Tuesday, March 22, 2016

ትምህርተ ሃይማኖት (ክፍል 2)


© በመልካሙ በየነ
መጋቢት 10/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ክፍል አንድ ስለ እምነት ትርጉም እና እምነትን በሁለት ከፍለን አይተናል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ ሃይማኖትን በስድት ነጥቦች እንመለከታለን መልካም ንባብ!
1.  ሃይማኖት የሚቀበሉት ነው፡- እምነትን በመመርመር ልናውቀው አንችልም፡፡ አንዳንድ ሰዎች በራሳቸው መንገድ ሄደው በዓይናቸው አይተው፣ በጆሯቸው ሰምተው፣ በእጃቸው ዳስሰው ማመን ይፈልጋሉ፡፡ በእውነት እንዲህ የሚሆን እና የሚረጋገጥ ነገር እምነት ነው ብሎ ለመቀበል አይከብድምን? ምናልባት እንደአብርሃም በተፈጥሮ እውቀታችን አምላክን ወደማወቅ ልንደርስ እንችላለን ነገር ግን ወደዚህ እውነት ለመድረስ በራሱ እምነት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ እምነትን ካላየን ካልሰማን ካልዳሰስን ሳንል ዝም ብለን የምንቀበለው ነው፡፡ ማወቅ የሚመጣውም ከአመንን በኋላ ነው፡፡ ሳይንስና እምነት ልዩነታቸው እዚህ ላይ ነው፡፡ ሳይንስ ያወቀውን የተረዳውን ያረጋገጠውን ነገር ብቻ ያምናል፡፡ እምነት ደግሞ ከአመነ በኋላ ያውቃል፣ ከአመነ በኋላ ያረጋግጣል፣ ከአመነ በኋላ ይረዳል ማለት ነው፡፡ ዮሐ6÷69 ላይ “እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ እንደሆንህ አምነናል አውቀናልም” ይላል ቅዱስ ጴጥሮስ ሲመልስ፡፡ አምነናል ካለ በኋላ ነው አውቀናልም ያለው እንጅ አውቀናል ካለ በኋላ አምነናልም አላለም፡፡ እምነትን ዝም ብለን የምንቀበለው ከስሜት በላይ  እና ከአእምሮ (ከእውቀት) በላይ ስለሆነ ነው፡፡ ስሜትን በሕዋሳት ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ቀይ፣ ጥቁር፣ ነጭ፣ ቢጫ የሚለውን በማየት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ሽታንም በማሽተት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ለስላሳ፣ ሻካራ የሚለውን ነገርም በመዳሰስ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ጣእምንም በመቅመስ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ እምነትን ግን በእነዚህ በተዘረዘሩት ሕዋሳት ማረጋገጥ አንችልም ምክንያቱም ከእነዚህ ስሜቶች ሁሉ በላይ ነውና፡፡ ለዚህም ማስረጃችን መስማት የማይችለው፣ ማየት የማይችለው፣ መቅመስ የማይችለው፣ መዳሰስ የማይችለው፣ መናገር የማይችለው ሁሉ እምነት አለው፡፡ ሁለተኛው ነገር እምነት ከእውቀት ወይም ከአእምሮ በላይ በመሆኑ ዝም ብለን እንቀበለዋለን፡፡ ሮሜ 12÷3 ላይ ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስቀመጠው አእምሮ ልክ እና ገደብ አለው፡፡ ማሰብ የምንችለው፣ ማወቅ የምንችለው ነገር ሁሉ የተሰፈረ፣ የተለካ እና የተገደበ ነው፡፡ ከዚህ ልክ እና ገደብ ማለፍ አንችልም እንለፍ ብንል እንኳ በጭንቀት ራሳችንን ከማሳበድ በቀር ምንም ማምጣ አንችልም፡፡ ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ ምን ይመስል እንደነበር ወደኋላ ዞረን ብናስብ ከእውቀታችን በላይ ነው፡፡ ከሞት በኋላ አፈር የሆነው የበሰበሰው ሥጋ ከነፍስ ጋር ይዋሐዳል ብሎ ማመን ከአእምሮ በላይ ነው፡፡ በጥምቀት ጊዜ ካሕኑ “አሐዱ አብ ቅዱስ፣ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ” ብሎ ውሐውን  ሲባርከው በዕለተ አርብ ከጌታ ጎን የፈሰሰውን ውኃ ይሆናል ብሎ ማመን ከአእምሮ በላይ ነው፡፡ ስለዚህ እምነትን ዝም ብለን እንቀበለዋለን ማለት ነው፡፡
