Wednesday, March 30, 2016

ውለታዋን የዘነጋ መንጋ

© መልካሙ በየነ
መጋቢት 21/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን  ገና ዳዴ ሳልል ለመጀመሪያ ጊዜ ከተወለድኩበት ቤት ወጥቼ የተመለከትኳት ዳግም ከአብራከ መንፍስ ቅዱስ ከማኅጸነ ዮርዳኖስ የተወለድኩባት የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ የበላሁባት ደሙንም የጠጣሁባት በልቤ ውስጥ ገና በጨቅላ ዕድሜየ የታተመች የፍቅር ቤት ናት፡፡ የዚህችን ቤት ፍቅሯን የቀመስኩት ጣዕሟንም ያጣጣምኩት ገና በ40 ቀኔ ነው፡፡ ከፍ ስልም ወተት እና የማር ወለላ ከዚያም በላይ ምሳሌ የሌለውን ትምህርቷን ሳትሰስት ሳትነፍግ መግባኛለችና ከእቅፏ መውጣት አልሻም፡፡ የቤተክርስቲያን እቅፏ ይሞቃል፣ የቤተክርስቲያን እናትነቷ ይለያል፣ የቤተክርስቲያን ሰላሟ ያሳርፋል፣ የቤተክርስቲያን ፍቅሯ ያጠግባል፡፡ ስለዚህም አልሸሻትም አልርቃትምም ዕለት ዕለት አስባታለሁ እርሷም ወልደ ማርያም ልጄ ና! እያለች ታስበኛለች ትስበኛለችም፡፡ እናቴ ናትና መቼም ቢሆን ጥፋቷን አልመኝም፡፡ ከቻልኩም እንደ አቤሜሌክ የኢየሩሳሌምን ጥፋት አታሳየኝ ብሎ ስድሳ ስድስት ዘመን በእንቅልፍ እንዳሳለፈ እኔም እንዲሁ የእናቴን ጥፋት አታሳየኝ ብየ እለምናለሁ፡፡ እናቴ ስትጠፋ ማየት አልሻምና፡፡

ዛሬ ብዙዎች የዚችን እናት ጡት ነክሰዋል፡፡ ዛሬ ብዙዎች የዚችን እናት ጣት ቆርጥመዋል፡፡ እናቴ ቤተክርስቲያን  ሆይ! እኔ ልጅሽ ነኝ እነርሱም ልጆችሽ እንደሆኑ ያወራሉ እኔ ጥፋትሽ አልታየኝም እነርሱ ግን ጥፋትሽ ጎልቶ ታያቸው፡፡ ለእኔ ያልታየኝ ጥፋትሽ ለእነርሱ እንዴት ጎልቶ ታየ? እናቴ ሆይ! ንገሪኝ በእርግጥ እናት ነሽና ገመናቸውን እንደምትሸሽጊላቸው አውቃለሁ ግን እኮ እኔም ልጅሽ ነኝ ፡፡ ከፊደል ጀምረሽ ያስተማርሻቸው፣ ዳዊት ያስደገምሻቸው፣ ቅኔውን ያስቆጠርሻቸው፣መጽሐፍትን  የመገብሻቸው ወተት ፍቅርሽን ያጠባሻቸው ናቸው አኮ ዛሬ አጥርሽን ለማፍረስ ላይ ታች የሚሉት፡፡ በእውነት እናቴ ሆይ ግልጹን ንገሪኝ ምንሽ ነው የጎሰቆለው? ምንሽስ ነው ያረጀው? ምንሽስ ነው እንቅፋት የሆነው? ምንሽስ ነው ለድኅነት ጉዞ መሰናክል የሆነው? እነርሱ እናድሳት እያሉ ነው፡፡ እኔ ደግሞ አንች ሁሌም አዲስ መሆንሽን ነው የማውቀው የምመሰክረው፡፡ የአንች እርጅና ለእነርሱ ብቻ ነው እንዴ የሚታየው? የአንች ጉስቁልና ለእነርሱ ብቻ ነው እንዴ የተገለጠው? ወይስ ደግሞ ዓይናችን አንድ አይደለም? ታሪክሽ ታሪኬ ነው፤ ፍቅርሽ ፍቅሬ ነው፣ ትምህርትሽ ትምህርቴ ነው፣ ሰላምሽ ሰላሜ ነው፣ ድካምሽ ድካሜ ነው፣ ብርታትሽ ብርታቴ ነው፣ ጉዳትሽም ጉዳቴ ነው፣ ጠላትሽም ጠላቴ ነው፡፡ ስለዚህ በአንች ለሚመጣብኝ ሁሉ ቅድሚያ ተሰላፊ እንደምሆንልሽ አስባለሁ፡፡

ግን እኮ የአገራችን ሁሉም ታሪክ አንችው ነሽ፡፡ ግን እኮ የአገራችን ሁሉም ነገር አንችው ነሽ፡፡ ግን እኮ የአገራችን ሰላምና ፍቅር አንችው ነሽ፡፡ ግን ብዙዎች ውለታሽን ዘንግተዋል፡፡ ላሊበላን ያነጸው ልጅሽ ነው፡፡ ላሊበላን የሚጎበኝ ከዓለም ዳርቻ የሚጎርፈው ሕዝብ አብዛኛውን ክፍያ የሚከፍለው ለመንግሥት ነው፡፡ የጥምቀት በዓል የመስቀል በዓል የአንች ንብረት የአንች ሃብት ነው፡፡ ይህንን አስገራሚ ድንቅ የሆነውን የበዓል አከባበርሽን ለማየት ከዓለም ዳርቻ የሚጎርፈው ህዝብ አብዛኛውን ነገር አሁንም ለመንግሥት ነው የሚከፍለው ግን ውለታሽን አላወቀም፡፡ ዩኔስኮ ከመዘገባቸው የሚዳሰሱም ሆኑ የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል ከእምነት ተቋማት መካከል ብቸኛዋ አንችው የእኛ ቤተክርስቲያን ነሽ፡፡ ዓለም ወደ ኢትዮጵያ የሚጎርፈው እኮ ላሊበላን ለመጎብኘት ነው፡፡ ዓለም ወደ ኢትዮጵያ የሚጎርፈው እኮ የጥምቀትን በዓል አከባበር ለመመልከት ነው፡፡ ዓለም ወደ ኢትዮጵያ የሚጎርፈው እኮ የመስቀልን (የደመራን) በዓል አከባበር ለመመልከት ነው፡፡ ዓለም እኮ አረፋ እና መውሊድን ለመጎብኘት ኢትዮጵያ መጥቶ አያውቅም፡፡ ዓለም እኮ የፕሮቴስታንቱን ጭፈራ ለመመልከት ኢትዮጵያ መጥቶ አያውቅም፡፡ ኢትዮጵያን ለዓለም ከጥንት ጀምራ እስከአሁን ድረስ እያስተዋወቀች ያለችው ብቸኛዋ እምነት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ናት፡፡ በዚህ እውነት ላይ ማንም ተቃውሞ ሊያነሣ አይችልም፡፡ ነገር ግን ለዚህ ሁሉ ውለታዋ የሚሰጣት ምላሽ የተገላቢጦሽ ነው፡፡ ተሐድሶ መናፍቃኑ ይህን ሁሉ ባህሏን፣ ታሪኳን፣ ትምህርቷን፣ ዶግማዋን እና ቀኖናዋን ካላደስናት እያሉ ሌሊት ከቀን መሠሪ ተግባራቸውን እያከናወኑ ናቸው፡፡ በእውነት የመስቀል (የደመራ) በዓል እና የጥምቀት በዓል ባይከበር አገሪቱስ አሁን እያገኘች ያለውን የውጭ ምንዛሬ ልታገኝ ትችላለችን? የተሐድሶዎቹ ዓላማ እኮ ሃይማኖታዊ ብቻም አይደለም አገራዊ ችግርም ነው፡፡ መንግሥት እነዚህን ትኩረት ሰጥቶ ሊፈትሻቸው ሊያጠናቸውም ይገባል፡፡ የቤተክርስቲያን ውለታ ለእኛ ለልጆቿ ብቻ አይደለም ለማንኛውም ዜጋ ሁሉ ነው፡፡ ይህን ውለታዋን ግን ላይረዱ ይችላሉ ይህን ውለታዋን ግን ላይገነዘቡ ይችላሉ እኛ ግን ልጆቿ ነንና እንረዳለን እንገነዘባለንም፡፡ እኛ ግን እናታችን ናትና ውለታዋን አንዘነጋም ውለታዋን እንከፍላለን እንጅ፡፡

ተሐድሶ መናፍቃኑ ከውስጥ ፕሮቴስታንቱ፣ ሙስሊሙ፣ መንግሥት ሳይቀር ከወጭ ጦራቸው የተሰበቀው ወደዚች እናታችን ነው፡፡ ግን ለምን? ለእኔ ይህ የሁልጊዜ ጥያቄየ ነው፡፡ መልሴ ደግሞ አንድ ብቻ ነው እርሱም “ውለታዋን የዘነጋ መንጋ ስለተፈጠረ ነው” እላለሁ፡፡ ማንም እኮ የመሰለውን እምነት ሊከተል ሕገመንግሥታዊ ብቻ ሳይሆን አምላካዊም መብት ነው፡፡ አንዱ በሌላው እየገባ ማማሰል ግን ሕገመንግሥታዊም አምላካዊም አይመስለኝም፡፡ ግን ብዙዎች በማይመለከታቸው እየገቡ ሲያማስሉ ዝም ተብለዋል፡፡ ቤተክርስቲያናችን ማሻሻል የሚገባት ነገር ካለ ለእናታችን ለመንገር የምንቀርበው እኛው ልጆቿ ሳለን መናፍቃኑ ትሻሻልልን ትታደስልን እያሉ የሚጮኹት ጩኸታቸው የት ሊያደርሰን እንደሚችል መገመት ቀላል ነው፡፡ ትሻሻል ትታደስ ማለት ምን ማለት ነው? ብዙ አሠራሮች አሉ መሻሻል መታደስ የሚገባቸው፡፡ ለምሳሌ የቤተክርስቲያናችን የሂሳብ አሠራር፣ የቤተክርስቲናችን የሙዳዬ ምጽዋእት አቀማመጥ ደኀንነት፣ የቤተ ክርስቲያናችን የአሥራት እና የበኩራት ክፍያ አሰባሰብ፣ የቤተክርስቲያናችን የመባእ አሰባሰብ ዘዴ ላይ ሊሻሻል  ሊስተካከል የሚገባው አሰራር አለ፡፡ ይህንን እኮ ማሻሻል ያለብን እኛው ልጆቿ እኛው አማኞቿ ነን፡፡ ሌላው ከውጭ ያለ  ምንም አይመለከተውም ምክንያቱም እናትነቷን አምኖ አልተቀበለምና፡፡  ግን በእውነት የሚፈልጉት እንዲህ ያለውን ለውጥና መሻሻል ነውን? አይደለም፡፡ እነርሱ የተነሡትና የዘመቱት ዶግማዋ እና ቀኖናዋ ላይ ነው፡፡ ዶግማዋ ደግሞ በማንም ጩኸት ሊሻሻል አይችልም ምክንያቱም የእምነታችን መሠረት ነውና፡፡ ዶግማችን የሆነውን በሥላሴ አንድነትና ሦስትነት ማመንን ካሻሻልነው፣ አምላክ ሰው ሆነ ሰውም አምላክ ሆነ በሥጋ ማርያም ተገለጠ የሚለውን የሥጋዌን ምሥጢር ከለወጥነው፣ ሰው ዳግም ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅጸነ ዮርዳኖስ ካልተወለደ በቀር መንግሥተ ሰማያትን አይወርስም የሚለውን ምሥጢረ ጥምቀት ከቀየርነው፣ ሥጋዬን ያልበላ ደሜንም ያልጠጣ የዘላለም ሕይወትን አያገኝም የሚለውን ምሥጢረ ቁርባንን ካሻሻልነው፣ የሰው ልጅ ከሞት በኋላ ትንሣኤ ዘለክብር ወይም ትንሣኤ ዘለሐሳር ይነሣል የሚለውን ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን ከሰረዝነው ወይም ካሻሻልነው እምነታችን መሠረቱ ምን ሊሆን ነው? ይህን ሁሉ ካሻሻልን በኋላስ እምነታችን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሊባል ይችላልን? በፍጹም ሊሆን አይችልም፡፡ ዶግማችን ትንሽም ብትሆን ከተዛባች ከተሻሻለች ከተበረዘች እምነታችንም አብሮ ተለወጠ ማለት ነው፡፡ ሙስሊሞች እኮ ሙስሊም የሚባሉት፣ ፕሮቴስታንቶችም ፕሮቴስታንት የሚባሉት ዶግማቸው ከእኛ ዶግማ ጋር አንድ ስላልሆነ ነው፡፡ እነርሱ የራሳቸው የሆነ ዶግማ አላቸው እኛም እንዲሁ የራሳችን የሆነ ዶግማ አለን፡፡ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሆኖ ለመጽናት ከዚህ ዶግማ ውጭ ወደ ግራም ሆነ ወደ ቀኝም መመልከት አይቻልም፡፡


ምንም እንኳ ውለታዋን የዘነጋ መንጋ ቢፈጠርም ቤተክርስቲያን ግን የገሐነም ደጆችም የማይችሏት ሰማያዊት ናት፡፡ ስለዚህ እናድሳት እያሉ ሥርዓቷን ጥሰው ለማስጣስ፣ ዶግማዋንም አፍርሰው ላማስፈረስ የሚጥሩ ሰዎችን በጥንቃቄ ልንታገላቸው ይገባል፡፡ አሁን እየመጡብን ያሉት በዓይናችን ብሌን በሆነችው እናታችን ቤተክርስቲያን ነው፡፡ በዚች እናታችን ደግሞ ከጥንትም ጀምረን ቀልደን አናውቅም አባቶቻችን በሰይፍ የተቀሉላት በመጋዝ የተሰነጠቁላት እንደ ሽንኩርት የተከተፉላት ናት፡፡ እባካችሁ ወገኖቼ ዘመኑ ክፉ ዘመን ነውና ለእናታችን እንቁምላት፡፡ መላእክት ሌሊት ከቀን በሚጠብቋት ቅድስት እናታችን ውስጥ የተሐድሶ መንፈስ ያደረባቸው ሰዎች እንዳያስተምሩ፣ እንዳይሰብኩና እንዳይዘምሩ እንከላከል፡፡ እናታችን እናታቸው ስላልሆነች ሊመርዟት ቆርጠዋልና፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ቢፈርስስ?

