ህዝቡ መጥቶ ህዝቡ ድንበራችንን ይጋፋል፣ ታሪካችንን ያደበዝዛል፣ ማንነታችንን ያሳጣል ወዘተ ብሎ ቅሬታ ሲያቀርብ ወደ ድብድብ እና ግድያ ከማምራቱ በፊት እውቅና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ አልታደል ብለን ነው እንጅ ቅሬታ ያቀረበ ሰው በእውነት ይደበደብ ነበር? ይታሠር ይገደል  ነበር? ለወደፊት እቅዳችን እኮ ግብአት ነው፡፡ የሕዝቡ ቅሬታ ለሚያስተውል መሪ በጣም ሲበዛ ጠቃሚ ነው፡፡ መልካም እየሰራን እንደሆነ የሚነግረን ሰው ምንም አይጠቅመንም ምክንያቱም እየሠራነው ያለው ነገር ስለሆነ፡፡ ጉድለታችንን የሚመለከት ዓይን ግን ተገቢ ነው እኛ መስሎን ከሠራነው በተጨማሪ ሌላ መንገድ ያሳየናልና፡፡
እኔ ይህንን ስጽፍ የሚሰማኝ ሰው ላይኖር ይችላል ምክንያቱም በማንም ዘንድ ቦታ ስለሌለኝ፡፡ ግን አንድ ቀን ታሪክ ሆኖ እንደማገኘው አልጠራጠርም፡፡ ይህ ትንቢት አይደለም አሁን እያየነው ያለ ነገር ነው፡፡ ስብራቱን በደንብ አላከሙትም፡፡ ህዝቡ ተሰብሮ እንደወጣ ሌላ ስብራት ተጨምሮበት እየገባ ነው ያለው፡፡ በተለያዩ ቦታዎች መልካቸውን እየቀያየሩ ተቃውሞዎች እየመጡ ናቸው፡፡ እስካሁን ግን ህዝቡን ሰብስቦ ምንድን በደልናችሁ? ያለ አካል የለም፡፡ በደሉን አጠገቡ ሆነን ካልሰማነው ምን የኅሊና እርካታ ሊሰጠን ይችላል፡፡ እየጠገንነው ያለው ስብራት ነገም መሰበሩ አይቀርም ምክንያቱም በአግባቡ አልጠገንነውምና፡፡ ወይም ከስብራቱ ውጭ ያለውን አካሉን ነውና የጠገንለት፡፡ ስለዚህ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ እኛ ማድረግ የምንችለውን ነገር እናድርግ፡፡ ህዝቡን ከሞት አገሩን ከመቅሰፍት እንዲጠብቅልን ወደ አምላካችን መጮኽ ብቸኛው አማራጫችን ነው ለእኛ ለሚገደልብን እና ወደፊትም ለምንገደል ሰዎች፡፡ በዚህ ጩኸት በየቤተ እምነታችን በርትተን አምላክን እንለምን እርሱ ምሕረት በእጁ አለችው፡፡ እርሱ ነገርን ይቀይራል አትጠራጠሩ ሁሉም ከስብራቱ ይጠገናል!!!!

አበዛሁ ይብቃኝ!

Thursday, August 11, 2016

“ወማየ ብሔራሰ እኩይ ውእቱ”