2.  ሃይማኖት በተስፋ የሚረዱት ነው፡- ዕብ 11÷1 ላይ "እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚስረግጥ የማናየውን ነገር የሚያስረዳ ነው” ይላል ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ ተስፋ የሌለው ሰው አያምንም ያላመነም ሰው ተስፋ የለውም፡፡ እምነት ውስጥ ተስፋ አለ፡፡ ወደፊት ብዙ ተስፋ አለን፡፡ ከሞት በኋላ ተነሥተን ዘላለማዊ መንግሥትን እንወርሳለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ የጸሎታችንን መልስ የምንጠብቀው በተስፋ ነው፡፡ ሥጋዊ እና ሰማያዊ ሕይወታችንን አምላክ ያስተካክልልናል ብለን የምንረዳው በተስፋ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን መግቦት ጠብቆት ጸጋና ረድኤቱን የምንጠብቀው በተስፋ ነው፡፡ ተስፋ የሌለው ሰው በአጠቃላይ እምነት የለውም ማለት ይቻላል፡፡ ለማየት የምንጓጓውን ነገር ጊዜውን ጠብቆ ያሳየናል ብለን የምንጠብቀው በተስፋ ነው፡፡
3.  ሃይማኖት በፍቅር የሚገለጥ ነው፡- ይህ ማለት ለሌሎች ደግ ማድረግ መራራት ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከድንግል ማርያም ተወልዶ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ እኛን ያዳነን ስለወደደን ነው፡፡ ዓለምን እንዲሁ የወደደ አምላክ እርስ በርሳችሁም ተዋደዱ ብሎናል፡፡ በዚህ መዋደዳችን ሃይማኖታችንን እንገልጣለን ማለት ነው፡፡ ያለው ለሌለው የሚሰጥበት፣ የራበውን የሚያበላበት፣ የተጠማውን የሚያጠጣበት፣ የታረዘውን የሚያለብስበት ነው ፍቅር ማለት፡፡ ሌላውን እንደራስ አስቦ ለራስ የሚያስፈልገውን ነገር ለሌሎችም ማድረግ ነው ፍቅር፡፡ ስለዚህ ሃይማኖታችን እንዲህ በፍቅር መልካም በማድረግ ለሌሎች በመራራት የምንገልጠው ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ፍቅርን እንዲህ ይገልጠዋል “በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሿሿ ጸናጽል ሆኛለሁ፡፡ ትንቢትም ቢኖረኝ  ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትንም ሁሉ ባውቅ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ፡፡ ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም፡፡ ፍቅር ይታገሣል ቸርነትንም ያደርጋል ፍቅር አይቀናም ፍቅር አይመካም ፍቅር አይታበይም የማይገባውን አያደርግም የራሱንም አይፈልግም  አይበሳጭም በደልንም አይቆጥርም ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጅ ስለ አመፃ ደስ አይለውም ሁሉን ይታገሣል ሁሉን ያምናል ሁሉን ተስፋ ያደርጋል በሁሉ ይጸናል፡፡ ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም… እንዲሁም ከሆነ እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው” /1ኛ ቆሮ13 ÷ 1-13/ ስለዚህ ትልቁን ጸጋ ፍቅርን ለሃይማኖት መግለጫ ልንጠቀምበት ይገባናል፡፡ ምክንያም ሃይማኖት በፍቅር የሚገለጥ ነውና፡፡ ይህ ፍቅር መታመንን የምናሳይበት ምግባር ነው፡፡ መታመናችንን ግን ለራስ ሳይሆን ለሌሎች የምናሳይበት መሣሪያ ነው ፍቅር፡፡