© መልካሙ በየነ
መጋቢት 20/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ


የብዙዎቻችን ጥያቄ ነው ማኅበረ ቅዱሳን ቢፈርስስ? የሚለው፡፡ ማኅበሩ የተመሠረተው በእግዚአብሔር ፈቃድ በብጹአን አባቶቻችን ጸሎት እና እገዛ ነው፡፡ እውቅና የተሰጠውም ከቤተክርስቲያናችን የበላይ ውሳኔ ሰጪ ከሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ የምሥረታ ታሪኩን መተረክ አልፈልግም ምክንያቱም ማኅበሩ ራሱ በሥራው በተግባር ስለሚናገር ስለሚመሰክር፡፡ ማኅበሩን ያወቅሁት ከ10 ዓመት በፊት የግቢ ጉባዔ ተማሪ በሆንኩበት ወቅት ነበር፡፡ ሰው ማዳን ባልችል እንኳ ራሴን ግን ማዳን እንደሚገባኝ ሀ ብየ ፊደል መንፈሳዊን የቆጠርሁበት ማኅበር ነው፡፡ ውዳሴ ማርያምን ያጠናሁበት የግቢ ኮርሶችን የተከታተልኩበት ማኅበር ነው፡፡ ማኅበሩን ለማዎቅ የግድ የማኅበሩ አባል መሆን አያስፈልግም ከፍሬው የምንረዳው ነውና፡፡ የማኅበሩ አባላት ለአባልነት ከሚከፍሉት ገንዘብ በተጨማሪ ብዙ ጊዜያቸውን በቤተክርስቲያናችን ወቅታዊ ችግሮች ላይ በጣም በመወያየት ያሳልፋሉ፡፡ በውይይት የማይፈቱትን ደግሞ በጸሎት እግዚአብሔርን የሚለምኑ፤ እንዲሁም በገዳማት እና አድባራት ላይ ዕጣኑን ዘቢቡን ጧፉን ይዘው ሂደው ጸሎት ምሕላ እንዲያዝላቸው አባቶችን ዝቅ ብለው ጉልበታቸውን ስመው እግራቸው ሥር ተደፍተው የሚማጸኑ ናቸው፡፡ ማኅበሩ ከምሥረታው ጀምሮ በርካታ ፈተና እንደነበረበት ሲመሠረት ጀምሮ የሚያውቁት ሁሉ ይናገራሉ፡፡ እኔ ካወቅሁት ጀምሮ እንኳ በርካታ ፈተናዎችን በትእግሥት ሲያሳልፍ አይቻለሁ፡፡ ፈተናዎቹ ከየት የሚመጡ ናቸው? የሚለውን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ይገባል ከዚያም ቢፈርስስ ምን ሊከሰት ይችላል የሚለውን ስጋት ማየት ተገቢ ነው፡፡
እኔ የማኅበሩ ፈተናዎች ከሦስት አቅጣጫ እንደሚመጡ እገምታለሁ፡፡ እነዚህም፡-
1.  ማኅበሩን በሚገባ ከሚያውቁ ሰዎች፤
2.  ማኅበሩን በሚገባ ከማያውቁ ሰዎች፤
3.  ለቤተ ክርስቲያን ቀናኢ ከሆኑ ሰዎች ናቸው፡፡
v  ማኅበሩን በሚገባ የሚያውቁ ሰዎች ማኅበረ ቅዱሳን ማን እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ ማኅበሩ ራሳቸውን ትተው ለቤተክርስቲያኒቱ ሌሊት ከቀን የሚጥሩ አባላትን የያዘ እንደሆነ ያውቃሉ፡፡ ማኅበሩ የቤተ ክርስቲያናችን ገንዘብ ለቤተክርስቲያኒቱ አገልግሎት ብቻ መዋል አለበት የሚሉ አባላትን ያቀፈ መሆኑን ይረዳሉ፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ለምን ቀኖናችን ተጣሰ ለምንስ ዶግማችን ተለወጠ ብለው የሚጠይቁ አባላትን የያዘ እንደሆነ ይገነዘባሉ፡፡ ማኅበሩ ጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያናችን ጥንታዊነቷን ይዛ ከመሠርቷ ሳትናወጥ መጽናት አለባት ትምህርቷ መከለስ መበረዝ የለበትም ብለው የሚሞግቱ አባላትን እንደያዘ ያውቃሉ፡፡ ስለዚህ በቤተክርስቲኒቱ ውስጥ ተሰግስገው ኑፋቄያቸውን ለመዝራት አልመቻቸው ያለ ይህ ማኅበር በመሆኑ ያለስሙ ስምን በመስጠት እንዲጠላ ማድረግ ይፈልጋሉ፡፡ ማኅበሩ እንዲዘጋም ጥረታቸውን ቀጥለዋል፡፡ እነዚህ ማኅበሩ ካልተዘጋ በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ እንደልባቸው መፈንጨት እንደማይችሉ የተረዱ ናቸው፡፡ ፓትርያርካችን በዚህ ውስጥ የሚመደቡ ናቸው፡፡ ማኅበሩን ጥንት ከመሠረቱ ጀምረው ያወቁታል፡፡
v  ሌሎቹ ደግሞ የእነዚህ ተቃራኒዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ከሰው የሚሰሙትን ወሬ ሁሉ እውነት እንደሆነ የሚቆጥሩ ናቸው፡፡ ማኅበሩን ቀርበው አያውቁትም በሩቅ ሆነው መንግሥት እንዲህ አለው፣ ፓትርያርኩ እንዲህ አሉት፣ የሆነ ሰው እንዲህ ብሎታል ስለዚህ ማኅበሩ ችግር አለበት ማለት ነው የሚሉ ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ ራሱ መንግሥት ነው፡፡ መንግሥት ስጋቱ ማኅበሩ በሙያም በእውቀትም በገንዘብም በሁሉም ነገር ስብጥር በመሆኑ እንደአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ ይመለከተዋል፡፡ በእውነት የፖለቲካ ዓላማ ቢኖረው ኖሮ  ዛሬ የአገራችን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቁጥራቸው ቀላል ነው እንዴ፡፡ የአሁኑ መንግሥት ትግሉን ከአንድ ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባ ተነሥቶ አይደለም እንዴ የጀመረው፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ የግቢ ጉባዔ ተማሪ ቢነሣ መንግሥት አንድ ቀን በሥልጣኑ ላይ መቆየት ይቻለው ነበር እንዴ፡፡ የሚገርመው ነገር ተቃዋሚዎች ደግሞ ተማሪውን በግቢ ጉባዔ አፍኖ ይዞ መንግሥትን እንዳይቃወሙ ከእኛ ጎራ እንዳይሰለፉ ፈሪዎች ልፍስፍሶች አደረገብን ብለው ይወነጅላሉ፡፡ እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ማኅበሩ ማን እንደሆነ ለምን እንደተመሠረተ ያልተረዱ ናቸው፡፡ በእውነት መንግሥትን ለመገልበጥ ሲኖዶስን እውቅና የሚጠይቅ ማነው? የመንግሥት አካላት በዚህ ሥጋት አይግባችሁ ማኅበሩ ፖለቲካ ነክ ሥራን አይሰራም የቤተክርስቲያን ጉዳይ ገና አላለቀለትምና፡፡ በግለሰብ ደረጃም ያለን ሰዎች ማኅበሩን ከመናፍቃን ጋር የምንደምር አለን፡፡ በእውነት የትኛው መናፍቅ ነው ለቤተክርስቲያናችን ዘብ ሊሆን የሚታገለው? ሞትን የምንፈራው ሞተን ስላላየነው ነው እንጅ ሞተን ዓይተን ሆኖ ኖሮ ሞትንም ልንወደው እንችል ነበር፡፡ ስለዚህ ማኅበሩን እንዲህ ነው ከማለት አስቀድሞ ማዎቅ ያስፈልጋል፡፡
v  ለቤተክርስቲያን ቀናኢ ከሆኑ ሰዎችም ተጸእኖ አለበት፡፡ የእነዚህ ሰዎች ተጽእኖ ከግልጽነት ችግር የመነጨ ሊሆን ይችላል፡፡ ለአንድ ዓላማ የሚተጉ ናቸው አንድ አይነት ርእይ አንድ አይነት ተልእኮ አላቸው ነገር ግን ለቤተክርስቲያናቸው በማሰብ ዘብ ይቆማሉ፡፡ ዘብ ሲቆሙ ማኅበሩን እንደ አንድ የቤተክርስቲያን ጠላት ይመለከቱታል፡፡ ይህ አመለካከታቸው ለቤተክርስቲያኒቱ ከማሰብ ለቤተክርስቲያኒቱ ከመቅናት አንጻር ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅና ቅዱስ አትናቴዎስ በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ቢጣሉ በማን ነው የሚፈረደው? በማንም መፍረድ አይቻልም ምክንያቱም ሁለቱም ለቤተክርስቲያኒቱ ራሳቸውን ሰጥተዋልና ነገር ግን አንድ ዓላማ እንዳላቸው ማሳወቅ ያስፈልጋል፡፡ ዓላማቸው አንድ እንደሆነ ከተረዱ ዮሐንስ አፈወርቅና አትናቴዎስ አንድ ላይ የሚያገለግሉ ቅዱሳን ናቸው፡፡ ስለዚህ ማኅበሩን የሚቃወሙ አንዳንድ ሰዎች ለቤተክርስቲያኒቱ ከማሰብ አንጻር ማኅበሩ ቤተክርስቲያንን እየጎዳ ነው ብለው ከማሰብ አንጻር ዘብ ለመቆም ፈልገው ይሆናል፡፡ ነገር ግን ዓላማችሁ ከማኅበሩ ጋር አንድ ነውና አንድ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ማኅበሩ እየተከሰሰ ያለው እኮ ቤተክርስቲያንን መዘበረ ተብሎ አይደለም፡፡ ማኅበሩ እየተከሰሰ ያለው እኮ ቤተክርስቲያንን አቃጠለ ተብሎ አይደለም፡፡ ማኅበሩ እየተከሰሰ ያለው እኮ ወንጌልን አጣመመ ተብሎ አይደለም፡፡ ማኅበሩ እየተከሰሰ ያለው እኮ ተሐድሶ አራማጅ ሆነ ተብሎ አይደለም፡፡ ማኅበሩ እየተከሰሰ ያለው እኮ ሥርዓት ጣሰ ቀኖና አፈረሰ ተብሎ አይደለም፡፡ ማኅበሩ እየተከሰሰ ያለው ለምን ተሐድሶን ታጋልጣለህ ተብሎ ነው፡፡ ታዲያ ተሐድሶ ያልሆነ ሰው ማኅበሩን እንዴት ሊተቸው ሊነቅፈው ይችላል፡፡ መናፍቃን ያልሆነ ስም ይሰጡታል፡፡ ምክንያቱም ቤተክርስቲያንን እንደልባቸው ሊፈነጩባት ስላልቻሉ ነው፡፡ ሌላ ምንም ምክንያት የላቸውም ስለዚህ አንድ ሆነን ለቤተክርስቲያኒቱ ዘብ ልንቆምላት ያስፈልጋል፡፡

እንግዲህ ተጽእኖዎች ከእነዚህ ሦስት አቅጣጫዎች ሊመጡ እንደሚችሉ እገምታለሁ፡፡ ተጽእኖዎችን የሚፈጥሩት ሰዎች በብዛት በተሐድሶ አራማጆች አሉባልታ ላይ ተመሥርተው ነው፡፡ አሁን አሁን ነገራቸውን ፖለቲካዊ ይዘት ማስያዝ ጀምረዋል፡፡ እነርሱ ተከራክረው መርታት የሚችሉበትን ትምህርት አልተማሩም፡፡ ስለዚህ ያላቸው አማራጭ ራሳቸውን ነጻ አድርገው ነገሩን ፖለቲካዊ ይዘት ሰጥተው ከመንግሥት ጋር በማጋጨት መንግሥት ነገሩን ሲይዘው እነርሱ አርፈው ኑፋቄያቸውን መዝራት ይፈልጋሉ፡፡ ለምሳሌ ዐውደ ርዕዩ አንድ ቀን ሲቀረው መዘጋቱ ሌላ ምንም ተልእኮ የለውም፡፡ ለምን ዐውደ ርዕዩ ይዘጋብናል ብሎ ሕዝቡ አመጽ የሚፈጥር መስሏቸው ነበር የዘጉት ነገር ግን ሕዝቡ ቀድሟቸዋል፡፡ ሕዝቡ እየቆረቆረው ያለው ቃለ ወንጌል እንጅ አመጽ አይደለም፡፡ ሕዝቡ ያለው ከእግዚአብሔር ጋር እጅ ከሰይጣን ጋር አልነበረም፡፡ ለዚያም ነው እስኪደነግጡ ድረስ የሕዝቡ ዝምታ የደነቃቸው፡፡ ድንጋይ የሚወራወር ሕዝብ ማኅበሩን አልተከተለውም፡፡ ጥይት የሚተኩስ የታጠቀ ሰው ማኅበሩን አልተከተለውም፡፡ ቦንብ የሚያፈነዳ አሸባሪ ማኅበሩን አልተከተለውም ለዚህም ነው በትእግሥት የሚጠባበቀው፡፡ ዐውደ ርዕዩን ማንም ይዝጋው ማን አይደንቀኝም እኔን የሚደንቀኝ ግን ለማየት ጓጉቶ ከክፍለ ሐገር ድረስ ሳይቀር አዲስ አበባ ሂዶ ዐውደ ርዕዩ ታገደ የሚለውን መርዶ ሲሰማ በትእግሥት ወደመጣበት መመለሱ ነው፡፡ በእውነት ነው የምላችሁ በማኅበሩ የኮራሁበት ቀን ቢኖር ያን ጊዜ ነው፡፡ አንድ ድንጋይ አልተወረወረም፣ አንድ ጥይት አልተተኮሰም፣ አንድ ቦንብ አልፈነዳም ምክንያቱም ዓላማው ሰማያዊ እንጅ ምድራዊ አይደለማ! እንዴ መንግሥትም ይህን ተግባር እኮ ማድነቅ ነበረበት ዕገዳው ላይ እጁ ሊኖርበት ቢችልም፡፡
አሁን አሁን መነጋገሪያ የሖነው ጉዳይ ማኅበረ ቅዱሳን ቢዘጋስ የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ማኅበሩ ሊዘጋ የሚችለው በቤተክርስቲያኒቱ የበላይ በሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ እንደሆነ አምናለሁ አውቃለሁም፡፡ ፓትርያርኩ እንደ አቡነ ሺኖዳ ሳልሳዊ መጽሐፍ የመጻፍ ብቃት ስለሌላቸው በሚጽፉት የብጹእነታቸው ማስፈራሪያ ደብዳቤ ምንም እንደማይሆን እገምታለሁ፡፡ ነገር ግን በብዙ ተጽእኖዎች ሲኖዶሱ እንዲዘጋ ቢወስንስ ምክንያቱም የምንኮራባቸው አባቶቻችን “ይህን የጥፋት ዘመን አታሳየን” ብለው ላይመለሱልን ዐርፈዋል፡፡ አሁን የቀሩን በጣም ጥቂት የሚባሉት አባቶቻችን  ናቸው፡፡ ስለዚህ ያፈርሱታል ቢባል ምኑ ነው የሚፈርሰው የሚል ጥያቄ አለኝ፡፡ በእርግጠኝነት ስሙ ይፈርሳል ስሙ ይለወጣል አገልግሎቱ ግን ይጨምራል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን የሚባለው አንድ ስም ሽህ ስም ሆኖ ይነሣል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን የሚለው ስም ወደ ቀደመ ስሙ ተለውጦ ወደ ማኅበረ ቅድስት ድንግል ማርያም፣ወደ ማኅበረ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ወደ ማኅበረ ቅዱሳን ሐዋርያት፣ ወደ ማኅበረ ቅዱስ ሚካኤል፣ ወደ ማኅበረ ቅዱስ ገብርኤል፣ ወደ ማኅበረ ቅዱስ ዮሐንስ ወዘተ ይለወጣል እንጅ ሌላ የሚዘጉት ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ማኅበረ ቅዱሳን የሚለው የመሰብሰቢያ ስም የአገልግሎት መስጫ ስም እንጅ እምነት አይደለማ፡፡ ሰዎች በአምላክ ፈቃድ የመሠረቱት እንጅ በራሳቸው ፈቃድ የመሠረቱት አይደለማ፡፡ ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳን ቢፈርስስ ለሚለው ጥያቄ የእኔ መልስ የሚሆነው መፍረስ ልንለው የምንችለው የሥም ለውጥ ነው እንጅ የአገልግሎት የዓላማ የርእይ እና የተልእኮ ለውጥ ይሆናል ብየ አላስብም አልገምትምም፡፡ ነገር ግን ለመንግሥትም ለሐገርም ትልቅ ተጽእኖ እንደሚኖረው እገምታለሁ፡፡


