Wednesday, March 30, 2016

የተቀመጡት በቆሙት ላይ


© በመልካሙ በየነ
መጋቢት 19/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ተጓዥ ነኝ መንገደኛ፡፡ ስጓዝ ስጓዝ ስ…ጓዝ ውየ ከሆነ ቦታ ላይ ደረስኩ፡፡ ሰው ሁሉ ተቀምጦ ከፊት ለፊታቸው ላይ ካለው ትልቅ ስክሪን ላይ ዓይናቸውን አፍጥጠዋል፡፡ የሚመለከቱት ነገር የእኔንም ቀልብ ሳይስብ አልቀረም፡፡ ለዚያም ነው ከተመልካቾች ፊት ላይ ቆሜ ስክሪኑ ላይ ያፈጠጥሁት፡፡ የተቀመጡ ተመልካቾች ጮኹብኝ፡፡ በእውነት ያንን ጩኸት የሰማው ጆሮየ “ስቅሎ ስቅሎ” ያሉትን የአይሁዳውያንን ድምጽ የሰማ ነበር የመሰለው፡፡ በእርግጥ በምመለከተው ነገር ከመመሰጤ የተነሣ ጩኸታቸውን ከምንም አልጣፍሁትም ነበር፡፡ ምክንያቱም የምመለከተው ነገር የቤቴ ጉዳይ ነበራ!፡፡ ጩኸታቸው ግን እየበረከተ ድምጻቸውም እየጎላ መጣ፡፡ እኔም የግድ መዞር ነበረብኝና ዞር ብየ ምንድን ሆናችሁ? ዝም ብላችሁ መመልከት አትችሉም እንዴ? አልኳቸው፡፡ “እንዴ በየት በኩል እንመልከት ጋረድከን እኮ!” አሉኝ በአንድ ድምጽ፡፡ ለካ እነርሱ ስለተቀመጡ እኔ ደግሞ ስለቆምኩ እንቅፋት ሆኘባቸዋለሁ፡፡ ለካ እነርሱ ስለተቀመጡ የእኔ ነቅቶ መቆም መሰናክል ሆኖባቸዋል፡፡ ለካ የእኔ በእነርሱ ፊት መቆም የሚያዩትን ነገር እንዳያዩ የሚሠሩትን ነገር እንዳይሠሩ አድርጓቸዋል፡፡ ለካ የእኔ መቆም አሻግረው የሚመለከቱትን ነገር ከልሏቸዋል፡፡ ለካ የእኔ በፊታቸው መቆም ስክሪኑን ጋርዷቸዋል፡፡ ታዲያ እንደእኔ መቆም አትችሉም እንዴ አልኳቸው፡፡ እነርሱ ግን አሁንም አብዝተው ጮኹ “እንዴ ለምንድን ነው እንደአንተ የምንቆመው? ምን በወጣን ነው እግራችን እስኪዝል ድረስ የምንቸገረው? ይልቅስ ወይ ተቀመጥ ወይ ከእኛ ኋላ ቁም ይህ ካልተመቸህ ደግሞ ውጣልን እኛ በሰላም እንመልከትበት” አሉኝ፡፡ አይ አንች አገር! አይ አንች ቤተክርስቲያን! አይ አንች የእናት የአባቴ ቤት! አልኩ በልቤ፡፡ አገሪቱ ውስጥ ለሥራ የቆመውን ሰው በስንፍና የተቀመጠ ሰው ጋረድከኝ ተቀመጥ ይለዋል፡፡ አገሪቱ ውስጥ ለሥራ የቆመውን ሰው በስንፍና የተቀመጠ ሰው ስንፍናየን እንዳላጣጥም ሙስናየን እንዳልቀበል ጋረድከኝ ተቀመጥ ይለዋል፡፡ አገሪቱ ውስጥ ለሥራ የቆመውን ሰው በስንፍና የተቀመጠ ሰው ተቀምጨ እንዳልበላ ሰርቄ እንዳልተዳደር ጋረድከኝ ስለዚህ ከኋላየ ቁም አልያም ተቀመጥ  አስተዳደሬ ካልተመቸህ ደግሞ ውጣ ይለዋል፡፡ አገሪቱ ውስጥ ለሥራ ነቅቶ ከቆመ ሰው ይልቅ በስንፍና ለተጋደመ ትልቅ ቦታ ትልቅ ሹመት እየተሰጠው ነው፡፡ ስለዚህ ምርጫችን መቀመጥ ወይም ከኋላቸው መቆም ወይም አልተመቸኝም ብሎ አገር ለቅቆ ንብረት ጥሎ መውጣት ነው፡፡ ሌላ ምርጫ አይሰጡህም፡፡ ግን እኮ አገሬ ናት ለምን?
