Tuesday, March 22, 2016

ትምህርተ ሃይማኖት (ክፍል 4)

© በመልካሙ በየነ
መጋቢት 13/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

በክፍል 3 ውስጥ የሃይማኖት መሠረቶች ምን ምን እንደሆኑ ተመልክተናል በዚህ ክፍል ደግሞ ሃይማኖት እንዴት መቼ ተጀመረ? ሃይማኖት ለማን ያስፈልጋል? የሚሉትን የሃይማኖትና የፍጥረታትን ግንኙነት እንመለከታለን፡፡ መልካም ንባብ!!!
ሃይማኖት ለፍጥረታት የተሰጠ ከፈጣሪያቸው ጋር የሚገናኙበት መስመር ነው፡፡ ስለዚህ ስለ ሃይማኖት ስናነሣ ሃይማኖት የሚያስፈልጋቸው እነማን ናቸው የሚለውን ማየት ተገቢ ነው፡፡ ፍጥረታት ሁሉ ከፈጣሪያቸው ጋር በራሳቸው ቋንቋ በራሳቸው መግባቢያ ይግባባሉ ይገናኛሉ፡፡ ነገር ግን የተፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ክብሩን ሊወርስ ስሙን ሊቀድስ አልተፈጠረም፡፡ ፍጥረታት የተፈጠሩበት የራሳቸው የሆነ ዓላማ አላቸው፡፡ ለምሳሌ ለምግበ ሥጋ ለምግበ ነፍስ የተፈጠሩ አሉ፤ ለአንክሮ ለተዘክሮ የተፈጠሩ አሉ እነርሱን እያየን እጹብ እጹብ እነርሱን የፈጠረ በማለት ፈጣሪን እንድናመሰግን ማለት ነው፡፡ ስሙን ቀድሰው ክብሩን ወርሰው እንዲኖሩም የተፈጠሩ አሉ፡፡ እነዚህ ናቸው እንግዲህ ሃይማኖት የሚያስፈልጋቸው፡፡ እነዚህም ሰውና መላእክት ናቸው፡፡  እነዚህ ከሌሎች ፍጥረታት ይለያሉ፡፡ በማወቅ ወይም እውቀት ያላቸው በመሆኑ እና መላእክት ፍጹም የማይሞቱ ሰውም ከሞት በኋላ የሚነሣ መሆኑ ልዩ ያደርጋቸዋል፡፡ ሌሎች ፍጥረታት ከምድር ከጠፉ ፈርሰው በስብሰው የሚቀሩ ናቸው ትንሣኤን አይጠብቁም ሰው ግን ትንሣኤን ይጠብቃልና ሃይማኖት ያስፈልገዋል ማለት ነው፡፡ መላእክትም እንዲሁ እምነት ያስፈልጋቸዋል፡፡
የሰው ልጅ ለማመን ብዙ ስጦታ አላቸው፡፡ የመጀመሪያው ነጻ ፈቃድ ነው፡፡ ፈጣሪ ማንንም አስገድዶ እንድናመልከው አያደርግም፡፡ እውቀቱን ተጠቅሞ ፈጣሪውን እንዲያውቅ ያደርገዋል እንጅ አስገድዶ አምልከኝ አይለውም፡፡ ማንም ሰው ፈጣሪውን ለማምለክም ሆነ ላለማምለክ ነጻ ፈቃድ አለው፡፡ አዳም ዕጸ በለስን ቢበላ እንደሚጎዳ ሳይበላ ቢጠብቃት እንደሚጠቀም አሳይቶ ባይተወው ኖር ለመብላት አይበቃም ነበር፡፡ እንዳትበላ ብሎ ማስገደድና እንዳይበላ ማድረግ ይቻለው ነበር ነገር ግን ነጻ ፈቃድ አለውና አላስገደደውም፡፡ ነጻ ፈቃድ ስላለን ብለን ግን እውቀት እንደሌላቸው እንስሳት መሆን የለብንም ለዚህም ነው