Tuesday, March 22, 2016

ትምህርተ ሃይማኖት (ክፍል 1)


© በመልካሙ በየነ
መጋቢት 9/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ትምህርተ ሃይማትን ሊቃውንቱ በሁለት ከፍለው እንደሚያስተምሩትና እንሚያስረዱት እኛም እንዲሁ በሁለት ከፍለን እንመልከተው፡፡
1.  ዶግማ፡- ቃሉ የግሪክ ሲሆን ትርጉሙም እምነት ማለት ነው፡፡ ዶግማ ወይም እምነት አይጨመርበትም፣ አይቀነስለትም፣ አይሻሻልም፣ አይለወጥም፡፡ ከጊዜው ጋር ስላልሄደ፣ ስላልተስማማን፣ አስቸጋሪ ስለሆነ ወዘተ በሚል ማንኛውም ምክንያት መሻሻል መለወጥ መጨመር መቀነስ የለበትም፡፡ ከከበደን ትተን መውጣት እንጅ ምንም ምክንያት አናቀርብበትም፡፡ ሌሎች እምነቶች የሚያስቸግሩን ቢሆኑ የምንሰዋለት ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል በተዋሕዶ እምነት ውስጥ የእግዚአብሔርን ሕልውና እናምናለን፡፡ ሥላሴ አንድ ሲሆኑ ሦስት፣ ሦስት ሲሆኑ አንድ ብለን እናምናለን፡፡ አምላካችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ በተዋሕዶ ተወለደ ብለን እናምናለን፡፡ ያመነ የተጠመቀ ይድናል ያላመነ ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል ብለን ስለምናምን በተወለድን በ40 እና በ80 የልጅነት ጥምቀትን ተጠምቀናል፡፡ ጥምቀታችንም ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅጸነ ዮርዳኖስ እንደሆነ እናምናለን፡፡ ሥጋዬን ያልበላ ደሜንም ያልጠጣ የዘላለም ሕይወት የለውም የሚለውንም አምላካዊ ቃል አምነን ኅብሥቱ ተለውጦ ሥጋ መለኮት ወይኑም ተለውጦ ደመ መለኮት ነው ብለን በማመን እንቆርባለን ወይም ሥጋና ደሙን እንቀበላለን፡፡ በመጨረሻም የሙታንን መነሣት ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ሙታን ሁሉ እንደየሥራቸው ትንሣኤ ዘለክብር ወይም ትንሣኤ ዘለሐሳር ይነሣሉ ብለን እናምናለን፡፡ እንዲሁም የእመብርሃን ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያምን ዘላለማዊ ድንግልና እና አማላጅነት እንዲሁም የመላእክትን ተራዳኢነት የቅዱሳኑን ጸሎት እናምናለን፡፡ ይህንን እምነታችንን ማንም ሊያናውጠን አይችልም፡፡ በመሆኑም ዶግማ ማለት እንዲህ የእምነታችን መሠረት ነው፡፡ ማንም የማይለውጠው ማንም የማያሻሽለው ማንም የማይቀንሰው ማንም የማይጨምረው ማንም የማይከልሰው ነው፡፡
2.  ቀኖና፡- ቃሉ የግሪክ ሲሆን ትርጉሙ ሥርዓት ማለት ነው፡፡ 1ኛቆሮ 14÷40 “ነገር ግን ሁሉ በአግባብና በሥርዓት ይሁን” ይላል ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ ስለዚህ ለማንኛውም ሥራችን ሥርዓት ያስፈልገዋል ማለት ነው፡፡ በእምነታችን ለመጽናት እምነታችንን ጠብቀን ለመቆየት ሥርዓት ያስፈልገናል፡፡ ሁሉም የመሠለውን የሚያደርግበት መሆን የለበትም፡፡ ይህ ሥርዓት ግን ሊጨመርበት፣ ሊሻሻል፣ ሊቀነስ የሚችል ነው፡፡ ነገር ግን ሁኔታውን አይቶ ማሻሻል የሚችለው ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ጥምቀትን በ40 እና  በ80 ብለናል ነገር ግን ሕጻኑን ለሞት የሚያበቃ ነገር ካገኘው ከዚያም ቀድሞ በሞግዚት ገብቶ እንዲጠመቅ አዝዘዋል፡፡ ይህ እንግዲህ ቀኖና ስለሆነ ነው፡፡ አርብ ረቡዕን ከዓመት እስከ ዓመት እንጾማለን ነገር ግን በበዓለ ሃምሳ፣ ገናና ጥምቀት በሆኑባቸው ዕለታት እንዳንጾም ታዝዘናል በዚህም መሠረት ዐርብና ረቡዕ መሆናቸውን