© መልካሙ በየነ
ነሐሴ 05/2008 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ኤልሳዕ መምህሩ ኤልያስን ሸኝቶ ሲመለስ ዮርዳኖስን ተሻግሮ ኢያሪኮ ደረሰ፡፡ ከዚያም ከከተማው ገባና “ሠናይት ንብረታ ለዛቲ ሐገር” አለ፡፡ ኤልሳዕ እየተመለከታት ያለችው ሀገር መልካም ናት፡፡ ከውጭ ሲመለከቷት መልካም ናት፣ ያማረች ናት፣ ያጌጠች ናት ለዚህም ነው ኤልሳዕ መልካምነቷን የሚመሠክርላት፡፡ ሆኖም ግን የሀገሪቱን መልካም መሆን አለመሆን የሚያውቁ በውስጧ የሚኖሩ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ ሌሎች የሚመለከቱት ህንጻውን ነው፣ ሌሎች የሚመለከቱት መንገዱን ነው፣ ሌሎች የሚመለከቱት የቤተ መንግሥቱን ልምላሜ ነው፣ ሌሎች የሚመለከቱት 24 ሰዓት ያለአገልግሎት የሚፈሰውን ፋውንቴን ነው እውነቱ ያለው ግን በኗሪዎች እጅ ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ነው ኤልሳዕ ሐገሪቱ መልካም ናት እያለ ስለሐገሪቱ መልካምነት ሲናገር ከታይታ መልካምነቷ ያልተጠቀመው ህዝብ  “ወማየ ብሔራሰ እኩይ ውእቱ፣ ነቢየ እግዚአብሔር ኤልሳዕ ሆይ! ውኃው ግን ወላድ ቢጠጣው ያመክናል፣ መካን ብትጠጣውም አንጀቷን ቆርጦ ሆዷን በጥብጦ ይገድላታል” ማለቱ፡፡
የአገራችን መልካምነት፣ ታይታነት፣ ዕድገትና ልማት፣ ብልጽግና ሰላም ወዘተ እንዲህ ነው፡፡ አሜሪካ ብትመሰክር፣ እስራኤል ብትመርቅ፣ ቻይና ብታሞግስ፣ ኮሪያ ብትሸልም፣ ጃፓን ብታደንቅ አይገርምም ምክንያቱም እነርሱ ያዩት ፎቁን እንጅ ከፎቁ ሥር የወደቁትን አይደለምና፡፡ እነርሱ የተመለከቱት የውኃ ማስተላለፊያ ቱቦውን እንጅ ውኃውን አይደለምና፡፡ እነርሱ የተመለከቱት አስፋልቱን እንጅ በአስፋልቱ ላይ ተኝቶ የሚያድረውን መጠለያ አልባ ወገኖቻችንን አይደለምና፡፡ እነርሱ የተመለከቱት የቤተ መንግሥቱን የ24 ሰዓት የመብራት አገልግሎት እንጅ የእኛን በኩራዝና በሻማ ማደራችንን አይደለምና፡፡ እነርሱ የተመለከቱት የቴሌቪዥኗን ኢትዮጵያ ነው እንጅ እኛ የምንኖርባትን እውነተኛዋን ኢትዮጵያ አይደለምና፡፡ ስለዚህም አንፈርድባቸውም፡፡ ደግሞም እኮ እኛ ተደራጅተን ለመኖሪያ እንኳ 200 ካሬ ሜትር ያላገኘነውን የአገራችንን መሬት በገፍ የሚያፍሱ ስለሆነ ቢያወድሱን አይገርምም፡፡ አለቃ ገብረ ሃናን ልጃቸው “አባቴ ሰው ሁሉ ድንቼ ድንቼ ይለኛል” አለቻቸው አሉ፡፡ እርሳቸውም ሲመልሱ “ልጄ እንዳይልጡሽ ተጠንቀቂ” አሏት ይባላል፡፡ ስለዚህ ነው እንግዲህ መጠንቀቅ የሚያሻን፡፡ ድንቼ ድንቼ የሚለንን የውጭ ሙገሳ አንሻም በሉልን ምክንያቱም ሊልጡን የተዘጋጁ ናቸውና፡፡
ኤልሳዕ የዚችን ሐገር እውነተኛ ማንነት ተረዳ፡፡ የሃይማኖት አባቶቻችን ሆይ ኤልሳዕን እንስማው እባካችሁ፡፡ ዝም ብለን ይህች አገር መልካም ናት ባንል መልካም ነው፡፡ ኤልሳዕ ውጯን ስለተመለከተ ነው እናንተ ግን ውስጧን ትመለከታላችሁና የመልካምነቷ ተካፋዮች ስለመሆናችሁ ማረጋገጥ አለባችሁ፡፡ አሁን ኤልሳዕ መልካም አገር እንደሆነች ተረድቷል ነገር ግን መልካምነቷን የሚለውጥ አንድ ችግር እንዳለ ከነዋሪዎች ሰምቷል፡፡ ታዲያ ሐገሪቱ መልካም ናትና እንዲህ ያለውን የማይገባ ስም አትለጥፉባት ነው እንዴ ያለው? ወይስ አንዴ መልካም ናት ብያለሁ ብያለሁ ዝም ብላችሁ መልካምነቷን ተቀበሉ ነው ያለው? አንዳንዴ እኮ እየኖርንበት ስላለው ሁኔታ ከጠፋን ራሱ የሚኖሩትን ማየት እና መጠየቅም ያስፈልገናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ እየኖርን ራሱ እየኖርን ስላለበት ሁኔታ የምናውቀው ነገር ላይኖር ይችላል፡፡ ስለዚህ የኤልሳዕን ድንቅ ተግባር ለህዝባችን ማሳየት ይጠበቅባችኋል ማለት ነው፡፡
