መጋቢት 20/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
የብዙዎቻችን ጥያቄ ነው ማኅበረ ቅዱሳን ቢፈርስስ? የሚለው፡፡
ማኅበሩ የተመሠረተው በእግዚአብሔር ፈቃድ በብጹአን አባቶቻችን ጸሎት እና እገዛ ነው፡፡ እውቅና የተሰጠውም ከቤተክርስቲያናችን የበላይ
ውሳኔ ሰጪ ከሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ የምሥረታ ታሪኩን መተረክ አልፈልግም ምክንያቱም ማኅበሩ ራሱ በሥራው በተግባር ስለሚናገር
ስለሚመሰክር፡፡ ማኅበሩን ያወቅሁት ከ10 ዓመት በፊት የግቢ ጉባዔ ተማሪ በሆንኩበት ወቅት ነበር፡፡ ሰው ማዳን ባልችል እንኳ ራሴን
ግን ማዳን እንደሚገባኝ ሀ ብየ ፊደል መንፈሳዊን የቆጠርሁበት ማኅበር ነው፡፡ ውዳሴ ማርያምን ያጠናሁበት የግቢ ኮርሶችን የተከታተልኩበት
ማኅበር ነው፡፡ ማኅበሩን ለማዎቅ የግድ የማኅበሩ አባል መሆን አያስፈልግም ከፍሬው የምንረዳው ነውና፡፡ የማኅበሩ አባላት ለአባልነት
ከሚከፍሉት ገንዘብ በተጨማሪ ብዙ ጊዜያቸውን በቤተክርስቲያናችን ወቅታዊ ችግሮች ላይ በጣም በመወያየት ያሳልፋሉ፡፡ በውይይት የማይፈቱትን
ደግሞ በጸሎት እግዚአብሔርን የሚለምኑ፤ እንዲሁም በገዳማት እና አድባራት ላይ ዕጣኑን ዘቢቡን ጧፉን ይዘው ሂደው ጸሎት ምሕላ እንዲያዝላቸው
አባቶችን ዝቅ ብለው ጉልበታቸውን ስመው እግራቸው ሥር ተደፍተው የሚማጸኑ ናቸው፡፡ ማኅበሩ ከምሥረታው ጀምሮ በርካታ ፈተና እንደነበረበት
ሲመሠረት ጀምሮ የሚያውቁት ሁሉ ይናገራሉ፡፡ እኔ ካወቅሁት ጀምሮ እንኳ በርካታ ፈተናዎችን በትእግሥት ሲያሳልፍ አይቻለሁ፡፡ ፈተናዎቹ
ከየት የሚመጡ ናቸው? የሚለውን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ይገባል ከዚያም ቢፈርስስ ምን ሊከሰት ይችላል የሚለውን ስጋት ማየት ተገቢ
ነው፡፡
እኔ የማኅበሩ ፈተናዎች ከሦስት አቅጣጫ እንደሚመጡ እገምታለሁ፡፡
እነዚህም፡-
1.
ማኅበሩን በሚገባ ከሚያውቁ
ሰዎች፤
2.
ማኅበሩን በሚገባ ከማያውቁ
ሰዎች፤
3.