የተቀመጡት በቆሙት ላይ


© በመልካሙ በየነ
መጋቢት 19/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ተጓዥ ነኝ መንገደኛ፡፡ ስጓዝ ስጓዝ ስ…ጓዝ ውየ ከሆነ ቦታ ላይ ደረስኩ፡፡ ሰው ሁሉ ተቀምጦ ከፊት ለፊታቸው ላይ ካለው ትልቅ ስክሪን ላይ ዓይናቸውን አፍጥጠዋል፡፡ የሚመለከቱት ነገር የእኔንም ቀልብ ሳይስብ አልቀረም፡፡ ለዚያም ነው ከተመልካቾች ፊት ላይ ቆሜ ስክሪኑ ላይ ያፈጠጥሁት፡፡ የተቀመጡ ተመልካቾች ጮኹብኝ፡፡ በእውነት ያንን ጩኸት የሰማው ጆሮየ “ስቅሎ ስቅሎ” ያሉትን የአይሁዳውያንን ድምጽ የሰማ ነበር የመሰለው፡፡ በእርግጥ በምመለከተው ነገር ከመመሰጤ የተነሣ ጩኸታቸውን ከምንም አልጣፍሁትም ነበር፡፡ ምክንያቱም የምመለከተው ነገር የቤቴ ጉዳይ ነበራ!፡፡ ጩኸታቸው ግን እየበረከተ ድምጻቸውም እየጎላ መጣ፡፡ እኔም የግድ መዞር ነበረብኝና ዞር ብየ ምንድን ሆናችሁ? ዝም ብላችሁ መመልከት አትችሉም እንዴ? አልኳቸው፡፡ “እንዴ በየት በኩል እንመልከት ጋረድከን እኮ!” አሉኝ በአንድ ድምጽ፡፡ ለካ እነርሱ ስለተቀመጡ እኔ ደግሞ ስለቆምኩ እንቅፋት ሆኘባቸዋለሁ፡፡ ለካ እነርሱ ስለተቀመጡ የእኔ ነቅቶ መቆም መሰናክል ሆኖባቸዋል፡፡ ለካ የእኔ በእነርሱ ፊት መቆም የሚያዩትን ነገር እንዳያዩ የሚሠሩትን ነገር እንዳይሠሩ አድርጓቸዋል፡፡ ለካ የእኔ መቆም አሻግረው የሚመለከቱትን ነገር ከልሏቸዋል፡፡ ለካ የእኔ በፊታቸው መቆም ስክሪኑን ጋርዷቸዋል፡፡ ታዲያ እንደእኔ መቆም አትችሉም እንዴ አልኳቸው፡፡ እነርሱ ግን አሁንም አብዝተው ጮኹ “እንዴ ለምንድን ነው እንደአንተ የምንቆመው? ምን በወጣን ነው እግራችን እስኪዝል ድረስ የምንቸገረው? ይልቅስ ወይ ተቀመጥ ወይ ከእኛ ኋላ ቁም ይህ ካልተመቸህ ደግሞ ውጣልን እኛ በሰላም እንመልከትበት” አሉኝ፡፡ አይ አንች አገር! አይ አንች ቤተክርስቲያን! አይ አንች የእናት የአባቴ ቤት! አልኩ በልቤ፡፡ አገሪቱ ውስጥ ለሥራ የቆመውን ሰው በስንፍና የተቀመጠ ሰው ጋረድከኝ ተቀመጥ ይለዋል፡፡ አገሪቱ ውስጥ ለሥራ የቆመውን ሰው በስንፍና የተቀመጠ ሰው ስንፍናየን እንዳላጣጥም ሙስናየን እንዳልቀበል ጋረድከኝ ተቀመጥ ይለዋል፡፡ አገሪቱ ውስጥ ለሥራ የቆመውን ሰው በስንፍና የተቀመጠ ሰው ተቀምጨ እንዳልበላ ሰርቄ እንዳልተዳደር ጋረድከኝ ስለዚህ ከኋላየ ቁም አልያም ተቀመጥ  አስተዳደሬ ካልተመቸህ ደግሞ ውጣ ይለዋል፡፡ አገሪቱ ውስጥ ለሥራ ነቅቶ ከቆመ ሰው ይልቅ በስንፍና ለተጋደመ ትልቅ ቦታ ትልቅ ሹመት እየተሰጠው ነው፡፡ ስለዚህ ምርጫችን መቀመጥ ወይም ከኋላቸው መቆም ወይም አልተመቸኝም ብሎ አገር ለቅቆ ንብረት ጥሎ መውጣት ነው፡፡ ሌላ ምርጫ አይሰጡህም፡፡ ግን እኮ አገሬ ናት ለምን?
ቤተክርስቲያንስ ብትሆን በእንዲህ ዓይነቶች አይደለም እንዴ ዛሬ እየታመሰች ያለችው፡፡ እኛ ደብሩን አጥቢያውን እየመራነው ነው እናንተ አይመለከታችሁም አትጋርዱን፡፡ እኛ ስብከቱን እየሰበክነው ነው እናንተ አይመለከታችሁም ከፊታችን አትቁሙ፡፡ እኛ መዝሙሩን እየዘመርነው ነው እናንተ አይመለከታችሁም ከፊታችን ቆማችሁ አትጋርዱን፡፡ እኛ ሰዓታቱን እየቆምነው ነው እናንተ አይመለከታችሁም ከኋላችን ቁሙ፡፡ እኛ ኪዳኑን እያደረስነው ነው እናንተ አይመለከታችሁም ከፊታችን አትቁሙ አርፋችሁ ተቀመጡ፡፡ እኛ ቅዳሴውን ውዳሴውን እየፈጸምነው ነው እናንተ አይመለከታችሁም ከፊታችን አትቁሙ አርፋችሁ ተቀመጡ፡፡ እናንተ ቆማችሁ የምትሠሩት ሥራ  እኛ ተቀምጠን አሻግረን እንዳንመለከት እንቅፋት ሆኖብናል ስለዚህ አርፋችሁ ተቀመጡ አልያም ከእኛ ኋላ “አቡነ አቡነ”፣ “አባ አባ”፣ “መምህር መምህር” እያላችሁ  ተከተሉን ከኋላችን ቁሙልን ከኋላችን አጅቡን ይህም የማይመቻችሁ ከሆነ ከቤተክርስቲያናችን ውጡልን እኛ ተቀምጠን ማየት የምንፈልገው ነገር አለንና ይሉናል፡፡ በእውነት ቤተክርስቲያናችን ቤተክርስቲያናቸው ናትን? ብትሆንማ እንዲህ ባላሉን ነበር፡፡ ብትሆንማ አጥንቷ እስኪታይ ድረስ ባልደበደቧት ነበር፡፡ ብትሆንማ ገንዘቧን ለግላቸው ባላደረጉት ነበር፡፡ ብትሆንማ ስትጮኽ ጩኸቷን በሰሟት ነበር፡፡ ብትሆንማ ባልገፏት ነበር፡፡ ብትሆንማ እስከሞት ድረስ በታመኑላት ነበር፡፡ ብትሆንማ ትህትናን ባወቁባት ነበር፡፡ ብትሆንማ ወንጌልን በተማሩባት ባስተማሩባት ነበር፡፡ ብትሆንማ ቅዳሴውን ባስቀደሱባት በቀደሱባት ነበር፡፡ ግን ምናቸውም አይደለችም! ለዚያም ነው መድረኳን ለምንፍቅና የተጠቀሙባት፡፡ ለዚያም ነው ምሥጢረ ተዋሕዶ እንዳይነሣ በጠላትነት የቆሙባት፡፡ ለዚያም ነው ሀብት ንብረቷን ለራሳቸው የሚያግበሰብሱ ወሮበሎች የተሠማሩባት፡፡ ለዚያም ነው ለመናፍቃን አዳራሽ ብቁ የሆነ ሰውን የሚፈለፍሉባት፡፡ ይህን ግብራቸውን ስትቃወም ነው እንግዲህ ከፓትርያርኩ ጀምሮ  እስከ ታች አጥቢያ ድረስ ሰንሰለታቸውን ተጠቅመው ተቀመጥልን እረፍልን የሚሉህ፡፡ ጋረድከኝ ተቀመጥ ይልሃል፡፡ ለምንፍቅናው እንቅፋት ሆነኽበታልና፡፡ ታዲያ ዝም እንበል? አንልም!!! በፍጹም አንልም!!!!

እናቴ ቤተክርስቲያን ሆይ! ሌሊት ከቀን ሊጠብቁሽ ነቅተው የቆሙ  ከመንበራቸው እየተሰደዱ የሰበኩሽ ለዓለም ሁሉ ያሳወቁሽ ልጆችሽ እነ ዮሐንስ አፈወርቅ እነ አትናቴዎስ ልጅ አልወለዱምን? ዛሬ እኮ የጠፋው እምነቱን በአደባባይ ደፍሮ የሚመሰክር በዓለም ገብቶ የሚያስተምር ሳይሆን  በመድረክሸ ላይ ቆሞ እምነቱን የሚመሰክር ሰው ነው፡፡ በፍርሐት ተሸብቦ ምሥጢረ ተዋሕዶን ሳይገልጥ ሲያስጨበጭብ ብቻ ቆይቶ ከመድረክ የሚወርድ መምህር ነው ያፈራን፡፡ እናንተ ተቀምጣችሁ በቤተክርስቲያን ጥላ ስር አርፋችሁ ሙዳዬ ምጽዋእትን ትገለብጣላችሁን? እናንተ የእናታችንን ጡት እየጠባችሁ ስትጠግቡ ጡቶቿን ትነክሳላችሁን? በእርግጥ ጡቶቿን ጠብታችኋል ለማለት የሚያስችል ነገር የለንም፡፡ እናንተ ተቀመጡ ችግር የለውም፡፡ እናንተ ተኙ ችግር የለውም፡፡ እናንተ ስረቁ ችግር የለውም፡፡ እናንተ ሙስና ሥሩ ችግር የለውም፡፡ አሜን ብለን ተቀብለናችኋላ! ግን እኛ እንቁምበት ተውን፡፡ ግን እኛ እንሥራበት ተውን፡፡ ግን እኛ እንጸልይበት ተውን፡፡ ግን እኛ እንጹምበት ተውን፡፡ ግን እኛ እንስገድበት ተውን፡፡ ግን እኛ እንመጽውትበት ተውን፡፡ ግን እኛ እናጉርሳችሁ ተውን፡፡ እንዴ የእኛን ብር ነው እኮ ፎቅ የሠራችሁበት፣ የእኛን ንብረት እኮ ነው ቤት የገባችሁበት፣ የእኛን ገንዘብ እኮ ነው የደለባችሁበት፡፡ የእኛን ገንዘብ እኮ ነው የተቀራመታችሁት፡፡ የእኛን ገንዘብ እኮ ነው ገንዘባችሁ ያደረጋችሁት፡፡ ታዲያ እኛ ቆመን ካልመጸወትናችሁ ምኑን ተቀምጣችሁ ትዘርፉታላችሁ? ምኑንስ ትሰርቁታላችሁ? መቀመጥን ገንዘቡ ያደረገ ሰነፍ በቆሙት እንዴት ይበሳጫል፡፡ እኛም እኮ የማንቀመጠው አላስችል ብሎን ነው አትፍረዱብን እንጅ፡፡ እናታችን ናታ ጡቷ የተነከሰው፡፡ እናታችን ናታ የተሰደበችው፡፡ እናታችን ናታ የተገፋችው፡፡ እናታችን ናታ የተደፈረቸው፡፡ እናታችን ናታ የተወገረችው፡፡ እናታችን ናታ ልብሷን የተገፈፈችው፡፡ እናታችን ናታ የተሰረቀችው፡፡ እሽ ከእናታችን ቤት ወዴት እንሂድላችሁ? እሽ ከእናታችን ብብት ወዴት እንጠለልላችሁ? እሽ ከእናታችን ጉያ ወዴት እንሽሽላችሁ? እንዴ ተረዱን እንጅ እኛንም፡፡ ዓላማችሁ ዓላማችን አይደለም፡፡ ትምህርታችሁ ትምህርታችን አይደለም፡፡ ምስጋናችሁ ምስጋናችን አይደለም፡፡ ቅዳሴያችሁ ቅዳሴያችን አይደለም፡፡ ጸሎታችሁ ጸሎታችን አይደለም፡፡ ቃላችሁ ቃላችን አይደለም፡፡ ንግግራችሁ ንግግራችን አይደለም፡፡ ሥርዓታችሁ ሥርዓታችን አይደለም፡፡ ዶግማችሁ ዶግማችን አይደለም፡፡ ቀኖናችሁ ቀኖናችን አይደለም፡፡ ነገር ግን እናታችን መድረክ ላይ እናንተም ለራሳችሁ ዓላማ እኛም ለራሳችን ዓላማ ተገናኘን፡፡ ያን ጊዜ እኛ ቆምን እናንተም ተቀመጣችሁ፡፡ ከዚያም የእናንተን ዓላማ ከለልነው ለዚያም ነው እንደእናንተ እንድንቀመጥ ግርግር የምትፈጥሩት፡፡ ለዚያም ነው ከእናንተ ኋላ ቆመን ዓላማችሁን ስታስፈጽሙ ዝም ብለን እንድንመለከት ሽብር የምትፈጥሩት፡፡ ለዚያም ነው የእናታችንን መድረክ ለቅቀን እንድንወጣ የሌለንን ስም ሰጥታችሁ ስማችንን የምታብጠለጥሉት፡፡ የቆመው ተዋሕዶ የተቀመጠው ደግሞ ተሐድሶ መሆኑን ብታውቁ ግን ሳታውቁ የተቀመጣችሁ ሁሉ በተነሣችሁ እና አብራችሁን በቆማችሁ ነበር፡፡ ግን…