ኤልሳዕም አገሪቱስ መልካም ነበረች ዳሩ ግን ውኃው መርዝ ነው፡፡ ወላድን ያመክናል፤ መካንንም ይገድላል እንጅ ያሉትን ወገኖች ሰምቶ መፍትሔ ፈለገላቸው፡፡ ምክንያቱም ኤልሳዕ  ንብረቱን ትቶ ለድኃ አብልቶ መምህሩ ኤልያስን የተከተለው ራሱን ለእግዚአብሔር ሰጥቶ ነውና የህዝቡን ሞት አይፈልግም፡፡ ስለዚህህዝቡ በውኃው መርዝነት አንጀቱ ሲቆረጥ ሆዱ ሲበጠበጥ መመልከት አላስቻለውምና “አዲስ ሸክላ ጨው ጨምራችሁ አምጡልኝ” አለ፡፡ ከአንድ አባት የሚጠበቀው መልካም ነገር ይኼ ነው፡፡ ስለዚህ የዛሬ አባቶቻችንም የሰላም ጨው፣ የፍቅር ጨው፣ የአንድነት ጨው፣ የመረዳዳት ጨው፣ የመተባበር ጨው፣ የመተሳሰብ ጨው፣ የመቻቻል ጨው፣ የመዋደድ ጨው በአዲስ ማሰሮ ጨምራችሁ እመጡልኝ አንጀታችሁን የሚቆርጠውን ሆዳችሁን የሚበጠብጠውን መርዝ ላስወግድላችሁ ማለት ያስፈልጋችኋል፡፡ ከዚህ በፊት ግን እንደ ኤልሳዕ ጥፋቱ ማን ላይ እንደሆነ በግልጽ መለየት ተገቢ ነው፡፡ ውኃው ላይ ነው ወይስ ውኃውን ከሚጠጡት ሰዎች ላይ ነው ችግሩ ያለው? የሚለውን በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት ላይ ነው ወይስ ሕዝቡ ላይ ነው ጥፋቱ? የሚለውን እንደ አባትነታቸው የማወቅና የመረዳት ግዴታ አለባቸው ምክንያቱም ያለሕዝብ የሕዝብ አባት መሆን አይቻልምና፡፡ አባቶች ከመንግሥት ጋር ወግነው ህዝቡ ሲታሰር፣ ሲደበደብ፣ ሲገደል እየተመለከቱ ዝም ማለት ግን የኢሳይያስን ለምጽ የሚያከናንብ ፍርሐትና አድርባይነት ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ደም ሲፈስ እየተመለከትን ለጸሎት ለሱባኤ ለምሕላ ያወጅነው የአባትነት ዐዋጅ የት አለ? የሙስሊሙም፣ የክርስቲያኑም የሃይማኖት አባቶች ለዚህ ለፈሰሰው ደም ምንም ዓይነት ከሃይማኖቱ የሚጠበቅ ተግባር አላሳዩም፡፡ ይልቁንም መንግሥት የተናገራቸውን ቃላት ሳንቀይር “እንደ በቀቀን” ብናስተጋባ ግን ታሪክ አንድ ቀን ይወቅሰናል፡፡ ዕድሜያችን አጭር ናት፣ ዛሬ ናት አልያም ነገ ብቻ ናት ያለችን ጊዜ በዚች ጊዜ ውስጥ ግን የሰላም ማሰሮንአምጡልኝ ማለት ይጠበቅብናል፡፡
ኤልሳዕ በአዲስ ሸክላ ጨው ጨምረው እንዲያመጡለት ጠየቀ ህዝቡም አመጡለት፡፡ ኤልሳዕ እውነተኛ አባት መሆኑን ተረድተዋል፣ የኤልያስ ደቀመዝሙር እንደሆነ አውቀዋል፣ እውነተኛ የእግዚአብሔር ነቢይ እንደሆነ ተረድተዋል ስለዚህም ታዘዙት በአዲስ ሸክላ ጨው ጨምረው አመጡለት፡፡ ከዚያም ምንጩን አሳዩኝ አላቸው ምንጩን አሳዩት፡፡በቃ ይህ ነው ዋናው መፍትሔ ምንጩን መለየት ያሻል፡፡ ዝም ብሎ ከሚፈሰው ውኃ ጋር መፍሰስ አይደለም ምንጩ ላይ መሄድ ነው እንጅ፡፡ የደም መፍሰሱ ምንጭ ምነድን ነው? የመገዳደላችን ምንጩ ምንድን ነው? ንብረታችን የመውደሙ ምንጭ ምነድን ነው? የህዝባችን መቆጣት ምንጩ የት ነው? ማለት ተገቢ ነው፡፡ ለዚህ ነው ኤልሳዕ ምንጩን አሳዩኝ ማለቱ፡፡ ህዝቡም ምንጩን አሳዩት፡፡  እርሱም እንደአባትነቱ “እግዚአብሔር አምላከ እስራኤል ፈወስክዎ ለዝንቱ ማይ ከመ አልቦ ዘይመክን እምኔሁ ወዘይመውት” ብሎ ጨው ያለበትን አዲሱን ሸክላ ከምንጩ ላይ አድርጎ ጸልዮበታል፡፡ ከዚህ በኋላ ውኃው ተፈውሶ ወላድ ብትጠጣው የማያመክን መካን ብትጠጣውም የማይገድል ሆኗል፡፡ ከሞት የከፋ ነገር የለም ኤልሳዕ ከዚህ ሞት የታደጋቸው የአባትነቱን አደራ የተወጣው በዚህ መልኩ ነው፡፡ ስለዚህ ዛሬም አባቶቻችን ሆይ የኤልሳዕን ሥራ ትሠሩ ዘንድ እንማልዳችኋለን፡፡ አገራችን መልካም ናት፣ አገራችን የሃብታሞች ሃብታም ናት፣ አገራችን ትልቅ አገር ናት ነገር ግን ወላድን የሚያመክን መካንን የሚገድል ውኃ አለባት፡፡ ይህንን ውኃ መፈወስ የአባቶችቻን ትልቅ ኃላፊነት ነው፡፡

