Friday, October 6, 2017

✍✝ “በጌታ ሞት የታረቁ ሔሮድስ እና ጲላጦስ” ✝✍



፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ላይክ ላይክ ላይክ
facebook.com/beyenemelkamuA
facebook.com/melkamubeyeneB
ላይክ ላይክ ላይክ
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ሔሮድስ ከጲላጦስ ጋር ጥል ነው ጲላጦስም ከሔሮድስ ጋር እንዲሁ፡፡ የፍቅር ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን በደሙ ፈሳሽነት ሊቀድሳት በሥጋ ማርያም ተገለጠ፡፡ ገና ከልደቱ አስቀድሞ በክፉ ምክር ጠላት ልባቸውን ያነሣሣቸው ሁሉ የጌታን መምጣት በክፉው ተቃወሙ፡፡ እንዲያውም ድንግል
ማርያም እንበለ ዘርእ መጽነሷን ሲሰሙ ቁጣቸው ገንፍሎ ለስደት ዳረጓት፡፡ እነሆ ዛሬ ጾመ ጽጌን ስንቀበል ይህንን አብዝተን እናስበዋለን፡፡ የሁሉ ገዥ የሁሉ ባለቤት ቤት አጥቶ በከብቶች በረት ተወለደ፡፡ በጌታ ላይ የተነሣሡት ጠላቶች በዚህ አላቆሙም ነበር፡፡ የሐሰት ክስ በመክሰስ እስከ መስቀል ሞት ድረስ ተቃወሙት እንጅ፡፡ ጌታማ የመጣውም በደሙ ፈሳሽነት ዓለምን ሊቀድስ ነውና ይሰቀል ዘንድ ፈቃዱ ነው፡፡ ጊዜው ሲደርስ የአዳም ተስፋ ተፈጸመ መድኃኒት መስቀልም የራስ ቅል በምትባለው ኮረብታ በቀራንዮ ላይ ተተከለ፡፡ ጌታም መስቀሉን ምቹ ዙፋን አድርጎ ነገሠበት፡፡ በዚህ ሂደት በጌታ ሞት በጣም ከፍተኛ ጥል ውስጥ የነበሩት ሔሮድስ እና ጲላጦስ እርቅ መሰረቱ፡፡ ጌታ የሁለቱም የጋራ ጠላታቸው ሆኖ ስለተገኘ ጌታን ገድለው ለመገላገል ሁለቱም ተስማሙ፡፡
ይህ ታሪክ ዛሬም በዘመናችን ተደግሟል፡፡ ቤተክርስቲያናችንን ለመጠበቅ ያልተስማሙ ሔሮድስ እና ጲላጦስ ለማፍረስ ግን ተስማምተዋል፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቶችን ለማጠናከር ያልተስማሙ ሔሮድስና ጲላጦስ ለማዳከም ግን ተስማምተዋል፡፡ ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን ለማስተማር ምእመናንንም በዚች እምነት እንዲጸኑ ለማስተማር ያልተስማሙት ሔሮድስና ጲላጦስ ዛሬ ከመሠረቷ ለማናጋት ግን ተስማምተዋል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንን በጸሎት ለማገዝ ያልተስማሙት ሔሮድስና ጲላጦስ ዛሬ ለውድቀቱ ተስማምተዋል፡፡ ምእመናንን በቃለ ወንጌል ለማነጽ ያልተስማሙት ሔሮድስና ጲላጦስ ዛሬ በብሎኬት ደርድረው በሠሩት ህንጻ ተስማምተዋል፡፡ አዎ ሔሮድስ እና ጲላጦስ ተስማምተዋል፡፡