Wednesday, March 23, 2016

ትምህርተ ሃይማኖት (ክፍል 5)


© በመልካሙ በየነመጋቢት 14/2008 ዓ.ምደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ


በክፍል 4 ሃይማኖት እንዴት እና መቼ ተጀመረ? ሃይማኖት ለማን ያስፈልጋል? የሚሉትን የሃይማኖትና የፍጥረታትን ግንኙነት ተመልክተናል በዚህ ክፍል ደግሞ ሰው ያለሃይማኖት መኖር ይችላልን የሚለውን እና የክርስትና እምነት ምን እንደሚመስል በአጭሩ እንመለከታለን መልካም ንባብ!
ሰው ያለሃይማኖት መኖር ይችላልን? ለሚለው ጥያቄ አጭሩ መልስ መኖር አይችልም የሚል ነው። ሰው የሚያመልከውን ነገር ላያውቅ ይችላል፣ ስለሚያመልከውም ነገር ላያውቅ ይችላል እንጅ የሚያመልከው ነገር ይኖረዋል። ምናልባት በእግዚአብሔር ላያምን የሚችል ሰው ቢኖር ሌላ የሚያመልከው ነገር ስላለው ሰው ያለሃይማኖት ሊኖር አይችልም። በምንም ነገር አላምንም የሚል ሰው ራሱ ይህ አለማመኑ ሃይማኖቱ ነው። ጠቅለል ሲል ሰው እግዚአብሔርን ባያመልክ እንኳ ጉልበቱን፣ ሥልጣኑን፣ ገንዘቡን፣ ወገኑን፣ ውበቱን፣ እውቀቱን ወዘተ ማምለኩ አይቀርም። ሰው ያለ አየር መኖር እንደማይችል ሁሉ ያለሃይማኖትም መኖር አይችልም። ምናልባት ስለአየሩ ምንም ላያውቅ እንደሚችለው ሁሉ ስለሚያምነውም ላያውቅ ይችላል እንጅ ያለእምነት ግን ሊኖር አይችልም። እኛ ወደምናምንበት የክርስትና ሃይማኖት ስንሄድ ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ነው ብለን እናምናለን። ክርስትና ምንድን ነው? የሚለውን እንመልከት።
የክርስትና ሃይማኖት በክርስቶስ ደም የተመሠረተ መሆኑን በወንጌል እንደተጻፈው አምነን የተቀበልነው ነው። ይህ ክርስትና የመገለጥ ሃይማኖት ነው። ክርስትና ሃይማኖት በማን ላይ ሊሆን እንደሚችል ሲያስረዳ አምላክ ሰማያዊ ሥጋ አዳምን ለብሶ ተገልጧል። 1ኛ ጢሞ3፥16 ላይ ኢየሱስ ክርስቶስን በሥጋ የተገለጠ ብሎ ገልጾታል። ስለዚህ ክርስትና በክርስቶስ መገለጥ ላይ የጸና ነው። ክርስትና በፈጣሪ የተመሠረተ በሐዋርያት ስብከት ላይ የታነጸ ነው። እንደሎሎች እምነቶች በፍጡር አልተመሠረተም። ሞተው በቀሩት በበሰበሱት ፍጡራን አልተመሠረተም ሞትን ድል በነሣው በሥጋ ማርያም በተገለጠው አምላክ እንጅ።
የክርስትና እምነት ልዩ ነው። መሠረቱ የክርስቶስ ማንነት ነው። ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ እንደተናገረው በሥጋ የተገለጠው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ማመን ነው። ይህ እምነት ልዩ የተባለው እንደሌሎች አንድ ብቻ አለማለቱ ነው። ምሥጢረ ሥላሴ ላይ ስንመለከት እግዚአብሔር አንድ ሲሆን ሦስት፤ ሦስት ሲሆን አንድ ነው። ልዩ ሦስትነት አለው አንድነቱ ሦስትነቱን አይጠቀልለውም፤ ሦስትነቱም አንድነቱን አይከፋፍለውም። ይህ ልዩ ምሥጢር ለአንዳንዶች አልገባቸውም ስላልገባቸውም ልዩ ከሆነው ክርስትና ኮበለሉ። በመለኮት፣ በስልጣን፣ በመፍጠር በማሳለፍ በባሕርይ በህልውና አንድ የሆነው እግዚአብሔር በስም በአካል በግብር ሦስት ይሆናል። ለዚህ ነው በዚህ እምነት ላይ የተመሰረተውን ክርስትና ልዩ ነው የምንለው። ወልድ በተለየ አካሉ ከድንግል ማርያም ሥጋን ለብሶ አዳነን ለማለት ያበቃንም ይኼው እውነት ነው። በደኃራዊ ልደቱ ቀዳማዊ ልደቱን ተረድተን ወልደ አብ ወልደ ማርያም ለማለት የበቃን ለዚህ ነው። በደኃራዊ ልደቱ ያለአባት ከድንግል ማርያም ሲወለድ እንዳየነው ሁሉ በቀዳማዊ ልደቱ ያለእናት ከአብ መወለዱን እናምናለን። ይህም ድንቅ ምሥጢር ክርስትናን ልዩ ያደርገዋል።
ሌላው የክርስትና እምነት በር ነው። የተለያዩ እምነቶች ሊድኑባቸው የሚችሉባቸውን መንገዶች ይከተላሉ። ለክርስትና ግን ዘላለማዊ ድኅነት ለማግኘት መንገዳችን አንድ ብቻ ነው እርሱም በሥጋ ማርያም በተገለጠው ክርስቶስ ማመን ነው። ከዚህ መንገድ ውጭ ሕግን ቢፈጽሙ፣ ምግባር ትሩፋት ቢሠሩ በምልጃ ቢያምኑም መዳን የለም። ዮሐ 10፥9 "በሩ እኔ ነኝ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል ይገባልም ይወጣልም መሰማሪያም ያገኛል" ዮሐ 14፥6 "እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም" በማለት ይናገራል። ይህንን ቃል የተናገረው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እንግዲህ እንደነገረን ለመዳን በበሩ በኩል መግባት ያስፈልገናል። በሥጋ ማርያም በተገለጠው ጌታ አምነን በስመ ሥላሴ ተጠምቀን ሥጋውን በልተን ደሙንም ጠጥተን ምግባር መሥራት ሕግ መፈጸም መመጽወት መጾም መጸለይ መማር ማስተማር እንችላለን ምክንያቱም በሩ መንገዱ እውነቱ እርሱ ነውና። እግዚአብሔር አብን እግዚአብሔር ለማለት የግድ በሥጋ ተግልጦ አባቱን የሰበከልንን ጌታ አምላክነቱን ማመን አለብን ምክንያቱም መንገድ እውነትና ሕይወት ጌታችን ነውና። በዚህ በር ያልገባ ማለትም በክርስቶስ አምላክነት ያላመነ በስመ ሥላሴ ያልተጠመቀ ሥጋውን ያልበላ ደሙንም ያልጠጣ ሊጸድቅ አይችልምና ክርስትና ጠባብ የጽድቅ በር ናት።
ተፈጸመ
ማጣቀሻ፡- ዲ.ን ብርሃኑ አድማስ፣ ትምህርተ ሃይማኖት መግቢያ-ማኅበረቅዱሳን 1996 ዓ.ም

Tuesday, March 22, 2016

ትምህርተ ሃይማኖት (ክፍል 4)