ሁሉም የሚጠቀምበትን ሰላም ፍቅር አንድነት ለህዝቦቻችን ያድልልን ዘንድ የፈጣሪያችን መልካም ፈቃዱ ይሁንልን አሜን፡፡

Wednesday, August 10, 2016

“ወሥሉጥ ስምኪ በኀበ እግዚአብሔር”


© መልካሙ በየነ
ነሐሴ 04/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
የአባ ሕርያቆስ ረድኤት በረከት ይደርብንና እመቤታችንን ባመሰገነበት ቅዳሴው እንዲህ አለ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም እንዲህ ብለው ተረጎሙልን፡፡ የቃሉ በረከት በሁላችን ላይ ይደርብን አሜን፡፡
ወሥሉጥ ስምኪ በኀበ እግዚአብሔር፡፡ ስምሽም በእግዚአብሔር ዘንድ በማማለድ ሥሉጥ ነው፡፡ ይህም በአንድ ሰው ታውቋል፡፡ ታሪክ እጅግ ገንዘቡ የበዛ የተረፈው አንድ ባለጸጋ ነበረ ላዝማሪ ለዘዋሪ እየሰጠ አለቀበት፡፡ አንድም የዚህ ዓለም ገንዘብ ሲሰበሰብ እንጅ ሲጠፋ አይታወቅምና፡፡ ኅልፈቱ ቅድመ አስተርእዮቱ እንዲል፡፡ ከዚህ በኋላ ከብሬ በኖርሁበት አገር ተዋርጄ ሰጥቼ በኖርሁበት አገር ለምኜ  አልኖርም ብሎ አገር ጥሎ ቁርበት ጠቅሎ ሲሄድ ሰይጣን የጨዋ ልጅ መስሎ ከጎዳና ቆይቶ ወዴት ትሄዳለህ አለው ከብሬ በኖርሁበት አገር ተዋርጄ ሰጥቼ በኖርሁበት አገር ለምኜ  አልኖርም ብየ አገር ጥየ ቁርበት ጠቅልየ መሄዴ ነው አለው፡፡ ያዘነ መስሎ ደንጊያውን በምትሐት ወርቅ አስመስሎ ይህን ብሰጥህ አትመለስምን አለው፡፡ ይህንንማ ካገኘሁ ስንኳን ለእኔ ለልጅ ልጄ አይበቃም አለው ከዚህ በኋላ ሰጠው አንተም ፈቃዴን ፈጽምልኝ አለው፡፡ ምን ላድርግልህ አለው፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስን ካድልኝ መላእክት ጻድቃን ሰማዕታትን አያማልዱም በል አለው፡፡ ካደ አያማልዱም አለ፡፡ ከተለያዩ በኋላ ነገር ረስቼ ቆየኝ አለው፡፡ ምእመናን አፍረው አክብረው ስሟን የሚጠሯት ማርያም የምትባል አለች ወላዲተ አምላክ መሆኗን ካድልኝ አለው፡፡ የለማኝ ምኩዜን ምን ይዞ ይሄዷል ጉዞ እንዲሉ እርሷንስ አይሆንም አለው፡፡ እንኪያስ አምጣ ብሎ ወርቅ አስመስሎ የሰጠውን ደንጊያ ተቀብሎ ልብ ራሱን ብሎ ገደለው፡፡ መላእክተ ጽልመት ነፍሱን ከሥጋው ለይተው እጅ አድርገዋታል፡፡ መላእክተ ብርሃንም የጌታን ቁርጽ ፍርድ ሳያዩ አይለዩምና ከእመቤታችን ዘንድ ሂደው ምነው ዝም አልሽ ይህች ነፍስ ከሥጋው የተለየች ባንቺ ምክንያ አይደለምን አታማልጅም አሏት፡፡ እርሷም መሐር ሊተ ወልድየ ዛተ ነፍሰ አለችው፡፡ ከልብኑ ይትመሐር  አባቴን እኔን የባሕርይ ሕይወቴ መንፈስ ቅዱስን የወዳጆቼ የመላእክትን የጻድቃን የሰማዕታት አማላጅነታቸውን የካደ ይማራልን አላት፡፡ ዘጸውዐ ስምኪ ወዘገብረ ተዝካረኪ እምሕር ለኪ ያልኸው ቃልህ ይታበላልን አለችው፡፡ ያውስ ቢሆን የሕጸጸ ምግባር ነው እንጅ የሕጸጸ ሃይማት ነውንነገር ግን ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነሥቼ ሰው መሆኔ ፈቃድሽን ላልፈጽምልሽ ነውን ምሬልሻለሁ አላት፡፡ እንኪያስ ከማርህልኝ ነፍሱን ከሥጋው አዋሕደህ አስነሣልኝ  አለችው፡፡ ነፍሱን ከሥጋው ጋር አዋሕዶ አስነሣላት  ለምን ካድህ አለችው፡፡ ባጣ አላት ያጣ ይለምናል እንጅ ይክዳልን  አሁንም ከልጄ አማልጄህ እንዲህ ካለ ቦታ ምግብህን አዞልሃልና ሂድ አለችው፡፡ በዚያች ቦታ አንድ ባለጸጋ ነበር፡፡ አንዲት መልከ መልካም ልጅ ነበረችው፡፡ ባለጸጋ መጥቶ ልጅህን ስጠኝ ያለው እንደሆነ ልጄን በመልክ አትተካከላትም ይለዋል፡፡ መልከ መልካም መጥቶ ስጠኝ ያለው እንደሆነ ልጄን በገንዘብ አትተካከላትም ይለዋል፡፡ እንዲህ አድርጎ ከፍቅሩ ጽናት የተነሣ ያኖራት ነበረ፡፡ በዚያች ቀን እመቤታችን ከቤተ ክርስቲያን እንዲሄድ አድርገዋለች፡፡ የባለጸጋ ጸሎት አጭር ነውና የሰጠኸኝን አትንሣኝ ይህችን አንዲት ቅንጣት ልጄን ባርክልኝ ብሎ ተቀመጠ፡፡ ወዲያው ተደሞ መጣበት፡፡ ያም ሰው ጠፈር ጠፈሩን እያየ ሲዞር ከሱ አጠገብ ደረሶ ቆመ፡፡ ልጅህንም ከብትህንም ለዚህ ሰው ስጠው አለችው፡፡ ቀና ቢል አየው፡፡ ከዚህ በኋላ ወስዶ ልጁንም ከብቱንም ሰጥቶት ወዲያው ዐረፈ፡፡ እርሱም ቆርቦ የእመቤታችንን ስሟን ሲጸራ ዝክሯን ሲዘክር የሚኖር ሁኗል፡፡ ከሞተም በኋላ በዚህ ጊዜ ያልፋልየማይባል መንግሥተ ሰማያትን አውርሰዋለችና እንዲህ አለ፡፡
፩ዱ ነዳይ ዘክሕደ ሃይማኖቶ ኪያኪ ክሕደ ሶበ አበየ በቅድመ ሰይጣን ዘአስሐቶ
አሚነ ዚአኪ ድንግል ለአድኅኖ ነፍሱ በቍዐቶ
እንዘ ይሴባሕ ተአምርኪ ወለጽጌኪ ምሕረቶ
ተንሥአ እምንዋሙ ወአተወ ቤቶ እንዳለ ደራሲ፡፡
(ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጉም ገጽ 30 እና 31)
ይቆየን……

“አትናገር፤ ተናገር ካሉህ ግን እውነቱን ብቻ ተናገር!”