ለቤተ ክርስቲያን ቀናኢ ከሆኑ
ሰዎች ናቸው፡፡
v ማኅበሩን በሚገባ የሚያውቁ ሰዎች ማኅበረ ቅዱሳን ማን እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ ማኅበሩ
ራሳቸውን ትተው ለቤተክርስቲያኒቱ ሌሊት ከቀን የሚጥሩ አባላትን የያዘ እንደሆነ ያውቃሉ፡፡ ማኅበሩ የቤተ ክርስቲያናችን ገንዘብ
ለቤተክርስቲያኒቱ አገልግሎት ብቻ መዋል አለበት የሚሉ አባላትን ያቀፈ መሆኑን ይረዳሉ፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ለምን ቀኖናችን ተጣሰ
ለምንስ ዶግማችን ተለወጠ ብለው የሚጠይቁ አባላትን የያዘ እንደሆነ ይገነዘባሉ፡፡ ማኅበሩ ጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያናችን ጥንታዊነቷን
ይዛ ከመሠርቷ ሳትናወጥ መጽናት አለባት ትምህርቷ መከለስ መበረዝ የለበትም ብለው የሚሞግቱ አባላትን እንደያዘ ያውቃሉ፡፡ ስለዚህ
በቤተክርስቲኒቱ ውስጥ ተሰግስገው ኑፋቄያቸውን ለመዝራት አልመቻቸው ያለ ይህ ማኅበር በመሆኑ ያለስሙ ስምን በመስጠት እንዲጠላ ማድረግ
ይፈልጋሉ፡፡ ማኅበሩ እንዲዘጋም ጥረታቸውን ቀጥለዋል፡፡ እነዚህ ማኅበሩ ካልተዘጋ በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ እንደልባቸው መፈንጨት
እንደማይችሉ የተረዱ ናቸው፡፡ ፓትርያርካችን በዚህ ውስጥ የሚመደቡ ናቸው፡፡ ማኅበሩን ጥንት ከመሠረቱ ጀምረው ያወቁታል፡፡
v ሌሎቹ ደግሞ የእነዚህ ተቃራኒዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ከሰው የሚሰሙትን ወሬ ሁሉ እውነት
እንደሆነ የሚቆጥሩ ናቸው፡፡ ማኅበሩን ቀርበው አያውቁትም በሩቅ ሆነው መንግሥት እንዲህ አለው፣ ፓትርያርኩ እንዲህ አሉት፣ የሆነ
ሰው እንዲህ ብሎታል ስለዚህ ማኅበሩ ችግር አለበት ማለት ነው የሚሉ ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ ራሱ መንግሥት ነው፡፡ መንግሥት
ስጋቱ ማኅበሩ በሙያም በእውቀትም በገንዘብም በሁሉም ነገር ስብጥር በመሆኑ እንደአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ ይመለከተዋል፡፡ በእውነት የፖለቲካ
ዓላማ ቢኖረው ኖሮ ዛሬ የአገራችን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቁጥራቸው
ቀላል ነው እንዴ፡፡ የአሁኑ መንግሥት ትግሉን ከአንድ ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባ ተነሥቶ አይደለም እንዴ የጀመረው፡፡ ታዲያ ይህ
ሁሉ የግቢ ጉባዔ ተማሪ ቢነሣ መንግሥት አንድ ቀን በሥልጣኑ ላይ መቆየት ይቻለው ነበር እንዴ፡፡ የሚገርመው ነገር ተቃዋሚዎች ደግሞ
ተማሪውን በግቢ ጉባዔ አፍኖ ይዞ መንግሥትን እንዳይቃወሙ ከእኛ ጎራ እንዳይሰለፉ ፈሪዎች ልፍስፍሶች አደረገብን ብለው ይወነጅላሉ፡፡
እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ማኅበሩ ማን እንደሆነ ለምን እንደተመሠረተ ያልተረዱ ናቸው፡፡ በእውነት መንግሥትን ለመገልበጥ ሲኖዶስን እውቅና
የሚጠይቅ ማነው? የመንግሥት አካላት በዚህ ሥጋት አይግባችሁ ማኅበሩ ፖለቲካ ነክ ሥራን አይሰራም የቤተክርስቲያን ጉዳይ ገና አላለቀለትምና፡፡
