፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍ላይክ ✍ላይክ ✍ላይክ
facebook.com/beyenemelkamuA
facebook.com/melkamubeyeneB
✍ላይክ ✍ላይክ ✍ላይክ
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
===================================================
·
ሕንጻው ራዕየ ቅዱስ ወሰማዕት አቡነ ቴዎፍሎስ ሕንጻ ተብሎ ተሰይሟል፡፡
·
አሁን በመሠራት ላይ ያለው የመርጡለ ማርያም ህንጻ ቤተክርስቲያን ሲጠናቀቅ ራዕየ ማትያስ ተብሎ ይሰየማል
ተብሏል፡፡
·
በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ ብጹእ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሥራ አስኪያጆች ወዘተ ተገኝተዋል፡፡
የምሥራቅ ጎጃም ህዝበ ክርስቲያን ይህንን ህንጻ ለዚህ ደረጃ ለማድረስ ብዙ መስዋእትነትን ከፍለዋል፡፡ የሕንጻው
ግንባታ በ፳፻፯ ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በዚህ ዓመት ሕንጻው ሙሉ በሙሉ ሊጠናቀቅ ይችላል፡፡ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ እንዳቀረቡት
ሪፖርት ከሆነ ይህን ሕንጻ ለመገንባት በጠቅላላው ዐሥራ ዘጠኝ ሚሊዮን ዐርባ ዘጠኝ ሽህ አምስት መቶ ሃምሳ ስድስት ብር ከ ስምንት
ሳንቲም መሆኑ ታውቋል፡፡ በዚሁ ሪፖርት አብሮ እንደተያያዘው አቡነ ማርቆስ ሐገረ ስብከቱን ከመረከባቸው በፊት የነበረው የካህናት
እና የመምህራን የደመወዝ መጠን በእጅጉ ይለያያል ተብሏል፡፡ በዚህም መሠረት ቅድመ አቡነ ማርቆስ ዲያቆን ሰባ ብር ካህን መቶ ሃምሳ
ብር መምህራን ሁለት መቶ ብር አስተዳዳሪዎች ሦስት መቶ ብር የነበረ ሲሆን ዛሬ አቡነ ማርቆስ ከመጡ በኋላ ግን ዲያቆን ሁለት ሲህ
ሰባት መቶ ብር ካህን ሦስት ሺህ ብር መምህራን ከሦስት ሺህ አምስት መቶ ብር በላይ አስተዳዳሪዎች ደግሞ ከዐራት ሽህ ብር በላይ
እየተከፈላቸው ነው ብለዋል፡፡ ከተነገረው ሪፖርት ሁሉ ይኸኛው ሪፖርት ግን አንድኛውን ዐይን ያወጣ ቅጥፈት ነው፡፡ ይህንን የምታነብቡ
የምሥራቅ ጎጃም አካባቢ ነዋሪዎች ይህንን የደመወዝ መጠን እውነት መሆነም አለመሆኑን ጠይቃችሁ አስተያየት ላይ እባካችሁ አስፍሩልን፡፡
ይህ ሪፖርት ምናልባት በዝምድና የቀጠሯቸው ሰዎችን ክፍያ ብቻ የተመለከተ ከሆነ መቶ በመቶ እስማማለሁ፡፡ ለሁሉም ሀገረ ስብከቱ
አገልጋዮች ከሆነ ግን ፍርዱን ለእናንተ እተወዋለሁ፡፡
ለዚህ ሕንጻ ግንባታ ምእመናን በጉልበት ብቻ ያደረጉት እገዛ ወደ ገንዘብ ሲተመን ወደ አምስት ሚሊዮን ሦስት
መቶ ስድሳ ዘጠኝ ሺህ ብር እንደሆነ በሪፖርቱ አድምጠናል፡፡ ከዚህ ከልዩ ልዩ አካላት ደግሞ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ
በድጋፍ ተገኝቷል ተብሏል፡፡ ይህ ሪፖርት እውነት ስለመሆን አለመሆኑ በሕንጻው ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የነበራችሁ አካላት ምስክሮች
ናችሁ፡፡
ህንጻው ገና ሳይጠናቀቅ የዚህ ሕንጻ ምረቃ መቅደሙ ዋና ዓላማው ምንድን ነው?