© መልካሙ በየነ
ነሐሴ 04/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

“አትናገር፤ ተናገር ካሉህ ግን እውነቱን ብቻ ተናገር!” የሚለውን ምርጥ ቃል እኔ በዚህ መልኩ ልጻፈው እንጅ የቀደሙ አባቶቻችን የኖሩበት የህይወት መንገድ ነው፡፡ ይህንን የተናገሩት አባቶቻችን ናቸው፡፡ በዚህ መልኩ የተናገሩት ቃል የለም የጻፉትም መጽሐፍ የለም ካላችሁኝ ግን ይህ ቃል ምርጥ ስለሆነ እኔ እንደተናገርኩት አድርጋችሁ ያዙት ምክንያቱም የሚያሳፍር የሚያሸማቅቅ እና የሚያዋርድ አይደለምና፡፡
ተናጋሪ አትሁን፣ አፈ ጮሌ አትሁን፣ ጥራዝ ነጠቅ አትሁን፣ ሳታይ አታውራ አትመስክር፣ ሰውን ያስቀይማልና ወሬ አታብዛ፣ መጥፎ ነገር ተናግረህ ሰው ታስቀይማለህና አትናገር በዚህ ብቻም ያይደለ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ እንደተናገረው “ወአርመምኩ ለሠናይ፤ ለመልካም ነገር ለበጎ ነገር እንኳ ዝም አልኩ አልተናገርኩም” እንዳለው ለመልካም ነገር እንኳ አትናገር፡፡ የምትናገርበት አፍህ የአንተ ነው፣ የምትናገርበት ምላስህ የአንተ ነው፣ የምትናገርበት ልሳንህ የአንተ ነው፡፡ ማንም አንተ ልሳን ውስጥ ገብቶ እንድትናገር አያደርግህም፤ ማንም የአንተን አንደበት ሊቆጣጠረው አይችልም፤ ማንም የአንተን አፍ ሊጠቀምበት አይችልም ምክንያቱም ገንዘብህ ነውና፡፡ የአንተን ገንዘብ ካልመጸወትከው አልያም ካልተሰረቅህ በቀር የአንተ የራስህ ነው፡፡ ስትመጸውተውና ስትሰረቀው ግን የአንተ መሆኑ ይቀራል ያኔ በገንዘብህ ሌላው ያዝበታል፡፡ አንደበት፣ ልሳን፣ ምላስህ ግን እስካልሞትክ ድረስ የአንተ እና የአንተ ብቻ ናቸው ስትሞት ግን ይለወጣሉ አንተም አንተ አትሆንምና፡፡ በሕይወት ሳለህ እነዚህን ንብረቶች የአንተ ማድረግ ካልቻልክ ግን ሰብአዊነትህ ላይ ጥያቄ ይፈጥራል፡፡
በዚህ በወቅታዊው የወገኖቻችን እልቂት ላይ መንግሥት በርካታ መግለጫዎችን ሲሰጥ የቆየ መሆኑን እናውቃለን፡፡ የየክልሉ ባለሥልጣናትም እንዲሁ በእነርሱ ሥር ባሉ የሚዲያ አካላት መግለጫዎቻቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ሆኖም ግን ከዕለት ዕለት እልቂቱ ሲባባስ ሲጨምር እንጅ ሲቀንስ ሲረግብ አላስተዋልንም፡፡ ምክንያቱም አብዛኛው መግለጫ ማስፈራሪያና ዛቻ የታከለበት ስለሆነ ሌላ ቁጭትን ሲፈጥር ነው የሚስተዋለው፡፡ በተለይ ከፍተኛ አመራር ላይ ያሉ ባለሥልጣናት ቃላትን መምረጥ ያሻቸዋል፡፡ እኛ የፈለግነውን ብንናገር ቃላትን ባንመርጥ ማንም ስለማይሰማን ለብጥበብጡ መባባስ መንስኤ አንሆንም እነርሱ ግን ዓለም ቁጭ ብሎ በሚመለከተው ሚዲያ ላይ ነው እየተናገሩ ያሉት፡፡ ስለዚህ በማስተዋልና በረዳት ቢሆን መልካም ነው እላለሁ፡፡ ከቻላችሁ አትናገሩ ምክንያቱም መናገራችሁ ብጥብጥን ፈጠረ፣ እልቂትን አባባሰ፣ ደምን አፋሰሰ፡፡ እንድትናገሩ ከተገደዳችሁ ግን ተናገሩ ያውም እውነቱን ብቻ ምንም ውሸትና ስላቅ ማስፋራራትና መዛት የሌለበትን ትምክህትና ቧልት ያለተቀላቀለበትን ንጹሑን ኢትዮጵያዊነት የሚገልጽ ንግግር ተናገሩ፡፡
የሃይማኖት አባቶችም እንዲሁ አትናገሩ፤ ተናገሩ ካሉዋችሁ ግን እውነቱን ብቻ ተናገሩ፡፡  የሃይማት አባቶች የምታስተዳድሩት ህዝብ መንግሥት ከሚያስተዳድረው ሕዝብ በላይ መሆኑን ተረዱ፡፡ መንግሥት ለዚህች አገር ብቻ ነው የሚጨነቀው፣ መንግሥት ለዚህች ሐገር ሰላም ብቻ ነው የሚያስበው፣ መንግሥት ለዚህች አገር እድገት ብቻ ነው የሚሠራው እናንተ ግን ለዓለም ነው የምትጸልዩት፤ እናንተ ግን ለዓለም እድገት ነው የምትሠሩት፡፡ ስለዚህ ከመንግሥት በላይ ናችሁ ከህዝቡም በላይ ናችሁ ይህን ከተረዳችሁ ደግሞ በህዝቡና በመንግሥቱ መካከል ገብታችሁ የማስተረቅ የመሸምገል ያጠፋውን የማውገዝ ሥልጣን አላችሁ፡፡ የእናንተ አደራ ሰው ሲሞት ፍትሐት አድርሶ መቅበር ብቻ አይደለም እንዳይሞት መጠበቅ ጭምር ነው እንጅ፡፡ መንግሥት የሚነግረንን ነገር ብትነግሩን ግን ምንም አይፈይድልንም ምክንያቱም የሚገድለንን ደግፋችኋልና፡፡ የሃይማኖት አባቶች ወገንተኞች መሆን አይገባችሁም ክልላዊ ዝቅ ብሎም ጎጣዊ የሆነ አስተሳሰብን ከእናንተ አንሻም፡፡ ሰማእተ ጽድቅ ዘኢትዮጵያ አቡነ ጴጥሮስን ከልባችሁ ጽላት ጻፏቸው እስኪ፡፡ ይህች አገር እኮ የታላላቅ ታሪክ ሰሪዎች አገር ናት፡፡ ታዲያ ለውጭ ጠላት አንንበረከክም ብሎ የአንድነት ታሪክን በጀግንነት የሠራ ህዝብን በአገሩ ልጆች በመከፋፈል ሲገደል ደሙ መሬት ሲፈስ እንዴት መስቀላችንን እንደብቀዋለን፡፡
ዋናው መልእክቴ አባቶቼ ሆይ አትናገሩ፤ ተናገሩ ካሉዋችሁ ግን እውነቱን ብቻ ተናገሩ የሚል ነው፡፡ አባታችን ቅዱስ ፓትርያርኩ ትናንትና መግለጫ ሲሰጡ ተመልክተናል፡፡ እኔ ለራሴ መግለጫውን አንድ የመንግሥት አካል ከሚሰጠው መግለጫ የተለየ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ አንድ የተቀየረ ቃል ቢኖር “መንግስታችን” የሚለው ቃል “ቤተክርስቲያናችን” በሚል መተካቱ ብቻ ነው፡፡ ይህ የአባታችን ንግግር ምእመናንን ያስቀይማል፣ ህዝቡን ላልተፈለገ ዓላማ ያነሳሳል ስለዚህ ነው ባንናገር መልካም የሚሆነው፡፡ የግድ ከሆነ ግን የአቡነ ጴጥሮስን አንደበት ለደቂቃዎች እንኳ መዋስ ያስፈልጋል፡፡ “ልጆቻችን” በማለት ፈንታ “ዜጎቻችን” ሲባል ቅር ያሰኛል፡፡ በእውነት አባት የለንምን ያስብላል፡፡ ንግግራችን ካላማረ ንግግሬ አያምርም ብሎ ዝም ማለት ይሻላል፡፡ ተናግሮ ከማስቀየም አለመናገር ይሻላል፡፡ መናገር ግድ ከሆነብን ግን ህዝቡን ጥፋተኛ መንግሥትን ትክክለኛ አድርገን ያለምንም መረጃ ወደአንዱ በማዘንበል መናገር ተገቢ አይደለም፡፡ ስለዚህ በሁለቱም መካከል ገብተው የቱ ነው ያጠፋ በማለት መመርመር ከንግግራቸው በፊት የሚቀድም ተግባር ነበር፡፡ አባቶቻችን ያቆዩን በጸሎት ማሰብ እንኳ መጀመሪያ ላሉበት ቦታ ነው ይላሉ ምክንያቱም ዐሥራቱን ቀዳማያቱን ትመገባለህና ይላሉ፡፡ ይህ እየሞተ ያለው ህዝብ እኮ ዐሥራት በኩራቱን እየከፈለ ሞገስ የሆነን ህዝብ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ህዝብ ሲሞት ወገኔ አይደለህም ልንለው እንችላለንን?