© በመልካሙ በየነ
መጋቢት 13/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

በክፍል 3 ውስጥ የሃይማኖት መሠረቶች ምን ምን እንደሆኑ ተመልክተናል በዚህ ክፍል ደግሞ ሃይማኖት እንዴት መቼ ተጀመረ? ሃይማኖት ለማን ያስፈልጋል? የሚሉትን የሃይማኖትና የፍጥረታትን ግንኙነት እንመለከታለን፡፡ መልካም ንባብ!!!
ሃይማኖት ለፍጥረታት የተሰጠ ከፈጣሪያቸው ጋር የሚገናኙበት መስመር ነው፡፡ ስለዚህ ስለ ሃይማኖት ስናነሣ ሃይማኖት የሚያስፈልጋቸው እነማን ናቸው የሚለውን ማየት ተገቢ ነው፡፡ ፍጥረታት ሁሉ ከፈጣሪያቸው ጋር በራሳቸው ቋንቋ በራሳቸው መግባቢያ ይግባባሉ ይገናኛሉ፡፡ ነገር ግን የተፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ክብሩን ሊወርስ ስሙን ሊቀድስ አልተፈጠረም፡፡ ፍጥረታት የተፈጠሩበት የራሳቸው የሆነ ዓላማ አላቸው፡፡ ለምሳሌ ለምግበ ሥጋ ለምግበ ነፍስ የተፈጠሩ አሉ፤ ለአንክሮ ለተዘክሮ የተፈጠሩ አሉ እነርሱን እያየን እጹብ እጹብ እነርሱን የፈጠረ በማለት ፈጣሪን እንድናመሰግን ማለት ነው፡፡ ስሙን ቀድሰው ክብሩን ወርሰው እንዲኖሩም የተፈጠሩ አሉ፡፡ እነዚህ ናቸው እንግዲህ ሃይማኖት የሚያስፈልጋቸው፡፡ እነዚህም ሰውና መላእክት ናቸው፡፡  እነዚህ ከሌሎች ፍጥረታት ይለያሉ፡፡ በማወቅ ወይም እውቀት ያላቸው በመሆኑ እና መላእክት ፍጹም የማይሞቱ ሰውም ከሞት በኋላ የሚነሣ መሆኑ ልዩ ያደርጋቸዋል፡፡ ሌሎች ፍጥረታት ከምድር ከጠፉ ፈርሰው በስብሰው የሚቀሩ ናቸው ትንሣኤን አይጠብቁም ሰው ግን ትንሣኤን ይጠብቃልና ሃይማኖት ያስፈልገዋል ማለት ነው፡፡ መላእክትም እንዲሁ እምነት ያስፈልጋቸዋል፡፡
የሰው ልጅ ለማመን ብዙ ስጦታ አላቸው፡፡ የመጀመሪያው ነጻ ፈቃድ ነው፡፡ ፈጣሪ ማንንም አስገድዶ እንድናመልከው አያደርግም፡፡ እውቀቱን ተጠቅሞ ፈጣሪውን እንዲያውቅ ያደርገዋል እንጅ አስገድዶ አምልከኝ አይለውም፡፡ ማንም ሰው ፈጣሪውን ለማምለክም ሆነ ላለማምለክ ነጻ ፈቃድ አለው፡፡ አዳም ዕጸ በለስን ቢበላ እንደሚጎዳ ሳይበላ ቢጠብቃት እንደሚጠቀም አሳይቶ ባይተወው ኖር ለመብላት አይበቃም ነበር፡፡ እንዳትበላ ብሎ ማስገደድና እንዳይበላ ማድረግ ይቻለው ነበር ነገር ግን ነጻ ፈቃድ አለውና አላስገደደውም፡፡ ነጻ ፈቃድ ስላለን ብለን ግን እውቀት እንደሌላቸው እንስሳት መሆን የለብንም ለዚህም ነው ሁለተኛው ነገር የተሰጠን፡፡ ሁለተኛው ነገር ምርጫ ነው፡፡ ነጻ ፈቃድ ቢኖረንም በጎውን ከክፉ፣ የሚጎዳውን ከሚጠቅመው መለየትና እና መምረጥ አለብን፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ነው ካልን ወይም አምላክነቱን ካልተቀበልን አምላክ የምንለውን ነገር መምረጥ አለብን መብታችን ነውና፡፡ ሶስተኛው ኃላፊነት ነው፡፡ ነጻ ፈቃዱን እና ምርጫውን ተጠቅሞ ለተቀበለውና ላደረገው ነገር ተጠያቂ የሚሆነው የሚመጣውን ማንኛውንም ነገር ሁሉ በኃላፊነት የሚቀበለው ራሱ መራጩ ሰው ነው፡፡ አዳምን ልብ ማለት ያሻል፡፡ መብላት አለመብላት ነጻ ፈቃድ ነው፡፡ መብላትን መምረጡ ምርጫ ነው፡፡ 5500 ዘመን በእግረ አጋንንት መረገጥ ኃላፊትን መውሰድ ነው፡፡ አታድርጉ የተባልነውን ነገር ለማድረግ ብንፈቅድ ለሚመጣው ማንኛውም ችግር ኃላፊነቱን ራሳችን እንወስዳለን ማለት ነው፡፡
 ሃይማኖት እንዴትና መቼ ተጀመረ የሚለውን ስንመለከት ፍጥረታት መፈጠር የጀመሩበትን ቀን ማስታወስ ያስፈልገናል፡፡ የሥነ ፍጥረት መጀመሪያ የነበሩት ክብሩን ሊወርሱ ስሙን ሊቀድሱ በዕለተ እሁድ የተፈጠሩት መላእክት ናቸው እምነትን የጀመሩት፡፡ አምላክ ፈጥሮ ተሠወራቸው አዋቂ አእምሮ ሰጥቷቸዋልና መርምረው ይወቁኝ ብሎ፡፡ በዚህ ጊዜ ማን ፈጠረን? ከየት መጣን? ብለው ፍጡርነታቸውንና የፈጣሪን መኖር አምነው ተናገሩ፡፡ በዚህ ጊዜ አኃዜ መንጦላእት የነበረው የመላእክት ሁሉ አለቃ ሳጥናኤል ከፍ ቢል ማንም የለም ዝቅ ሲል ግን መላእክት አሉ፡፡ በዚህ ሰዓት ነጻ ፈቃዱን ተጠቅሞ እኔ ፈጠርኳችሁ አላቸው፡፡ ጥርጥር ወይም ክህደትና እምነት ያንጊዜ ጀመረ ማለት ነው፡፡ ሌሎች ሊቃነ መላእክት እውቀታቸውን ተጠቅመው አምላካቸው ሳጥናኤል መሆን አለመሆኑን አረጋገጡ። ቅዱስ ገብርኤል ዝቅ ሲል ከእርሱ በታች ያሉ እልፍ አእላፋት መላእክትን ተመለከተ። እነዚህ ሁሉ ከእኔ በታች ናቸው ግን እኔ አልፈጠርኳቸውም አለ። ከዚያም ሳጥናኤልን አሁን እያየንህ እስኪ ፈጥረህ አሳየን አሉት እሱም አያፍርም እጁን ወደ እሳት ያስገባል ያን ጊዜ ያቃጥለዋል ዋይ ብሎ ይጮኸል አምላክ ግን በስውር ይፈውሰዋል። ነገር ግን አሁንም አምላክ ነኝ እንዳለ ቀጠለ። የተወሰኑ መላእክት ተከተሉት የተወሰኑት ግራ ተጋብተው ቀሩ የተወሰኑትም ከቅዱስ ገብርኤል በኩል ሆኑ። ቅዱስ ገብርኤል አጽናናቸው አምላካችንን እስግናገኝ ድረስ በያለንበት እንጽና አላቸው። ከዚህ እንደምንረዳው እምነት የተጀመረው በዚህ ወቅት ነው። እምነት በቅዱስ ገብርኤል ክህደት በሳጥናኤል በኩል መጣ ማለት ነው። በመላእክት ዘንድ እምነት እንዲህ ነበር በተፈጠሩበት ዕለት የተጀመረው። እምነት ወደ ሰው ልጅ እንዴት መጣ ስንል ብዙዎች የሚጠቅሱት የፍርሐት መኖርን ነው። ሰው ሲፈራ የሚረዳውን መምረጥና ማምለክ ግዴታው ነው። ነገር ግን ሊረዳው የማይችለውን ማምለኩ ስህተት ነው። ሰዎች በፀሐይ በጨረቃ ያመልኩ እንደነበር ግልጽ ነው። ዕለታት ሁሉ እንደተሰየሙላቸው የምናውቀውእውነት ነው። ሰኞን moon day ዛሬ monday እሁድን sunday ብለውታል። ስለዚህ እነዚህ ፍጥረታት እንደ አምላክ ተቆጥረው ተመልከዋል ማለት ነው። ግን እነዚህ ፍጥረታት እንድናመልካቸው አስገድደውናልን? አላስገደዱንም። እነዚህ ፍጥረታት ግን አምላክ መሆን ይቻላቸዋልን? እስኪ የአምላክን መገለጫዎች እንመልከት።
ü  አስገኝ የሌለው፣
ü  ማንም ማን ሊተካከለው የማይችል፣
ü  ዓለምን ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣ፣
ü  ሁሉን የሚመግብ፣
ü  የሚያሸንፈው የሌለ፣
ü  እርሱንየ ሚገድበው የሌለ፣
ü  ከእርሱ የሚበልጥ የሌለበት፣
ü  ሰማይን የዘረጋ ምድርን በውኃ ላይ ያጸና፣
ü  ጊዜ የማይለውጠው ዘመን የማይሽረው፣
ü  ዓለምን አሳልፎ የሚኖር ዘላለማዊ፣
ü  የሚመጣውንየ ሚያውቅ፣
ü  ሁሉን በፈቃዱ የሚያደርግ፣
ü  ድካም የሌለበት፣
ü  እንቅልፍ የማያሸንፈው፣
ü  አማክሩኝ የማይል፣
ü  ሌላ አጋዥ የማይሻ፣
ü  ዘመናትን በዘመናት ጊዜያትን በጊዜያት የሚተካ፣
ü  ሁሉን የሚገዛ፣
ü  ሁሉን የሚያስተደድር፣
ü  በሥራው የማይፀፀት፣
ü  የማይዳሰስ፣ የማይጨበጥ ረቂቅ
ü  በሁሉ ቦታ ያለ /ምሉዕ በኩለሄ የሆነ/፣
ü  ከእርሱ ፈቃድ ውጭ አንድ ነገር እንኳ የማይደረግ፣
ü  እውነተኛ ፈራጅ፣
ü  ውሸት የሌለበት፣
ü  ንፁሕ ኃጢአት የማይስማማው፣
ü  በማንም የማይመራ፣
ü  ሁሉ በእርሱ የሆነ፣
ü  ተመርምሮ ሊደረስበት የማይችል፣
ü  ከአእምሮ በላይ የሆነ ነው፣
ü  የማይደረስበት ምጡቅ የማይጨበጥ ረቂቅ::
አምላክ የምንለው ቢያንስ እነዚህን ነገሮች ማሟላት ይኖርበታል፡፡ እነዚህን የማያሟላ አምላክ ግን ፍጡር እንጅ ፈጣሪ ሊሆን እንዴት ይችላል?


ሰው ያለሃይማኖት መኖር ይችላልን የሚለውን እና የክርስትና እምነት ምን እንደሚመስል በአጭሩ በሚቀጥለው ክፍል እንመለከታለን። ይቀጥላል...

ትምህርተ ሃይማኖት (ክፍል 3)


© በመልካሙ በየነ
መጋቢት 12/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

በክፍል 2 የእምነትን ስድስት መገለጫዎች ተመልክተናል በዚህ ክፍል ደግሞ የሃይማኖት መሠረቶችን በዝርዝር እናያለን መልካም ንባብ!
ለሃይማኖት መኖር የተለያዩ መሠረቶች አሉ፡፡ አንዳንዶች ለእምነታቸው መሠረት የሚያደርጉት የተለያየ ነገር አላቸው፡፡ ፍርሐታቸውን፣ በራስ አለመተማመናቸውን፣ ድንጋጤያቸውን፣ መጨነቃቸውን ወዘተ ለእምነታቸው መሠረት ያደርጋሉ፡፡ እነርሱ እንደሚያስቡት የፍርሐታቸው፣ የድንጋጤያቸው፣ የጭንቀታቸው፣ በራስ ያለመተማመናቸው ምንጭ ከእነርሱ በላይ የሆነ ነገር ስላለ ነው፡፡ ስለዚህ በዚያ ከእነርሱ በላይ በሆነው ነገር ማመን እንዳለባቸው ይረዳሉ፡፡ እምነታቸው በዚህ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ነገር ግን ለእምነታችን መሠረት ልናደርገው የሚገባው ነገር ይህ አይደለም ምክንያቱም እምነትን ስናወራ የግድ እምነት እንዲኖረን ሊያደርግ የሚችለውን ነገር ነውና መሠረት ማድረግ ያለብን፡፡ ስለዚህ ለእምነታችን መሠረቱ የፈጣሪ መኖር እና ሥልጣን ያላቸው ነገሮች መኖራቸው እንደሆነ በማኅበረ ቅዱሳን የተዘጋጀው ትምህርተ ሃይማኖት መግቢያ በሚል የታተመው የግቢ ጉባዔ ማስተማሪያ መጽሐፍ ያስረዳናል፡፡
1.  የፈጣሪ መኖር፡- ያለፈጣሪ ስለሃይማኖት ማውራት አይቻልም፡፡ ማንኛውም ሃይማኖት ሃይማኖት ለመባል የግድ ፈጣሪ እንዳለ ማመንን ይጠይቃል፡፡ ፈጣሪ የሌለበት ወይም ፈጣሪ እንዳለ የማይታመንበት እምነት የለም፡፡ ይህን ፈጣሪ አለማዎቅ ግን ፈጣሪ የለም እንድንል አያደርገንም፡፡ ነቢዩ ዳዊት መዝ 13(14)÷1 “ሰነፍ በልቡ አምላክ የለም ይላል” በማለት ይገልጻል፡፡ ፈጣሪን ካለማዎቅ የተነሣ አምላክ የለም ብሎ መናገር ሰነፍነት ነው፡፡ አምላክ የለም ብሎ የሚያምን ሰው ቢኖር እርሱ ራሱ እንዴት እንደመጣ፣ እንዴት እንደተፈጠረ፣ እንዴት እንደሚኖር፣ ለምን እንደሚኖር፣ የመኖርና የመሞት ጥቅምና ጉዳት ወዘተ የማይረዳ ነው፡፡ አንዳንዶች ገነት፣ ሲዖል፣ መንግሥተ ሰማያት፣ ገሐነመ እሳት ወዘተ የሉም ስለዚህ አሁን ከመሞታችን በፊት እንብላ እንጠጣ እንደሰት እንደፈለግን እንሁን ብለው ያምናሉ፡፡ ነገር ግን እዚህ ላይም መመለስ የሚገባቸው ጥያቄ አለ፡፡ መብላት ካለመብላት፣ መደሰት ካለመደሰት፣ መጠጣት ካለመጠጣት፣ አለመሞት ከመሞት ለመሻሉ ምን ማረጋገጫ አለን፡፡ በሕይወት ከመኖር ይልቅ በመቃብር አፈር ሆኖ መኖር የተሻለ ቢሆንስ ምን ማረጋገጫ አለ፡፡ ከሞት በኋላስ መደሰት መብላት መጠጣት እንደፈለገ መሆን መቻል አለመቻሉን በምን እርግጠኞች መሆን ቻሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው ሞትን እንደሚፈሩት ነው፡፡ አንድ ሰው ፈጣሪ የለም ብሎ ካመነ የእርሱን ሰው መሆን ወይም ፍጡርነቱን አልተረዳም ማለት ነው፡፡ በመሆኑም እምነቱ በፈጣሪ ላይ አልተመሰረተም ማለት ነው፡፡ ነገር ግን የፈጣሪን መኖር የተረዳ ሰው የእርሱን ፍጡርነት ስለሚረዳ ፈጣሪውን ለማስደሰት ለፈጣሪ ሊደረግ የሚገባውን ሁሉ ያደርጋል መልካሙን ነገር መርጦ ክፉውን ነገር ሁሉ ያስወግዳል፡፡ ፍጡራን እንኳ የፈጣሪን መኖር ባያምኑ ፈጣሪ ግን ህልው ሆኖ ይኖራል፡፡ በመሆኑም ለእምነታችን መሠረት ሀልዎተ ፈጣሪ ወይም የፈጣሪ መኖር ነው፡፡
2.  ሥልጣን ያላቸው ነገሮች መኖር፡- እውነትን እንድንመሰክር እውነትን እንድንናገር በማስገደድ እንድናምን የሚደርጉን ሥልጣን ያላቸው ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህም የቤተ ክርስቲያናችን ትውፊትና ቅዱስ መጽሐፍ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ወደ እውነት የመምራት ሥልጣን አላቸው፡፡ በመሆኑም እውነትን ይዘን የፈጣሪን መኖር ተረድተን እምነታችንን እናጠነክራለን ማለት ነው፡፡
1.1 የቤተ ክርስቲን ትውፊት፡- ሰው የቤተክርስቲያንን ሥልጣን ከአወቀና እውነቷን ከተረዳ ሃይማኖቱን ማወጅ ይችላል፡፡ ትውፊትን ካልተቀበልን መጽሐፍ ቅዱስንም መቀበል አንችልም፡፡ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ከአንዱ ወደ አንዱ የመጣው በትውፊት ነው፡፡ አዳም ከገነት ከተባረረ በኋላ የወለዳቸው ልጆች እግዚአብሔርን ያመልኩ የነበረው መጽፍ ቅዱስ አንብበው አልነበረም፡፡ ከእነርሱም በኋላ የተነሡት እግዚአብሔርን ያመለኩት መሥዋእት የሰውት በትውፊት ባገኙት ትምህርት እንጅ መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎላቸው መምህር ሰብኮላቸው አልነበረም፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ እኛ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተጻፉ ነገር ግን በትውፊት አንዱ ለአንዱ እያቀበለው የመጣውን ትምህርት ሁሉ የምንቀበለው፡፡ ጌታችን ደቀመዛሙርቱን “ ወደዓለም ሂዱ፡- ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” አላቸው፡፡ በዚያ ሰዓት ወንጌል በመጽሐፍ መልኩ አልታተመም ነበር ነገር ግን እኔ በቃል ያስተማርኳችሁን ሂዱና አስተምሩ ሲላቸው ነው፡፡ ስለዚህ በቃል የወረስነው ትውፊት እውነትን እንድናውቅ የሚረዳ እና ለመጻሕፍትም መጻፍ መሠረት ነውና ለእምነታችን መሠረት ነው፡፡ ዛሬ ትውፊትን ከመምህራን፣ ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከአባቶቻችን እናገኛለን ይህ ትውፊት አንዱ ለአንዱ እያወረሰው የሚቀጥል እውነት ነው፡፡