እያወቅን እንበላለን ይህ ቀኖና ነው፡፡ በቤተክርስቲያን የቅዳሴ ሥርዓት ላይ 5 ቀዳስያን ያስፈልጋሉ ነገር ግን ከባድ በሆነ ችግር አምስት ካልተገኘ ከአምስት በታች ሁነው ቀድሰው ማቁረብ ይችላሉ ይህ ቀኖና ነው፡፡ ሰው የታወቀ ደዌ ቢኖርበት በአጽዋማት ቀን እንዲጾም አይገደድም በምትኩ ሲሻለው ግን ይጾማል ይህ ቀኖና ነው፡፡ ነገር ግን እዚህም ቢሆን እኛ እንደፈለግን የምናሻሽለው የምንለውጠው የምንጨምረው የምንቀንሰው አይደለም ምክንያቱም መሠረታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና፡፡ 1ኛ ቆሮ 3÷11 “ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና ርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” 
ዶግማ እና ቀኖና እንዲህ ናቸው፡፡ ቀኖና ድካማችንን አይቶ የምንችለውን ያህል ይሰጠናል ዶግማ ላይ ግን ከቻልን ቻልን ነው ካልቻልን ግን ትተን ከመውጣት በቀር ሌላ ማሻሻያ መጠየቅ አንችልም፡፡ ትምህርተ ሃይማኖት እንዲህ ተከፍሎ ይታያል፡፡ የእኛ ትምህርት ትኩረት የሚያደርገው ወደ ዶግማው ነው፡፡ ሥርዓትን ወይም ቀኖናን በተመለከተ የሥርዓት መጻሕፍት ማንበብ መመልከት ይገባናል፡፡ አሁን ግን ወደ እምነት ወይም ዶግማ እንለፍ፡፡
እምነት (ሃይማኖት) ማለት ምን ማለት ነው? እምነት የሚለው ቃል “አምነ” አመነ ካለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ሃይማኖት (እምነት) የሚል ሥም ይወጣል ትርጉሙም ማመን መታመን ማለት ነው፡፡ ማመን ስንል በዓይን አይተን፣ በጆሮ ሰምተን፣ በልብ አስበን፣ በስሜት ሕዋሳት መርምረን መድረስ የማንችላቸውን ነገሮች በርኅቀት (ሩቅ ያሉትን)  አልያም በርቀት (ረቂቅ የሆኑ ነገሮችን) እንዳሉ እንደሚደረጉልን እንደሚሆኑልን በመረዳት መቀበል ነው፡፡ መታመን ስንል ደግሞ እነዚህ ያመናቸው ነገሮች እንዲሆኑልን የምንመልሰው ተግባራዊ መልስ ነው፡፡ ለምሳሌ ሰው በጥምቀት ከሥላሴ ልጅነት ያገኛል ብለን ማመን አለ ይህን እምነታችንን ግን በመጠመቅ ተግባራዊ ምላሽ እንሰጣለን ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው ሥጋና ደሙን በመቀበል የዘላለም ሕይወትን እንደሚወርስ ያምናል ይህንን እምነቱን ግን በመቁረብ ተግባራዊ ምላሽ በመስጠት መታመኑን ያረጋግጣል፡፡ እምነት የሚረጋገጠው በመታመን እንጅ በቤተሙከራ ውስጥ አይደለም፡፡ የገነትን መኖር፣ የሲዖልንም መኖር እናምናለን ከሞት በኋላ ሕይወት እንዳለም እናምናለን፡፡ ይህንን ግን በመታመን ማሳየት ካልሆነ በቀር በምንም ዓይነት ዘዴ ልናረጋግጠው አንችልም፡፡ ለምሳሌ ነፋስ አይጨበጥም አይዳሰስም አይታይም ነገር ግን አሁን ነፋስ ነፈሰ አሁን ነፋስ ጠፋ እንላለን፡፡ ነፋስ መሆኑን በምን እርግጠኞች ሆንን? እርግጠኞች እንድንሆን ያደረገን ሥራውን ተረድተን ነው፡፡እምነትንም እንደዚሁ ነው እርግጠኞች ለመሆን በመታመን ማረጋገጥ እና ሥራውን መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በመነሣት መጻሕፍት እምነትን በስድስት ነጥቦች ይገልጡታል፡፡
1.  ሃይማኖት የሚቀበሉት ነው፡፡
2.  ሃይማኖት በተስፋ የሚረዱት ነው፡፡
3.  ሃይማኖት በፍቅር የሚገለጥ ነው፡፡
4.  ሃይማት በሥራ የሚተረጎም ነው፡፡
5.  ሃይማኖት የማናየውን የምናይበት ረቂቅ መሣሪያ ነው፡፡
6.  እግዚአብሔርን ደስ የምናሠኝበት ነው፡፡

እነዚህን ስድስት ነጥቦች እያንዳንዳቸውን በሚቀጥለው ክፍል እንመለከታለን፡፡ ይቀጥላል…

No comments:

Post a Comment