፩ኛ. የምሥራቅ ጎጃም ምእመናን አቡነ ማርቆስን እንዲነሡላቸው እየጠየቀ ስለነበረ እና በጥቅምቱ ሲኖዶስም
ይህ ምላሽ ያገኛል እየተባለ ይጠበቅ በነበረበት ወቅት ከሲኖዶሱ ስብሰባ ቀድመው ቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምረው በቦታው ማምጣታቸው በህዝቡ
ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት የተደረገ ሙከራ ነው፡፡
፪ኛ. አቡነ ማርቆስን የልማት አባት ናቸው ብሎ በምእመናን ዘንድ ለማሞካሸት ነው፡፡ ይህም በህዝቡ ዘንድ
የተፈጠረባቸውን አለመግባባት በግድ ለመፍታት ይችላል ተብሎ ታስቦ ነው፡፡
፫ኛ. ደጋፊዎቻቸውን በማምጣት ጳጳሳት እና ቅዱስ ፓትርያርኩ አቡነ ማርቆስን በምእመናን ዘንድ በማወደስ
ጥቅምት ሲኖዶስ ላይ ምንም ለውጥ አናሳይም እንዲያውም ትምህርታቸውን ተቀበሉ ብለው መልእክታቸውን በግልጽ ላማስተላለፍ፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩ አቡነ ማርቆስን ባመሰገኑበት ንግግራቸው “ይህ ሁሉ ሥራ የተሠራው በዋናው አስተባባሪ በብጹእ
አቡነ ማርቆስ ነው፡፡ የብጹእ አባታችሁን ትምህርት አዳምጡ ሃይማኖታችሁን ጠብቁ ወዘተ” ብለዋል፡፡ ለማጨብጨብ ተመርጠው በጉባዔው
የተሳተፉ አካላትም ዐሥር ጊዜ ሲያጨበጭቡ ተደምጧል፡፡ ከዚህ የተረዳነው የምእመናን አቤቱታ የዞኑ ጸጥታ ዘርፍም የጻፈው ደብዳቤ
አቡነ ዘካርያስም የጻፉት ደብዳቤ ሁሉም ነገር ተቀባይነት የለውም ወደዳችሁም ጠላችሁም ከአቡነ ማርቆስ ጋር ትቀጥላላችሁ ማለታቸው
ነው፡፡
የአዊው ሊቀ ጳጳስ (ትንሹ አቡነ ማርቆስ) አቡነ ቶማስም አቡነ ማርቆስን ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር
በማነጻጸር አሞጋግሰዋቸዋል፡፡ ቅዱስ አባታችን ተመልከቱት እንዲህ ያለ ትልቅ ሥራ ሠርተዋል በማለት ለአቡነ ማርቆስ ያላቸውን ጥብቅና
ጠቁመዋል፡፡ በጣም የማዝነው የሃይማኖት ጉዳይ ሁሉም አለማንሣታቸው ነው፡፡ ሁሉም ተነሣ ህንጻ ሁሉም ተነሳ ግንብ ሁሉም ተነሣ ብሎኬት
ድርደራ ነው የሚናገረው፡፡ በእውነቱ የአንድ ጳጳስ ዋና ተግባሩ ብሎኬት ማስደርደር ነው እንዴ አረ ምን ነካችሁ ይህማ የግንበኛ
ሥራ ነው፡፡
በዚህ ስብሰባ የተገኙት ደግሞ በጣም የሚገራርሙ ሰዎች ናቸው፡፡
፩ኛ. ቅዱስ ፓትርያርኩ
፪ኛ. አቡነ ማርቆስ
፫ኛ. አቡነ ሩፋኤል የጋንቤላው
፬ኛ. አቡነ አረጋዊ የደቡብ ጎንደሩ
፭ኛ. አቡነ ጴጥሮስ የሽረ እንዳ ሥላሴው
፮ኛ. አቡነ ቶማስ የአዊው
፯ኛ. አቡነ ዲዎናስዮስ የአሶሳና መተከሉ (የመርጡለ ማርያም ተወላጅ ናቸው፡፡ እርሳቸው ዘንድ እውነት እውነት
ናት፡፡ ያመጧቸውም ደጋፊዎቻቸውን ብቻ ነው የሰበሰቡ እንዳይባሉ ነው እንጅ አያስከትሏቸውም ነበር)
፰ኛ. አቡነ መልከጼዴቅ የጉራጌው (ለተሐድሶ መናፍቃን እሳት የሆኑ የማይቀመሱ እውነተኛ አባት ናቸው፡፡
ያመጧቸውም ደጋፊዎቻቸውን ብቻ ነው የሰበሰቡ እንዳይባሉ ነው እንጅ አያስከትሏቸውም ነበር)
፱ኛ. አቡነ ፊልጶስ ደቡብ ኦሞ ጅንካ (ያመጧቸው ደጋፊዎቻቸውን ብቻ ነው የሰበሰቡ እንዳይባሉ ነው እንጅ
አያስከትሏቸውም ነበር)
፲ኛ. ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ
፲፩ኛ. መጋቢ ካህን ኃይለ ሥላሴ ዘማርያም