1.2 ቅዱስ መጽሐፍ፡- እውነትን የሚናገር፣ ሥልጣን ያለው፣ በቅዱሳን አባቶች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው የተጻፈ ልዩ መጽሐፍ ነው፡፡ ይህንን የታላቅነት ሥልጣን የሰጠው ራሱ ጌታችን ነው፡፡ በዮሐ5÷47 “መጻሕፍትን ካላመናችሁ ግን ቃሌን እንዴት ታምናላችሁ” ብሎ አይሁድን ገስጿል፡፡ በሌላም ዘንድ እንዲሁ ስለአልዓዛርና ነዌ ጌታ ሲያስተምር “ሙሴንና ነቢያትን የማይሰሙ ከሆነ ከሙታን አንዱ እንኳ ቢነሣ አያምኑም” ብሏል፡፡ ይህን ያለው ሙሴና ነቢያቱ እስከዚያ ድረስ በሕይወት ኖረው አይደለም በመጽሐፎቻቸው ካላመኑ ለማለት ነው እንጅ፡፡ “ከሙታን አንዱ እንኳ ቢነሣ አያምኑም” ማለቱ ደግሞ ለእምነታችን መሠረቱ መጽሐፍ እንጅ ተአምር እና ምልክት እንዳልሆነ ለማስተማር ነው፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ለእምነታችን መሠረት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የያዘውን ሁሉ እውነት እንደሆነ እንቀበለዋን እናምነዋለን፡፡ 
ሃይማኖት እንዴት መቼ ተጀመረ? ለማን ያስፈልጋል? የሚሉትን የሃይማኖትና
የፍጥረታትን ግንኙነት በቀጣይ ክፍል እንመለከታለን፡፡ ይቀጥላል…

ትምህርተ ሃይማኖት (ክፍል 2)


© በመልካሙ በየነ
መጋቢት 10/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ክፍል አንድ ስለ እምነት ትርጉም እና እምነትን በሁለት ከፍለን አይተናል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ ሃይማኖትን በስድት ነጥቦች እንመለከታለን መልካም ንባብ!
1.  ሃይማኖት የሚቀበሉት ነው፡- እምነትን በመመርመር ልናውቀው አንችልም፡፡ አንዳንድ ሰዎች በራሳቸው መንገድ ሄደው በዓይናቸው አይተው፣ በጆሯቸው ሰምተው፣ በእጃቸው ዳስሰው ማመን ይፈልጋሉ፡፡ በእውነት እንዲህ የሚሆን እና የሚረጋገጥ ነገር እምነት ነው ብሎ ለመቀበል አይከብድምን? ምናልባት እንደአብርሃም በተፈጥሮ እውቀታችን አምላክን ወደማወቅ ልንደርስ እንችላለን ነገር ግን ወደዚህ እውነት ለመድረስ በራሱ እምነት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ እምነትን ካላየን ካልሰማን ካልዳሰስን ሳንል ዝም ብለን የምንቀበለው ነው፡፡ ማወቅ የሚመጣውም ከአመንን በኋላ ነው፡፡ ሳይንስና እምነት ልዩነታቸው እዚህ ላይ ነው፡፡ ሳይንስ ያወቀውን የተረዳውን ያረጋገጠውን ነገር ብቻ ያምናል፡፡ እምነት ደግሞ ከአመነ በኋላ ያውቃል፣ ከአመነ በኋላ ያረጋግጣል፣ ከአመነ በኋላ ይረዳል ማለት ነው፡፡ ዮሐ6÷69 ላይ “እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ እንደሆንህ አምነናል አውቀናልም” ይላል ቅዱስ ጴጥሮስ ሲመልስ፡፡ አምነናል ካለ በኋላ ነው አውቀናልም ያለው እንጅ አውቀናል ካለ በኋላ አምነናልም አላለም፡፡ እምነትን ዝም ብለን የምንቀበለው ከስሜት በላይ  እና ከአእምሮ (ከእውቀት) በላይ ስለሆነ ነው፡፡ ስሜትን በሕዋሳት ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ቀይ፣ ጥቁር፣ ነጭ፣ ቢጫ የሚለውን በማየት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ሽታንም በማሽተት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ለስላሳ፣ ሻካራ የሚለውን ነገርም በመዳሰስ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ጣእምንም በመቅመስ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ እምነትን ግን በእነዚህ በተዘረዘሩት ሕዋሳት ማረጋገጥ አንችልም ምክንያቱም ከእነዚህ ስሜቶች ሁሉ በላይ ነውና፡፡ ለዚህም ማስረጃችን መስማት የማይችለው፣ ማየት የማይችለው፣ መቅመስ የማይችለው፣ መዳሰስ የማይችለው፣ መናገር የማይችለው ሁሉ እምነት አለው፡፡ ሁለተኛው ነገር እምነት ከእውቀት ወይም ከአእምሮ በላይ በመሆኑ ዝም ብለን እንቀበለዋለን፡፡ ሮሜ 12÷3 ላይ ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስቀመጠው አእምሮ ልክ እና ገደብ አለው፡፡ ማሰብ የምንችለው፣ ማወቅ የምንችለው ነገር ሁሉ የተሰፈረ፣ የተለካ እና የተገደበ ነው፡፡ ከዚህ ልክ እና ገደብ ማለፍ አንችልም እንለፍ ብንል እንኳ በጭንቀት ራሳችንን ከማሳበድ በቀር ምንም ማምጣ አንችልም፡፡ ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ ምን ይመስል እንደነበር ወደኋላ ዞረን ብናስብ ከእውቀታችን በላይ ነው፡፡ ከሞት በኋላ አፈር የሆነው የበሰበሰው ሥጋ ከነፍስ ጋር ይዋሐዳል ብሎ ማመን ከአእምሮ በላይ ነው፡፡ በጥምቀት ጊዜ ካሕኑ “አሐዱ አብ ቅዱስ፣ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ” ብሎ ውሐውን  ሲባርከው በዕለተ አርብ ከጌታ ጎን የፈሰሰውን ውኃ ይሆናል ብሎ ማመን ከአእምሮ በላይ ነው፡፡ ስለዚህ እምነትን ዝም ብለን እንቀበለዋለን ማለት ነው፡፡
2.  ሃይማኖት በተስፋ የሚረዱት ነው፡- ዕብ 11÷1 ላይ "እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚስረግጥ የማናየውን ነገር የሚያስረዳ ነው” ይላል ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ ተስፋ የሌለው ሰው አያምንም ያላመነም ሰው ተስፋ የለውም፡፡ እምነት ውስጥ ተስፋ አለ፡፡ ወደፊት ብዙ ተስፋ አለን፡፡ ከሞት በኋላ ተነሥተን ዘላለማዊ መንግሥትን እንወርሳለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ የጸሎታችንን መልስ የምንጠብቀው በተስፋ ነው፡፡ ሥጋዊ እና ሰማያዊ ሕይወታችንን አምላክ ያስተካክልልናል ብለን የምንረዳው በተስፋ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን መግቦት ጠብቆት ጸጋና ረድኤቱን የምንጠብቀው በተስፋ ነው፡፡ ተስፋ የሌለው ሰው በአጠቃላይ እምነት የለውም ማለት ይቻላል፡፡ ለማየት የምንጓጓውን ነገር ጊዜውን ጠብቆ ያሳየናል ብለን የምንጠብቀው በተስፋ ነው፡፡
3.  ሃይማኖት በፍቅር የሚገለጥ ነው፡- ይህ ማለት ለሌሎች ደግ ማድረግ መራራት ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከድንግል ማርያም ተወልዶ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ እኛን ያዳነን ስለወደደን ነው፡፡ ዓለምን እንዲሁ የወደደ አምላክ እርስ በርሳችሁም ተዋደዱ ብሎናል፡፡ በዚህ መዋደዳችን ሃይማኖታችንን እንገልጣለን ማለት ነው፡፡ ያለው ለሌለው የሚሰጥበት፣ የራበውን የሚያበላበት፣ የተጠማውን የሚያጠጣበት፣ የታረዘውን የሚያለብስበት ነው ፍቅር ማለት፡፡ ሌላውን እንደራስ አስቦ ለራስ የሚያስፈልገውን ነገር ለሌሎችም ማድረግ ነው ፍቅር፡፡ ስለዚህ ሃይማኖታችን እንዲህ በፍቅር መልካም በማድረግ ለሌሎች በመራራት የምንገልጠው ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ፍቅርን እንዲህ ይገልጠዋል “በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሿሿ ጸናጽል ሆኛለሁ፡፡ ትንቢትም ቢኖረኝ  ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትንም ሁሉ ባውቅ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ፡፡ ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም፡፡ ፍቅር ይታገሣል ቸርነትንም ያደርጋል ፍቅር አይቀናም ፍቅር አይመካም ፍቅር አይታበይም የማይገባውን አያደርግም የራሱንም አይፈልግም  አይበሳጭም በደልንም አይቆጥርም ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጅ ስለ አመፃ ደስ አይለውም ሁሉን ይታገሣል ሁሉን ያምናል ሁሉን ተስፋ ያደርጋል በሁሉ ይጸናል፡፡ ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም… እንዲሁም ከሆነ እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው” /1ኛ ቆሮ13 ÷ 1-13/ ስለዚህ ትልቁን ጸጋ ፍቅርን ለሃይማኖት መግለጫ ልንጠቀምበት ይገባናል፡፡ ምክንያም ሃይማኖት በፍቅር የሚገለጥ ነውና፡፡ ይህ ፍቅር መታመንን የምናሳይበት ምግባር ነው፡፡ መታመናችንን ግን ለራስ ሳይሆን ለሌሎች የምናሳይበት መሣሪያ ነው ፍቅር፡፡
4.  ሃይማት በሥራ የሚተረጎም ነው፡- እንደ ፍቅር ሁሉ ይህም መታመንን የምናረጋግጥበት ነው፡፡ መታመንን ከራሳችን የምንጀምርበት ነው፡፡ ለምሳሌ በጥምቀት የሥላሴን ልጅነት እንደሚገኝ ያመነ ሰው መጠመቅ አለበት፡፡ ሥጋና ደሙን በመቀበል የዘላለም ሕይወት እንደሚወርስ ያመነ ሰው መቁረብ አለበት፡፡ ልዑል መለኮት ራሱን ዝቅ አድርጎ ደካማ ሥጋን እንደበሰ፣ የሐዋርያትን እግር ዝቅ ብሎ እንዳጠበ ያመነ የተረዳ ሰው የትሕትና ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅበታል ማለት ነው ምክንያቱም ሃይማኖት በሥራ የሚተረጎም ነውና፡፡
5.  ሃይማኖት የማናየውን የምናይበት ረቂቅ መሣሪያ ነው፡- ሃይማኖት የማናየውን የምንረዳበት ነው፡፡ ከላይ ያየናቸውን ነገሮች በአግባቡ ከጠበቅን ለአንድ ነገር ያበናል ማለት ነው፡፡ እርሱም ረቂቃንን አጉልተን ሩቆችን አቅርበን እናይበታለን ማለት ነው፡፡ በእምነት ውስጥ ረቂቅ የሆኑትን እግዚአብሔርን እና መላእክትን እንዲሁም ሩቅ የሆኑትን ገነትን መንግሥተ ሰማያትን እናይበታለን ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ከእምነቱ ጽናት የተነሣ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጥቆ አይቷል፡፡ 2ኛ ቆሮ 12 ÷2 ሄኖክንም ወደ ብሔረ ሕያዋን እንዲሄድ ያደረገው እምነቱ ነው፡፡ ዕብ 11÷5 ሠለስቱ ደቂቅ ከእሳት የዳኑት በእምነት ነው። ዳንኤል ከተራቡ አናብስት የዳነው በእምነት ነው። ሌሎችንም ምሳሌዎችን ማየት ይቻላል ለዚህ ትምህርት ግን ይበቃናል፡፡እምነት በስሜት ማረጋገጥ የማንችለውን አእምሮ የማይደርስበትን ነገር ሁሉ ሩቁን አቅርበን ረቂቁን አግዝፈን የምናይበት ረቂቅ መሣሪያ ነው፡፡
6.  እግዚአብሔርን ደስ የምናሠኝበት ነው፡- እግዚአብሔርን ደስ የምናሰኘው በምንድን ነው የሚለውን ነገር ማወቅ ይገባናል፡፡ በጭፈራ በዳንስ አናስደስተውም፡፡ በየመንገዱና በየፌርማታው “ኢየሱስ” እያሉ በመጮህም አናስደስተውም፡፡ እናቱን በመሳደብ ቅዱሳንን በመናቅም አናስደስተውም፡፡ በእምነታችንና በምንሠራቸው ሥራዎች ብቻ ነው ደስ የምናሰኘው፡፡ የመቶ አለቃውን እምነትና ምግባር የያዕቆብን እምነትና ምግባር መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አንችልም” ዕብ 11÷6 በማለት ይገልጻል፡፡ ስለዚህ አምላክን ለማስደሰት እምነት ሊኖረን ይገባል፡፡ የታመመ ልጁን እንዲፈውስለት ኢየሱስ ክርስቶስን የጠየቀው መቶ አለቃ እምነቱ ትልቅ ስለነበር ኢየሱስ ከታመመው ልጅህ ዘንድ ሄጄ ልፈውስልህ ሲለው እዚህ ሆነህ ቃል ተናገር ልጄ ባለበት ይፈወስልኛል ብሎ ማመኑ ጌታን አስደስቶታል፡፡ መቶ አለቃው ይህንን ማንም ሳያስተምረው እንዴት አወቀው? ያዕቆብስ ብኩርና እንደሚጠቅም ማን አስተማረውና ነው በምስር ወጥ ብኩርናን ከኤሳው የተቀበለ? ይህ እምነት ነው ለዚህም ነው አምላክን ያስደሰቱት፡፡ ስለዚህ እምነት አምላክን ደስ የምናሰኝበት ነው ማለት ነው፡፡

የሃይማኖት መሠረቶች ምን ምን እንደሆኑ በዝርዝር በሚቀጥለው ክፍል እንመለከታለን፡፡ ይቀጥላል….

