© በመልካሙ በየነ
መጋቢት 12/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
በክፍል 2 የእምነትን
ስድስት መገለጫዎች ተመልክተናል በዚህ ክፍል ደግሞ የሃይማኖት መሠረቶችን በዝርዝር እናያለን መልካም ንባብ!
ለሃይማኖት መኖር
የተለያዩ መሠረቶች አሉ፡፡ አንዳንዶች ለእምነታቸው መሠረት የሚያደርጉት የተለያየ ነገር አላቸው፡፡ ፍርሐታቸውን፣ በራስ አለመተማመናቸውን፣
ድንጋጤያቸውን፣ መጨነቃቸውን ወዘተ ለእምነታቸው መሠረት ያደርጋሉ፡፡ እነርሱ እንደሚያስቡት የፍርሐታቸው፣ የድንጋጤያቸው፣ የጭንቀታቸው፣
በራስ ያለመተማመናቸው ምንጭ ከእነርሱ በላይ የሆነ ነገር ስላለ ነው፡፡ ስለዚህ በዚያ ከእነርሱ በላይ በሆነው ነገር ማመን እንዳለባቸው
ይረዳሉ፡፡ እምነታቸው በዚህ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ነገር ግን ለእምነታችን መሠረት ልናደርገው የሚገባው ነገር ይህ አይደለም ምክንያቱም
እምነትን ስናወራ የግድ እምነት እንዲኖረን ሊያደርግ የሚችለውን ነገር ነውና መሠረት ማድረግ ያለብን፡፡ ስለዚህ ለእምነታችን መሠረቱ
የፈጣሪ መኖር እና ሥልጣን ያላቸው ነገሮች መኖራቸው እንደሆነ በማኅበረ ቅዱሳን የተዘጋጀው ትምህርተ ሃይማኖት መግቢያ በሚል የታተመው
የግቢ ጉባዔ ማስተማሪያ መጽሐፍ ያስረዳናል፡፡
1. የፈጣሪ መኖር፡- ያለፈጣሪ ስለሃይማኖት ማውራት አይቻልም፡፡ ማንኛውም ሃይማኖት ሃይማኖት ለመባል የግድ ፈጣሪ
እንዳለ ማመንን ይጠይቃል፡፡ ፈጣሪ የሌለበት ወይም ፈጣሪ እንዳለ የማይታመንበት እምነት የለም፡፡ ይህን ፈጣሪ አለማዎቅ ግን ፈጣሪ
የለም እንድንል አያደርገንም፡፡ ነቢዩ ዳዊት መዝ 13(14)÷1 “ሰነፍ በልቡ አምላክ የለም ይላል” በማለት ይገልጻል፡፡ ፈጣሪን
ካለማዎቅ የተነሣ አምላክ የለም ብሎ መናገር ሰነፍነት ነው፡፡ አምላክ የለም ብሎ የሚያምን ሰው ቢኖር እርሱ ራሱ እንዴት እንደመጣ፣
እንዴት እንደተፈጠረ፣ እንዴት እንደሚኖር፣ ለምን እንደሚኖር፣ የመኖርና የመሞት ጥቅምና ጉዳት ወዘተ የማይረዳ ነው፡፡ አንዳንዶች
ገነት፣ ሲዖል፣ መንግሥተ ሰማያት፣ ገሐነመ እሳት ወዘተ የሉም ስለዚህ አሁን ከመሞታችን በፊት እንብላ እንጠጣ እንደሰት እንደፈለግን
እንሁን ብለው ያምናሉ፡፡ ነገር ግን እዚህ ላይም መመለስ የሚገባቸው ጥያቄ አለ፡፡ መብላት ካለመብላት፣ መደሰት ካለመደሰት፣ መጠጣት
ካለመጠጣት፣ አለመሞት ከመሞት ለመሻሉ ምን ማረጋገጫ አለን፡፡ በሕይወት ከመኖር ይልቅ በመቃብር አፈር ሆኖ መኖር የተሻለ ቢሆንስ
ምን ማረጋገጫ አለ፡፡ ከሞት በኋላስ መደሰት መብላት መጠጣት እንደፈለገ መሆን መቻል አለመቻሉን በምን እርግጠኞች መሆን ቻሉ፡፡
ይህ የሚያሳየው ሞትን እንደሚፈሩት ነው፡፡ አንድ ሰው ፈጣሪ የለም ብሎ ካመነ የእርሱን ሰው መሆን ወይም ፍጡርነቱን አልተረዳም
ማለት ነው፡፡ በመሆኑም እምነቱ በፈጣሪ ላይ አልተመሰረተም ማለት ነው፡፡ ነገር ግን የፈጣሪን መኖር የተረዳ ሰው የእርሱን ፍጡርነት
ስለሚረዳ ፈጣሪውን ለማስደሰት ለፈጣሪ ሊደረግ የሚገባውን ሁሉ ያደርጋል መልካሙን ነገር መርጦ ክፉውን ነገር ሁሉ ያስወግዳል፡፡
ፍጡራን እንኳ የፈጣሪን መኖር ባያምኑ ፈጣሪ ግን ህልው ሆኖ ይኖራል፡፡ በመሆኑም ለእምነታችን መሠረት ሀልዎተ ፈጣሪ ወይም የፈጣሪ
መኖር ነው፡፡
2. ሥልጣን ያላቸው ነገሮች መኖር፡- እውነትን እንድንመሰክር እውነትን እንድንናገር በማስገደድ እንድናምን የሚደርጉን ሥልጣን ያላቸው
ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህም የቤተ ክርስቲያናችን ትውፊትና ቅዱስ መጽሐፍ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ወደ እውነት የመምራት ሥልጣን አላቸው፡፡
በመሆኑም እውነትን ይዘን የፈጣሪን መኖር ተረድተን እምነታችንን እናጠነክራለን ማለት ነው፡፡
1.1 የቤተ ክርስቲን ትውፊት፡- ሰው የቤተክርስቲያንን ሥልጣን ከአወቀና
እውነቷን ከተረዳ ሃይማኖቱን ማወጅ ይችላል፡፡ ትውፊትን ካልተቀበልን መጽሐፍ ቅዱስንም መቀበል አንችልም፡፡ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ
ራሱ ከአንዱ ወደ አንዱ የመጣው በትውፊት ነው፡፡ አዳም ከገነት ከተባረረ በኋላ የወለዳቸው ልጆች እግዚአብሔርን ያመልኩ የነበረው
መጽፍ ቅዱስ አንብበው አልነበረም፡፡ ከእነርሱም በኋላ የተነሡት እግዚአብሔርን ያመለኩት መሥዋእት የሰውት በትውፊት ባገኙት ትምህርት
እንጅ መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎላቸው መምህር ሰብኮላቸው አልነበረም፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ እኛ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተጻፉ ነገር ግን
በትውፊት አንዱ ለአንዱ እያቀበለው የመጣውን ትምህርት ሁሉ የምንቀበለው፡፡ ጌታችን ደቀመዛሙርቱን “ ወደዓለም ሂዱ፡- ወንጌልንም
ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” አላቸው፡፡ በዚያ ሰዓት ወንጌል በመጽሐፍ መልኩ አልታተመም ነበር ነገር ግን እኔ በቃል ያስተማርኳችሁን ሂዱና
አስተምሩ ሲላቸው ነው፡፡ ስለዚህ በቃል የወረስነው ትውፊት እውነትን እንድናውቅ የሚረዳ እና ለመጻሕፍትም መጻፍ መሠረት ነውና ለእምነታችን
መሠረት ነው፡፡ ዛሬ ትውፊትን ከመምህራን፣ ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከአባቶቻችን እናገኛለን ይህ ትውፊት አንዱ ለአንዱ እያወረሰው
የሚቀጥል እውነት ነው፡፡
1.2 ቅዱስ መጽሐፍ፡- እውነትን የሚናገር፣ ሥልጣን ያለው፣ በቅዱሳን
አባቶች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው የተጻፈ ልዩ መጽሐፍ ነው፡፡ ይህንን የታላቅነት ሥልጣን የሰጠው ራሱ ጌታችን ነው፡፡ በዮሐ5÷47
“መጻሕፍትን ካላመናችሁ ግን ቃሌን እንዴት ታምናላችሁ” ብሎ አይሁድን ገስጿል፡፡ በሌላም ዘንድ እንዲሁ ስለአልዓዛርና ነዌ ጌታ
ሲያስተምር “ሙሴንና ነቢያትን የማይሰሙ ከሆነ ከሙታን አንዱ እንኳ ቢነሣ አያምኑም” ብሏል፡፡ ይህን ያለው ሙሴና ነቢያቱ እስከዚያ
ድረስ በሕይወት ኖረው አይደለም በመጽሐፎቻቸው ካላመኑ ለማለት ነው እንጅ፡፡ “ከሙታን አንዱ እንኳ ቢነሣ አያምኑም” ማለቱ ደግሞ
ለእምነታችን መሠረቱ መጽሐፍ እንጅ ተአምር እና ምልክት እንዳልሆነ ለማስተማር ነው፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ለእምነታችን መሠረት
ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የያዘውን ሁሉ እውነት እንደሆነ እንቀበለዋን እናምነዋለን፡፡
ሃይማኖት እንዴት መቼ ተጀመረ? ለማን ያስፈልጋል? የሚሉትን የሃይማኖትና
የፍጥረታትን ግንኙነት በቀጣይ ክፍል እንመለከታለን፡፡ ይቀጥላል…
ሃይማኖት እንዴት መቼ ተጀመረ? ለማን ያስፈልጋል? የሚሉትን የሃይማኖትና
የፍጥረታትን ግንኙነት በቀጣይ ክፍል እንመለከታለን፡፡ ይቀጥላል…
No comments:
Post a Comment