፲፪ኛ. ጎይቶም ያይኑ የአዲስ አበባው ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪጅ
፲፫ኛ. ሊቀ ማእምራን ቆሞስ አባ እንባቆም ጫኔ
፲፬ኛ. የዐሥራ ሰባቱ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪጆች
፲፭ኛ. የምእመናን ተወካይ የሀገር ሽማግሌዎች
፲፮ኛ. የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች ነበሩ፡፡
የምእመናን ተወካዮች እና የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች ያላቸውን አቤቱታ ለማቅረብ በቦታው የተገኙ ሲሆን
በምርኃ ግብሩ ግን ድምጻቸውን ሊሰማ የሚችል ሰው አልነበረም፡፡ በአቡነ ሩፋኤል ዘጋንቤላ የተመራው የአጨብጫቢው ቡድን በጭብጨባ
ሲደግፍ ውሏል፡፡ ይህ የከንቱ ውዳሴ ጉባዔ ምእመናንን ልባቸውን ያከሰለ ሰንበት ትምህርት ቤቶችንም ያበሳጨ እንደነበር ተገንዝበናል፡፡
ሙስናን እንዋጋለን ያሉት ፓትርያርኩ አስከትለውት የመጡ ማንን ነው ጎይቶምን እኮ ነው፡፡ ለማንኛውም እኔ በግሌ የምፈልገው ብሎኬት
የሚደረድር አባት ሳይሆን ምእመናንን በእምነት የሚያንጽ እውነተኛ እረኛ ነው፡፡ የወደፊት እቅዳቸውን በገለጹበት የአቡነ ማርቆስ
ንግግር የህዝቡን ተቀባይነት ለማግኘት የመልአከ ብርሃን እና የአለቃ አያሌው ታምሩ መታሰቢያ በብቸና ከተማ እንገነባለን ብለዋል፡፡
እርሳቸው ሲጀመር መልአከ ብርሃንን መቸ ተቀብለዋቸው ያውቃሉ በግል ቀርባችሁ እስኪ ጠይቋቸውማ፡፡ ቅባት ጸጋ ተዋሕዶ ካራ ብሎ መርዝ
ረጭቶ የሄደ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ነው፡፡ የእርሱን አተላ እየተጋታችሁ አትረብሹን ነው የሚሉ፡፡ ታዲያ መታሰቢያው እንዴት
ነው የሚሠራላቸው፡፡
ሕንጻ ለማቆም የምሥራቅ ጎጃም ሕዝብ ጥበብ አላነሰውም፡፡ ገና ብዙ የሚሠራ ህዝብ ነው፡፡ በሃይማኖቱ ለሚመጣበት
ግን ማንንም ቢሆን ይገስጻል ለዚህም ምስክራችን ቅዱስ ወሰማእት አቡነ ቴዎፍሎስ ናቸው፡፡ እርሳቸው በደርግ አገዛዝ በእስር የተንገላቱ
በመጨረሻም የተገደሉ ቆራጥ የእምነት አባት ናቸው፡፡ ይህ ሕንጻም በስማቸው መሰየሙ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ስለዚህ ስለእምነታችን
እስኪ እናውራ፡፡ በእኔ በኩል ነገሩ ሁሉ ምንም አላማረኝም፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ መካከልም መከፋፈል እንዳይፈጠር እሰጋለሁ፡፡ ግድ
ደግፉ ድግ ተቀበሉ ሲባል ዛሬ ተመለከትሁ፡፡ ነገር ሁሉ ለበጎ ነው አምላክ ሥራውን ይሠራል ጅራፉን መዝዞ ቤቱን ያጸዳል ግድ ነው፡፡
ይህ የተያያዘውን ቪዲዮ አዳምጡት፡፡ በቅደም ተከተል ዋና ዋና ሃሳብ የተባለው የተካተተበት ነው፡፡
የመጀመሪያው የዞኑ መልእክት ቀጥሎም አቡነ ቶማስ ዘአዊ ቀጥሎም አቡነ ማትያስ ቀጥሎም ሥራ አስኪጁ አባ
እንባቆም በመጨረሻም አቡነ ማርቆስ ናቸው በዚህ ቪዲዮ ድምጻቸው የተካተተው፡፡
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝
© መልካሙ በየነ
መስከረም ፳፱
/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝
No comments:
Post a Comment