በግለሰብ ደረጃም ያለን ሰዎች ማኅበሩን ከመናፍቃን ጋር የምንደምር አለን፡፡ በእውነት የትኛው መናፍቅ ነው ለቤተክርስቲያናችን ዘብ
ሊሆን የሚታገለው? ሞትን የምንፈራው ሞተን ስላላየነው ነው እንጅ ሞተን ዓይተን ሆኖ ኖሮ ሞትንም ልንወደው እንችል ነበር፡፡ ስለዚህ
ማኅበሩን እንዲህ ነው ከማለት አስቀድሞ ማዎቅ ያስፈልጋል፡፡
v ለቤተክርስቲያን ቀናኢ ከሆኑ ሰዎችም ተጸእኖ አለበት፡፡ የእነዚህ ሰዎች ተጽእኖ ከግልጽነት ችግር
የመነጨ ሊሆን ይችላል፡፡ ለአንድ ዓላማ የሚተጉ ናቸው አንድ አይነት ርእይ አንድ አይነት ተልእኮ አላቸው ነገር ግን ለቤተክርስቲያናቸው
በማሰብ ዘብ ይቆማሉ፡፡ ዘብ ሲቆሙ ማኅበሩን እንደ አንድ የቤተክርስቲያን ጠላት ይመለከቱታል፡፡ ይህ አመለካከታቸው ለቤተክርስቲያኒቱ
ከማሰብ ለቤተክርስቲያኒቱ ከመቅናት አንጻር ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅና ቅዱስ አትናቴዎስ በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ቢጣሉ በማን
ነው የሚፈረደው? በማንም መፍረድ አይቻልም ምክንያቱም ሁለቱም ለቤተክርስቲያኒቱ ራሳቸውን ሰጥተዋልና ነገር ግን አንድ ዓላማ እንዳላቸው
ማሳወቅ ያስፈልጋል፡፡ ዓላማቸው አንድ እንደሆነ ከተረዱ ዮሐንስ አፈወርቅና አትናቴዎስ አንድ ላይ የሚያገለግሉ ቅዱሳን ናቸው፡፡
ስለዚህ ማኅበሩን የሚቃወሙ አንዳንድ ሰዎች ለቤተክርስቲያኒቱ ከማሰብ አንጻር ማኅበሩ ቤተክርስቲያንን እየጎዳ ነው ብለው ከማሰብ
አንጻር ዘብ ለመቆም ፈልገው ይሆናል፡፡ ነገር ግን ዓላማችሁ ከማኅበሩ ጋር አንድ ነውና አንድ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ማኅበሩ እየተከሰሰ
ያለው እኮ ቤተክርስቲያንን መዘበረ ተብሎ አይደለም፡፡ ማኅበሩ እየተከሰሰ ያለው እኮ ቤተክርስቲያንን አቃጠለ ተብሎ አይደለም፡፡
ማኅበሩ እየተከሰሰ ያለው እኮ ወንጌልን አጣመመ ተብሎ አይደለም፡፡ ማኅበሩ እየተከሰሰ ያለው እኮ ተሐድሶ አራማጅ ሆነ ተብሎ አይደለም፡፡
ማኅበሩ እየተከሰሰ ያለው እኮ ሥርዓት ጣሰ ቀኖና አፈረሰ ተብሎ አይደለም፡፡ ማኅበሩ እየተከሰሰ ያለው ለምን ተሐድሶን ታጋልጣለህ
ተብሎ ነው፡፡ ታዲያ ተሐድሶ ያልሆነ ሰው ማኅበሩን እንዴት ሊተቸው ሊነቅፈው ይችላል፡፡ መናፍቃን ያልሆነ ስም ይሰጡታል፡፡ ምክንያቱም
ቤተክርስቲያንን እንደልባቸው ሊፈነጩባት ስላልቻሉ ነው፡፡ ሌላ ምንም ምክንያት የላቸውም ስለዚህ አንድ ሆነን ለቤተክርስቲያኒቱ ዘብ
ልንቆምላት ያስፈልጋል፡፡
እንግዲህ ተጽእኖዎች ከእነዚህ ሦስት አቅጣጫዎች ሊመጡ እንደሚችሉ
እገምታለሁ፡፡ ተጽእኖዎችን የሚፈጥሩት ሰዎች በብዛት በተሐድሶ አራማጆች አሉባልታ ላይ ተመሥርተው ነው፡፡ አሁን አሁን ነገራቸውን
ፖለቲካዊ ይዘት ማስያዝ ጀምረዋል፡፡ እነርሱ ተከራክረው መርታት የሚችሉበትን ትምህርት አልተማሩም፡፡ ስለዚህ ያላቸው አማራጭ ራሳቸውን
ነጻ አድርገው ነገሩን ፖለቲካዊ ይዘት ሰጥተው ከመንግሥት ጋር በማጋጨት መንግሥት ነገሩን ሲይዘው እነርሱ አርፈው ኑፋቄያቸውን መዝራት
ይፈልጋሉ፡፡ ለምሳሌ ዐውደ ርዕዩ አንድ ቀን ሲቀረው መዘጋቱ ሌላ ምንም ተልእኮ የለውም፡፡ ለምን ዐውደ ርዕዩ ይዘጋብናል ብሎ ሕዝቡ
አመጽ የሚፈጥር መስሏቸው ነበር የዘጉት ነገር ግን ሕዝቡ ቀድሟቸዋል፡፡ ሕዝቡ እየቆረቆረው ያለው ቃለ ወንጌል እንጅ አመጽ አይደለም፡፡