ቤተክርስቲያንስ ብትሆን በእንዲህ ዓይነቶች አይደለም እንዴ ዛሬ እየታመሰች ያለችው፡፡ እኛ ደብሩን አጥቢያውን እየመራነው ነው እናንተ አይመለከታችሁም አትጋርዱን፡፡ እኛ ስብከቱን እየሰበክነው ነው እናንተ አይመለከታችሁም ከፊታችን አትቁሙ፡፡ እኛ መዝሙሩን እየዘመርነው ነው እናንተ አይመለከታችሁም ከፊታችን ቆማችሁ አትጋርዱን፡፡ እኛ ሰዓታቱን እየቆምነው ነው እናንተ አይመለከታችሁም ከኋላችን ቁሙ፡፡ እኛ ኪዳኑን እያደረስነው ነው እናንተ አይመለከታችሁም ከፊታችን አትቁሙ አርፋችሁ ተቀመጡ፡፡ እኛ ቅዳሴውን ውዳሴውን እየፈጸምነው ነው እናንተ አይመለከታችሁም ከፊታችን አትቁሙ አርፋችሁ ተቀመጡ፡፡ እናንተ ቆማችሁ የምትሠሩት ሥራ  እኛ ተቀምጠን አሻግረን እንዳንመለከት እንቅፋት ሆኖብናል ስለዚህ አርፋችሁ ተቀመጡ አልያም ከእኛ ኋላ “አቡነ አቡነ”፣ “አባ አባ”፣ “መምህር መምህር” እያላችሁ  ተከተሉን ከኋላችን ቁሙልን ከኋላችን አጅቡን ይህም የማይመቻችሁ ከሆነ ከቤተክርስቲያናችን ውጡልን እኛ ተቀምጠን ማየት የምንፈልገው ነገር አለንና ይሉናል፡፡ በእውነት ቤተክርስቲያናችን ቤተክርስቲያናቸው ናትን? ብትሆንማ እንዲህ ባላሉን ነበር፡፡ ብትሆንማ አጥንቷ እስኪታይ ድረስ ባልደበደቧት ነበር፡፡ ብትሆንማ ገንዘቧን ለግላቸው ባላደረጉት ነበር፡፡ ብትሆንማ ስትጮኽ ጩኸቷን በሰሟት ነበር፡፡ ብትሆንማ ባልገፏት ነበር፡፡ ብትሆንማ እስከሞት ድረስ በታመኑላት ነበር፡፡ ብትሆንማ ትህትናን ባወቁባት ነበር፡፡ ብትሆንማ ወንጌልን በተማሩባት ባስተማሩባት ነበር፡፡ ብትሆንማ ቅዳሴውን ባስቀደሱባት በቀደሱባት ነበር፡፡ ግን ምናቸውም አይደለችም! ለዚያም ነው መድረኳን ለምንፍቅና የተጠቀሙባት፡፡ ለዚያም ነው ምሥጢረ ተዋሕዶ እንዳይነሣ በጠላትነት የቆሙባት፡፡ ለዚያም ነው ሀብት ንብረቷን ለራሳቸው የሚያግበሰብሱ ወሮበሎች የተሠማሩባት፡፡ ለዚያም ነው ለመናፍቃን አዳራሽ ብቁ የሆነ ሰውን የሚፈለፍሉባት፡፡ ይህን ግብራቸውን ስትቃወም ነው እንግዲህ ከፓትርያርኩ ጀምሮ  እስከ ታች አጥቢያ ድረስ ሰንሰለታቸውን ተጠቅመው ተቀመጥልን እረፍልን የሚሉህ፡፡ ጋረድከኝ ተቀመጥ ይልሃል፡፡ ለምንፍቅናው እንቅፋት ሆነኽበታልና፡፡ ታዲያ ዝም እንበል? አንልም!!! በፍጹም አንልም!!!!