ለሀገራችን ሰላም እንማልዳለን!!!

Monday, August 8, 2016

"ውዳሴ ዘሠሉስ ውዳሴ በሠሉስ... አክለለ ምክሕነ"

©መልካሙ በየነ
ነሐሴ 3/2008 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ ኢትዮጵያ
ውዳሴሃ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ ዘይትነበብ በዕለተ ሠሉስ፡፡
ለምስጋና ሁለተኛ ለፍጥረት ሦስተኛ ቀን ነው፡፡ በዚህም ቀን እመቤታችን ትመጣለች የብርሃን ምንጻፍ ይነጸፋል የብርሃን ድባብ ይዘረጋል፡፡ ከዚያ ላይ ሁና ሰላም ለከ ኦ ፍቁርየ ኤፍሬም ትለዋለች እርሱም ታጥቆ እጅ ነሥቶ ይቆማል፡፡ ወድሰኒ ትለዋለች በዕለተ ሰኑይ ክርክር አልቋልና ባርክኒ ይላታል፡፡ በረከተ ወልድየ ወአቡሁ ወመንፈስ ቅዱስ ይኅድር በላእሌከ ትለዋለች፡፡ ተባርኮ ምስጋናዋን ይጀምራል፡፡
ውዳሴ ዘሠሉስ ውዳሴ በሠሉስ ውዳሴሃ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ ዘይትነበብ በዕለተ ሠሉስ ይላል ቃለ ጸሐፊ ነው እርሱ ግን አክሊለ ምክሕነ ብሎ  ይጀምራል፡፡
አክሊለ ምክሕነ…. አክሊል የወዲህኛው ምክሕ የወዲያኛው
ወቀዳሚተ መድኃኒትነ…. ቀዳሚት የወዲህኛው መድኃኒት የወዲያኛው
ወመሠረተ ንጽሕነ…. መሠረት የወዲህኛው ንጽሕ የወዲያኛው
ኮነ በማርያም ድንግል… በማርያም ድንግል ሆነልን አለ፡፡ ማርያም ናት ሲል ነው፡፡ አንድም በዚህ ቀን ከነገሥታት ዳዊትን፣ ከመሣፍንት ኢያሱን፣ ከደናግል ኤልያስን አስከትላ መጥታለች፡፡ ዳዊት ምንም ንጉሠ ነገሥት ብትባል የመመኪያችንን ዘውድ ማምጣት አልተቻለህም፡፡ ኢያሱም መድኃኒት ብትባል የደኅንነታችን መጀመሪያ መሆን አልተቻለህም፡፡ ኤልያስም ንጹሕ ድንግል ብትባል የንጽሕናችን መሠረት መሆን አልተቻለህም፡፡ የመመኪያችን ዘውድ የደኅንነታችን መጀመሪያ የንጽሕናችንም መሠረት ድንግል ማርያም ናት ሲል ነው፡፡ አንድም አክሊሎሙ ለሰማዕት እንዲለው አክሊለ ሰማዕት የሚባል ጌታ፤ ጥንተ ሕይወቶሙ እንዲለው ጥንተ ሕይወት የሚባል ጌታ አኃዜ ዓለም በእራኁ ኩሉ እኁዝ ውስተ እዴሁ መሠረተ ዓለም ይጸውር ድደ ወይነብር ጠፈረ እንዲል፡፡ መሠረተ ዓለም የሚባል ጌታ በድንግል ማርያም   ተገኘልን፡፡
ትላንት ስሟን አላነሣም ዛሬ ስሟን አነሣ በእንግዳ ልማድ እንግዳን ዕለቱን ስሙን አይጠሩትም ከዋለ ካደረ በኋላ ስሙን ይጠሩታል በዚያ ልማድ ማርያም ማለት ፍጽምት ማለት ነው፡፡ ለጊዜው መልክ ከደም ግባት አስተባብራ ተገኝታለችና፡፡ ፍጻሜው ግን ንጽሐ ሥጋ ከንጽሐ ነፍስ ድንጋሌ ሥጋ ከድንጋሌ ነፍስ አስተባብራ ተገኝታለችና፡፡ አንድም ጸጋ ወሐብት ማለት ነው ለጊዜው ለእናት ለአባቷ ጸጋ ሆና ተሰጥታለች ፍጻሜው ግን ለሰው ሁሉ ጸጋ ሁና ተሰጥታለችና፡፡ አንድም መርሕ ለመንግሥተ ሰማያት ማለት ነው ምእመናንን መርታ ገነት መንግሥተ ሰማያት አግብታለችና፡፡ አንድም ልዕልት ማለት ነው፡፡ ሮም አርያም ማለት ልዑል ማለት እንደሆነ፡፡ እርሷንም መትህተ ፈጣሪ መልዕልተ ፍጡራን ይላታልና፡፡ አንድም ማኅበረ መሐይምናን ወሕዝብ ተለአኪተ እግዚአብሔር ወሰብእ ተፈሥሒ ቤተ እስራኤል ወተሐሰዪ ቤተ ይሁዳ ማለት ነው፡፡ አንድም ማርያም ማለት እግዝእተ ብዙኃን ማለት ነው ያንንማ ዘዕብራይስጢ እንጅ አይለውም ብሎ ማሪሃም ማለት ቅሉ እግዝእተ ብዙኃን ማለት ነው፡፡ አብርሃም ማለት አበ ብዙኃን ማለት እንደሆነ፡፡
እንተ ወለደት ለነ ዘእግዚአብሔር ቃለ… መመኪያነቷን በቅጽል አመጣው አካላዊ ቃልን በወለደችልን በድንግል ማርያም ተገኘልን፡፡
ዘኮነ ሰብአ በእንተ መድኃኒትነ… እኛን ስለማዳን ሰው የሆነ
እምድኅረ ኮነ ሰብአ ጥዩቀ አምላክ ፍጹም ውእቱ… ሰውም ከሆነ በኋላ ፍጹም አምላክ ነው፡፡ ሐራ ጥቃ ቃል ሥጋ ሆነ ያለውን ይዘው ወደ ታች ተለወጠ ይላሉና ሰውም ከሆነ በኋላ ፍጹም አምላክ ነው አለባቸው፡፡
ወበእንተዝ ወለደቶ እንዘ ድንግል ይእቲ… ስለዚህ ነገር ማኅተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ ወለደችው
መንክር ኃይለ ወሊዶታ ዘኢይትነገር… ድንቅ የሚሆነው የመውለዷ ሥራ የማይመረመር ነው፡፡ የማይመረመር የመውለዷ ሥራ ድንቅ ነው፡፡
ሰአሊ ለነ ቅድስት… በማይመረመር ግብር ከወለድሽው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኝልን፡፡ ሐተታ እንደ ሰኞ ።