ትምህርተ ሃይማኖት (ክፍል 1)


© በመልካሙ በየነ
መጋቢት 9/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ትምህርተ ሃይማትን ሊቃውንቱ በሁለት ከፍለው እንደሚያስተምሩትና እንሚያስረዱት እኛም እንዲሁ በሁለት ከፍለን እንመልከተው፡፡
1.  ዶግማ፡- ቃሉ የግሪክ ሲሆን ትርጉሙም እምነት ማለት ነው፡፡ ዶግማ ወይም እምነት አይጨመርበትም፣ አይቀነስለትም፣ አይሻሻልም፣ አይለወጥም፡፡ ከጊዜው ጋር ስላልሄደ፣ ስላልተስማማን፣ አስቸጋሪ ስለሆነ ወዘተ በሚል ማንኛውም ምክንያት መሻሻል መለወጥ መጨመር መቀነስ የለበትም፡፡ ከከበደን ትተን መውጣት እንጅ ምንም ምክንያት አናቀርብበትም፡፡ ሌሎች እምነቶች የሚያስቸግሩን ቢሆኑ የምንሰዋለት ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል በተዋሕዶ እምነት ውስጥ የእግዚአብሔርን ሕልውና እናምናለን፡፡ ሥላሴ አንድ ሲሆኑ ሦስት፣ ሦስት ሲሆኑ አንድ ብለን እናምናለን፡፡ አምላካችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ በተዋሕዶ ተወለደ ብለን እናምናለን፡፡ ያመነ የተጠመቀ ይድናል ያላመነ ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል ብለን ስለምናምን በተወለድን በ40 እና በ80 የልጅነት ጥምቀትን ተጠምቀናል፡፡ ጥምቀታችንም ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅጸነ ዮርዳኖስ እንደሆነ እናምናለን፡፡ ሥጋዬን ያልበላ ደሜንም ያልጠጣ የዘላለም ሕይወት የለውም የሚለውንም አምላካዊ ቃል አምነን ኅብሥቱ ተለውጦ ሥጋ መለኮት ወይኑም ተለውጦ ደመ መለኮት ነው ብለን በማመን እንቆርባለን ወይም ሥጋና ደሙን እንቀበላለን፡፡ በመጨረሻም የሙታንን መነሣት ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ሙታን ሁሉ እንደየሥራቸው ትንሣኤ ዘለክብር ወይም ትንሣኤ ዘለሐሳር ይነሣሉ ብለን እናምናለን፡፡ እንዲሁም የእመብርሃን ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያምን ዘላለማዊ ድንግልና እና አማላጅነት እንዲሁም የመላእክትን ተራዳኢነት የቅዱሳኑን ጸሎት እናምናለን፡፡ ይህንን እምነታችንን ማንም ሊያናውጠን አይችልም፡፡ በመሆኑም ዶግማ ማለት እንዲህ የእምነታችን መሠረት ነው፡፡ ማንም የማይለውጠው ማንም የማያሻሽለው ማንም የማይቀንሰው ማንም የማይጨምረው ማንም የማይከልሰው ነው፡፡
2.  ቀኖና፡- ቃሉ የግሪክ ሲሆን ትርጉሙ ሥርዓት ማለት ነው፡፡ 1ኛቆሮ 14÷40 “ነገር ግን ሁሉ በአግባብና በሥርዓት ይሁን” ይላል ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ ስለዚህ ለማንኛውም ሥራችን ሥርዓት ያስፈልገዋል ማለት ነው፡፡ በእምነታችን ለመጽናት እምነታችንን ጠብቀን ለመቆየት ሥርዓት ያስፈልገናል፡፡ ሁሉም የመሠለውን የሚያደርግበት መሆን የለበትም፡፡ ይህ ሥርዓት ግን ሊጨመርበት፣ ሊሻሻል፣ ሊቀነስ የሚችል ነው፡፡ ነገር ግን ሁኔታውን አይቶ ማሻሻል የሚችለው ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ጥምቀትን በ40 እና  በ80 ብለናል ነገር ግን ሕጻኑን ለሞት የሚያበቃ ነገር ካገኘው ከዚያም ቀድሞ በሞግዚት ገብቶ እንዲጠመቅ አዝዘዋል፡፡ ይህ እንግዲህ ቀኖና ስለሆነ ነው፡፡ አርብ ረቡዕን ከዓመት እስከ ዓመት እንጾማለን ነገር ግን በበዓለ ሃምሳ፣ ገናና ጥምቀት በሆኑባቸው ዕለታት እንዳንጾም ታዝዘናል በዚህም መሠረት ዐርብና ረቡዕ መሆናቸውን እያወቅን እንበላለን ይህ ቀኖና ነው፡፡ በቤተክርስቲያን የቅዳሴ ሥርዓት ላይ 5 ቀዳስያን ያስፈልጋሉ ነገር ግን ከባድ በሆነ ችግር አምስት ካልተገኘ ከአምስት በታች ሁነው ቀድሰው ማቁረብ ይችላሉ ይህ ቀኖና ነው፡፡ ሰው የታወቀ ደዌ ቢኖርበት በአጽዋማት ቀን እንዲጾም አይገደድም በምትኩ ሲሻለው ግን ይጾማል ይህ ቀኖና ነው፡፡ ነገር ግን እዚህም ቢሆን እኛ እንደፈለግን የምናሻሽለው የምንለውጠው የምንጨምረው የምንቀንሰው አይደለም ምክንያቱም መሠረታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና፡፡ 1ኛ ቆሮ 3÷11 “ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና ርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” 
ዶግማ እና ቀኖና እንዲህ ናቸው፡፡ ቀኖና ድካማችንን አይቶ የምንችለውን ያህል ይሰጠናል ዶግማ ላይ ግን ከቻልን ቻልን ነው ካልቻልን ግን ትተን ከመውጣት በቀር ሌላ ማሻሻያ መጠየቅ አንችልም፡፡ ትምህርተ ሃይማኖት እንዲህ ተከፍሎ ይታያል፡፡ የእኛ ትምህርት ትኩረት የሚያደርገው ወደ ዶግማው ነው፡፡ ሥርዓትን ወይም ቀኖናን በተመለከተ የሥርዓት መጻሕፍት ማንበብ መመልከት ይገባናል፡፡ አሁን ግን ወደ እምነት ወይም ዶግማ እንለፍ፡፡
እምነት (ሃይማኖት) ማለት ምን ማለት ነው? እምነት የሚለው ቃል “አምነ” አመነ ካለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ሃይማኖት (እምነት) የሚል ሥም ይወጣል ትርጉሙም ማመን መታመን ማለት ነው፡፡ ማመን ስንል በዓይን አይተን፣ በጆሮ ሰምተን፣ በልብ አስበን፣ በስሜት ሕዋሳት መርምረን መድረስ የማንችላቸውን ነገሮች በርኅቀት (ሩቅ ያሉትን)  አልያም በርቀት (ረቂቅ የሆኑ ነገሮችን) እንዳሉ እንደሚደረጉልን እንደሚሆኑልን በመረዳት መቀበል ነው፡፡ መታመን ስንል ደግሞ እነዚህ ያመናቸው ነገሮች እንዲሆኑልን የምንመልሰው ተግባራዊ መልስ ነው፡፡ ለምሳሌ ሰው በጥምቀት ከሥላሴ ልጅነት ያገኛል ብለን ማመን አለ ይህን እምነታችንን ግን በመጠመቅ ተግባራዊ ምላሽ እንሰጣለን ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው ሥጋና ደሙን በመቀበል የዘላለም ሕይወትን እንደሚወርስ ያምናል ይህንን እምነቱን ግን በመቁረብ ተግባራዊ ምላሽ በመስጠት መታመኑን ያረጋግጣል፡፡ እምነት የሚረጋገጠው በመታመን እንጅ በቤተሙከራ ውስጥ አይደለም፡፡ የገነትን መኖር፣ የሲዖልንም መኖር እናምናለን ከሞት በኋላ ሕይወት እንዳለም እናምናለን፡፡ ይህንን ግን በመታመን ማሳየት ካልሆነ በቀር በምንም ዓይነት ዘዴ ልናረጋግጠው አንችልም፡፡ ለምሳሌ ነፋስ አይጨበጥም አይዳሰስም አይታይም ነገር ግን አሁን ነፋስ ነፈሰ አሁን ነፋስ ጠፋ እንላለን፡፡ ነፋስ መሆኑን በምን እርግጠኞች ሆንን? እርግጠኞች እንድንሆን ያደረገን ሥራውን ተረድተን ነው፡፡እምነትንም እንደዚሁ ነው እርግጠኞች ለመሆን በመታመን ማረጋገጥ እና ሥራውን መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በመነሣት መጻሕፍት እምነትን በስድስት ነጥቦች ይገልጡታል፡፡
1.  ሃይማኖት የሚቀበሉት ነው፡፡
2.  ሃይማኖት በተስፋ የሚረዱት ነው፡፡
3.  ሃይማኖት በፍቅር የሚገለጥ ነው፡፡
4.  ሃይማት በሥራ የሚተረጎም ነው፡፡
5.  ሃይማኖት የማናየውን የምናይበት ረቂቅ መሣሪያ ነው፡፡
6.  እግዚአብሔርን ደስ የምናሠኝበት ነው፡፡

እነዚህን ስድስት ነጥቦች እያንዳንዳቸውን በሚቀጥለው ክፍል እንመለከታለን፡፡ ይቀጥላል…

Tuesday, March 15, 2016

ለምን በምንፍቅና ውስጥ ተደበቁ?



