© በመልካሙ በየነመጋቢት 14/2008 ዓ.ምደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
በክፍል 4 ሃይማኖት እንዴት እና መቼ ተጀመረ? ሃይማኖት ለማን ያስፈልጋል? የሚሉትን የሃይማኖትና የፍጥረታትን ግንኙነት ተመልክተናል በዚህ ክፍል ደግሞ ሰው ያለሃይማኖት መኖር ይችላልን የሚለውን እና የክርስትና እምነት ምን እንደሚመስል በአጭሩ እንመለከታለን መልካም ንባብ!
ሰው ያለሃይማኖት መኖር ይችላልን? ለሚለው ጥያቄ አጭሩ መልስ መኖር አይችልም የሚል ነው። ሰው የሚያመልከውን ነገር ላያውቅ ይችላል፣ ስለሚያመልከውም ነገር ላያውቅ ይችላል እንጅ የሚያመልከው ነገር ይኖረዋል። ምናልባት በእግዚአብሔር ላያምን የሚችል ሰው ቢኖር ሌላ የሚያመልከው ነገር ስላለው ሰው ያለሃይማኖት ሊኖር አይችልም። በምንም ነገር አላምንም የሚል ሰው ራሱ ይህ አለማመኑ ሃይማኖቱ ነው። ጠቅለል ሲል ሰው እግዚአብሔርን ባያመልክ እንኳ ጉልበቱን፣ ሥልጣኑን፣ ገንዘቡን፣ ወገኑን፣ ውበቱን፣ እውቀቱን ወዘተ ማምለኩ አይቀርም። ሰው ያለ አየር መኖር እንደማይችል ሁሉ ያለሃይማኖትም መኖር አይችልም። ምናልባት ስለአየሩ ምንም ላያውቅ እንደሚችለው ሁሉ ስለሚያምነውም ላያውቅ ይችላል እንጅ ያለእምነት ግን ሊኖር አይችልም። እኛ ወደምናምንበት የክርስትና ሃይማኖት ስንሄድ ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ነው ብለን እናምናለን። ክርስትና ምንድን ነው? የሚለውን እንመልከት።
የክርስትና ሃይማኖት በክርስቶስ ደም የተመሠረተ መሆኑን በወንጌል እንደተጻፈው አምነን የተቀበልነው ነው። ይህ ክርስትና የመገለጥ ሃይማኖት ነው። ክርስትና ሃይማኖት በማን ላይ ሊሆን እንደሚችል ሲያስረዳ አምላክ ሰማያዊ ሥጋ አዳምን ለብሶ ተገልጧል። 1ኛ ጢሞ3፥16 ላይ ኢየሱስ ክርስቶስን በሥጋ የተገለጠ ብሎ ገልጾታል። ስለዚህ ክርስትና በክርስቶስ መገለጥ ላይ የጸና ነው። ክርስትና በፈጣሪ የተመሠረተ በሐዋርያት ስብከት ላይ የታነጸ ነው። እንደሎሎች እምነቶች በፍጡር አልተመሠረተም። ሞተው በቀሩት በበሰበሱት ፍጡራን አልተመሠረተም ሞትን ድል በነሣው በሥጋ ማርያም በተገለጠው አምላክ እንጅ።
የክርስትና እምነት ልዩ ነው። መሠረቱ የክርስቶስ ማንነት ነው። ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ እንደተናገረው በሥጋ የተገለጠው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ማመን ነው። ይህ እምነት ልዩ የተባለው እንደሌሎች አንድ ብቻ አለማለቱ ነው። ምሥጢረ ሥላሴ ላይ ስንመለከት እግዚአብሔር አንድ ሲሆን ሦስት፤ ሦስት ሲሆን አንድ ነው። ልዩ ሦስትነት አለው አንድነቱ ሦስትነቱን አይጠቀልለውም፤ ሦስትነቱም አንድነቱን አይከፋፍለውም። ይህ ልዩ ምሥጢር ለአንዳንዶች አልገባቸውም ስላልገባቸውም ልዩ ከሆነው ክርስትና ኮበለሉ። በመለኮት፣ በስልጣን፣ በመፍጠር በማሳለፍ በባሕርይ በህልውና አንድ የሆነው እግዚአብሔር በስም በአካል በግብር ሦስት ይሆናል። ለዚህ ነው በዚህ እምነት ላይ የተመሰረተውን ክርስትና ልዩ ነው የምንለው። ወልድ በተለየ አካሉ ከድንግል ማርያም ሥጋን ለብሶ አዳነን ለማለት ያበቃንም ይኼው እውነት ነው። በደኃራዊ ልደቱ ቀዳማዊ ልደቱን ተረድተን ወልደ አብ ወልደ ማርያም ለማለት የበቃን ለዚህ ነው። በደኃራዊ ልደቱ ያለአባት ከድንግል ማርያም ሲወለድ እንዳየነው ሁሉ በቀዳማዊ ልደቱ ያለእናት ከአብ መወለዱን እናምናለን። ይህም ድንቅ ምሥጢር ክርስትናን ልዩ ያደርገዋል።
ሌላው የክርስትና እምነት በር ነው። የተለያዩ እምነቶች ሊድኑባቸው የሚችሉባቸውን መንገዶች ይከተላሉ። ለክርስትና ግን ዘላለማዊ ድኅነት ለማግኘት መንገዳችን አንድ ብቻ ነው እርሱም በሥጋ ማርያም በተገለጠው ክርስቶስ ማመን ነው። ከዚህ መንገድ ውጭ ሕግን ቢፈጽሙ፣ ምግባር ትሩፋት ቢሠሩ በምልጃ ቢያምኑም መዳን የለም። ዮሐ 10፥9 "በሩ እኔ ነኝ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል ይገባልም ይወጣልም መሰማሪያም ያገኛል" ዮሐ 14፥6 "እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም" በማለት ይናገራል። ይህንን ቃል የተናገረው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እንግዲህ እንደነገረን ለመዳን በበሩ በኩል መግባት ያስፈልገናል። በሥጋ ማርያም በተገለጠው ጌታ አምነን በስመ ሥላሴ ተጠምቀን ሥጋውን በልተን ደሙንም ጠጥተን ምግባር መሥራት ሕግ መፈጸም መመጽወት መጾም መጸለይ መማር ማስተማር እንችላለን ምክንያቱም በሩ መንገዱ እውነቱ እርሱ ነውና። እግዚአብሔር አብን እግዚአብሔር ለማለት የግድ በሥጋ ተግልጦ አባቱን የሰበከልንን ጌታ አምላክነቱን ማመን አለብን ምክንያቱም መንገድ እውነትና ሕይወት ጌታችን ነውና። በዚህ በር ያልገባ ማለትም በክርስቶስ አምላክነት ያላመነ በስመ ሥላሴ ያልተጠመቀ ሥጋውን ያልበላ ደሙንም ያልጠጣ ሊጸድቅ አይችልምና ክርስትና ጠባብ የጽድቅ በር ናት።
ተፈጸመ
ማጣቀሻ፡- ዲ.ን ብርሃኑ አድማስ፣ ትምህርተ ሃይማኖት መግቢያ-ማኅበረቅዱሳን 1996 ዓ.ም
No comments:
Post a Comment