Sunday, August 7, 2016

"መንግሥት ማለት ሕዝብ ነው"


የሀገራችን መሪዎች እና በሥሮቻቸው የሚገኙት ባለሥልጣናት "መንግሥት ማለት ሕዝብ ነው" የምትለዋን አባባል ከአፋቸው አይለዩአትም በተለይ ደግሞ የምርጫ ሰሙን!
በነገራችን ላይ መንግሥትን እንደ መንግሥት በአንድ ግዛት ላይ ለመመስረት 5 መሠረታዊ ጉዳዮች መኖር እንደአለባቸው ብዙ የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ። እነዚህም የሚከተሉት ናቸው:-
ሉአላዊነት
ህዝብ
ድንበር/ወሰን
መንግሥት
እውቅና ናቸው።
ከዚህ እንደምንረዳው መንግሥት ማለት ሕዝብ ማለት አይደለም። መንግሥት ማለት ሕዝብ ማለት ቢሆን ኖሮማ ISIS የተባለው መንግሥትም ሕዝብ ነው በተባለ ነበር። ነገር ግን እውቅና ስላልተሰጠው የራሱ የግዛት ወሰን ወይም ድንበር ስለሌለው እርሱን መንግሥት ነው ልንለው አንችልም። መንግሥት እንደ መንግሥት ለመቀጠል ሕዝብ ያስፈልገዋል ሕዝብ ብቻ ሳይሆንም መንግሥት የሚሆንበትንም ወሰን ማስከበር አለበት። ሱማሊያ መንግሥት አልባ ሐገር ናት እየተባለች ያለችው እኮ ሕዝብ ስለሌላት አይደለም ሉአላዊነቷን ስላላስከበረች ነው እንጅ።
መንግሥት ማለት ሕዝብ ነው የሚባለው እኮ ሕዝቡ የመሾምና የመሻር ሙሉ ስልጣን የያዘ ሲሆን እና የመምረጥና የመመረጥ መብቱ ያለምንም ገደብ በነጻነት የተፈቀደለት ሲሆን ነው። የአገራችን መንግሥት ይህንን መብት የሰጠ ቢሆንም ወደዚህ ለመግባት ግን በርካታ ደረጃዎች ተቀምጠዋል። እነዚያን ደረጃዎች ለማለፍ ደግሞ በወቅቱ ከሚገኘው መንግሥት ጋር መስማማት ይኖርብሃል። ተስማምተህ መቃወም ደግሞ በሕዝብ ዘንድ ነቀፌታን ያስከትላል። ይህ የዋህ ሕዝብ ለቅድስናው አብልጦ ይጨነቃል። ለዚህም ነው ውኃ መብራት ኔትወርክ ዘይት ስኳር ወዘተ ሲቋረጥ ሁሉ አሜን ብሎ ሲቀበል የኖረው። ይህን የህዝብ የዋህነት ተመልክቶ እንኳ አጥፍቻለሁ ብሎ መንግሥት ይቅርታ አይጠይቅም ምክንያቱም ሥራው ነውና።
ሕዝብ ማለት ከፖለቲካ አስተሳሰብ በላይ ነው። መንግሥት ደግሞ በፖለቲካ አስተሳሰብ ሥር የተወሽቀ ነው። መንግሥት ማለት ሕዝብ ማለት ነው ስንል መንግሥት ከፖለቲካ በላይ ነው እንደማለት ነው። መንግሥት ማለት ሕዝብ ማለት ከሆነ ሕዝቡ ውረድልኝ ሲልህ መውረድ ውጣ አስተዳድረኝ ምራኝ ሲልህ ሥልጣን ላይ መውጣት ተግባርህ ይሆን ነበር። ምክንያቱም መንግሥት የሚመሠረተው በሥሩ ላሉ ሰዎችም ሥልጣን የሚሰጣቸው ሕዝቡ ስለፈቀደላቸው ብቻ መሆን አለባቸው። ይህ ሥልጣን እኮ የባሕርያችን አይደለም በጸጋ ያገኘነው ሥልጣን ነው። ጸጋው ደግሞ ከአምላክ ብቻ ሳይሆን ከሕዝቡም የሚሰጠን ነው። ስለዚህ የሕዝብን ቅሬታ አቤቱታ እና ጩኸት መስማት ያስፈልገናል ምክንያቱም መንግሥት ማለት ሕዝብ ነው ብለናላ። የሕዝቡ ጩኸት የመንግሥትም ጩኸት መሆን አለበት።
ስለአገራችን ሰላም ጸልዩ። አባቶቻችን ሆይ በጸሎታችሁ አስቡን የሕዝቡ ደም እየፈሰሰ ነውና። እንደ ባሮክ እና አቤሜሌክ የአገራችንን ጥፋት አታሳየን እያልን ፈጠሪያችንን እንለምነው። የወገናችንን እልቂት አታሳየን እንበለው። ትናንትና በድርቅ በረሃብ ስንገርፈው የነበረውን ሕዝብ ዛሬ ደግሞ በጥይት ልንደበድበው እንዴት እንደፍራለን? መንግሥት ማለት ሕዝብ ማለት ከሆነማ በአደባባይ የሚፈሰው የሕዝብ ደምም ደማችን በሆነ ነበር።
እኛ የምንበረታው በወንድሞቻችን ላይ ነው። ትናንትና ድንበራችንን ጥሰው የጋምቤላ ተወላጆችን አርደው ንብረታቸውን እና ልጆቻቸውን ዘርፈው ሲወጡ እኮ አንድ ጥይት አላባከንንም ነበር። ምክንያቱም ጉዳዩ ከሌላ አገር ጋር ከሌላ ሕዝብ ጋር ነበርና። እነዚያ ታጥቀው መጥተው ገደሉን ዝም ተባለ ዛሬ ሳይታጠቁ መልካም አስተዳድርን ናፍቀው አደባባይ ላይ ወጡ ጥይት ዘነበባቸው ደማቸው ፈሰሰ። ታዲያ የወገኖቻችንን ደም እንዲህ ደመ ከልብ የምናደርገው መንግሥት ማለት ሕዝብ ማለት ሰለሆነ ይሆን?
እንዲህ አይነቱን የሕዝብ ጥያቄ ለመመለስ ጆሮን መስጠት ከመንግሥት ይጠበቃል። መስቀላቸውን ይዘው እንደ ሰማእተ ጽድቅ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ቆሞ ደም እንዳይፈስ መገላገል ደግሞ ከአባቶቻችን ይጠበቃል። ሆኖም ግን መንግሥት እሥር ቤቶቹ ስለማይሞሉበት ጥይቱም ተተኩሶ ስለማያልቅበት ማሰርና መግደል ሥራውን ካደረገ ግን አገራችን ወደ ከፋ አደጋ መጓዟ አያጠራጥርም። ሰለዚህ በቅርበት የሕዝቡን ጩኸት ብታዳምጡት እድሜያችሁ ይረዝማል እንጅ አያጥርም ነበር። አንሰማችሁም በባዶ ሜዳ ላይ ጩኹ የምትሉን ከሆነ ግን መንግሥት ማለት ሕዝብ ነው ልትሉን ባልተገባም ነበር።
የትናንቱ ጩኸት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጩኸት ነበር፣ የትናንትናው ጩኸት የመቃወም ጩኸት ነበር፣ የትናንትናው ጩኸት የክልል ጩኸት ነበር፣ የትናንትናው ጩኸት የግለሰብ ጩኸት ነበር፣ የትናንትናው ጩኸት የመለያየት ጩኸት ነበር፤ የዛሬው ጩኸት ግን ከዚያም በላይ ነው። የማንነት ጥያቄ ነው፣ የሰብአዊነት ጥያቄ ነው፣ የሀገር ጥያቄ ነው፣ የአንድነት ጥያቄ ነው፣ የሁሉም ጥያቄ ነው፣ የኢትዮጵያዊነት ጥያቄ ነው። ሰለዚህ እንደትናንትናው ሁሉ አንሰማችሁም ልንባል አይገባንም። መሰማማት፣ መደማመጥ፣ መረዳዳት፣ መወያየት እና መስማማት  ይገባናል እኮ ምክንያቱም በአገራችን ጉዳይ ላይ ሁላችን እኩል እንደሆንን ስለሚሰማን። እኛ ድንበር ሲወረር ድንበራችንን ለማስከበር ብቻ አይደለም ኢትዮጵያዊ የሆነው በውስጧ ካለው ንብረትም ገንዘብም እኩል ለመሳተፍ ጭምር እንጅ። አንዱ እየተራበ ሌላው የሚጠግብባት፣ አንዱ እየተጠማ ሌላው የሚሰክርባት፣ አንዱ ዘይት አጥቶ በቃሪያ እየተቃጠለ ሌላው በቅቤ የሚመገብባት፣ አንዱ በረንዳ ላይ ወድቆ እያደረ ሌላው ከ5ቤት በላይ የሚሠራባት፣ አንዱ ሥራ አጥቶ ሌላው ሳይማር በዝምድና እና በፖለቲካ ከሥራ ሥራን የሚያማርጥባት አገር ሰትሆን ስናይ እኛም ይቆጨናል እኮ። ይህ የማይቆጨው ሰው ካለ ምናልባትም ሰው አይደለም። መንግሥት ደግሞ ሕዝብ ነኝ ይላልና ይበልጥ ቁጭታችን ሊቆጨው ይገባል። ያ ካልሆነ ግን ሕዝቡ ጠያቂ መንግሥት አጥቂ መሆናችን መቆሚያ አይኖረውም።
ይህን የሕዝብ ጩኸት ኔትወርክ በማጥፋት፣ በጥይት በማስፈራራት፣ መብራት በማጥፋት ማፈንና ማዳፈን ይከብዳል። ለጩኸት ማዳፈኛውና ማፈኛው ማደመጥ ብቻ ነው። አዳምጦ ምላሽ መስጠት ከበሳል መሪ የሚጠበቅ ነው። ምክንያቱም በመግደልና በመደፍለቅ ሕዝብን ለመጨረስማ መንግሥት ባላስፈለገንም ነበር። ምሩን አስተዳድሩን ከእኛ ትሻላላችሁ ብሎ በራሱ ላይ ያሰለጠናችሁ እኮ ሕዝብ ነው። ታዲያ እንዴት መንግሥት ሕዝብ ነው እያልን እያወራን ቃላችንን መጠበቅ ተሳነን?
አምላከ ቅዱሳን ለሀገራችን ሰላምን ለህዝቦቿም አንድነትን ፍቅርን መረዳዳትን አድልልን አሜን። እመ ብርሃን ሆይ በዚህ በያዝነው ሱባኤ ምሕረትን ረድኤትን ጸጋ እና በረከትን አድይን አሜን።