ሁለተኛው ነገር የተሰጠን፡፡ ሁለተኛው ነገር ምርጫ ነው፡፡ ነጻ ፈቃድ ቢኖረንም በጎውን ከክፉ፣ የሚጎዳውን ከሚጠቅመው መለየትና እና መምረጥ አለብን፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ነው ካልን ወይም አምላክነቱን ካልተቀበልን አምላክ የምንለውን ነገር መምረጥ አለብን መብታችን ነውና፡፡ ሶስተኛው ኃላፊነት ነው፡፡ ነጻ ፈቃዱን እና ምርጫውን ተጠቅሞ ለተቀበለውና ላደረገው ነገር ተጠያቂ የሚሆነው የሚመጣውን ማንኛውንም ነገር ሁሉ በኃላፊነት የሚቀበለው ራሱ መራጩ ሰው ነው፡፡ አዳምን ልብ ማለት ያሻል፡፡ መብላት አለመብላት ነጻ ፈቃድ ነው፡፡ መብላትን መምረጡ ምርጫ ነው፡፡ 5500 ዘመን በእግረ አጋንንት መረገጥ ኃላፊትን መውሰድ ነው፡፡ አታድርጉ የተባልነውን ነገር ለማድረግ ብንፈቅድ ለሚመጣው ማንኛውም ችግር ኃላፊነቱን ራሳችን እንወስዳለን ማለት ነው፡፡
 ሃይማኖት እንዴትና መቼ ተጀመረ የሚለውን ስንመለከት ፍጥረታት መፈጠር የጀመሩበትን ቀን ማስታወስ ያስፈልገናል፡፡ የሥነ ፍጥረት መጀመሪያ የነበሩት ክብሩን ሊወርሱ ስሙን ሊቀድሱ በዕለተ እሁድ የተፈጠሩት መላእክት ናቸው እምነትን የጀመሩት፡፡ አምላክ ፈጥሮ ተሠወራቸው አዋቂ አእምሮ ሰጥቷቸዋልና መርምረው ይወቁኝ ብሎ፡፡ በዚህ ጊዜ ማን ፈጠረን? ከየት መጣን? ብለው ፍጡርነታቸውንና የፈጣሪን መኖር አምነው ተናገሩ፡፡ በዚህ ጊዜ አኃዜ መንጦላእት የነበረው የመላእክት ሁሉ አለቃ ሳጥናኤል ከፍ ቢል ማንም የለም ዝቅ ሲል ግን መላእክት አሉ፡፡ በዚህ ሰዓት ነጻ ፈቃዱን ተጠቅሞ እኔ ፈጠርኳችሁ አላቸው፡፡ ጥርጥር ወይም ክህደትና እምነት ያንጊዜ ጀመረ ማለት ነው፡፡ ሌሎች ሊቃነ መላእክት እውቀታቸውን ተጠቅመው አምላካቸው ሳጥናኤል መሆን አለመሆኑን አረጋገጡ። ቅዱስ ገብርኤል ዝቅ ሲል ከእርሱ በታች ያሉ እልፍ አእላፋት መላእክትን ተመለከተ። እነዚህ ሁሉ ከእኔ በታች ናቸው ግን እኔ አልፈጠርኳቸውም አለ። ከዚያም ሳጥናኤልን አሁን እያየንህ እስኪ ፈጥረህ አሳየን አሉት እሱም አያፍርም እጁን ወደ እሳት ያስገባል ያን ጊዜ ያቃጥለዋል ዋይ ብሎ ይጮኸል አምላክ ግን በስውር ይፈውሰዋል። ነገር ግን አሁንም አምላክ ነኝ እንዳለ ቀጠለ። የተወሰኑ መላእክት ተከተሉት የተወሰኑት ግራ ተጋብተው ቀሩ የተወሰኑትም ከቅዱስ ገብርኤል በኩል ሆኑ። ቅዱስ ገብርኤል አጽናናቸው አምላካችንን እስግናገኝ ድረስ በያለንበት እንጽና አላቸው። ከዚህ እንደምንረዳው እምነት የተጀመረው