እናቴ ቤተክርስቲያን ሆይ! ሌሊት ከቀን ሊጠብቁሽ ነቅተው የቆሙ  ከመንበራቸው እየተሰደዱ የሰበኩሽ ለዓለም ሁሉ ያሳወቁሽ ልጆችሽ እነ ዮሐንስ አፈወርቅ እነ አትናቴዎስ ልጅ አልወለዱምን? ዛሬ እኮ የጠፋው እምነቱን በአደባባይ ደፍሮ የሚመሰክር በዓለም ገብቶ የሚያስተምር ሳይሆን  በመድረክሸ ላይ ቆሞ እምነቱን የሚመሰክር ሰው ነው፡፡ በፍርሐት ተሸብቦ ምሥጢረ ተዋሕዶን ሳይገልጥ ሲያስጨበጭብ ብቻ ቆይቶ ከመድረክ የሚወርድ መምህር ነው ያፈራን፡፡ እናንተ ተቀምጣችሁ በቤተክርስቲያን ጥላ ስር አርፋችሁ ሙዳዬ ምጽዋእትን ትገለብጣላችሁን? እናንተ የእናታችንን ጡት እየጠባችሁ ስትጠግቡ ጡቶቿን ትነክሳላችሁን? በእርግጥ ጡቶቿን ጠብታችኋል ለማለት የሚያስችል ነገር የለንም፡፡ እናንተ ተቀመጡ ችግር የለውም፡፡ እናንተ ተኙ ችግር የለውም፡፡ እናንተ ስረቁ ችግር የለውም፡፡ እናንተ ሙስና ሥሩ ችግር የለውም፡፡ አሜን ብለን ተቀብለናችኋላ! ግን እኛ እንቁምበት ተውን፡፡ ግን እኛ እንሥራበት ተውን፡፡ ግን እኛ እንጸልይበት ተውን፡፡ ግን እኛ እንጹምበት ተውን፡፡ ግን እኛ እንስገድበት ተውን፡፡ ግን እኛ እንመጽውትበት ተውን፡፡ ግን እኛ እናጉርሳችሁ ተውን፡፡ እንዴ የእኛን ብር ነው እኮ ፎቅ የሠራችሁበት፣ የእኛን ንብረት እኮ ነው ቤት የገባችሁበት፣ የእኛን ገንዘብ እኮ ነው የደለባችሁበት፡፡ የእኛን ገንዘብ እኮ ነው የተቀራመታችሁት፡፡ የእኛን ገንዘብ እኮ ነው ገንዘባችሁ ያደረጋችሁት፡፡ ታዲያ እኛ ቆመን ካልመጸወትናችሁ ምኑን ተቀምጣችሁ ትዘርፉታላችሁ? ምኑንስ ትሰርቁታላችሁ? መቀመጥን ገንዘቡ ያደረገ ሰነፍ በቆሙት እንዴት ይበሳጫል፡፡ እኛም እኮ የማንቀመጠው አላስችል ብሎን ነው አትፍረዱብን እንጅ፡፡ እናታችን ናታ ጡቷ የተነከሰው፡፡ እናታችን ናታ የተሰደበችው፡፡ እናታችን ናታ የተገፋችው፡፡ እናታችን ናታ የተደፈረቸው፡፡ እናታችን ናታ የተወገረችው፡፡ እናታችን ናታ ልብሷን የተገፈፈችው፡፡ እናታችን ናታ የተሰረቀችው፡፡ እሽ ከእናታችን ቤት ወዴት እንሂድላችሁ? እሽ ከእናታችን ብብት ወዴት እንጠለልላችሁ? እሽ ከእናታችን ጉያ ወዴት እንሽሽላችሁ? እንዴ ተረዱን እንጅ እኛንም፡፡ ዓላማችሁ ዓላማችን አይደለም፡፡ ትምህርታችሁ ትምህርታችን አይደለም፡፡ ምስጋናችሁ ምስጋናችን አይደለም፡፡ ቅዳሴያችሁ ቅዳሴያችን አይደለም፡፡ ጸሎታችሁ ጸሎታችን አይደለም፡፡ ቃላችሁ ቃላችን አይደለም፡፡ ንግግራችሁ ንግግራችን አይደለም፡፡ ሥርዓታችሁ ሥርዓታችን አይደለም፡፡ ዶግማችሁ ዶግማችን አይደለም፡፡ ቀኖናችሁ ቀኖናችን አይደለም፡፡ ነገር ግን እናታችን መድረክ ላይ እናንተም ለራሳችሁ ዓላማ እኛም ለራሳችን ዓላማ ተገናኘን፡፡ ያን ጊዜ እኛ ቆምን እናንተም ተቀመጣችሁ፡፡ ከዚያም የእናንተን ዓላማ ከለልነው ለዚያም ነው እንደእናንተ እንድንቀመጥ ግርግር የምትፈጥሩት፡፡ ለዚያም ነው ከእናንተ ኋላ ቆመን ዓላማችሁን ስታስፈጽሙ ዝም ብለን እንድንመለከት ሽብር የምትፈጥሩት፡፡ ለዚያም ነው የእናታችንን መድረክ ለቅቀን እንድንወጣ የሌለንን ስም ሰጥታችሁ ስማችንን የምታብጠለጥሉት፡፡ የቆመው ተዋሕዶ የተቀመጠው ደግሞ ተሐድሶ መሆኑን ብታውቁ ግን ሳታውቁ የተቀመጣችሁ ሁሉ በተነሣችሁ እና አብራችሁን በቆማችሁ ነበር፡፡ ግን…

No comments:

Post a Comment