Friday, August 5, 2016

“ቃና የለሹ ቃና”

© መልካሙ በየነ
ሐምሌ 29/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ዓላማ አድርጎ የተነሣው ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ውስጣችን እንድናደርገው ነው፡፡ ውስጣችን ስናደርገው ደግሞ ባሕል፣ ወግ፣ እሴት፣ እምነት እና ፍቅር ከእያንዳንዳችን ይርቃሉ፡፡ ላይ ላዩን ስንመለከተው በመዝናናት የሚጀምር ይሁን እንጅ ውስጡ እና ፍጻሜው ግን  ሃይማኖታዊ ሳይሆን አይቀርም የቃና የለሹ ቃና!
አንድ የኢትዮጵያ ብሮድ ካስቲንግ ባለሥልጣን በእነዚህ የግል ቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይ ተጠይቆ በገሪቱ ቴሌቪዥን ማሰራጫ በኢ.ቢ.ሲ ሲመልስ “የእኛ ባለሥልጣን ለማንኛውም የግል ቴሌቪዥን ጣቢያ እውቅና አልሰጠንም፡፡ ሆኖም ግን እስካሁን ድረስ ከተከፈቱት የቴሌቪዥን ጣቢያ ፕሮግራሞች የአገራችንን ባህል፣ ወግ እና እሴት የሚጻረሩ አይደሉም” ብሏል፡፡ በእውነት የእኛ ባሕል ቀኑን ሙሉ ከቴሌቪዥን ስክሪን ላይ አፍጥጦ መዋል ነው እንዴ? የእኛ ባሕል እና እሴት እኮ መረዳዳት፣ መከባበር፣ መፈቃቀር፣ እንግዳን መቀበል፣ ፈጣሪን ማመስገን፣ሥራን አብዝቶ መሥራት፣ ጀግንነት ወዘተ ነው፡፡ ባሕልና እሴት ፖለቲካ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ፖለቲካ ደጋፊም አለው ተቃዋሚም አለው ህላችን ግን ለሁላችን ነው ለተቀዋሚውም ለደጋፊውም፡፡ በእውነት እነዚህ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሀገራችንን መንግሥት ደካማ ጎኖች የሚገልጹ ቢሆኑ ኖሮ ይህን ያህል ዕድሜ ይኖራቸው ነበር? የኢሳትን እድል ይገጥማቸው ነበር፡፡ እንደ ዳይኖሰር ከምድረ ገጽ ይጠፋ ነበር፡፡
የእኛ ባህል፣ ወግ እና እሴት በቃና የለሹ ቃና እንደሚቀርበው ዛራ እና ቻንድራ የተንዛረረ እና የተቸናደረ፣ እንደ ኩዚና ጉኒ የተንኳዘዘ እና የተንጓነነ፣ እንደ ጥቁር ፍቅር ውስጡ የጠቆረ፣ እንደ ውበት እስረኞች በውበት የታሠረ፣ እንደ መንታ ገጽ ልቡ በመንታ መንገድ የሚጓዝ አይደለም፡፡ እነዚህ ፊልም ተብየዎቹ የሚቀርቡባቸውን ሰዓታት ተመልከቱት፡፡ ተያይዘው ለ24 ሰዓታት ለ7 ቀናት የሚዘልቁ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ በተለይ ወጣቶቹን ከሥራ አግቶ ተቀምጠው እንዲውሉ እና የቴሌቪዥናቸውን የስክሪን መጠን  ወይኔ 21 ቢሆን ኖሮ! ወይኔ 41 ኢንች ቢሆን ኖሮ! ወይኔ ፍላት ቢሆን ኖሮ!ወይኔ እንዲህ ሆኖልኝ ኖሮ! ወዘተ ብቻ እንዲሉ አስገድዷቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሃይማታዊም፣ ባህላዊም እሴት የለውም፡፡ ዓላማው ከሃይማኖት፣ ከሐገር ፍቅር፣ ከፖለቲካ፣ ከማንኛውም ማኅበራዊ ግንኙነት ግዴለሾች ማድረግ ብቻ ነው፡፡
ዓላማው ሃይማታዊ ግዴለሾች ለማድረግ ነው የምለው ዝም ብየ አይደለም፡፡ የሚተላለፉበት ሠዓት ግን ከብዙ ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች የሚያርቅ ነው፡፡ በዛራና ቻንድራ ስንንዛረርና ስንንቸናደር የሰርክ መርሀ ግብር ያልፈናል፡፡ ችግር የለውም አንዴ ደርሼ እመጣለሁ እያልን ስንጠብቅ እነ ኩዚና ጉኒ መጥተው ያንጓንኑናል ያንኳዝዙናል፡፡ በቃ ቀረ ነገ እሄዳለሁ እንል እና ራሳችንን እንጽናናለን ከዚያም ነገ እንደዛው ይኼው ተመሳሳይ ሂደት ይቀጥላል፡፡ ስለዚህ ዓላማው ሃይማታዊ ነው የምላችሁ ለዚህ ነው፡፡
እንደዚህ ዓይነት ተጽእኖዎች ምናልባትም የፕሮቴስታንቱ ሊሆኑ እንደሚችሉ እገምታለሁ፡፡ መብራትና ውኃን ተመልከቷቸው መቸ መቸ እንደሚመጡና መቸ መቸ እንደሚሄዱ አስተውሉ፡፡ ውኃ እሁድና ቅዳሜ ስትፈስ ትውልና ሰኞ ጀምራ ትደርቃለች፡፡ ሰንበትን ውኃ ከቤቴ አላስገባም የሚለው የአገራችን አማኝ ሳይወድ በግዱ እንዲያስገባ ይገደዳል ማለት ነው፡፡ መብራትንም እንዲሁ ተመልከቱት፡፡ ገጠር ላይ እና ከተማ ላይ የሚጠፋበት ቀን ይለያያል፡፡ ገጠር ላይ በዓላትን እየጠበቁ ማብራት ሥራን እየጠበቁ ማጥፋት ልማድ ሆኗል፡፡ ከበረሃው ከደጋው ወደ ወፈጮ ቤቶች እህላቸውን ጭነው ይተምማሉ፡፡ በዚያም ወፍጮ ቤት ይከትሙና መብራት መጣ መብራት ሄደ ሲሉ ይከርማሉ፡፡ በጣም ታላላቅ በሚባሉ በዓላት ዕለት መብራት ይመጣል፡፡ መብራትን በመጠበቅ ከቤቱ ሳምንት ያህል ርቆ የሰነበተ ህዝብም በዓሉን ከምንም ሳይቆጥር አስፈጭቶ ይኼዳል፡፡  ከተማ ላይ ስትሄዱ ግን መብራት የሚጠፋው በታላቅ በዓላት ቀን ነው፡፡ በእነዚህ ታላለቅ በዓላት አብያተ ክርስቲያናት የማኅሌት ሥርዓቱን ለህዝቡ ለማሰማት በድምጽ ማጉያ ተጠቅመው ስለሚቆሙ ይህንን ህዝቡ እንዳይሰማ መብራት ይቋረጣል፡፡ በእርግጥ ይህ እንደሚደረግ የታወቀ ስለሆነ አብዛኞቹ በከተማ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የራሳቸው የሆነ ጀነሬተር ገዝተው በመገልገል ላይ ናቸው፡፡
ቃና የለሹ ቃናም ከእነዚህ የፕሮቴስታንት ዓላማ ካነገቡ ሰዎች እጅ የገባ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ስለዚህ በተለይ ወጣቱ ሱስ እንዳይሆንባችሁ ቃና የሚለውን የቴሌቪዥን ፕሮግራም በመጠን እና በልክ እንጠቀምበት፡፡ ብንችል ከቻናል ሊስቱ ላይ እናጥፋው ባንችል የምንመለከትበትን ሰዓት ሃይማኖታዊ እሴቶቻችንን በማይጋፋ መልኩ እናመቻች፡፡ ቃና ውስጤ ነው የሚለው መፈክራቸው ቀላል እንዳይመስለን፡፡ ውስጣችን እየሆነ መጥቷል ውስጣችን ደግሞ ደማችን ነው ደማችን ደግሞ ድንግል ማርያም ያለችበት ደም ነው፡፡ ታዲያ ውስጣችን ነው ሲሉን እኮ ደማችን ውስጥ ያለችውን ድንግል ማርምያን አስወግደው በእነርሱ ቃናነት ሊለውጡት ነው፡፡

በእርግጥ 2008 ለቃና መፈጠር ብቻ አልነበረም ዘመን የሆነው፡፡ ሌሎችም እንደ አሸን የፈሉ ጣቢያዎች ተፈልፍለዋል፡፡ ባህላችንን፣ ወጋችንን፣ እሴታችንን፣ ሃይማኖታችንን የሚጋፋ ቃና የለሹ ቃና ስለሆነ ብቻ ነው እንጅ፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን የቴሌቪዥን ሥርጭት ጀምሯል ታላቅ ፓትርያርክ የነበሩትን የጸሎት እና የትህትና አባት የነበሩትን 3ኛው ፓትርያርክ አቡነ ተክለሃይማትን ከዘመናቸው ዘመን ባይገጥመንም እንኳ ትምህርታቸው እየተላለፈ ነውና እንስማው እስኪ፡፡ በቃና የለሹ ቃና ውስጣችንን ከምናጣ ውስጣችን ይሆን ዘንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤትክርስቲያንን የቴሌቪዥን ሥርጭት እንከታተል እላለሁ፡፡ ይህን የምላችሁ ግን እንደ ምክር ነው እንጅ ለማስተዋወቅ ወይም ጥላቻን ለመፍጠር አይደለም፡፡ እንደምትሩኝ ግን ተስፋ አደርጋለሁ!!!