© በመልካሙ በየነ
መጋቢት 6/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

እምነት ውስጥ ማመን እና መታመን የሚሉ ዐበይት ነገሮች አሉበት፡፡ ማመን ማለት ያላየነውን ያልጨበጥነውን ያልዳሰስነውን ነገር እንዳየነው እንደጨበጥነው እንደዳሰስነው አድርገን መቀበል ነው፡፡ ለምሳሌ፡- እግዚአብሔር አምላክ ነው ስንል ሳናየው፣ ሳንጨብጠው ሳንዳስሰው እንዳየነው እንደጨበጥነው እንደዳሰስነው አድርገን ተቀብለን ነው፡፡ ሌሎችንም እንዲሁ ሳናይ ሳንዳስስ ሳንጨብጥ ነው አሉ ብለን የተቀበልናቸው፡፡ ገነት መንግሥተ ሰማያት ሲዖል ገሐነመ እሳት መላእክት አሉ ስንል በተመሳሳይ ሳናይ ሳንዳስስ ሳንጨብጥ ነው፡፡ መታመን ስንል ደግሞ ለማመናችን ተግባራዊ ምላሽ የምንሰጥበት ነው፡፡ እግዚአብሔር አለ ስንል ህልውናውን የምናምንበት ትእዛዙን በመጠበቅ ነው፡፡ አድርጉ ያለንን በማድረግ አታድርጉ ያለንንም ባለማድረግ ተግባራዊ ምላሽ ከሰጠን እሱ መታመናችንን ገልጸናል ማለት ነው፡፡ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት፣ ምጽዋት እነዚህ ሁሉ የመታመን ተግባራት ናቸው፡፡ ምግባራችን ወይም መታመናችን ግን ከሰው ሰው ይለያያል፡፡ የበረታ አለ የደከመም አለ፡፡ ድካምህ ግን ከደካማነትህ ባለፈ ወደ እምነት ሕጸጽ ሊወስድህ አይገባህም፡፡ ብዙዎች ወደ ምንፍቅና የሚሄዱበት ነገር ከዚህ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ በመሆኑም ብዙዎች ለምን በምንፍቅና ውስጥ ተደበቁ? የሚለውን ትልቅ ጥያቄ መመለስ ተገቢ በመሆኑ ወደእሱ እናምራ መልካም ንባብ!
ብዙዎች ለምን በምንፍቅና ውስጥ ተደበቁ? ለሚለው ዐቢይ ጥያቄ በርካታ መልሶችን መስጠት እንችላለን፡፡ ዋናዋና የሚባሉት ግን የሚከተሉት ናቸው፡-
1.  መታመን አለመቻል
2.  ገንዘብን መውደድ
3.  ዓለምን መናፈቅ
4.  አቋራጭ ጽድቅን መሻት ናቸው፡፡ እነዚህን አራት ነጥቦች በዝርዝር እንመልከታቸው፡፡
v  መታመን አለመቻል፡- በእምነታችን ውስጥ መታመን መንፈሳዊ ግዴታችን ነው፡፡ በተዋሕዶ እምነት ውስጥ አባል የሆነ ሰው ሁሉም ሰው ሊጾማቸው የሚገባቸውን ጾሞች እስከታዘዘው ሰዓት ድረስ መጾም የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ ለምሳሌ አርብና ረቡዕን እስከ ዘጠኝ ሰዓት ጹሙ ይላል፡፡ ዐቢይ ጾምን ደግሞ የመጀመሪያውን ሳምንት እስከ አሥራ ሁለት ሰዓት ከሕማማት አስቀድሞ ያለውን እስከ አሥራ አንድ ሰዓት የሕማማትን ሳምንት ደግሞ እስከ አንድ ሰዓት እንድንጾም ታዝዘናል ይህን መፈጸም የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ በዚሁ ልክ ደግሞ ስግደትም ምጽዋትም ጸሎትም ይጨመርበታል፡፡ ጠዋት ተነሥቶ መብላት ሆዱ አምላኩ የሆነበት ሰው ግን ይህን ማድረግ ይከብደዋል፡፡ ነገር ግን ካልቻልን ማለትም የታወቀ ደዌ ካለብን አምላክ አያስገድደንም፡፡ እኛ የምንጾመው እኮ በዚያች ጾማችን ገነት መንግሥተ ሰማያትን እንወርሳለን ብለን አይደለም መታመናችንን ለማሳየት መገዛታችንን ለማረጋገጥ ነው እንጅ፡፡  ስለዚህ የቻልነውን ነገር ማድረግ ይጠበቅብናል ብዙዎች ግን ጾም ጸሎት ስግደት ምጽዋት ወደሚቀልበት እንዲያውም ጭራሽ ስሙም ወደማይነሣበት ምንፍቅና ራሳቸውን ይወስዳሉ፡፡ መጾም አለመቻል፣ መስገድ አለመቻል፣ መጸለይ አለመቻል በአጠቃላይ መታመን አለመቻል እምነትህን እንድትለውጥ ሊያደርግህ አይገባም፡፡ ራስህን ከኅሊና ወቀሳ ነጻ ለማድረግ ብለህ እምነትህን ለመለወጥ አትሻ፡፡ ከዚያስ የቻልከውን ያህል እየሠራህ “አንተ ተአምር ድካሞ ለሰብእ” የሰውን ድካም አንተ ታውቃለህ እያልህ ብትጸልይ ይሻልሃል፡፡ አምላከ ቅዱሳን የእኛን ድካም ያውቃል የእኛን ድካም ይረዳል ስለሆነም እርሱን አላመልክህም ብሎ ከመኮብለል ይልቅ ድካሜን አይተህ ማረኝ ይቅር በለኝ ብንለው የተሻለ ነው፡፡ በብዛት ለሰዎች የምንፍቅና መሠረታቸው ጾም ነው፡፡ ታዲያ ጾሞ ጹሙ ያለንን አምላክ በመጾም ካልመሰልነው መታመናችን እርሱን ማምለካችን እርሱን መውደዳችን በምን ይታወቃል? በሕክምና ጊዜ ለሥጋዊ ፈውስ ብለን ይህን ይህን አትብሉ ተብለን ስንከለከል እናደርገው የለም እንዴ? ታዲያ ለዘላለማዊ የነፍስ ድኅነት ጹሙ ስንባል ለምን እንሰቀቃለን? እውነት ነው የምላችሁ አንድ ቀን ሞክሩት አይደለም እስከዘጠኝ ሰዓት እስከ ምሽቱ ሦስት ሰዓት ድረስ እንኳ እንድትቆዩ አምላክ ብርታቱን ይሰጣችኋል፡፡  አምላክን አበርታኝ እንበለው እርሱ ያበረታናል፡፡ ነገር ግን ምንም ይሁን ምን ምንም ይፈጠር ምን መጾም ባለመቻላችን፣ መስገድ መጸለይ ባለመቻላችን እምነታችንን ልንለውጥ አይገባንም፡፡ ከዚያስ እምነታችንን ይዘን አለመጾም አለመጸለይ አለመስገድ ይሻላል፡፡ ምክንያቱም አንድ ቀን አምላክ ብርታቱን ጽናቱን ሰጥቶ ለንሥሐ ያበቃናልና ፡፡
v  ገንዘብን መውደድ፡- ከሦስቱ አርስተ ኃጣውእ መካከል አንዱ ፍቅረ ንዋይ ገንዘብን መውደድ ነው፡፡ ጌታ በወንጌል እንዳስተማረን ለሁለት ጌቶች መገዛት አይቻላችሁም ያለን ገንዘብን ነው፡፡ እንግዲህ ገንዘብ እንደ አንድ ጌታ ነው የተቆጠረው፡፡ ከውጭ እርዳታ እየለቃቀመ ገንዘብ በሚያከፋፍለው እምነት ውስጥ ብዙዎች ራሳቸውን ደብቀዋል፡፡ “”ገንዘቡን ላግኝ እንጅ እኔ ምን ቸገረኝ” በሚል የከሰረ አስተሳሰብ ብዙዎች ለገንዘብ ሲሉ ዕንቁ የሆነች ተዋሕዶ እምነታቸውን ትተው ኮብልለዋል፡፡ ገንዘብ ያው ገንዘብ ነው ስታገኝም ስታጣም እኩል የሚያስጨንቅ ነው፡፡ ሠርተህ መለወጥ ሠርተህ ማግኘት አልቻል ሲልህ እምነትህን ሸጠህ ገንዘብ ልታጠራቅም አይገባህም፡፡ ከገንዘብ በፊት የሚቀድመው እምነት ነው፡፡ ለድቃቂ ሳንቲም፣ ለእራፊ ጨርቅ ብለህ እምነትህን የምትለውጥ ከሆነ በዓለም ካሉ ከንቱዎች መካከል አንዱ አንተ ነህ፡፡
v  ዓለምን መናፈቅ፡- በተዋሕዶ እምነት ስትኖር ሁሉ ነገርህ ሰማያዊ ነው፡፡ አስተሳሰብህ ሰማያዊ፣ አነጋገርህ ሰማያዊ፣ አለባበስህ ሰማያዊ፣ አኗኗርህ ሰማያዊ፣ ዜማህ ሰማያዊ፣ ጸሎትህ ሰማያዊ ነው፡፡ ብዙዎች ግን ዳንኪራ ይናፍቃቸዋል፣ መዝፈን መጨፈር መብላት መጠጣት መስከር መወላገድን፣ ዝሙት መዳራትን ይሻሉ፡፡ ስለዚህ ይህን በነጻነት ወደምታገኝባቸው እምነትን ሽፋን ወዳደረጉ ተቋማት ለመጓዝ አትቸኩል፡፡ እነዚህ ሁሉ ጉዳታቸው እንጅ ጥቅማቸው አይመዝንም፡፡ መናፍቃኑ አዳራሽ ላይ ሴቶች ዕርቃናቸውን ስታይ ልብህ ሊደሰት ይችላል፣ አጠገብህ ቁጭ ብላ ደረቷን ገልጣ ጡቶቿን አፍጥጣ ስታሳይህ ልትማረክ ትችል ይሆናል፡፡ ይህን ለመመልከት በዚህ ለመደሰት በዚህ ለመርካት ምንፍቅናን መምረጡ ጅልነት ካልሆነ በቀር ምን ሊባል ይችላል? ይህ እኮ ዓለም ውስጥም አስፓልት ላይ ወጥተህ ስትንቀሳቀስ የምትመለከተው ከንቱነት ነው፡፡ እምነት ማለት እኮ ዘላለማዊ ነው ዓለም ደግሞ ታልፋለች ትጠፋለች ትለወጣለች፡፡ ስለዚህ ሽህ ጊዜ ዓለማዊ ሁን እንጅ እምነትህን ለውጠህ በመናፍቃን አዳራሽ ያለውን ርኩሰት አትሻ፡፡ እነርሱ አዳራሽ ውስጥ እንደገባህ አንድ ፍጹም ዓለማዊ የሆነች ሴት ትመደብልሃለች ወንጌልን የምታስተምርህም ከአንተ ጭን ላይ ቁጭ ብላ ነው፡፡ በፍቅር ልብህን በመስረቅና በማማለል እዛው ስለእሷ ፍቅር ስትል እንድትኖር ይፈልጋሉና የምትመደብልህ ሴት እንዲህ ያለች ናት፡፡ ታዲያ ይኼ ሰማያዊ ነውን? አይደለም፡፡ ስለዚህ ራስህን ከዚህ ዓለማዊ ርኩሰት ልትጠብቅ ያስፈልጋል፡፡ መዝሙር የሚሉትን ዳንኪራ እና ጭፈራ አትናፍቅ፡፡

v  አቋራጭ ጽድቅን መሻት፡- መናፍቃን በተወሰኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶች ላይ ተመሥርተው በአቋራጭ መጽደቅን ይሻሉ፡፡ “ኢየሱስ ያድናል፣ ኢየሱስ ጌታ ነው፣ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ” በማለት ገነት እንገባለን ብለው ያስባሉ፡፡ ተዋሕዶን ሲተቹ ምን ይላሉ መሰላችሁ “አንድ መሪጌታ ነበር… አንድ ቄስ ነበር…. አንድ ዲያቆን ነበር…. አንድ መነኩሴ ነበር…. ነገር ግን ስለመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ስጠይቀው ምእራፍና ቁጥር ማዎቅ አልቻለም፡፡ እኛ ግን ምእራፍና ቁጥር እንነግራቸዋለን እነርሱ አያነቡም እኛ ግን ጌታ ይባረክ ምሥጢሩን ገልጾልን ጸጋውን አብዝቶልን ሁሉን እናውቀዋለን” ይላሉ፡፡ በእውነት ማነው ጸጋ የለሹ? አለማዎቅ ጥፋት አይደለም አለማዎቅን አለማዎቅ ግን በጣም ትልቅ ጥፋት ነው፡፡ መናፍቃኑ ትልቁ ችግራቸው አለማወቃቸውን አለማወቃቸው ነው፡፡ ለመዳን አቋራጭ መንገድ የተጠቀመ ማነው? መናፍቃኑ አይደሉም እንዴ? በእውነት የእነርሱን ያህል ጥቅስ መጥቀስ ያቃተው የትኛው መሪጌታ፣ የትኛው ቄስ፣ የትኛው ዲያቆን፣ የትኛው መነኩሴ ነው? እንዴ 81 መጽሐፍ ቅዱስ በዝቶባቸው ከ66 ውጭ ፍንክች አንልም ያሉ እነማን ናቸው? አዋልድ መጻሕፍትን ገድላትን ድርሳናትን ተአምራት አንቀበለም ያሉት እነማን ናቸው? እነዚህ መጻሕፍትን ለመሸምደድ ስላልቻሉ ይሆንን? የእኛ ሊቃውንትማ አንድ ጥቅስ ሮሜ 8÷34 ን ብቻ እንደ ቴፕ የሚያጠነጥኑ አይደሉም እኮ፡፡ ከመናፍቃኑ 66 መጽሐፍ ቅዱስ ባለፈ 81 መጽሐፍ ቅዱስን ምንባቡን ከነትርጓሜው፤ ቅዳሴውን፣ ድጓውን፣ ጾመ ድጓውን፣ ሰዓታቱን ዜማውን ከነምልክቱ፣ ድርሳናትን እና ገድላትን ተአምራትን ሁሉ በቃላቸው የሚያስተምሩ ናቸው፡፡ ወዴት ጠጋ ጠጋ ነው፡፡ አቋራጭ ጽድቅን የሚሻ መናፍቅ በ66 መጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ብቻ ይከራከራል፡፡ መላእክትን አንቀበልም፣ ድንግል ማርያምን አንቀበልም የሚሉ እነማን ናቸው? በአቋራጭ መዳን የሚፈልጉት አይደሉምን? ቅዱሳንን ስናከብር የማይወዱት እነርሱም ማክበር የማይሹት እኮ የእነርሱን ክብር የተሻሙባቸው ስለሚመስላቸው ነው፡፡ በጣም ክብር ፈላጊዎች ናቸው እነርሱ በጸሎታቸው እንፈውሳለን እናድናለን ይላሉ ቅዱሳኑ ግን ይህን ማድረግ አይችሉም በእነርሱ ቤት፡፡ ያሳዝናል ምን ጅልነት እና አለማስተዋል ነው? አብዛኞቹ አቋራጭ ድኅነት ፈላጊዎች ናቸው፡፡ ልጄ ካንሰር ታምማ ነበር፣ እናቴ የወገብ አጥንት መንሸራተት ነበረባት፣ አባቴ መራመድ አይችልም ነበር ወዘተ ብቻ የሌለ ልቦለዳዊ ገጸባሕርይ ይፈጥራሉ ከዚያሳ ከዚያማ ጸበል ብንወስዳቸው መዳን አልቻሉም ፣ ብናቆርባቸውም፣ መፈወስ አልቻሉም፣ እምነት ብንቀባቸውም አልተሻላቸውም ከዚያም ወደዚህ አመጣናቸውና ፓስተሩ ጸሎት ሲያደርጉላቸው ሙሉ በሙሉ ዳኑ የሚል የፈጠራ ምሥክርነት ይሰጣሉ፡፡ በጣም የሚያስቀኝ የሁልጊዜ ተረታቸው ቢኖር ይህ ብቻ ነው፡፡ ጸበል፣ እምነት፣ ቁርባን ያላዳነውን በሽታ ፓስተሩ ጸልዮ አዳነው አቤት ቀልድ፡፡ እሽ ይዳን መቼም የአምላክ ድንቅ ሥራ ብዙ ነው ጠንቅዋይስ ያድናል እያሉ የሚሰግዱ አሉ አይደል፡፡ እንደጠንቅዋዩ ሁሉ ፓስተሩም ያድናል ይፈውሳል እንበል የሚድነው ግን ከነፍስ በሽታ ነውን? አይደለም፡፡ ሁሉንም ስትሰሟቸው የሚመሰክሩት ሁሉ የሥጋ ደዌ ነው፡፡ ጸበል አያድንምን? ያድናል፤ ቁርባን አያድንምን? ያድናል፤እምነት አያድንምን? ያድናል፡፡ ግን ትእግሥትና ጊዜ እምነትና ጽናት ይጠይቃል፡፡ ግን እኮ ደግሞ የግድ ሁሉም በሽታ መዳን የለበትም፡፡ ምክንያቱም እነ ጳውሎስና ጴጥሮስ በጥላቸው ድውይ እየፈወሱ እነርሱ ግን በሽታ ነበረባቸው፡፡ መድኃኒቶች ራሳቸው በሽታ ነበረባቸው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ትእግሥት ስናጣ አቋራጭ ድኅነትን አቋራጭ ጽድቅን መፈለግ አያስፈልገንም ኢዮብን አትዘንጉ እንጅ ወገኖቼ፡፡ የሰጠኸኝን ውሰድ እንበለው እኛ ምን አገባን አምላክ የፈቀደውን ቢያደርግ፡፡ አብዛኛው የመናፍቃኑ አባላት ሲጠየቁ የሚመልሱት ይህንን ነው እንዲህ ተደርጎልኝ እንዲህ ተፈውሶልኝ ወዘተ የሚል የማይረባ ትርኪ ምርኪ፡፡ ቅዱሳኑንም አማላጅ አንላቸውም የሚሉት ለዚሁ ነው፡፡ እኛው ራሳችን በአቋራጭ ፈጣሪችንን ማናገር ስለምንችል ማንንም አማልዱን አንልም ይላሉ፡፡ በቃ በአቋራጭ ራሳቸውን ጻድቅ አድርገውታል፡፡ መድረክ ላይ ወጥቶ መንፈራፈር፣ መንፈስ ነው እያሉ መውደቅ ጽድቅ ነው ብለው ጽፈውታል፡፡ መውደቅ ጽድቅ ከሆነ ታዲያ ማን ሞኝ አለ በጾም በጸሎት በስግደት በምጽዋት የሚንገላታ? እነዚህ የተቀደሱ ተግባራት መንገላታት ናቸው ብለው ካመኑ ማለት ነው፡፡ እናንተ ግን ወገኖቼ አደራ አደራ አደራ አቋራጭ መንገድን አቋራጭ ጽድቅን ምርጫችሁ አታድርጉ ምክንያቱም ያ መንገድ የጥፋት ነውና!!!