ሕዝቡ ያለው ከእግዚአብሔር ጋር እጅ ከሰይጣን ጋር አልነበረም፡፡ ለዚያም ነው እስኪደነግጡ ድረስ የሕዝቡ ዝምታ የደነቃቸው፡፡ ድንጋይ
የሚወራወር ሕዝብ ማኅበሩን አልተከተለውም፡፡ ጥይት የሚተኩስ የታጠቀ ሰው ማኅበሩን አልተከተለውም፡፡ ቦንብ የሚያፈነዳ አሸባሪ ማኅበሩን
አልተከተለውም ለዚህም ነው በትእግሥት የሚጠባበቀው፡፡ ዐውደ ርዕዩን ማንም ይዝጋው ማን አይደንቀኝም እኔን የሚደንቀኝ ግን ለማየት
ጓጉቶ ከክፍለ ሐገር ድረስ ሳይቀር አዲስ አበባ ሂዶ ዐውደ ርዕዩ ታገደ የሚለውን መርዶ ሲሰማ በትእግሥት ወደመጣበት መመለሱ ነው፡፡
በእውነት ነው የምላችሁ በማኅበሩ የኮራሁበት ቀን ቢኖር ያን ጊዜ ነው፡፡ አንድ ድንጋይ አልተወረወረም፣ አንድ ጥይት አልተተኮሰም፣
አንድ ቦንብ አልፈነዳም ምክንያቱም ዓላማው ሰማያዊ እንጅ ምድራዊ አይደለማ! እንዴ መንግሥትም ይህን ተግባር እኮ ማድነቅ ነበረበት
ዕገዳው ላይ እጁ ሊኖርበት ቢችልም፡፡
አሁን አሁን መነጋገሪያ የሖነው ጉዳይ ማኅበረ ቅዱሳን ቢዘጋስ
የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ማኅበሩ ሊዘጋ የሚችለው በቤተክርስቲያኒቱ የበላይ በሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ እንደሆነ አምናለሁ አውቃለሁም፡፡
ፓትርያርኩ እንደ አቡነ ሺኖዳ ሳልሳዊ መጽሐፍ የመጻፍ ብቃት ስለሌላቸው በሚጽፉት የብጹእነታቸው ማስፈራሪያ ደብዳቤ ምንም እንደማይሆን
እገምታለሁ፡፡ ነገር ግን በብዙ ተጽእኖዎች ሲኖዶሱ እንዲዘጋ ቢወስንስ ምክንያቱም የምንኮራባቸው አባቶቻችን “ይህን የጥፋት ዘመን
አታሳየን” ብለው ላይመለሱልን ዐርፈዋል፡፡ አሁን የቀሩን በጣም ጥቂት የሚባሉት አባቶቻችን ናቸው፡፡ ስለዚህ ያፈርሱታል ቢባል ምኑ ነው የሚፈርሰው የሚል ጥያቄ አለኝ፡፡
በእርግጠኝነት ስሙ ይፈርሳል ስሙ ይለወጣል አገልግሎቱ ግን ይጨምራል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን የሚባለው አንድ ስም ሽህ ስም ሆኖ ይነሣል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን የሚለው ስም ወደ ቀደመ ስሙ ተለውጦ ወደ ማኅበረ ቅድስት ድንግል ማርያም፣ወደ ማኅበረ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ወደ ማኅበረ
ቅዱሳን ሐዋርያት፣ ወደ ማኅበረ ቅዱስ ሚካኤል፣ ወደ ማኅበረ ቅዱስ ገብርኤል፣ ወደ ማኅበረ ቅዱስ ዮሐንስ ወዘተ ይለወጣል እንጅ
ሌላ የሚዘጉት ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ማኅበረ ቅዱሳን የሚለው የመሰብሰቢያ ስም የአገልግሎት መስጫ ስም እንጅ እምነት
አይደለማ፡፡ ሰዎች በአምላክ ፈቃድ የመሠረቱት እንጅ በራሳቸው ፈቃድ የመሠረቱት አይደለማ፡፡ ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳን ቢፈርስስ ለሚለው
ጥያቄ የእኔ መልስ የሚሆነው መፍረስ ልንለው የምንችለው የሥም ለውጥ ነው እንጅ የአገልግሎት የዓላማ የርእይ እና የተልእኮ ለውጥ
ይሆናል ብየ አላስብም አልገምትምም፡፡ ነገር ግን ለመንግሥትም ለሐገርም ትልቅ ተጽእኖ እንደሚኖረው እገምታለሁ፡፡
No comments:
Post a Comment