4.  ሃይማት በሥራ የሚተረጎም ነው፡- እንደ ፍቅር ሁሉ ይህም መታመንን የምናረጋግጥበት ነው፡፡ መታመንን ከራሳችን የምንጀምርበት ነው፡፡ ለምሳሌ በጥምቀት የሥላሴን ልጅነት እንደሚገኝ ያመነ ሰው መጠመቅ አለበት፡፡ ሥጋና ደሙን በመቀበል የዘላለም ሕይወት እንደሚወርስ ያመነ ሰው መቁረብ አለበት፡፡ ልዑል መለኮት ራሱን ዝቅ አድርጎ ደካማ ሥጋን እንደበሰ፣ የሐዋርያትን እግር ዝቅ ብሎ እንዳጠበ ያመነ የተረዳ ሰው የትሕትና ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅበታል ማለት ነው ምክንያቱም ሃይማኖት በሥራ የሚተረጎም ነውና፡፡
5.  ሃይማኖት የማናየውን የምናይበት ረቂቅ መሣሪያ ነው፡- ሃይማኖት የማናየውን የምንረዳበት ነው፡፡ ከላይ ያየናቸውን ነገሮች በአግባቡ ከጠበቅን ለአንድ ነገር ያበናል ማለት ነው፡፡ እርሱም ረቂቃንን አጉልተን ሩቆችን አቅርበን እናይበታለን ማለት ነው፡፡ በእምነት ውስጥ ረቂቅ የሆኑትን እግዚአብሔርን እና መላእክትን እንዲሁም ሩቅ የሆኑትን ገነትን መንግሥተ ሰማያትን እናይበታለን ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ከእምነቱ ጽናት የተነሣ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጥቆ አይቷል፡፡ 2ኛ ቆሮ 12 ÷2 ሄኖክንም ወደ ብሔረ ሕያዋን እንዲሄድ ያደረገው እምነቱ ነው፡፡ ዕብ 11÷5 ሠለስቱ ደቂቅ ከእሳት የዳኑት በእምነት ነው። ዳንኤል ከተራቡ አናብስት የዳነው በእምነት ነው። ሌሎችንም ምሳሌዎችን ማየት ይቻላል ለዚህ ትምህርት ግን ይበቃናል፡፡እምነት በስሜት ማረጋገጥ የማንችለውን አእምሮ የማይደርስበትን ነገር ሁሉ ሩቁን አቅርበን ረቂቁን አግዝፈን የምናይበት ረቂቅ መሣሪያ ነው፡፡
6.  እግዚአብሔርን ደስ የምናሠኝበት ነው፡- እግዚአብሔርን ደስ የምናሰኘው በምንድን ነው የሚለውን ነገር ማወቅ ይገባናል፡፡ በጭፈራ በዳንስ አናስደስተውም፡፡ በየመንገዱና በየፌርማታው “ኢየሱስ” እያሉ በመጮህም አናስደስተውም፡፡ እናቱን በመሳደብ ቅዱሳንን በመናቅም አናስደስተውም፡፡ በእምነታችንና በምንሠራቸው ሥራዎች ብቻ ነው ደስ የምናሰኘው፡፡ የመቶ አለቃውን እምነትና ምግባር የያዕቆብን እምነትና ምግባር መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አንችልም” ዕብ 11÷6 በማለት ይገልጻል፡፡ ስለዚህ አምላክን ለማስደሰት እምነት ሊኖረን ይገባል፡፡ የታመመ ልጁን እንዲፈውስለት ኢየሱስ ክርስቶስን የጠየቀው መቶ አለቃ እምነቱ ትልቅ ስለነበር ኢየሱስ ከታመመው ልጅህ ዘንድ ሄጄ ልፈውስልህ ሲለው እዚህ ሆነህ ቃል ተናገር ልጄ ባለበት ይፈወስልኛል ብሎ ማመኑ ጌታን አስደስቶታል፡፡ መቶ አለቃው ይህንን ማንም ሳያስተምረው እንዴት አወቀው? ያዕቆብስ ብኩርና እንደሚጠቅም ማን አስተማረውና ነው በምስር ወጥ ብኩርናን ከኤሳው የተቀበለ? ይህ እምነት ነው ለዚህም ነው አምላክን ያስደሰቱት፡፡ ስለዚህ እምነት አምላክን ደስ የምናሰኝበት ነው ማለት ነው፡፡

የሃይማኖት መሠረቶች ምን ምን እንደሆኑ በዝርዝር በሚቀጥለው ክፍል እንመለከታለን፡፡ ይቀጥላል….

No comments:

Post a Comment