ምእመናን በመቀነታቸው ያለውን ሽርፍራፊ ሳንቲም ገብረውበታል፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ለግንባታ የተዘጋጀውን ስእል እየዞሩ ሸጠው ገንዘቡን ገቢ አድርገዋል፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት በነፍስ ወከፍ ተቆጥሮ የተሰጣቸውን የህንጻ ማሠሪያ ስእል ገንዘቡን ከፍለው ወስደዋል፡፡ እንዲያውም ህንጻው ይሰራ ዘንድ ከፍተኛ ምኖት የነበራቸው የማኅበሩ አባላት አምስት አምስት ስእላትን እንደ ግዴታ አድርገው ማከፋፈላቸውን አስታውሳለሁ፡፡ ለዚሁ ህንጻ ማስገንቢያ ተብሎ ወረዳ ቤተክህነቶች በስራቸው ያሉ አጥቢያዎችን እንደ ግዴታ ገንዘብ በመጣል ገንዘብ ተሰብስቧል፡፡ በዚህ ሁሉ ህዝብ ትብብር ነው እንግዲህ ነገ መስከረም ፳፯/፳፻፲ ዓ.ም ለምረቃ የደረሰውን ህንጻ በደብረ ማርቆስ ከተማ በደብረ ፀሐይ መልእልተ አድባር ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ የገነባው፡፡ ይህ ህንጻ የካህናት ማሰልጠኛ ተብሎ የተገነባ ሲሆን ከምረቃ በፊት የግል ኮሌጆች ተከራይተው እየሠሩበት ያለ ህንጻ ነው፡፡
ይህን ህንጻ ለመመረቅ ቅዱስ ፓትርያርኩ እና ሌሎችም በርካታ ጳጳሳት በቦታው ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በቦታው ስላለው እንቅስቃሴ ለመቃኘት የሞከርሁ ሲሆን አካባቢውን በማስዋብ በኩል ብዙ ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙ ተመልክቻለሁ፡፡ የእንግዶች መቀመጫ ወንበሮችም ወደ ቦታው ሲጓጓዙ ለመመልከት ችያለሁ፡፡ ይህን ህንጻ ለመመረቅ በእውነት የቅዱስ ፓትርያርኩ መገኘት ተገቢነቱ ምኑ ላይ ነው? እኛ በእምነታችን ላይ እየተሠራብን ስላለ ደባ በግልጽ ቅዱስ ፓትርያርኩ ድረስ ፊርማ አሰባስበን በህጋዊ መንገድ ጠይቀናል፡፡ የሚያሳዝነው ነገር ይኸው ነው፡፡ እነ ቅዱስ አትናቴዎስ መንበራቸውን እየተው እየተሰደዱ እየታሠሩ እነ ቅዱስ ዲዎስቆሮስ ጽህማቸውን እየተነጩ ጥርሳቸውን እያወለቁ በብዙ ተጋድሎ ለእኛ ያደረሷትን ንጽሕት ርትዕት ሃይማኖታችንን አጠንክረን እንድንይዝ አንድ ቀን በቅዱስ ፓትርያርኩ ትምህርት አልተሰጠንም ቃለ ምእዳን አላገኘንም፡፡ በብዙ ድካም እና ተጋድሎ የገነቡንን መእመናንን ያልመረቁ ቅዱስ አባታችን ይህን ብሎኬት ተደርድሮ የተሰራ ግንብን ለመመረቅ እንዴት ሊመጡ ቻሉ የሚለው ጥያቄየ መልስ አልባ ነው፡፡ መጀመሪያ ምእመናን በአግባቡ በእምነት በምግባር እንታነጽ እኛ ከታነጽን ብሎኬት ደርድረን ለማነጽ ጊዜ አይወስድብንም የሚቀድመውን እናስቀድም፡፡ ይህ ህንጻ በመሠራቱ ምንም ተቃውሞ የለብኝም ግን እኛ የእግዚአብሔር ህንጻዎች በክህደት ትምህርቶች ፈራርሰን አልቀናል፡፡
ብጹእ አባታችን አቡነ ማርቆስ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ያቀረብን እኛው ነን፡፡ ይህንን ህንጻም ለዚህ ደረጃ ያደረስነው እኛው ነን፡፡ ብጹእ አባታችን በተለይ በሀገረ ስብከቱ ላይ እንዲያንሠራራ የፈቀዱለት የቅባት እምነት ድሮ በአባቶቻችን የተወገዘ አስተምህሮ የያዘ ነው፡፡ እርስዎን ግን ፊርማ አሰባስበን ሁሉ ብንጠይቅዎ ምንም መልስ አልሰጡንም እንዲያውም እነዚህን መጻሕፍትን ያሳተሟቸውን ሰዎች “ቅዱሳን” አሳታሚዋን ገዳምም “በየትም የማይገኝ መጽሐፍ የሚገኝባት” እያሉ ሲያሞካሹ ነበር፡፡ ይህንንም በመረጃ ይዘነዋል ለሚመለከተው አካልም አድርሰናል፡፡ በገና በዓል አከባበር ላይ በ ፳፱ በ ፳፰ አትበሉ እርሱ “ካሌንደር ነው” ሲሉን “ተዋሕዶ ካራ ጸጋ ቅባት የሚባል መርዝ ረጭተው ሄዱ፡፡ ይህ እኮ ቃል ነው ቃል ደግሞ ሃይማኖት አይሆንም” ሲሉን ይህም አልበቃ ብሎዎት “ሰኔ ጎልጎታ ልብ ወለድ ነው ከእግዚአብሔር ጋር አያገናኝም” ሲሉን ታግሰን መረጃውን ከመያዝ ያለፈ ሌላ አምባጓሮ አልፈጠርንም አንፈጥርምም፡፡ ይህ ሁሉ ወደፊት በቪዲዮ መረጃው ይሰራጫል፡፡ “የልማት አባት” እያሉ እንዲያወድሱዎ በየቦታው ያስቀመጧቸው እና በዝምድና የሾሟቸው ሰዎች እስከ ቀራንዮ ድረስ እንደ ፍቁረ እግዚእ ቅዱስ ዮሐንስ ጸንተው አይዘልቁልዎም፡፡ አሁን እንደምንሰማው ከሆነ ደግሞ የቅባት እምነት አራማጆች በተለይም ግቢ ጉባዔያት ላይ እንዲንቀሳቀሱ እውቅና ሰጥተው እና አሰልጥነው ከደብረ ወርቅ ከጉንደ ወይን እና ከሞጣ የላኳቸው “ማኅበረ ሐዋርያት” በሚል የሚንቀሳቀሱ ወጣቶች እርስዎን ከተዋሕዶ ጳጳስነት ገንጥለው በቅባት የመጀመሪያው ጳጳስ አድርገው በደብረ ወርቅ መንበረ ጵጵስና አዘጋጅተው ሊያስቀምጡዎ እንደሆነ ነው፡፡
እንደምንሰማው ከሆነ ቅዱስ ፓትርያርኩ እና ብጹእ አባታችን በተለያዩ ነገሮች አይግባቡም ነበር፡፡ ዛሬ ግን አንድ ጉዳይ እርሱም ማኅበረ ቅዱሳንን የማፍረስ ጉዳይ ላይ አንድ አቋም ኖሯቸው ተግባብተዋል ተስማምተዋል፡፡ በዚሁ ከተማ ገዳመ አስቄጥስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን ሲመረቅ ቅዱስ አባታችን አልመጡም ነበር ዛሬ ግን ይመጣሉ፡፡ አመጣጣቸው ብጹእ አባታችሁን አትቃወሟቸው የልማት አባት ናቸው እንዲህ ያለ ህንጸ እያስገነቡላችሁ ነው ወዘተረፈ ብለው አባታችንን በግድ እንድንቀበላቸው ሊደርጉን ነው፡፡ ጥቅምት ሲኖዶስን በጉጉት የምንጠብቀው አቡነ ማርቆስ ከዚህ ሀገረ ስብከት እንዲነሡ ብቻ ሳይሆን እስካሁን ባስተማሯቸው የክህደት ትምህርቶች መልስ እንዲሰጡ ጭምር ነው፡፡ መልሳቸውንም ቅዱስ ሲኖዶስ በሚገባ አድምጦ ተገቢውን ውሳኔ እንዲሰጥ እንማጸናለን፡፡ ሔሮድስ እና ጲላጦስ በጌታ ሞት ቢስማሙም ጌታ ግን ከሞት በኋላ በሦስተኛው ቀን ይነሣል በዐርባኛውም ቀን ያርጋል፡፡ በመቃብር በስብሶ አይቀርም እውነት ምንጊዜም እውነት ናት፡፡ቅዱስ አባታችን እንደመጡ ሊመልሱልን የሚገባ ጥያቄ ይኖረናል እርሱንም እርስዎ በሚገኙበት እንጠይቃለን፡፡
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠

© መልካሙ በየነ
መስከረም ፳፮/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✝✝✝✝✝
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት #comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡
✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝
— with Tesfaye Tadese, Alem Gebray, Mekdes Shuemet and 12 others.

No comments:

Post a Comment