በዚህ ወቅት ነው። እምነት በቅዱስ ገብርኤል ክህደት በሳጥናኤል በኩል መጣ ማለት ነው። በመላእክት ዘንድ እምነት እንዲህ ነበር በተፈጠሩበት ዕለት የተጀመረው። እምነት ወደ ሰው ልጅ እንዴት መጣ ስንል ብዙዎች የሚጠቅሱት የፍርሐት መኖርን ነው። ሰው ሲፈራ የሚረዳውን መምረጥና ማምለክ ግዴታው ነው። ነገር ግን ሊረዳው የማይችለውን ማምለኩ ስህተት ነው። ሰዎች በፀሐይ በጨረቃ ያመልኩ እንደነበር ግልጽ ነው። ዕለታት ሁሉ እንደተሰየሙላቸው የምናውቀውእውነት ነው። ሰኞን moon day ዛሬ monday እሁድን sunday ብለውታል። ስለዚህ እነዚህ ፍጥረታት እንደ አምላክ ተቆጥረው ተመልከዋል ማለት ነው። ግን እነዚህ ፍጥረታት እንድናመልካቸው አስገድደውናልን? አላስገደዱንም። እነዚህ ፍጥረታት ግን አምላክ መሆን ይቻላቸዋልን? እስኪ የአምላክን መገለጫዎች እንመልከት።
ü  አስገኝ የሌለው፣
ü  ማንም ማን ሊተካከለው የማይችል፣
ü  ዓለምን ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣ፣
ü  ሁሉን የሚመግብ፣
ü  የሚያሸንፈው የሌለ፣
ü  እርሱንየ ሚገድበው የሌለ፣
ü  ከእርሱ የሚበልጥ የሌለበት፣
ü  ሰማይን የዘረጋ ምድርን በውኃ ላይ ያጸና፣
ü  ጊዜ የማይለውጠው ዘመን የማይሽረው፣
ü  ዓለምን አሳልፎ የሚኖር ዘላለማዊ፣
ü  የሚመጣውንየ ሚያውቅ፣
ü  ሁሉን በፈቃዱ የሚያደርግ፣
ü  ድካም የሌለበት፣
ü  እንቅልፍ የማያሸንፈው፣
ü  አማክሩኝ የማይል፣
ü  ሌላ አጋዥ የማይሻ፣
ü  ዘመናትን በዘመናት ጊዜያትን በጊዜያት የሚተካ፣
ü  ሁሉን የሚገዛ፣
ü  ሁሉን የሚያስተደድር፣
ü  በሥራው የማይፀፀት፣
ü  የማይዳሰስ፣ የማይጨበጥ ረቂቅ
ü  በሁሉ ቦታ ያለ /ምሉዕ በኩለሄ የሆነ/፣
ü  ከእርሱ ፈቃድ ውጭ አንድ ነገር እንኳ የማይደረግ፣
ü  እውነተኛ ፈራጅ፣
ü  ውሸት የሌለበት፣
ü  ንፁሕ ኃጢአት የማይስማማው፣
ü  በማንም የማይመራ፣
ü  ሁሉ በእርሱ የሆነ፣
ü  ተመርምሮ ሊደረስበት የማይችል፣
ü  ከአእምሮ በላይ የሆነ ነው፣
ü  የማይደረስበት ምጡቅ የማይጨበጥ ረቂቅ::
አምላክ የምንለው ቢያንስ እነዚህን ነገሮች ማሟላት ይኖርበታል፡፡ እነዚህን የማያሟላ አምላክ ግን ፍጡር እንጅ ፈጣሪ ሊሆን እንዴት ይችላል?


ሰው ያለሃይማኖት መኖር ይችላልን የሚለውን እና የክርስትና እምነት ምን እንደሚመስል በአጭሩ በሚቀጥለው ክፍል እንመለከታለን። ይቀጥላል...

No comments:

Post a Comment